Saturday, March 8, 2014

የኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ ለዉጥ ስናስብ


ከተስፋዬ ደምመላሽ

ዲሞክራሲ በአለም ያሉ የሌሉ አገሮችንና ህዝቦችን የሚስብ፣ ሁላችን የምንፈልገዉና ብዙ የምንልለት የፖለቲካ
እሴት ነዉ። ሆኖም ዲሞክራሲ፣ ዲሞክራሲ የምንለዉን ምን ያህል በጥሞና እናስበዋለን? በአለም ዙሪያ፣ በኛም
አገር ጨምር፣ ዲሞክራሲ ሳቢነቱና ተፈላጊነቱ በትኩረት ፖለቲካዊና አገራዊ ይዘቱን እንድንