Monday, June 2, 2014

በአባይ ጉዳይ ላይ "አባይ"

በአባይ ጉዳይ ላይ "አባይ"
(ዮሴፍ ወርቁ ደገፌ)

ታዋቂው ባለቅኔ የአለም ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን “አባይ ! አባይ ! አባይ ! ለሀገሩ ባእድ--ጠላት፤ ለውጭ ሲሳይ--በረከት፤ ” በማለት
ግኡዝን ወንዝ ሲወቅስ፤ አባይን ለሀገሩ---ጠላት፤ ለውጭ ግን ሲሳይ/በረከት ያደረገውን የእኛን ስንፍናም ባለቅኔው
በውስጠ-ወይራ (ቅኔ) ሸንቆጥ በማድረግ አልፎአል።

በአለም ላይ በርዝመቱ አንደኛ የሆነውን (6,400 Mile) ታላቁን የአባይን ወንዝ መሰረት/ምንጭ አድርጎ የተገነባው የግብፅ ኢኮኖሚ
ዋልታና-ምሰሶ የሆነው የአስዋን ግድብ ከተገደበና ለግብፅ መጠነ ሰፊ ጥቅም መስጠት ከጀመረ ከ46 አመታት በላይ
እንደሞላው ታውቁ ነበርን? የአስዋን/አባይ ግድብ ለግማሽ ምዕተ አመት ያህል ለግብፅ ከፍተኛ ጥቅሞችን ሲያበረክት፤ ኢትዮጵያ
በተባለችው ምድር ላይ የሚኖረውና የአባይ ምንጭ የሆነው ህዝብ ግን መፅሀፍ ቅዱስ እንደሚገልፀውና እንደ አብዛኛው ህዝብም
የሁለት ሺ አመታት የክርስትና እምነት መርህ መሰረት “እንደ እባብ ብልህ እንደ እርግብ የዋህ ሁን” እንደተባለው ሆኖ ያልተገኘ
“ምስኪን” ህዝብ ነው። ርግብነቱ(?) አለን ብንል እንኳን፤ ብልህነቱ የታል? ፈጣሪ የሰጠውን በረከት ሳይጠቀምበት ከርሃብም ሳይወጣ
ለዘመናት በድህነትና በጦርነት አዙሪት ውስጥ አለና።

የጦርነትና ድህነትአዙሪት

ኢትዮጵያ በረጅም ዘመናት የእርስ በርስ ጦርነት ታሪክዋ ያፈራችው ጦረኛ መሪዎችን፤ ርሀብ እና ድህነት (በኢኮኖሚ የደቀቀ ህዝብ
/ሀገር) እንጂ ልማትና ብልፅግና አልነበረም። በግብፅ ወይም በሌሎች ሳይሆን በራሳችን ችግር ምክንያት፤ አባይንም ይሁን ሌሎች
በረከቶቻችንን ለመጠቀም ባለመቻላችን፤ ለዘመናት በመባከን የተራቆትን ህዝቦች ነን። ስለሆነም እስከዛሬ ድረስም በአለም ፊት
ችጋራምና-ተመፅዋች፤ መከረኛና-ስደተኛ፤ የርሀብ (ድርቅ) እና የጦርነት ጥሩ ማስረጃ ሀገር ሆነን እንገኛለን።

በዘመናት የጦርነት አዙሪት እኛ ስንተላለቅ፤ “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” እንዲሉ አባይንም ይሁን ሌሎች ወንዞቻችንን፤ የተፈጥሮ
ድንግል መሬታችንን፤ የሰውሀይል ሀብታችንን፤ ...ሳንጠቀምባቸው በድህነት አዙሪት (Vicious Circle of Poverty)
የግሎባላይዜሽን ዘመን ላይ ደርሰናል። እህል ሊሆን ባልቻለና ጥቅም ባልሰጠን ታሪክም በሜዳ ላይ ስንፎክርና-ስናቅራራ፤ የበረከት
ምንጮቻችን ለዘመናት በከንቱ ባከኑ። ከዚህ አንጣር ኢትዮጵያ፤ ርሀብን እንደ ብልፅግና ቆጥራ፤ ዜጎችዋን በመከራና በእርዛት
ለዘመናት በመፍጀትዋ ከንቱነትዋን ያረጋገጠች አገር ስትሆን፤ ለውጭው አለም ግን ሲሳይና በረከት የመሆንዋን እንቆቅልሽ በእፍረትም
በድፍረትም መናገር ያስፈልጋል።

አባይ ለግብፅ!

የግብፅ አስዋን ግድብ አስር ቢሊዮን ኪሎዋት ሰዓት በአመት የሚያመነጭ አቅም ያለው ሲሆን፤ ከ46 አመታት በፊት ግንባታው አንድ
ቢሊዮን ዶላር እንደፈጀ ተጠቅሶአል። የአስዋን ግድብ አንድ መቶ አስራ አንድ ሜትር ጥልቀት፤ አራት ኪሎ ሜትር የወርድ
ስፋትና፤ ሃያ ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል ርዝመት ያለው ሰው ሰራሽ ታላቅ ሀይቅና የውሀ ሀብት ክምችት የፈጠረላቸውም መሆኑን ግብፆች
በኩራት ይገልፃሉ። በቀድሞው የግብፅ ፕሬዜዳንት ጋማል አብዱል ናስር ስም የተሰየመው የ“ናስር” ሰው ሰራሽ ሀይቅ ከዚህ በታች
የተዘረዘሩትን ጥቅሞች እየሰጠ እንደሚገኝና የአባይ ወንዝ ለግብፅ ብቻ እንደተፈጠረ፤ በዚህም ደግሞ እንደሚቀጥል የግብፆች ሀሳብ
የትየለሌ ነው።

አባይ ለግብፅ ከሚሰጣቸው ዋና ዋና ጥቅሞች ውስጥ አንዱ በየአመቱ አርባ ሚሊዮን ቶን ደለል ለም አፈር ከኢትዮጵያ ምድር
አግበስብሶ ለግብፅ ተፈጥሮአዊና ዘመናዊ የግብርና ልማት ከፍተኛ በረከት መስጠቱ ነው። በዚህም የሰሜኑ ኢትዮጵያ የሀገራችንን ክፍል
የለም አፈር ደሀ አድርጎታል። ከዚህም የተነሳ ነው አባይ ወንዝ ለኢትዮጵያ እንደ ባእድና ጠላት የተቆጠረው። አባይ ለግብፅ ቢያንስ
በሚከተሉት ስምንት የኢኮኖሚ መሰረቶች ማገልገሉን መረዳታችን ሳይሆን የሚጠቅመን፤ እኛስ? የሚል ተገቢ እልህና ቁጭት
ሲያድርብንና ለመስራትም ስንችል ብቻ ነው።

1/ በሀይድሮ (የውሀ ሃይል) ኤሌክትሪክ ምንጭነት
2/ የአሳ ሀብት ማስገሪያ (አሳ ማርቢያና መሰብሰቢያ) ሀይቅነት
3/ በውሀ ትራንስፖርትነትና የመዝናኛ አገልግሎት ሰጭነት
4/ በዘመናዊ መስኖ የግብርና ልማት
5/ አርባ ሚሊዮን ቶን ደለል ለም አፈር (Fertile/Organic Soil)
6/ በምግብና በመጠጥ ውሀ አገልግሎት 7/ በግንባታና የተለያዩ ውሀ ስራዎች አገልግሎት
8/ በረሀማነትን የመቀነስ አገልግሎት ...ዋነኞቹ ናቸው

የኢትዮጵያ በድንገት መባነን!

ኢትዮጵያ ዛሬ ድንገት በመባነን አባይን ብትገነባና እንደተባለውም 6,000 (ስድስት ሺ) ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ብታመነጭ ግብፅ
ትጎዳ ይሆን? "የማይመስል ነገር ለ --- አትናገር” የሚባለው ተረት ግብፅ ውስጥ ለመኖሩ አላውቅም...ነገርግን የግብፅ አካሄድ
ያስታውቃል...ግብፅ የውሃ እጥረት እንደማያጋጥማት የታወቀና የአለም አቀፍ የኤክፐርቶችም ቡድንም ያረጋገጠው ጉዳይ ሆኖ ሳለ፤
የግብፅ ጫጫታ ከየት የመጣ ነው? ግብፅን ይህን ያህል ያሰጋት ከቶ ምንድን ይሆን? ግብፅ ሊፈጠርባት የማይችለው ችግር አይደለም
ያሰጋት---ይልቁንም---ምናልባት ኢትዮጵያ ወደፍት ሊኖራት የሚችለው ፖለቲካዊ ዲፖሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ታላቅነት ግብፅን
ስጋት ገብቶአት ይሆን? ኢትዮጵያ ግን እንዲያውም ግብፅንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ እንምትሰራ ነው የታመነው፤ ይኸውም 1ኛ/
ሐይድሮ ኤለክትሪክ በማቅረብ 2ኛ/ በአፈር ደለል እየተሞላ የሚያስቸግራትን የአስዋን-ግድብዋ ንጡህ ውሀ በመላክ ናቸው ወዘተ ።
ዝርዝሩን ለባለሙያዎቹ እተወዋለሁ።

በአባይ ጉዳይ የእኛ አመለካከት

ኢትዮጵያ ሀገሬ !!!…ህዝባችን ህዝባችን !!!…ኢትዮጵያዊነት !!!...ወዘተ እያልን የምንቆጭ ሁሉ፤ የአባይ ጉዳይ ኢኮኖሚያዊ ብቻ
ሳይሆን ጂኦ-ፖለቲካዊ እንደሆነና ከእኛም አልፎ አፍሪካ ሀገራትንና እንዲሁም በአረብ-እስራኤል ላይም ትልቅ ፖለቲካዊ
ተፅእኖ እንዳለው ማስተዋል የመጀመሪያው ታላቅ መረዳት ነው። አባይ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ታላቅነት የሚያሳድግ
ብቻ ሳይሆን ትልልቅ ሁለገብ ጠቀሜታዎችን የሚያመጣ (To mention a few, besides the vast economic gains
(benefits), the Ethiopian Nile dam brings about a national pride and greater
impact on the making of Ethiopian Unity (as a nation). Moreover, it creates big
socio-economic ties among Eastern African nations which ultimately helps the
eradication of poverty in the sub-Saharan African countries. Most importantly, the
Ethiopian Blue Nile dam creates sustainable political stability or regional peace in
that volatile part of the world etc.) መሆኑን መረዳት ሁለተኛው ታላቅ ግንዛቤ ይሆናል። ደግሞም አባይን እንጠቀምበት
ብሎ ለመስራት መነሳት ሶስተኛውና ከሁሉ የሚልቀው ጠቀሜታ ያለው ተግባራዊ ስራ ነው። በመሆኑም የውስጥ/የጋራ ችግራችንን
(አለመግባባታችንን) በጋራ በመፍታት ለአባይ ጉዳይ በህብረት ካልተነሳን በስተቀር፤ በግሎባላይዜሽን ዘመን ላይ፤ እንደ ሰው እያሰብን
የምንኖር ሰዎች ለመሆናችን ጥርጣሬ ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያውያን በርግጥ የሰብእና ጉድለት (Personality Disorders)
እንደሌለብን በሚገባ መፈተሽ ያለበት ይመስለኛል።

ህዝባችንን ከሺ አመታት ድንቁርናና ርሀብ ከማውጣት ይልቅ ምናልባትም የግል ስምና ጥቅም ወይም የፖለቲካ - ዝና በልጦብን፤
በታሪካችን እንደተለመደው እርስ በርስ መቆራቆዝ አሁንም ብንቀጥል፤ በእኛ ለመጠቀምና የእኛን ሀብት እየበላ ለመኖር የሚፈልግ ሁሉ
የምንጨራረስበትን መሳሪያ ያቀብለናል። እዚህ ላይ አንባቢ መረዳት ያለባችሁ ነገር ቢኖር፤ ለአባይ ግድብ ስራ ኢትዮጵያ ምንም አይነት
የውጭ እርዳታ እንዳታገኝ ግብፅ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ድል ማግኘትዋን ልብ በሉ። ከዚህ የተነሳም ነው ኢትዮጵያ ግድቡን በራሴ
ወጭ እሰራለሁ በማለት የምትውተረተረው።

በቅድሚያ ኢትዮጵያ አባይን ለብቻዬ ልጠቀም አላለችም። ኢትዮጵያ ያለችው “አንድ ቤተሰብ በቤቱ ውስጥ ምግብ አዘጋጅቶ
ለመብላት፤ ጎረቤቱን ማስፈቀድ አያስፈልገውም” ነው። ኢትዮጵያ አባይን በመገደብ የዘመናት ድሀ ህዝብዋን ለመጥቀም፤ የቅርብም
ይሁን የሩቅ ጎረቤትዎችዋን ማስፈቀድ ፈፅሞ አይገባትም ነው ባጭር አገላለፅ። ምናልባት አብረን ሰርተን እንብላ በማለትም ግብፅን
ጋብዛለች። ለአባይ ምንጭ/መነሻ ያልሆነችው ግብፅ ይህን ያህል በአባይ የውሀ ሀብት የመጠቀም መብት ካገኘች፤ የአባይ ዋነኛ ምንጭ
የሆነችው ኢትዮጵያ እጅግ ዘግይታም ቢሆን፤ የውሀ ሀብትዋን ዛሬ ልትጠቀምበት ስትሞክር፤ ግብፅ “እንዴት ተደርጎ?” በማለት
መፎከርዋ ጎረቤት ጎረቤቱን ያንተን ቤት የማስተዳድረው እኔ ስለሆንኩ በቤትህ ለምትበላው ምግብ እኔን አስፈቅድ---ይመስላል የግብፅ
አቀራረብ። እኔን የሚገርመኝና የሚያሳዝነኝ የግብፅ ማንኛውም አይነት ፉከራ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ የውሀ ሀብትዋን ለመጠቀም 3,000
አመታት ሙሉ ወደ ሁዋላ የመቅረትዋ ጉዳይ ነው።!

የግብፅ ፖለቲከኞች ግልብ ሀሳብ

የግብፅ ፕሬዜዳንት ሙርሲ የካቢኔ አበላትና የፖለቲካ መሪዎች ያደረጉትን ስብሰባ በተለያዩ ቻናሎች ላይ ተመልክተን ከሆነ
የሚያስገርምና የማስፈራራት ውይይት ማድረጋቸው፤ ከላይ ያለውን ሀሳቤን የሚያጠናክር ነው። ከውይይታቸው ውስጥ የሚከተለው ባጭሩ ይገኝበታል “ኤምባሲያችን በስለላ ስራ በመሰማራት የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ያልተረጋጋ ስለሆነ ጣልቃ እየገባን
ማተራመስ አለብን”....,"ከኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ ከ35% በላይ የሆነውን የሚወክለው ተቃዋሚ ሀይል (ኦነግ)ን በመጠቀም ግድቡ
እንዳይሰራ በሀይል ማደናቀፍ አለብን”,...”ኤርትራን-ጅቡቲንና-ሶማሊያን የሚያካትት ትሪያንግል አክሲስ ሰርተን ኢትዮጵያን ማጥቃትና
ማዳከም አለብን”,...."ሁሉንም አማራጮች አድርገን ካቃተን ደግሞ ሀይል በመጠቀም ግድቡን ማውደም አለብን"....ወዘተ
የመሳሰሉትን ጠንካራና ነገር ግን ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ብስለት የሌላቸውን ግልብ ሀሳቦችን ሲወያዩ ነበር የተስተዋሉት። ....
("ኢትዮጵያ ማለት የግብፅ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን ዘወትር የሚያሸንፋት ሀገር"...ወዘተ በማለት ሲቀለድም ሁሉ ነበር) እንዲያውም
ፕሬዜዳንት ሙርሲ ስለምትሰጡት ሀሳብ ጥንቃቄ አድርጉ፤ ውይይታችን በቀጥታ ስርጭት (Live) እየተላለፈ ነውና በማለት
ባያቋርጡአቸው ኖሮ፤ የግብፅ ባለስልጣናትን የከፋና ጥበብ የጎደለውን ውይይት በተጨማሪ በተመለከትን ነበር።

"ከኢህአዴግ ያነሰ የአገር ስሜት" (ዶ/ር መረራ ጉዲና)

ወደ ስምምነት ከሚያመጡን ወቅታዊ አባባሎች ውስጥ አንዱ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በዶ/ር መረራ ጉዲና የተጠቀሰው “...የአገራችን
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለውጭ ሃይል መጠቀሚያ ለመሆን ይዘጋጃሉ የሚል ግምት የለኝም...”, “...አባይን በሚመለከት ከኢህአዴግ ያነሰ
የአገር ስሜት አላቸው ብዬ አልገምትም...” ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አባባል ነው። ስለሆነም “ከእኔ በላይ አዋቂና ለሀገር አሳቢ ለአሳር
ነው” ወይም “ከእኛ ወዲያ ፉጨት አፍ ለማሞጥሞጥ ነው” ከሚባለው ጎጂ ሀገርኛ አባባል ነፃ በመውጣት የመቻቻልና የመደራደር
ተስማምቶም ለመስራት ( for Politic is the Science of Compromising) በተግባር እንነሳና አባይን ብቻ ሳይሆን
ሌሎችንም የልማት ስራዎችን እንስራ። “የእኔ መንገድ ብቻ ትክክል ነው” (My Way is the Highway) የሚለው ያረጀና
ያፈጀ በግሎባላይዜሽን ዘመን ከማይሰራ አስተሳሰብ “የጋራ ውሳኔ ትክክል ነው” በሚለው አስተሳሰብ መተካት ያለበት አሁኑኑ ነው።

የቱ ይቅደም? ዲሞክራሲ ወይስ ልማት?

Though few autocratic countries like China have shown economic development in the past few
decades, my understanding is that, democracy and sustainable economic development are
inseparable. ይሁንና ከአባይ ግድብ ግንባታ በፊት “ሰብአዊ መብት ይከበር !!!”,... "ዲሞክራሲ ይገንባ !!!”...የምንልም ሰዎችም
እንሁን፤ ወይሞ ደግሞ "ታላቁን ጠላት ድህነትን አስቀድመን እንዋጋ !!! ” ... " ዲሞክራሲ እህል ከጠገብን በሁዋላ !!!”... የምንል
ሁላችን፤ የአባይ ግድብ ግንባታ ጉዳይ ያንድ ወገን (ግሩፕ) ወይም ፓርቲ ጉዳይ ሳይሆን፤ የሁላችንም የጋራ ጉዳይ ነውና፤ በአባይ ጉዳይ
ማንም ማንንም እንዳያገልል ሁላችንም እንጠንቀቅ። አጥርተንም እንመልከት አርቀንም ለትውልድ እናስብ ዘንድ ይገባል።

ስለሆነም ፖለቲከኛ ነኝ የምንል ሁሉ የግል አጀንዳንና በተለይም የእርስ በርስ ጥላቻንና ክፋትን በማስወገድ ለሀገር ልማትና ለህዝብ
አንድነት ሲባል በአባይ ግንባታ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ታላላቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ብሄራዊ መግባባት (National
Consensus) በመፍጠር በልዩነትም ቢሆን ባብላጫ ድምፅ ተስማምተን የሚገባውን እንናድርግ። ከፖለቲከኛነት የሀገር የበላይነትና
ልማት የህዝብ አንድነትም ይቅደም።

የልብ አይኖቻችንን እግዚአብሄር ያብራልን የሚል ፀሎት ብቻውን የእኛ ፈቃደኝነት ከሌለበት ከምኞት ያላለፈና ዋጋ የሌለው መሆኑን
እንወቅ። ያለ እኛ ፈቃድ እግዚአብሄርም ሊረዳ አይችልም። ህብረትና-አንድነት፤ ሰላምና-ልማት፤ ለምድራችን
የሚመጣው በእኛና በእኛ ፈቃድ (መስማማት) ብቻ ነውና።



ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
May 29, 2014 

No comments:

Post a Comment