Wednesday, December 18, 2013

የዚህ ትውልድ መነቃቃት

8 DECEMBER 2013 ተጻፈ በ  

የዚህ ትውልድ መነቃቃት የተንፀባረቀበት መድረክ

ታዋቂው የግሪክ ፈላስፋ ፕሌቶ በዘመኑ ስለተመለከተው ወጣት ትውልድ እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር፡፡
“What is happening to our young people? They disrespect their elders, they disobey their parents. They ignore the law. They riot in the streets inflamed with wild notions. Their morals are decaying. What is to become of them?” በግርድፉ ትርጉሙ፣ ‹‹በወጣቱ ትውልድ ላይ የሚስተዋለው ነገር ምንድነው? ታላላቆቻቸውን አያከብሩም፣ ወላጆቻቸውን አይታዘዙዋቸውም፣ ሕግንና ደንብን ይጥሳሉ፣ እዚህ ግባ በማይባል ከንቱ አስተሳሰብ ተገፋፍተው በየጎዳናው ላይ ያምፃሉ፡፡ ሞራላቸውም እየበሰበሰ ነው፡፡ ስለዚህም ምንድነው ከእነሱ የሚጠበቀው?›› ሲል ወቀሳውን በጥያቄ ይደመድማል፡፡
በእርግጥ ፕሌቶ በታላቁ ፈላስፋ ሶክራጥስ ሥር የተማረና ያደገ እንደመሆኑ በእሱ ዘመን የተመለከታቸው ወጣቶች ከእሱ የአስተሳሰብ ደረጃ ጋር የሚመጣጠን ሰብዕና ይዘው ባለመገኘታቸው ቢበሳጭባቸው ላይገርም ይችላል፡፡ በተለይ በጥንታዊ ሥልጣኔ፣ በሳይንስ፣ በሥነ ጠፈርና በሕክምናው ዓለምን የተቆጣጠረው የዚያን ዘመኑ የግሪክ ትውልድ በምርጡ ዘር መካከል እንደ እንክርዳድ ብቅ ብቅ ይል የነበረውን ተመጣጣኝ ያልሆነ ትውልድ በዚህ መውቀሱ የሚያስተቸው ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ዛሬ ግሪክ የምትገኝበትን አጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታ በውሉ ላጤነው፣ የጥንቱን የግሪክ ትውልድ ወቀሳ በአዎንታዊው ጎኑ መመልከቱ የማያስገርም መሆኑ ነው፡፡ 
በሰው ልጅ ረዥም ዕድሜ ታሪክ ውስጥ ለተከናወኑ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው በጎም ሆኑ መጥፎ ታሪኮች ትውልድ ባለቤት ሆኖ አልፏል፤ እያለፈም ነው፡፡ እንደ አገሮቹ ታሪክም በድንቅ ሰብዕና ታሪክ የሠራ ትውልድ የመኖሩን ያህል፣ ከንቱ ሆኖ ያለፈና ለወገንም ለአገርም ያልጠቀመ ትውልድ ተፈጥሮ ማለፉ አሌ የማይባል ሀቅ መሆኑን ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ 
እነሆ በኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ውስጥ እያንዳንዱ ትውልድ የራሱን አሻራ ጥሎ አልፏል፡፡ በተለይ በንጉሡ ጊዜ የመሬት ላራሹንና ሌሎችንም የፖለቲካዊ ጥያቄዎች አንግቦ ሲንቀሳቀስ የነበረው የተማሪ ንቅናቄ ዛሬ ላይ መንግሥት እንደ አዲስ ተፈጥራለች ለሚላት ኢትዮጵያ መሠረት እንደሆነ ብዙዎችን የሚያስማማ ሀቅ ነው፡፡ በዚያን ጊዜው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የነበሩትና ግንባር ቀደሞቹ ዋለልኝ መኮንንና ጥላሁን ግዛው በድንገት በወታደራዊው ኃይል ቁጥጥር ሥር ለወደቀው የተማሪው አብዮት ተጠቃሾች ሲሆኑ፣ በዘመኑ ለነበረው ‹‹እሳት›› ትውልድም መታወቂያ ሆነው ማለፋቸውን የታሪክና የፖለቲካ ተንታኞች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚያወሱት ነው፡፡ 
‹‹አንድ ትውልድ›› ያህል አልቆበታል ከሚባልለት አብዮት ጀምሮ እየተከተቡ ባሉት በርካታ ድርሳናት ውስጥ ‹‹ያ ትውልድ›› ምን ያህል በዕውቀት የጠገበና በጀግንነት ለአገሩ የተሰዋ እንደነበር ታትቷል፡፡ ‹‹ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ›› የሚል መጠሪያን የያዘው የዛሬው የአገሪቱ መሪ ትውልድም በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ የራሱን ታሪክ እያሰፈረ ነው፡፡ ኢሕአዴግ አገሪቷን ከተቆጣጠረበት 1983 ዓ.ም. ወዲህ የተፈጠረውና ዛሬ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኘው ትውልድ በግሎባላይዜሽንና በሌሎችም ዘመን አመጣሽ ባህሎች የተወረረ ስለመሆኑና ስለአገሩ ነባራዊ ሁኔታ እምብዛም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ የሚያወሱ አሉ፡፡ 
ከዚያም ባሻገር የቀድሞውን ትውልድ የሚያስታውስ ተጨባጭ ሰብዕና እንደሌለው በተለያዩ አጋጣሚዎች ተወርቶለታል፡፡ ፋሽን ተከታይ፣ የውጭ ባህል ናፋቂ፣ ስለአገሩና ስለባህሉ ደንታ የሌለው ትውልድ እንደሆነም ይነገራል፡፡ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያሉ ወጣቶች እንደቀድሞው ትውልድ መጻሕፍትን ጓደኛ ከማድረግ ይልቅ በአልባሌ ነገሮች ላይ ማተኮሩን የሚተቹ አሉ፡፡ የትምህርት ፖሊሲው ከወለደው ሥርዓተ ትምህርት ጋርም በተያያዘ በዕውቀትና ኃላፊነትን በመወጣት ደረጃ ከቀድሞው ትውልድ አንፃር ሲመዘን ትውልዱ ደካማ ስለመሆኑም የሚከራከሩ አሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በስፖርቱና በኪነ ጥበቡ መስክ እየተስተዋሉ የመጡት የወጣቱ እንቅስቃሴዎች ግን በመጠኑም ቢሆን ይህን ትችት ያቃለሉ ስለመሆናቸው የሚሞግቱም አልጠፉም፡፡ ይኼውም ቀስ በቀስ በሌሎች የፖለቲካና ማኅበራዊ መድረኮች ስለመታየቱ ፍንጭ የሚሰጡ እውነታዎች መታየት መጀመራቸው፣ የዛሬው ትውልድ የራሱን አሻራ ጥሎ ለማለፍ የሚችልበት ዕድል ስለመኖሩ አመላካች ሁኔታዎች ያሉ ይመስላሉ፡፡
በቅርቡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በተዘጋጀው ስምንተኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ላይ ከተስተዋሉት ጉዳዮች አንዱ ይህንን እውነታ የሚገልጽ ነበር፡፡ የዋናው በዓል አካል ተደርገው ከሁለት ቀናት በፊት የተካሄዱት ሲምፖዚየሞች ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ የወጣቶችን ተሳትፎ ያየለበት ይመስል ነበር፡፡ በዕለቱ ለወጣቱ አሰልቺ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው በሚታሰቡ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ወጣቶቹ የላቀ ተሳትፎ ከማድረጋቸውም በላይ፣ በአገራቸው ላይም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አላቸው ተብሎ የሚታሰበው ዝቅተኛ ግንዛቤ የተሳሳተ መሆኑን በሚጠቁም አኳኋን በመድረኩ ላይ ነበሩትን ፖለቲከኞች የሚፈትኑ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡፡
በእንዲህ መሰሉ አገራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ባላቸው በዓላትና ስብሰባዎች ላይ የሚገኙት ተሳታፊዎች በአንድም በሌላም ሁኔታ ለገዥው ፓርቲ በሚያስወግኑ ሁኔታዎች ውስጥ አልፈው ሊመጡ እንደሚችሉ ቢጠበቅም፣ ሁሉም ተሳታፊዎች ግን ተመሳሳይ የፖለቲካ አመለካከት ነበራቸው ማለት አይቻልም፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ‹‹አንድ ለአምስት›› በሚል አደረጃጀት ከገጠሩ አርሶ አደር ጀምሮ የከተማውን የመንግሥት ሠራተኛና ተማሪውን ድረስ የደረሰ ‹‹ልማታዊ ሰንሰለት›› በመዘርጋቱ፣ የራሱን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በሕዝቡ ውስጥ ለማስረፅ መንገዱ አልጋ ባልጋ ቢመስልለትም፣ ውጣ ውረድ እንዳለውም የሚጠቁሙ ምልክቶች በመድረኩ በተማሪዎቹ ተንፀባርቀዋል፡፡ 
