Friday, December 27, 2013

ከማዲባ ማን ምን ይማር? ግርማ ሠይፉ ማሩ

ከማዲባ ማን ምን ይማር?
ግርማ ሠይፉ ማሩ

ባለፈው ሳምንት የማንዴላን (ማዲባን) ሞትና ቀብር አስመልክቶ ብዙ ነገር ተብሎዋል፡፡ የተባሉትን ሁሉ ግን እንደ
አመለካከታችን የተለያየ ትርጉም እና ትንተና ልንሰጥ እንደምንችል ጉልህ ማሳያ የሚሆነው ፋክት መፅሔት
ከሚኒሊክ ጋር በንፅፅር ይዛው የወጣችው አንዱ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ከማዴላ ረጅም የህይወት ውጣ ውረደ መከራና
ሰኬት ማን ምን ይማር? ብለን መጠየቅ ተገቢ መሰለኝ፡፡ መንግሰት አፋቃሪ የሚባሉ ሚዲያዎች ጭምር ስለ
ማንዴላ የትግል ተሞክሮ ብዙ ሲነግሩን ነበር፡፡ እንደ ግዑዝ ካልቆጠሩን በስተቀር አንድ አንዶቹን ልንማርባቸው
እንደምንችል የዘነጉት ይመሰለላል፡፡ ልንማረው የምንችለውን ነገር ግን ልማታዊ ጋዜጠኝነታቸው የሚፈቅድላቸው
አልመሰለኝም፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅመው የልማታዊ ጋዜጠኛን ድንበር ያለፉ ሁሉ ነው የሚመስለኝ፡፡ በዘህ
አጋጣሚ መንግሰቱ ኃይለማሪያምም ሰፊ የሚዲያ ሽፋን አግኝተው የከረሙ ሲሆን አዲሰ ዘመን እንኳን ከነባለቤታቸው ፎቶዋቸውን ይዞት
ብቅ ብሎ ነበር፡፡ ሚዛናዊነት ተጀመረ እንዴ ማለቴ አልቀረም፡፡

ማንዴላ ትግሉን ሲጀምሩ መሳሪያ እንደማያሰፈልግ እምነታቸው የነበረ ቢሆንም የአፓርታይድ አገዛዝ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ
የሚያሰሙ ንፁዓን ላይ በሚወስደው እርምጃ እና ርህራኤ አልባነት የተነሳ አሁንስ በቃ ብሎ ፓርቲያቸወች የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ
በትጥቅ ትግል ሁሉ ማሰገደድ እንደሚገባው አስረግጠው ተናግረው ተግባራዊም አድርገዋል፡፡ ይህም ተገቢ ነው ብላ ሀገራችን ኢትዮጵያም
ቡራኬዋን በተግባር ካስመሰከሩት አንዷ ስትሆን፤ ታሪኩን ተቀብለን በበጎነት እያወሳነው እንገኛለን፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታም በሀገራችን
ኢትዮጵያም ይህ በተግባር የታየ ትምህርት የተወሰደበት ይመስላል፡፡ ከ1997 ምርጫ በፊት የሰላማዊ ትግል አርበኛ ነን ሲሉ የነበሩ ሰዎች፤
በፅሁፍም በቃልም ሲሰብኩን የነበሩ ሰዎች መንግሰት ስላማዊ ትግልን ለማፈን በወሰዳቸው ዘግናኝ እርምጃዎች ተማረው፤ አሁንስ በቃ
ብለው ሁሉን አቀፍ ትግል በመከተል ይህን አገዛዝ ማሰገደድ ይገባል ቢሉ ከማንዴላ አልተማሩም ልንል እንችላለን ወይ?

መሰረቱን በውጭ ያደረገ ኢ.ቢ. ኤሴ የተባለ አፍቃሪ መንግሰት ቴሌቪዥን ጣቢያ ማንዴላን ለመዘከር ባቀረበው አንድ ፕሮግራም ማንዴላ
ህገ ወጥ ህጎችን በመጣስ እስር ቤት በገፍ መግባትን እንደ ትግል ስትራቴጂ ይጠቀሙ ነበር ብሎ በምሳሌ ሲያቀርብ ነበር፡፡ መቼም
በድናችን ካልሆነ በቴሌቪዝን ፊት ለፊት የተጎለተው ለእኛ ምን ትምህርት አለው? የሚል ጥያቄ ማጫሩ ግድ ነው፡፡ መንግሰት ድምፃችንን
አልሰማም ካለ እኛም ልንከተለው የሚገባን ትግል ህገ ወጥ ህጎችን በመጣስ በገፍ ወህኒ መውረድ ነው፡፡ ይህ ለማንዴላ ክብር ያሰጠ
የሰላማዊ ትግል ስልት በኢትዮጵያ ምድር ስንሞክር አሸባሪ፤ ህገ መንግሰት ለመናድ የተነሱ ወይም ሌላ ቅጥያ ሊያሰጠን እንደሚችል
አውቀን ህገ ወጥ ህጎችን እና ውሳኔዎችን በመጣስ እስር ቤት መግባትን መማር ይኖርብናል፡፡ ይህ ልምድ ሊቀሰምበት የሚችል የትግል
አማራጭ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ማንዴላን ለክብር ያበቃው ይህ የትግል ስልት ነው ወይ? የሚለው በቅጡ መታየት
ይኖረበታል፡፡

ከዚህ ጋር የሚያያዝ ባለፈው ሳምንት በመረጃ መረብ ላይ “አሸባሪነትን የሚያበረታታ መንግስት” በሚል እንዲለጠፍ ባደረኩት ፅሁፍ
ሰዎች የሚደርስባቸውን ግፍ መሰረት አድርገው በግል ወደ ሽብር ተግባር ወይም በቡድን አሸባሪነትን እንደ አማራጭ ከሚያራምዱ ጋር
ወደ መቀላቀል ሊገፋፉ ይችላሉ የሚል ሃሳብ አንስቼ ነበር፡፡ መቼም ቡድኖቹ እራሳችውን አሽባሪ እንደማይሉ ይታወቃል፡፡ ማንዴላም
አሽባሪ መዝገብ ውስጥ እንደነበሩ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ አንድ አንድ አንባቢያን አማራጩ ይህ ብቻ ነው ወይ? ለምን ወደ ሰላማዊ ትግል
አይገቡም የሚል አስተያየት ሰንዝረውልኝ እንደ ተጨማሪ አማራጭ ለማየት ሙከራ አድርጌ ነበር፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ይህ አማራጭ ያለ
ቢሆንም በሰላማዊ ትግል ለማደረግ ሙከራ የሚያደርጉትን መንግሰት እንዴት አድርጎ በሩን እየዘጋ እንደሆነ ሰመለከት፤ ተስፈኝነቴን
የሚገዳደር ነገር ነው የተሰማኝ፡፡

መንግሰት በግለሰቦች ላይ ከሚያደርሰው ግፍና በደል (ስብዓዊ መብት ጥሰት) በተነፃፃሪ በስላማዊ ትግል ለውጥ በሚፈልጉት ቡድኖች
ላይም ተመሳሳይ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ለነገሩ የግለሰቦችን መብት እየጣሱ የቡደን እናከብራለን ቢሎ ተግባራዊነቱ አስቸጋሪ እንደሆነ
ይረዱታል፡፡ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ በህዝብ ውስጥ ተንቀሳቅሶ ዓላማውን የሚገልፅ በራሪ ወረቀት መበተን ሲከለከል ይህም የሚፈፀመው
በጋራ እንዲጠብቁን ደሞዝ የምንከፍላቸውን የፖሊስ ኃይሎችን ተጠቅሞ መሆኑ፤ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔውን ወይም ሌላ
ህዝባዊ ስብሰባ ለማከናወን ገንዘብ ከፍሎ አዳራሽ ለመከራይት በማይችልበት ደረጃ የማስፈራራት ዘመቻ በአዳራሽ አከራዮች ላይ ሲፈፀም
ወዘተ. ስንመለከት ማንዴላን ለክብር ካበቃው የትግል መንገድ እና ማንዴላ ይመራው ከነበረው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ የእኛዎቹ
ፓርቲዎች ምን ሊማሩ ይችላሉ ብለን መጠየቅም የአባት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

እውነቱን ለመናገር ማንዴላን በክብር ማማ ላይ ያወጣቸው፤ በዋነኝነት የጀመሩትን የነፃነት ትግል ያሳረጉበት መንገድ እንጂ በሂደት
ያሳለፏቸው ውጣ ውረዶች አይደሉም፡፡ ማንዴላ ከ27 ዓመት እስር በኋላ ቂምና በቀልን ሳይሆን ይቅር ባይነትን፤ ለተበዳዮች ብቻ ሳይሆን
ለበዳዮችም ነፃነት የሚሆን ስርዓት ለመመስረት የወሰዱት ቆራጥ ግን ከባድ እርምጃ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከማንዴላ፤
ከዴክለርክም ሆነ እነርሱ ከሚመሯቸው ፓርቲዎች የምንማረውን መምረጥ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ቶማስ ኤዲሰን “አምፖልን” ለመስራት
ሞክሮ የተሳሳታቸውን ብዙ ሺ መንገዶች መሞከር አይጠበቅብንም፤ መማር ያለብን አምፖሉን እንዴት እንደሰራው ነው፡፡ ብልጥ ሰው
ከሰው ስህተት ይማራል ማለት፤ ሌሎች የሰሩትን ስህተት መስራት አይጠበቅበትም ማለት ነው፡፡ ሰለዚህ ምን እንማር ?

ግርማ ሠይፉ ማሩ ለማንዴላ የዘመናት ትግል በውጤት እንዲጠናቀቅ የአፓርታይዱ መንግስት ጉልዕ ሚና እንደነበረው መዘንጋት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ይህን
ማስታወስ ደግሞ የእኛዎቹ ገዢዎች ትምህርት የሚገበዩበት ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የእኛዎቹ ገዢዎች አፓርታይድ የሰራውን ግፍ
ያህል አልሰራንም ብለው የእርሱን ያህል ግፍ የምንሰራበት ጊዜ ይሰጠን ካላሉ በስተቀር፤ የአፓርታይድ መሪዎች ማንዴላን ከእስር በመልቀቅ
እና የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ላይ ጥለውት የነበረውን እግዳ በማንሳት ለሰላማዊ አንቅስቃሴ፣ ለነፃ ውድድር እና ምርጫ በር ለመክፈት
በቁርጠኝነት መወሰናቸው፤ የማንዴላ የዘመናት ትግል ፍሬ እንዲያፈራ የአፓርታይድም መሪዎች ታሪክ ሰርተዋል፡፡ ጥያቄው የእኛ መሪዎች
ከሌላው ስህተት በመማር እና ማንዴላን ለውጤት ያበቃውን ተግባር በመቀመር ተገቢ ርምጃ ለመውሰድ ይችላሉ ወይ? የሚለው ነው፡፡
ይህንን ታሪክ ለመስራት የሚያስችለው ዕድል በእጃቸው ላይ ሆኖ የገዢዎቻችን ውሳኔ እየጠበቀ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎችና መሪዎች ከዚህ በላቀ ሁኔታ የሚጠበቅ ነገር እንዳለም መዘንጋት አያስፈልግም፡፡ ተቃዋሚዎች ያለፈ ታሪክን
በማንሳት በቂምና በበቀል ሂሣብ ለማወራረድ አድብቶ መጠበቅን እንደ አንድ እስትራቴጂ ይዘውት ከሆነ እንደ እባብ መርዝ ሊተፉት
የሚገባ ነገር ነው፡፡ ይህ የሚተፉት መርዝ መድሃኒት ሆኖ ሀገራችን ኢትዮጵያን ሊታደጋት የሚችል የሚሆንበት ዕድል አለ የሚል ፅኑ
እምነት አለኝ፡፡ ማንዴላ/ማዲባ ያደረገው ይህንን ነው፡፡ ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን የደረሰባቸውን መከራና ግፍ በመርሳት ሳይሆን ከልብ
የመነጨ የይቅርታ ሰሜትን በመፍጠር ዓለም መቼም ሆነ መቼ የማይዘነጋውን ታሪክ እንዲፃፍ አድርጎዋል፡፡ እኛስ ይህን ታሪክ ለመፃፍ
ዕድል ቢገኝ የልባችን በር ክፍት ይሆን? የይቅርታ ልባችን እንዲከፈት ፈጣሪ ይርዳን፡፡

ቸር ይግጠምን








ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
December 22, 2013 

No comments:

Post a Comment