ይድረስ የካቲት 11ን ለምታከብሩ ታጋይ ወላጆቼ! (አብርሃ ደስታ – ከትግራይ)
የካቲት 11ድን ታከብራላቹ። የታሪካቹ መሰረት ነውና አክብሩት። ግን አሁን ስታከብሩት የሰነቃችሁትን ዓላማ ስለተሳካ እየተደሰታችሁ ነው ወይስ መስዋእት የከፈላችሁበት ዓላማ ተጠልፎ በመኮላሸቱ ምክንያት እየቆዘማችሁ?
ዓላማቹ ስለተጠለፈ እየቆዘማችሁ ከሆነ ከዚህ በኋላ ትርጉም ያለው ሰለማዊ ትግል ለማድረግ አብረን እንነሳ። ከኛ ጋ በመሆን ዓላችሁን ከግብ አድርሱ። የየካቲት ዓላማ በመሳካቱ እየተደሰታችሁ የሚታከብሩ ከሆነ ግን የየካቲት ዓላማ ምን እንደነበር ንገሩንና እኛ ልጆቻችሁም እንከተላቹ። ዓላማችሁ ምን ነበር? የደርግን ዓፋኝ ስርዓት በሌላ ዓፋኝ ስርዓት መቀየር? ወይስ ለልጆቻቹ ነፃነት ለማስፈን? ጭቆናና ጨቋኞችን ማስወገድ ወይስ ጨቋኝ ባለስልጣናትን በሌሎች ጨቋኞች መቀየር?
ዓላማችሁ የደርግ ጨቋኞችን በህወሓት ጨቋኞችን መቀየር ከሆነ ስህተት ነው። መስዋእትነት የሚጠይቅ ትክክለኛ ዓላማ የነፃነት ዓላማ ነው። ስለዚህ ሁላችን ለነፃነታችን እንታገል። እናንተም ከኛ ጋ ታገሉ። ትግላቹ ነፃነትን ለማምጣት ከነበረ ግን የየካቲት 11 ዓላማ አልተሳካም ማለት ነው። ነፃነት አልተገኘምና። ስለዚህ ከኛ ጋ ታገሉ።
ባጭሩ የየካቲት 11 ዓላማ ከተሳካ በነፃነት እንኑር፤ በነፃነት ያለ ምንም ፖለቲካዊ ወይ ማህበራዊ ወይ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ የፈለግነውን የፖለቲካ ድርጅት እንደግፍ፣ ያልፈለግነውን እንቃወም ወይም እንደፍላጎታችን እንሁን። ይህንን ካልተፈቀደልን ግን ነፃነታችን ተገድቧል ማለት ነው። ስለዚህ ነፃነታችንን የሚገድብ ማንኛውም አካል መወገድ ይኖርበታል። ለነፃነታችን እንነሳ፤ ከተፈቀደልን ነፃነታችንን እንጠቀማለን። ካልተፈቀደልን ደግሞ ነፃነታችንን አሳልፈን ላለመስጠት ጨቋኞችን እንታገላለን።
ትግላቹ ለነፃነት ከነበረ እንደግፈዋለን። እናንተን ተከትለን ለነፃነታችን እንቆማለን። ዓላማቹ ለጭቆና ከነበረ ግን ታሪኩ መስተካከል አለበት። መስዋእት መክፈል ያለብን ለነፃነታችን ብቻ ነውና።
No comments:
Post a Comment