ባገር አቋራጭ ወንዞች ላይ
ከተፈረሙ ስምምነቶች መማር እንችላለን?
በዶ/ር ከፍያለው አባተ
1.0 መቅድም
ድሮ አንዳንድ ጥቃቅን ጽሑፍ ስንጽፍ ሆሄያት አልጠበቃችሁም እየተባልን እንተች ነበር። ለብዙዎቻችን ሆሄያት ጠብቆ መጻፍ
አልሆንልን ብሎ እንደፈለግን ስንጽፍ ኖርን። አሁን ሆሄያት መርጠው በጥንቃቄ የሚጽፉ በጣት አይቆጠሩም። ያ እንደመለመድ
ብሎ ሌላ ነገር ብቅ አለ። አማርኛና እንግሊዝኛ እያደባለቁ መናገር(ጉራማይሌ ቋንቋ)። አማራጭ ካለ ጉራማይሌ ቋንቋ መናገር
አሁንም እሚደገፍ አይደለም። ነገር ግን እሚሰነዘረው ትችት አልገድበው ብሎ፣ ቋንቋ እየቀላቀሉ መናገሩ ስለቀጠለ ጉራማይሌ
ቋንቋ መናገርና መስማት ባሁኑ ጊዜ በጣም የተለመደ ነው። ይባስ ብዬ በጉራማይሌ ቋንቋ የተጻፈ ጽሑፍ ላስነብባችሁ ነው።
ጽሑፉ ጉራማይሌ የሆነበትን ምክንያት ለመረዳት የሚገዳችሁ አይመስለኝም። ወድጄ አላደረግሁትምና እንደምንም ብላችሁ
አንብቡት።
2.0 መግቢያ
በርካታ ምሁራን ደጋግመው እንደገለጹት ውሀ ልዩ የሆነ፣ ምትክ እማይገኝለት የተፈጥሮ ሀብት ነው። ያለውሀ ሰውም፣
እንስሳትም፣ እጽዋትም በሕይወት አይኖርሩም። ባጭሩ ያለውሀ ሕይወት የለም።
በቀደሙት ዘመናት ውሀ ልክ-የለሽና እማያልቅ(unlimited and renewable)የተፈጥሮ ሀብት ተደርጐ ይቆጠር ነበር።
ባሁኑ ዘመን ግን የሕዝብ ብዛት በፍጥነት ሲያድግ፣ የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች የውሀ ፍላጐትና ፍጆታ
ሲጨምርና ሲንር፣ የውሀ መጠን ግን ከዘመን ዘመን ‘ለውጥ የማያሳይ’ ስለሆነ ውሱን (limited and scarce
resource) የተፈጥሮ ሀብት ሁኖ በመታየት ላይ ነው።
በግልጽ እንደሚታወቀው ሁሉ ከየትኛውም አካባቢ ይልቅ የውሀ እጥረት ጐልቶ የሚታየው ደረቅ ያየር ንብረት (dry
weather/climate) ባላቸው፣ ወይም የዝናም እጥረት አዘውትሮ በሚከሰትባቸው የዓለም ክፍሎች ነው። ደረቅ ያየር ንብረት
ያለው የመሬት ስፋትን በተመለከተ አፍሪካን የሚወዳደር ሌላ አህጉር የለም። ይህ ድርቀት (የውሀ እጥረት) ከአህጉሩ
ጅኦግራፊያዊ አቀማመጥ ጋር የተያያዘ ነው።
ከመቶ ሰባ አምስት(75%)እጅ በላይ የሚሆን የአፍሪካ ምድር የሚገኘው በሁለቱ ኬንትሮሶች(between the tropic of
Cancer and Capricorn or b/n 23½º N and 23½º S latitudes)መካከል ነው። ከነዚህ ሁለት ኬንትሮሶች ውጭ
ያሉት በስተሰሜን በአትላስ ተራራ(Atlas Mts.)እና በስተደቡብ ደግሞ በድራክነስ በርግ ተራራ(Draknesberg
Mts.)አካባቢ የሚገኙት አንስተኛ የአህጉሩ ክፍሎች ብቻ ናቸው። ይህ ጅኦግራፊያዊ አቀማመጥ ሌሎቹ አህጉራት
እማይጋሩት(አፍሪካን “tropical continent” ያሰኘ)የአፍሪካ ብቸኛ አቀማመጥ ነው።
በዚህ ጅኦግራፊያዊ አቀማመጥ(በሁለቱ ኬንትሮሶች መካከል በመሆኑ)የተነሳ ከየትኛውም አህጉር የበለጠ ካመት እስካመት
ከፍተኛ የፀሐይ ኃይል(solar energy)የሚያገኝ ሙቅ(hot׃ relative to other continents)አህጉር ነው። የአህጉሩ
ሞቃትነት መሬት ላይ የሚገኘውን(ያፈሩንና የእጽዋቱን)እርጥበትና በወንዞችና በሀይቆች የሚገኘውን ውሀ ለከፍተኛ
ትነት(evapotranspiration)ይዳርገዋል። በዝናም ከሚገኘው ውሀ ይልቅ በትነት እሚጠፋው የውሀ መጠን
እሚበልጥበት(negative water balance)የአፍሪካ ስፋት ቀላል አይደለም። በዚህም የተነሳ(ባጠቃላይ መልኩ)ሰፊ የሆነ
የአፍሪካ ክፍል ከጨፌያማና ከለምለም ምድር ይልቅ፣ የውሀ እጥረት(ድርቀት)በሰፊው የሚስተዋልበት፣ የወንዞች
ብዛት(በኪሎ ሜትር ካሬ)/(river network density)
1 አንስተኛ የሆነበት፣ ማለትም ወንዞች እንደልብ እማይገኙበት
አህጉር ነው። ያሉት ወንዞችም በርካታዎቹ ሀገር-አቋራጭ ወንዞች ስለሆኑ አጠቃቀማቸው የሉዐላዊ ሀገሮችን መግባባትና
ስምምነት የሚጠይቅ ነው። ያለያም በተቃራኒው ውዝግቦችንና ውጥረትን እሚያስነሳ ነው።
ደሴቶቹ አፍሪካዊያን ሀገሮች ሳይቆጠሩ፣ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ሀገር-አቋራጭ ወንዝ እማይነካው አንድም ሀገር
አይገኝም(UN ECA, 2000 cited by Jonathan Lautze & Mark Giordano 20012?)። ስድሳ ሁለት
በመቶ(62%)የሚሆነው የአፍሪካ ምድር ቢያንስ ቢያንስ አንድ ሀገር-አቋራጭ ወንዝ ይሄድበታል/ያልፍበታል2። ይህ ስሌት
1 River network density = number of rivers or streams per unit area.
2
----- the boundaries of all of continental Africa’s countries are crossed by at least one transbounary
watershed (UN CEA 2000).የአፍሪካን ሀገር-አቋራጭ ወንዞች በዘላቂ ሁኔታ ለመጠቀምና ለማልማት የአፍሪካን ሀገሮች ተባብሮ የመስራት አስፈላጊነት
ያመለክታል። በተቃራኒው ደግሞ(ወንዞቹን ተስማምተው ለመጠቀም ካልቻሉ)ውሎ-አድሮ በሀገር-አቋራጭ ወንዝ ተጋሪ
ሀገሮች መካከል ፉክክርንና ፍጥጫን የሚፈጥር፣ ከጠና ደግሞ ጦርነት ሊያስነሳ የሚችል መሆኑን ያሳያል።
ሌላው አፍሪካን ከሌሎቹ አህጉራት የተለየ እሚያደርገው፣ ከላይ በተጠቀሰው ጅኦግራፊያዊ አቀማመጡ ምክንያት፣ አህጉሩ
እሚያገኘው አጠቃላይ የዝናም መጠን አንስተኛ መሆኑ ነው። ወደ አየር ንብረት ጥናት ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ ሳንገባ፣ ከላይ
በጠቀስኳቸው(አብዛኛው የአፍሪካ አህጉር በሚገኝባቸው)ሁለት ኬንትሮሶች መካከል የሚዘንበው ዝናም(tropical
rainfall)በመጠኑ፣ ባጀማመሩ/ባመጣጡና ባጨራረሱ/ባካሄዱ ሁሉ የሚለዋወጥ፣ ጸባዩ እማይታወቅና ለመተንበይ
እሚያስቸግር ነው3። እስካሁን ድረስ የተጠኑ ጥናቶች በወንዝ ውሀ አፈሳሰስና በዝናም አዘናነብ ላይ ቀጥተኛ የሆነ ጥብቅ
ግንኙነት(no strong linear relationship)ባያገኙም፣ የዝናሙ ተለዋዋጭነት ወንዞች ይዘውት የሚወርዱትን
ወቅታዊ(seasonal flow) እና ያጭር ጊዜ (short term) የውሀ መጠን አብሮ እንደሚለዋውጠው እማይታበል ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ይህ በመጠኑም ሆነ ባመጣጡ ተለዋዋጭነት እሚታይበትና አስተማማኝ ያልሆነ ዝናም በእቅድ ለመዝራትና
ለማጨድ ያስቸግራል። የሚዘራውን የእህል ዓይነትም ለመምረጥ አያመችም። ዝናም እሚጥልበት ወቅትና የተዘራው እህል ዝናም
እሚፈልግበት(እህሉ እሚያብብበት)ወቅት ሳይገናኙ እየቀሩ አርሶ አደሩ ሕዝብ ዘሩን እንኳን ለመመለስ እሚያስችል ምርት
ሳያገኝ የሚቀርበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም። ይህ አስተማማኝ ያልሆነ ዝናም እሚያስከትለውን ችግር ለመቅረፍ የወንዞችን
ውሀ (ቢያንስ ቢያንስ እንደ መደጐሚያ በመስኖ ልማት)መጠቀም አስፈላጊ ይሆናል።
ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ የምርምር ስራዎች የሚያሳዩን አጠቃላይ ስዕል ደስ እሚያሰኝ አይደለም። ቮሮስማርቲ የተባሉ
ምሁር ከሌሎች ተመራማሪዎች ጋር(Vorosmarty et.al. 20054
) ሁነው በጣምራ ያጠኑት ጥናት፣ ከ1961 ዓ.ም እስከ
1990 ዓ.ም ድረስ(ለሰላሳ ዓመታት ያህል) የአህጉራችን(የአፍሪካ)ጠቅላላ የዝናም መጠንና የወንዞቹ ውሀ እየቀነሰ
መሄዱን ይገልጻል።
ታዲያ የአህጉራችን አብዛኛው ክፍል የውሀ ችግር(የውሀ ውሱንነት)በግልጽ የሚታይበት ስለሆነ፣ የውሀ እጥረት ችግር ያለበት
ሁሉ ዓይኑን በወንዝ ውሀ ልማት ላይ ሲጥል፣ በወንዝ ውሀ አጠቃቀምና ክፍፍሎሽ ላይ ውዝግብ ለማስነሳት አመቺ ሁኔታን
ይፈጥራል። በውሀ አጠቃቀም ታሪክም የምንታዘበው፣ የውሀ ውሱንነት ከጊዜ ጊዜ ገሀድ እየሆነና እየጐላ በሄደ ቁጥር፣
የተገኘውን የወንዝ ውሀ አብሮ ባግባቡ የመጠቀሙና የመከፋፈሉ(ድርሻን የመደላደሉ)ጉዳይ፣ ሀ)ወደ ድርድሮችና
ስምምነቶች(negotiations and agreements)፣ ለ)ወደ ውዝግቦችና ውጥረቶች(conflicts and tensions)እያመራ
መሄዱን ነው።
ድርድሮች ሲደረጉ ከወንዞቹ ውሀዎች አጠቃቀም ጋር የተያያዙ፣ የባለቤትነት ጥያቄዎች፣ የመብት ጥያቄዎች፣ የሉዐላዊነት
ጥያቄዎች፣ የቀደምትነት(የታሪክ)ጥያቄዎች፣ የኢኮኖሚና የእድገት ደረጃ ጥያቄዎች አብረው መነሳት ከጀመሩ ውለው
አድረዋል። ባገር አቋራጭ ወንዞች አጠቃቀም የተነሳ የተከሰቱ ውዝግቦችንና ውጥረቶችን ለመፍታት የገላጋይነትና የሽምግልና
ስራዎች ሲሰሩ ኑረዋል። ውሎችና ስምምነቶች ተፈርመዋል። ባህላዊ ሽምግልናውንና ስምምነቱን መሠረት ያደረጉ፣ ለዳኝነት
አቅጣጫ ሊሰጡ የሚችሉ የሀገር አቋራጭ ወንዞች አጠቃቀም ድንጋጌዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ወጥተዋል። ከነዚህ ሁሉ
የራሳችን ሀገር-አቋራጭ ወንዞች ለመጠቀም ትምህርት እናገኝባቸዋለን ወይ? በሕግጋቱ አንጻር የራሳችን ወንዞች አጠቃቀም
ስናይ እምን ሁኔታ ላይ እንገኛለን?
ከዚህ ላይ አንባቢዎች ሊገነዘቡት የሚገባቸው አንድ ነገር አለ። በወንዞች የተነሳ የሚፈጠር ውዝግብ በደረቅ አካባቢዎች
ይጠና/ይብስ ይሆናል እንጂ፣ ድርቅ ወይም የውሀ እጥረት በሌለባቸው አካባቢዎችና አህጉሮችም በተደጋጋሚ ተከስቷል።
ወንዞች በተፈጥሮ ሚዛን ጠባቂነት፣ በአሳ ማጥመጃነት፣ በመጓጓዣነት፣ በመስኖ አገልግሎት፣ በኃይል አመንጭነት፣ በቱሪስት
መስህብነት፣ ወ.ዘ.ተ ስለሚያገለግሉ (የውሀ እጥረት ኖረም አልኖረም) በነዚህ ሁሉ አገልግሎቶች ሳቢያ በተጋሪ ሀገሮች
መካከል ውዝግብና ንትርክ ሊፈጠር ይችላል። ውዝግቡን ለማስወገድና ውጥረቱን ለማርገብ ውሎችና ስምምነቶች ይፈረማሉ።
ስለዚህ የወንዝ ውሀ ውዝግብና ውጥረት በፖለቲካ፣ በባህል፣ በማህበራዊ ኑሮና በኢኮኖሚ ስበቦች ሁሉ ሊከሰት ስለሚችል፣
የውሀን ውዝግብ ሁልጊዜ ከውሀ እጠረት/ችግር ጋር ብቻ አጣምሮ ማየት ትክክል አይሆንም።
3.0 የጽሑፉ ዓላማ
የሀገር አቋራጭ ወንዞችን ውሀ ክፍፍሎሽና አጠቃቀም በተመለከተ በዓለም ዙሪያም ሆነ በአፍሪካ ብዙ ልምዶች አሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የግብርናና የምግብ ድርጅት(UN FAO1978; 1984)ከ805 ዓ.ም እስከ 1984 ዓ.ም ድረስ
በዓለም ዙሪያ 3,600 ያገር አቋራጭ ወንዞች አጠቃቀምን የሚመለከቱ ስምምነቶች መፈጸማቸውን ይዘግባል። የተባበሩት
3 ይህ የዝናም ተለዋዋጭነትና ለትንበያ አስቸጋሪነት በምድር ሰቅ አቅራቢያ ያሉትን አካባቢዎችና እርጥበት ያዘለ ንፋስ መናኸሪያ የሆኑትን
አንዳንድ ክፍተኛ/ተራራማ ቦታዎች አይጨምርም።
4
በዚህ ጽሑፍ የሰፈሩ ዓመተ ምህረቶች ሁሉ ባውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር የታሰቡ ናቸው።መንግሥታት ዓለም አቀፍ የሕግ ኮሚሽን(International Law Commission/ILC)ያገር-አቋራጭ ወንዞችን አጠቃቀም
በተመለከተ ሕግ ለማርቀቅ እንዲረዳው፣ በዓለም ዙሪያ የተከናወኑ 300(ሦስት መቶ)ያገር አቋራጭ ወንዞች ስምምነቶችን
ለመሰብሰብ ችሎ ነበር(Aaron Wolf, 1999)። በአህጉራችን(በአፍሪካ)ውስጥም ባለፉት 140(አንድ መቶ
አርባ)ዓመታት ውስጥ የተፈጸሙ 150(አንድ መቶ ሃምሳ)ያገር አቋራጭ ወንዞች ውሎችንና ስምምነቶችን ለመመዝገብ
ተችሏል(Jonathan Lautze & Mark Giordano, 2012?)።
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በዓለም ዙሪያም ሆነ በአህጉራችን(በአፍሪካ)የተፈጸሙትን ውሎችና ስምምነቶች ሙሉ ዝርዝር
ከነይዘታቸው ለማቅረብ ሳይሆን፣ ባገር አቋራጭ ወንዞች ክፍፍልና አጠቃቀም(allocation and use)ላይ የሚነሱ ክርክሮች፣
ድርድሮች፣ ውሎችና ስምምነቶች አጠቃላይ ጸባያቸው ምን እንደሚመስል፣ ከጊዜ ወደ ጊዜም ውሎችና ስምምነቶች ምን መልክ
እየያዙ እንደመጡ ለማሳየት ነው። ከብዙዎቹ ጥቂቶቹን ብቻ በምሳሌነት በማንሳት ስለራሳችን ሀገር-አቋራጭ ወንዞች
አጠቃቀም፣ ስለመብትና ግዴታችን ትምህርትና ተመክሮ ለማስገኘት መሞከር ነው።
የብዙ ሀገር-አቋራጭ ወንዞችና የገባር ወንዞቻቸው መነሻ ስለሆንን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ እሚቀርበው ትምህርት ከኛ የበለጠ
እሚያስፈልገው አፍሪካዊ ሀገር እሚኖር አይመስለኝም።
በሀገር አቋራጭ ወንዞች አጠቃቀም ላይ የሚፈጸሙ ውሎችና ስምምነቶች፣ የሚረቀቁና የሚጸድቁ ድንጋጌዎችና ደምቦች
ብዙውን ጊዜ የሕግ ባለሙያዎች የሚሳተፉባቸው ናቸው። ይህ ጽሐፊ የሕግ ባለሙያ ስላልሆነ የተከናወኑትን የውሀ ውሎች፣
ስምምነቶች፣ ደምቦችና ድንጋጌዎች ሕጋዊ አንድምታዎቻቸውን(legal implications)ተንትኖና/ተርጉሞ ለማቅረብ
አይችልም። ስለዚህ ይህ ጽሑፍ በዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያ(International lawyers)ወገኖቻችን(ካሉ)ቢነበብና
የባለሙያ ትንተናቸውን ቢያቀርቡልን የተሻለ ትምህርት እንቀስምበት ይሆናል።
4.0 ዋና ዋናዎቹ ሀገር-አቋራጭ ወንዞቻችን
እንደሚታወቀው ከተራራማው የሀገራችን ክፍል እየተነሱ፣ የሀገራችን ድንበር አቋርጠው ወደ ጐረቤት ሀገሮች የሚፈስሱ
ታላላቅ ወንዞች አሉን። በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ ከሚጠቃለሉት ታላላቅ ወንዞች መካከል ባሮና አኮቦ(ሱዳን ውስጥ ሶባት)፣ ጥቁር
ዐባይ፣ ዲንደር፣ ረሀድ እና ተከዜ ይገኙበታል። እነዚህ የዐባይ ገባር ወንዞች ይዘውት የሚጓዙትን ወራጅ ውሀ ከሱዳንና ከግብጽ
ጋር ‘በጋራ’(በጋራ ከተባለ)ስንጠቀም ኑረናል። በጋራ የመጠቀም ድርድር፣ ውልና ስምምነት ግን የለንም(በ1902 ዓ.ም የሱዳንንና
የኢትዮጵያን ድምበር ከመለየት ጋር ተያይዘው በእንግሊዞችና በዳግማዊ አፄ ምኒልክ መካከል የተደረጉ የማስታወሻዎች ልውውጥ እንደውል ካልተቆጠረ
በስተቀር)።
ደቡባዊ አቅጣጫ ይዞ ወደ ኬንያ ድምበር(ወደ ቱርካና ሀይቅ)የሚፈስሰው ኦሞ የተባለው ወንዛችን ደግሞ ከኬንያ ጋር
ያገናኘናል። ገናሌና ዳዋ(ሱማሌያ ውስጥ ጁባ)፣ ዋቢና ሸበሌ(ሱማሊያ ውስጥ ሸበሌ)የሚባሉት ወንዞቻችን ከሱማሊያ ጋር
ውሀ እንድንጋራ አድርገውናል። በአፍሪካ ሀገር-አቋራጭ ወንዞች ላይ ስለተደረጉ ያጠቃቀም ድርድሮች፣ ውሎችና ስምምነቶች
በሰፊው የጻፉ፣ ላውትዜና ጅኦርዳኖ የተባሉ ሰዎች(2012, 1070)የኦሞ ወንዝ በሚገባበት የቱርካና ሀይቅና በጁባ ሸበሌ
ወንዞች አጠቃቀም ላይ (ጽሁፋቸውን እስከ ጻፉበት እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ) የተፈረሙ ውሎች እንዳልነበሩ በእርግጠኝነት
ተናግረዋል።
እነዚህ ወደ ጐረቤት ሀገሮች የሚፈስሱ ወንዞች ይዘውት የሚጓዙት ውሀ ከተራራማው ሀገራችን የተለያየ ክፍል ከሚነሱት ገባር
ወንዞች ሁሉ የተሰበሰበ ነው። ስለዚህ ስለአንድ ሀገር-አቋራጭ ወንዝ ስናወሳ ስለወንዙ ገባር ወንዞችም ጭምር ነው እምናወሳው።
አብዛኛው ካገራችን ተራራ የሚነሳው ጥቃቅን ወንዝ ሁሉ ያገር አቋራጭ ወንዞቻችን ገባር ነውና ይህን ሁሉ ገባር ወንዝ
እንደፈለግን ለመጠቀም ምን ያህል ነፃ ነን? ከጐረቤት ሀገሮች ጋር እማያነካኩን፣ በሙሉ ነፃነት ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው
‘የአዋሽ ሸለቆ’
5 ተፋሰስንና ወደ ስምጥ ሸለቆ ሀይቆች የሚገቡ ጥቃቅን ወንዞችን ብቻ ነው።
5.0 የሀገር አቋራጭ ወንዞች ውሎች ገጽታዎች በአፍሪካ
ጆናታን ላውትዜ (Jonathan Lautze) እና ማርክ ጅኦርዳኖ (Mark Giordano) የተባሉ ምሁራን በአፍሪካ ውስጥ
የተፈጸሙትን(ያገር አቋራጭ ወንዞች)ውሎች ታሪክ በሦስት ከፍለው አቅርበውታል።
ሀ) በዘመነ ቅኝ ግዛት የተፈጸሙ ውሎችና ስምምነቶች (ከ1862-1958)
ለ) በመጀመሪያው የነጻነት ዘመን የተደረጉ ውሎችና ስምምነቶች (ከ1959-1989)
ሐ) በኋለኝው የነጻነት ዘመን የተደረጉ ውሎችና ስምምነቶች (ከ1990-2004)
5 አዋሽ የሚገባበት አሳሌ ሀይቅ ከጅቡቲ ብዙ አይርቅም። በአሳሌ ሀይቅ አካባቢ ያለው የከርሰ ምድር ውሀ (ground water) ወደፊት
በሚካሄድ ጥናት ምናልባት ስፋት ያለውና፣ ውስጥ ለውስጥ ወደጅቡቲ ድምበር ውስጥ የሚገባ ሁኖ ቢገኝ የአዋሽ ወንዝም ቢሆን ተቀናቃኝ
ሊያመጣ ይችል ይሆናል። (ይህ የጽሐፊው የግል ግምት ነው)።በዚህ ጽሑፍ የውሎቹን ዝርዝር ሳይሆን፣ የውሎቹን አጠቃላይ ጸባይ/ገጽታ ለማቅረብ ይሞከራል።
ሀ) በዘመነ ቅኝ ግዛት የተፈጸሙ ውሎችና ስምምነቶች(1862-1958)ገጽታዎች
ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ከመቀራመታቸው በፊት አፍሪካዊያን ባመዛኙ በሀገር ግምባታ ሂደት ላይ ነበሩ። የተደራጁ መንግሥታት
ነበሩዋቸው የሚባሉት እንኳን ካንዱ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ እየዘመቱ፣ ያሸነፉትን ሕዝብ እያስገበሩ ከሚኖሩ በስተቀር
ለግዛቶቻቸው ዳር(frontier)እንጂ ድምበር አልነበራቸውም። ድምበር ከሌለ ድምበር-አቋራጭ ወንዞች አይኖሩም። በድምበር
የተለየ ሀገርም ከሌለ ሀገር-አቋራጭ ወንዞች ሊኖሩ አይችሉም።
አውሮፓውያን አፍሪካን ሲቀራመቱ፣ በወንዝ ተፋሰሶች(river catchments and/or watersheds)እና በወንዝ
ገበቴዎች(river basins)ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን ሕዝቦች(nations and nation states)በሀገር ከፋፍለው
ድምበር/መስመር ሲያወጡላቸው ድምበር-አቋራጭ ወይም ሀገር-አቋራጭ ወንዞች ተፈጠሩ። ካንዱ አካባቢ ተነስቶ ወደ
ሌላው አካባቢ ይወርድ የነበረው ወንዝ፣ ካንድ ‘ሉዐላዊ’ ሀገር ወደ ሌላ ‘ሉዐላዊ’ ሀገር የሚፈስስ ሀገር-አቋራጭ ወንዝ
ሆነ። ስለዚህ ብዙዎቹ ሀገር-አቋራጭ ወንዞች ቅኝ ገዢዎች ከፈጠሯቸው ያገር ድምበሮች ጋር የተፈጠሩ ናቸው።
በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረሙ የውሀ አጠቃቀም ስምምነቶችም ከዚሁ ድምበር ከመለየት ጋር የተያያዙ ናቸው። ይህን በተመለከተ
እኛ በምሳሌነት ልንጠቀስ የምንችል ነን። እንግሊዞች የባሮን ወንዝ፣ የዐባይን ወንዝ ከነገባሮቹ፣ እንዲሁም የጣናን ውሀ
አጠቃቀም በተመለከተ ከአፄ ምኒልክ ጋር የተደራደሩት፣ በ1902 ዓ.ም ባደረጉት በሱዳንና በኢትዮጵያ የድምበር ውል
አስታከው ነው።
አንዳንድ ወንዞች እንደ ድምበር(መስመር)እንዲያገለግሉ በመደረጋቸው በወንዞቹ ግራና ቀኝ ይኖሩ የነበሩ ተመሳሳይ ልማድና
ባህል የነበራቸው ሕዝቦች ግማሾቹ ወደ አንዱ ሀገር፣ ግማሾቹ ደግሞ ወደ ሌላው ኩታ-ገጠም ሀገር ተከልለው የተለያዩ ሀገሮች
ዜጐች ሆነዋል። እንደፈለጉ ወዲያም ወዲህም ይሻገሯቸውና እንዳሻቸው ይጠቀሙባቸው የነበሩት ወንዞች ያለ(መውጫና
መግቢያ)ቪዛ ሊሻገሯቸው አልቻሉም። የድምበሩን ወንዝ ውሀ ለመጠቀምም በሚመለከታቸው ኩታ-ገጠም ሀገሮች መካከል
ያጠቃቀም ውል መዋዋል አስፈላጊ ነበር። በምእራብ አፍሪካ፣ በጊኒና በሴራሊዮን መካከል በሚወርደው ታላቁ
ስካሪሲስ(Great Scarcies River)በሚባለው ወንዝ ላይ የተከሰተው ይኸው ነው።
ስካርሲስ የተባለውን ወንዝ በሸለቆው ውስጥ የሚኖሩ፣(በኋላ በድምበር የተነሳ ተለያይተው የጊኒ እና የሴራሊዮን ዜጐች
የሆኑ)ሕዝቦች አሳ ለማጥመድም ሆነ ለመጓጓዣ(navigation)እንዳሻቸው በጋራ ይጠቀሙበት ነበር። እንግሊዞች
ሴራሊዮንን፣ ፈረንሳዮች ደግሞ ጊኒን ሲይዙ፣ ስካርሲስ የተባለውን ወንዝ የሁለቱ ሀገሮች (የሴራሊዮንና የጊኒ) ድምበር
እንዲሆን(በጥር 1895 ዓ.ም ፓሪስ ላይ ተገናኝተው)ተስማሙ። በዚህ የድምበር ስምምነት የተነሳ በስካርሲስ ወንዝ ግራና
ቀኝ ይኖሩ የነበሩ ተመሳሳይ ልምድና ባህል የነበራቸው ሕዝቦች የተለያዩ ሀገሮች ዜጐች ሆኑ። እንግሊዞችና
ፈረንሳዮች(በ1895 ዓ.ም)በተስማሙበት መሠረት፣ እንግሊዞች በያዙት በወንዙ በስተቀኝ(ሴራሊዮን ክልል
ውስጥ)የሚኖሩት ነዋሪዎች ወንዙን እንደድሮው(ለፈለጉት ጉዳይ)እንዲጠቀሙበት ሲደረግ፣ በወንዙ በስተግራ በኩል ይኖሩ
የነበሩት በፈረንሳዮች ስር(በጊኒ ክልል ውስጥ)የተጠቃለሉት የስካርሲስ ወንዝ ነዋሪዎች ግን ወንዙን እንዳይጠቀሙ(በዚያው
በ1895ቱ የእንግሊዞችና የፈረንሳዮች ውል)ተከለከሉ(Giordano and Lautze, 2012,1058)።
ይህን የመሰሉ ነባሩን ሕዝብ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሲጠቀምበት ከኖረው የተፈጥሮ ሀብቱ የለዩ፣ ተመሳሳይ ማህበራዊ ኑሮ፣
ባህልና ልማድ ያላቸውን ሕዝቦች የተለያዩ ሀገሮች ዜጐች ያደረጉ፣ ሌሎች 18(አስራ ስምንት)ከድምበር ጋር የተያያዙ የወንዝ
አጠቃቀም ስምምነቶች በቅኝ ገዥዎች መፈረማቸውን ላውትዜና ጅኦርዳኖ(2012? 1058)ይዘግባሉ። ባህላቸውና
ህልውናቸው የተመሰረቱባቸው ወንዞቻቸው፣ በቅኝ ገዢዎች ድምበር(ክለላ)የተነሳ “የጀርመን ግምብ” የሆኑባቸው
አፍሪካውያን ጥቂት አይደሉም።
በፈረንሳይዎች ስር የወደቁት አፍሪካዊያን(ጊኒዎች)የስካርሲስን ወንዝ እንዳይጠቀሙ ሲከለከሉ በእንግሊዞች
ስር(በሴሪያሊዮን ውስጥ)የወደቁት ለምን የወንዙ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደተደረገ ለዚህ ጽሐፊ ግልጽ አይደለም። የዚህ ጽሐፊ
ግምት ምናልባት ከእንግሊዞች አንጻራዊ ኃያልነት ጋር የተያያዘ ይሆናል የሚል ነው። በዚያ ወቅት ከፈረንሳዮች ይልቅ እንግሊዞች
በወታደራዊ ድርጅትም ሆነ በኢኮኖሚ ጥንካሬ ላቅ ያሉ ነበሩ። በዓለም አቀፍ ተደማጭነትም ቢሆን እንግሊዞች ግምባር ቀደም
ደረጃ የያዙ ነበሩ። ስለዚህ አንጻራዊ ኃይላቸውንና ተደማጭነታቸውን በመጠቀም የስካርሲስን ወንዝ በብቸኝነት ለመጠቀም
ወስነው ይሆናል። ያም ሆነ ይህ የ1895ቱ የፈረንሳይና የእንግሊዞች ስምምነት የሰርካሲስን ወንዝ ውሀ ሙሉ በሙሉ
ለእንግሊዝ (ግዛት) ጥቅም እንዲሆን ያደረገ ነበር። ይኸ የውሀ ድልድል ነው? ወይስ ቅሚያ ነው?
