Monday, March 24, 2014

ዓረና ከሀገረሰላም ህዝብ ጋ ተወያየ (አብርሃ ደስታ – ከትግራይ)


ትናንት እሁድ (መጋቢት 14, 2006 ዓም) ዓረና ፓርቲ በደጉዓ ተምቤን ወረዳ ሀገረሰላም ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ አካሂደዋል። ለእሁዱ ስብሰባ ቅዳሜ ቅስቀሳ የተደረገ ሲሆን የሀገረሰላም ህዝብ በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎናል።
Abrha desta
Abrha desta
የህዝቡን ስሜት ያስደነገጣቸው ባለስልጣናት የከተማው ወጣቶች ሰብስበው በስድስት መኪኖች ጭነው ስልጠና አለ፣ ስራ ይሰጣችኋል፣ አበል ይሰጣችኋል ወዘተ በማለት ሕዋነ ወደሚባል ከተማ ሲያጓጉዟቸው አመሹ። ሌሊትም ቁጥራቸው በዉል ያልታወቁ ወጣቶች ሲጓጓዙ አደሩ። ቁጥራቸው ያልታወቀ ወጣቶችም ቅዳሜ ማታ በፖሊሶች እየታደኑ ታስረዋል፤ የዓረና ስብሰባ እስኪጠናንቀቅ ድረስ። ጥረቱ ግልፅ ነበር። ወጣቶቹ በዓረና ስብሰባ እንዳይሳተፉና በአባልነት እንዳይመዘገቡ ለማራቅ ነው፤ ዓረና ከወጣቶች ጋር እንዳይገናኝ ለማድረግ ነው። በብዙ አከባቢዎች በዓረና ስብሰባ የሚሳተፉ ወጣቶች ናቸውና።
ወጣቶቹ ከከተማ በመውጣታቸው ምክንያት የስብሰባው ተሳታፊ ብዙ አልነበረም። ነገር ግን ከብዙ የገጠር ጣብያዎች የተወከሉ አርሶአደሮች፣ መምህራንና የተመሪዎች ተወካዮች ነበሩ። እናም ስብሰባው የተሳካ ነበር ማለት ይቻላል።
አንዳንድ የህወሓት ካድሬዎች (የከተማው የካቢኔ አባላት) በዓረና አባላት ላይ ችግር ለመፍጠር ሞክረው ነበር። አልጋ እንዳንይዝ ባለሆቴሎችን ያስፈራሩ ነበር፣ በአንዳንድ አባሎቻችንም አክታ የመትፋትና የመሳደብ እንዲሁም ለመረበሽ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ግን እነዚህ ተግባራት የፈፀሙ የከተማው የካቢኔ ሐላፊዎች በተናጠል (በግል) የሰሩት እንጂ እንደ የዓዲግራቱ ቀውስ ሆን ተብሎ በፓርቲ ደረጃ የተፈፀመ አልነበረም። ምክንያቱም በሀገረሰላም ካድሬዎች ችግር ሲፈጥሩ ፖሊስ ያስቁመው ነበር። በዓዲግራት ግን ፖሊስ የችግሩ ተሳታፊ ነበረ።
እሁድ ጧት ስብሰባ የጠራንበት የከተማው ማዘጋጃቤት በፖሊሶችና ካድሬዎች ተከቦ ለስብሰባ የመጣ ህዝብ ለማስፈራራት ጥረት ተደርጓል። ብዙዎች እንዲመለሱ ተደርጓል። ባጠቃላይ የህወሓት ባለስልጣናት በዓረና አባላት ላይ ይፈፅሙት የነበረ ግፍ ወደ ተሰብሳቢው ህዝብ አሸጋግረውታል።
አሁን ጥቃት የሚፈፀመው በዓረናዎች ሳይሆን ጥያቄ በሚያነሳና በዓረና ስብሰባ ለመሳተፍ ፍላጎት ባለው ሰለማዊ ህዝብ ላይ ነው። የህዝብ የመሰብሰብ መብት እየጣሱ ነው ማለት ነው። የደጉዓ ተምቤን ህዝብ ለውጥ እንደሚፈልግ አረጋግጦልናል።

No comments:

Post a Comment