Wednesday, July 9, 2014

የሽብር - ዘፍጥረት ፪



የሽብር - ዘፍጥረት ፪
(ተመስገን ደሳለኝ)

 በ1990ዎቹ መጨረሻ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ሶማሊያ ግዛት ዘልቆ የመግባቱ ታላቅ
ስህተት “አልሸባብ” የተባለ ሽብርተኛ ቡድን እንዲፈጠር መግፍኤ ስለመሆኑ በብዙ ተወስቷል፡፡ ቡድኑ
በአሁኑ ወቅት የአልቃይዳ የምስራቅ አፍሪካ ክንፍ ከመሆኑም ባለፈ፣ በየጊዜው በሚያደርሳቸው አሰቃቂ
የሽብር ጥቃቶች አካባቢውን የስጋት ቀጠና ማድረጉ በገሀድ የሚታይ እውነታ ነው፡፡ ይሁንና በዚህ
ተጠየቅ የምንዳስሰው የአልሸባብን አደገኛነት ብቻ አይደለም፣ ኢህአዴግም የሽብር ፖለቲካን እንዴት
ሥልጣኑን ለማራዘም እንደሚጠቀምበት አብረን እንፈትሻለን፡፡ በቅድሚያ ግን የኢትዮጵያ ሠራዊት
ሶማሊያ ውስጥ ገብቶ ጦርነት ባካሄደበት ወቅት ስለከፈለው መስዋዕትነት እና ተያያዥ ጉዳዮች ጨርፈን
እንድንመለከት የሚያደርጉ ሶስት ገፊ-ምክንያቶች መኖራቸውን አስተውያለሁ፡፡ የመጀመሪያው
ከዘመቻው መልስ ትርፍና ኪሳራን በተመለከተ ገዥው-ፓርቲ መረጃዎችን ይፋ ካለማድረጉም በዘለለ፣
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩ ተቃዋሚዎች ‹በሠራዊታችን ላይ ስለደረሰው ጉዳት በዝርዝር
ይነገረን?› ሲሉ ላቀረቡት ጥያቄ፣ ‹ስለዚህ ጉዳይ ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ የለብኝም› በማለት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ
ዜናዊ አዳፍኖ ማለፉ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ያኔም በመከላከያ ውስጥ የነበሩ ችግሮች ዛሬም ባለመቀረፋቸው ነው፤ ሶስተኛውና
ዋነኛው ግን ያ ጀግና ሠራዊት ምንም እንኳ በማይመለከተው ጉዳይ (ያውም በሰው ሀገር) ውድ ዋጋ እንዲከፍል ቢገደድም፣
ስለፈፀመው ታላቅ ተጋድሎም ሆነ ከሞቋዲሾ እስከ ኪስማዩ ስለደረሱበት አስከፊ መስዋዕትነቶች ያለመዘከሩ እውነታ ነው፡፡

 እንደወጣ የቀረ ወታደር
 የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ የዘመተበት ዋነኛ ግዳጅ ሀገሪቱን ከእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ሕብረት ነፃ ማውጣት ሲሆን፣ ይህንን
ተልዕኮ ለመፈፀምም የተጋነነ መስዋዕትነት አለመክፈሉ አይስተባበልም፤ ይህ እንግዲህ ከ44ኛው ክፍለ ጦር 4ኛ፣ 5ኛ ሬጅመንት እና
8ኛ ሜካናይዝድ፤ ከ32ኛ ክፍለ ጦር ከመጣ ድጋፍ ሰጪ አንድ ሻለቃ ጋር በመሆን፣ ከሞቋዲሾ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ድንሱር
በተባለች ከተማ ላይ ባደረጉት ውጊያ የደረሰውን የበርካታ ወታደሮች ህይወት ማለፍ፣ ቁስለኝነት እና የአንድ ታንክ መቃጠልን ሳንዘነጋ
ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከሶስት ቀን በኋላ ከሞያሌ የመጣችው 6ኛ ሬጅመንት (የዚሁ ክፍለ ጦር አባል) በውጊያው ላይ በአጋዥነት
ባትሰለፍ ኖሮ መስዋዕትነቱ ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችል እንደነበረ ከጦርነቱ ወላፈን ያመለጡ የአይን እማኞች ይናገራሉ፡፡

 በተቀረ የኢትዮጵያ ሠራዊት በሶማሊያ ቆይታው ፈታኝ ሁኔታ ያጋጠመው ራሱን ‹‹አልሸባብ›› ብሎ የሚጠራው ቡድን ከተመሰረተ
በኋላ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ በተለይም በሞቋዲሾ ጥቂት የማይባሉ ደም-አፋሳሽ ውጊያዎች ስለመደረጋቸው ማስረጃዎች አሉ፤
ለማሳያነትም ሠራዊቱ ከሞላ ጎደል ሀገሪቱን ተቆጣጥሮ፣ በይበልጥም ኃይሉን በመዲናይቱ አጠናክሮ ሕዝቡን በፍርሃት ጠፍንጎ ከያዘ
በኋላ የተካሄደውን እንጥቀሰው፡፡ …ከዕለታት በአንዱ ቀን አልሸባብ ከተማይቱ መሀል በቀላሉ የማይበገር ምሽግ በአንድ ጀምበር ሰርቶ
የኢትዮጵያ ሠራዊትን በተጠንቀቅ የመጠባበቁ ወሬ በስፋት ተናፈሰ፡፡ ከዚያስ? በውጊያው ላይ የተሳተፈና ከአመራር ሰጪዎች መካከል
አንዱ የነበረው ከበደ ንጉሴ (ስሙ የተቀየረ) ክስተቱን እንዲህ ይተርከዋል፡-

“እኛ ሞቋዲሾን ሙሉ በሙሉ ከመቆጣጠር አልፈን አንፃራዊ ሰላም አስፍነናል ባልንበት፣ ሚያዝያ 12 ቀን 1999 ዓ.ም፤ ‹አልሸባብ ከቤላ
ባይደዋ (በመሀል መዲናይቱ የሚገኝ የሠራዊቱ ካምፕ ነው) 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ዋናውን አስፓልት በዶዘር ቆፍሮ፣ ጠንካራ ምሽግ
ሰርቶ ለውጊያ አድፍጧል› የሚል መረጃ ደረሰን፤ ማመን አቃተን፤ ይህ እንዴት ይሆናል? በርግጥ ከምንም በላይ አፍንጫችን ስር ይህ ሁሉ
እስኪሆን ድረስ አንዳችም ነገር አለማወቃችን እጅግ አስገርሞን ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ የዚያኑ ዕለት ምሽት ሶስት ሰዓት አለፍ እንዳለ፣
ለሠራዊቱ ጠዋት ግዳጅ እንዳለ ነግረን፣ ኮዳውን እንዲሞላና ትጥቁን አዘገጃጅቶ በተጠንቀቅ እንዲጠብቅ ትዕዛዝ ሰጥተን አደርን፤ ንጋት
አስራ ሁለት ሰዓት ተኩል ላይም እተጠቀሰው ቦታ ደርሰን ቀጥታ ጥቃት ሰነዘርን፣ አስቀድሞ ጠንካራ ምሽግ ሰርቶ ያደፈጠውና በንቃት
ሲጠባበቅ የቆየው የአልሸባብ ኃይል ግን በቀላሉ የሚበገር አልሆነም፤ በተለይ ደግሞ በከተማዋ የተለያዩ ማዕዘናት ከሚገኙ ህንፃዎች ላይ
እየተወነጨፉ ይደበድቡን የነበሩ የከባድ መሳሪያ እሩምታዎች ፈተናችንን አብዝተውት ነበር፤ ብቻ ከቀኑ ወደ 5 ሰዓት አካባቢ ድሉ የእኛ
ሆነ፤ የማይካደው እውነታ ግን በሠራዊታችን ላይ እጅግ ከባድ ጉዳት ማድረሳቸው ነው፤ ከመቶ በላይ ወታደሮቻችንን የህይወትና የአካል
መስዋዕትነት አስከፍለዋል፡፡ ሌላው የዕለቱ አስገራሚ ክስተት ደግሞ ከዚህ ሁሉ ትንቅንቅ በኋላ ምሽጋቸውን ሰብረን ስንገባ ከአንድ
አባላቸው ሬሳ በቀር ምንም ያገኘነው ነገር አለመኖሩ ነው፤ ታዲያ! እንዲያ ገትረው ሲዋጉ የነበሩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሽፍቶች የት ገቡ?
ማናችንም መልስ አልነበረንም፡፡ የተሰዉ ጓዶቻቸውን አስከሬን በጭራሽ ትተው እንደማይሸሹ የተረዳነው እጅግ ዘግይተን ነበር፡፡”

 በሌላ ጊዜ ደግሞ የ44ኛው ክፍለ ጦር 3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ሬጅመንት፣ ከአዋሽ አርባ ከመጣ ታንከኛ ጋር በመሆን፣ ከምሽቱ 2 ሰዓት
አካባቢ ‹‹ጂልፕ›› የተሰኘች ቦታ ላይ ካደፈጡ አሻባሪዎች ጋር ከባድ ውጊያ አድርገው ያሸንፋሉ፤ ታጣቂዎቹም እግሬ አውጪኝ ብለው
ያመልጣሉ፤ ሠራዊቱም እዛው ቦታ ላይ ደፈጣ ይዞ ያድርና ልክ ከንጋቱ 12 ሰዓት ወደ ሞቃዲሾ ለመጓዝ ይንቀሳቀሳል፤ ይሁንና ሃምሳ
ሜትር ርቀት እንኳን ሳይጓዝ በተቀበረ ፈንጂ የ107 አባላት ከእነ ከባድ መሳሪያ ተኳሻቸው በሙሉ ያለቁበት ዘግናኝ አደጋ ሊፈጠር
ችሏል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
2

 ከወራት በኋላም ሞቋዲሾን ተቆጣጥረው የነበሩት የአግአዚ ሻለቃዎች፣ ቦታቸውን ለ44ኛ ያስረክባሉ፤ የኢትዮጵያ መንግስትም
‹አጠቃላይ ሰላም ለማስፈን› በሚል ከጎሳ መሪዎች ጋር ድርድር ለማድረግ ይሞክራል፡፡ ግና፣ በታላቅነቱም ሆነ በተዋጊነቱ ከሁሉም
እንደሚልቅ የሚነገርለት የሃዊ ጎሳ አባላት የሰላም ሃሳቡን ከማጣጣልም አልፈው በአደባባይ እንዲህ ሲሉ አቋማቸውን አስታወቁ፡-
“ሶማሊያን ማስተዳደር ያለብን እኛ እንጂ እናንተ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁም፤ ስለዚህ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ሀገራችንን
ለቃችሁ ውጡ!”

 ይህንንም ተከትሎ፣ ሃዊን ጨምሮ የሌላ ጎሳ አባላት የተሳተፉበት ከባድ ውጊያ በመቀስቀሱ በሁለቱም ወገኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት
ሊደርስ ችሏል፡፡

 እዚህ ጋ ሳይጠቀስ የማይታለፈው፣ በመከላከያ ሠራዊቱ የመረጃ ባለሞያዎች ድክመት (እንዝህላልነት) ከባድ ጉዳት የደረሰበት
አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ ይኸውም በመሀመድ ዚያድባሬ ዘመን በዩኒቨርስቲነትና በመንግስታዊ ሆስፒታልነት ያገለግል በነበረበት ግቢ
ውስጥ ማረፊያውን ያደረገው 5ኛ ሬጅመንት፣ የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር መሰሪያ ቤት ወደነበረው ‹‹ጋሻ አንዲ›› እንዲዘዋወር፤ 3ኛ
ሬጅመንትም የ5ኛ ሁለት ሻምበሎች የተወሰነ ርቀት ድረስ ሸኝተውት ወደ ስቴዲየሙ እንዲሄድ ትዕዛዝ ይተላለፋል፤ ለጉዞ የተመረጠው
ጎዳና ደግሞ በመረጃ ባለሙያዎች ተጠንቶ ሰላማዊ መሆኑ አስቀድሞ ተረጋግጧል፡፡ ይሁንና ሁለቱ ሻምበሎች የሽኝት ተልዕኮዋቸውን
ጨርሰው ሲመለሱ ‹‹ሰላማዊነቱ›› በመረጃ መኮንኖቹ የተመሰከረለት መንገድ ዱብዳን ይዞ ጠበቃቸው፤ በጎዳናዎቹ ዳርቻ አድፍጠው
የነበሩ የአልሸባብ ተዋጊዎች ድንገት መብረቃዊ ጥቃት ሰንዝረው፣ በጥቂት ደቂቃዎችም ከ40 በላይ ወታደሮች ሙትና ቁስለኛ እንዲሆኑ
አድርገዋል፤ ወደ ስታዲየም በማቅናት ላይ ከነበረው የ3ኛ ሬጅመንት ወታደራዊ ቡድን ውስጥም በአንድ ሻምበል የሚመራ አንድ ስታፍ
በኦራል መኪና ላይ እንደተጫነ በከባድ መሳሪያ ተመትቶ ሁሉም አልቀዋል፤ ስታዲየሙ ጋ መድረስ የቻለው ሠራዊትም ቢሆን፣ 7ኛ
ሬጅመንት ከቡሬ በአንቶኖቭ ተጭኖ ከሶስት ቀን በኋላ ደርሶ ነፃ እስኪያወጣው ድረስ በአልሸባብ ታጣቂዎች የከበባ ቀለበት ውስጥ
ወድቆ ምግብና ህክምና ማግኘት ባልቻለበት በህይወትና በሞት አጣብቂኝ ተጠፍንጎ እንደነበረ የፋክት ወታደራዊ የመረጃ ምንጮች
ይናገራሉ፡፡

 መከላከያ ሠራዊቱ ከአሳቻ ቦታ ድንገት ከሚሰነዘርበት ጥቃት በተጨማሪ ሶማሊያን ለቅቆ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ሁሌ በየቀኑ
ምሽት ከ12 ሰዓት ጀምሮ እስከ 4 ሰዓት፤ እንዲሁም ከሌሊቱ 10 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ ምሽግ ውስጥ ደፈጣ ይዞ በስጋት
ያሳልፍ እንደነበረ እቦታው ከነበሩት ውጪ የሰማ ማንም አልነበረም፤ ሌላው ቀርቶ ምግብና ውሃ የማመላለሱ ሥራ ከምሽቱ 2 ሰዓት
በኋላ ጨለማን ተገን በማድረግ ነበር የሚከናወነው፡፡ ግና፣ ጥንቃቄው የዚህን ያህል ጠንካራ ቢሆንም እንኳ በየዕለቱ ከመቁሰልና
ከመሞት አደጋ ሊታደጋቸው አለመቻሉ መስዋዕትነቱን ዘግናኝ ማድረጉን ማስረጃዎች ያስረግጣሉ፡፡

 እነሆም አቶ መለስ ዜናዊ ሠራዊቱ የደረሰበትን ጉዳት በተመለከተ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለትን ጥያቄ ‹ሪፖርት
የማቅረብ ግዴታ የለብኝም› በሚል እብሪት ዳምጦት ቢያልፍም፣ የ‹‹ፋክት›› ምንጮች ሶማሊያ ከዘመተው የኢትዮጵያ ሠራዊት፣
በአብዛኛው ሊባል በሚችል ደረጃ ከአንድ ጋንታ አራት ወይም አምስት ሰው ብቻ ያለጉዳት መትረፉን ያስታውሳሉ፡፡

