Wednesday, December 18, 2013

ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን ለሚመሠርቱት ኮሚቴ የአባላት ዝርዝር ሊለዋወጡ ነው

18 DECEMBER 2013 ተጻፈ በ  

ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን ለሚመሠርቱት ኮሚቴ የአባላት ዝርዝር ሊለዋወጡ ነው

የኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን የውኃ ሚኒስትሮች ከሳምንት በፊት በሱዳን ተገናኝተው እንዲቋቋም በወሰኑት ኮሚቴ ውስጥ እያንዳንዳቸው የሚወክሏቸውን አባላት ዝርዝርና ማንነት የተመለከተ ሰነድ ሊለዋወጡ ነው፡፡
ሚኒስትሮቹ በሱዳን ተገናኝተው ባደረጉት ድርድር እንዲቋቋም የተስማሙበት ኮሚቴ፣ ከዚህ ቀደም ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የተካተቱበት ቡድን የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ጥናት በማካሄድ ያቀረባቸውን ሐሳቦች ተግባራዊነት የሚከታተል ነው፡፡  እንዲቋቋም በተወሰነው ኮሚቴ ውስጥ ሊካተቱየሚገባቸውን አባላት
በተመለከተ ከዚህ ቀደም ተወዛግበው የነበረ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ግን በኢትዮጵያ የቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት ማግኘቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 
የኮሚቴው አባል መሆን የሚገባቸው የሦስቱ አገሮች ዜጐች የሆኑ ባለሙያዎች ብቻ ናቸው በሚለው የኢትዮጵያ ሐሳብ ላይ ሚኒስትሮቹ እንደተስማሙ ለሪፖርተር የገለጹት የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ምንጮች በዚህ መሠረት በአገሮቹ የሚወከሉ አባላት ማንነትን የሚዘረዝር ሰነድ በቀጣዩ ሳምንት እንደሚለዋወጡ ገልጸዋል፡፡ ይህ የሚደረገው በውሳኔ መሠረት የተባሉት አባላት ብቻ መካተታቸውን ለማረጋገጥ እንደሆነና በአባላቱ ዝርዝር ላይ ተቃውሞ ካልተነሳ የኮሚቴው መመሥረት ይፋ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
የግብፅ የውኃ ሐብትና የመስኖ ሚኒስትር ሞሐመድ አብዱል ሙታሊብ ሰሞኑን ለግብፅ ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ፣ በህዳሴው ግድብ ላይ በሱዳን የተካሄደው የሚኒስትሮቹ ድርድር ቀና መንፈስ ነበረው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ በወሳኝ ነጥቦች ላይ መግባባት እንደሚቀር፣ ይህንንም ለመጨረስ ከ15 ቀናት በኋላ ሱዳን ለመገናኘት መስማማታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ወሳኝ ናቸው ያሏቸውን ነጥቦች ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ 
የሚቋቋመው ኮሚቴ ከዚህ ቀደም በቀረበው የባለሙያዎች የመፍትሔ ሐሳብ ተግባራዊ መሆን የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር የአንድ ዓመት ጊዜ እንደሚሰጠው የተናገሩት የግብፅ ሚኒስትር፣ ሦስትም አገሮች በግድቡ ላይ ጠቃሚ የሆኑ ተጨማሪ መረጃዎቻቸውን እንደሚለዋወጡ አስታውቀዋል፡፡ የኮሚቴውን ወጪ በተመለከተም ሦስቱ አገሮች የየድርሻቸውን ለመሸፈን እንደተስማሙ አክለው ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment