የት ነው ያለነው?
ወይ ባል አላገባሽ ወይ አልመኮነስሽ
እንዴው ልጅ አገረድ ይባላል ስምሽ
እንደሚባለው ወይ በአማርኛ(በራሳችን ቋንቋ) በሚገባ ተምረን አልተግባባን፤ ወይ በፈረንጅ ቋንቋ በሚገባ ተምረን አልተግባባን፡፡ እንዴው ምን ይሻላል?
ድሮ ድጎማ የሚባል መምህር ነበር አሉ፡፡ መቶ ብር በማይሞላ ደሞዝ ነበር አሉ የሚቀጠሩት፡፡ ክፍል ውስጥ ክኖው፣ ዲጂቡቲ፣ ክናይፍ know, Djibouti , knife, እያለ ያስተምራል፡፡ ተቆጣጣሪው (ሱፐርቫይዘሩ) እንዴት እንዲህ ታስተምራለህ? ኖው፣ ጂቡቲ፣ ናይፍ በል ይለዋል፡፡ መምህሩም ‹‹በድጎማ ደሞዝማ እንዲያ ብዬ አላስተምርም›› አለ ይባላል፡፡
በባሕላዊው የጥንት ትምህርታችን ንባብ ወሳኙና የመጀመሪያው ትምህርት ነበር፡፡ የፊደል ዘር መለየት ብቻ ሳይሆን አነባበብም ጭምር፤ በየሠፈራችን የነበሩትን የቄስ ትምህርት ቤቶች እናስታውሳቸው፡፡ ፊደሎቹን ከነዜማቸው እስክንሸመድድ ድረስ አንገት ላንገት ተቃቅፈን የምንናጥባቸውን ትምህርት ቤቶች አስታውሱ፡፡
ማንበብ የዕድገት ቁልፍ ነው፡፡ ለዚህም ነው በጥንት ሥልጣኔ የምናውቃቸው ሀገሮች ሁሉ የራሳቸውን ፊደል ለመፍጠር የተሳካላቸው ሀገሮች የነበሩት፡፡ በሥልጣኔ መጥቆ ፊደልና ጽሕፈት የሌለው ሀገር አናገኝም፡፡ የማያነብብና የማይጽፍ ትውልድ መፍጠር ከዕውቀት የተቆራረጠ ትውልድ መፍጠር ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በዐረብ ሀገሮች በሚገኙ ዜጎቻችን ዘንድ አንዱ ፈተና ‹ማኑዋል አንብቦ› መሣሪያዎችን ለመጠቀም አለመቻል ነው፡፡
ወላጆች፣ የእምነት ተቋማት፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ሚዲያዎችና የሚመለከተን ሁሉ ልናስብበት የሚገባ ቁልፍ ችግር - ማንበብ የማይወድ ሳይሆን ማንበብ የማይችል ትውልድ በየክልሉ እየተፈጠረ ነው፡፡ ፊደልና አጻጻፍ መለየት የእንግሊዝኛም የሀገራዊ ቋንቋዎችም ችግር እየሆነ ነው፡፡
እናም፣ የፊደልን ዘር መለየት፣ አጻጻፍን ማወቅና አነባበብን ማርታትን ከነባሩ የትምህርት ሥርዓታችን በሚገባ ቀስመን ወደ ዘመናዊ ትምህርት በጊዜ ካላስገባነው - ትውልድ አደጋ ላይ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment