Sunday, February 23, 2014

የግብፅ የመጨረሻ አማራጭ ምን ይሆን?


በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ በግብፅ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ሲካሄድ የከረመው የሦስትዮሽ ውይይት መቋረጡ የተገለጸው በካርቱም በሦስተኛው ዙር ውይይት ነበር፡፡
ሆኖም የግብፅ ተወካዮች ‹‹መንግሥታችንን አማክረን እናሳውቃለን›› በማለታቸው በቀጣይ ውይይቱ ይቀጥል እንደሆነ እርግጠኛ ሳይኮን ነበር  የተበተነው፡፡
ይኼው የሦስትዮሽ ውይይቱ በመቋረጡ ምክንያት ግብፆች አንዳንድ ተግባራትን የፈጸሙ ሲሆን፣ እነሱም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ካላቋረጠች በምንም ሁኔታ መደገፍ ማቆም እንዳለባቸው መወትወት፣ ጉዳዩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እንዲዳኝ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መውሰድና በፖሊሲ ደረጃ የነበረው የዓባይ ወንዝ ደኅንነትና አጠቃቀም በሕገ መንግሥታቸው አንቀጽ 44 ውስጥ ማካተታቸው በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ 
እነዚህ እንቅስቃሴዎች ግን በሌላ አኳኋን እየታጀቡ ነበር፡፡ ከ100 ሺሕ በላይ ቅጂዎች ሥርጭት ያለው አል አህራም ጋዜጣን ጨምሮ በአገሪቱ ያሉት ሚዲያዎች፣ ውይይቱ የተቋረጠበት ምክንያት በኢትዮጵያ እምቢተኝነት መሆኑን ከፍተኛ ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡ ከኢትዮጵያና ከየትኞቹም የዓባይ ተፋሰስ አባል አገሮች በላይ ተፅዕኖ የመፍጠር ኃይል ያላቸውን የግብፅ ሚዲያዎችን እየተቀባበሉ፣ የኢትዮጵያን ‹‹እምቢተኝነት›› ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ የሚዘግቡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም አራግበውታል፡፡ 
‹‹የመጨረሻ አማራጭ››?
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በዓባይ ወንዝ ላይ የመገንባት ዕቅድ ይፋ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ፣ ግብፃዊያን ፖለቲከኞችና ምሁራን በተለያዩ ዛቻዎች የታጀቡ ንግግሮችን አድርገዋል፡፡ ከኢትዮጵያም ተመሳሳይ የአጸፋ ምላሾች ሲሰጡ ተስተውሏል፡፡ የቃላት ጦርነቱ ጋብ ያለው፣ ኢትዮጵያ ሦስቱም አገሮች በጋራ የግድቡን ጥቅምና ጉዳት እንዲያጠኑ ሐሳብ በማቅረብዋ ምክንያት ነበር፡፡
በዚህም መሠረት ከሦስቱ አገሮች ማለትም ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳንና ከግብፅ የተውጣጡ ተወካዮችና ዓለም አቀፍ የውኃ ባለሙያዎች የተካተቱበት ቡድን ተመሥርቶ ጥናት ሲያካሂድ ቆይቶ ሪፖርቱን ባለፈው ዓመት ይፋ አድርጓል፡፡
የሪፖርቱ ዋነኛ ገዢ ሐሳብ ግድቡ በአመዛኙ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን፣ ነገር ግን አንዳንድ የዲዛይን ማሻሻያ ቢደረግበት በታችኛው የተፋሰስ አገሮች ላይ ሊያስከትለው የሚችለው ጉዳት ይቀንሳል በሚል አንዳንድ ምክረ ሐሳቦች አቅርቦ ነበር፡፡ የግብፅ መንግሥት በአንድ በኩል የሪፖርቱን ውጤት በይፋ ለመቀበል እያቅማማ፣ በሌላ በኩል ሪፖርቱ ያዛቸው የተባሉ አንዳንድ ጉድለቶችን በማጉላት በግድቡ ላይ አሉታዊ ገጽታ ለመፍጠር ተንቀሳቅሷል፡፡ 
ያም ሆነ ይህ ምክረ ሐሳቡን ተግባራዊ ለማድረግ ተከታታይ ውይይት የተደረገ ቢሆንም፣ ሦስተኛው ግን ያለ ውጤት ነበር የተቋረጠው፡፡ 
ከኢትዮጵያ የውይይቱ ተወካዮች መካከል ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለውይይቱ መቋረጥ ምክንያት የሆነው ግብፆች ጠቅላላ ሒደቱን ወደኋላ የሚመልስ ሐሳብ ይዘው በመቅረባቸው ነው፡፡ ይህ የግብፆች ድርጊት ደግሞ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የተፈለገውም የኢትዮጵያን ‹‹እምቢተኝነት›› በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ለመንዛትና የዲፕሎማሲ ትርፍ ለማግኘት ነው፡፡ 
ያንን ተከትሎ በግብፅ በኩል አንዳንድ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ  ውይይቱን የመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው የሚያመላክት በሚመስል ሁኔታ የግብፅ የመስኖና የውኃ ሚኒስትር መሐመድ አብዱል ሙታሊብ ከአቻቸው ከአቶ ዓለማየሁ ተገኑ ጋር አዲስ አበባ በመምጣት ተነጋግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የመስኖ፣ ውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የወሰንና የወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የግብፁ ሚኒስትር ውይይቱ መቀጠል እንዳለበት ተስማምተው ቢሄዱም፣ አገራቸው እንደደረሱ የሰጡት መግለጫ ከዚህ መንፈስ ያፈነገጠ ነበር፡፡