 የተጭበረበረ ሠራዊት
 በመከላከያ ውስጥ አንድ የተለመደ ተግባር አለ፤ ይኸውም በግዳጅ ወይም በዘመቻ መልክ የሚከወን ሥራ ከሌለ በቀር ሠራዊቱ
ብዙውን ጊዜ ረብ-የለሽ የሆኑ ጉዳዮችን ሳይቀር እያነሳ ሲገማገም የሚውልበት ተዘውታሪ ተግባር፡፡ የዚህ መነሾ ደግሞ አንድም አምባ-
ገነን አገዛዝ በምንም ሁናቴ ውስጥ ከስጋት ነፃ ሊሆን አለመቻሉ፤ ሁለትም በፍለጠው-ቁረጠው ሥርዓት አራማጆች ዘንድ የመንፈስ
አባት ተደርጎ ከሚታየው ኒኮሎ ማኪያቪሊ ‹‹ሥራ የፈታ ሰራዊት፣ ተንኮል ይጠነስሳል›› አስተምህሮ በመነሳት ይመስለኛል፡፡ በርግጥ
እዚህ ጋ ለማውሳት የፈለኩት ምንጊዜም በአሰልቺዎቹ የግምገማ መድረኮች ላይ የሠራዊቱ መተዳደሪያ ደንብ እንዲነበብ ከመደረጉ ጋር
የሚያያዝ ነው፡፡ በደንቡ ውስጥ ከተካተቱ አንቀፆች መሀል ደግሞ፣ አንድ አባል ከሀገር ውጪ ከሶስት ወር በላይ ካገለገለ ደሞዙ በሰላም
አስከባሪ ደረጃ በዶላር እንደሚከፈለው የሚገልጽ አንቀፅ ይገኝበታል፡፡ ይህንን አሳፋሪ መንግስታዊ ሽፍትነት ወደ ሶማሊያ የአግአዚ
ኮማንዶ አባል ሆኖ የዘመተው መሀመድ ሽኩር (ስሙ የተቀየረ) እንዲህ በማለት ይገልፀዋል፡-

“ደንቡን ብዙ ጊዜ ስለተወያየንበት እያንዳንዳችን ጠንቅቀን እናውቀዋለን፤ በተለይ ደግሞ ይህች አንቀፅ በሁላችንም አእምሮ ውስጥ
በቀዳሚነት ሰርፃ ነበር፡፡ ከዚህም አኳያ ሞቋዲሾ ገብተን ልክ ሶስት ወር እንዳለፈን በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት በዶላር እንደሚከፈለን
እርግጠኞች በመሆናችን አብዛኞቻችን የቋጠርናትን ጥሪት በሙሉ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስናባክነው ምንም አላሳሳንም፤ ሆኖም
ከሶማሊያ ልንወጣ ሁለት ወር ሲቀረን አንቀጿ ከመተዳደሪያ ደንባችን ላይ ተፍቃ የሀገር ሉአላዊነትን ለማስከበር በውጭ ሀገር የሚደረግ
የግዴታ ዘመቻ የተለየ ክፍያ እንደማይኖረው በሚገለፅ ሌላ አንቀፅ እንደተቀየረች ሰማን፤ እጅግ በጣም ከፋን፡፡ እንግዲህ እግዜር
ያሳይህ! በማይመለከተን ጦርነት ያን ያህል ግዙፍ መስዋዕትነት ከፍለን፣ ለሁለት ዓመት ገደማም በከባድ ስጋት ውስጥ አሳልፈን
በተአምር በህይወት ከተመለስነው ላይ ገንዘብ ለመንጠቅ ሲባል አዲስ ደንብ ማውጣት ምን አይነት ሀፍረተቢስነት ነው?! መቼም ከዚህ
የበለጠ አይን ያወጣ መንግስታዊ አጭበርባሪነት የትም ይገኛል ብዬ አላምንም!!”

 ሌላው በእጅጉ አስገራሚ የሆነው ጉዳይ በሶማሊያ የተለያዩ አካባቢዎች ለተሰዉ አባላት ዶሎ ላይ የመታሰቢያ ሀውልት ለማቆም
ሠራዊቱ ገንዘብ እንዲያዋጣ የተጠየቀበትን አውድ ይመለከታል፤ በርግጥ አጀንዳው ከመከላከያ ሚኒስቴር ቢመጣም ሠራዊቱ ሃሳቡን
ደግፎ፣ ነገር ግን ሀውልት ሳይሆን፣ ከመታሰቢያነቱ በተጨማሪ ሀገርንም ትውልድንም እንዲጠቅም ትምህርት ቤት ወይም ጤና ጣቢያ
መሰራት አለበት የሚል አቋም ይይዛል፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በሃሳቡ ይስማማና መዋጮውን ተመን ያወጣለታል፤ በዚህም ተራ
ወታደር ብር 100፣ ምክትል አስር አለቃ ብር 150፣ አስር አለቃ ብር 200…. እያለ ቀጥሎ እያንዳንዱ በማዕረጉ ልክ በተተመነበት መሰረት
3

እንዲያዋጣ ይደረጋል፤ ገንዘቡም ይሰበሰባል፤ በ2000 ዓ.ም አጋማሽም አቶ መለስ ግንባታው ይካሄዳል የተባለበት ቦታ ተገኝቶ የመሰረት
ድንጋይ ያስቀምጣል፤ ግና፣ ዛሬም ድረስ አንድም የተሰራ ነገር የለም፤ ከሠራዊቱ የደም ጠብታ የተዋጣውንም ገንዘብ መንግስት
ይብላው፣ አዛዦቹ ለግል ጥቅማቸው ያውሉት ማንም አያውቅም፤ ጦሩም ቢሆን በማይታይ ስውር መዳፍ ተጨምድዶ በፍርሃት ቆፈን
ስለተያዘ እንኳን ከኪሱ የለገሰውን ጥቂት መቶ ብር ቀርቶ፣ የልፋቱን ሕጋዊ ክፍያም ተከልክሎ ትንፍሽ ለማለት አልደፈረም፡፡

 ደህና ሰንብቺ ሶማሊያ
 በ2000 ዓ.ም አቶ መለስ ዜናዊ ሶማሊያ ሄዶ የሠራዊቱን ተወካዮች ሰብስቦ ባነጋገረበት ወቅት በዋናነት የቀረበለት ጥያቄ እንዲህ
የሚል ነበር፡- ‹በሰው ሀገር እየደረሰብን ያለው መከራ እጅግ አስመርሮናልና፣ ከዚህ ቦታ በቅያሪም ቢሆን አስወጡን›፤ ጠ/ሚንስትሩም
በአጭር ጊዜ ውስጥ በሌሎች የሠራዊቱ አባላት እንደሚቀየሩ ቃል ገብቶላቸው ወደ ሀገሩ ተመለሰ፤ በቃሉም መሰረት በ43ኛ ክፍለ ጦር
ተተኩ፤ ይሁንና ጥቂት ወራት ቆይቶ 43ኛም ከሶማሊያ ምድር ድንገት ጠቅልሎ እንዲወጣ ተደረገ፡፡ ለዚህ እርምጃ መንግስት የሰጠው
ሰበብ ‹ብቻችንን መዋጋቱ በቃን፤ የሌሎች ሀገራት ሰላም አስከባሪዎች አብረውን ካልገቡ በቀር አንመለስም!› የሚል መሆኑ አንድ ሰሞን
ከልብ የሚሳቅበት ቀልድ ሆኖን ነበር፡፡ ምክንያቱም ከሁለት ዓመት በፊት ‹የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ሕብረት› የተባለው አክራሪ ኃይል
‹የጀሀድ ጦርነት አውጆብናል፣ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓታችንን በኃይል ለመናድ የተነሱ ቡድኖችን አሰልጥኖና አስታጥቆ እየላከብን ነው›
ከማለትም አልፎ ከ‹‹ሉዓላዊ››ነት ጥያቄ ጋር አያይዞ ማስጮሁን ዘንግቶት፣ ‹የጎረቤት ሀገርን ሰላም ማስከበር የእኛ ብቻ ዕዳ አይደለም›
ወደሚል መገልበጡ ነው አስቂኝ የሆነው፡፡ መቼም እንዲህ አይነቱ መከራከሪያ ከኢትዮጵያ መንግስት ይልቅ ዘመቻውን ‹ቅጥረኝነት
(ተላላኪነት)› አድርገው ሲተቹ የነበሩ ሀገራትንም ሆነ ምሁራንን እውነተኝነት ያስረገጣል፤ ይህ ደግሞ የሽብር ፖለቲካን ገዥው-ፓርቲ
ለሥልጣን ማራዘሚያ እየተጠቀመበት እንደሆነ በግላጭ የሚያሳይ ነው፡፡ በተቀረ የአሜሪካንን ተልዕኮ ለመፈፀም ንፁሃንን በፈንጅ
ማጋየትም ሆነ የሰው ሀገር መውረር-የፅድቅ ተግባር፤ ወደ ኤርትራ መሄድ ደግሞ-ሽብርተኝነት የሚሆንበት ሕግ በምንም መልኩ
ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡ በነገራችን ላይ መከላከያ ሠራዊቱ ወደ ሶማሊያ የመግባቱ ክሽፈት አልሸባብን እንደፈጠረ ሁሉ፤
በድንገት ጥሎ የመውጣቱ ካልአዊ ስህተትም ይህንን ኃይል ዛሬ ለደረሰበት አስፈሪነት አብቅቶታል ብዬ አምናለሁ፤ ምክንያቱም በአፍሪካ
ሕብረት ስም የተለያዩ አገራት ሰላም አስከባሪዎች በድጋሚ ወደ ሶማሊያ እስከገቡበት ድረስ፣ ሀገሪቱ ከሞላ ጎደል በእጁ ላይ በመውደቋ
ራሱን ለማጠናከርና ከተለያዩ ሀገራት ከመጡ አደገኛ አሸባሪዎች ጋር ዓላማውን ለማሳካት ምን ማድረግ እንዳለበት በጠረጴዛ ዙሪያ
የሚመካከርበትን በቂ ጊዜ ጨምሮ፣ የተትረፈረፈ ሀብት እንዲያገኝ አስችሎታልና ነው፡፡

 የሆነው ሆኖ ሠራዊቱ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል ሳሞራ የኑስ በየዕዙ እየዞረ ማነጋገሩ ይታወሳል፤
የምዕራብ ዕዝ ተወካዮችን ባህር ዳር በሚገኘው ጦር ሰፈራቸው በሰበሰበበት ወቅት ከቀረቡለት ጥያቄዎች መካከልም ሁለቱን ለማሳያነት
ልጥቀሳቸው፤ የመጀመሪያው፡-

‹‹በላይቤሪያም ሆነ በሶማሊያ የዘመትን የሠራዊቱ አባላት በመተዳደሪያ ደንባችን መሰረት ተገቢውን ክፍያ አላገኘንምና እርስዎ መፍትሔ
ይሰጡናል ብለን እናምናለን?›› የሚል ነበር፤ ጄነራሉም በተለመደው አሿፊ አነጋገሩ፡-
‹‹እውነት ነው፣ ከእናንተ ላይ ያስቀረነው ገንዘብ አለ፤ ዛሬ ብትጠይቁን አንሰጣችሁም፤ ወደፊት ግን በብድር መልክ ልትወስዱት
ትችላላችሁ!››
ሁለተኛው ጥያቄም ተከተለ፤
‹‹ኑሮ በጣም ከብዶብናልና፣ መንግስት ደሞዝ ይጨምርልን?››፤ ሳሞራም የፌዝ ሳቅ ባጀበው ድምፅ እንደሚከተለው መለሰ፡-
‹‹እንዴት እንዲህ ትላላችሁ? ለስላሳ መጠጥ እንኳ በብር ከሃምሳ አይደለም እንዴ የምናቀርብላችሁ?››፤ አሁን ሠራዊቱ ትዕግስቱን
በመጨረሱ ከፍተኛ የተቃውሞ ድምፅ አሰማ፤ ይኼኔም ከጎኑ መድረክ ላይ የተቀመጠውን የዕዙን አዛዥ ስለሁኔታው ጠየቀው፤
እርሱም፡-
‹‹አይ! በሰባት ብር ነው የምናቀርብላቸው›› በማለት አረመው፤ ይህም ሆኖ ጄነራል ሳሞራ የኑስ በሚመራው ሠራዊት ብሶት ላይ ዳግም
ከማላገጥ አልታቀበም፡-
‹‹እኔ ከፍዬ ስለማልጠጣ ይሆናል ዋጋውን ያላወኩት!››

…ዛሬም በሚያገባውም በማያገባውም ጉዳይ የከበደ መስዋዕትነት እየከፈለ ያለው የሀገር ዘብ በከፋ ድህነት እየማቀቀ መሆኑ እውነት
ነው፤ በሐምሌ ወር ለመንግስት ሠራተኞች ይደረጋል የተባለው የደሞዝ ጭማሪም ከርታታውን ወታደር አለማካተቱ ርግጥ ነው፡፡ ከዚህ
የከፋው ደግሞ አገዛዙ ሠራዊቱን እንደግል አገልጋዩ ቆጥሮ በሕገ-ወጥ ድርጊት ላይ ጭምር እንዲሳተፍ ማስገደዱ ነው፡፡ ለማስረጃ
ያህልም በሰላማዊ የምርጫ ውድድር ሳይቀር ጭቁን ወንድም-እህቶቹ ላይ አፈ-ሙዙን እንዲያዞር ማድረጉን ማስታወሱ በቂ ነው፡፡
ይህንንም እንደ ሕጋዊ ተግባር በመውሰድ አቶ በረከት ስምዖን በምርጫ 97 የተቃዋሚ ፓርቲ የአመራር አባላትን እንዳስፈራራበት
ያለይሉኝታ “የሁለት ምርጫዎች ወግ” በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉ እንዲህ በማለት ነግሮናል፡፡

“(ተቃዋሚዎችን) አንዳንዴ በቀላሉ ይገባቸው እንደሆነ ብለን ሠራዊቱ በአንድ ወቅት የኢህአዴግ መንትያ ፍጥረት እንደነበረና ክፉ ነገር
ከመጣ አሰላለፉ ከማን ወገን እንደሚሆን የሚገነዘብ መሆኑን ብንነግራቸውም ከልባቸው አልጣፍ ብሏል፡፡” (ገፅ 119)

 በርግጥ ይህ አይነቱ ኢ-ፍትሀዊነት ኢህአዴግ በሥልጣን ኮርቻ ላይ እስከተፈናጠጠ ድረስ መቀጠሉ አይቀሬ መሆኑ እውነት ነው፡፡
ህይወቱን ለመስጠት የማያመነታ ጀግና ወታደር፣ ያውም ጠብ-መንጃ ታቅፎ በሥርዓታዊ ፖሊስዎች ክሽፈት እስኪጠግብ እንኳ
መብላት ከማይችልባቸው ጥቂት ሀገራት መካከልም የእኛይቱ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም መሆኗ ሌላ እውነታ ነው፡፡

 ክብር ለጀግናው የኢትዮጵያ ሠራዊት!! ይቀጥላል 

No comments:

Post a Comment