Wednesday, February 12, 2014

አለምነው መኮንን: ኃላፊነት የጎደለው ኃላፊ


ነጋ ዓለማየሁ
n_alemayehu@hotmail.com
2/8/2014
ሰሞኑን የአማራ ክልል ባለሥልጣን ነቻው የተባሉ ሰው በአማራው ሕዝብ ላይ የጀምላ ስድብ ሲሳደቡ
ተደምጠዋል። ሰውየውን ስሙንም ሰምቼው አላውቅም። እንዲህ አይነቱን ሰው አንቱ ማለትም የሚገባ
አልመሰለኝም። ሀገሪቱን የሚመራው መንግሥት ከየት አምጥቶ እንዳስቀመጠው እራሱ ነው የሚያውቀው።
በሕዝብ ተመርጨ ሥልጣን ይዣለሁ የሚል መንግሥት ባለሥልጣን የመረጠውን ሕዝብ አይደለም አንድን
ግለሰብም ቢሆን በመሳደብ ጸያፍ አነጋገር አይናገርም። ይህ ሰው የክልሉ መንግሥት ሁለተኛ ባለሥልጣን ነው
ተብሏል። ሥልጣኑን ሕግን ለማስከበር እንደማይጠቀምበት እያረጋገጠ ነው። የፈለገውን እየተናገረ፣ መረጠኝ
የሚለውን ሕዝብ እያዋረደና “ለሀጫም” በማለት እየተሳደበ በስልጣኑ ከቆየ መንግሥት የሕግ የበላይነትን
እንደማያከብር ብቸኛ ማረጋገጫ ነው። ለሕግ የበላይነት ቆሜአለሁ የሚል ከሆነ ተሳዳቢው ባለሥልጣን ካለበት
ሥልጣን እንዲነሳ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለሕግም ሊያቀርበው ይገባል። ስለእኩልነት እያወሩ አንደኛውን ወገን
በማቆሸሽ ያሰቡትን ማምጣት አይቻልም።
ቀደም ሲል “ትምክህተኛ አማራ” እና “ጭቁን አማራ” እያሉ እየከፋፈሉ የገዢው ፓርቲ ኃላፊዎችና ካድሬዎቻቸው
ይነግሩን ነበር። ጥያቄ ሲጠየቁ መልስ ከመስጠት ይልቅ “እናንተ ትምክህተኞች” ማለት ይቀላቸው ነበር።
እንዲያውም “ጭቁኑ አማራ” የትግል አጋራቸው እንደሆነ ይዘክሩ ነበር። “ገበሬው የእኛ ነው፣ የእኛን የኢሕአዴግን
ፖሊሲ ይደግፋል ወዘተ” በማለት ያሰለቹ ነበር። አሁን ደግሞ ይህ ግለሰብ ያንን አለቆቹ “ወዳጃችን ነው” ያሉትን
ረስቶ “በባዶ እግሩ እየሄደ” ብሎ ለመስማት የሚዘገንን ስድብ ሲሰድብ እንሰማለን። እንዴት አይነት ነገር ነው?
በዚህ ልሳን የሚናገር ሰው ይህ ዓይነት ኃላፊነት እንዴት ሊሰጠው ቻለ? ይህ ሰው ያለበትን ቦታ ያውቀዋልን?
ከላይ እንደጠቀስኩት የወያኔ/ኢሕአዴግ አስተዳደር ለሕግ መከበር ቆሜአለሁ ካለ ይህንን ግለሰብ ካለበት ኃላፊነት
በማንሳት ለፍርድ ማቅረብ ይኖርበታል። ይህንን ማድረግ ካልቻለ ግን ለሕግም ለሕዝብም ተገዢ አለመሆኑን
እራሱ ያረጋግጣል። በእርግጥ ገዢው ፓርቲ ሕግንም ሆነ ሕዝብን የሚያውቀው ለእራሱ እድሜ ማራዘሚያ
ሲፈልገው ብቻ ነው።
ሥልጣን ነጻ አይደለም። ኃላፊነት መውሰድን ይጠይቃል። በኃላፊነት ያለ ሰው ይሰደብ፣ ይወቀስ፣ የሃያስያን ርዕስ
ሆኖ በጽሑፍም እንዲሁም በሌሎች መገናኛ ብዙሃን ይወቀስ እንደሆነ እንጂ ባለሥልጣኑ ግን ሌሎችን የመስደብ
ነጻነት የለውም። ሥልጣን ከኃላፊነት ጋር ከተጠያቂነት ጋር የሚመጣ ነገር ነው። ባለሥልጣን ግዴታዎቹ ብዙ
ናቸው። የአማራን ጎሳ በአጠቃላይ መስደብ ምን ይሉታል? ይህ ባለሥልጣን ይህን ስድብ የሚሳደበው ፓርቲዬ
የሚለው ወያኔ/ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ከሃያ ዓመት በላይ መሆኑን ረስቶታል። እወክለዋለሁ የሚለውን ሕዝብ
