ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ከካርቱም ከተቀዳጀች እ.ኤ.አ. ከ2011 ወዲህ የውስጥ ፖለቲካዋ መረጋጋት አልቻለም፡፡
ከነዳጅ ጋር በተያያዘ ከካርቱም ስትጋጭ፣ በፖለቲካ አመራር ልዩነት ደግሞ በውስጧ ስትታመስ የቆየችው ደቡብ ሱዳን በያዝነው ሳምንት መጀመርያ ነው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተደረገባት፡፡ ለመፈንቅለ መንግሥቱ መነሻው ደግሞ ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ለመቀዳጀት ከዋናዋ ሱዳን ጋር ከተፋለመችበት ካለፉት ሦስት አሥር ዓመታት ወዲህ ጀምሮ ሲብላላ የቆየ፣ ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላም በአመራሮቹ መካከል በተፈጠረውና መፍትሔ ባላገኘው የሥልጣን ሽኩቻ፣ የዘርና የፖለቲካ ልዩነት ነው፡፡
ትናንት ዘግይተው የወጡ መረጃዎች እንደሚሉት በመፈንቅለ መንግሥቱ 66 ወታደሮች ተገድለዋል፡፡ የተገደሉት ወታደሮች መፈንቅለ መንግሥቱን ያከሸፉ ወይም ያካሄዱ ለመሆናቸው ማረጋገጫ አልተገኘም፡፡ እስካሁን ድረስ አራት የቀድሞ ሚኒስትሮች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፣ የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሪክ ማቻር የገቡበት አልታወቀም፡፡
በተለይ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ምክትል ፕሬዚዳንታቸውን ዶ/ር ሪክ ማቻር እ.ኤ.አ. ሐምሌ 2013 ከሥልጣን ማውረዳቸው አገሪቷ ላስተናገደችውና ለከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ቁልፍ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡ ዶ/ር ማቻርን ጨምሮ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ፕሬዚዳንት ኪር ምክትላቸውን ከሥራ ማሰናበታቸውን አስመልክተው፣ ‹‹ፕሬዚዳንት ኪር ትዕግሥት የለሽ አምባገነን እየሆኑ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡
በደቡብ ሱዳን በብዛት ትልቁን ብሔር ከሚወክለው ዲንካ ብሔር የተወለዱት ፕሬዚዳንት ኪርና በአገሪቱ በብዛት ሁለተኛውን ብሔር ከሚወክለው ኑዌር የተወለዱት ዶ/ር ማቻር ደቡብ ሱዳንን ነፃ ለማውጣት አብረው ታግለዋል፡፡ ሆኖም በመካከላቸው ያለው የብሔር ልዩነት እስከ ሠራዊቱ ድረስ ዘልቆ የወታደሮቹ ታዛዥነትና ታማኝነት ከብሔራቸው ለተወለደው ባለሥልጣን እስከመሆን ደርሷል፡፡
አገሪቷ ያስተናገደችውና የከሸፈው መፈንቀለ መንግሥትም ለዶ/ር ማቻር ታማኝ በሆኑ ወታደሮች የተጀመረ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከ12 ሰዓታት ላላነሰ ጊዜ ከዘለቀው የተኩስ ልውውጥ በኋላ በደቡብ ሱዳን መረጋጋት ይታያል ቢባልም፣ በሕዝቡና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን ሰላም አስከባሪ ኃይል በኩል ያለው ሥጋት አልረገበም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ አገሪቱ ለረዥም ዓመታት ከካርቱም ጋር ስትዋጋ በመኖሯና ሕገወጥ መሣርያ የታጠቁ በመኖራቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል በፕሬዚዳንት ኪርና በዶ/ር ማቻር መካከል ያለው ውስብስብ የፖለቲካና የብሔር ልዩነት ከራሳቸው አልፎ የአገሪቱን ዜጐች ከፋፍሏል፡፡ የአሁኑ አለመረጋጋት ለጊዜው ረገብ ብሏል ቢባልም፣ በቅርቡ ለተመሠረተችውና እ.ኤ.አ. በ2015 ምርጫ ለምታካሂደው ደቡብ ሱዳን መጪው ጊዜ ፈታኝ ይሆናል ተብሏል፡፡
በጁባ ባለፈው እሑድ ሌሊቱን የተቀሰቀሰው ግጭት እስከ ማክሰኞ ማለዳ ድረስ ዘልቆ የከባድ ጦር መሣርያ የፍንዳታ ድምፅ ይሰማ እንደነበር የዓይን እማኞች መግለጻቸውን ዘገባዎች ያስረዳሉ፡፡ የአገሪቷ አውሮፕላን ማረፊያ የተዘጋ ሲሆን፣ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያውም ለረዥም ሰዓታት ሥርጭቱን አቋርጦ ነበር፡፡
ደቡብ ሱዳን በጥቂቱም ቢሆን ተረጋግታለች የተባለው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በሲቪል ልብሳቸው ሳይሆን ሙሉ ወታደራዊ ዩኒፎርማቸውን ለብሰውና በባለሥልጣናት ታጅበው በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ሲሉ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ኪር በሰጡት መግለጫ ‹‹የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት መንግሥት ተቆጣጥሮታል፡፡ የመፈንቅለ መንግሥቱ ተሳታፊዎች ተመትተዋል፤›› ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኪር እንዳሉት ማንነታቸው ያልተለየና ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱ ታጣቂዎች ተኩስ የከፈቱት የሱዳን ፒዩፕል ሊብሬሽን ሙቭመንት (ኤስፒኤልኤም) ስብሰባ እያካሄደ ባለበት ጊዜ ነበር፡፡ ቀጥሎም የዶ/ር ሪክ ማቻርና የቡድኑ ደጋፊ ወታደሮች በጦር ኃይሉ ጠቅላይ መምርያ ላይ ተኩስ ከፍተዋል ብለዋል፡፡
‹‹እንደዚህ ዓይነቱን ድርጊት በአዲሲቷ አገራችን ውስጥ የምፈቅደውም የምታገሰውም አይደለም፡፡ ይህን ወንጀል አወግዘዋለሁ፡፡ ድርጊቱን የፈጸሙትም ሕግ ፊት ይቀርባሉ፤›› ሲሉ ፕሬዚዳንት ኪር ተናግረዋል፡፡
በደቡብ ሱዳን አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው መንግሥት ሥልጣን በኃይል እንዲሸጋገር አይፈልግም፡፡ መንግሥት የዜጐቹን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚገባውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡
የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባርናባ ማርኤል ቤንጃሚን ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደተናገሩት፣ በመፈንቅለ መንግሥቱ የተሳተፉ በጁባ የሚገኘውን የጦር መሣርያ መጋዘን ለመውረር ሞክረው አልተሳካላቸውም፡፡ ግጭቱ ከተነሳ ጀምሮ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ፖለቲከኞችም ታስረዋል፡፡
በመፈንቅለ መንግሥቱ እጃቸው አለበት የተባሉትና ባለፈው ሐምሌ ከኃላፊነታቸው የተባረሩት የቀድሞ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሪክ ማቻር በሱዳንና በደቡብ ሱዳን ላለፉት ሦስት አሥር ዓመታት በነበረው የከረረ ፖለቲካ ቁልፍ ሰው ነበሩ፡፡ በ1990ዎቹም የኤስፒኤልኤም ዋና ወታደራዊ ክፍልን ይመሩ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2005 በተደረገው የሰላም ስምምነት የሽግግር መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፣ ደቡብ ሱዳን እ.ኤ.አ. በ2011 ነፃ ስትወጣ እስከተሰናበቱበት ጊዜ ድረስ በሥልጣን ላይ ቆይተዋል፡፡
በደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ እንዳላቸው የሚነገረው ዶ/ር ማቻር እስካሁን ድረስ ያሉበት አልታወቀም፡፡ አስተያየት ሲሰጡም አልተሰማም፡፡ ቃል አቀባያቸው ግን በመልካም ሁኔታ እንደሚገኙና ታስረዋል የሚባለውም ሐሰት እንደሆነ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
በዓለም በድህነት ወለል ውስጥ ከሚገኙ አገሮች የምትመደበዋ ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ከተቀዳጀችበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ወዲህ እንድትረጋጋ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ የውስጥ መረጋጋትን ልትጐናፀፍ ግን አልቻለችም፡፡
በነዳጅ ዘይት ሀብቷ ከአንጐላና ከናይጄሪያ በመቀጠል ከአፍሪካ በሦስተኝነት ደረጃ ብትገኝም፣ በቅርቡ ከመመሥረቷና የመሠረተ ልማት ክፍተት በመኖሩ ዛሬም ዜጐቿ በድህነት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ዜጐቿ በብሔርና በፖለቲካ የተከፋፈሉና አብዛኞቹም የታጠቁ በመሆናቸው፣ የአገሪቱን የነዳጅ ዘይት ሀብት ለመጠቀምም ሆነ አገሪቱን በሥርዓት ለመምራት እንቅፋት ሆኗል፡፡
ፕሬዚዳንት ኪር ባለፈው ሐምሌ ካቢኔያቸውን ከበተኑና ምክትል ፕሬዚዳንቱን ዶ/ር ማቻር ካባረሩ በኋላ አገሪቷ ይበልጥ ተናግታለች፡፡
ፕሬዚዳንት ኪርና ዶ/ር ማቻር ከቀድሞውም ጀምሮ እርስ በርስ ሲጋጩ ከኖሩት የዲንካና የኑኤር ብሔረሰብ የመጡ በመሆናቸው፣ የብሔር ልዩነታቸውን አቻችለው ባለመሄዳቸው፣ በሥልጣን ዘመናቸው አንዱ ባንዱ ላይ እጃቸውን ሲያነሱ ነበር፡፡ በአገሪቱ ከፍለውን ሥልጣን ዲንካዎቹ የተሻለ ውክልና አግኝተዋል በሚልም ሲናቆሩ ከርመዋል፡፡
ከሰኞ ጀምሮ ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት የሰዓት እላፊ የተጣለባት የደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ መረጋጋት እንደታየባት ሮይተርስ ቢዘግብም፣ ማክሰኞ ግን በተኩስ እየተናወፀች ነበር ተብሏል፡፡
ሕፃናትና ሴቶችም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መጠለያ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በደቡብ ሱዳን በተፈጠረው አለመረጋጋት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጐች በጁባ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕከል ሰፍረዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአገሪቱ መረጋጋት እንዲፈጠር ጥሪ አቅርቦ ለዜጐች መሠረታዊና ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰጠው መግለጫ በጁባ ያለው አለመረጋጋት በቅርቡ እንደሚሰክንና መጠለያ ውስጥ ያሉት ዜጐች ወደየቤታቸው እንደሚመለሱ አስታውቋል፡፡ ነገር ግን የጁባ ፀጥታ በመታወኩ ሰባት ሺሕ ዜጎች ቤታቸውን ጥለው መሸሻቸው ተሰምቷል፡፡
ሦስት አሥርታትን በጦርነት ያሳለፉ ደቡብ ሱዳናውያን ዛሬም ካለመረጋጋት ሊወጡ አልቻሉም፡፡ ደቡብ ሱዳን የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ውድቀት ገጥሟታል፡፡ አገሪቱ ነፃ ወጥታ በእግሯ ሳትቆም ዜጐቿ የብሔር ልዩነታቸውን በማንገብ ሰላም አደፍርሰዋል፡፡ ሕዝቡን ይጠብቃሉ የተባሉት ወታደሮችም በብሔር ተከፋፍለው ለመንግሥት ታማኝ የማይሆኑበት ደረጃ ደርሰዋል፡፡
ደቡብ ሱዳን እንደ ነዳጅ ዘይት ሀብቷ በኢኮኖሚዋ እየበለፀገች ሳይሆን በብሔር ልዩነቶች እየታመሰች ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የሲቪል ልብሳቸውን አውልቀው በወታደራዊ ልብሳቸው ብቅ ብለዋል፡፡ በከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት በደቡብ ሱዳን የታየው አለመረጋጋት ወደ ብሔር ጦርነት ያመራ ይሆን የሚለው ሌላ ጥያቄ ሆኗል፡፡ ማክሰኞ ረፋዱ ላይ ጁባ ውስጥ እንደገና የከባድ መሣሪያ ድምፅ መሰማቱ ለበርካቶች መፈናቀል ምክንያት እንደሆነ አልጄዚራ ዘግቧል፡፡ ፕሬዚዳንቱ መፈንቅለ መንግሥቱ ከሸፈ ካሉ በኋላ የተሰማው የከባድ ጦር መሣሪያ ፍንዳታ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ አልተረጋገጠም፡፡ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ፕሬዚዳንቱ መፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፉን በእርግጠኝነት እየተናገሩ ነበር፡፡
No comments:
Post a Comment