Monday, May 19, 2014

ልማታዊ መንግስት-እንደ ቻይና፤ ነገሩስ ባልከፋ



 ደስታው አንዳርጌ (ዶ/ር)

 ግንቦት ፲ ቀን ፪ሺ፮ ዓ.ም


እስያውያን፤ በተለይም ደግሞ ሀገረ ቻይና ለብዙ ድሃ አገራት አርዓያ የሚያደርጓት ብዙ ምክንያትቶች አሉ።
በዋነኝነት ግን ቻይና ከሌሎቹ የእስያ አገራት በተቃራኒ ተዓምራዊ እድገት ያስመዘገበችው በምዕራባውያን ድጋፍ
ሳይሆን ከምዕራባውያን ፍላጎት በተቃራኒ መሆኑ ነው። ምዕራባውያን እንደነ ጃፓን፣ ታይዋን፣ ደቡብ ኮሪያ
የመሳሰሉትን አገራት ለመደገፍ ግልጽ ጅኦፖለቲካዊ ምክንያት አላቸው። ቻይናን ግን ቢችሉ ቢኮረኩሟት
ይወዳሉ። በቻሉት መጠን ሲኮረኩሟትም ብዙ ጊዜ አይተናል። ምሳሌ ላቅርብ፤ ባለፉት ፳ አመታት ቻይና
ብቻዋን ከድህነት ማጥ ያወጣችው ህዝብ ቁጥር ሌላው አለም ባጠቃላይ ተደምሮ ካደረገው ሁሉ ይበልጣል። ይህ
ምናልባትም በታሪክ አቻ የሌለው ስኬት ነው። በአንጻሩ የጦር መሳሪያ በመሸመት በአለም ተወዳዳሪ የሌላት ሕንድ
አንድ ሦስተኛው ህዝቧ በየቀኑ በርሀብ አለንጋ ይገረፋል። ከዚህ በላይ የሰብአዊ መብት መጓደል የለም።
ምእራባዊያን መንግስታትና ተመሳሳይ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ምዕራባዊያን ‘የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች’ ግን
ህንድ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ያላግባብ (በነገራችን ላይ አገሪቱ ብዙ ሚሊዮን ቶን ትርፍ የምግብ እህል
ታመርታለች)በርሃብ ሲረግፍ ሳይሆን ቻይና ውስጥ አንድ ተቃዋሚ ሲታሰር ነው ሰብአዊ መብት ትዝ የሚላቸው።
እውነቱ ግን ቻይና ከሰብአዊ መብት ኣንጻር እንኳን ቢታይ ከብዙ አገራት (ከብዙ ምዕራባዊያንም ጭምር) የተሻለ
ሪኮርድ ነው ያላት። ስለሆነም በተለይ እንዳሁኑ አቅሟ ሳይፈረጥም በሚደርስባት ተፅእኖ ሳትበገር ለስኬት
በመብቃቷ ቻይና በራስ የመተማመንና በጥረት ለስኬት የመብቃት ተምሳሌት ተደርጋ ብትወሰድ አግባብ ነው።
ከዚህ አንጻር እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ድሀ አገራት የቻይናን አርዓያነት ቢከተሉ በመሰረቱ ችግር አይመስለኝም። ችግሩ
ቻይና ና ሌሎች እስያውያን የታደሉት ኢትዮጵያ የጎደላት በርካታ ቁም ነገሮች መኖራቸው ላይ ይመስለኛል።
የአንድን አገር ብልጽግና ከሚወስኑት ዋና ዋና ጉዳዮች ግንባር ቀደሞቹ፤ ብቃትና ተአማኒነት ያለው የፖለቲካ
አመራር፣ የዜጎች ሳይንሳዊነት፣ የአገር ፍቅርና የሃላፊነት ስሜት፣ የመቻቻልና የመተባበር መንፈስ፣ ታታሪነትና
ተወዳዳሪነት ይመስሉኛል። የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በእነዚህ ሚዛኖች እንየው፤