‹‹በወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ትብብር ግዴታ እንጂ አማራጭ አይደለም፤›› የሚሉት አቶ ፈቅአህመድ፣ የግብፅ ባለሥልጣናት በአንድ በኩል እንተባበር በሚል፣ በሌላ በኩል የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን በማሳሳት ተንቀሳቅሰው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እየሞከሩ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያን በጦርነት ለማስፈራራት ተነስተዋል በማለት አስረድተዋል፡፡ 
አቶ ፈቅአህመድ እንደሚሉት፣ ትብብር ከማድረግ ውጪ ምንም ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ‹‹በፈቃደኝነት እንዲመጡ እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም በዚህ ደረጃ ከእነ ክብራቸውና ልዕልናቸው ይመጣሉ፡፡ አለበለዚያ አለመተባበር የሚያስከትለውን ጉዳት ተቀብለው እንዲመጡ ማድረግ ነው፡፡ ያኔ ክብራቸውና ልዕልናቸውን አጥተው ነው የሚመጡት፡፡ ምክንያቱም አለመተባበር የሚያስከትለው አደጋ አስገድዷቸው ነው የሚመጡት፤›› ብለዋል፡፡
ያለመተባበር የሚያስከትለው አደጋ ምን እንደሆነ እንዲህ ሲሉ ያብራሩታል፡፡ ‹‹መተባበር ከሌለ ሁሉም አገር የየራሱን የተናጠል አማራጭ ይወስዳል፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁን በምትሠራው ግድብ የታችኛው ተፋሰስ አባል አገሮች እንዳይጎዱ በመጠንቀቅ ነበር፡፡ የሁለቱንም አገሮች ጥቅም ለማስጠበቅ ስትል ነው፡፡ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ተባባሪ ካልሆኑ ምን እንደሚጎዳቸውና ምን እንደሚጠቅማቸው መረጃ አይኖርም፤ ማወቅ አይቻልም፡፡ ማንም ተጠቃሚ አይሆንም፤ በበለጠ ጉዳት የሚደርስባቸው የታችኛው ተፋሰስ አባል አገሮች ናቸው፤›› በማለት ነው የገለጹት፡፡ 
ግብፆች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይ ኢትዮጵያን በፋይናንስ ይደግፋሉ ለሚባሉት አገሮች የተሳሳተ መረጃ አቅርበው የኢትዮጵያን ገጽታ እያበላሹ መሆናቸው ይገለጻል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በግድቡም ሆነ አጠቃላይ በሒደቱ ላይ እውነተኛውን መረጃ በመውሰድ ለማስረዳት ጥረት እያደረገ መሆኑን አቶ ፈቅአህመድ ይናገራሉ፡፡ በውጭ የሚገኙት የኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ አካላት በዚሁ ሥራ ላይ መጠመዳቸውንም ያስረዳሉ፡፡ 
ግብፆች ወደ ተመድና ወደ ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ለመውሰድ መነሳታቸውን በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ ከመነሻው ጀምሮ ፕሮጀክቱ ፍትሐዊ በመሆኑ ምንም የሚያሰጋት ነገር እንደሌለ፣ ያለሁለቱ ሉዓላዊ አገሮች ፈቃደኝነት በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች የሚታይ እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡ 
ግብፅ በሌላው አማራጩዋ ‹‹የኃይል ዕርምጃ እወስዳለሁ›› ማለቷን በተመለከተም ምላሽ የሰጡት አቶ ፈቅአህመድ፣ ‹‹ይኼ አማራጭ ያዋጣል ከተባለ ሁሌም ክፍት ነው፡፡ መሐመድ ሙርሲም ደጋግመው ሲሉት ነበር፤›› ብለው፣ ‹‹መፍትሔው ቀላል ነው፤›› በማለት የሚያስረዱት አቶ ፈቅአህመድ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት የሰጡትን ምላሽ ዋቢ አድርገዋል፡፡ ‹‹ለማስፈራራት መፍትሔው አለመፍራት ነው፡፡ መተኛት ማለት ግን አይደለም፡፡ መንግሥት አስፈላጊ የተባለውን ሁሉ ዝግጅት አድርጓል፡፡ የሚያሰጋ ነገር የለም፤›› ማለታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ገዥ ሐሳቡ ‹‹ግብፆች አይሞክሩትም›› ያሉት ግድቡን የማጥቃት ሙከራ ሲሆን፣ ‹‹ከሞከሩት ግን የሚኖረው የአፀፋ ምላሽ ሉዓላዊነትን የማስከበር ጉዳይ ነው፡፡ በእነሱ ላይ የሚያስከትለው አደጋ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ትልቁ ነገር እነሱም ከቃላት በዘለለ ለራሳቸው ሲሉ አያደርጉትም፤›› በማለት፡፡
የልማት አማራጭ?
‹‹የምሥራቅ አፍሪካ የውኃ ማማ›› የሚል ስያሜ የተሰጣት ኢትዮጵያ የዓለማችን ታላቁ የዓባይ ወንዝ 86 በመቶውን ውኃ ታመነጫለች፡፡ ይህ አሥራ አንድ አገሮች የሚጋሩት ተፋሰስ ጥቅም ላይ እንዳይውል ግብፅና ሱዳን የፈረሙዋቸው እ.ኤ.አ. 1929 እና 1959 የውኃ ስምምነቶች ሌሎችን የተፋሰሱ አገሮች ያላካተቱ በመሆናቸው፣ በጉዳዩ ላይ አለመግባባት፣ ብዥታና ሥጋት ፈጥረው ቆይተዋል፡፡
በአፍሪካ ከነዳጅ አልባ አገሮች በግንባር ቀደምትነት ኢኮኖሚዋ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ያለችው ኢትዮጵያ፣ ይህንን ዕድገቷን የሚደግፍ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት እንደሚያስፈልጋት ይነገራል፡፡ 
የወደፊት ዕድገቷ ከዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ጋር የሚያያዝ እንደሆነ የሚናገሩ ምሁራን ሲኖሩ፣ ለጊዜው በ2002 ዓ.ም. ይፋ የሆነውና በብዙዎች እንደ ‹‹ሕልም›› የታየው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተጠቃሽ ነው፡፡ የአገሪቱን የድህነት ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡ ወደ መካከለኛ ገቢ አገሮች ተርታ ለመሠለፍም መንደርደሪያ ይሆናታል ይባላል፡፡  
የዕቅዱ አካል የሆነው የዓባይ ግድብ የሚሰጠው ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ መልካም ቢሆንም፣ አንድም የአገሪቱ የኃይል አቅርቦት ፍላጎትን ለማሟላት፣ በሌላ በኩል በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የሚታውን የኃይል ፍላጎት ገበያ የተመለከተ ይመስላል፡፡ 
ታላቁ የዓባይ ግድብ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ቀዳሚው የውኃ ኃይል ግድብ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይፋ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ በግብፅ ፖለቲከኞች ላይ እየፈጠረው ያለው ሥጋት ቀላል አይደለም፡፡
ግብፅ የዓባይ ግድብ ይፋ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ የገጠማት የፖለቲካ ቀውስ እስካሁን እልባት ያላገኘ በመሆኑ፣ የዕድሜ ልክ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሆስኒ ሙባረክ በአብዮቱ ከሥልጣናቸው ከመባረራቸው በፊት፣ በምርጫ ወደ ሥልጣን የመጡት የሙስሉም ወንድማማቾች ሊቀመንበር ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲም በኢትዮጵያ ላይ ወታደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ዝተው ነበር፡፡ አንዳንድ ሾልከው የወጡ ዓለም አቀፍ የደኅንነት መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በመገንባት ላይ ያለውን የዓባይ ግድብ ለማፈራረስ ዕቅድ ነበራቸው፡፡ 
ፕሬዚዳንት ሙርሲ በአገር ውስጥ በገጠማቸው ተከታታይ አመፅ ምክንያት ኢትዮጵያን እንደ ማስተንፈሻ ለማድረግ አቅደው እንደነበር የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ 
የተንታኞቹ ምልከታ የሚያረጋግጠው ደግሞ በአንድ ወቅት ከሥልጣናቸው ከመባረራቸው ትንሽ ቀደም ብሎ ራሳቸው በመሩት ብሔራዊ ኮንፈረንስ ላይ የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች በመርዳት ጭምር ኢትዮጵያን ለመውጋት መናገራቸው፣ በስህተት ባመለጠ የቴሌቪዥን ሥርጭት መጋለጡ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment