Wednesday, February 12, 2014

‹‹እስካሁን ያለው ሒደት አንዳች መፍትሔ ሊያመጣ እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ›

02 FEBRUARY 2014 ተጻፈ በ  

‹‹እስካሁን ያለው ሒደት አንዳች መፍትሔ ሊያመጣ እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ››

 አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ፣ በደቡብ ሱዳን የአሜሪካ ልዩ ልዑክ
በደቡብ ሱዳን የተፈጠረው ቀውስ ለሺዎች ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎችም ተፈናቅለዋል፡፡
በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና በቀድሞ ምክትላቸው በአሁኑ ወቅት ደግሞ የተቃውሞውን ኃይል በመመራት ላይ ያሉት ዶ/ር ሪክ ማቻር መካከል የተፈጠረው የፖለቲካ አለመግባባት አዲሷን አገር በጣም አደገኛ ወደሆነ ቀውስ ከቷታል፡፡ ለአካባቢው ሥጋትም ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት በምትንቀሳቀስበት በኢጋድ አማካይነት ሁለቱንም ወገኖች በገለልተኝነት እየሸመገለች ነው፡፡ ኢጋድ አምባሳደር ሥዩም መስፍንን ልዩ አደራዳሪ አድርጎ ሾሟል፡፡ ጐን ለጐንም አስፈላጊውን የፖለቲካና የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ቡድን ተቋቁሟል፡፡ ቡድኑን የሚያስተባብሩት በኢትዮጵያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ ናቸው፡፡ አምባሳደር ዶናልድ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን የአሜሪካ መንግሥት ልዩ ልዑክ ሲሆኑ፣ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ዊልያም ቦርንስና ከአምባሳደር ሥዩም ጋር በጋራ ባለፈው ሐሙስ በሸራተን አዲስ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አምባሳደር ዶናልድ ከተጣበበ ጊዜያቸው በመሽረፍ በተለይ ለሪፖርተር በሰጡት ዕድል ከ የማነ ናግሽ ጋር የአፍታ ቆይታ አድርገዋል፡፡   
ሪፖርተር፡- በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ቀውስ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ያስጨነቀ ይመስላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ምን ይመስላል? እርስዎስ ምን እየሠሩ ነው?
አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ፡- በደቡብ ሱዳን የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ታህሳስ 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ወደ ጎሳ ግጭት ደረጃ መውረዱ ይታወሳል፡፡ ችግሩ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ትኩረትም ስቧል፡፡ በአሁኑ ወቅት ችግሩ በቁጥጥር ሥር በመዋል ላይ ይገኛል፡፡ ተቀናቃኝ ወገኖች ማለትም የደቡብ ሱዳን መንግሥትና አማፂዎች አሁን በኢጋድ ሸምጋይነት አንድ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ የተኩስ አቁም ስምምነት ባለፈው ሳምንት በመካከላቸው ሊፈጸም ችሏል፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት ሁለቱም ወገኖች ከፀብ አጫሪነት እንዲቆጠቡና የጦር ኃይላቸውን እንዲቆጣጠሩ የሚያስችል ነው፡፡ ይኼ ትልቅ ድል ነው፡፡ ምክንያቱም በቀጣይነት የሚፈለገውን የፖለቲካ ዕርቅ ለማድረግ መሠረት የሚጥል ነው፡፡ 
በእኛ በኩል የኖርዌይ፣ የእንግሊዝ፣ የቻይናና የአሜሪካ መንግሥታት ያሉበት ዓለም አቀፍ ቡድን ተቋቁሞ ከኢጋድ አደራዳሪዎችና ተደራዳሪዎች ጋር በቅርበትና በትብብር እየሠራን ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በስምምነቱ መሠረት የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ ሁኔታውን የሚያጠናና የሚቆጣጠር ኮሚቴ ይቋቋማል፡፡ ይህንን በተመለከተ ከሌሎች ባለጉዳዮች ጋር ተከታታይ ውይይት ስናደርግ ሰንብተናል፡፡ ስምምነቱ ወደ ተግባር እንዲገባ እየሠራን ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- ይኼ ዓለም አቀፍ ቡድን የኢጋድ የሰላም ሒደትን በቅርበት እየተከታተለና እየደገፈ እንደሆነ ነግረውኛል፡፡ በተለይ የአሜሪካ መንግሥት በዚህ የዕርቅ ሒደት ሚናው ምንድን ነው?
አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ፡- አሜሪካ የሰላም ሒደቱን የምትደግፈው ትልቅ ትኩረት በመስጠት ሲሆን፣ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተዋናዮች ጋር በጋራ በመሆን ነው፡፡ በኢጋድ ለሚካሄደው የሰላም ሒደት ሙሉ ድጋፍ እንሰጣለን፡፡ የደቡብ ሱዳን መንግሥትና ተቀናቃኙ ፈቃደኛ ሆነው ተደራዳሪ ቡድኖችን ወደ አዲስ አበባ ከላኩ ጊዜ ጀምሮ እየሠራሁ ነኝ፡፡ ከኢጋድ ዋና አደራዳሪዎቹ አምባሳደር ሥዩም መስፍን [የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአሁኑ ወቅት የቻይና አምባሳደር] እና ከሌተናል ጄነራል ላዘርየስ ሱምባዬ [የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር] ጋር በቅርበት እየተመካከርኩኝ እሠራለሁ፡፡ አስፈላጊውን ዕርዳታ እናደርግላቸዋለን፡፡ አንዳንዴም ከሁለቱም ተደራዳሪ ቡድኖች እየተናኘሁ እሠራለሁ፡፡ 
ለምሳሌ ከእነዚህ የኢጋድ አደራዳሪዎች ጋር በጋራ በመሆን ወደ ደቡብ ሱዳን በመጓዝ፣ የተቃዋሚውን መሪ ዶ/ር ሪክ ማቻር አግኝተን ማነጋገር ችለናል፡፡ በቅድሚያ በሁለቱም ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈረም ነበር ጥረት የምናደርገው፡፡ አሁንም ለተፈጻሚነቱ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ አብዛኛዎቹ በእስር ላይ የነበሩ ፖለቲከኞች ተፈተዋል፡፡ ይኼም ትልቅ የስምምነቱ ስኬት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ለተኩስ አቁም ስምምነቱ ዋነኛ እንቅፋት ይኼው ነበር፡፡ እስረኞቹ በቅድመ ሁኔታነት እንዲፈቱ በተቃዋሚው ተደራዳሪ የቀረበ ጥያቄ ነበር፡፡
አሁን ወደ ቀጣዩ ሒደት ለመጓዝ እያሰብን ነው፡፡ በዚህ ሁለተኛው የሰላም ዕርቅ ሒደት የቀውሱ ዋና ፖለቲካዊ ምክንያትን የሚመለከት ይሆናል፡፡ በአጭሩ አሁን እየሠራን ያለነው ስምምነቱን መሬት ላይ ተፈጻሚ ማድረግና ማረጋገጥ ነው፡፡ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዲሆን አንድ የጋራ ተቆጣጣሪ ቡድን እንዲቋቋም የታሰበ ሲሆን፣ ሙሉ ወጪው የሚሸፈነው በአሜሪካ መንግሥት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባው የተኩስ አቁም ስምምነት መልካም ሁኔታን እንደሚፈጥር ቢገመትም፣ አሁንም ያልበረደ ግጭት መኖሩን በአንዳንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ይዘገባል፡፡ እርስዎ እስካሁን ባለው የሰላም ድርድር ውጤታማነት ላይ ምን ያህል ተስፋ ያደርጋሉ?
አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ፡- አሁንም ቢሆን ዋናው የሒደቱ አካል የግጭቱ መንስዔ እንደሆነ የሚገመተው ፖለቲካዊው አለመግባባት ቢሆንም፣ እስካሁን ያለው ሒደት አንዳች መፍትሔ ሊያመጣ እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከዚህ በኋላም የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተግባራዊነት በመከታተሉ ረገድ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉን እናስባለን፡፡ በተጨባጭም የእስካሁኑ ሒደት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተደረሰ በኋላ መሆኑ ተስፈኛ ያደርገናል፡፡  
ሪፖርተር፡- ይህ የመግባቢያ ሒደት እንዳለ ሆኖ የኢጋድ ዋነኛ አባል ከሆኑት መካከል ዑጋንዳ በደቡብ ሱዳን ግጭት ውስጥ ወታደሮቿን ማሳተፏ የኢጋድን ገለልተኝነት አደጋ ላይ አይጥለውም ብለው ያስባሉ?
አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ፡- እርግጥ ነው በኢጋድ አባል አገሮች መካከል የጋራ የሆነ አቋም አለ፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ. ባለፈው ታህሳስ 27 በናይሮቢ በተካሄደው የኢጋድ ስብሰባ የኡጋንዳ ሠራዊት በደቡብ ሱዳን መሰማራቱን ተቀብሎታል፡፡ ይህም የጁባን አውሮፕላን ማረፊያና ሌሎችንም የመንግሥት መሠረተ ልማቶች ከጥቃት ለመከላከል ታስቦ ነው፡፡ አሁን ግን በተደረሰው ስምምነት መሠረት በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚካሄደው ግጭት ጋብ በማለቱ ኡጋንዳ ወታደሮቿን ከአካባቢው ማስወጣት በምትገደድበት ሁኔታ ላይ ነው ያለችው፡፡ በዚህ ረገድ ኡጋንዳም ወታደሮቿን ከአካባቢው ለማስወጣት በማሰብ የደቡብ ሱዳን መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንዲቀበል የራሷን ሚና እንደተወጣች እናስባለን፡፡ 
ሪፖርተር፡- የኡጋንዳ ኃይሎች በአካባቢው መሥፈራቸውን ተከትሎ አንዳንድ ወገኖች ኡጋንዳ የደቡብ ሱዳንን መንግሥት እየደገፈች መሆኗን ይገልጻሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ፡- እርግጥ ነው የደበብ ሱዳን መንግሥት ተቃዋሚዎች የኢጋድ አባል አገር የሆነችው ኡጋንዳ ወታደሮቿን በደቡብ ሱዳን ምድር ውስጥ አስገብታ የሽምግልና ሚናዋን ልትወጣ እንደማትችል ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የሸምጋዩ ቡድን ዋና ተዋናዮች የሆኑት አምባሳደር ሥዩም መስፍንና ሌተና ጄኔራል ላዛሪየስ ሱምባዬ ላይ ሙሉ እምነት በማሳደራቸው የተፈራውን መስተጓጎል አስቀርቶታል፡፡ 
ሪፖርተር፡- በአካባቢው ግጭት ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ፣ በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በሺሕ የሚቆጠሩም ለሞት ተዳርገዋል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት በቀውሱ ሳቢያ የተፈጠረውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመታደግ ምን እየሠራ ነው?
አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ፡- ግጭቱን ተከትሎ በአካባቢው የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከድበብ ሱዳን ተፈናቅለው በጎረቤት አገሮች በስደት ላይ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ 30 ሺሕ ስደተኞች ይገኛሉ፡፡ 680,000 የሚሆኑትም በአገር ውስጥ ከቀያቸው ተፈናቅለው ይገኛሉ፡፡ በቅድሚያ ትኩረት እየሰጠን ያለነው ስደተኞቹ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማለትም ምግብ፣ መጠለያና ልብስ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች እንዲያገኙ የበኩላችንን እያደረግን እንገኛለን፡፡ አሁን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተፈርሟል፡፡ ቀጥለን የምናደርገው ስደተኞቹ ወደ ቤታቸው ተመልሰው መደበኛ የቀድሞ ሕይወታቸውን መምራት እንዲችሉ ማድረግ ነው፡፡ ያ እንዲሆን የአካባቢውን ደኅንነትና ፀጥታ ማረጋገጥ አለብን፡፡ 
 

No comments:

Post a Comment