Monday, December 16, 2013

አልሸባብ ወደ ኢትዮጵያ - ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ!?

5 DECEMBER 2013 ተጻፈ በ  

አልሸባብ ወደ ኢትዮጵያ - ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ!?


በአረንጓዴ፣ ቀይ፣ ቢጫ ኅብረ ቀለማት ሁለመናቸውን አሸብርቀው፣ የመኪናውን ጎዳና ከተቆጣጠሩት የአዲስ አበባ ወጣቶች መካከል ዳዊት ብሩክ አንዱ ነው፡፡
ከፊሉ ፊታቸውን በኅብረ ቀለማቱ አስውበው፣ ገሚሶቹ በቀለማቱ ያሸበረቁ የብሔራዊ ቡድን ማልያ ለብሰው፣ ሌሎቹ ደግሞ በእነዚሁ ኅብረ ቀለማት ያሸበረቀውን ሻርፕ ጣል ያደረጉ ነበሩ፡፡ ዳዊት በሦስተኛው ቀንም ፊቱ ላይ ያቀለማቸው ኅብረ ቀለማት አልጠፉም፡፡ 
በመጪው ሰኔ ለሚካሄደው የብራዚል 2014 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ለማለፍ ከአፍሪካ ምርጥ አሥር ቡድኖች መካከል የነበረውን የናይጀሪያን ብሔራዊ ቡድን በጥቅምት ለመግጠም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቀጠሮ ይዟል፡፡ 
እንደ ዳዊት ጨዋታውን ለመታደም ዕድል አግኝተው ስታዲየም ከገቡት ውጪ በተለያዩ ስክሪኖች ተሰባስበው ለመመልከት የሚጋፉ የከተማይቱ ወጣቶች ደግሞ ቁጥር ስፍር የላቸውም፡፡ በተለይ በሚሌኒየም አዳራሽ ጨዋታውን ለመመልከት ከፍለው የገቡ ደግሞ ብዛት ነበራቸው፡፡ በብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና ናይጄርያውያን የሚጠበቀው ጨዋታ አሥር ሰዓት ላይ ሊጀመር አሥራ አምስት ደቂቃ ሲቀረው በአቅራቢያው ለነበሩት ሰዎች ድንጋጤን የፈጠረ አንድ ነገር ነበር፡፡ በወቅቱ ትኩረታቸው ዋልያዎች አሸንፈው ለማየት ብቻ የሆነው የከተማይቱ ወጣቶች ግን የነበረው የቦንብ ፍንዳታ የአንዳቸውንም ቀልብ የሳበ አልነበረም፡፡ 
ፌዴራል ፖሊስ አጣርቶ አገኘሁት ባለው መረጃ ተመርኩዞ መንግሥት በሰጠው መግለጫ እንዳሳወቀው፣ በዚሁ ቀውጢ ሰዓት ጭምጭምታው የተሰማው ፍንዳታ፣ በተለምዶ ሩዋንዳ እየተባለ በሚጠራው የቦሌ ክፍለ ከተማ አካባቢ ተከስቶ የሁለት ሶማሊያውያን ሕይወትን ቀጥፏል፡፡ እንደ መንግሥት እምነት፣ በክስተቱ ሕይወታቸው ያለፈው እነዚህ ሶማሊያውያን ዒላማ፣ በታሪካዊው የእግር ኳስ ዕለት በተሰበሰቡ የአዲስ አበባ ተመልካቾች ላይ ሊያፈነዱት የነበረው ቦንብ ከግቡ ሳይደርስ መፈንዳቱ ነው፡፡ 
ዜናውን ያዳመጠው ዳዊት ብሩክም፣ አሸባሪዎቹ ተሳክቶላቸው ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያንና የናይጄሪያን ጨዋታ ለመመልከት ከስታዲየሙ ውስጥና ውጭ ተሰባስቦ በነበረው ሕዝብ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ሲያስብ ዘግንኖታል፡፡ በሌሎች አካባቢዎች አስቀድሞ የተፈጸሙ የሽብር ተግባራትንም እንዲያስብ አስገድዶታል፡፡ 
በወቅቱ አስደንጋጭ የነበረው የሽብር ሙከራ ግን ያለምንም ማሳሰቢያ ድንገት የሆነ አልነበረም፡፡ በመስከረም ወር በኬንያ መዲና ናይሮቢ በሚገኘው ዌስት ጌት ትልቁ የገበያ አዳራሽ ላይ በአሸባሪዎች የተፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት፣ በኢትዮጵያም ሊደገም ይችላል የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ በነበሩበት አጋጣሚ ነው ሙከራው የመከነው፡፡ በኬንያው ጥቃት 67 ንፁኃን ዜጎች ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ ቀደም ሲል አልሸባብ በካምፓላ (ኡጋንዳ) የዓለም ዋንጫ ይከታተሉ በነበሩት ላይ በፈጸመው ጥቃት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የ74 ሰዎች ሕይወት መቅጠፉ አይዘነጋም፡፡ 
በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውና ‹‹ሊጠፋ ምንም የቀረው ነገር የለም›› እየተባለ ሲነገርለት የነበረውና ከአልቃኢዳ ጋር ትስስር ያለው አልሸባብ በኬንያ ለተፈጸመው ድርጊት ኃላፊነቱን መውሰዱ ደግሞ ጥርጣሬውን ከፍ አድርጎት ነበር፡፡ 
ዘመቻ አንድና ሁለት
እ.ኤ.አ. ከ2006 ጀምሮ አብዛኛው የደቡባዊ ሶማሊያ ከፍል ተቆጣጥሮ የነበረውና በሼክ ዳሂር አወይስ ይመራ የነበረው የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት የሽግግሩን መንግሥት ለማጥፋት ምንም አልቀረውም ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለውና በኢትዮጵያ የሚደገፈው የሽግግሩ መንግሥት፣ ለ20 ዓመታት ገደማ መንግሥት አልባ ለሆነችው ሶማሊያ መፍትሔ ይሆናል በሚል ተስፋ ቢጣልበትም የራሱን ህልውና በራሱ ወታደራዊና የደኅንነት ኃይል መቋቋም የሚችል አልነበረም፡፡ የሽግግሩ አካል ወደ ስፍራው የመጣውም ከበርካታ የሰላም ሒደቶችና ድርድሮች በኋላ ነበር፡፡ 
የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት አመጣጥ ግን ከዚሁ በተቃራኒው ሲሆን፣ በአብዛኛው የሶማሊያ ወጣቶች ተቀባይነት ያገኘና በግብፅ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ሊቢያና በሌሎች በነዳጅ የበለፀጉ የመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች ይደገፍ እንደነበር በወቅቱ የወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ ከእነዚህ ድጋፎች ጀርባ ሆኖ ያሽከረክር የነበረው ደግሞ የኤርትራ መንግሥት መሆኑን የተመድ አጣሪ ቡድንን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሪፖርቶች ያረጋገጡት ነው፡፡ አወይስን ጨምሮ ወደ አስመራ በመመላለስ ላይ የነበሩት የኅብረቱ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ግዛትን መቆጣጠር እንደሚፈልጉ በመግለጽ በኢትዮጵያ ላይ ጅሃድ አውጀው ነበር፡፡  
በፌዴራል ሽግግር መንግሥቱ ጥሪ፣ ሶማሊያ ዘልቆ ወታደራዊ ዘመቻ ያደረገው የኢትዮጵያ ሠራዊት፣ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን መበታተን ቢችልም፤ በተለይ በኤርትራ የማይቋረጥ ድጋፍ የተነሳ የመጀመሪያ ዘመቻው ለሁለት ዓመታት ቆይቶበት ነበር፡፡ መንግሥት ለሕዝቡ ይፋ ማድረግ ያልፈቀደው ከፍተኛ የገንዘብና የሰው ኃይል ኪሳራ መክፈሉም ይነገራል በዚህም የተለያዩ ትችቶች አስተናግዷል፡፡ የሁለት ዓመታት ቆይታው ግን አሁንም በቂ አልነበረም፡፡ ድርጅቱ ቢበታተንም ሙሉ ለሙሉ የተንኮታኮተ አልነበረም፡፡ ቀስ በቀስ እንደ አዲስ የወጣቶች ክንፍ የሆኑትን ኃይሎች ያካተተው አልሸባብ የተባለው ኃይል አንሰራፍቶ ስለነበር ዳግመኛ ዘመቻ ለማድረግ ተገዷል፡፡ 
በዚሁ ወቅት ከተለያዩ አገሮች (ከኡጋንዳ፣ ብሩንዲና ጂቡቲ) የተውጣጣው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ (አሚሶም) በአካባቢው ተሰማርቶ የነበረ ቢሆንም፣ አልሸባብን ጨርሶ ማጥፋት አልቻለም ነበር፡፡ ሆኖም አሚሶምን ጨምሮ በአንድ በኩል በኬንያ፣ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ወታደሮች በሦስት ግንባሮች የተሰነዘረበት ወታደራዊ ጥቃት መቋቋም የቻለ አልነበረም፡፡ የኬንያና የኢትዮጵያ ወታደሮች ስምሪት ግን ለየቅል ነበር፡፡ የኬንያ ወታደሮች በአፍሪካ ኅብረት ውሳኔ መሠረት በተመድ በሚደገፈው የአሚሶም እንዲጣመሩ የተደረገ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች በተናጠልና በአገሪቱ በራሷ ወጪ የሚካሄድ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች ዘመቻ ከሁለት ዓመት በፊት በኢጋድ መድረክ በሽግግሩ መንግሥት ጋባዥነት የነበረ ቢሆንም፣ ኬንያ ወታደሮች ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ጥቅሞቻቸው አልተጠበቀላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትንም ለተጨማሪ የገንዘብ ወጪና ኪሳራ ዳርጐታል የሚሉ ትችቶች እየተሰሙ ነበር፡፡ 
ጣምራ ዘመቻ
በሦስት ግንባር ጥቃት የተከፈተበት አልሸባብ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አቅሙን መመናመኑ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘገባ እንደሚያመላክቱት፣ አልሸባብ እንደ ድርጅት በሶማሊያ የመቆየት ህልውናው አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚሰነዝራቸው ጥቃቶች የተስፋ መቁረጥና ተራ የሽብር ተግባራት እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን፣ አንድ የደኅንነት ተመራማሪ እንደሚሉት፣ አልቃኢዳ እስካለ ድረስ አልሸባብ ፈጽሞ ይጠፋል ማለት አይታሰብም፡፡ አልሸባብ በሞት አፋፍ ላይ ነው ተብሎ በአፍሪካ ኅብረት በተነገረ ማግስት በኬንያ ላይ የሰነዘረው ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ ድንጋጤ ፈጥሯል፡፡ አሜሪካን ጨምሮ የአልቃኢዳ ሽብር ሥጋት ያለባቸው ምዕራባውያንም በአፍሪካ ቀንድ ችላ ብለውት የነበረውን ጉዳይ እንዲከልሱ አድርጓቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የፈጠረው ድንጋጤ ደግሞ ድርብርብ ይመስላል፡፡ ከመጀመርያው የአልሸባብ ምንጭ የሆነውን የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ለመበታተን ዋነኛ መሳሪያ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ዳግመኛም፣ ድርጅቱ ከአልቃኢዳ ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያለው ቢሆንም ዋነኛ ድጋፍ የሚያገኘው የኢትዮጵያ ቁጥር አንድ ጠላት ከሆነው ከኤርትራ መንግሥት ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት የበለጠ የሚያጠናክረው ደግሞ፣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ የኤርትራ መንግሥት ለአልሸባብ የሚሰጠው ወታደራዊና ሎጂስቲካዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን መግለጹ ነው፡፡ በዚሁ ጣልቃ ገብነት የተነሳ፣ ቀደም ሲል ሁለት ጊዜ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ የተጣለበት የኤርትራ መንግሥት ሁሌም እንዳስተባበለ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2006 ጀምሮ ላለፉት በርከት ያሉ ዓመታት ደጋግሞ ወደ ሶማሊያ ወታደራዊ ዘመቻ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት የተሳካለት ቢመስልም ከፍተኛ ወጪ እንዳስከተለበት ይነገራል፡፡ በአሁኑ ወቅት አልሻባብ በኢትዮጵያ ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም መዘጋጀቱን መረጃ የደረሰው መንግሥት ዜጎቹን አስጠንቅቋል፡፡ የኤርትራ እጅም እንዳለበት አሳውቋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በተናጠል እስከ ስምንት ሺሕ ወታደሮች የያዘ የጦር ኃይል በሶማሊያ አሰማርቶ የቆየ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ይኼው ኃይል ወደ አሚሶም መቀላቀሉ በብዙዎች ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የወታደሮቹን ወደ አሚሶም መቀላቀል አልሸባብን ለማጥፋት በአካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሰላም አስከባሪ ኃይሎችና የሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎች መካከል የቆየው ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የደኅንነት ተንታኝ ደግሞ፣ ወደ ጎረቤት አገር በሰላም ማስከበር ሥራ መሰማራት የተለመደ ባይሆንም፣ አሁን በአካባቢው ያለውን ሥጋት ለማስወገድ አማራጭ እንደሌለው ይናገራሉ፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ በመጠቆም፡፡ እንደእሳቸው እምነት፣ አሚሶም ውስጥ የነበረው ወታደራዊ ድክመትና ክፍተት ለመሙላት በጣም ጠቃሚ ዕርምጃ ይሆናል፡፡  
በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የደኅንነት ፖሊሲ ጥናት ፕሮግራም ኃላፊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት፣ ፖል ዊልያምስ እንደሚሉት ግን፣ የችግሩ አካል የሆነችው ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ሥራውን መሳተፍ የለባትም፡፡ እንደ እሳቸው እምነት፣ በአካባቢው ስለኢትዮጵያ አለ ያሉት አሉታዊ አመለካከት በአሚሶምም ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ በአካባቢው የተሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል ለረዥም ጊዜ በዚሁ መልኩ ከማቆየት ይልቅ ከአገሪቱ ለቅቆ የሚወጣበት ፍኖተ ካርታ ዕቅድ ነው መዘጋጀት እንዳለበት አስምረውበታል፡፡

No comments:

Post a Comment