የደሴው ሰላማዊ ሰልፍ በድምቀት ተካሄደ! (ከተጨማሪ ፎቶዎች ጋር)
(EMF) ዛሬ መጋቢት 28 ቀን በደሴ የሚደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ ያስተባበረው አንድነት ፓርቲ ነው:: የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት በትላንትናው እለት ቅስቀሳ እያደረጉ በነበረበት ወቅት ፖሊስ እና ደህንነቶች ቅስቀሳውን ለማስቆም ጥረት አድርገው ነበር:: በተለለይም የከተማው የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ ነው የተባለው ሰው የቅስቀሳ መሳሪያዎችን ጭምር ለመንጠቅ ሙከራ አድርጎ ነበር – ባይሳካለትም::
ይህ ሁሉ አልፎ ዛሬ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ በአስተዳደሩ ላይ በተለይም በመሬት ይዞታ ባለቤትነት ጉዳይ እና አላግባብ ስለታሰሩት ኢትዮጵያውያን ድምጹን ከፍ አድርጎ እያሰማ ይገኛል:: ሰላማዊ ሰልፉ እንደተጀመረ ፖሊስ መንገዱን በመዝጋት ሰልፈኛውን ለማወክ ጥረት አድርጎ ነበር:: ህዝቡ ግን ፖሊስን እየጣሰ ሰልፉን በሰላማዊ መንገድ እያደረገ ነው::


በሰልፉ ላይ…
-ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀል ይቁም
- መሬት ለህዝብ ይመለስ
- ጭቆና በቃን
- ድል የህዝብ ነው
- በግፍ የታሰሩ ይፈቱ
- መሬት ከካድሬው ወደ ህዝቡ ይመለስ
- አንድነት ኃይል ነው
- የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ… የሚሉ መፈክሮች ሲስተጋቡ ነበር::
ለተሰበሰበውም ህዝብ በደሴ የአንድነት ተወካይ በቅድሚያ ንግግር አድርገዋል:: ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ እና የአንድነት ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ተክሌ በቀለ ንግግር አድርገው ሰላማዊ ሰልፉ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ተጠናቋል:: የደሴም ህዝብ ብሶቱን የሚያሰማበት መድረክ በመፈጠሩ ምስጋናውን ለፓርቲው አመራሮች አቅርቧል::
ተጨማሪ ፎቶዎችን ከፓርቲው ምንጮች ስናገኝ በርከት አድርገን እናቀርባለን!
No comments:
Post a Comment