ለሐውልቱ የሚገባውን ክብር እንስጥ
በማኅደር ገብረ መድኅን
በአንድ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ወሳኝ አቅጣጫ ጠቋሚ፣ አመልካችና የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች መካከል ሐውልቶች ከዋነኞቹ ተርታ ይመደባሉ፡፡
ሐውልቶች የአንድን አገር፣ ከተማና ሕዝብን አስተሳሰብና ፍልስፍናዎች የሚገለጽባቸው የጥበብ ሥራዎችም ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙት ሐውልቶች መካከል አራት ኪሎ የሚገኘው “የድል ሐውልት” ለነፃነት የተከፈለን ዋጋ የሚያስረዳ አንድ የከተማዋ ምልክት ነው፡፡
ይህ ሐውልት የቀደሙ እናቶችና አባቶች የነፃነትን ዋጋ መጪው ትውልድ እንዲረዳው፣ ነፃነቱን አሳልፎ እንዳይሰጥና እንዲያከብር ለማስታወስና ለማስተማሪያ ተብሎ የታነፀ ነው፡፡
ልቅም ተደርጐ የተሠራው ይህ ሐውልት የነፃነት ዓርማ ከመሆኑ በተጨማሪ በጥበብ ዓይን የማያከራክር የከተማ ፈርጥ ነው፡፡
ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ በሐውልቱ የምሥራቅ ወገን ‹‹ለጥበቃ›› ተብሎ የተቀመጠ በፕላስቲክ የተሠራ ባዕድ ነገር ይታያል፡፡ ለምን ‹‹የጥበቃው›› መቆያ ሐውልቱ ሥር እንደተወሰነ ባይገባኝም የራሱን መልዕክት የሚያስተላልፍ ይመስላል፡፡ ‹‹ምልክትነት›› በብዙ ቢገለጽም አንድ ባልተገባው ቦታ የሚቀመጥ ባዕድ ነገር የሚያስተላልፈው መልዕክት ሆን ተብሎ ከተደረገ ነገር ሊጐላ ይችላል፡፡ የአንድ ትውልድ ዘመናዊነትና አርቆ አሳቢነት ከሚለካባቸው ነጥቦች መካከል የራሱን ታሪክ መሥራትና ለቀደሙ የጋራ ታሪኮችና ቅርሶች የሚሰጠው ክብር ሁለቱ ናቸው፡፡ ለአዲስ አበባም ሆነ ለየትኛውም ከተማ የቱሪስት መስህቦች የሆኑት ሐውልቶች ተገቢው ጥንቃቄና ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
ላለፉት ሦስት ወራት ከሐውልቱ ግርጌ ውስጥ የተቀመጠው ይህ ‹‹የፕላስቲክ የጥበቃ ገሳ›› የምንኮራበትን ነፃነት ላጐናፀፉን ጀግኖች እናቶቻችንና አባቶቻችን ተገቢውን ክብር ካለመስጠት አልፎ ንቀት ሊመስልብን ስለሚችል ጊዜ ሳይሰጥ ሊነሳ ይገባዋል፡፡
ጥበቃም ካስፈለገ በአራት አቅጣጫ ከመንገዱ ማዶ በቂ ቦታዎችና ሌሎች አማራጮች ስላሉ እነሱን ማፈላለግ ይቻላል፡፡ የሐውልቶች ፋይዳ ከቱሪስት መስህብነትና አቅጣጫ ከመጠቆም ያለፈ መሆኑን ልንረዳው ይገባል፡፡
እኛ የእመውና የአበውን ታሪክ ካላከበርንና ካልተንከባከብን ልጆቻችንና የልጅ ልጆችን የኛን ሥራና ሐውልቶች በምን መልኩ ይሆን እንዲረዱና እንዲንከባከቧቸው የምንጠብቀው? እኛ ያላደረግነውን እንዴት መጠየቅ እንችላለን?
ይህ ሐውልት የወል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እንደ አንዳንድ ሐውልቶች የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም፣ የሃይማኖት ወይም የሌላ አቋም መግለጫ አይደለም፡፡ የአገሪቱን ሉዓላዊነት ያረጋገጠ የኢትዮጵያውያንን ትግል የሚገልጽ የጋራ ሐውልታችን ነው፡፡
ይህ የነፃነት ምልክት የሆነ “የድል ሐውልት” ነው የሚገባውን ነፃነትና ክብር ልንሰጠው ይገባል፡፡
No comments:
Post a Comment