Saturday, July 6, 2013

ዜና መጽሀፍ፤ የአቶ ግርማ ሰይፉ መፅሀፍ እየመጣ ነው፡፡

ዜና መጽሀፍ፤  የአቶ ግርማ ሰይፉ መፅሀፍ እየመጣ ነው፡፡
ኢህአዴግዬ ባለፈው ምርጫ መቶ ፐርሰንት እንዳታሸንፍ ጉድ ያደረጉዋት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ናቸው፡፡ አቶ ግርማ በፓርላማ ውስጥ ባይተዋርነቱን ተቋቁመው፣  የአቶ መለስን ቁጣ ተቋቁመው፣ የአቶ ሃይለማሪምን ድራማ ተቋቁመው፣ የፓርላማ አባላቱን ጭብጫቦ ቷቁመው፣ የአባዱላ ገመዳን ፌዘኝነት ተቋቁመው አንዴም በጆሮ ማዳመጫ አንዴም በጆሯቸው ብዙ የፓርላማ ቀልዶችን ሲሰሙ የቆዩ ሰው ናቸው፡፡
ሰውየው ከሌሎች ተቃዋሚዎች በተለየ መልኩ፤ በአንድ ፓርላማ ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትር ለማየት ታድለዋል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊን እና የአቶ መለስ ዜናዊን ፎቶግራፍ፡፡ በሁለቱም ጊዜ የሚወክሉትን ህብረተሰብ ጥያቄ ሲያቀርቡ አንጀት ላይ ጠብ የሚል መልስ አግኝተው አያውቁም፡፡ አቶ መለሱም መልሳቸው ቁጣ ነበር ፎቶግራፋቸውም መልሱ ፀጥታ ነው፡፡ አቶ ሀይሌም ከመለስ ቁጣ ትንሽ ከመለስ ፎቶግራፍ ዝምታ ትንሽ እየወሰዱ መልሳቸው ራሱ ጥያቄ ነው፡፡
አቶ ግርማ ሰይፉ አሁን ደግሞ በአዲሱ መጽሀፋቸው እኛን እየጠየቁን ነው የነፃነት ዋጋው ስንት ነው…? ይሉናል፡፡
መጽሀፉ ሀምሌ ሶስት በውሃ እና ኢነርጂ መስሪያ ቤት አዳራሽ ውስጥ ይመረቃል፡፡ ያ ቀን የአቶ ግርማ የልደት ቀናቸውም መሆኑን ከፌስ  ቡክ ግድግዳቸው ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ ትራንስፖርት ያገኘን በሙሉ እንድንሄድ ተጋብዘናል!
በነገራችን ላይ፤
ከተቃዋሚዎች አቶ ግርማ ፌስ ቡክን በመጠቀም ከማይቃወሙት ደግሞ ዶክተር ቴውድሮስ አድሃኖም ትዊተርን በመጠቀም በፓርላማ ለሚገኙ ሰዎች አርአያ ናቸው፡፡ እባካችሁ ተወካዮቻችን እንዲህ ቀረብ ቀረብ በሉንና ምን እያልን እንደሆነ ስሙን አሰሙልንም!

No comments:

Post a Comment