ካንዱ ቅኝ ገዢ ክልል ወደ ሌላው ቅኝ ገዢ ክልል አቋርጠው የሚሄዱ ወንዞች ደግሞ ሀገር-አቋራጭ ወንዞች ሆኑ። እዚህ ላይ
“ሀገር-አቋራጭ” የሚለውን ቃል ጠንቅቆ መረዳት ይገባል።
ለምሳሌ ያህል ጊኒና አይቮሪ ኮስት የፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች ነበሩ። ከጊኒ ተነስቶ ወደ አይቮሪ ኮስት የሚፈስስ ወንዝ ቢኖር ሀገር-
አቋራጭ ወንዝ አይባልም ነበር። ምክንያቱም፣1ኛ/ ጊኒም አይቮሪ ኮስትም የፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች በነበሩበት ጊዜ ድምበር አልነበራቸውም። ከላይ እንደጠቀስኩት ድምበር
ከሌለ ድምበር-አቋራጭ ወንዝ አይኖርም።
2ኛ/ ድምበር ቢኖራቸውም ነፃነታቸውን የተገፈፉና ሉዐላዊነት(sovereignty)ያልነበራቸው ቅኝ ግዛቶች ስለነበሩ፣
የሀገራቸውን የተፈጥሮ ሀብት(የወንዝ ውሀን ጨምሮ)በፈለጉት መንገድ ለመጠቀም ስልጣን አልነበራቸውም። በቅኝ
ግዛቶቻቸው ውስጥ ሉዐላዊነት የነበራቸው ቅኝ ገዢዎቹ ብቻ ነበሩ። በግዛቶቻቸው ውስጥ ያለውን ወንዝ (ጊኒ ውስጥም ይሁን
አይቮሪ ኮስት) በፈለጉት መንገድ እንዳይጠቀሙበት የሚከለክላቸው ወይም የሚቀናቀናቸው ባለጋራ አልነበረም። ስለዚህ በዚህ
ምሳሌ የጊኒም፣ የአይቮሪ ኮስትም ሉዐላዊ ባለሥልጣኖች በዚያን ጊዜ ፈረንሳይዎች ነበሩ። ባንድ ሉዐላዊ መንግሥት (በዚህ
ምሳሌ በፈረንሳይ) ክልል ውስጥ የሚፈስስ ወንዝ ሀገር-አቋራጭ ወንዝ አይባልም።
ከአይቮሪ ኮስት ተነስቶ ወደ ጋና የሚወርድ ወንዝ ቢኖር ግን፣ ያ ወንዝ ሀገር-አቋራጭ ወንዝ ይሆን ነበር። ምክንያቱም ጋና
በእንግሊዞች ስር የነበረ(ሀገር)ሲሆን አይቮሪ ኮስት ግን በፈረንሳዮች ስር የነበረ ሀገር ነው። ስለዚህ ከፈረንሳይ ቅኝ
ግዛት(ከአይቮሪ ኮስት) ተነስቶ ወደ እንግሊዝ ቅኝ ግዛት(ወደ ጋና)የሚፈስስ ወንዝ ሀገር-አቋራጭ ወንዝ ይሆናል6። ስለዚያ
ወንዝ አጠቃቀምም ውልና ስምምነት የሚፈራረሙት እንግሊዞችና ፈረንሳይዎች ናቸው።
ለምሳሌ ያህል የናይጀር ወንዝ ሀገር-አቋራጭ ወንዝ የሆነው፣ ስላጠቃቀሙም ውልና ስምምነት የተከናወነው እንግሊዞችና
ፈረንሳይዎች በናይጀር ወንዝ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኙትን የምእራብ አፍሪካ ሀገሮች ተከፋፍለው፣ ለተከፋፈሏቸው ሀገሮች
ድምበር ሲያወጡ ነው(Giordano and Lautze, 2012)። በዚያው በምእራብ አፍሪካ በሴኔጋል ወንዝ ተፋሰስ ውስጥ
የሚገኙት ሀገሮች ግን ሙሉ በሙሉ ፈረንሳይዎች ይዘዋቸው ስለነበረ፣ የሴኔጋል ወንዝ ሀገር-አቋራጭ ወንዝ ሳይሆን ለረዢም
ጊዜ ቆይቷል። የሴኔጋል ወንዝ ሀገር-አቋራጭ የሆነው ጊኒ የተባለቺው የሴኔጋል ወንዝ እሚያልፍባት ሀገር፣ በ1958 ዓ.ም
ከቅኝ ገዧ (ከፈረንሳይ) ነፃ ስትወጣና ሉዐላዊ ሀገር ስትሆን ነው።
በዘመነ ቅኝ ግዛት በምስራቃዊው አህጉራችን የተፈጸሙትን የወንዞች ውሎችና ስምምነቶች ብንመለከት ተመሳሳይ ሁኔታ
እናያለን። በ1920ዎቹ አካባቢ በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ የሚካተቱ፣ በዐባይ አጠቃቀም ላይ ሊደራደሩና ሊዋዋሉ የሚችሉ
6(ስድስት)(six riparian states) ሉዐላዊ መንግሥታት ነበሩ7። እነሱም፣
ሀ) እንግሊዝ (ለሱዳን፣ ለዩጋንዳ፣ ለኬንያ፣ ለታንዛኒያ)
ለ) ፈረንሳይ (ለመካከለኛው የአፍሪካ ሪፑብሊክ/Central African Rep. (CAR)
ሐ) ቤልጅየም (ለዲሞ. ሪ. ኮንጐ፣ ለሩዋንዳ፣ ለቡሩንዲ)
መ) ጣሊያን (ለኤርትራ)
ሰ) ግብጽ
ረ) ኢትዮጵያ ናቸው።
የዚህን (የዐባይን) ተፋሰስ ውሀ ክፍፍሎሽና አጠቃቀም በተመለከተ ከፈረንሳዮችም፣ ከቤልጅየሞችም፣ ከጣሊያኖቹም፣
ከኢትዮጵያዊያንም ጋር ሲደራደሩ፣ ሲዋዋሉና ሲፈራረሙ የነበሩት እንግሊዞች ናቸው።
በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈጸሙ ውሎችና ስምምነቶች አብዛኞቹ ያተኮሩት በወንዞቹ ውሀ ክፍፍሎሽ ላይና ወንዞችን በመጓጓዣነት
በመጠቀም ላይ ነበር። የውሀው ድልድል/ክፍፍል በምን መስፈርት እንደተካሄደ ባይገለጽም፣ አብዛኛዎቹ የውሀ ክፍፍሎሽ
በሦስት ዋና ዋና መስፈርቶች ላይ የተመሠረቱ ይመስላሉ።
ቀዳሚ/ታሪካዊ ተጠቃሚነት(prior or historical use)፡ የወንዙን ውሀ ከጥንት ጀምረው(ለመስኖ፣ ለአሳ
ማስገር፣ ለመጓጓዣ፣ ወ.ዘ.ተ) ሲጠቀሙ የኖሩ የተፋሰስ ሀገሮች የተለመደው (customary use) ጥቅማቸው
እንዳይነካባቸው ተደርጓል። እነዚህም ውሎች ሱዳንንና ግብጽን የመሳሰሉትን የበታች ተፋሰስ ሀገሮችን ጥቅም
አስጠብቀዋል። በዐባይ ወንዝ ላይ ያበበው የግብጽ ጥንታዊ ሥልጣኔ ካምስት ሺህ ዘመናት በላይ ያስቆጠረ፣ በመስኖ
አጠቃቀም ታሪክም(በተፋሰሱ ውስጥ)ቀዳሚና ተወዳዳሪ የሌለው ነው። በኋላ እንደምናየው ነባሩን የውሀ
አጠቃቀም ማክበርና አለመንካት እስካሁን ድረስ በዓለም ዙሪያ በሚደረጉ ባብዛኞቹ ስምምነቶች የተጠበቀ ነው።
6
በዚህ አጠቃቀም ሀገር ማለት ቅኝ ግዛት ማለት ነው። አገር አቋራጭ ወንዞች የሚባሉት ካንድ ሉዐላዊ ሀገር ክልል ውስጥ ተነስተው፣
የተነሱበትን ሀገር ድምበር አቋርጠው ወደ ሌላ ሉዐላዊ ሀገር ክልል ውስጥ የሚገቡ ሲሆን ነው። ከሞላ ጐደል ራሳቸውን በነፃነት
የሚያስተዳድሩ መሆናቸው እውቅና ያገኘላቸው፣ ነገር ግን ገና በሉዐላዊ ሀገርነት እውቅና ያላገኙትን፣ የፍልስጤሞችን ምድር (ጋዛ ስትሪፕ
እና ዌስት ባንክ)፣ የኩርዶችን ግዛትና የመሳሰሉትን ክልሎች አቋርጠው የሚሄዱ ወንዞች አገር-አቋራጭ ወንዞች አይባሉም። ስለዚህ አገር-
አቋራጭ የሚባሉት ወንዞች ቢያንስ ቢያንስ ሁለት ሉዐላዊ ሀገሮችን እሚያገናኙ መሆን አለባቸው።
7 ባሁኑ ጊዜ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች (Nile riparian states) 11 (አስራ አንድ) ናቸው። እነሱም ግብጽ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣
ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጐ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኤርትራ ናቸው። መዋእለ ንዋይ (investment)፡ ሀገር አቋራጩን ወንዝ (ለመስኖ፣ ለኃይል ማመንጫ፣ ለአሳ ማርቢያና
ማጥመጃ፣ ለመጓጓዣ፣ ወ.ዘ.ተ) ለማልማት የተፋሰሱ ሀገሮች ተመጣጣኝ መዋእለ ንዋይ(equal
investment)አፍስሰዋል ወይ? የቅኝ ገዢዎቹ የውሀ ክፍፍሎሽ “በወንዙ ልማት ላይ እኩል መዋእለ ንዋይ ያፈሰሰ
የተፋሰስ ሀገር፣ ወንዙ የሚሰጠውን ጥቅም8 እኩል(መሳ ለመሳ፣ 50-50)እንዲካፈል ለማድረግ መሞከሩን
ጅኦርዳኖና ላውትዜ(Giordano and Lautze, 2012, 1060) ያብራራሉ።
የኢኮኖሚ እድገት ደረጃ (level of economic development)፡ በቅኝ ገዢዎች የተፈጸመው የሀገር-
አቋራጭ ወንዝ አጠቃቀም ውልና ስምምነት የኢኮኖሚ እድገት ደረጃን ግምት ውስጥ ያስገባ ይመስላል። ጅኦርዳኖና
ላውትዜ (2012) እንደሚያብራሩት፣
─ በምእራብ አፍሪካ፡ ከናይጀር ወንዝ ውሀ ከሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገሮች የበለጠ ናይጀሪያ እንድታገኝ
ተደርጓል።
─ በምስራቅ አፍሪካ፡ የዐባይን ውሀ ሙሉ በሙሉ ሱዳንና ግብጽ እንዲጠቀሙበት ተደርጓል። ከሁለቱ
ሀገሮች(ከሱዳንና ከግብጽ) መካከል ደግሞ አብዛኛውን ውሀ ግብጽ እንድትወስድ ተደርጓል።
─ በደቡብ አፍሪካ፡ የኦሬንጅ ወንዝ(Orange River)ውሀና የኩኔኔ(Cunene River)ወንዝ ውሀ
ዓይነተኛ ተጠቃሚ ደቡብ አፍሪካ እንድትሆን ተደርጓል (Giordano and Lautze, 2012,
1066)።(ኩኔኔ ወንዝ አንጐላን አቋርጦ ድሮ South West Africa በመባል ይጠራ በነበረው፣ በደቡብ አፍሪካ መንግሥት
ባላደራነት ስር ይተዳደር በነበረው፣ ባሁኑ ናሚቢያ (Namibia) ውስጥ የሚያልፍ ወንዝ ነው)።
ጂኦርዳኖና ላውትዜ እንደሚሉት ከሆነ፣ ሃምሳ በመቶ(50%)በሚሆኑት የወንዞች ስምምነቶች ውስጥ ግብጽ፣ ናይጀሪያና
ደቡብ አፍሪካ ይገኙበታል። የሀገር-አቋራጭ ወንዞቻቸውን ውሀ ክፍፍል በተመለከተ የነዚህ ሀገሮች ታሪክ ሲመረመር፣ ካንድ
ሌላ የተፋሰስ አባል ሀገር ጋር(bilateral)ተደራድረው ይፈራረማሉ እንጂ፣ ከብዙ የተፋሰሶቻቸው አባል ሀገሮች ጋር
(multilateral)የውል ስምምነት ሲፈራረሙ አይታዩም። ይህንንም እሚያደርጉት በድርድሩና በስምምነቱ ወቅት አንጻራዊ
ጥቅም(comparative advantage)ማግኘት እንዲችሉ ነው ይላሉ። የግብጽን ሁኔታ ብቻ ለይተን ብንመለከት የዚህን አባባል
እውነትነት እናያለን። ግብጽ ከሱዳን ጋር፣ ግብጽ ከዩጋንዳ ጋር፣ ግብጽ (በሞቡቱ ሴሴ ሴይኮ ዘመን) ከዲሞክራቲክ ኮንጐ ጋር
እንጂ፣ እንደ አንድ የዐባይ ተፋሰስ ሀገር ከሌሎቹ ዘጠኝ ሀገሮች ጋር አንድ ላይ ተደራድራ የተፈራረመቺው የውሀ ክፍፍሎሽ
ውልና ስምምነት የለም።
እነዚህ ሦስት ሀገሮች(ናይጀሪያ፣ ግብጽና ደቡብ አፍሪካ) የየአካባቢዎቻቸው አውራዎች/ኮርማዎች(hegemons)ናቸው
ማለት ይቻላል። ከላይ እንደተጠቀሰው ምንም እንኳን በሰነድ የተመዘገበ የውሀ አደላደል መስፈርት ባይገኝም፣ ከፍተኛውን
የውሀ ድርሻ እንዲያገኙ የተደረጉትን ሀገሮች(ናይጀሪያን፣ ግብጽን፣ ደቡብ አፍሪካን)ስናይ አንጻራዊ የሆነ የኢኮኖሚ
ጥንካሬያቸውን መሠረት ያደረገ አደላደል ይመስላል። ቅኝ ገዢዎቹ ያንን የመሰለ የውሀ ክፍፍሎሽ ሲያደርጉ(ከራሳቸው የግል
ጥቅም በተጨማሪ)በኢኮኖሚ አንጻራዊ እድገትና ጥንካሬ ያሳየ ሀገር ብዙ ውሀ ይገባዋል፣ በኢኮኖሚ ደካማ የሆነው ሀገር
ደግሞ አንስተኛ ውሀ ብቻ ይበቃዋል የሚል ውሳኔ የወሰኑ ይመስላል።
አዎ! በመሠረቱ የውሀ ፍላጐትና ፍጆታ(water needs)ጉዳይ ከኢኮኖሚ እድገት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለው እሙን
ነው። የደከመና ወደ ኋላ የቀረ ኢኮኖሚ ብዙ ውሀ አይፈልግም፣ ብዙ ውሀ አይፈጅም። የሁለት ሀገሮች የኢኮኖሚ እድገት
ደረጃ እየተራራቀ በሄደ ቁጥር የሚፈጁት የውሀ መጠን ልዩነትም የትየ-ለሌ (እጅግ በጣም ሰፊ) እየሆነ ይሄዳል።
ለማጠቃለል ያህል፣ በቅኝ ግዛት ዘመን ባገር አቋራጭ ወንዞች ላይ የተከናወኑ ውሎችና ስምምነቶች፣
ያተኮሩት ድምበር በመካለልና በውሀ ድርሻ (ክፍፍል) ላይ እንጂ፣ ውሀውን በጋራ በማልማትና አብሮ በመጠቀም
ላይ ባለመሆኑ ውል በተፈጸመባቸው ተፋሰሶች ሁሉ የጋራ የወንዝ ልማት ድርጅቶች(joint river basin
organizations)አልተቋቋሙም።
8 ወንዙ የሚሰጠውን ጥቅም መካፈልና፣ የወንዙን ውሀ መካፈል ልዩነት እንዳላቸው አንባቢ ልብ እንዲለው ያስፈልጋል። ለምሳሌ ወንዙ አሳ
ቢኖረው፣ አሳው ከወንዙ የሚገኝ ጥቅም ነው። ወንዙ የቱሪስት መስህብነት ቢኖረው፣ ከቱሪስቱ የሚገኘው ገቢ ከወንዙ የሚገኝ ጥቅም ነው።
ወንዙ ለመጓጓዣነት እሚያገለግል ቢሆን፣ ከንግዱ የሚገኘው ገቢ ወንዙ እሚሰጠው ጥቅም ነው። ውሀውን መካፈል ማለት ግን ውሀውን
ለቤት ፍጆታ፣ ለኢንዱስትሪ ፍጆታ፣ ለግብርናው (ለመስኖና ለመኖ) መስክ ፍጆታ፣ ወ.ዘ.ተ. እንዲውል የውሀ ድርሻ ማግኘት ማለት
ነው። በዘላቂነትእ ንዲያገለግሉ የታሰቡ ስለነበሩ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲሻሻሉ እና እንዲስተካከሉ(did not give
provisions for amendments) መሠረት ጥለው አልሄዱም።
ለ) በመጀመሪያው የነጻነት ዘመን (ከ1959-1989) የተደረጉ ውሎችና ስምምነቶች ገጽታዎች
በዚህ ዘመን (በ31 ዓመታት ውስጥ) ብዙ ነጻ የወጡ የአፍሪካ ሀገሮች በጋራ ወንዞቻቸው አጠቃቀም ላይ 72 (ሰባ ሁለት)
ውሎችና ስምምነቶችን መፈረማቸውን ጂኦርዳኖና ላውትዜ (2012) ይዘግባሉ። የውሀ ልማት ስራዎች በደረጁባቸውና የውሀ
እጥረት አሳሳቢ በሆነባቸው፣ በደቡብ አፍሪካ(በኦሬንጅና በኩኔኔ ወንዞች)በሱዳንና በግብጽ(በዐባይ ወንዝ)የውሀ ድርሻ
ስምምነቶች ተፈርመዋል።
በሌሎች ተፋሰሶችም ቅኝ ገዢዎች የፈጸሟቸውን ውሎችና ስምምነቶች ከሞላ ጐደል ተቀብለው ከነጻነት በኋላም በዚያው
መቀጠላቸውን ጂኦርዳኖና ላውትዜ ይገልጻሉ። በዚህም የተነሳ (በተለይ በምእራብ፣ በደቡብና በመካከለኛው አፍሪካ)በውሀ
ሰበብ በተፋሰስ ሀገሮች መካከል ብዙ ውዝግብና ውጥረት ሲፈጠር አልታየም ይላሉ (እንደላይኛው)።
በዐባይ ተፋሰስ በተፈጸሙ ውሎች ግን ከሱዳንና ከግብጽ በስተቀር የትኛውም የተፋሰስ አባል/ሀገር ደስተኛ አልሆነም። ይሁን
እንጂ እንግሊዞች(በ1929 ዓ.ም)የተከሉትን፣ በኋላም በ1959 ዓ.ም ሱዳንና ግብጽ የተካፈሉትን የዐባይ ወንዝ ውሀ ድርሻ
እስካሁን የነካ የለም። በዐባይ ውሀ ክፍፍሎሽና አጠቃቀም ላይ እስካሁን ድረስ ውዝግብና ውጥረት ቢኖርም፣ የዐባይ የበታች
ተፋሰስ ሀገሮች(ግብጽና ሱዳን)የወንዙ ውሀ ሙሉ ተጠቃሚዎች መሆናቸው እንደጸና/እንደቀጠለ ነው። ይህ የነበረውንና
የተለመደውን የውሀ ድርሻ ሳይነካኩ እንደነበረ የመተው(not to change existing use)አዝማሚያ በዓለም ዙሪያ
በተደረጉ የወንዝ አጠቃቀም ድርድሮች በሰፊው እንደሚስተዋል አሮን ወልፍ(Aaron Wolf, 1996) የተባሉ፣ በሀገር
አቋራጭ ወንዞች ስምምነቶች ላይ በሰፊው የጻፉ ምሁር ያስረዳሉ።
ከዚህ በተረፈ በመጀመሪያው የነጻነት ዘመን የተደረጉ ውሎች ከቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች የሚለዩባቸው ዓይነተኛ ጸባዮች፣
ከውሀ ክፍፍሎሽ ይልቅ ከመቶ ዘጠና(90%)የሚሆኑት ስምምነቶች ዓላማዎቻቸው ወንዞችን በጋራ በማልማት
(water development)
9 ላይ ያተኮሩ ነበሩ (እንደላይኛው)። ውሀን ማልማት ማለት ለኃይል ማመንጫነት
እሚያገለግሉ ግድቦችን በመገደብና የመስኖ ስራዎችን በማስፋፋት የወንዞችን ውሀ አጠቃቀም ማሳደግ ማለት ነው።
ስምምነቶቹ ወንዞቹን በጋራ የማስተዳደር (joint management)
10 ዓላማ የያዙ ነበሩ። ወንዞቹን በጋራ ለማልማት
የጋራ አስተዳደር አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን ሀላፊነት የያዙ የጋራ የውሀ ልማት ድርጅቶች(River basin
authorities እንዲቋቋሙ ተደረገ። ከዚህ ዓላማ በመነሳት በ1980 ዓ.ም(በናይጀር ወንዝ አባል ሀገሮች
መካከል)በተደረገው ስምምነት የናይጀር ወንዝ ባለሥልጣን(Niger Basin Authority)ተቋቋመ። የባለሥልጣኑ
ዓላማ፣ 1)በናይጀር ወንዝ ተፋሰስ አባል ሀገሮች መካከል ጠንካራ ትብብር(ኅብረት)መፍጠር፣ 2)በናይጀር
ወንዝ/ገበቴ ውስጥ(በኃይል ማመንጨት፣ በውሀ ሀብት፣ በግብርና፣ በከብት እርባታ፣ በአሳ እርባታ/ማጥመድ፣ በደን
ልማት፣ በመገናኛ፣ በኢንዱስትሪ፣ ወ.ዘ.ተ)የተቀናጀ ሁሉ-አቀፍ ልማት(integrated basin development in
all fields)መካሄዱን ማረጋገጥና መከታተል ነበር።
በተመሳሳይ(የናይጀርን ተፋሰስ በሚመስል)የትብብር መንፈስ፣ የሴኔጋል ወንዝ ልማት ድርጅት፣ የጋምቢያ ወንዝ ድርጅት፣
የካጌራ ወንዝ ድርጅት፣ የዛምቤዚ ወንዝ ድርጅት፣ የዐባይ ታችኛ ተፋሰስ ሀገሮች(የግብጽና የሱዳን)ቋሚ የቴክኒክ ኮሚቴ፣
ወ.ዘ.ተ ተቋቋሙ።
9 An agreement was defined to have “water development” as a goal if it included an explicit statement
regarding increased exploitation of shared water resources. Such increased exploitation generally takes
the form of dam construction to facilitate hydropower development/or expansions in the area of irrigated
land (Jonathan Lautze & Mark Giordano (2012), Trans boundary water law in Africa: Development, Nature and
Geography; Natural Resources Journal, vol.45, p1062).
10 An agreement was defined to have “joint management” as a goal if it included an explicit statement
regarding the creation of an institution or mechanism through which water resources would be
collectively managed as a means to achieve overall benefit and avoid potential conflict (Jonathan Lautze &
Mark Giordano (2012), Trans boundary water law in Africa: Development, Nature and Geography; Natural
Resources Journal, vol.45, p1062).እነዚህ የጋራ ድርጅቶች፣ ላይ-ላዩን ሲያይዋቸው የተፋሰሱ ሀገሮች አብረው ለመስራት መዘጋጀታቸውን ያመለክቱ ይሆናል።
አንዳንድ ተቺዎች እንደሚሉት ግን ድርጅቶቹ በተፋሰስ ሀገሮች ውስጣዊ አነሳሽነትና ፍላጐት የተፈጠሩ ሳይሆኑ፣ ባበዳሪ
ሀገሮችና(ባበዳሪ)ድርጅቶች ግፊት የተፈጠሩ ናቸው። አበዳሪ ሀገሮችና(አበዳሪ)ድርጅቶች “የጋራ የወንዝ ልማት
ባለሥልጣኖች” እንዲቋቋሙ የገፋፉበት/የሚገፋፉበት ምክንያት፣ የተፋሰሱ አባል ሀገሮች ከብጥብጥ ነፃ የሆኑ(conflict
free)አስተማማኝ ተበዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግና ለእጅ-አዙር ቅኝ አገዛዝ(neocolonialism)የተመቻቹ እንዲሆኑ ነው
ይላሉ።
በቅኝ ግዛት ዘመን አብዛኞቹ ስምምነቶች በሁለት ሀገሮች (bilateral agreements) መካከል የተካሄዱ ነበሩ።
አፍሪካዊያን ነፃ ከወጡ በኋላ ግን በርከት ያሉ የተፋሰሶች አባል ሀገሮች የተሳተፉባቸው(multilateral
agreements) ስምምነቶች (በዛምቤዚ ወንዝ፣ በናይጀር ወንዝ፣ በሴኔጋል ወንዝ፣ በካጌራ ወንዝ)ተከስተዋል።
የጋራ(የተፋሰስ)ውል ተፈራራሚ ሀገሮች ቁጥር ከፍ ባለ ቁጥር፣ አበዳሪዎች በልበ ሙሉነት(with confidence)
ብድር ይሰጣሉ የሚሉ አሉ።
በዚህ የመጀመሪያው የነፃነት ዘመን ከተካሄዱት የወንዞች ስምምነቶች መካከል ሃምሳ በመቶ(50%)ያህሉ ክርክር
ቢነሳ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት(OAU now AU)እና በተባበሩት መንግሥታት(UN)ዳኝነት?
(arbitration)መፍትሄ እንዲያገኝ ተስማምተዋል። ሲሶ(አንድ ሦስተኛ)የሚሆኑ ስምምነቶች የውሀ
ጥራት(water quality)አጠባበቅን ያካተቱ ሲሆኑ፣ ወደ ሁለት ሦስተኛ(⅔) የሚሆኑት ስምምነቶች ደግሞ የውሀ
ነክ መረጃዎች(exchange of hydrological data)ልውውጥን ይጨምራሉ(Giordano & Lautze,
2012, 1064)።
ሐ) በኋለኝው የነጻነት ዘመን (ከ1990-2004) የተደረጉ ውሎችና ስምምነቶች ገጽታዎች
በዚህ ዘመን(ከ1990-2004)የተፈጸሙ ውሎችና ስምምነቶችም የበፊተኞቹን ስምምነቶች አልሻሩም። በመጀመሪያው
የነፃነት ዘመን የተደረጉት ስምምነቶች ዓላማ ሀገር-አቋራጭ ወንዞችን ሁለ-ገብ በሆነ መልኩ በጋራ ማልማት ነበር። በኋለኛው
የነጻነት ዘመን የተደረጉት ውሎች የጨመሩት ነገር ቢኖር፣ የወንዞች ልማት ቀጣይነትና ዘለቄታ ያለው (sustainable water
development) እንዲሆን ማድረግ ነው። ይህም ማለት፣ ያሁኑን (ጊዜያዊ) ፍላጐት ለማርካት ብቻ በወንዞች ልማት ላይ
ርብርብ ሲካሄድ፣ የወደፊቱ ትውልድ ጥቅም እንዳይቃወስ፣ ውሀ እንዳይባክን፣ የወንዝ አሳዎች እንዳያልቁ/እንዳይጠፉ፣
ወንዞች ከኢንዱስትሪውና ከግብርናው መስክ በሚመነጩ ኬሚካሎች እንዳይበከሉ፣ የተፋሰሶች የተፈጥሮ ሚዛን እንዳይዛባ
ከልማት ስራው ጋር ጐን ለጐን ማስኬድ ማለት ነው።
ዘላቂ የወንዞች ልማትን በተመለከተ ከየትኛውም የአህጉሩ ክፍሎች፣ በደቡባዊ አፍሪካ ሀገሮች ኅብረት(Southern African
Development Community/SADC)ስር የተካተቱት በርከት ያሉ ውሎችን ተፈራርመዋል። ይሁን እንጂ የውሀ
ፍላጐትና ፍጆታ ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ፣ በዚህም ምክንያት ድሮ በቅኝ ግዛት ዘመን ይደረግ የነበረው የውሀ ድርሻ
ወይም የውሀ ክፍፍሎሽ ጉዳይ እንደገና በማገርሸቱ፣ አብዛኞቹ “ዘላቂ የወንዝ ልማት” sustainable water development
ውሎች የተፈረሙት በብዙ(multilateral)የተፋስስ አባል ሀገሮች ሳይሆን፣ በሁለት (bilateral) የተፋሰስ አባል ሀገሮች
ብቻ ነው። ይህም ማለት ብዙ የተፋሰሶች አባል ሀገሮች “ዘላቂ የውሀ ልማት” ውሎች ተሳታፊ/ፈራሚ አልሆኑም ማለት ነው።
6.0 የሀገር አቋራጭ ወንዞች ክርክሮችና ስምምነቶች ጸባይ
ወራጅ ውሀን ሙሉ በሙሉ ላልተወሰነ ጊዜ ለመገደብና ለማጠራቀም አይቻልም። ቢሞከርም ማጠራቀሚያውን አፈራርሶ
ስለሚሄድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ወራጅ ውሀን ለመካፈል ያስቸግራል። መጠኑ ከጊዜ ጊዜ (በክረምት፣ በበጋ)፣ ከቦታ
ቦታ (ከመነሻው፣ ከመሀሉ፣ ከመድረሻው) ይለያያል። ወራጅ ውሀን (የወንዝን ውሀ) በግል ባለቤትነት ለመያዝም ያስቸግራል።
ወራጅ ውሀ (ወንዝ) ከመነሻው እሰከመድረሻው አንድ አካል ነው። “ከድምበራችሁ ውስጥ ያለው የወንዝ ክፍል የናንተ፣
ከድምበራችን ውስጥ ያለው የወንዙ ክፍል የኛ ነው” ተብሎ፣ በክልላችሁና በክልላችን “እናንተም ያሻችሁን፣ እኛም ያሻንን
እናደርግበታለን” ለማለት አያስችልም። የላይኛው ተፋሰስ ነዋሪ ወንዙን ከቆረጠው፣ ለታችኛው ተፋሰስ የሚደርስ ውሀ
ስለማይኖር የቧንቧ ውሀ እንደመዝጋት የሚቆጠር ነው። ስለዚህ ሀገር-አቋራጭ ወንዝ በተፈጥሮው (በቅንነት ከተመለከትነው)
በመወያየት አብሮ ለመጠቀም የሚያመች እንጂ፣ በግል ባለቤትነት እንደፈለጉት እሚያደርጉት አይደለም።
እውነታው እሚጠይቀው ይህ ሁኖ ሳለ፣ የሀገር አቋራጭ ወንዞች ተጠቃሚ ሀገሮች ግን በወንዞቹ አጠቃቀምና በውሀ ድርሻ የተነሳ
አለመግባባት እየፈጠሩ ሲደራደሩ፣ ሲወዛገቡና ሲሟገቱ፣ ከጠናም በጦር መሳሪያ ሲፋጠጡ ይታያሉ። የክርክሮቻቸው ጭብጦች
መነሻ ብዙውን ጊዜ ከመብት ጋር የተያያዙ ናቸው።
6.1 የባለቤትነት መብት (ownership rights)፡ ይህ የባለቤትነት መብት ጥያቄ ብዙውን ጊዜ በበላይ ተፋሰስ ሀገሮች
የሚነሳ ነው። ሀገር አቋርጠው የሚሄዱት ወንዞች በሀገራችን ክልል ውስጥ የፈለቁ ስለሆኑ ባለቤቶቹ እኛ ነን (Water rights originate where the water falls/rises)፣ ያገራችን ድምበር አቋርጠው እስከሚሄዱ ድረስ እኛ እንደፈለግን
እንጠቀምባቸዋለን። በሀገራችን ድምበር ክልል ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት (ወንዞቻችን ጭምር) ለመጠቀም ካልቻልን፣
የባለቤትነት መብታችን ብቻ ሳይሆን ሉዐላዊነታችንም (absolute sovereignty) ተገፈፈ ማለት ነው በማለት ይከራከራሉ።
እንደ ኢራቅና እንደ ግብጽ ካሉ (ደረቅ በረሃ) የበታች ተፋሰስ ሀገሮች ጋር የወንዝ ውሀ የሚካፈሉ፣ ኢትዮጵያንና ቱርክን
የመሳሰሉ የበላይ ተፋሰስ ሀገሮች ሉዐላዊነትን መከራከሪያ ለማድረግ ሲሞክሩ ይስተዋላሉ።
ይህንን (የሉዐላዊ ባለቤትነትን) የመከራከሪያ ጭብጥ፣ በ1895 ዓ.ም በሪኦ-ግራንድ (Rio Grande River) ወንዝ
አጠቃቀም ላይ አሜሪካና ሜክሲኮ ባደረጉት ክርክር፣ ሀርመን (Harmon) የተባለ የአሜሪካ የሕግ ጠበቃ ተቀባይነት ሊኖረው
ይገባል በሚል ተከራክሮበታል (Aaron T. Wolf, 1999)። እንዲያውም ይህንን (የበላይ ተፋሰስ ሀገሮች ሉዐላዊነት)
“the Harmon Doctrine or the Harmon Principle” በማለት እስከመጥራት ደርሰው ነበር። ይሁን እንጂ በኋላ
የመጡ እንደ መካፍሬ (McCaffrey, 1996) ያሉ ሌሎች የአሜሪካ የሕግ ባለሙያዎች በየትኛውም የዓለም አቀፍ የሕግ
መድረክ፣ በየትኛውም የወንዝ ስምምነት፣ በየትኛውም የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ተቀባይነት አግኝቶ የማያውቅ፣ ዳር የወጣ
(extreme) አቋም ነው በማለት የሀርመንን አቋም ውድቅ አድርገውበታል። የሪኦ-ግራንድን ወንዝ አጠቃቀም በተመለከተም
አሜሪካና ሜክሲኮ የተስማሙት መብትን ከግዴታ ጋር ባጣመረ መላ/ዘዴ ነው።
ሜክሲኮ የሪኦ-ግራንድ ወንዝ የበታች ተፋሰስ ሀገር ነች። ሪኦ-ግራንድ የተባለው ወንዝ አሜሪካ ግዛት ውስጥም ሜክሲኮ ግዛት
ውስጥም የሚነሱ ገባር ወንዞች አሉት። በየሀገራቸው ክልል ውስጥ የሚገኙትን ገባር ወንዞች ሁለቱም ሀገሮች እንዳሻቸው
እንዲጠቀሙባቸው ተስማሙ። ይህ በገባሮቹ ወንዞች ላይ ያደረጉት ስምምነት የሁለቱንም ሀገሮች ሉዐላዊነት (Absolute
territorial sovereignty) አከበረላቸው። ገባሮቹ ሁሉ የተቀላቀሉበትን የዋናውን ወንዝ ውሀ ግን የአሜሪካን ሉዐላዊነት
በገደበ መልኩ (limited or restricted American territorial sovereignty)፣ የሜክሲኮንም የውሀ ድርሻ መብት
ሙሉ በሙሉ ባልጣሰ ሁኔታ ወንዙን ለመጠቀም “reasonable/fair use” ተስማሙ። ይሁን እንጂ በሜክሲኮና በአሜሪካ
መካከል የኢኮኖሚ እድገት ልዩነት ስላለ ይመስላል፣ ከሪኦ-ግራንድ ወንዝም ሆነ ከኮሎራዶ ወንዝ (Colorado River)
ሜክሲኮ የምታገኘው የውሀ ድርሻ ከአሜሪካ ያነሰ ነው (Aaron T. Wolf, 1999)።
6.2 የጥቅም ቀደምትነት (prior use; acquired/historic rights): ይህ የቀደምትነት ጭብጥ የሚነሳው ግብጽንና
ኢራቅን በመሳሰሉ፣ ደረቅና በረሃማ በሆኑ፣ ባመዛኙ በወንዝ ውሀ ብቻ በሚኖሩ የበታች ተፋሰስ ሀገሮች ነው። ወንዞቹ
ኢትዮጵያን፣ ምስራቅ አፍሪካንና ቱርክን ከመሳሰሉ ደጋና ዝናባማ ሀገሮች ተነስተው፣ በረሃ አቋርጠው ሂደው፣ ድርቅ
በሚጠናባቸው የበታች ተፋሰስ ሀገሮች ጥቅም ላይ እሚውሉ ወንዞች (exotic rivers11) ናቸው። የነዚህ ወንዞች የበላይ
ተፋሰስ ሀገሮች በዝናም ስለሚጠቀሙ እነዚህን ወንዞች ለረዢም ዘመናት ሳይጠቀሙባቸው ኑረዋል። የወንዝ ውሀ የመጠቀም
ረዥም ታሪክ የላቸውም፣ ማለትም ማህበራዊ ኑሯቸው፣ ባህላቸውና ኢኮኖሚያቸው በወንዞች አጠቃቀም ላይ የተመሠረተ፣
ከወንዞች ጋር በጥብቅ የተሳሰረ አይደለም። የበላይ ተፋሰስ ሀገሮች ብዙውን ጊዜ እሚያመቹት የውሀ ኃይል ለማመንጨት ነው።
የውሀ ኃይል ማመንጨት ደግሞ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በጣም አጭርና የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው።
በታች በኩል ያሉት ግብጽንና ኢራቅን የመሳሰሉት ሀገሮች ግን ሌላ አማራጭ ስለሌላቸው ከጥንት ጀምሮ ሕይወታቸው የተገነባው፣
ጥንታዊ ሥልጣኔያቸው (የመስኖ አጠቃቀምን ጨምሮ) ያበበው በነዚህ ሀገር-አቋራጭ ወንዞች ላይ ነው። ስለዚህ የወንዙን ውሀ
ለረዥም ጊዜ ስንጠቀም የኖርን ስለሆንን ታሪካዊ መብት (historic rights) አለን፣ ከየትኛውም የበላይ ተፋሰስ ሀገር በፊት
በወንዙ ስንጠቀም የኖርን የቀደምትነት መብት (prior use rights) አለን። ስለዚህ የነዚህን ሀገር-አቋራጭ ወንዞች ጥቅም
‘ትናንት’ ማየት የጀመረ የበላይ ተፋሰስ ሀገር፣ ነባሩን የውሀ ተጠቃሚነት መብታችን (acquired rights) ሊያዛባ
አይችልም/አይገባውም ባዮች ናቸው።
6.3 የወንዞች አንድ አካልነት (Absolute riverain integrity)፡ የዝናም እጥረት የሌለባቸውን ያውሮፓን፣ የላቲን
አሜሪካንና የሩቅ ምስራቅ ሀገሮችን አቋርጠው የሚሄዱ ወንዞች፣ በበታች ተፋሰስ ሀገሮችና በበላይ ተፋሰስ ሀገሮች መካከል
በተለያየ ጊዜ ውዝግብ አስነስተዋል። የውዝግቦቻቸው ጭብጦች ከላይ(በ6.1 እና በ6.2)ካብራራኋቸው ብዙ የሚለዩ
አይደሉም። ተከራካሪ ሀገሮችንም ለማቀራረብና ለማስማማት እማያመቹ ናቸው።
ወንዞቹ የሚነሱባቸው የበላይ ተፋሰስ ሀገሮች የወንዞቹ ሉዐላዊ ባለመብቶች ነን፣ በድምበራችን ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት
በፈለግነው መልክ የመጠቀም መብታችን የተጠበቀ ነው ይላሉ (Absolute territorial sovereignty)። የበታች ተፋሰስ
11 Exotic rivers are those rivers that flow across different climatic regions. The rivers rise in humid areas
and flow across arid regions. In other words, the upper segment of the river is in humid climates, whereas,
the lower segment of the river is in arid climates.ሀገሮች ደግሞ ከበላይ ተፋሰስ ተነስቶ እስከ ታችኛው ተፋሰስ ድረስ የሚወርደው ወንዝ በተፈጥሮው የተያያዘ፣ የተሳሰረ፣
ሊከፈልና ሊቆረጥ እማይችል አንድ አካል ነው ይላሉ። ያንን የተፈጥሮ መልኩን ይዞ የሚወርደውን ውሀ የማግኘትና የመጠቀም
መብት አለን። ይህንን የወንዝ ተፈጥሯዊ መልክና አንድ አካልነት (absolute riverain integrity) የበላይ ተፋሰስ ሀገር
እንዲያናጋው አንፈቅድም ይላሉ።
እነዚህ ከላይ ከቁጥር 6.1 እስከ ቁጥር 6.3 የተዘረዘሩት የክርክር አቋሞች፣ የበላይና የበታች ተፋሰስ ሀገሮችን
እማያቀራርቡ፣ በመብት (rights) ላይ ያተኮሩ፣ አጥባቂነት የሚታይባቸው፣ የግል ጥቅምን ብቻ ለማስከበር የሚሞክሩ፣
እልህ ውስጥ እሚያስገቡና አስፈላጊ ያልሆነ ውጥረት (tension) የሚፈጥሩ ግትር አቋሞች ናቸው። እስካሁን ድረስ
እነዚህን (ከ6.1 እስከ 6.3 የተዘረዘሩትን) ግትር አቋሞች ይዘው በሀገር አቋራጭ ወንዞች ላይ የተዋዋሉና ስምምነት ላይ
የደረሱ የሀገር-አቋራጭ ወንዝ ተደራዳሪዎች አልታዩም/የሉም(Aaron Wolf 1999, 10)። እነዚህ ግትር መብት-ነክ
የክርክር ጭብጦች መሟገቻ እንጂ መስማሚያ አይደሉም።
ብዙ የወንዝ ድርድሮችንና ስምምነቶችን የመረመሩ (Gilbert White 1957, Vlachos 1990, Dellapenna 1994,
Wescoat 1995, Aaron Wolf 1999, እና ሌሎችም) ጽሐፊዎች እንደሚሉት፣ ተደራዳሪዎች መጀመሪያ በመብት ጥያቄ
ይነሱና፣ በመጨረሻ ስምምነት ላይ የሚደርሱት ግን መብትን ከቁጥር በማያስገባ ለየት ባለ (አስታራቂ) ዘዴ ነው። ለዚህ ዓይነቱ
አስታራቂ ዘዴ በታሪክ የተከሰቱ አንዳንድ ልምዶችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።
በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ በፈረንሳይና በስፔን (Spain) መካከል ካሮል (Carol River) በሚባል ሀገር-አቋራጭ
ወንዝ አጠቃቀም ላይ የተከሰተ ታሪክ አለ። ካሮል የሚባለው ወንዝ ፈረንሳይን አቋርጦ ወደስፔን የሚፈስስ ወንዝ ነው።
ፈረንሳዮች (በበላይ ተፋሰስ ሀገርነታቸው) የካሮልን ወንዝ የተፈጥሮ መስመር ለውጠው፣ ግድብ ገድበው የውሀ ኃይል
ለማመንጨት ወሰኑ። ስፔኖች ለሚያጡት ውሃ ማካካሻ የሚሆን ፈረንሳዮች ገንዘብ ለመክፈል ፈቃደኛ መሆናቸውን ገለጹ።
ስፔን ግን የፈረንሳዮችን ሀሳብ (የገንዘብ ክፍያውን ጭምር)አልተቀበለቺውም። ፈረንሳዮች የካሮልን ወንዝ የተፈጥሮ
አፈሳሰስ(absolute riverain integrity) እንዲነካኩ እንደማትፈቅድና የካሮልን ወንዝ ለመስኖ ልማት የምትፈልገው
መሆኗን ስፔን አስታወቀች (Aaron T. Wolf, 1999)። በዚያ ሁኔታ ማለትም ፈረንሳይዎች በሉዐላዊነታችን
(Absolute territorial sovereignty) በክልላችን ውስጥ ያለውን (የካሮልን) ወንዝ እንደፈለግን እንጠቀምበታለን
በማለቱ ቢጸኑ፣ ስፔኖች ደግሞ የወንዛችን ተፈጥሯዊ አወራረድና መልክ (absolute riverain integrity) አናስነካም
በማለቱ ቢጸኑ ኖሮ ውጤቱ መፋጠጥና መጋጨት እንጂ፣ ወንዙን ጥቅም ላይ ለማዋል እሚያስችል አይሆንም ነበር።
ስለዚህ ሁለቱን ሀገሮች (ፈረንሳይንና ስፔንን) ሊያስማማ የሚችል አስታራቂ ያጠቃቀም አማራጭ መፈጠር ነበረበት። አስታራቂ
ሆኖ የተገኘው ሀሳብ፣ ፈረንሳይ የካሮልን ወንዝ ገድባ የውሀ ኃይል እንድታመነጭ፣ ውሀው ኃይል ካመነጨ በኋላ እዚያው
ፈረንሳይ ክልል ውስጥ ተመልሶ ወደ ወንዙ ውሀ እንዲቀላቀልና የተፈጥሮ አፈሳሰሱን ይዞ ወደ ስፔን እንዲፈስ ማድረግ ነበር።
ይህ ውል Lac Lanoux treaty በመባል ይታወቃል። የተፈረመውም በ1958 ዓ.ም ነው። ይህ ስምምነት የሁለቱንም ሀገሮች
ግትር አቋም ያስወገደ፣ የፈረንሳዮቹን ሉዐላዊነት በትንሹ የገደበ፣ የስፔኖቹን የወንዝ አንድ አካልነት (absolute riverain
integrity)ጥያቄም በከፊል የጣሰ አስታራቂ “reasonable, fair use” አሰራር ነበር። ስለዚህ ሁለቱም ሀገሮች ከመብታቸው
ትንሽ ትንሽ ቀንሰው በመተው ወደ ስምምነት ደረሱ።
ከኦስትሪያ (Austria) ወደ ባቫሪያ (Bavaria)/ጀርመን የሚወርድ አምስት ገባር ወንዞች ያሉት አይሳር (Isar River)
የሚባል ወንዝ አለ። በ1950 ዓ.ም በኦስትሪያና በባቫሪያ/ጀርመን መካከል ድምበር ሲከለል፣ በሁለቱ ሀገሮች ስምምነት
አንዱ ገባር ወንዝ ሙሉ በሙሉ ወደ ባቫሪያ/ጀርመን እንዲፈስስ ተደረገ። ሁለቱ ወንዞች ሙሉ በሙሉ በኦስትሪያ እንዲለሙ
ተደረገ። ሌሎቹ ሁለቱ ደግሞ ኦስትሪያ እንድታለማቸው፣ በክረምት ወቅት ግን (ከነዚሁ ወንዞች) በቂ ውሀ ለባቫሪያ/ጀርመን
እንዲለቀቅ ሁለቱ ሀገሮች (ኦስትሪያና ባቫሪያ) ወሰኑ (Aaron T. Wolf, 1999)። ይህ የውሀ ክፍፍሎሽ የሁለቱንም ሀገሮች
ጥቅም የጠበቀ “reasonable“ ስምምነት ነበር። በኦስትሪያና በቸኮዝላቫኪያ፣ በሀንጋሪና በቸኮዝላቫኪያ መካከልም እንደዚሁ
የወንዞቻቸውን ውሀ እኩል ለኩል ሊካፈሉ ተስማምተዋል (እንደ ላይኛው)።
ስለዚህ ባገር አቋራጭ ወንዞች ተጠቃሚዎች መካከል የሚነሳው ውዝግብ (dispute) መጀመሪያ ላይ መብት በማስከበር ላይ
የተመሠረተ ቢሆንም፣ ተደራድረው በመጨረሻ ለስምምነት እሚበቁት ግን መብቶቻቸውን በሚገድቡ፣ እንደየ ተፋሰሱ ሊለያዩ
በሚችሉ አስታራቂ ሀሳቦች ላይ ነው።
አሮን ወልፍ(Aaron Wolf, 1996)እንደሚሉት ድርቅ ባለባቸው ሀገሮች የተፈረሙ የውሀ ድርሻ (water allocations)
ውሎች ሁሉ፣ ሙሉ በሙሉ በውሀ አስፈላጊነት (needs-based) ላይ የተመሠረቱ እንጂ በመብት (rights-based) ላይ
የተመሰረቱ አይደሉም ይላሉ። ለዚህ አባባላቸውም የሚከተሉትን ሀገሮች በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። በ1929 ዓ.ም እና በ1959 ዓ.ም ከሱዳን ጋር ሲነፃፀር ብዙ ሕዝብና (በተለያዩ ቅኝ ገዢዎቿ አስተዋጽኦና
በእንግሊዞችም ድጋፍና ግፊት ጭምር ያስፋፋቺው) በጣም ሰፊ የመስኖ እርሻ ስለነበራት፣ እንደ ዋተርበሪ
(Waterbury,1979) አባባል ለግብጽ ባመት 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ ሲመደብላት፣
ለሱዳን ግን ባመት 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ተመደበላት። በዚያው (በ1959ኙ) ውላቸው፣
ወደፊት እንደ ልማት ደረጃቸው የወንዙን ውሀ እኩል እኩል እንደሚካፈሉ ሱዳንና ግብጽ ተስማምተዋል።
የዮርዳኖስን ወንዝ (Jordan River) አጠቃቀም በሚመለከት፣ ጆንስተን (Johnston)12 የተባለ ሰው
በወንዙ ተፋሰስ ውስጥ ያለውን የውሀ ፍላጐት የወሰነው፣ በተፋሰሱ ውስጥ (ያለመሳሪያ) በመስኖ ሊለማ
የሚችለውን የመሬት ስፋት (irrigable land by gravity flow) በመለካት ነበር። ከዚያ በኋላ
ተፋሰሱን በሚጋራ በያንዳንዱ ሀገር ድምበር ውስጥ ምን ያህል በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት (area of
irrigable land) እንዳለ ማወቅና፣ የወንዙን ውሀ እንደመሬቱ ስፋት (proportionately) አስልቶ
ማከፋፈል ነበር። የውሀው አከፋፈል ዘዴ እያንዳንዱ ሀገር የራሱን ድርሻ እንዳሻው እንዲያደርገው
የሚያስችል ነበር።
የአደላደሉ ዘዴ በመስኖ ሊለማ የሚችል የመሬት ስፋትን እንጂ፣ የሕዝብን ብዛትና የኢኮኖሚን የእድገት
ደረጃ ግምት ውስጥ ያስገባ አልነበረም። በዚህ አደላደል ውሀ ያነሳቸውና ውሀ የተረፋቸው ሀገሮች ነበሩ።
ነገር ግን የዮርዳኖስ ተፋሰስ ሀገሮች ሁሉ ዘዴውን አልጠሉትም። እንደ ዮርዳኖስ ያሉ የወደፊቱ የውሀ
ፍላጐታቸው ከሚደርሳቸው የውሀ ድርሻ በታች የሆነላቸው ሀገሮች፣ ውሀ ከሚያንሳቸው ሀገሮች ጋር
በመደራደር የአካባቢውን የውሀ ችግር ለመፍታት እሚያስችል አዲስ የውሀ አደላደል ዘዴ ነበር። በዚህ
አደላደል ፍልስፍና “የውሀ ፍላጐት” ማለት የመስኖ ውሀ ፍላጐት ማለት ነው።
በ1995 ዓ.ም እስራኤል ለመጀመሪያ ጊዜ በዌስት ባንክ (West Bank) ለፍልስጤሞች የውሀ ድርሻ
እውቅና ስትሰጥ፣ ፍልስጤሞች (ለቤት ፍጆታና ለግብርናው መስክ የሚሆን) ባመት ከ70 እስከ 80
ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ እንደሚያስፈልጋቸው ተሰልቶ ነበር። ከዚህ ውስጥ ባመት 28.6 ሚሊዮን
ኪዩቢክ ሜትር ውሀ ለመስጠት እስራኤል ተስማምታ ነበር።
ሜክሲኮና አሜሪካ የኮሎራዶን ውሀና የሪኦ-ግራንድን ውሀ የተደላደሉት የሜክሲኮን የመስኖ እርሻ የውሀ
ፍላጐት መስፈርት በማድረግ ነበር (Aaron Wolf, 1996)። ስለዚህም ነው ሜክሲኮ ከነዚህ ወንዞች
ካሜሪካ ያነሰ ውሀ እንድታገኝ የተደረገው።
ባንግላዲሽ ከጋንጀስ ወንዝ የምታገኘው ውሀ በመስኖ እርሻዋ ስፋት ላይ የተመሠረተ ነው (እንደላይኛው)።
እነዚህ ምሳሌዎች እሚያሳዩን፣ የወንዝ ውሀ አደላደል በፍላጐት/በውሀ ተፈላጊነት(needs-based) ላይ የተመሠረተ እንጂ
በባለመብትነት ላይ (rights-based) የተመሠረተ አለመሆኑን ነው። ስለዚህ ባለመብት መሆን ጠቃሚ ቢሆንም፣ መብት ላይ
ማተኮር ብቻውን የረባ የውሀ ድርሻ አያስገኝም። በድርድር የረባ የውሀ ድርሻ ለማግኘት፣ ፍላጐት (need) መኖሩን
በተጨባጭ ማሳየት/ማሳመን ያስፈልጋል።
አሮን ወልፍ(1996)አበጥረው ካጠኗቸው ከ145(አንድ መቶ አርባ አምስት)የወንዞች ስምምነቶች ተነስተው
እንደሚናገሩት፣ በዓለም ዙሪያ የተፈጸሙት አብዛኛዎቹ ስምምነቶች በፍላጐት (needs-based) ላይ የተመሠረቱ ናቸው
ይላሉ። ዋናዎቹ የውሀ ፍላጐት መገለጫዎች/መመዘኛዎች (needs are defined by)፣
12
----- Johnston’s approach was to estimate, without regard to political boundaries, the water needs for all
irrigable land within the Jordan Valley which could be irrigated by gravity flow. National allocations
were then based on these in-basin agricultural needs, with the understanding that each country could then
use the water as it wished, including to divert it out-of-basin. This was not only an acceptable formula to
the parties at the time, but it also allowed for a break-through in negotiations when a land survey of
Jordan concluded that its future water needs were lower than previously thought. (Aaron T. Wolf 1999,
Criteria for equitable allocations: The heart of international water conflict: Natural Resources Forum, Vol.23, #1,
p11).1ኛ/ በመስኖ ሊለማ የሚችል የመሬት ስፋት (irrigable land)
2ኛ/ የሕዝብ ብዛት (population)
3ኛ/ የሚታወቅ ፕሮጀክት የውሀ ፍጆታ(water requirements of a specific project) ናቸው ይላሉ።
ከነዚህ ከሦስቱ መስፈርቶች በተጨማሪ ድርድርና ስምምነት ከመደረጉ በፊት የነበሩ የውሀ አጠቃቀሞች(prior uses;
existing uses)፣ የውሀ ፍላጐትን(needs)ጥሩ አድርገው ያሳያሉ ይላሉ አሮን ወልፍ(1999)። በዚህም የተነሳ ውሎችና
ስምምነቶች ሲፈጸሙ፣ ነባሩ የውሀ አጠቃቀም ሳይነካ እንደተከበረ እንዲቀጥል መደረጉን ወልፍ (1999) ይገልጻሉ።
7.0 ለየት ያሉ የውሀ ስምምነቶች
እስካሁን ካየናቸው ለየት የሚሉ የውሀ ስምምነቶች አልፎ አልፎ ተከስተዋል። ከነዚህም ለምሳሌ ያህል ጥቂቶቹ የሚከተሉት
ናቸው።
1ኛ) ውሀው ከሚያስገኛቸው የተለያዩ የኢኮኖሚ ጥቅሞች መካከል መርጦ ለተሻለው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲውል
መስማማት፣
ለምሳሌ በ1950 ዓ.ም አሜሪካና ካናዳ በናያጋራ ፏፏቴ(Niagara Falls)አጠቃቀም ላይ ሲደራደሩ፣ በበጋ ወራት
ፏፏቴው በኃይል ማመንጫነት ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ፣ እንዳለ እንዲወርድ ቢደረግ ከቱሪስት
መስህብነቱ(በያንዳንዱ ኪዩቢክ ሜትር ውሀ) የበለጠ ገቢ እንደሚገኝ አስልተው፣ በበጋ ጊዜ የፏፏቴው ውሀ ሳይነካ
እንዲወርድና ጉብኚቱ እሚያስገኘውን ገቢ ለመሰብሰብ በስምምነት መርጠዋል።
በሰኔ ወር 1925 ዓ.ም የሱዳን ገዥ የነበረው የእንግሊዞች ጀኔራልና የኤርትራ ገዥ የነበረው ጣሊያናዊ በጋሽ ወንዝ