ሀ.. . . ተአማኒነት ያለው የፖለቲካ አመራር
ስኬታማወቹ የእስያ አገራት መንግስታት ሁሉም (ያለምንም ልዩነት) የሚያመሳስላቸው ቢኖር ጠንካራ ብሄርተኞች
መሆናቸው ነው። ለምሳሌ ከቻይና ጋር ወዳጅነት የሚፈልግ መንግስት ሁሉ በመጀመሪያ ‘አንድ ቻይና’ የሚል
መፈክር ማሰማት ይጠበቅበታል። ለ ‘አንድ ቻይና’ እውቅና ሳይሰጥ ከቻይና ጋር መልካም ግንኙነት ያለው
መንግስት የለም (ስለሆነም ታይዋን በጣም የበለጸገች ዲምክራሲያዊና የተረጋጋች አገር ብትሆንም ለዘመናት
ከጥቃቅን የፓስፊክ ደሴት አገሮች ውጭ እውቅና የሰጣት ብዙም አገር የለም)። ጠንካራ ብሄርተኝነት ማለት ይህ
ነው። ብሄርተኝነት የጎሰኝነት ተቃራኒ ነው፤ አንዱ ሲገን ሌላው ይቀጭጫል። ብሄርተኝነት አንድነትን ማጽናት
ሲሆን ጎሰኝነት በተቃራኒው አንድነትን መሸርሸር፣ ልዩነትን መስበክ ነው። ብሄርተኝነት እንደዝንጀሮ በጎሳ
ከመቧደን ወጥቶ እንደሰለጠኑት ሕዝቦች ዘመን በሚሻገሩ ሀሳቦችና ዘላቂ የጋራ ጥቅም ዙሪያ መተባበር ማለት
ነው። ብሄርተኝነት ከፖለቲካ በላይ ነው። ተወደደም ተጠላም የአለም ህዝብ የተዋቀረው በሉአላዊ አገራት ነው።
በአንድ ሉአላዊ አገር ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ደግሞ እጣቸው የተሳሰረ ነው። ከፖለቲካ በላይ የሆኑ ጉዳዮች የግድ
አንድ ያረጓቸዋል። የፈለገው ስልጣንና ገንዘብ ይኑርህ በኢትዮጵያዊነትህ ትለካለህ። አንድ ጊዜ የቀድሞው ጠቅላይ
ሚኒስትር ጂ፡፰ ስብሰባ ላይ ይመስለኛል የሚያናግረው አጥቶ ሲቁለጨለጭ አይተናል። አንዳንድ የዋህ
ኢትዮጵያውያን መለስን ስለሚጠሉ ብቻ በሁኔታው ቀልደዋል። ነገር ግን መለስ ከጆርጅ ቡሽ ያነሰ ፖለቲከኛ
ስለሆነ አልነበረም የሚያናግረው የጠፋው፤ የደሀና ለማኝ አገር መሪ ስለሆነ እንጂ። በሌላ አነጋገር የተዋረደው
መለስ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ነው። የአገር መሪም ብትሆን በደሀ አገርህ ሚዛን ነው የምትታየው። የትም አገር ሂድ
የየትኛው ጎሳ አባል መሆንህ ግድ የሚሰጠው የለም።

ብሄርተኝነት ፖለቲካዊ ችግሮች ቢኖሩም እንኳን ከፖሊቲካ በላይ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አንድ መሆን ማለት
ነው። ብሄርተኝነት ለየትኛውም የውጭ ሀይል በር አለመስጠት ማለት ነው። ብሄርተኝነት እንኳን የኢትዮጵያን
ጥፋት ከሚመኙ (ሸአቢያን ከመሰሉ) ሀይሎች ይቅርና ኢትዮጵያ ውስጥ ሰብአዊ መብት እንዲከበር እንታገላለን
ከሚሉን የውጭ ሀይሎች (ሃሳዊ መሳዮች) ጋር አለማበር ማለት ነው። ብሄርተኝነት የአሜሪካ መንግስት ወያኔን  2
እንዲያስታግስልህ አለመማጸንም ነው። ብሄርተኝነት እንደ ቻይና በራስ መተማመን ነው። ብሄርተኝነት እኛ
ኢትዮጵያውያን የራሳችን ችግሮች ራሳችን መፍታት እንችላለን ብሎ ከልብ ማመን ነው። ብሄርተኝነት ያለጥርጥር
ሀይል ነው (በጣም ተለጥጦ ወደእብሪት እስካልሄደ ድረስ)። ከነቻይናና ሌሎች እስያውያን ስኬት ጀርባ ያለው
አንዱ ሚስጥር ይህ ሃይል ነው። ወደኛ ስንመጣ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ያሚተጋ መንግስት ነው ያለን። ጎሰኛ
መንግስት ደግሞ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አስተባብሮ እንደቻይና ተአምር ለመስራት ዕድል የለውም። አብዛኛው
ተቃዋሚም ቢሆን አንጋጦ የውጭ አዳኝ (ኤክስተርናል ሳልቬሽን) የሚጠብቅ ነው። በኢትዮጵያውያን ህዝብ
ሀይል(ኤጄንሲ)ሳይሆን በሃሳባዊ የውጭ ድጋፍ የሚተማመነው ይበዛል። ለመረጣቸው ህዝብ ጊዜ ያልነበራቸው
የቅንጅት መሪወች ከእስር በተፈቱ ማግስት ወደውጭ ለመፈርጠጥ እንዴት እንደተራወጡ ማስታወስ ብቻ በቂ
ነው።

ሌላው ቻይና ውስጥ የፓርቲ አምባገነንነት እንጅ የግለሰብ አምባገነንነት የለም። የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ አመራር
በየጊዜው በሚደረግ ምርጫ ይቀየራል። ያ ደግሞ ተጠያቂነት እዲኖር ያደርጋል። ከምንም በላይ የቻይና መንግስት
ሊብራል ባይሆንም ጨዋ(ዲሰንት)መሆኑ አይካድም። ወደኛ ስንመጣ ሊብራሊዝምን በታሪካችን አናውቀውም።
ጨዋ(ስልጡን) መንግስታት ግን ነበሩን። ለምሣሌ በንጉሱ ዘመን ተማሪዎች ፊውዳሊዝም ይውደም እያሉ ሲፎክሩ
የጸጥታ ሀይሎች በሰለጠነው አለም እንደምናየው መስመራቸውን ጠብቀው ሁኔታውን ይከታተላሉ እንጅ በጥይት
ጭንቅላት ሲመቱ አልታዩም። በአጠቃላይ በንጉሱ ረጅም የስልጣን ዘመን በፖለቲካ ምክንያት ያለፍርድ የተገደሉት
ሰወች በጣት ይቆጠራሉ። ደርግ ሲመጣ ያ ጨዋነት ገደል ገባ። ቢሆንም የደርግ ሹማምንቶች አገር ሽጠዋል ወይ
ደግሞ ሚሊዮን ብር ዘርፈው ወደ ውጭ አሽሽተዋል ያላቸው የለም። ስለዚህ ቢያንስ የሚታመኑበት አንድ ሁለት
ጉዳዮች ነበሯቸው ማለት ነው። ህወሃት/ኢህአዲግን ግን ይህን አያደርግም ብሎ የሚወራረድ አይገኝም።
በኢትዮጵያ መንግስታት ታሪክ ከስልጣናቸውና ከገንዘብ በላይ የሚያዩት ቁምነገር የሌላቸው ምንም አይነት
የሃይማኖት፣ የአይዲዮሎጂ፣ ወይ ደግሞ የሞራል ገደብ (ሪስትሪየንት) የሌላቸው ይህን አያረጉም የማይባሉ ርጉሞች
እነሱ ብቻ ይመስሉኛል። እድገት ይሏችኋል ይሄ ነው…

ለ.. . . ሳይንሳዊነት ሳይንሳዊነት ሳይንሳዊነት (እውቀትና ዕምነት)
የሰውልጅ ታሪክ ረጅም ነው። የኢኮኖሚ ብልጽግና ታሪክ ግን ግፋ ቢል ከሁለት መቶ ዓመት አይዘልም።
አብዛኛው የሰውልጅ ታሪክ የድህነተና የጉስቁልና ነው። ከስምንት ሺ አመት በፊት (ኒኦሌቲክ ዘመን በሚባለው)
ጊዜ የሰው ልጅ አደንና ፍራፍሬ ለቀማን ትቶ እርሻ እንደጀመረ ይታመናል። ከተሞች ተቆረቆሩ፤ ንግድም ተጀመረ።
ይሁን እንጅ ረሀብና ቸነፈር በየጊዜው ይጨርሰው ስለነበር የአለም ህዝብ ቁጥር ፩ ቢሊዮን የሞላው ከብዙ ሺ
አመታት በኋላ በ ፲ ፻፰፻ (1800) ዓ.ም አካባቢ ነው። ከዚያ ግን ፪ ቢሊዮን ለመሙላት ፻፳፫ (123) አመታትን
ነው የፈጀበት። ፫ ቢሊዮን ለመሙላት ደግሞ ፴፫ (33) አመታትን ብቻ። ይህ የሆነው በተአምር አይደለም።
በተለይ የአውሮፓውያንን የኢንዱስትሪ አብዮት ተከትሎ ለበርካታ በሽታዎች መድሃኒት መስራት በመቻሉና
ለህይዎት አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮችን በዋንኛነት ምግብን በቀላሉ ማምረት በመቻሉ እንጂ። ባጭሩ በሰውልጅ
ረጅም የጉስቁልና ታሪክና አጭር የብልጽግና ጉዞ መካከል ያለው ልዩነት አንድ ብቻ ነው፤ ሳይንስ። ርግጥ ነው፤
ሳይንስ ለጥፋትም ሊውል ይችላል። ነገር ግን ወደ እውቀትና እድገት የሚያደርሰው መንገድ ሳይንስ ብቻ ነው።

እድገት በምትሀት አይመጣም። ለምሳሌ ስለተዓምራዊ የኢኮኖሚ እድገት ሲነሳ ጃፓን በግንባርቀደምትነት
ትጠቀሳለች። ርግጥ ነው ጃፓን በሁለተኛው የአለም ጦርነት ዶግ አመድ ሆና ነበር። ብዙዎቻችን ስለ ሂሮሽማና
ናጋሳኪ ሰምተናል። ነገር ግን የጃፓን ዋና ዋና ከተሞች በሞላ በኢንሴንዴሪ ቦምብ ጋይተው በአገሩ መጠለያ፣
የሚላስ-የሚቀመስ ጠፍቶ ነበር። ይሁን እንጅ ጃፓናዊያን አገራቸውን መለሶ መገንባት ብቻ ሳይሆን በአለም
ሁለተኛዋ ታላቅ ኢኮኖሚ ለማድረግ የፈጀባቸው ሶስት አስርት አመታት ብቻ ነበር። ይህ የሆነው ግን
እንደሚባለው በተአምር ሳይሆን ጃፓናውያን ምናልባትም በአለም ላይ አቻ የሌለው የአገር ፍቅርና ታታሪነት
የታደሉ ብቻ ሳይሆኑ በሳይንሳዊ እውቀት የበለጸጉ ስለሆኑ ነው። በ ፲ ፱ ነኛው መቶ ክፍለዘመን እንኳን ጃፓን
ከአውሮፓውያን (ይህ ማለት ከአለም)የላቀ የእውቀት ብርሀን (ሊትሬሲ ሬት) ነበራቸው። በተመሳሳይ ዛሬ ሁሉም
ሰው ስለ ቻይና ተዓምራዊ እድገት ያወራል። ብዙ ሰው ግን ቻይና ኢኮኖሚዋ ከመተኮሱ ከአርባና አምሳ አመት
በፊት እጂግ ግዙፍ የተማረ የሰው ሀይል እንደነበራት ይዘነጋል። እድገት የሚጀምርው ከሰወች አስተሳሰብ ነው።
የአንድ አገር ህዝብ ሳይንሳዊ እውቀት ከታጠቀ፣ የአገር ፍቅር፣ የመተባበር መንፈስ፣ ታታሪነት፣ መቻቻልን
ከተጎናጸፈ መንገዱና ህንጻው ዝርዝር ጉዳይ ነው፤ በአጭር ጊዜ የሚደርስ። እስያውያን ለሳይንስ በጣም ቅርብ
ናቸው።

