Monday, March 24, 2014

ደ.ኢ.ህ.ዴ.ን ፓርቲ Vs ሚዲያ

ደ.ኢ.ህ.ዴ.ን
ፓርቲ Vs ሚዲያ
 ከዲበኩሉ/አዋሳ/
አንዳንድ ጊዜ የሚዲያ ባለሙያ ከመሆን ታዳሚ መሆን ምንኛ መታደል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ምንም እንኳ በመንግስት የሚዲያ ተቋም ውስጥ የምሰራና ለጉዳዩ የበለጠ ቅርብ መሆኔን
ሳስበው እየሆነ ያለው ድራማ የቶሚና ጄሪ አይነት ነገር ይሆንብኛል፡፡ እንደአገራችን ተጨባጭ
ሁኔታ በመንግስት ሚዲያውና በገዢው ፓርቲ መካከል ያለው ግንኙነት ብዙ ሊባልለትም ብዙ
ሊባልበትም የሚችል ነው፡፡ አጠቃሎ መናገሩ አንሸራታች ቁልቁለት ነው እንጂ ብዙዎቹ
የገዢው ፓርቲ ድርጅቶች እና ፖለቲከኞች ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን ብዙዎቹ ጋዜጠኞች
በምንረዳበት መጠንና ልክ የሚረዱም የሚደግፉም አይመስለኝም፡፡ ለብዙዎቹ ሚዲያ ማለት
ተራ ሐሳብ ማስተላለፊያ መሣሪያ እንጂ ከዚህ የዘለለ ጽንሰ ሀሳብ ያለው አይመስላቸውም፡፡
ዝርዝሩ ይቆየንና የመንግስት ሚዲያውና ፓርቲው ባላቸው ግንኙነት አንድ ነጠላ ጉዳይ ላይ
ትኩረት ላድርግ፡፡
እርግጥ ነው ይህ ጉዳይ አዲስ አይደለም፡፡ ሲባልና ሲወቀጥ የቆየ አጀንዳ ነው፡፡ መንግስትም
በበኩሉ ሚዲያው የህዝብ እንጂ የፓርቲው ልሳን አይደለም ሲል ለዘመናት ተሟግቷል፡፡
ለማሳመንም ያልወጣው ተራራ ያልወረደው ቁልቁለት የለም፡፡ ይልቁንም ጋዜጠኞቹ የፓርቲው
አባል ወይም ነጻ ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ የመጣ ችግር በመሆኑ ሚዲያውንም የህዝብ
እንዳይሆን አድርጎታል ሲባልም ይደመጣል፡፡ ለመንግስት ጋዜጠኞች የሚዲያው ነፃነት ወይም
የስራ ነጻነታችን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ለዚህ ጥያቄ አጭርና አጠቃላይ መልስ እንስጥ
ካልን መልሱ የሚዲያም ሆነ የፕሬስ ነፃነትን የሚያከብርና የሚጠብቅ ሕገ መንግሥትና ሕጎች
አሉን፣ በተግባር ግን እየተደናቀፉና እየተሽመደመዱ ናቸው የሚል ይሆናል:: ነውም::

እንዴት? ለምን? ሕገ መንግሥትና ሕግ ከተግባር ጋር እንዴት አንድ ሊሆን አልቻለም?

በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 29 ላይ የሰፈረው የፕሬስ ነፃነት ይዘት ቃል በቃል የተወሰደው
የተባበሩት መንግሥታት የፕሬስ ነፃነትን አስመልክቶ ካሰፈረው ሰነድ ላይ ነው:: ዓለም ያለውን
በደፈናው እንቀበላለን ብሎ ያስቀመጠ ሕገ መንግሥት አይመስለኝም፣ በዓለም አቀፉ ሰነድ
አንቀጽ 19 ላይ የሰፈረውን ቃል በቃል በእኛ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ላይ ሰፍሯል::

ትክክልም፣ የሚያኮራም ነው:: ቁምነገሩ ግን ማስቀመጡ አይደለም አተገባበሩ ላይ ነው፡፡
አስፈፃሚው አካል የመሰለውን አዋጅና ደንብ እያወጣ ከህጎች ሁሉ የበላይ ነው የሚባለውን ህገ
መንግስት እየጣሰና እየሸራረፈ የህዝብ የተባለውን ሚዲያ የፓርቲ ልሳን የሚያደርገው ከሆነ
የህዝብን የነፃነት አንደበት ከመድፈቅ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ አይነተኛ
ማሳያ እኔ የምሰራበት የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን አደረጃጀት በቀላሉ መውሰድ
የሚቻል ነው፡፡

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የክልሉን ህዝቦች የመረጃ ጥማትና ፍላጎት ያረካል ተብሎ
ከተቋቋመበት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በዘፈቀደ አደረጃጀት ሲመራ ቆይቷል፡፡ የሚገርመው ለዚህ
ተቋም የሚቆረቆሩና ለሚዲያው ህዝባዊነት የሚጨነቁ እጅግ ብዙ ብቃትና ስም የነበራቸው ጋዜጠኞች ያለስራቸው ታርጋ እየተለጠፈባቸው ያለምንም የስራ ላይ ዋስትና እንዲፈናቀሉ
ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የኢሳት ጋዜጠኛ በመሆን በመስራት ላይ ካለው መሳይ መኮንን
ጀምሮ አሰግድ ሀምዛ፣ የወይንእሸት አስፋው፣ አወቀ አብርሀም፣ ዳንኤል ገ/እግዚአብሔር፣
ይርጋለም፣ አንተነህ ደምሰው(ፋና)፣ ጥላሁን ካሳ(ፋና)፣ ዳንኤል አድሀኖም(ፋና)፣ አብይ
ይልማ፣ አሳምሬ ሳህሉ፣ ሸዋንግዛው፣ ሙሉቀን አባይነህ፣ በሃይሉ ታደሰ፣ መቱሳላ( ያለምንም
ቅድመ ሁኔታ ከስራ ከተባረረ በኋላ ጉዳዩን ፍርድ ቤት ከሶ ከስራ ከተፈናቀለበት ጊዜ ጀምሮ
ያለው ጥቅማጥቅሙና ደሞዙ ተሰልቶ ወደ ስራው እንዲመለስ ቢፈረድለትም ሰሚ አላገኘም፡፡
ምክንያቱም አባቱ ዳኛ…ነውና፡፡ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለምን አልተፈጸመም ብሎ የሚጠይቅና
የሚያስፈጽም ሀይል የሌለበት እንዳሻው የሚፈነጭ ተቋም ነው)፡፡ ሌሎች ያልጠቀስኳቸው 21
ጋዜጠኞች የሚዲያ ተቋሙን በዚህ 9 ዓመት ውስጥ ብቻ ለቀዋል፡፡ ይህ ሲሆን ግን ማንም
ምን ሆኑ? የት ገቡ? ብሎ የጠየቀ የለም፡፡

ይልቁንም የሚዲያው የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት የደ.ኢ.ህ.ዴ.ን ስራ አስፈጻሚና ም/ል ርዕሰ
መስተዳድሩ አቶ አለማየሁ አሰፋ የፈለጉትን እንደፈለጉት በአቶ ዮሐንስ ቱሬ ፈፃሚነት
የፈነጩበት የሚዲያ ተቋም ነው፡፡ ለዚህ ነው ከላይ የሚዲያው ባለቤት ህዝብ ሳይሆን ፓርቲ
ነው ለማለት የደፈርኩት፡፡ ፓርቲው የሚመራውና የሚቆጣጠረው መሆኑ ችግር ላይኖረው
ይችል ይሆናል ነገር ግን በየጊዜው ሚዲያው አቅጣጫ የሚወስደውና የሚያስፈጽመው
ከደ.ኢ.ህ.ዴ.ን. ከፓርቲ /ከድርጅት/ ጽ/ቤት የሚሰጡ አስተሳሰቦችን መሆኑ የህዝብን መሠረታዊ
እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ወደጎን በመተው የአንድ አስተሳሰብ ብቻ ባሪያ እንዲሆኑ
የሚያደርገው ነው፡፡ በዚህም ህዝቡ ስሜትና አስተሳሰቡን የሚያስተናግድበት አንዳችም አይነት
መድረክ እንዳይኖር ማድረግ በህገ መንግስቱ የተረጋገጡለትን ከሚዲያና ከማናቸውም የመረጃ
አውታሮች የሚያገኘውን ህገ መንግስታዊ መብቱን የሚጋፋ ነው፡፡ ማንም የሚዲያ እውቀት
እና አስተሳሰብ ያለው ባለሙያ ሚዲያው ያለውን አጠቃላይ ፎርማት አይቶ ሊፈርድ ይችላል፡፡
ሀቁ አዲስ ራእይ ወይም አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋዜጣ ሆኖ ያገኘዋል፡፡

የደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ማንም እንደሚያውቀው እና እንደሚረዳው እጅግ
ብዙና ተዝቆ የማያልቅ የማህበረሰብ ነባር እውቀትና የባህል መስተጋብር የሚገኝበት አከባቢ
እንደመሆኑ መጠን በስሙ የተቋቋመለት ሚዲያ እሱንና የሱን ኢኮኖሚያዊ መሰረቶችና
ፖለቲካዊ እምነቶች ሊያንጸባርቁለት የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ይልቅ ጉልቻ እየለዋወጡ
ሚደያውን የባለስልጣኖች ገጽታ መገንቢያ እና የዝና ገበያ የሚሸምቱበት ሸቀጥ እያደረጉት
ህዝቡን የሚደልሉበት አካሄድ ማብቃት አለበት፡፡ ጋዜጠኞችም የተራ ሹም ሽረት አድማቂና
አጎብዳጅ ከመሆን መታቀቡ አዋጭነት ያለው መስሎ ይሰማኛል፡፡ እኛም ህዝብ ነን እና እንደ
ህዝብ ስሜትና አስተሳሰብ ህመሙን እየታመምን ስሜቱን ልናጸባርቅ ይገባል፡፡ በተራ አበልና
ጥቅማ ጥቅም እየተደለልን መልሰን ይህንን ምስኪን ህዝብ ግራ እያጋባን በአወዛጋቢ መረጃ
የምናደናግረው ድርጊት መቆም ቢችል ጥሩ ነው ካልሆነ ግን ብታስቡበት መልካም ነው፡፡

በዚህ ሂደት የገረመኝ ያለፈውን የ6 ወር አፈጻጸም ሊገመግም የተቀመጠው የደቡብ ክልል
ም/ቤት 4ተኛ ዙር 8ተኛ መደበኛ ጉባኤ ካጸደቃቸው ውሳኔዎች መካከል የደቡብ ብዙሀን
መገናኛ ድርጅትን እንደገና ለማቋቋም ያወጣው አዋጅ122/2006 ድርጅቱ ከዚህ በኋላ የደቡብ
ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ተብሎ እንደሚጠራ ይደነግጋል፡፡ ይሁን አዋጅና ደንብ ብርቃችን
አይደለም ግን በውስጡ ምን ይዞ ነው እንደገና ለማቋቋም ያስፈለገው? ለህዝብ አንዳች አይነት
ፋይዳ ሳይሰጥ ቀላል የማይባል ጊዜ አስቆጥሮ ሲያበቃ የ2007 ምርጫን ታሳቢ በማድረግ
እንደገና በማዋቀር የደ.ኢ.ህ.ዴ.ን/የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ/ ልሳን በማድረግ አጠናክሮ ለመምራት የታሰበ
ይመስላል፡፡
ምናልባት ይህ አዋጅ ከቀደመው የሚለየው ነገር ቢኖር በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች
ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የቦርድ ሰባሳቢነት ይመራ የነበረው የሚዲያ ተቋም አሁን በክልሉ ንግድ
ኢንዱስትሪና የከተማ ልማት ቢሮ ጠርናፊነት በም/ል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ መለሰ ዓለሙ
የገዢነት ዘመን የሚመራ ይሆናል፡፡ እንዳጠቃላይ በአገራችን የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ስርዓት
ውሥጥ ወጥነት የሌለው ቡራቡሬ አስተዳደር መኖር የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን
ለህዝብ ጥቅምና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የሚሳራ ተቋም እንዳልሆነ የሚያመላክት
ነው፡፡ በፌደራል መንግስት ደረጃ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ
የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ጽ/ቤት ሚኒስትር የሆኑት አቶ ረዱዋን ሁሴን ናቸው፡፡
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም በተመሳሳይ የአማራ መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች
ጽ/ቤት ኃላፊ የአማራ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢ ነው፡፡ በትግራይም ተመሳሳይ
ነው፡፡

እርግጥ ነው ይህ ተቋም ምንም እንኳ የድርጅት ተልዕኮ ፈጻሚ ቢሆንም ከሚዲያ ጋር
ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ በመስራቱና መረጃ አምራች በመሆኑ የየሚዲያዎቹ
የቦርድ ሰብሳቢ ቢሆን ከጉዳዩ ጋር ባላቸው ቅርበትና ትስስር ሊሆን ይችላል፡፡ ታዳያ እዚህ
አንዴ ደኢህዴን አንዴ ደግሞ የንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ እያደረጉ ከጉዳዩ ጋር
ጭራሽ ቅርበትና የስራ ዝምድና በሌላቸው አስፈጻሚ ተቋማት እንዲመራ ማድረጋቸው ለህዝብ
ሚዲያ ማሰባቸው ነው ወይስ አዛዥ ናዛዥ ስለሌለባቸው?

ኧረ በህግ አማላክ! ገዢው ፓርቲም የታገልኩለትና ዋጋ የከፈልኩለት የዜጎች የሀሳብን በነፃነት
የመግለጥ መብት ነው ብሎ ቢደነግግም ዘብ ሊቆም አልቻለም:: መንግሥት ራሱ ላወጣው
የፕሬስ ነፃነትም ሆነ ለዜጎች መረጃ የማግኘት መብት ሲጨነቅ አልታየም:: የዚህ መገለጫው
የተለያዩ አዋጆችና ደንቦች እያወጡ መዋቅራዊ አደረጃጀቶችን ማሽመድመድ ነው፡፡ የደቡብ
ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት አንዱ ማሳያ ቢሆንም የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትንም
ሌላው ማሳያ ነው፡፡

በአንድ ሀገር ለሚመዘገበው የማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ሚና ያላቸው
ዘርፈ ብዙ አውዶች እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ ከነዚህ መካከል ግን የሚዲያዎችም ድርሻ ቀላል
የሚባል አይደለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሚዲያ አውታሮች የማህበረሰቡን አመለካከትና
አስተሳሰብ በበጎም ይሁን በእኩይ መንገድ በመቅረጽ ተጽእኖ የማሰደር አቅማቸው እጅግ
ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሀግሬው ሲተርት “ጦር ከፈታው …” የሚለው፡፡
ሚዲያ የአስተሳሰብን ለውጥ በማምጣቱ ረገድ ያለው ሚና ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡
በተገቢው ከተያዘ እና በአግባቡ ከተመራ ለመሰረታዊ ለውጥ ያለው አስተዋዕፆ እንደተባለውም
ጦር ከሚፈታው በላይ አቅም ያለው ነው፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው የአንድ ፓርቲ ልሳንና
አቀንቃኝ ከሆነ በተለይም በግለሰቦች በጎ ፈቃድ ላይ ተመስርቶ የሚመራ ከሆነ ያኔ የሰማዕታቱ
አጽምና ደም መና ይቀራል፡፡ እነሆ የህዝቡን ለህዝቡ ተዉለት… አሊያ ግን ከህዝብ በላይ ህዝብ
አለና ይቀጣችኋል፡፡
ሰላም!! 

No comments:

Post a Comment