አጠቃቀም ላይ ሲዋዋሉ፣ ጣሊያኖች የጋሽን ውሀ ሳይገድቡ ወደ ሱዳን እንዲፈስስ የሚያደርጉ ከሆነ፣ ሱዳኖች በያመቱ
50,000(ሃምሳ ሺህ)ስተርሊንግ ፓውንድ የውሀ ኪራይ ለጣሊያን ሊከፍሉ፣ ከሚመረተው ሰብል ጣሊያን ሃያ
በመቶ (20%) ከሱዳን ልትቀበል ተስማምተው ነበር(Waterbury 2002, 47)። ይህ ስምምነት እሚያሳየው
የጋሽን ወንዝ ሙሉ በሙሉ ኤርትራ ውስጥ ከመጠቀም ይልቅ ወደ ሱዳን እንዲፈስስ ቢደረግ የተሻለ የኢኮኖሚ ጥቅም
ማስገኘቱን ጣሊያኖች ያመኑበት መሆኑን ነው። ስምምነቱም ጣሊያን ኤርትራን ለቅቃ እስከሄደችበት እሰከ 1941
ዓ.ም ድረስ በተግባር ሲተረጐም ቆይቷል(Aaron Wolf 1999)። (በነገራችን ላይ ይህ ውል የበላይ ተፋሰስ ሀገሮች የውሀ
መብቶች ሙሉ በሙሉ ከተከበሩባቸው በጣም ጥቂት ውሎች አንዱ ነው)።
2ኛ) የሀገርን የውሀ ሀብት በውጭ መንግሥት እንዲለማ አስደርጐ የሚገኘውን ጥቅም መጋራት/መካፈል።
ለምሳሌ በ1986 ዓ.ም ደቡብ አፍሪካና የሌሶቶ መንግሥት ባደረጉት ስምምነት መሠረት፣ ደቡብ አፍሪካ የሌሶቶን
ወንዞች ለማልማት(ግድብ ለመገደብ)ብዙ ወጭ አውጥታለች። የሌሶቶ መንግሥትም ከግድቡ የሚወጣውን
የኤሌትሪክ ኃይል ተጠቅሞ፣ የተረፈውን ለደቡብ አፍሪካ ይሸጣል። ደቡብ አፍሪካ ደግሞ ከሌሶቶ ወንዞች ነፃ
የመጠጥ ውሀ ጠልፋ ለጆሀንስበርግ ከተማ ውሀ ፍጆታ ታቀርባለች። ይህንን የመሰሉ ስምምነቶች የሜኮንግን ወንዝ
በሚመለከት በታይላንድና በላዎስ መካከል ተፈርመዋል። በመካከለኛው ምስራቅ የያምሩክን ወንዝ በተመለከተ
በሲሪያና በጆርዳን መካከል ውሎች ተፈርመዋል(Aaron Wolf 1999)።
በ1959 ዓ.ም እና በ1966 ዓ.ም ሕንድ የጋንጀስ ወንዝ(Ganges River)የበላይ ተፋሰስ አካባቢ
እንዳይጐዳባትና ደለል ለመቀነስ ስትል፣ የበላይ ተፋሰስ ሀገር በሆነው በኔፓል(Nepal)ውስጥ ዛፍ እንድትተክልና
አካባቢያዊ እንክብካቤን ያጣመሩ የመስኖ ልማትን፣ የውሀ ኃይል ማመንጨትን፣ አሳ ማርባትን፣ መጓጓዣንና የደን
ልማትን ሁሉ የሚያካትቱ የልማት ፕሮጀክቶች በኔፓል ውስጥ እንዲካሄዱ ለመርዳት ከኔፓል ጋር ውል
ተፈራርማለች(እንደላይኛው)።
8.0 የተወሰኑ (selected) ያገር አቋራጭ ወንዞች አጠቃቀም ድንጋጌዎች
እያንዳንዱ ሀገር-አቋራጭ ወንዝ ልዩ የሆነ መልክና ጸባይ አለው። በጂኦሎጂው፣ በመልካ ምድሩ፣ ባየር ንብረቱ፣ በነዋሪው
ሕዝብ ማህበራዊ ኑሮ፣ በባህሉ፣ በኢኮኖሚውና በፖለቲካው ሁሉ የእያንዳንዱ ሀገር አቋራጭ ወንዝ ከሌላው የተለየ
ነው(peculiar)። ይህ ሲባል ግን ሀገር-አቋራጭ ወንዞች የሚመሳሰሉበት የጋራ ጸባይ(common characteristics)
የላቸውም ማለት አይደለም። ከልዩ ጸባያቸው ተነስቶ በዓለም ደረጃ ለሁሉም ወይም ላብዛኛዎቹ የሚሆን ያጠቃቀም ሕግጋት
ለማውጣት ያስቸግራል። በዚህም ምክንያት ሳይሆን አይቀርም በዓለም ደረጃ (ለሁሉም የሚበጅ) ተቀባይነት ያለው የውሀ ድርሻ
መስፈርት/ደምብ የሌለው።እያንዳንዱ ወንዝ የግል ጸባይና መልክ ቢኖረውም ከሌሎች ወንዞች ጋር የሚጋራው የጋራ ገጽታዎች ይኖሩታል። ያጠቃቀም
ድንጋጌዎችና ሕግጋት ማውጣት እሚቻለውም፣ 1ኛ)ከወንዞቹ የጋራ ጸባይ በመነሳት 2ኛ)ቀደም ሲል በዓለም ዙሪያ በየተፋሰሶቹ
ከተደረጉ ድርድሮችና ስምምነቶች ልምድ በመነሳት ነው።
ከነዚህ ሁለት ገጽታዎች በመነሳት በ1966 ዓ.ም ሄልስንኪ(Helsinki Rules of 1966) ላይ የተሰበሰበው የዓለም ዓቀፍ
የሕግ ማህበር (International Law Association/ILA) የተፋሰስ ሀገሮች ተመጣጣኝ(reasonable and
equitable sharing)በሆነ መልኩ የወንዞቻቸውን ውሀ እንዲከፋፈሉ ድንጋጌዎች አወጣ። “ተመጣጣኝ”(equitable)
የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ለመግለጽ (to define) በሕጉ አንቀጽ አምስት(Article V) ላይ የሚከተሉት 11(አስራ አንድ)
ነገሮች(factors)ግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው አሳወቀ።
1) የተፋሰሱ መልካ ምድር (geography of the basin)
2) የተፋሰሱ ውሀ ክምችት (hydrology of the basin)
3) የተፋሰሱ ያየር ንብረት (climate of the basin)
4) የቀድሞውና ያሁኑ ውሀ አጠቀቀም ታሪክ (past and existing water utilization)
5) የተፋሰሱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የውሀ ፍላጐት (economic and social needs of the riparians)
6) የሕዝብ ብዛት (population)
7) ሌላ የውሀ ምንጭ (availability of other sources)
8) አማራጭ የውሀ አጠቃቀም እሚያስከትለው ወጭ(comparative costs of alternative water sources)
9) ብክነትን ማስወገድ (avoidance of waste)
10) ግጭትን ለማስወገድ ካሳ የመክፈል አማራጭ(practicability of compensation as a means of
adjusting conflicts)
11) በሌላው የተፋሰስ ሀገር ላይ ጉዳት ሳያስከትሉ ውሀ የመጠቀም ጉዳይ(the degree to which a state’s
needs may be satisfied without causing substantial injury/harm to a co-basin state).
ይህንን ጽሑፍ ያንዛዛዋል እንጂ እነዚህን ነጥቦች አንድ ባንድ እያብራሩ ለሀገራችን ካላቸው አንድምታ(implications)ጋር
ቢተነትኗቸው የበለጠ ግንዛቤ ያስጨብጡ ነበር። ያም ሆነ ይህ እነዚህ የሄልስንኪ(1966)ድንጋጌዎች ምናልባት ተቀባይነት
ቢያገኙ በሚል በ1970 ዓ.ም ለተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ሲቀርቡ “ተፋሰስ/drainage” በሚለው ቃል(የትርጉም
አሻሚነት)የተነሳ ሙሉ ድጋፍ13 ባለማግኘታቸው እንዲጠኑ፣ የተበበሩት መንግሥታት የሕግ ክንፍ/የሕግ አማካሪ ለሆነው
ለዓለም አቀፍ የሕግ ኮሚሽን(International Law Commission/ILC)ተላለፉ። በ1966 ዓ.ም የተረቀቁትን
የሄልስንኪ ድንጋጌዎች ለሰላሳ ዓመታት ያህል ሲበርዝና ሲሰልስ ቆይቶ በ1997 ዓ.ም በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት
ጠቅላላ ጉባኤ(UN General Assembly) “መጓጓዣን እማይጨምሩ የዓለም አቀፍ ወንዞች አጠቃቀም ሕግ”(Law of
the Non-Navigational Uses of International Watercourses) በሚል አስጸደቀ።
በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የጸደቀው የ1997ቱ ሕግ ከ1966ቱ ከሄልስንኪ ድንጋጌ ምን ያህል ልዩነት እንዳለው
በጥልቀት እሚያውቁት የዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች ናቸው። በሕግ መሀይምነቴ ላይ-ላዩን(on the surface)ልረዳው
እንደቻልኩትና ባገኘኋት ቅንጭብ መረጃ ስመለከተው ግን ከሄልስንኪ ድንጋጌዎች የሚለይ ብዙ ፍሬ ነገር(substantial
difference) ያለው አይመስልም።
የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ(በ1997 ዓ.ም)ያጸደቀው ያገር አቋራጭ ወንዞች አጠቃቀም ሕግ የሚከተሉት
አንቀጾች ይገኙበታል።
ሀገሮች ተመጣጣኝ(equitable/reasonable)በሆነ መልኩ የወንዞቻቸውን ውሀ እንዲጠቀሙ
ያ(ዝ)ዛል(Article 5)። “ተመጣጣኝ”(equitable/reasonable) የሚለው ቃል ግልጽነት የሌለው አሻሚ
እንደሆነ ቀርቷል።
13 የሄልስንኪን (የ1966 ዓ.ም) የወንዝ ተፋሰሶች ውሀ አጠቃቀም ረቂቅ ድንጋጌዎች በ1970 ዓ.ም በተካሄደው የተባበሩት
መንግሥታት ስብሰባ ላይ ከተቃወሙት ሀገሮች መካከል ብራዚል፣ ቤልጅየም፣ ቻይና እና ፍራንስ ይገኙበታል። ድጋፍ ከሰጡት ሀገሮች
መካከል ደግሞ አርጀንቲና፣ ፊንላንድና ኔዘርላንድስ ይገኙበታል። (Biswas 1993 cited by Aaron Wolf 1999, p4). ሀገሮች እንዲነጋገሩና እንዲተባበሩ(communicate and cooperate)ያዝዛል። መረጃ እንዲለዋወጡ፣
አካባቢያዊ ጉዳትና አደጋ፣ እንዲሁም ያጠቃቀም ቀውስ የሚያስከትሉ ውጥኖች ቢኖሩ አስቀድመው እንዲያሳውቁ
ያዛል።
ሀገሮች በየክልላቸው ውሀ ሳይባክን ባግባቡ(optimal use)ዘለቄታ ባለው ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዲያውሉና
ለወንዙም እንክብካቤ እንዲያደርጉለት(Article 5) ይደነግጋል።
በሀገራቸው ድምበር ውስጥ የወንዞችን ውሀ በሚጠቀሙበት ጊዜ በሌሎች የወንዞቹ ተጠቃሚዎች ላይ ጉልህ
ጉዳት(significant harm or appreciable harm)እንዳይደርስ አስፈላጊውን ቅደመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣
ጉልህ ጉዳት ከደረሰ፣ ጉዳቱም የደረሰው የተፋሰሱ ሀገሮች ባልተስማሙበት የስራ እንቅስቃሴ የተነሳ ከሆነ፣ ጉዳት
ከደረሰበት ሀገር ጋር በመመካከር ጉዳቱ የሚወገድበትንና የሚቃለልበትን ዘዴ ይፈጥራሉ፣ አስፈላጊ ሁኖ ከተገኘም
ጉዳት ለደረሰበት ሀገር ካሳ ስለሚከፈልበት ሁኔታ ይነጋገራሉ ይላል(Article 7)።
በሌሎች የውሀ አጠቃቀምች ላይ ቅደም ተከተል ያላወጣ ቢሆንም፣ ግጭቶች ቢፈጠሩ ከሁሉም በፊት ቅድሚያ
የሚሰጠው ለመጠጥ ውሀ(for vital human needs) መሆኑን ይገልጻል(Article 10)።
ከጥንት ጀምሮ ውሀውን የመጠቀም ባህል እንዳለው ካልታወቀ በስተቀርና በተፋሰሱ ሀገሮች ስምምነት ላይ
ተመስርቶ የሚካሄድ የውሀ አጠቃቀም ካልሆነ በስተቀር፣ የቀዳሚ ተጠቃሚነት(inherent priority or
historic-use) መብት ሊኖረው አይችልም ይላል(Article 10)።
የወጡትን ውሀ ነክ ሕግጋት እሚያስፈጽመውና(enforcement)እሚተረጉመው(interpreter)በግልጽ አይታወቅም። የዓለም
አቀፍ ፍትሕ ፍርድ ቤት(International Court of Justice/ICJ) እሚያየው የተወሰኑ ነጥቦችን ነው(Aaron Wolf,
1999, 5)። በሁለት ሀገሮች መካከል ሙግት/ክርክር ቢነሳ ጉዳዩን የዓለም አቀፍ ፍትሕ ፍርድ ቤት እሚያየው፣ ሁለቱ
ተከራካሪዎች ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤቱ እንዲቀርብ ሲስማሙ ብቻ ነው(እንደላይኛው)። ሁለቱ ተከራካሪዎች፣ በስምምነት
ወደ ዓለም አቀፍ ፍትሕ ፍርድ ቤት ቢቀርቡና፣ ባንዱ ላይ ቢበየንበት፣ ብይኑን እሚያስፈጽመው(enforcer)ማን ነው?
ባፈጻጸሙ ላይ ከተከራካሪዎቹ አንዱ እምቢተኛ ቢሆን ችግሩ ተመልሶ ወደ ወንዙ ተጠቃሚ ሀገሮች የሚሄድ ነው የሚሆነው።
ያፈጻጸም ችግር በመኖሩም የተነሳ ሕጉና ድንጋጌው ኃይልና ጉልበት በተሰማቸው አንዳንድ የተፋሰስ ሀገሮች ሲጣስ ታይቷል።
በአፍሪካ ውስጥም አንዳንድ አውራ(hegemonic countries)ሀገሮች ከሕግጋቱ ለማፈንገጥ አይቃጡም ብሎ በእርግጠኝነት
ለመናገር ያስቸግራል። ይሁን እንጂ የሉዐላዊ መንግሥትነት እውቅና ያላቸው 54 የአፍሪካ ሀገሮች በሙሉ የተባበሩት
መንግሥታት አባል ናቸውና፣ ሕጉንም(በ1997 ዓ.ም)አብረው አጽድቀዋልና፣ የውሳኔያቸው ተገዢ መሆንን እንደሚምርጡ
ተስፋ ይደረጋል።
ያም ሆነ ይህ(በሄልስንኪ ድንጋጌም ይሁን በ1997ቱ የዓለም አቀፍ የሕግ ኮሚሽን ሕግ በግልጽ ጐልተው የወጡት፣
ተመጣጣኝ(equitable allocation, reasonable use) የሆነ ያጠቃቀም ዘዴ እና ጉልህ ጉዳት
አለማድረስ(significant harm)የተሰኙት ናቸው። እነዚህ የሞራል ጥያቄዎች ስለሆኑ በግልጥ የሚቃወማቸው ሀገር
አይኖርም። በመሠረቱ ሁሉም ይስማማባቸዋል። በተግባር አተረጓጐማቸው ላይ ግን ብዙ ውስብስብ ሁኔታዎች ይታዩባቸዋል።
ለምሳሌ ያህል በ1970 ዓ.ም የ1966ቱን የሄልስንኪ “ተመጣጣኝ”equitable allocation የውሀ ክፍፍል ድንጋጌዎች
በግልጽ ተቀብሎ ሊጠቀምበት የወሰነው የቻይናው ሜኮንግ ወንዝ(Mekong R.)ኮሚቴ ነበር። በ1975 ዓ.ም በተደረገው
የሜኮንግ ውል (the 1975 Mekong Accord) ላይ ግን ቻይናዎች “በወንዝ ባለመብትነት እኩል መሆን ማለት፣ የወንዙን
ውሀ እኩል መካፈል ማለት አይደለም--------” ነው ያሉት። የቻይናዎቹን አባባል አሮን ወልፍ(Aaron Wolf, 1999)
እንደሚከተለው ይገልጸዋል።
“---- the 1975 Mekong Accord defines “equality of rights” not as equal shares of water, but as equal rights
to use water on the basis of each riparian’s economic and SOCIAL needs.” (Aaron Wolf 1999, p16).
ግብጽም በመሠረቱ አፍ አውጥታ ይህንን “ተመጣጣኝ”/equitable የውሀ ክፍፍል ስትቃወም አልተደመጠችም። ከሱዳን ጋር
በ1959 ዓ.ም የተስማማችበትን የውሀ መጠን የሚያነሳባት ግን አትወድም። “ተመጣጣኝ” የተሰኘው ቃል በግብጽ እንዴት
ዓይነት ትርጉም እንደሚሰጠው አይታወቅም። ያም ሆነ ይህ፣ “ተመጣጣኝ”(equitable) የሚለውን ቃል የተለያዩ ሀገሮች ለራሳቸው ጥቅም በሚያስገኝ መንገድ ትርጉም ሊሰጡት ይችላሉ። የሄልስንኪው ድንጋጌ የደረደራቸው 11 መስፈርቶችም ቃሉን
በተለያየ መንገድ ለመተርጐም በር የሚከፍቱ ይመስላሉ።
9.0 ትንታኔ/Analysis
የሀገር አቋራጭ ወንዞችን በጋራ ለመጠቀም እስካሁን ድረስ በዓለም ዙሪያ ሲደረጉ የቆዩትን ድርድሮች፣ ውሎችና ስምምነቶች
አጠቃላይ ገጽታቸውን ባጭር ባጭሩ ለማሳየት ተሞክሯል። በአህጉራችን ውስጥም ከቅኝ ግዛት ዘመን ጀምሮ የሀገር አቋራጭ
ወንዞች ውሀ ክፍፍሎሽ ምን መልክ እንደነበረውና በምን መስፈርት ክፍፍሎሹ ይከናወን እንደነበር ተመልክተናል።
ከነዚህ የውሀ ክፍፍሎሽ ስምምነቶች ጋር ከተቆራኙ፣ የውሀ መብትን(water rights)፣ ቀደምት ተጠቃሚነትን(prior use)፣
ጥንታዊ/ታሪካዊ ተጠቃሚነትን(historic rights)፣ ጉልህ ጉዳት ማድረስን(appreciable harm or significant
harm)፣ ተመጣጣኝ ተጠቃሚነትን(equitable use or reasonable use)፣ ከመሳሰሉ ጽንሰ ሀሳቦች ጋር ተዋውቀናል።
የ1966ቱ የሄልስንኪ የሕግ ባለሙያዎች ጉባኤ ካወጣቸው ድንጋጌዎች አንዳንዶቹን፣ የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ
የሕግ ኮሚሽን(በ1997 ዓ.ም) ካስጸደቀው ሕግ ውስጥም ለዚህ ጽሑፍ ይጠቅማሉ ተብሎ የታመነባቸውን አንድ ሁለት ያህል
አንቀጾችን ተመልክተናል። እያንዳንዱ ወንዝ(በተፈጥሮ መልኩ፣ በሕዝቡ ባህልና አሰፋፈር፣ በባህሉ፣ በኢኮኖሚውና
በፖለቲካው) የግል መልክና ጸባይ ስላለው ያገር አቋራጭ ወንዞች ስምምነትና የውሀ ክፍፍል ከተፋሰስ ተፋሰስ ሊለያይ ይችላል።
የተፋሰሱ ሀገሮች ተስማምተው ውልና ስምምነት እስከተፈራረሙ ድረስ፣ “የሄልስንኪን ሕግጋት ወይም የተባበሩት መንግሥታትን
ሕግ አልተከተላችሁምና ስምምነታችሁ አይጸድቅም” የሚላቸው የለም። የሄልስንኪም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ሕግጋትና
ድንጋጌዎች ባገር አቋራጭ ወንዞች ላይ ለመደራደርና ለመስማማት አቅጣጫ የሚሰጡ፣ ለሽምግልናና ለዳኝነት እንደ መነሻ ሁነው
እሚያገለግሉ እንጂ፣ የተፋሰስ ሀገሮች በሌላ አማራጭ እንዳይስማሙ የሚከለክሉ አይደሉም።
በዚህ ጽሁፍ የተገነዘብነው፣ በሀገር አቋራጭ ወንዝ አጠቃቀምና ክፍፍሎሽ ድርድር ሲደረግ፣ መጀመሪያ የሚነሳው የመብት
ጥያቄ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ስምምነት ላይ የሚደረሰው ግን በተደራዳሪዎቹ የውሀ ፍላጐት(water need)ላይ የተመሠረተ
መሆኑን ነው። የውሀ ፍላጐት መኖር አለመኖር የሚታወቅበት፣ የፍላጐቱ ጥልቀትና ክብደት እሚለካበት መለኪያ፣
1ኛ) ያሁኑ አጠቃቀም(existing use)፡ አሁን በጥቅም ላይ የሚውለው የወንዝ ውሀ፣ አሁን ያለውን የውሀ
ፍላጐት(existing water need) ያሳያል። ያሁኑ አጠቃቀም ያሁኑን የውሀ ፍላጐት ብቻ ሳይሆን ያለፈውንም ልማዳዊ ወይም
የቆየ አጠቃቀም ይጠቁማል። በብዙ ያገር አቋራጭ ወንዞች ውሎችና ስምምነቶች፣ ያለፈውና አሁን ያለው የውሀ አጠቃቀም
ሳይነካ እንደተከበረ ሲቀመጥ ይታያል። አንድ ሀገር ወደፊት የሕዝቤ ቁጥር ይጨምራል፣ በኢንዱስትሪም አድጋለሁና ተጨማሪ
የውሀ ድርሻ ይገባኛል የሚል ጥያቄ ቢያነሳ፣ ካለፉት ውሎችና ስምምነቶች እንደታየው ከሆነ፣ የባለጋራውን ሀገር (ያለፈውንና
ያሁኑን) ውሀ አጠቃቀም እሚያናጋ ስለሆነ ከ1966ቱ የሄልስንኪ ድንጋጌም ሆነ ከ1997ቱ የዓለም አቀፉ የሕግ ኮሚሽን
ደምብ ውጭ ይሆናል። በሌላ አነጋገር ያሁኑና ያለፈው የውሀ ፍላጐት፣ ወደፊት ይከሰታል ተብሎ ከሚተነበየው የውሀ ፍላጐት
የበለጠ ቅድሚያ ሲሰጠው ታይቷል(existing use prevails over future use)።
ያለፈው ወይም የተለመደው ያገር አቋራጭ ውሀ አጠቃቀም፣ ጥንታዊ ወይም ታሪካዊ(historic rights or acquired
rights)የውሀ ባለመብትነትን ያጠቃልላል። ከጥንት ጀምረው የመስኖ ውሀ እየተጠቀሙ የግብርና ምርታቸውን ሲያዳብሩ
የኖሩ፣ እንደ ግብጽ ያሉ የበታች ተፋሰስ ሀገሮች፣ ‘አዲስ ደራሽ’ በሆነ በበላይ ተፋሰስ ሀገር የውሀ ፍላጐት የተነሳ መዛባት
እንደማይገባውና በዚያው እንዲቀጥል እንደሚደረግ ባብዛኞቹ የወንዝ ስምምነቶች(ታሪክ) አይተናል።
በዚህ(existing use) መለኪያ ውስጥ ኢትዮጵያን አስገብተን ስንገመግም፣ ሀገር አቋራጭ ወንዞቿን በተመለከተ አሁን
የሚታየው የውሀ አጠቃቀም(existing use)በጣም አንስተኛ ነው። በተለይ ካሁኑ የግብጽና የሱዳን(ሀገር-አቋራጭ ወንዞች)
አጠቃቀም ጋር ሲወዳደር የኢትዮጵያ ከቁጥር የሚገባ አይደለም። ይህም እስከዛሬ በዓለም ዙሪያ በተደረጉ የወንዞች አጠቃቀም
ውሎችና ስምምነቶች እይታ ሲታይ፣ የኢትዮጵያ ውሀ ፍላጐት(water need) አንስተኛ መሆኑን እሚጠቁም ነው። የወንዞችን
ልማት በተመለከተ (ከአዋሽ ወንዝ በስተቀር) ያለፈው የኢትዮጵያ ታሪክ(historical use)ከነጭራሹ የወንዝ ውሀ ድርሻ
ለመጠየቅ (ለመደራደር) እሚያስችል አይደለም። አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ወንዞች ጥቅም ላይ ሳይውሉ በከንቱ ወደ ሱማሊያ፣
ወደ ኬንያ(ቱርካና ሀይቅ)፣ በሱዳን በኩል ወደ ግብጽ ሲፈስሱ የኖሩ ናቸው። ስለዚህ ያለፈ የወንዝ ውሀ የመጠቀም ልማድና
ታሪክም የለንም ማለት ይቻላል። ያገር አቋራጭ ወንዞቻችን የመጠቀም የቆየ ታሪክ አለመኖር፣ የውሀ ድርድር በሚደረግበት ጊዜ
የወንዝ ውሀ ፍላጐት (water need) ኑሮን እንደማያውቅ እሚያመለክት ይሆናል።
2ኛ) በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት ስፋት(irrigable land)፡ ቀደም ሲል በጽሑፉ ውስጥ ለማሳየት እንደተሞከረው፣
በመካከለኛው ምስራቅ የውሀን ፍላጐት(water need) ለመለካት የተሞከረው በመስኖ ሊለማ የሚችለውን መሬት ስፋት
ግምት ውስጥ በማስገባት ነበር። አሜሪካና ሜክሲኮ የኮሎራዶን ወንዝና የሪ-ኦግራንድን ወንዝ ውሀ የተከፋፈሉት፣ ሜክሲኮ ውስጥ የነበረውን የመስኖ ልማት እንደ መስፈርት በመጠቀም ነው። ይህም ማለት ሰፊ የመስኖ መሬት ያለው ብዙ ውሀ
ይፈልጋል፣ ብዙ ውሀ ይመደብለታል ማለት ነው። ትንሽ የመስኖ መሬት ያለው ደግሞ የውሀ ፍላጐቱ ትንሽ ስለሆነ፣
እሚመደብለት የውሀ መጠን ትንሽ ይሆናል ማለት ነው።
ይህንን(የመስኖ መሬት) በመስፈርትነት በመጠቀም የኢትዮጵያን ሁኔታ ስንገመግም የተሻለ የውሀ መጠን ለማግኘት አመቺ
መደራደሪያ ሁኖ አናገኘውም። የኢትዮጵያ ማእከላዊ ፕላን ብሔራዊ ኮሚቴና የሕንዶች የውሀና የኃይል ምህንድስና
ድርጅት(1990)፣ በመስኖ ሊለማ የሚችለው የኢትዮጵያ መሬት ስፋት 3.5 ሚሊዮን ሄክታር ይሆናል ይላል። የአስዋን
ግድብ ከመሰራቱ በፊት ግብጽ በመስኖ ያለማቺው መሬት 2.8 ሚሊዮን ሄክታር ነበር(FAO, 1995)። በ1970ዎቹ
የአስዋን ግድብ እንደተጠናቀቀ ግብጽ በመስኖ ያለማቺው የመስኖ መሬት ስፋት 4.1 ሚሊዮን ሄክታር ነበር(እንደላይኛው)።
በ1990 ዓ.ም ደግሞ እህል የተዘራበት የመስኖ መሬት ስፋት 6.5 ሚሊዮን ሄክታር ነበር(እንደላይኛው)። ታዲያ ኢትዮጵያ
በመስኖ ሊለማ የሚችለውን መሬቷን(3.5 ሚሊዮን ሄክታር) ሙሉ በሙሉ ብታለማ እንኳን እሚያስፈልጋት የመስኖ ውሀ
በ1970ዎቹ ግብጽ ለመስኖ ከተጠቀመችበት የመስኖ ውሀ አይደርስም። እነዚህ አሀዞች ሲታዩ ያሁኑም ሆነ የወደፊቱ
የኢትዮጵያ የመስኖ ውሀ ፍላጐት (ከግብጽ ጋር ሲነጻጸር) በጣም አንስተኛ መሆኑን እንገነዘባለን።
የኢትዮጵያ ማእከላዊ ፕላን ብሔራዊ ኮሚቴና የሕንዶች የውሀና የኃይል ምህንድስና ድርጅት(1990)እንደጠቆመው፣
በመስኖ ሊለማ ይችላል ከተባለው ከ3.5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ፣ በመስኖ የለማው መሬት 200.000 (ሁለት መቶ
ሺህ) ሄክታር ብቻ ነበር። በመስኖ ከለማው(200,000 ሄክታር) መሬት 74% በመቶ የሚሆነው በአዋሽ ሸለቆ ውስጥ
የሚገኝ ነው። በሀገር አቋራጭ ወንዞቻችን ተፋሰሶች ውስጥ(በዋቢ ሸበሌ፣ በገናሌና በዳዋ፣ በኦሞ፣ በባሮ-አኮቦ፣ በዐባይና
በተከዜ) በመስኖ የለማው መሬት በድምሩ 52,000 (አምሳ ሁለት ሺህ) ሄክታር ወይም ቀሪው 26% ብቻ ነበር። ይህ
አንስተኛ የመስኖ ልማት፣ የመስኖ ውሀ ፍላጐታችን(ባሁኑ ጊዜ) ዝቅተኛ መሆኑን ያመለክታል።
የሀገራችን የመስኖ ልማት ከበታች ተፋሰስ ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር የሚሰጠን ስዕል የተሻለ የውሀ ድርሻ ይገባናል ብሎ ለመደራደር
እሚያሳፍር ነው(የሚከተለውን ሰንጠረዥ ይመልከቱ)።
ሰንጠረዥ 1፡ በመስኖ የለማ መሬት ስፋት በተወሰኑ ሀገሮች ውስጥ
ሀገር (ዓመተ ምህረት) የመስኖ መሬት ስፋት
(በኪሎ ሜትር ካሬ)
ግብጽ (2003) 34,220.00
ኢትዮጵያ(2003) 2,896.00
ኤርትራ (2003) 215.00
ኬንያ (2003) 1,032.00
ሩዋንዳ (2007) 96.25
ሱዳን (2010) 18,900.00
ዩጋንዳ (2010) 1,442.00
Source: Central Intellegence Agency (CIA): The World Factbook.
ይህ ሰንጠረዥ እሚያሳየን ሱዳንና ግብጽ ከሌሎቹ ሀገሮች ጋር ሲነጻጸሩ እጅግ በጣም ሰፊ የመስኖ ልማት ያላቸው መሆኑን ነው።
ይህ በመስኖ የለማ ሰፊ መሬት፣ ግብጽና ሱዳን ብዙ ውሀ የሚጠቀሙ መሆናቸውን(existing use) እና ብዙ ውሀ
እሚፈልጉ(water need) መሆናቸውን ያሳያል። እስካሁን እንደተደረጉት የውሀ ድርድሮች ከሆነ(የመስኖ ልማቱ ሲካሄድ
የቆየ፣ አሁንም በመካሄድ ላይ ያለ ስለሆነ) ይህንን የመስኖ ውሀ ፍጆታ እሚያስቀንስ ውል ለመዋዋል በጣም ከባድ/አዳጋች
ነው። የለመዱትን የውሀ መጠን በሚያስቀንስ ድርድር ውስጥ ለመግባት ግብጽና ሱዳን ፈቃደኛ አይሆኑም። ቀደም ብለው የነበሩ
አጠቃቀሞች(prior use) እንዲከበሩ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ(1997) የጸደቀው ድንጋጌም(በቀደምት
ተጠቃሚነታቸው/prior use የተነሳ ግብጽንና ሱዳንን ይደግፋቸዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ እስካሁን የመስኖ ስራ ሳያስፋፉ ቆይተው አሁን እንጀምራለን የሚሉ፣ የተለመደውን (የቆየውን) የበታች
ተፋሰስ ሀገሮች የውሀ ፍጆታ ስለሚያቃውሱ፣ ብሎም በበታች ሀገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት(appreciable harm or significant
harm)ሊያስከትሉ ስለሚችሉ፣ ከበታች ተፋሰስ ሀገሮች ጋር ለመስማማት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። ተደራድሮ መስማማት
የሚቻለው ምናልባት በተራፊው (እስካሁን ድረስ የበታች ተፋሰስ ሀገሮች ጥቅም ላይ ባላዋሉት) ውሀ ላይ ብቻ ነው። እሱም ቢሆን
ተራፊ ውሀ ከተገኘ ነው።“እንደራደር” እሚያሰኝ ተራፊ ውሀ እንዳይኖር፣ ግብጽ ተጨማሪ የመስኖ ስራ በማስፋፋት(increasing existing use)
የውሀ ፍላጐቷን(expanding its water needs) ለማሳደግ በመጣደፍ ላይ ነች።
የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የግብርና ድርጅት(UN FAO, 1995) እንደዘገበው ግብጽ በ1990 ዓ.ም ሦስት ትልልቅ
የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጀምራለች። እነሱም፣
ሀ) የቶሽካ ፕሮጀክት(Toshka or the New Valley Irrigation Project)፡ ይህ ፕሮጀክት ከአስዋን ግድብ
ወደ ምእራብ 70(ሰባ) ኪሎሜትር ያህል እርቆ 234,000 (ሁለት መቶ ሰላሳ አራት ሺህ) ሄክታር መሬት
በመስኖ እሚያለማ ፕሮጀክት ነው።
ለ) የዐባይ ዴልታ ፕሮጀክት(Nile Delta Irrigation Project)፡ ይህ ፕሮጀክት 500,000(አምስት መቶ
ሺህ) ፌዳን14 መሬት በመስኖ እሚለማበት ነው። ከዚህ ከ500,000(አምስት መቶ ሺህ) ፌዳን መሬት ውስጥ
170,000(አንድ መቶ ሰባ ሺህ) ፌዳን መሬት ድሮ የነበረ፣ ግን የመስኖው ቦይና ማከፋፈያው ፈራርሶ ስለነበር
ተጠጋግኖ እንደገና ስራ እሚጀምር ነው።
ሐ) የሰሜን ሲናይ ፕሮጀክት(Northern Sinai Irrigation Project)፡ የሰሜን ሲናይ ፕሮጀክት፣ ምእራባዊ
ሲናይና ምስራቃዊ ሲናይ ተብሎ በሁለት የተከፈለ ነው። ምእራባዊው የሲናይ ፕሮጀክት ከሱዊዝ ካናል በስተምእራብ
የሚገኝና 200,000(ሁለት መቶ ሺህ) ፌዳን መሬት በመስኖ የሚለማበት ፕሮጀክት ነው። ምስራቃዊው ሲናይ
ደግሞ ከስዊዝ ካናል በስተምስራቅ በኩል የሚገኝ፣ የወንዙ ውሀ በቱቦ ስዊዝ ካናልን እንዲሻገር ከተደረገ በኋላ በሲናይ
በረሃ ውስጥ 400,000(አራት መቶ ሺህ) ፌዳን መሬት በመስኖ የሚለማበት ፕሮጀክት ነው።
ይህ ሁሉ አዲስ የመስኖ ፕሮጀክት ተጨማሪ ውሀ ይጠይቃል። የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የግብርና ድርጅት(FAO,
1995) እንደሚለው ከሆነ፣ ግብጽ ፍሳሹንና ቆሻሻውን ውሀ እንደገና እያጣራች ካልተጠቀመች በስተቀር፣ የውሀ ፍላጐቷ
በዐባይ ውሀ ብቻ ሊሟላ አይችልም። የ1959ኙ(ከሱዳን ጋር የተካፈለቺው) ውሀ በዝቶባታል በማለት ኢትዮጵያና ሌሎቹ
የበላይ ተፋሰስ ሀገሮች ሲያማርሩ፣ ከነኣካቴው እርሱም አይበቃትም እየተባለ(በ FAO) እየተመሰከረላት ነው። ይህ ሁሉ
እሚያሳየን ግብጽ የውሀ ፍላጐቷ(water need)ከፍተኛ መሆኑን እና ብዙ ውሀ እሚገባት መሆኑን በተጨባጭ
ለማሳየት/ለማሳመን በመጣደፍ ላይ መሆኗን ነው።
የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገሮች ጉልህ ጉዳት(appreciable harm) እንዳይደርስባቸው፣ የበላይ ተፋሰስ ሀገሮች (አዳዲስ የልማት
ፕሮጀክት ሲያወጡ) የበታች ተፋሰስ ሀገሮችን አዎንታ እንዲጠይቁ ተደንግጓል። በኢትዮጵያና በግብጽ እንደሚስተዋለው ከሆነ
ግን፣ የበታች ተፋሰስ ሀገሮች ቀድመው በማልማትና/የውሀ ፍላጐታቸውን በማሳደግ፣ በበላይ ተፋሰስ ሀገሮች “የወደፊት”
15
የውሀ አጠቃቀምና የውሀ ፍላጐት ላይ ጉልህ ጉዳት(significant harm) እያደረሱ ነው። ኢትዮጵያም ግብጽ አዳዲስ
የመስኖ ፕሮጀክቶች በጀመረች ቁጥር ተቃውሞዋን ከማስተጋባት በስተቀር፣ ለውሀ ፍላጐቷ ማረጋገጫ የሚሆን የውሀ ልማት
ፕሮጀክት ስትጀምርና ስታስፋፋ አልታየችም። በዚህ ላይ(ዝናቡ ባብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል አስተማማኝ ባይሆንም)ዝናብ
የሚዘንብላት ሀገር በመሆኗ የወንዙን ውሀ ከልብ እንደማትፈልገው ያስመስላታል።
እስካሁን ከተደረጉት ያገር አቋራጭ ወንዞች ድርድሮችና ስምምነቶች ልምድ ከተነሳን፣ በወንዝ ውሀ ላይ የተመሠረተ ልማት
ማሳየት ለማይችልና ለአብዛኛው እህል (የውሀ ፍላጐት) የሚበቃ መጠነኛ ዝናብ ለሚያገኝ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሀገር፣ ግብጽን
ከመሰለ(በተለያዩ መስፈርቶች ሲታይ) ከፍተኛ የውሀ ፍላጐት ካለው ሀገር ጋር ተደራድሮ፣ ከተለመደው የግብጽ የውሀ ድርሻ
እሚያስቀንስ ስምምነት ላይ የሚደርስ አይመስልም።
3ኛ) በወንዙ ልማት ላይ የፈሰሰ መዋዕለ ንዋይ (investment on river development)፡ በወንዝ ላይ ብዙ መዋዕለ
ንዋይ ማፍሰስንም በሚመለከት በዐባይ ተፋስስ ውስጥ ግብጽን የሚወዳደር የለም። ግብጾች ሰማኒያ በመቶ(80%) የሚሆነውን
የዐባይን ውሀ እሚጠቀሙበት ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ነው(FAO, 1995)። የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ዘመናዊና
ውስብስብ በሆነ የመስኖ ስራ የሚካሄድ ነው። ለዚህ ውስብስብ የመስኖ ስራ ያፈሰሰቺው ሀብትና ንብረት ከተፋሰሱ ሀገሮች ጋር
ሲነፃፀር በጣም ከፍተኛ ነው። ለውስብስቡ የመስኖ ልማት የውሀ አከፋፋይ የሆነውን አስዋን ግድብ ለመስራት ብዙ ወጭ
አውጥተዋል። ስለዚህ በዚህ መስፈርት ለመደራደር ቢሞከርም ከተፋሰሱ ሀገሮች ሁሉ የበላይነቱን የምትይዘው ግብጽ ነች።
በወንዙ ልማት ላይ ብዙ መዋእለ ንዋይ ማፍሰሷ ራሱ የግብጽን ከፍተኛ የውሀ ፍላጐት ያሳያል።
14 አንድ ፌዳን 0.42 ሄክታር ነው።
15
“የወደፊት” ያልኩበት ምክንያት ባሁኑ ጊዜ በሀገር አቋራጭ ወንዞች ተፋሰሶቻችን ውስጥ ከቁጥር የሚገባ የመስኖ ልማት ስለሌለን ነው።
ያሁኑን የመስኖ ውሀ ፍላጐታችን መስፈርት አድርገን የወንዞቻችን ውሀ ለመካፈል እንደራደር ብንል የረባ ውሀ አናገኝም። ምክንያቱም
ባሁኑ ጊዜ ከቁጥር የሚገባ የመስኖ ልማት የለንም። በሌላ አነጋገር የረባ የመስኖ ልማት ከሌለን የረባ የመስኖ ውሀ አንፈልግም ማለት ነው።የዐባይ የበላይ ተፋሰስ ሀገሮች ለወንዙ ልማት (ለመስኖ ስራና ለኃይል ማመንጫ) ብዙ መዋእለ ንዋይ አለማፍሰሳቸው የወንዙን
ውሀ የመጠቀም ፍላጐታቸው አንስተኛ መሆኑን ያመለክታል። ግብጽም የበላይ ተፋሰስ ሀገሮች (በተለይ ኢትዮጵያ) በዐባይ
ወንዝ ልማት ላይ መዋእለ ንዋይ አፍስሰው የውሀ ፍላጐታቸውን እንዲያሳዩ ስለማትፈልግ ባገኘቺው አጋጣሚ ሁሉ እንቅፋትና
መሰናክል ከመፍጠር አትቆጠብም። ግብጽ እንቅፋትና መሰናክል የምትፈጥርበት ምክንያት የበላይ ተፋሰስ ሀገሮች የውሀ ፍላጐት
ከፍ ካለ ለእርሷ የሚደርሳት የውሀ ድርሻ ዝቅ ስለሚልባት (ስለሚቀንስባት) ነው።
4ኛ) የእድገት ደረጃ (level of economic development)፡ ከዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ሁሉ የግብጽ የእድገት ደረጃ ከፍ
ያለ መሆኑ በግልጽ የሚታወቅ ስለሆነ ማስረጃ ማቅረብ አስፈላጊ አይመስለኝም። የመስኖው መሬት መስፋትና ለወንዙ ልማት
የፈሰሰው በርካታ መዋእለ ንዋይ ራሱ ግብጽ የምትገኝበትን ከፍተኛ የእድገት ደረጃ እሚያንጸባርቅ ነው። የግብርናው ክፍለ
ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የኢንዱስትሪውና የሕዝብ አገልግሎቱ ክፍልም ብዙ ውሀ ይፈልጋል፣ ብዙ ውሀ ይፈጃል። ያንድ ሀገር
የኢኮኖሚ ደረጃ ከፍ እያለ በሄደ ቁጥር የውሀ ፍላጐቱም እያደገ ይሄዳል። ስለዚህ በዚህ (የእድገት ደረጃ) መስፈርትም
ከየትኞቹም የተፋሰሱ ሀገሮች ይልቅ ግብጽ ከፍተኛ የውሀ ፍጆታና ፍላጐት ያላት መሆኗ ነው የሚታየው። የሚከተለው ሰንጠረዥ
ይህንን አባባል እሚያጠናክር ነው።
ሰንጠርዥ 2፡ ከ1998 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም የነበረው አማካይ የውሀ ፍጆታ
(water consumption) በሴክተር (በቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር/billion m3)
ሀገር
Country
ለግብርና
Agriculture
ለቤተሰብ
Household
ለኢንዱስትሪ
Industry
ግብጽ 59.0000 5.3000 4.0000
ኢትዮጵያ 5.2040 0.3300 0.0210
ሱዳን 36.0700 0.9900 0.2600
ዩጋንዳ 0.1200 0.1300 0.0500
ኬንያ 1.0100 0.4700 0.1000
ታንዛኒያ 4.6320 0.5300 0.0250
ዲ.ሪ. ኮንጐ 0.1100 0.1900 0.0600
ሩዋንዳ 0.1000 0.0360 0.0120
ቡሩንዲ 0.2200 0.0490 0.0170
ኤርትራ 0.2900 0.0100 0.0000
Source: www. water-for-africa.org (last accessed on September 12. 2014).
በሰንጠረዥ 2 እንደሚታየው፣ የግብጽ አማካይ ውሀ ፍጆታ በቤተሰብ ፍጆታውም፣ በግብርናውም ሆነ በኢንዱስትሪው መስክ
ከየትኞቹም የተፋሰሱ ሀገሮች የበለጠ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ ውሀ ተጠቃሚ ሱዳን ነች። ስለዚህ በሁለቱም የዐባይ ታችኛ
ተፋሰስ ሀገሮች አንጻራዊ የሆነ ከፍተኛ የውሀ ፍጆታና ፍላጐት(need) መኖሩ ቁልጭ ብሎ ይታያል። ብዙ የውሀ ፍጆታ
የሚታየው በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ነው። ለዚህ መሠረታዊ ለሆነ ክፍለ ኢኮኖሚ ብዙ ውሀ ሲጠቀሙ መታየታቸው፣ ብዙ
ውሀ እንደሚያስፈልጋቸው ማስረጃና ማሳመኛ ይሆናቸዋል። ስለዚህ በብዙ መስፈርቶች ሲገመገም የውሀ ፍላጐቱን በተጨባጭ
ለማሳየት ላልቻለ (እንደ ኢትዮጵያ ላለ) የበላይ ተፋሰስ ሀገር የተሻለ የውሀ ድርሻ ለማግኘት ድርድር ላይ ቢቀርብ ሽማግሌንም
ሆነ ዳኛን ለማሳመን ከባድ ይሆንበታል።
5ኛ) የሕዝብ ብዛት(population size)፡ በወንዝ ውሀ ድርድሮችና ክፍፍሎሽ ታሪክ ውስጥ፣ ውሀ ፈላጊነትን ለማሳየት
ሲወሰዱ ከቆዩት መስፈርቶች አንዱ የሕዝብ ብዛት ነው። መሠረታዊ ሀሳቡ ብዙ ሕዝብ ያለው ሀገር ብዙ ውሀ
ይፈጃል(uses)፣ ስለዚህ ለተለያዩ ጉዳዮች(ለግብርና ስራው ጭምር)ብዙ ውሀ ያስፈልገዋል(needs) የሚል ነው። የሕዝብ
ብዛትን በተመለከተ(በ20013 ዓ.ም በተደረገው ስሌት መሠረት) ከዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ሁሉ ኢትዮጵያ አንደኛ
ናት(ሰንጠረዥ 3ን ይመልከቱ)። ግብጽ ሁለተኛ ደረጃ ይዛለች። ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጐ ደግሞ ሦስተኛ ናት።ሰንጠርዥ 3፡ የሕዝብ ብዛትና እያንዳንዱ ሰው ባመት የቀዳው አማካይ የውሀ መጠን (per capita water
withdrawal16 in m3
/year)
ሀገር የሕዝብ ብዛት ግምት
(በ2013 ዓ.ም)*
ግለሰብ በአማካይ የሚቀዳው ውሀ መጠን (በኪዩቢክ
ሜትር/በዓመት)**
ግብጽ 82,056,378 937.00 በ2002 ዓ.ም
ኢትዮጵያ 94,100,756 80.48 በ2002 ዓ.ም
ሱዳን 37,964,306 602.00 በ2002 ዓ.ም
ዩጋንዳ 36,824,000 12.66 በ2002 ዓ.ም
ኬንያ 44,351,000 72.44 በ2007 ዓ.ም
ታንዛኒያ 49,253,126 --------- -----------
ዲሞ.ሪ. ኮንጐ 67,513,677 11.55 በ2002 ዓ.ም
ሩዋንዳ 11,776,522 17.57 በ2002 ዓ.ም
ቡሩንዲ 10,162,532 42.56 በ2002 ዓ.ም
ኤርትራ 6,333,135 21.70 በ2007 ዓ.ም
Sources: *countryeconomy.com (last accessed on September 12, 2014)
**chartsbin.com (last accessed on September 12, 2014).
በሰንጠረዥ 3 እንደሚታየው የነፍስ ወከፍ ውሀ አቀዳዳቸው ግን ይህን ቅደም ተከተል የጠበቀ አይደለም። በ2002 ዓ.ም
ከየትኛውም የዐባይ ተፋሰስ ግለሰብ ዜጐች የበለጠ የሱዳንና የግብጽ ግለሰብ ዜጐች ብዙ ውሀ ቀድተዋል። አንድ ግብጻዊ
የቀዳውን አማካይ የውሀ መጠን ስናይ በዚያው ዓመተ ምህረት አንድ ኢትዮጵያዊ የቀዳውን አማካይ የውሀ መጠን አስራ ሁለት
እጥፍ ያህል ይሆናል። ይህ እሚያሳየን ካንድ ኢትዮጵያዊ ይልቅ አንድ ግብጻዊ ብዙ ውሀ እሚፈጅና(uses)
እሚፈልግ(needs) መሆኑን ነው።
በ2002 ዓ.ም የታየው የግለሰብ ውሀ አቀዳድ በያመቱ እንደሚደጋገም ብናስብና፣ እያንዳንዱ ግለሰብ የቀዳውን ውሀ
በ2013 ዓ.ም በተገመተው ሕዝብ ብዛት ብናባዛው፣ እያንዳንዱ ሀገር ባጠቃላይ ሊቀዳ የሚችለውን የውሀ መጠን
በግርድፉ(roughly)ያሳየናል። ታዲያ በ2002 ዓ.ም ግለሰቦች የቀዱትን ውሀ በ2013 ዓ.ም በተገመተው ጠቅላላ የየሀገሩ
ሕዝብ አባዝተን ስናየው (አሁንም) ግብጾች ባጠቃላይ የሚቀዱት ውሀ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚቀዳው፣ ሌሎቹም የተፋሰሱ
ሀገሮች ከሚቀዱት ውሀ በጣም ይበልጣል።
ይህንን ሁሉ መረጃ በማየት (በቅን አስተሳሰባችን) የዐባይ ታችኛ ተፋሰስ ሀገሮች ብዙ ውሀ እየተጠቀሙ ነውና፣ የበላይ ተፋሰስ
ሀገሮች ካሁኑ የተሻለ የውሀ ድርሻ ሊያገኙ ይገባቸዋል የሚል ፍርድ እንሰጥ ይሆናል። እስካሁን በታሪክ የታዩ በርካታ የወንዝ
ስምምነቶች እሚያሳዩት ግን በጥቅም ላይ ያለ የውሀ(prior use, existing use) ድርሻ አለመነካቱን ነው። ብዙ ውሀ
መጠቀም ከፍተኛ የውሀ ፍላጐት መኖሩን(higher needs)፣ ትንሽ ውሀ መጠቀም ደግሞ(በተለያየ ምክንያት) ብዙ የውሀ
ፍላጐት አለመኖሩን(lower water needs) እሚያመለክቱ ሁነው ነው እሚታዩት። በዚህም የተነሳ(ብዙውን ጊዜ) የበላይ
ተፋሰስ ሀገሮች እሚያሰሙት ሮሮ እምብዛም አድማጭ አያገኝም(ስምምነት ሳይሹ የግል እርምጃ ካልወሰዱ በስተቀር)።
ታዲያ እንደዚህ ከሆነ “ተመጣጣኝ”(equitable distribution or allocation)ክፍፍሎሽ እሚባለው አነጋገር
ተግባራዊነት የት ላይ ነው? የስካሁኑ አጠቃቀም በዚያው ከቀጠለ ዘለቄታ ይኖረዋል ወይ?
መልሱን በሌላ ጊዜ ለማቅረብ ይሞከራል።
16 Water withdrawal does not necessarily mean water consumed. A portion of the withdrawn water from a
source may, for some reason, be returned back to the river system.

No comments:
Post a Comment