‹‹ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ተዘጋጅቶ በነበረው በዚሁ ሲምፖዚየም ላይ የተሰየሙት ጥናት አቅራቢዎችና የሥርዓቱ መሥራቾች ባቀረቡዋቸው የስኬት ትንታኔዎች ላይ ተማሪዎቹ በበኩላቸው ውድቀት ያሉዋቸውን ተፃራሪ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት የታሰበውን ያህል ውጤት አላስገኘም፣ አንድነትን ሸርሽሯል፣ ቋንቋን መሠረት በማድረጉ አካባቢያዊነትን አጎልብቷል፣ ወዘተ. ሲሉ ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ በፍትሕ፣ በትምህርት ጥራትና በሙስና ላይ ሥርዓቱ ተፈትኖ ወድቆባቸዋል ያሏቸውን ነጥቦችም አንስተዋል፡፡
እመቤት የተባለች የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በፌዴራሊዝም ትሩፋቶች ላይ እንደማትስማማና ይልቁንም ፌዴራሊዝም ያመጣዋል ተብሎ የተጠበቀውን ለውጥ እንዳላመጣ ተናግራለች፡፡ ደቡብ ክልል ከ56 በላይ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ብሔር ብሔረሰቦችን የያዘ እንደመሆኑ መጠን፣ ሌሎቹ ክልሎች የተዋቀሩበትንና ቋንቋና አሰፋፈርን መሠረት ላደረገው አከላለል አመቺ እንዳልሆነም አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡ ሌላዋ የዩኒቨርሱቲ ተማሪም እንዲሁ በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ስትናገር፣ ለዚህም አንዱ ምክንያት ተማሪዎች ያለ ፍላጎታቸው ውጤታማ በማይሆኑባቸው የትምህርት ዘርፎች መመደባቸው እንደሆነ ግምቷን አስቀምጣለች፡፡ በኮምቦልቻ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማረው ሌላው ወጣት በበኩሉ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ያሉትን ችግሮች በመጠቆም መንግሥት አሳክቼዋለሁ በሚለው የፍትሕ ሥርዓት ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ 
በሲምፖዚየሙ ጥናታዊ ጽሑፉ አቅራቢ ከነበሩትና ከሕግ አንፃር የፍትሕ ሥርዓቱንና የፌዴራሊዝም ሥርዓቱን የተነተኑት አቶ ዘፋኒያ ዓለሙ ፍርድ ቤቶች ነፃ ስለመሆናቸውና የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችም በፍትሕ አሰጣጥ ሒደት ውስጥ ሙሉ መብት መጎናፀፋቸውን በመግለጽ የተማሪውን ጥያቄ ለመመለስ ሞክረዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ የሆኑት አቶ ዓባይ ፀሐዬም ተማሪዎቹ ባነሱዋቸው ጥያቄዎች ላይ ከሥርዓቱ ግንባታ መሠረት ተነስተው ማብራሪያቸውን ሲያክሉ፣ የፌዴራል ሥርዓቱ ኢትዮጵያን ከመበታተን ያዳነና ብቸኛ አማራጭ ስለመሆኑ ምሳሌዎችን በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡ ‹‹ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም የእኛ ብቻ አይደለም፡፡ ቤልጅየምም የፈረንሳይኛ ተናጋሪውን አካባቢ ከተቀረው የአገሪቱ ክፍል ተለይቶ እንዲከለል ያደረገችው ቋንቋን መሠረት አድርጋ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 
በሲምፖዚየሙ ላይ ጥያቄና አስተያየታቸውን የሰነዘሩት ተማሪዎች ብቻ አልነበሩም፡፡ ከተለያዩ ሲቪክ ማኅበራት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ተቋማት የተውጣጡ ግለሰቦችም በጥያቄውና በአስተያየቱ ላይ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ የተማሪዎቹ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ግን በተለየ ሁኔታ የተሳታፊዎችን ቀልብ ስለመግዛታቸው የተናገሩት ሌሎች ተሳታፊዎች፣ ወጣቶቹ በነፃነት የጠየቋቸውና ለመላሾቹም አስቸጋሪ የመሰሉት አስተያየቶች የሌሎችን የመልካም አስተዳደርና ቢሮክራሲያዊ ጥያቄዎች ያኮሰሱ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ ተሳታፊ የተማሪዎቹን ጥያቄዎችና አስተያየቶች ያልተጠበቁ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ክስተቱ በአሁኑ ዘመን ተማሪዎች ላይ አብዛኛው ማኅበረሰብ የያዘውን ጭፍን ምልከታ ትዝብት ውስጥ የሚጥል መስሎ እንደተሰማቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹እንዲያውም ለአንዳንዱ ሰው እነዚህ ልጆች በተቃዋሚ ፖለቲከኞች የተላኩ ሊመስለው ይችላል፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡ 
የዛሬው ትውልድ በነፃነት ማሰብ እንደሚፈልግና ያልገባውንና ያልመሰለውን ነገርም ፊት ለፊት አቅርቦ መጠየቅን ስለመልመዱ አመላካች ነው የሚሉ ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ፣ በወጣቶች ላይ የሚያስተውሉት ባህሪ በአደባባይ ስለመገለጹ ይናገራሉ፡፡ እንደሳቸው አስተያየት፣ ልጆቹ ያልገባቸውንና ያላመኑበትን ነገር በነፃነት እስካልተረዱ ድረስ ‹‹ለምን?›› ብለው መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ ይህ ልማድ ደግሞ እያደገ ሲመጣ ታላላቅ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ሳይቀር ፊት ለፊት ቆመው ለመጠየቅና ማብራሪያን ለመሻት አይቸገሩም ባይ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል የሰሜን አፍሪካ አገሮችንና የመካከለኛው ምሥራቅን የለውጥ አብዮት ያቀጣጠሉትን ወጣቶች ዞር ብሎ መመልከት ያሻል የሚሉ ወገኖች የወጣቶችን መነቃቃት ከዚሁ የዓረብ የፖለቲካ ትኩሳት ጋር ያያይዙታል፡፡ ቁም ነገሩ ግን ትውልዱ በአንዳንድ የማኅበረሰቡ አካላት የሚሰነዘርበትን ያህል ወኔ ቢስ፣ ፋሽን ተከታይና ለአገሩ ጉዳይ ደንታ ቢስ አለመሆኑን ፍንትው አርጎ ማሳየት የሚችል አጋጣሚ ስለመሆኑ ብዙዎችን ያስማማ ይመስል ነበር፡፡ ይህ በመሆኑም መንግሥት ለተማሪዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተገቢውን ትኩረትና ቦታ መስጠት፣ እንዲህ በግልጽና በነፃነት ያሻቸውን ነገር በመጠየቃቸውም ትክክል መሆናቸውን ማበረታቻና ድጋፉን በመለገስ የተሻለች ኢትዮጵያን በመገንባት ውጥኑ ውስጥ ሚና እንዲኖራቸው ማስቻል እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡ አያይዘውም ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመናመኑበት  በዚህ ወቅት በተማሪዎች ላይ የሚስተዋለው እንዲህ መሰሉ መነቃቃትና ግልጽነት ለመፃኢው የአገሪቱ ፖለቲካ መልካም ዘመን እየመጣ ስለመሆኑም ተስፋቸውን ይገልጻሉ፡፡

No comments:

Post a Comment