Friday, June 13, 2014

“የቀድሞው ጦር” መጽሐፍ እንዴት ተፃፈ?


ስለሺ ቱጂ
ስለቀድሞው ጦር ታሪክ የሚያትት መጽሐፍ ታትሞ ገበያ ላይ ውሏል፡፡ መጽሐፉ በአገራችን ታትመው ከሚሰራጩት አብዛኛዎቹ
መጽሐፍት ጋር ሲነፃፀር ትልቅ የሚባል ነው፡፡ ሰባት መቶ አርባ ግድም ገፆች ያሉት ሲሆን ስለቀድሞው ጦር አመሰራረትና ዕድገት
እንዲሁም ስላሳለፋቸው ውጣውረዶችና ስለውድቀቱም ይተርካል፡፡ መጽሐፉን ያዘጋጁት ማለትም መረጃ በማሰባሰብና በማሳተም
የተሳተፉት የቀድሞው የኢትዮጵያ ምድር ጦር ሠራዊት ወታደሮችና ሲቪል ሠራተኞች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና
ሌሎች ግለሰቦች ታሪክ በማዘጋጀትና በማጠናቀር እንዲሁም የአርትዖት ስራ በመስራት ተሳትፈዋል፡፡ በመጨረሻም የታሪኩን ቅደም
ተከተል በመጠበቅ የመጽሐፍ ቅርፅ የሰጠውና የፃፈው፣ገስጥ ተጫኔ ነው፡፡
መጽሐፉን ለማዘጋጀት ሶስት ስልቶች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ይኸውም ቃለ መጠይቅ ማካሄድ፣የግል ማስታወሻዎችን መፈተሽና
ከመጽሐፍት መረጃዎችን መውሰድ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ከአምስት ከፍተኛ መኮንኖች ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉ ሲሆን የአስራሶስት
ከፍተኛ መኮንኖችን ማስታወሻዎችን አገላብጠዋል፡፡ አርባ ስምንት መጽሐፍት ደግሞ በዋቢነት ተጠቅሰዋል፡፡ የተጠቀሱት መጽሐፍት
በጦር መኮንኖች፣በሲቪል ግለሰቦችና በተቋማትም የተፃፉ ናቸው፡፡
መጽሐፉ በምሁራን የተፃፉ የታሪክም ሆነ የፖለቲካል ሳይንስ መጽሐፍትን እንደ ዋቢ አልተጠቀመም፡፡ የመጽሐፉ አዘጋጆችም ሆነ
ፀሐፊ ይህን አለማድረጋቸው በመጽሐፉ ዕውቀት ሰጭነት ላይ ዕንቅፋት ፈጥረዋል፡፡ በዚህ ረገድ አንድ ታላቅ መጽሐፍ በፍፁም
መታለፍ አልነበረበትም፡፡ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ የፃፉት The Ethiopian Revolution: War in the Horn of Africa የተሰኘው
መጽሐፍ የ30 ዓመቱን ጦርነት በተመለከተ በስፋትና በጥልቀት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ በአስር ምዕራፎች የሚተነትን ነው፡፡ በሰነድና
በቃለመጠይቅ ተደግፎ በእኚህ ምሁር የተፃፈው ይህ መጽሐፍ በበርካታ ምሁራን አድናቆትን ተችሯል፡፡ መጽሐፉ በውብና ማራኪ
እንግሊዝኛ ቋንቋ ከመፃፉም በላይ ወታደራዊ ትንተናውም አስደናቂ ነው፡፡ መጽሐፉ ከዋቢ መጽሐፍት ውስጥ ተካቶ እንደመረጃ
ሰጭነት ቢያገለግል ኖሮ ለመጽሐፉ ክብደት ይሰጠው ነበር፡፡ አለመደረጉ ያሳዝናል፡፡
ከመጽሐፉ ርዕስ ብንጀምር ‘የቀድሞው ጦር-1927-1983’ ስለምድር ጦር ብቻ ስለሆነ የሚያትተው ‘የቀድሞው ምድር ጦር-1927-1983’
ቢባል የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ጦሩ የተመሰረተበት ዘመንም ችግር አለበት፡፡ በግልፅ እንደሚታወቀውና መጽሐፉ ውስጥም እንደተገለፀው
የዘመናዊ ጦር ሠራዊት ጥንስስ የተጀመረው በ1910 ዓ.ም የክቡር ዘበኛ ጦር በቤልጂጎች ዕርዳታ ሲቋቋም ነበር፡፡ በርዕሱ ላይ ግን መነሻ
የተደረገው የቀዳማዊ ሃይለስላሴ ጦር ት/ቤት (በኋላ ገነት ጦር ት/ቤት) ከተቋቋመበት ከ1927 ዓ.ም አንስቶ ነው፡፡ ፀሐፊዎቹ ለምን
ይህን እንዳደረጉ አሳማኝ ምክንያት አላቀረቡም፡፡
መጽሐፉ በአምስት ክፍሎችና በአስራስድስት ምዕራፎች ተዋቅሯል፡፡ እያንዳንዱ ክፍል ዋና ርዕስ ያለው ሲሆን በስሩም ንዑሳን ርዕሶች
በምዕራፎች ተከፋፍለው ይገኛሉ፡፡ ክፍል አንድ በአንድ ምዕራፍ የጥንት ነገሥታት ሠራዊታቸውን እንዴት እንዳደራጁና አገር
የመመስረት ተልዕኳቸውን እንዴት እንደተወጡት ያሳያል፡፡ ከዚያም በመቀጠል የአፄ ቴዎድሮስን የተማከለና የተደራጀ ሠራዊት
የመመስረትን ጥረት በመቃኘት ከእንግሊዝ ጦር ጋር ገጥመው የደረሰባቸውን ሽንፈት ይተርካል፡፡ በአፄ ቴዎድርስ ዘመን የተጀመረው
አገር የመመስረትና ግዛት የማስፋት ተልዕኮ በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግስትም ቀጥሎ በትጥቅም ሆነ በሰው ሃይል ጠንካራ ጦር
እንደተመሰረተ ይተርካል፡፡ ከዚያም የአፄ ዮሐንስ ጦር ከግብፅና ከጣሊያን ጋር ገጥሞ በተደጋጋሚ በማሸነፍ የአገሩን ዳር ድንበር
እንዳስከበረ ያትትና ከአፄ ዮሐንስ ሞት በኋላ አፄ ምንሊክ የተሻለ ጦር አደራጅተው የጣሊያንን ጦር አድዋ ላይ ድል ነስተው
የአውሮፓውያንን የቅኝ ግዛት ትልም እንዳከሸፉና፤የኢትዮጵያን ግዛትም ወደ ደቡብ፣ምዕራብና ምስራቅ እንዳስፋፉ ያትታል፡፡
በመጽሐፉ ርዕስ ላይ ዕውቅና ባይሰጠውም በኢትዮጵያ ዘመናዊ ጦር በ1910 ዓ.ም በአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን እንደተመሠረተ
መጽሐፉ ውስጥ ሠፍሯል፡፡ አሰልጣኞቹም የቤልጂግ የጦር መኮንኖች ነበሩ፡፡ የወታደር ደሞዝም በአይነት መክፈል የተጀመረው ከዚህ
ጊዜ አንስቶ ነበር፡፡ የዘመናዊ ጦር ጥንስስ ከአድዋ ድል 22 ዓመታት በኋላ ተጀመረ ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም 12 ወጣቶች ወደ
ፈረንሳይ ሳን ሲር (St.Syr) ጦር አካዳሚ ተልከው ዘመናዊ ወታደራዊ ትምህርት ገብይተው ተመልሰዋል፡፡ ወጣት መኮንኖቹ ግን
ዘመናዊ ጦር እንዲያደራጁ ሁኔታውን ከማመቻቸት ይልቅ ቢሮ ውስጥ ተመድበው እንዲሠሩ ነው የተደረጉት፡፡ አልጋ ወራሽ ተፈሪ
መኮንን ዘመናዊ ጦር ከመሠረቱ ስድስት ዓመት በኋላ ማለትም በ1916 ዓ.ም ወደ አውሮፓ ሄደው ጣሊያንን በጎበኙበት ወቅት ጣሊያን
ወታደራዊ ዝግጅቷን ለማሳየት ወታደራዊ ሠልፍና የመድፍ ተኩስ ትርኢት እንዲመለከቱ አድርጋለች፡፡ በአንፃሩ ግን በኢትዮጵያ
የዘመናዊ ጦር ግንባታ ከጅምሩ ፈቀቅ አላለም፡፡ የዚህ ችግር ዋነኛው ምክንያት መሣፍንቱና መኳንንቱ ዘመናዊ አሠራርና ቴክኖሎጂ
በተጠናከረ መልኩ ወደ አገር እንዲገባ ፈቃደኛ አለመሆናቸውና አልጋወራሽ ተፈሪም የእነሱ ተባባሪ መሆናቸው ሊሆን እንደሚችል
መጽሐፉ አመላክቷል፡፡ ዘመናዊ ጦር በማደራጀት ረገድ የአልጋ ወራሹን ግማሽ ልብ መሆን አስመልክቶ አዘጋጆቹ የሚከተለውን ለስለስ
ያለ ሂስ አቅርበዋል፡- “ከአልጋ ወራሽነታቸው ጀምረው የኢጣሊያ ወረራ አስጊ እስከሆነበት ድረስ ለአስር ዓመታት ስልጣናቸውን
ለማማከል ሲደክሙ በመቆየታቸው ሌላውን አገራዊ ተግባር፣ይልቁንም የመከላከያ ሃይልን በዘመናዊ መልክ የማደራጀት ጅምራቸውን
ሊያፋጥኑት አልተቻላቸውም፡፡” (ገፅ 32) ጣሊያን ግን ወታደራዊ ዝግጅቷን እያፋጠነችና ለወረራም እያቆበቆበች መሆኗ ስለታወቀ
አልጋ ወራሽ ተፈሪ ምርጫ በማጣታቸው ሌላ ጦር ት/ቤት ለማቋቋም ወሰኑ፡፡ 2

በዚህም መሠረት በህዳር ወር 1927 ዓ.ም ሆለታ ላይ የቀዳማዊ ሃይለስላሴ ጦር ት/ቤት በስዊድንውያን አምስት መኮንኖች አሰልጣኝነት
ተቋቋመ፡፡ ቀደም ሲል ፈረንሳይ ተልከው ለሁለት ዓመታት የሰለጠኑት አስራሁለት መኮንኖችን በተመለከተ የመጽሑፉ አዘጋጆች
እንዲህ ብለዋል፡- “ቁጥራቸው በማነሱ ውጤታማ አይሆኑም ተብለው አሰልጣኝነታቸው ተቀባይነት አጥቶ የቢሮ ሠራተኛ ሆነው ሲቀሩ
በቁጥር አናሳ የሆኑት ስድስት አውሮፓውያን መኮንኖች ብቻቸውን በቂ ናቸው የተባሉበት አመክንዮ አልተገለፀም፡፡” (ገጽ 33)
ለማንኛውም ጦር ት/ቤቱ 107 ዕጩ መኮንኖችን ተቀብሎ ስልጠና ጀመረ፤በተለያየ ጊዜ ሌሎች ዕጩ መኮንኖች ተጨምረው ከዓመት
በኋላ ሲመረቁ ቁጥራቸው 148 ደርሶ ነበር፡፡ የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን ለመውረር እያሰፈሰፈ ስለነበር ተመራቂ መኮንኖቹ ብርጌድ
ሃይለስላሴ በሚል ዕዝ ተደራጅተው ለዘመቻ ተሰማሩ፡፡ እነዚህ መኮንኖች በሠራዊቱ ታሪክ ውስጥ የሚታወቁት በአምስቱ ዓመት
የአርበኝነት ትግላቸውና በጥቁር አንበሳ ጦር ውስጥ በከፈሉት መስዋዕትነት ነው፡፡ስለ አምስት ዓመቱ የአርበኝነት ትግል መጽሐፉ
በስፋት አትቷል፡፡
ከነፃነት በኋላ አፄ ሃይለስላሴ የእንግሊዞችን ተፅዕኖ በመቋቋም መንግስታቸውን መመስረት ቀጠሉ፡፡ በእነሱም ዕርዳታ የሆለታው ጦር
ት/ቤት እንደገና ተከፍቶ እጩ መኮንኖችን ተቀብሎ ማሰለጠን ጀመረ፡፡ ሠላጣኞቹ በአብዛኛው ከአርበኝነት የተመለሱ በመሆናቸውና
የውጊያ ልምድም ስለነበራቸው ዘመናዊ ጦር እንደገና የማዋቀሩ ሂደት የተሳካ ሆነ፡፡ አገሪቱም በሶስት ክፍለጦር የተዋቀረ ጦር ባለቤት
ሆነች፡፡ ጦር ት/ቤቱ እየተጠናከረ በመምጣቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የእንግሊዞች ጦር መኮንኖችን በአገር ልጆች በመተካት ራሱን ቻለ፡፡
መጽሐፉ ላይ እንደተገለፀው በ1938 ዓ.ም ለተቋቋመው የኢትዮጵያ አየር መንገድና በ1940 ዓ.ም ለተከፈተው የአየር ሃይል ት/ቤት
አስኳል የሆኑት አብዛኞቹ ከዚሁ ት/ቤት የተመረቁ መኮንኖች ነበሩ፡፡
የክቡር ዘበኛ ጦር እንደገና ተደራጅቶ በሶስት ዙር መኮንኖች ማስመረቁ ተነግሯል ነገር ግን በዝርዝር አልተገለፀም፡፡ ነገር ግን የኋላ ኋላ
በጦር ሠራዊቱና በክቡር ዘበኛ መሐከል ስለተፈጠረው ቅራኔ መጽሐፉ ፍንጭ ሰጥቷል፡፡ ለምሳሌ ያህል ጦሩ ትዕዛዝ ይቀበል የነበረው
ከምድር ጦር ሳይሆን ከንጉሡ እንደነበር ተገልጻÿል፡፡ በዕዝና በአደረጃጀቱም ከምድር ጦር ጠቅላይ መምሪያ በሚስተካከል አመራር
ሲዋቀር ትጥቁም ከአንድ ክፍለ ጦር እንዲበልጥ ተደርጓል፡፡ሌሎች የጦር ክፍሎች አስቸጋሪ ህይወትና በየጠረፉም ድንበር ጠባቂ
ወታደሮች አሰቃቂ የሚባል ኑሮ ሲመሩ ለክቡር ዘበኞች ግን የተለየ እንክብካቤ ይደረግ ነበር፡-
 …ለምሳሌ ሌሎች የምድር ጦር አባላት ቀኑን ሙሉ ስራቸውን ሲያከናውኑ፣እነርሱ ግን እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሠዓት ብቻ ሠርተው ተራፊውን ሠዓት
ስለሚያርፉ (ዘብ ተራ ከሆኑት በቀር) የግል ኑሯቸውን በሚደጉም ተግባር ላይ ይሰማሩ ነበር፡፡ ስለዚህ ከሌላው ጦር መጠነኛ መሻል
የሚታይበት አኗኗር ነበራቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በሌላው ጦር ላይ የነበረው የኑሮ ሰቆቃ እነርሱን እምብዛም አይሰማቸውም ነበር፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ወታደራዊ ስሜታቸውን የሚገነባ አስተማሪና አዝናኝ የሆነ ጠቅል የተባለ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያና ወታደርና ጊዜው
የተሰኘ ጋዜጣ ነበራቸው፡፡ በስፖርት እንቅስቃሴና በሌላም ማህበራዊ ጉዳዮች ያልተቋረጠና ሁሉን አሳታፊ ግንኙነት እንዲያደርጉ ቀና
ሁኔታ ስለተፈጠረላቸው የእርስ በርስ መቀራረባቸው እንዲጠነክር ዕድል ሰጥቷቸዋል…፡፡ በአጠቃላይ ይደረግላቸው የነበረ የተሻለ
እንክብካቤና የተለየ ግንባታ ንጉሠ ነገስቱን በፍቅርና በታማኝነት እንዲጠብቁ ስነ-ልቦናዊ ጫና ከማሳደር አልፎ አንዳንድ አባሎቹ ራሳቸውን
ከሌላው የአገሪቱ ወታደሮች በላቀ ደረጃ እንዲገምቱ አድርጓቸዋል፡፡ ድስት አለላ ተከድኖ፣ቀሚስ ለብሶና አጊጦ ከንጉሡና
ከሹማምንቶቻቸው ፊት በመቅረቡ ከባልንጀራው ከምጣድ ተለይቶ ክብር ያገኘ መሠለው… እንዲሉ ንጉሡ ላራሳቸው ክብር ብለው
እንዳስጌጧቸው ሳያጤኑ የተሳሳተ ትምክህት አደረባቸው…፡፡ (190)
ከላይ ከተጠቀሰው ፅሁፍ መረዳት የምንችለው በክብር ዘበኛና በጦር ሠራዊት መካከል ውስጥ ውስጡን ከፍተኛ ቅራኔ እየተፈጠረ
መሄዱንና ለወደፊቱም ደም አፋሳሽ ግጭት መንገድ እንደተጠረገ መሆኑን ነው፡፡ ጦር ሠራዊቱ አመቺ ቀን ይጠብቅ ነበር ማለት
ሳይቻል አይቀርም፡፡ እዚህ ላይ ጦር ሠራዊቱ በክብር ዘበኛ ላይ የነበረውን ቁጭት የምትመስል አገላለፅ ገፅ 180 ላይ እናገኛለን፡፡
ይኸውም የዩጎዝላቪያው ፕሬዚዳንት ማርሻል ብሮዝ ቲቶ ኢትዮጵያን ጎብኝተው ከተመለሱ በኋላ ለጥበቃ ተሰማርቶ የነበረው ጦር
ሠራዊት ወደ ካምፑ ሲገባ ክብር ዘበኞች ግን በጦር ሠራዊቱ ያልተወደደ አንድ ድርጊት ፈፀሙ፡- “በአጀባና በጥበቃ የተዳከመው
የምድር ጦር ሠራዊት በየሠፈሩ ተመልሶ እፎይ ሲል በዚህ ስራ የተነቃቁት የክብር ዘበኛ ጦር አዛዦችና የመምሪያ መኮንኖች ከ6 ወራት
መሠናዶ በኋላ ጦራቸው የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ ለንጉሠ ነገሥቱና ለህዝቡ ለማመልከት በሱሉልታ ታላቅ የውጊያ ትርኢት አሳዩ፡፡
… እርሳቸው ትዕይንቱን ካዩና ይዘቱን ካስተዋሉ በኋላ አድናቆታቸውንና ምስጋናቸውን ገለጡ፡፡ ከልክ በላይ የተሰነገለ (የተሳለ) ጎራዴ
አያያዙን ካላወቁበት አደጋው ለታጣቂው መሆኑን ሰንብተው አገኙት፡፡” እዚህ ላይ ግን ፀሐፊዎቹ ሊነግሩን (አያውቁትም ማለት
አይቻልም) የሚገባው የክብር ዘበኛ ጦር አለማመፁን ነው፤የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው የጄነራል መንግስቱ ንዋይና የአጋር
መኮንኖቻቸው ስራ ነበር፡፡ ጦራቸው ሙሉ ለሙሉ ተሳታፊ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ የክብር ዘበኛ ጦር በጦር ሠራዊት ይበልጥ ጥርስ
ወስጥ መግባቱን የሚያሳየው ደግሞ የጦር ሃይሎች ኤታ ማዦር ሹሙ ጄነራል መርዕድ መንገሻ ሐምሌ 2 ቀን 1952 ዓ.ም በምስጢር
ለንጉሡ በፃፉት ደብዳቤ ነው፡- “…ክብር ዘበኛ ሠራዊት ባለው የወታደር (የሰው ሃይል)፣የመሣሪያ፣የመኮንኖች ብቃትና አዲስ አበባ
ከሚገኘው የምድር ጦር ጋር ሲመዛዘን የበላይነት ስላለው፣ከዚህም በላይ የምሰጠውን ትዕዛዝ አሻፈረኝ በማለት ላይ በመሆኑ
እንዳያምፅ የምጠረጥር ስለሆነ አንድ መፍትሄ ይታሰብበት…” (215) ለታህሳሱ (1953) መፈንቅለ መንግስት ሙከራ መክሸፍ
ጦራቸውን ለተግባር በጊዜው ባለማዘጋጀታቸው የሚወቀሱት ጄነራል መንግስቱ ናቸው፤ነገር ግን መጽሐፉ በሰጠን አዲስ መረጃ
መሠረት ግን ጦር ሠራዊቱ ከክብር ዘበኛ ሊሰነዘር የሚችልን አድማ በንቃት ይጠብቅ እንደነበርና በማክሸፉም ረገድ ሳያመነታ
መስራቱን ነው፡፡
የታህሳሱን መፈንቅለ መንግስት ሙከራ በተመለከተ ከዚህ በፊት ብዙ የተፃፈ ቢሆንም መጽሐፉ ስለ ሙከራው ከጅምሩ እስከ
ፍፃሜው ሰፋ ያለ ዘገባ አቅርቧል፡፡ ምናልባት ከዚህ በፊት ብዙም የማይታወቅ ነገር ቢኖር መጨረሻው ሠዓት ላይ እነ ጄረራል
መንግስቱ ንዋይ ለጄነራል መርዕድ መንገሻ የድርድር ሃሳብ ማቅረባቸው ነው፡፡ የድርድሩን ሃሳብ በወቅቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ
አምባሳደር የነበሩት ለጄነራል መርዕድ ቢያቀርቡላቸውም ድል ጫፍ ላይ ስለነበሩ አሻፈረኝ አሉ፡፡ ምናልባት በነጄነራል መንግስቱ
ታግተው የነበሩት የአፄ ሃይለስላሴ ባለስልጣናት ከሞት የመትረፍ አጋጣሚ አምልጧል ማለት ይቻላል፡፡ ጄነራል መንግስቱ ፍርድ ቤት 3

ቀርበው ክሳቸው እየተሰማ እያለ ስለተፈፀመባቸው ክብረነክ ድርጊትና በኋላም ስለተሰጠው የሞት ፍርድ ተተርኮ መጨረሻም
“…የተሰጠኝ ፍርድ አግባብ ስለሆነ ይግባኝ አልልም…” ብለው የስቅላት ቅጣቱ ተፈፀመባቸው በማለት ትረካው ያበቃል፡፡ ነገር ግን
ጄነራል መንግስቱ ንዋይ ከሞት ፍርዱ በኋላ ይግባኝ መጠየቅ ይፈልጉ እንደሆነ ሲጠየቁ ሰፋ ያለ ንግግር አድርገዋል፡፡ በአጭሩ
መልዕክታቸው የሚከተለውን ይመስላል፡-
እናንት ዳኞች የበየናችሁብኝን የሞት ፍርድ ያለይግባኝ ተቀብዬዋለሁ፡፡ ይግባኝ ብዬ ጉዳዬን የሚመለከትልኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢሆን
ኖሮ ይግባኝ ማለት በፈለግሁ ነበር… ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፣ ነፃነትና ዕርምጃ የተነሳሁ ወዳጅ እንጂ ላፋጀው የተነሳሁ ወንበዴ
አይደለሁም፡፡ ይህን ማድረግ ፈልጌ ቢሆን ኖሮ ማንም የማይወዳደረው ሠራዊትና መሣሪያ ሳላጣ ዛሬ እዚህ እናንተ ፊት ለመቆም
ባልበቃሁ ነበር፡፡ እኔ ከአፄ ኃይለስላሴ ድንክ ውሾች ያነሰ ደሞዝ የሚያገኙ ሁለት የተራቡ ወታደሮችን አጣልቼ ለማደባደብና አገር
ለማፍረስ አለመምጣቴን የሚያረጋግጥልኝ እናንተ በትዕዛዝ ያገኛችሁትን ፍርድ ለመቀበል እዚህ መቆሜ ነው፡፡ …የጀመርኩት ስራ ቀላል
አይደለም፡፡ አልተሸነፍኩም!!... እኔ የተነሳሁት ከትክክለኛ ህግና ከህሊናችሁ ውጭ ለመፍረድ እንዳትገደዱ ለማድረግ ነበር፡፡ በአጭሩ
በእኔ ላይ ለመፍረድ የቸኮላችሁትን ያህል አስርና አስራምስት ዓመት በቀጠሮ የምታንገላቱትን የድሃውን ህዝብ ጉዳይ እንደዚህ
አፋጥናችሁ ብትመለከቱትና ብትሸኙት ኖሮ የእኔ መነሳት ባላስፈለገ ነበር፡፡ ከእናንት ከዳኞችና የሞት ፍርድ እንድትበይኑብኝ ካዘዛችሁ
ሰው ይልቅ እኔ ፍርድ ተቀባዩ የዛሬ ወንጀለኛ የነገ ባለታሪክ ነኝ…
…የዛሬ ወንጀለኛ የነገ ባለታሪክ ነኝ፡፡ ጄነራል መንግስቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግስታቸውን ሞክረው ሠማዕት ከሆኑ 13 ዓመት በኋላ
የኢትዮጵያ አብዮት ፈንድቶ አፄ ሃይለስላሴን ካሽቀነጠረ በኋላ የእሳቸውና የወንድማቸው እንዲሁም የሌሎች ሠማዕታት ፎተግራፎች
ታትመው በየቦታው ተሰራጩ፣ታሪካቸውም በስፋት ተፃፈ፤እስካሁንም አላቆመም፡፡ ካነሷቸውም ጥያቄዎች መካከልም የወታደሩ
የደሞዝ ጭማሪ ጉዳይ ስለነበር ንጉሡ እያቅማሙም ቢሆን አስቸኳይ ምላሽ ሰጡ፡፡ መፈንቅለ መንግስት አክሻፊው ጄነራል መርዕድ
መንገሻም ከአምስት ዓመት በኋላ ጄነራል መንግስቱን ተከትለው ሄዱ፡፡ መጽሐፉ ላይ እንደተጠቀሰው የሶማሊያ መንግስት መጠነ ሰፊ
ወታደራዊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተጨባጭ መረጃ ስላገኙ ንጉሡ አንድ መፍትሄ እንዲሹ ጉትጎታቸውን ቀጠሉ፡፡ ነገር ግን ንጉሡ
ዳተኝነት ሲያሳዩ ጄነራል መርዕድ ትዕግስታቸው አለቀ፣የመንግስቱ ንዋይም መንፈስ አደረባቸው፡፡ ከጄነራል ጃገማ ኬሎ ጋር ሲገናኙም
እንዲህ አሉ፡- ‘እግዝዕተነማሪያምን አሁንስ ቆርጫለሁ፣እኚህ ሰው ካሁን በኋላ መቆየት የለባቸውም፤ይህችን አገር ወደ ውርደት
እየመሯት ነው፡፡’ (309) ምን ያደርጋል! መርዕድ መንገሻ ተቀደሙ፣ኮሽታ ሳያሰሙ ምክንያቱ ባልታወቀ መንስኤ ሞቱ ተባለ፡፡
ስለ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ/ሐረር ጦር አካዳሚ መከፈትና መዘጋት መጽሐፉ የሚለው አለው፤ የተዛባም ቢሆን፡፡ በዕርግጥም ጦር
አካዳሚው የማሰልጠን ተግባሩን የጀመረው ሚያዚያ 27 ቀን 1950 ዓ.ም ነው፡፡ ነገር ግን ስለመሰናዶ ት/ቤት የተጠቀሰው ትክክል
አይደለም፡፡ የአካዳሚው የመጀመሪያ ኮርስ ዕጩ መኮንኖች የተመረጡት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነበር፤ከዚያ በኋላ ያሉትም ኮርሶች
እንዲሁ ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጆችና ከከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የአስራሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ካለፉት መካከል ነበር፡፡ እነዚህ
ዕጩ መኮንኖች ወደ አካዳሚው በቀጥታ ገብተው ለሶስት ዓመት ወታደራዊና የቀለም ትምህርት ካጠናቀቁ በኋላ በምክትል መቶ አለቃ
ማዕረግ ይመረቁ ነበር፡፡ ነገር ግን የአስራ ሁለተኛ ክፍልን መልቀቂያ ፈተና አልፈው ወደ ጦር አካዳሚ ለመግባት ፈቃደኛ የሚሆኑ
ተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱ 11ኛ እና 12ኛ ክፍልን አስተምሮና የ12ኛ መልቀቂያ አስፈትኖ ወደ አካዳሚው
የሚያስገባ የወታደራዊ መሰናዶ ት/ቤት በ1961 ዓ.ም ተቋቋመ፡፡ የመጀመሪያዎቹ የት/ቤቱ ተማሪዎችም የ13ኛ እና የ14ኛ ኮርስ አባላት
ነበሩ፡፡ ት/ቤቱ ይህንኑ ሂደት ቀጥሎ 10 ኮርሶችን ከሞላ ጎደል አስተምሮ አስከ 22ኛ ኮርስ ድረስ ለአካዳሚው አዘጋጅቶ አካዳሚው
በድንገት ሲዘጋ እሱም ህልውናው አክትሟል፡፡
እዚህ ላይ አካዳሚውን በተመለከተ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ፀሐፊዎቹ አንስተዋል፡፡ ይኸውም “የሆለታ ገነት ጦር ት/ቤት እያለ የሐረር
ጦር አካዳሚ ለምን ተፈለገ? ነባሩን ደረጃውን ከፍ አድርጎና አስፋፍቶ እንዲቀጥል ማድረግ አይቻልም ነበር ወይ? የሚል ጥያቄ ይነሳ
ይሆናል፡፡” (195) ብለዋል፡፡ መጽሐፉ ከአንጀት ባይሆንም ለዚህ ጥያቄ እንደሚከተለው መልስ ለመስጠት ሞክሯል፡፡ የሆለታው
የቀዳማዊ ሃይለስላሴ ጦር ት/ቤት መጀመሪያ አካባቢ ወጣቶችን ከት/ቤት እየተቀበለ ቢያሰለጥንም የኋላ ኋላ ግን ሠራዊቱ ውስጥ
ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ ባለሌላ ማዕረግ ወታደሮችን በመቀበል ወደ አመራር ማምጣት ጀመረ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከጦር ት/ቤቱ የሚወጡት
መኮንኖች ደግሞ ሠራዊቱ ውስጥ ረዥም ጊዜ በማገልገላቸው የተነሳ በመኮንንነት ብዙ አይቆዩም፡፡ ስለዚህ ከጦር አካዳሚ በቀጥታ
የሚወጡ ወጣት ዕጩ መኮንኖችን ወደ ሠራዊቱ ማስገባት አስፈላጊ ሆነ፡፡
ይህ ክስተት ግን የራሱ የሆነ ሌላ ችግር ይዞ መጣ፡፡ የመጀመሪያው መጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሰው የደሞዝ ልዩነት ያመጣው ችግር ነው፡፡
የአካዳሚው ምሩቃን ለትምህርት ማስረጃቸው ተብሎ ከምክትል መቶ አለቃ 125 ብር ደሞዝ ላይ 90 ብር ሲጨመርላቸው ከሌሎች
ጦር ት/ቤቶች ከወጡ በሻምበል ደረጃ ከሚገኙትም በለጠ፡፡ የአካዳሚው የመጀመሪያ አካበቢ ኮርሶች በስፋት እንደሚናገሩት፣ይህ
ከፍተኛ ቅሬታን አስነሳ፤እኛ ደም እነሱ ወተት ነወይ የሚያፈሱት? ተባለ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ/ሐረር ጦር አካዳሚ
አንደኛ ኮርስ የተመረቁበት ጊዜና የሆለታው 19ኛ ኮርስ የተመረቁበት ጊዜ መቀራረብ ወደ ፊት ለሚከሰቱ አሉታዊ ሁኔታዎች የበኩሉን
አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም የተገኙት ከ19ኛ ኮርስ ነበር፡፡
ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ሐረር ሶስተኛ ክፍለጦር በነበሩበት ጊዜ በጦር አካዳሚ መኮንኖች ላይ ብሶት ከሚያሰሙት መካከል
አንዱ ነበሩ ይባላል፡፡ እነሱ ወተት ነወይ የሚያፈሱት? ከሚሉት ውስጥ ነበሩ፡፡ አንድ ወቅት ተመርቀው አብረዋቸው ሠራዊቱን
የተቀላቀሉት የአካዳሚው መኮንኖች በከፍተኛ የጦር መኮንኖች የተሻለ ተሰሚነት ሲያገኙና ለከፍተኛ ትምህርትም ወደተለያዩ አገሮች
ሲሄዱ ቁጭት ሳያድርባቸው አልቀረም፡፡ የአካዳሚው መኮንኖች ዶክተሮች፣መሐንዲሶች፣የሕግ ሰዎች ወዘተ እየሆኑ ብቅ ብቅ ማለት
ጀመሩ፡፡ ከክብር ዘበኛ መኮንኖች ጋር የነበረው ቅራኔ ከታህሳሱ ክስተት በኋላ ቢከስምም ከአካዳሚ መኮንኖች ጋር የነበረው ቅራኔ ግን
እየጋመ ቀጠለ፡፡ በዕርግጥ ይህ መጽሐፉ ውስጥ አልተጠቀሰም ነገር ግን ዕውነትነቱ አጠራጣሪ አይደለም፡፡ 4

በየካቲት 1966 ዓ.ም የፈነዳው የኢትዮጵያ አብዮት ለቀዳማዊ ኃይለስላሴ/ሐረር ጦር አካዳሚ መልካም ነገርን ይዞ አልመጣም፡፡
በአካዳሚው ላይ ዘወትር ብሶታቸውን ያሰሙ የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር የሆነው ደርግ ቁንጮ
ሆኑ፡፡ ኮሎኔል መንግስቱ የሐረር ጦር አካዳሚን (ከዚህ በኋላ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የሚለው ቀርቷል) የማፍረስ ውጥናቸውን የጀመሩት
ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ ይህንንም ጉዳይ ከዳር እንዲያደርሱላቸው ቀኝ እጃቸው የነበሩትን ኮሎኔል ተስፋዬ ገ/ኪዳንን መደቡ፡፡
በአንድ ዕድለቢስ ቀን (የካቲት ግማሽ ላይ፣1968 ዓ.ም) ኮሎኔል ተስፋዬ ገብረኪዳን አካዳሚው ድረስ በመሄድ የ18ኛ ኮርስ ዕጩ
መኮንኖችን በመሰብሰብ የስልጠና መርሃ ግብራቸው በዚያው ዓመት እንደሚቋረጥና አገሪቷ እንደዚህ ዓይነት አካዳሚ የማስተናገድ
አቅም እንደሌላት አረዷቸው፡፡ በማከልም አፄ ኃይለስላሴ ለጉራ እንዳቋቋሙትና አስፈላጊም እንዳልሆነ ነገሯቸው፡፡ ዕጩ መኮንኖቹ
ግን የኮሎኔሉ ንግግር የሚዋጥላቸው አልሆነም፤ስለዚህ አመፁ፣አድማ መቱ፡፡ ወታደር ቤት ማመፅ መዘዙ ክፉ ስለሆነ የአድማ መሪዎቹ
ተለይተው ወጥተው ለከፋ ቅጣት ተዳረጉ፡፡
ኮሎኔሉ የፎከሩትን ሳይፈፅሙ የ18ኛ ኮርስ ዕጩ መኮንኖች በ1969 ዓ.ም የሶስተኛ ዓመት ትምህርታቸውን ቀጥለውና ኮርሳቸውን
አጠናቀው አዲስ አበባ መጥተው ከተመረቁ በኋላ ታጠቅ የነበረው ሚሊሺያ ጦር አዛዦች ሆነዋል፡፡ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም
በ1969 ዓ.ም አካዳሚውን ለማፍረስ አሰፍስፈው የሚጠብቁበት ዓመት ነበር፡፡ በዚሁ ዓመት አካዳሚው አምስት ኮርሶች ነበሩት፤
እነሱም 18፣19 እና 20 (አካዳሚው ውስጥ)፤ 21 እና 22 ደግሞ (መሰናዶ ውስጥ) ነበሩ፡፡ ይኸው ዓመት ደግሞ ለነኮሎኔል መንግስቱ
ሌላ ገፀ በረከት ይዞ ብቅ አለ፤ይኸውም መጀመሪያ በሰርጎ ገብ በኋላ ደግሞ በቀጥታ ወረራ የሶማሊያ ጦር ጥቃት መፈፀሙ ነው፡፡ በዚህ
ረገድ የሶማሊያ ሰርጎ ገቦች የመጀመሪያውን ግንባር የከፈቱት ከሐረር ጅጅጋ መስመር ላይ በምትገኘው ቆሬ በምትባል ቦታ ላይ ነበር፡፡
የአካዳሚው አሰልጣኝ መኮንኖችም ከስልጠና መርሃ ግብራቸው እየተነሱ እንዲዘምቱ ታዘዙ፡፡ሁኔታው በዚህ ቀጥሎ አሰልጣኝ
መኮንኖቹ በየግንባሩ ተበትነው በሐምሌ ወር የሐረር ከተማ ጦርነት ቀጣና ውስጥ ስለገባች አካዳሚው ሐምሌ/1969 ወደ ሆለታ ገነት
ጦር ት/ቤት ተዛወረ፡፡ የ19ኛ ኮርስ ዕጩ መኮንኖች የምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው ወደ የጦር ግምባሩ ሄዱ፡፡ የ20ኛ
ኮርስ ዕጩ መኮንኖች ደግሞ ብዙ ሳይቆዩ በዚያው በነሐሴ ወር እዚያው ሆለታ በም/መቶ አለቅነት ተመርቀው (በነጭ ጥብጣብ
አልተደለደሉም) ለፓራኮማንዶ ስልጠና ሰንዳፋ፣አዋሽ አርባና ሻሸመኔ ተላኩ፡፡ የ21ኛ ኮርስ ዕጩ መኮንኖች ሆለታ ከገቡ በኋላ ብዙም
ሳይቆይ የ22ኛ ኮርስ አባላት ለዕረፍት ከሄዱበት ተጠርተው ሆለታ ከተቱ፡፡ ሌሎች 80 የሚሆኑ የ11ኛ ክፍልን ያጠናቀቁ ተማሪዎች
ደግሞ በአካዳሚው መስፈርት ተመርጠው ቀድመው የገቡትን ተቀላቀሉ፡፡ ሶስቱም አንድ ላይ የ21ኛ ኮርስ ዕጩ መኮንኖች ተብለው
ለአንድ ወር ከአስራምስት ቀን እጅግ የተጣደፈ የእግረኛ ወታደራዊ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ደብረዘይት (ቢኤም 21)፣ናዝሬት (ታንክ)፣
ፍቼ (ልዩ ልዩ መድፎች) እና አሰብ (አየር መቃወሚያ) ተመደቡ፡፡ ብዙም ሳይቆዩ በምስራቅና በሰሜን ወታደራዊ ግዳጃቸውን
ተወጥተዋል፤ከዚያም ወደሶቭየት ህብረትና ሌሎችም አገሮች በመሄድ ከፍተኛ ወታደራዊ ዕውቀት ገብይተዋል፡፡ መጽሐፉ ላይ
እንደተጠቀሰው ከ33ኛ ኮርስ ዕጩ መኮንኖች ጋር በመሆን ለአንድ ዓመት ሆለታ ውስጥ አልቆዩም፤በዚያ ቀውጢ ወቅት ማንም ከሶስት
ወር በላይ ሊቆይ አይችልም፡፡ መጽሐፉ ውስጥ እንደተጠቀሰው የሐረር ጦር አካዳሚ ለጊዜው ነው የተዘጋው ቢባልም ኮሎኔል
መንግስቱ ኃይለማሪያም ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደከረቸሙት አንዳንድ ጠቋሚ ማስረጃዎች አሉ፡፡ በመጀመሪያ አካዳሚው
ለ19 ዓመታት ያካበታቸው ሰነዶችና መዛግብት እንዲወድሙ ተደርገዋል፣ ሁለተኛ አካዳሚው ከተለያዩ አቻ የውጭ አገር አካዳሚዎች
ያገኛቸው ገፀ በረከቶች ተዘርፈው በየአልባሌ ስፍራዎች ተበትነዋል፤ እንዲሁም የሳይንስ ላቦራቶሪ ኬሚካሎች በጊዜው ባለመነሳታቸው
ተበላሽተው ባክነዋል ሌላም፣ሌላም ወዘተ ወዘተ…፡፡
በ1956 ዓ.ም በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ስለተደረገው ጦርነት መጽሐፉ በዝርዝር አትቷል ነገር ግን ስለጄነራል አማን አንዶም
የተገለፀው ከሰማነውና ቀደም ብሎ ከተፃፈው የደበዘዘ ይመስላል፡፡ ጄነራል አማንን ደርጉ ሊቀመንበሩ አድርጎ ሲሾማቸው የኦጋዴን
ጀግና እንደነበሩና በኋላም በሠፊው እንደተወራው ድንበር ካልጣስኩ ብለው በንጉሡ ትዕዛዝ (በህመም ሳይሆን) ወደ አዲስ አበባ
እንደመጡ ነው የምናውቀው፤በእምቢተኝነታቸው የተነሳም ከሠራዊቱ ተሰናብተዋል፡፡ የሰማነው የተጋነነ ከሆነ ማስተካከያ ቢሰጥ
መልካም ነበር፤አለበለዚያ እኝህን የመንግስቱ ኃይለማሪያም የግፍ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ስመጥር ጄነራልን ማሳነስ አግባብ አይደለም፡፡
የሶማሊያ መንግስት በ1956 ዓ.ም ከደረሰበት ውርደት ካገገመ በኋላ ለሌላ ፍልሚያ ዝግጅቱን ማጧጧፉን መጽሐፉ ውስጥ በጥሩ
ሁኔታ ተገልጻÿል፡፡ ጄነራል ዚያድ ባሬ በ1961 ዓ.ም በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ይዘው ሶሻሊዝም የመንግስታቸው ርዕዮተ ዓለም
መሆኑን ካሳወቁ በኋላ ከሶቭየት ህብረት ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመው ሶስት ቢሊዮን የሚጠጋ የጦር መሣሪያ አግኝተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ግን ዝግጅቱ የተገላቢጦሽ ነበር፡፡ የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የጦር መሣሪያ ዕርዳታ በዕጅጉ
ከመቀነሱም ባሻገር የተገዛውንም ለመስጠት ዳተኝነትን አሳየ፡፡ ጉዳዩ ያሳሰባቸው ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ደብዳቤ በመፃፃፍ ለንጉሡ
አመለከቱ፤እሳቸው ግን ደንታም አልሰጣቸው፡፡ ወታደሩን አላመኑትም፤መጽሐፉ ውስጥ እንደተገለፀው፡፡
ደርጉ ከመጣ በኋላ የጦሩን ይዞታ ለማሻሻል የወሰደው ዕርምጃ ስለመኖሩ መጽሐፉ ውስጥ አልተገለፀም፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ኋላ ቀር
መሣሪያ ታቅፎ በተጎሳቆለ ህይወት ውስጥ ሲዳክር የሶማሊያ ጦር ግን ዝግጅቱን አጠናቆ በ1969 ዓ.ም ሰባት ብርጌዶችን በአምስት
ግንባሮች አሰማራ፡፡ ይህን በተመለከተ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ የሚከተለውን ብለዋል፡-
Why did the Somali irredentists take on such a perilous gamble? The political situation in
Ethiopia in 1977 and the state of the country’s military could not have been more alluring. First,
though the Ethiopians had a clear numerical advantage in fighting men (47,000 to 35,000) they
were at an overall technical and tactical disadvantage in the air and on the ground.The Somalis
outnumbered the Ethiopians in mobile battalions, tanks, combat aircraft, artillery, armour, and
armored personnel carriers. Not only were the Ethiopians far more poorly equipped, but much of
their weaponry was outdated and inferior. (The Ethiopian Revolution: War in the Horn of Africa) 5

የሶማሊያ መንግስት የኢትዮጵያን ጦር ለማዳከም መጀመሪያ ሠርጎ ገቦችን ወደተለያዩ የሐረርጌ አካባቢዎች በመላክ በኢትዮጵያ ጦር
ሠራዊት ላይ አዘመተ፡፡ ጦሩም በተቻለው አቅም በመከላከል ይዞታውን ላለማስነጠቅ ታገለ፣በተለይ የኢትዮጵያ አየር ሃይል የፈፀመው
አኩሪ ገድል የማይረሳ ነው፡፡ ብዙም ሳይቆይ የሶማሊያ ጦር መጠነ ሰፊ ዘመቻ ከፈተ፡፡ ጎዴ ላይ የኢትዮጵያ ጦር በፅናት ተዋግቶ
የሶማሊያን ጦር ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ መልሶታል፡፡ ነገር ግን በመድፍና በታንክ የታገዘ ሜካናይዝድ ጦርን በእግረኛ ጦር ብቻ
መመከት ስለማይቻል ሠራዊቱ ወደ አመቺ ስፍራ እንዲያፈገፍግ መታዘዙን መጽሐፉ ያብራራል፡፡ የጅጅጋ ከተማንም የጠላት ጦር
ስለያዛት የከተማው ህዝብና ጦሩ ስለተደበላለቀ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ሆነ፡፡
እዚህ ላይ ጦሩ ስለደረሰበት ሽንፈትና ማፈግፈግ የመጽሐፉ አዘጋጆች ወይም ፀሐፊ ተደጋጋሚ ነገር ግን ተጨባጭ ያልሆነ ክስ
በኢሕአፓ ላይ ደርድረዋል፡፡ በጅጅጋው ሽንፈትና ስርዓት የለሽ ማፈግፈግ (disarray) የተነሳ ከ20 ጊዜ በላይ የአሕአፓ ስም በክፉ
ተነስቷል፡፡ ለምሳሌ ገጽ 423 ላይ “አጥቂው ጦር በጥሩ ሁኔታ የተያያዘውን የመልሶ መቋቋም ውጊያ ትቶ ወደ ካራማራ በር ያፈገፈገው
ደጀኑ ጦር ጀርባውን አጋልጦት ስለተመለሰ ብቻ አልነበረም፡፡ በዚያ ምስቅልቅል ሁናቴ የመስክ ሬዲዮ ግንኙነት ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ
ስለነበር የክፍል መገናኛ ሬዲዮኖች በኢሕአፓ ሰዎች እጅ ገብተው፣ወይም ሬዲዮ ሠራተኞች የእነርሱን ትዕዛዝ ተቀብለው ይሆናል…”
መጽሐፉ ጠንካራ ክስ እያቀረበ ማስረጃው ግን “ይሆናል” ሆነ!! የማፈግፈጉ ትዕዛዝ የመጣው ከኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም
መሆኑን በሚቀጥለው ገጽ 424 ላይ እናገኛለን፡-“…ንጋት ላይ በ0200 ሠዓት ወደ አደው ተጠርተን ማፈግፈጉ የሊቀመንበሩ ትዕዛዝ
መሆኑ ተገልፆልን ወደ ጦራችን ተመለስን፡፡ ይህን ትዕዛዝ የነገሩን የሦስተኛ ክፍለ ጦር ዘመቻና መረጃ መኮንኖች ናቸው…” ታዲያ
መወቀስ ያለባቸው ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም እንጂ ኢሕአፓ ምን በወጣው!! ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ሁኔታውን አስመልክተው
ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፋቸው ውስጥ የሚከተለውን ብለዋል፡- It is clear that disharmony contributed to the army’s
initial setbacks, but it is wrong to ascribe the loss of Jijiga to a seditious group; the defeat was primarily due to
the imbalance in firepower. As Lieutenant Colonel Tesfaye Gabre Kidan, admitted in a communiqué to the
commander in chief, it was simply beyond the unit’s power to prevent the capitulation of Jijiga. እስቲ የሚከተለውን
እንቀፅ እንመልከት፡- “…ኢሕአፓ በአመራሩ ላይ በተጫነ ሶስተኛ እጅ፣ በውስጡም በተፈጠረ የፖለቲካ ቀውስና ምንደኝነት የተነሳ
ብዙዎቹን የኢትዮጵያ ወጣቶች ለሶማሊያ ወራሪ ጦር ጊዜያዊ አሸናፊነት እንዲሰሩ አመራር በመስጠታቸው በኢሕአፓ የትግል ሂደት
ላይ ከባድ እንቅፋት ጋረጡ፡፡ ታላቅ የታሪክ ስህተትም ሰሩ፡፡ በሕዝቡም ፊት ተነቃፊና ተሰዳጅ ሆኑ፡፡ ወደ ውድቀትም አቆለቆሉ፡፡
የጠሉት መንግስትም በስልጣነ መንበሩ እንዲቆይ አስተዋፅዖ አደረጉ፡፡” (428) የኢሕአፓ ውድቀት ምክንያቱ ሌላ ነው፤ከሶማሊያ ወረራ
ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ በፅሁፉ ሊተላለፍ የተፈለገው መልዕክት የኢሕአፓ አመራር ወጣቱን ከሶማሊያ ጋር ተሰልፎ አገሩን
እንዲወጋ የሚያስችል መልዕክት አስርጻÿል ከሆነ መሠረተ ቢስ ክስ ነው፡፡ በአንድ በኩል የሶማሊያ ጦር በትጥቅ የበላይነቱ የተነሳ
ልንቋቋመው ስላልቻልን አፈገፈግን እየተባለ፣በሌላ በኩል ደግሞ የኢሕአፓ አመራር ለወጣቱ ከሶማሊያ አመራር በመስጠት ለሽንፈት
ዳረገን ማለት የማይመስል ነገር ነው፡፡ ዕውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኢሕአፓ በወቅቱ በማንኛውም መስፈርት የአገሪቱን ምርጥ ልጆች
ያሰባሰበና ለአንዲትም ሰከንድ የአገራቸውን ዳር ድንበር መደፈር የማይሹ ታጋዮች የነበሩበት ነበር፡፡ የኢሕአፓ አባላት በአገር
ወዳድነታቸው፣በቆራጥነታቸውና በጀግንነታቸው አቻ የሌላቸው ነበሩ፡፡ ትግላቸውና መስዋዕትነታቸው የሚዳደረው በአምስቱ ዓመት
የጣሊያን ወረራ ወቅት በዱር በገደሉ ከታገሉ አርበኞች ጋር ነው፤የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር ትውልድ አልነበረም፡፡ ድሬዳዋን
ላለማስነጠቅ በተደረገው ትግል ጦሩ ውስጥ የነበሩ በርካታ አባላቱ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ በኋላም የሐረር ከተማን ለማዳን
በተደረገው ተጋድሎ የተሳተፉት ሐረር ጦር አካዳሚ የፓራኮማንዶ 20ኛ ኮርስ መኮንኖች አብዛኛዎቹ የኢሕአፓ አባላት ነበሩ፡፡
(የየመን መድፈኞችና የኩባ ታንከኞችና እግረኞች እንዲሁም ኩባውያን ሚግ 17 አብራሪዎች ውለታ ሳይዘነጋ ማለት ነው፡፡)ከ20ኛ ኮርስ
አባላት የተወሰኑት የሶማሊያ ጦር ከተባረረ አንድ ዓመት በኋላ ቀብሪደሃር ውስጥ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያምን ለመግደል
በተካሄደ አድማ ተጋልጠው ሠራዊቱ በተሰበሰበበት ተረሽነዋል፡፡ አሰብም ውስጥ ሌሎች የ20ኛ ኮርስ መኮንኖችም መስዋዕትነት
ከፍለዋል፡፡ ደርግ በወቅቱ በኢሕአፓ ላይ መጠነ ሰፊ የማጥላላት ፕሮፓጋንዳ ከፍቶ ነበር፣ ይህን ፕሮፓጋንዳ እንደማስረጃ መጠቀም
በምንም መለኪያ አግባብ አይሆንም፡፡ በተጨማሪ ከከተሞች የሄዱ አንዳንድ የስነምግባር ችግር ያለባቸው ወጣቶች ገንዘብ ለመዝረፍ
ሲሉ የሚሊሺያ ጦር አባላትን ከጀርባቸው እንደወጓቸው አይዘነጋም፤እነሱም ከጦሩ ተመንጥረው ወጥተው ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ አዛዡን የገደለ ሚሊሽያ ወታደር ነበር፣ይህንንም በኢሕአፓ ላይ ልንደፈድፈው ነው? ሰራዊቱን አመራር በማሳጣት
ረገድ በታሪክ ተወቃሽ መሆን ያለበት ደርግ ነው፡፡ በተለይ ከ1970 ዓ.ም በኋላ አድሃሪ መኮንኖችን ማፅዳት በሚል ሰበብ በርካታ
መኮንኖች እየተለቀሙ ተረሽነዋል፡፡ ለምሳሌ ጄነራል ሁሴን አህመድ መጽሐፋቸው ውስጥ እንዳሰፈሩት በአሜሪካና በሌሎችም ቦታዎች
ከፍተኛ ወታደራዊ ትምህርት የወሰዱ ኮሎኔል አስማማው ይመር የተባሉ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ መኮንን ባረንቱ ውስጥ በአንድ የአስር
አለቃ ደንቆሮ ካድሬ ቢሮአቸው ውስጥ ተገድለዋል፡፡
በዕርግጥ ችግር አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ አንዱ ችግር የሶማሊያ መንግስት ጦር መሣሪያ አስታጥቆ በሰርጎ ገብነት ያስገባው
የምዕራብ ሶማሊያ ነፃ አውጭ ግንባር (WSLF) ከፍተኛ ውዥንብር መፍጠሩ ነበር፡፡ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅት ስለሆንኩ
ተቀላቀሉኝ በማለት በግለሰብ ደረጃ ከጅጅጋ አካባቢ አንዳንድ ወጣቶች ተቀላቅለውት ነበር፡፡ ይህንንም ሁኔታ ነጋ መዝለቂያ Notes
from the Hyena's Belly በተሰኘ መጽሐፉ ውስጥ ገልጾታል፡፡ እንዳሰቡት እንዳልሆነም አስፍሯል፡፡ ሌሎች ወጣቶች ደግሞ
መጀመሪያ ነፃ ዕርምጃን በኋላ ቀይ ሽብርን ሸሽተው ወደ ጅቡቲ ሲሄዱ ብዙዎቹ በሶማሊያ ታጣቂዎች ታግተው ኦጋዴን የሶማሊያ
መሆኗን እንዲቀበሉ ሲጠየቁ ባለመቀበላቸው ከ11 ዓመት በላይ አሰቃቂ እስር ተዳርገዋል፡፡ በሐረርጌም የድርጅቱ አመራር ወረራውን
ለማውገዝ የበኩሉን ጥረት ቢያደርግም በድርጅቱ ላይ የተካሄደው አፈናና ጭፍጨፋ አስከፊ ስለነበር ድምፁ ብዙም አልተሰማም፡፡
በተጨማሪ 1969 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ጦር ሠራዊቱ የተሳተፈበት በከተሞች አሰሳና መንጥር ዘመቻ በመካሄዱ የኢሕአፓ አመራር
ክፉኛ ተጎድቶ ነበር፡፡ ስለዚህ ድርጅቱ በወቅቱ የተቀናጀ አመራር ነበረው ማለት አይቻልም፡፡ አንዳንድ የድርጅቱ አባላት ደርግ
በጓዶቻቸው ላይ ባካሄደው አስከፊ ጭፍጨፋ የተናሳ በተናጥል የራሳቸውን ዕርምጃ ወስደው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በተጧጧፈ
ትግል ወቅት የሚያጋጥም ነው፣ተጋንኖ መቅረብ ያለበት አይደለም፡፡ 6

የኢትዮጵያ ጦር የምስራቁን ጦርነት በድል ካጠናቀቀ በኋላ ፊቱን ወደ ሰሜን አዙሮ በስድስት ግብረሃይል ከተደራጀ በኋላ በሻቢያና
በጀብሃ ላይ መጠነ ሠፊ ጦርነት ከፈተ፡፡ በዘመቻውም ከፍተኛ መስዋዕትነትን የተከፈለበት ጦርነት በማካሄድ በሻዕቢያ የተያዙ
ቦታዎችን አስለቀቀ፡፡ የግብረሃይሎችን ዘመቻ በተመለከተ ስለእያንዳንዱ ውጊያ ሰፋ ያለ ሃተታ ቀርቧል፡፡ አንባቢ መረዳት የሚችለው
ግን ጦሩ ሻዕቢያን ማባረር እንጂ ማሸነፍ እንዳልቻለ ነው፡፡ ለምን ማሸነፍ አልቻለም? ጦርነቱ የእርስ በርስ መሆኑ፣ፖለቲካዊ መፍትሄ
ስለመሻት ጉዳይ፣የመሬት አቀማመጥ ወዘተ ወዘተ.. ለሚለው ጥያቄ መጽሐፉ መልስ ሳይሰጥ ስለ ጦር ሃይሎች ጉባኤ ማተት ጀመረ፡፡
መጽሐፉ ውስጥ እንደተጠቀሰው የጉባዔው ዋና ዓላማ የሠራተኛውን ፓርቲ ለመመስረት የሚያስችል አደራጅ ኮሚሽን በሊቀመንበር
መንግስቱ ኃይለማሪያም ማዕከልነት ማቋቋም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ጦር አገርና ሕዝብ የመጠበቅ ሃላፊነቱን ዘንግቶና በሕዝብ የተመረጠ
መንግስት ለማቋቋም መጣሩን ትቶ መንግስቱ ኃይለማሪያም የተባለ ጨካኝ አምባገነንን ለማንገስ ታች ማለት ጀመረ፡፡ የውድቀት
ቁልቁለት ጉዞውንም ጀመረ፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ሃይል (ደህንነቱና ፓሊሱም ጭምር) አንድ አብዮታዊ ትውልድ ከጨረሰ በኋላ ከራሱ
ግላዊ ጥቅም ሌላ ለምንም ነገር ደንታ ለሌለው በኋላም ሜዳ ላይ ጥሎት ለሚፈረጥጥ ጨካኝና ፈሪ ግለሰብ አገልጋይ ሆነ፡፡
ለማጠቃለል በምስራቅ አፍሪካ ጂዮ ፖለቲካ ትልቅ ስፍራ ባለት አገር ከሰባ ዓመት በላይ ከፍተኛ ሚና የተጫወተን ጦር ታሪክ ስንፅፍ
ምን፣ምን ጉዳዮችን ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን? ምን ዓይነት ጥንቃቄስ ማድረግ አለብን? የሚሉት ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ
አለባቸው፡፡ የቀድሞው ጦር በአገር ምስረታ (Nation Building) ላይ ትልቅ ሚና የተጫወተና በኢትዮጵያ ታሪክም ትልቅ ስፍራ
የሚሰጠው ነው፡፡ በርካታ ጀግኖችን ያፈራ፣ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፈ ነበር፡፡ ተሸንፏል፣ተበትኗል ብለን የምናጣጥለው አይደለም፡፡
ይህን የሚል አላዋቂነቱንና ድንቁርናውን ከማሳየት ውጭ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ታዲያ የዚህ ታላቅና ገናና የነበረ ተቋም ታሪክ
እንዴት ነው መፃፍ ያለበት? ታሪክን፣ፖለቲካ ሳይንስን፣ ወታደራዊ ሳይንስንና ማህበራዊ ሳይንስን እንዴት ነው አቀናጅተን ተዓማኒነት
ያለው ፅሁፍ የምናቀርበው? መጽሐፍ ዘመን ተሻጋሪ ነው፣ትውልድ ተሻጋሪ ነው፡፡ የመጽሐፍ ዋነኛ ዓላማ ዕውቀት መጨመር ነው፣
አዲስ አመለካከት ማሳየት ነው፡፡ ለጋዜጣና ለመጽሔት እንደምናደርገው የይድረስ ይድረስ ወይም በችኮላ የሚሰራ አይደለም፡፡ በአሁኑ
ወቅት በአገራችን የሚታተሙት አብዛኞቹ መጽሐፍት ከዚህ ችግር የፀዱ አይደሉም፡፡ ለሚነሱት ነጥቦች አፅንዖት ሰጥቶ፣ከስሜትና
ከወገናዊነት በፀዳ መልኩ በሳል ትንተና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት የመጽሐፉ አዘጋጆች በጉዳዩ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች
መሆናቸው መጽሐፉን በመረጃ በማበልፀግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ሊኖራቸው እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ ግን ምን ያህል ከወገንተኝነት
ሊፀዱ ይችላሉ? የታሪክ፣የፖለቲካና የወታደራዊ ሳይንስን ትንተናስ እንዴት አቀናጅተው ማቅረብ ይችላሉ? በበኩሌ ለዚህ ጥሩ መፍትሄ
ሊሆን ይችል የነበረው የመጽሐፍ ዝግጅት ኮሚቴው በተለያየ ሙያ ምሁራንን ያካተተ አማካሪ ቦርድ ቢኖረው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ
መጽሐፉ አላስፈላጊ ሃተታዎችን፣ድግግሞሾችን ከመያዙም በላይ በመጠኑም ቢሆን በጦር ክፍሎች መሐል (ለምሳሌ በክቡር ዘበኛ ላይ
የተሰጠው አስተያየት) ወገናዊነትን አሳይቷል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ጦሩ ለደረሱበት ሽንፈቶችና ውድቀቶች ዋና ዋና መንስሄዎችንና
ተጠያቂዎችንም ጭምር ለይቶ አላወጣም፡፡ ወታደራዊ ትንተናውም ጥልቀት ይጎድለዋል፤ተልፈስፍሷል፡፡ ጦሩን በሂደት በመበተን
በታሪክ ወንጀለኛ የሆኑትን ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያምን እንደጀግና ለመቁጠርም የመጽሐፉ አዘጋጆች ዳድቷቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳ
መጽሐፉ አዳዲስ መረጃዎችን በመያዝ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ቢሆንም አስተማሪነቱ ግን ተገድቧል፡፡




ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
June 9, 2014 

No comments:

Post a Comment