ወደኛ ስንመጣ በመጀመሪያ ስለሳይንስም ስለእድገትም ያለን ግንዛቤ ግራ ያጋባል። በልመና ገንዘብ በልመና ባለሞያ
የተሰራ ህንጻ የእድገት ምልክት የሚመስለን ብዙ ነን። ዱቄት መለመን ራሱ ሞት ነው። ጋጋሪ መለመን ግን የሞት  3
ሞት ነው። እኛ ግን ዱቄት ለምነን፤ ጋጋሪ ለምነን ባስጋገርነው ቂጣ ተዓምር የፈጠርን ያህል አገር አይብቃን ስንል
ሀፍረት እንኳን አይሰማንም። ከእውቀትና ከእውነት ጋር ተጣልተን የምንኖር ይመስለኛል። ድርቅ ያለ እውነት
አንወድም። ፕሮፌሰር መስፍን አንድ ጊዜ አበሻ ስንት ልጆች አሉህ ብትለው ክብሩ ይስፋ ሁለት ሶስት አሉኝ እንጂ
ሁለት ወይም ሶስት ብሎ ርግጡን አይናገርም ያሉት ትዝ ይለኛል። ሪኮርድ አንዎድም። ሌላው ቀርቶ እድሜያችን
እንኳን ስንጠየቅ የምንደናገጥ ብዙዎቻችን ነን። ለአበሻ ሁሉ ነገር የእምነትና የምልኪ ጉዳይ ነው። ሽዎች በየጊዜው
በርሀብ የሚረግፉባት አገር እየኖርን ‘ፈጣሪ የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው አያድርም’ እያል የምንቀልድ ጀግኖች እኮ
ነን። ለምን እንደሆነ አላውቅም በምናየው ነገር አናምንም፤ ወይም የምናየውን አናስተውልም። ተምረንም
ከሳይንሳዊ አስተሳሰብ ጋር ብዙም አንላመድም።

ሐ.... የአገር ፍቅርና የሃላፊነት ስሜት
መንግስትን ማማት በጣም ቀላል ነው፤ የሚቸግረው ራስን መጠየቅ ነው። ባላፉት በርካታ አመታት ኢትዮጵያ
ውስጥ የተወጠኑ ጅምሮች ሁሉም ማለት ይቻላል ከሽፈዋል(የፕሮፌሰሩን ቃል ልዋስና)። ችግራችን ፖሊቲካዊ
ቢሆን ኑሮ ይህ ባልሆነ። ቢያንስ ፖለቲካዊ ያልሆኑ ጉዳዮች ለምን ይከሽፋሉ? እንዲያውም የኢትየጵያ (በአጠቃላይ
የአፍሪካ) ችግር በመሰረቱ ፖለቲካዊ አይመስልም። ችግሩ ፖሊቲካዊ ቢሆን ኑሮ ናጽነትን መረጡ የተባሉት
ወገኖቻችን አሁንም ናጽነት ላም አለኝ በሰማይ ባልሆነባቸው ነበር። የአንድ አገር ፖለቲካ ከዚያ አገር ህዝብ
ተጨባጭ ሁኔታ (ማለትም ታሪክ፣ባህል፣ አስተሳሰብ፣ ስልጣኔ፣ ወዘተ)ውጭ ሊሆን አይችልም። ወያኔ
ተቃዋሚዎችን አይታገስም ስንል በታሪካችን ነገስታት በተቀቡ ማግስት የመጀመሪያ ስራቸው ወንድሞቻቸውን
አምባ ማጎር መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል። ሌላው ቀርቶ በተቃዋሚው ጎራ ያሉት አንዳንዶቹ መሪዎች ያው
እንደወያኔ መሪወች ለ፳ ምናምን አመታት አልተቀየሩም። ብዙወቹ እንደወያኔ በመርህ ሳይሆን በቋንቋ የተደራጁ
ናቸው (አቅም የሌላቸው ወያኔወች/መለሶች ሊባሉ ይችላሉ)። አመራራቸው በማያሻማ ሁኔታ ከሽፏል (ይህቺ ቃል
ተመችታኛለች)፤ እነሱ ግን ቦታ አይለቁም። በወያኔ የመጀመሪያ ዓመታት እነ መለስ የባህር በር ከግመል
ማጠጫነት ያለፈ ጥቅም የለውም ሲሉ፤ አወ ርግጥ ነው እያሉ ሲያጨበጭቡ የነበሩ አሁን ደግሞ ተቃዋሚ ነን
የሚሉ ብዙወች እንዳሉም እናውቃለን። ሌሎቹ ደግሞ ከወያኔ ጋር ሊሄዱ የሚችሉትን ያህል ሄደው ያሰቡትን
ያህል ጥቅም አላገኝ ሲሉ ወይም ተፈላጊነታቸው ሲቀዘቅዝ ተገልብጠው ተቃዋሚ ነን የሚሉ ናቸው። ከዚያ በቃ
ሲያጎበደዱላቸው የነበሩትን ጌቶቻቸውን ገመና ያለሀፍረት መቀባጠር ውርደት ሳይሆን ጀብዱ የሚመስላቸው
ናቸው (በጣም የሚገርመው እንደነዚህ ያሉ ነውረኞች ሰሚ ያገኛሉ)። ጡሬታ ሲወጣ ኢትዮጵያ ትዝ የምትለውም
ብዙ ነው። ስለሆነም ባህላችን (በተለይም የሞራል እሴቶቻችን) መመርመር የሚያስፈልግ ይመስላል።

በጣም የሚቸግረን ሌላው ጉዳይ ደግሞ ለስራችን ሀላፊነት መውሰድ ነው። ሁልጊዜ ሃላፊነቱን ለሆነ አካል ነው
የምናስተላልፈው። ቢቻል ደግሞ ያ አካል የማይታይ ቢሆን ይመረጣል። ለምሳሌ ሰውየው ሚስቱን አንቆ የገደላት
ክፉ ወይም ደደብ ስለሆነ ሳይሆን ሰይጣን አሳስቶት ነው፤ ወይ ቀን ጥሎት። ያ ሁሉ ካልተሳካ ግን ሃላፊነቱን
የግድ መንግስት መውሰድ ይኖርበታል። ሀላፊነቱን ለውጭ ሀይሎች ማስተላለፍም በኛ ቤት ችግር የለውም።
ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህና ነጻነት እንዲኖር ማድረግ የአሜሪካ መንግስት ሀላፊነት ነው። በየጊዜው
ዋሽንግተን ዲሲ የሚካሄደው ሰልፍ እኮ አላማው አሜሪካ ይህን ሀላፊነቷን እንዳትዘነጋ ለማስታወስ ነው።
ፕሬዘደንት ኦባማ ምነው ከዳኸን አይነት ሮሮም በየጊዜው እንሰማለን፤ አፍሪካን ማስተካከል የፕሬዘደንቱ የቤት
ስራ ይመስል። ድርቅ ብለን የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከታችኋል የምንላቸው ሀይሎች መብዛታቸው! ሃላፊነቱ
ለጠላት ማስተላለፍም ቢሆን ለኛ ችግር የለውም። ለምሳሌ ወያኔ የበተናቸው የደርግ ሰራዊት አባላት ለደረሰባቸው
ውርደት ራሳቸውን አይደለም የጠየቁት፤ ሃላፊነቱ የወያኔ ነው። የአመራር ችግር ነው ወዘተ እያሉ ከሀላፊነት መሸሽ
ይቻል ይሆናል፤ እውነቱ ግን ራሱን መከላከል የማይችልን ሰራዊት ከመበተን ውጭ ምን ምርጫ ይኖራል?

ለበጎውም ለክፉውም ተጠያቂው ሁልጊዜ ሌላ ነው። እንዲያውም ይህ የአፍሪካውያን በተለይም የምስራቅ አፍሪካ
ችግር ይመስለኛል። ለምሳሌ ሶማሊያ ሂዳችሁ አንድን ሶማሌ ለምንድነው መንግስት የሌላችሁ፤ ይህን ያህል ጊዜ
የአለም መሳቂያ የሆናችሁ ብላችሁ ብትጠይቁት መልሱ ‘በኢትዮጵያ ምክንያት ነው’ ነው ሊሆን የሚችለው።
ራስን መጠየቅ፤ እውነታን መጋፈጥ መንፈሳዊ ወኔ ይጠይቃላ። ቅንጅት ፈረሰ። ማን አፈረሰው? አቶ እከሌ። አለቀ።
ከዚያ በቃ ስድብና አሉባልታ ነው። አንዴት አርጎ አፈረሰው? በምን ምክንያት አፈረሰው? የሚሊዮኖችን ድርጅት
አንድ ሰው እንዲያፈርሰው አንዴት እንፈቅድለታለን፤ እኛ ሞተን ነው በቁማችን? አንዱ ፓርቲ ቢያፈገፍግስ የቀሩቱ
ለምን አልቀጠሉም? ወዘተ የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ማንሳት ከእውነት ጋር መታረቅን፤ ሀላፊነት መውሰድን
ይጠይቃል። ራስን መጠየቅ ደግሞ በጣም ያስፈራል። ለሁሉም ችግር ወያኔን እያሙ መኖር ሲቻል ለምን ራስህን
ትጠይቃለህ? ግን ከእውነት የተጣላ ህዝብ ትንሳዔ አይኖረውም። እውነት መነጋገር መጀመር ይኖርብናል።
መንግስት ከሰማይ አይወርድም፤ ከህዝቡ ነው የሚወጣው። ቀዳማውዊ ኃይለስላሴ አርበኞችን እያገለሉ ባንዳ
በመሾም ይወቀሳሉ። እውነቱ ግን ግማሹ የኢትዮጵያ ህዝብ በሰባራ የጣሊያን ሊሬ የሚታለል ባንዳ ነበር። እነበላይ  4
ዘለቀን አምስት አመት ሙሉ ሲጠዘጥዛቸው የነበረው የጣሊያን ወታደር ሳይሆን በሰባራ ሊሬ የተገዛ ጎጃሜ ነበር።
በትግራይ፣ በጎንደር፣ በኢሊባቦር ወዘተ ብናይ ታሪኩ ተመሳሳይ ነው። መለስ ዜናዊ የባንዳ ልጅ መሆኑን ስንናገር ያ
የብዙ ኢትዮጵያውያን ታሪክ መሆኑንና በዘመኑ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ስለኢትዮጵያዊነት ብዙም እውቀት
የሌለው ከቤተሰቡና ከጎጡ ያለፈ ማሰብ የማይችል መሃይም መሆኑን እንረሳለን። ዐጼ ምኒሊክ የአድዋን ዘመቻ
ሲያውጁኮ ለኢትዮጵያ ህዝብ አገራችን ተደፍራለችና ጠላታችን መክተን እንመልስ አይደለም ያሉት፤ ለልጆችህ፣
ለሚስትህና ለዕምነትህ ስትል ተከተለኝ ነው ያሉት። በሚገባው ቋንቋ፤ በግል ህይወቱ ነው የመጡበት። ያኔ ይቅርና
በ ፳፩ ኛው ክፍለ ዘመን ለምን ከተማ ይስፋፋል ብሎ የሚቃወም ከጎጡ ያለፈ ማሰብ የማይችል ትውልድ እኮ
ነው ያለው (የፖሊቲካ ትርፍ የሚያገኙ መስሏቸው እንዲህ አይነቱ ጎጠኛ ጥያቄ ፍትሀዊ መሆኑን ሊነግሩን የሞከሩ
‘ተንታኞችም’ አይተናል)። ይህ ሁሉ የመንግስት ፖሊሲ ያመጣው ነው ምናምን ማለት ይቻላል። ነገር ግን
መንግስት ጭንቀላቱን የወሰደበት ሰው የለም፤ ማሰብ መቻል የእያንዳንዱ ሰው ሀላፊነት ነው።

እንዲያውም ስለተጠያቂነትን አመክኗዊ ብንሆን ከብዙ ስህተት በዳንን። ከአስር አመት በፊት የገጠመኝን
ላውጋችሁ። አንድ አዲስ አበባ ሜክሲኮ ታክሲ መያዣው ላይ የሚለምኑ ትግሬ ነበሩ። አንድ ቀን ታክሲ ውስጥ
እያለሁ እኒያ ትግሬ መጥተው ስለአቡነአረጋዊ ብለው ይለምናሉ። ፊት የተቀመጠው ተሳፋሪ ብስጭት ብሉ ሂድ
ከዚህ አንተ ቆሽቋሻ ትግሬ፤ ኧረ ከላይና ከታች ሁናችሁ እንደ ሳንዱይች ጠበሳችሁን ሲል ሁላችንም ባነጋገሩ
ሳቅን። ግን በምን ሂሳብ ይሆን ወያኔ በሚሰራው ግፍ እኒያ ምስኪን የሚጠየቁት? እንደአብዛኛው ኢትዮጵያዊ
በፍርሃትና በጉስቁልና የሚኖር ትግሬ ምን ተጠያቂነት አለበት? ህዝባዊ ውክልና የሌለው አምባገነን መንግስት
ይቅርና በህዝብ የተመረጠ መንግስት እንኳን ቢሆን ለሰራው በደል ተጠያቂነትቱ ያ መንግስት በሰራው ወንጀል
ተሳታፊ የሆኑት ግለሰቦች ብቻ ናቸው። በመንግስት ሀጢያት ህዝብ የሚጠየቀው በምን ሎጂክ ነው? ባለፉት
ዘመናት ‘የአማራ’ ገዥዎች የፈጸሙት በደል ካለ (ካለ የምለው በአለም ላይ ጉልበት እንጂ ሰብአዊ መብት የሚባል
ጽንሰ ሀሳብ ባልነበረበት ዘመን የነበሩ ነገስታትን በሰብአዊ መብት ጥሰት መክሰስ መሀይምነት ስለሚመስለኝ ነው)
አብሮ ሲበደል የኖረው አማርኛ ተናጋሪ ህዝብ ምን ተጠያቂነት አለበት? አንድ ሰው እንኳን በገዥወቹ በደል
ይቅርና ወላጅ አባቱ በሰራው ወንጀልም የሚጠየቅበት ምክንያት የለም። አብዛኞቻችን ግን ከስሜት ሆያሆየ
ወጥተን እንዲህ ያሉ እውነቶችን መቀበል ያስቸግረናል።

መ.... የመቻቻልና የመተባበር መንፈስ
መቻቻልና መተባበር ለአፊሪካውያን ብርቅ ናቸው። ብዙ ሰው ይህን አለመቻቻል የአፍሪካ ህዝቦች የተለያየ ቋንቋ
ተናጋሪ ከመሆናቸው ጋር ያያይዙታል። ይህ ስህተት ነው። ሲጀመር የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩት የአፍሪካ ህዝቦች
ብቻ አይደሉም። እንዲያውም የቋንቋና ሀይማኖት መመሳሰል የመቻቻል ቅመም ቢሆን ኖሮ ሶማሊያ የመቻቻል
ተምሳሌት በሆነች ነበር። እውነቱ ከድንቁርና ወጥቶ አጎጥ ባሻገር ማየት አለመቻል ነው። ችግሩ ሳይለፉ ባቋራጭ
ደጃዝማች መሆን መፈለግ ነው። ለምሳሌ በጎሳ የተደራጁ የፖለቲካ ቡድኖች ሁሉ የጎሳቸው ዘላቂ ጥቅም
ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም የተለየ እንዳልሆነ የሚረዱ ይመስለኛል። ግልጽ እኮ ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ
መሰረታዊ ችግር ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ የፍትህ መጓደል፣ የዲሞክራሲና ነጻነት እጦት ወዘተ ናቸው። እነዚህ ችግሮች
ደግሞ ሊወገዱ የሚችሉት በየጎጡ በመፍጨርጨር ሳይሆን አገራዊ ራዕይ ሰንቆ በጋራ በመስራት ነው። እያደጉ
ያሉት እስያዊያንም ሆነ ሌሎች የበለጸጉ አገራት ታሪክ በሙሉ የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው። ነገር ግን ራሳቸውን
የየጎሳቸው የማይተካ ደጃዝማች አርገው የሚያቀርቡ ግለሰቦች ከሌላው ጋር በጋራ ለመስራት ያስፈራቸዋል።
ውድድር ያስፈራላ። ከሌላው ጋር መስራት በቋንቋ አጋጣሚ ሳይሆን በሀሳብ ጥራትና ተጨባጭ ውጤት መመዘን
ያስከትላላ። ኤርትራ ባትገነጠል ኑሮ ወይ መለስ ወይ ኢሳያስ ምትክ የሌለው መሪ የመሆን እድላቸው ያከትም
ነበር። ያን ደግሞ አይፈልጉትም። አሁንም እኮ በኢትዮጵያ ‘ቅኝ ገዥነት’ ተማረው መገንጠል የሚሹት ሀይሎች
ህልማቸው ራሳቸውን እንደ ኢሳያስ ምትክ የሌለው መሪ ማድረግ ነው። እንጂማ ኤርትራን ማየት ብቻ ከመገንጠል
የሚያተርፍ እንደሌለ በተረዱ ነበር። መቸም ከኤርትራ የተሻለ ስትራቴጂካዊ መልክዐምድር ወይ ደግሞ ከሸአቢያ
የተሻለ አደረጃጀትና የአመራር ልምድ አለን ብለው እንደማያስቡ እገምታለሁ።

በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመተባበር ተመሳሳይ መልክ፣ ጸባይ፣ የፖሊቲካ አቋም ወዘተ አያስፈልግም። እንደ ህዝብ
ዘላቂ ጥቅማችን የተሳሰረ መሆኑን መረዳት ብቻ ይበቃል። ብዙወቻችን ግን ሁሉን ነገር በአጭር ጊዜ የፖለቲካ
መነጽር ነው የምናየው። ወያኔ ግድብ ሲሰራ የሚያማቸው ኢትዮጵያውያንን ማየት በጣም ያማል። የረቀቀ አጀንዳ
ካላቸው ምዕራባውያን ‘የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች’ ጋር ሆነን በማናውቀው የምንጮህም አለን። ሰማኒያ
በመቶው ህዝብ የኤሌክትሪክ ብርሀን በማያውቅበትና የአገሪቱ የደን ሽፋን በአስደንጋጭ ሁኔታ ተጨፍጭፎ እያለቀ
ባለበት አገር ይኼ ግድብ ያንን ደረጃ (ስታንዳርድ) አያሟላም ወዘተ እያሉ አፍሪካን ከትርፍ የምግብ እህል
ማራገፊያነት ባለፈ የማያዮ ተመጻዳቂዎችን ፕሮፖጋንዳ ማስተጋባት ደመኝነት ነው። አላማችን አገራዊ ከሆነ ወያኔ
ይቅርና ሰይጣንም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ግድብ የሚሰራ ከሆነ ከቻልን ድንጋይ ማቀበል ነው ያለብን። መተባበር  5
ያለብህ ለኢትዮጵያ ስለሚበጅ እንጂ ግላዊ የአጭር ጊዜ ትርፍ ስለሚያስገኝልህ መሆን የለበትም። ከእስያውያን
መማር ያለብን ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ይህ ይመስለኛል፤ ትልቁን ስዕል ማየት።

ሠ.. . . ታታሪነትና ተወዳዳሪነት ተወዳዳሪነት ተወዳዳሪነት
ኢትዮጵያውያን ሰነፎች ነን በሚለው ቁንጽል አነጋገር አልስማማም። የአገራችን ገበሬና ነጋዴ የምሳ ጊዜ እንኳን
አያውቅም። የተማረውም ቢሆን ለግል ጉዳዩ ልቡ እስኪጠፋ ነው የሚሰራው። አበሻ የሚያለምጠው የሚሰራው
ስራ የተለየ የአጭር ጊዜ የግል ጥቅም ካላስገኘለት ብቻ ነው። ለምሳሌ ተቀጣሪ ሲሆን ቢተጋም ባይተጋም ደመወዙ
እንደማይቀርበት ያውቃል። ያኔ ማልመጡ ነው። የሃላፊነት ስሜት ለአብዛኞቻችን ባዕድ ነው። የአገር ፍቅርም
በአብዛኛው ከፉከራ አያልፍም። እያንዳንዳችን በየተሰማራንበት የምናደርገው ተደምሮ አገራዊ ፋይዳ እንዳለው ያ
ደግሞ ሲሆን በህይወታችን የምናየው ያ ባይሆን እንኳን ልጆቻችን አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ
የሚያስችል ውጤት እንደሚያመጣ ወይ አይገባንም ወይ ግድ የለንም። ደሀ የሆንነው በምርጫችን መሆኑን
የምንረዳ አይመስልም። በድሮው ጊዜ ድህነት እዳ ነበር፤ አሁን ግን ምርጫ ነው። ድህነት ማጥፋት ተዓምር
መስራትን አይጠይቅም። ድህነትን የተጸየፉ ህዝቦች በአጭር ጊዜ አሽቀንጥረው ሲጥሉት አይተናል። እኛም
ድህነትን አሽቀንጥረን የማንጥልበት ምንም ምክንያት የለም፤ ግን ሀላፊነት መውሰድ ይኖርብናል። ያ ደግሞ ሁሉን
መቃወም ብቻ ሳይሆን መደጋገፍን ይጠይቃል። ተወዳዳሪነትንና በተገቢ ውድድር ማመንን ይጠይቃል።
አውቃለሁ ውድድር ለብዙወቻችን ያስፈራል። ለምሳሌ በአራችን ወደ መቶ የሚጠጉ የፖለቲካ ፓርቲወች አሉ።
አንድላይ የማይሰሩት መሰረታዊ የሆነ የአይዲዮሎጂ ወይም ሌላ ልዩነት ስላላቸው አይደለም፤ ውድድርን
ስለሚፈሩ እንጂ። ሁሉም ራሱን የየጎሳው እንደራሴ አድርጎ የሚያቀርበው እኮ በዋነኝነት ውድድርን ከመፍራት
ነው። የግላችን የሆነው ተምረንም የማይለቀን ምቀኝነት የሚባል በሽታ በመሰረቱ ጤናማ ውድድርን ከመፍራት
ነው የሚሚነጨው፤ ከውድድር ጣጣ ለመዳን ተወዳዳሪውን ማጥፋት። መቀጠል ይቻላል።

ማጠቃለያ
እንደቻይና ብልጽግናን የሚሻ ህዝብና መንግስት እንደቻይናውያን በኮንፊሸሲዝም ማመን የለበትም።
እንደቻይናውያን ጠንካራ አገራዊ ራዕይ፣ እውነተኛ የአገር ፍቅርና የሃላፊነት ስሜት፣ የመቻቻልና የመተባበር
መንፈስ፣ ታታሪነትና ተወዳዳሪነት ሊኖሩት ግን የግድ ይላል። ከምንም በላይ አንድ ህዝብ የራሱን መስቀል
መሸከም የግድ ይለዋል። በአለም ታሪክ ዋሽንግተን ዲሲ በመሰለፍ የመጣ ለውጥ ስለመኖሩ አንድም ማስረጃ
የለም፤ ሊኖርም አይችልም። ሰብአዊ መብት፣ የህግ የበላይነት ወዘተ ከዲስኩር (ሪቶሪክ) ባለፈ የማንም አገር
የውጭ ፖሊሲ ማጠንጠኛ ሆኖ አያውቅም። አለም አሁንም በአመዛኙ የውድድር እንጂ የትብብር መድረክ
አይደለችም። ስለሆነም የምር ለውጥ ከፈለግን በግልም በጋራም መጠየቅ ያለብን ራሳችንን ይመስለኛል። በዚሁ
ላብቃ።

ስላም

No comments:

Post a Comment