“በባዶ እግሩ እየሄደ” ብሎ ለመናገር የሚከብድ ቃላት በመጠቀም ይሳደባል። ለመሆኑ በአሁኑ ዘመን በባዶ እግሩ
እንዲሄድ ያደረጉት እንደ እርሱ ያሉ ከእድገት ጎዳና ውጭ በሆነ መንገድ በሥልጣን ኮርቻ ላይ የተቀመጡ
ባልሥልጣኖች መሆናቸውን አያስተውልም? ሰው ሳይማር ተምሬአለሁ ብሎ ሲጠመጥም (ወይም የመማር
ምልክት ሲያደርግ)፣ ሳይነግድና ሳያርስ ሲከብር ጠመንጃ ይዞ ዳኛውን እያስፈራራ የሚጫወት ተጫዋች ይሆናል
ማለት ነው። ይህ ሰው ሜዳውም የእርሱ፣ ተጫዋቹም እርሱ፣ ዳኞችም የእርሱ አሻንጉሊቶች በመሆናቸው የተለዬ
ዓለም ያለ ይመስለዋል። ይህ አለምነው መኮንን የተባለው ባለሥልጣን ስድቡን በሚሳደብበት ጊዜ ንግግሩን
ሲሰሙ የነበሩት አድናቂዎቹ ካድሬዎች ሲስቁ ይሰማሉ። ምን አይነት የጨዋታ ሜዳ ነው፣ ምን አይነት ዳኛ
ያለበት፣ ምንስ አይነት ተመልካች ያለበት? ሲሰድባቸው የሚስቁ። እንደአባ ገብረሃና በሰምና ወርቅ ሳይሆን በግልጽ
እየሰደባቸው የሚስቁ ምን አይነት ተዋናዮች ናቸው? ማንም ሕዝብ እንደ ሕዝብ ሊሰደብ አይገባውም። ጫማቸው ላይ ባህር ዛፍ ያደርጋሉ፣ ይህ ደግሞ ቴክኖሎጂ ነው
በማለት ከአንድ ባለሥልጣን የማይጠበቅ ንግግር ያስደምጠናል። ይህ አድርባይነት ነው። ባለሥልጣን የመሳደብ
መብት የለውም። የሚያወራበትን ርዕስ “እኩልነት” አንዱን ወገን በማቆሸሽ እንዴት ሊያመጣው ይችላል? መቸም
የወያኔ/ኢሕአዴግ ባለሥልጣኖች መሳደብን እንደትልቅ ነገር ተያይዘውታል። የስድብ ት/ቤት የገቡና በመሳደብ
የተካኑ ነው የሚመስለው። ነገሩ ሲጀመር የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት አቶ ታማራት ላይኔ ወደ
ምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ሂደው አማራ የተባለውን ሕዝብ በመሳደብ በክልሉ ያሉትን ጎሳዎች “አሳዩት” በማለት
መቀስቀሳቸው ይታወሳል። አቶ መለስ ዜናዊም በምክር ቤታቸው በቴሌቪዥን በሚተላለፍ ፕሮግራም ሳይቀር
ለሥልጣናቸው የማይገባ ቃላትን በስድብ መልክ ሲናገሩ እንሰማ ነበር። ምክር ቤታቸውም ከመሳቅ በስተቀር
አግባብ አለመሆኑን የገለጸበት ጊዜ አልነበረም። በአንድ ወቅት የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የነበሩት አቶ ተመስገን
ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የሚናገሩት ቃላት ወደታች የወረደ በመሆኑ እርሳቸው በዚያ ደረጃ ለመነጋገር
እንደሚቸግራቸው መግለጻቸውን እናስታውሳለን።
የገዢው ፓርቲ ባለሥልጣናት ከአለቆቻችሁ ስድብን ልትማሩ አይገባም። የሕዝብ ዓይን ያያል፣ ልቦናውም
ያገናዝባል። ዝምታውን እንደ ይሁንታ አድርጋችሁ አትውሰዱ። ጋዜጠኞችን የተሰማቸውን መልካም ነው ያሉትን
በመጻፋቸው በአሸባሪነት ከሶ በእስራት እንዲቀጡ የፈረደ ሥርዓት ሕዝብን በጀምላ የሰደበና ያዋረደ ባለሥልጣን
የሚጠየቅበት አግባብ የለም ከተባለ ሥርዓቱ እራሱን ለማቆየት ከመታገል ባለፈ ለሕዝብና ለሕግ የበላይነት
እንዳልቆመ ብቸኛ ማረጋገጫ ይሆናል። በመሆኑም ገዢው ፓርቲ ሌላው ቢቀር ለእራሱ ሲል አቶ አለምነው
መኮንንን ከስልጣኑ አውርዶ በአስቸኳይ ለሕግ ማቅረብ ይኖርበታል እላለሁ።

No comments:

Post a Comment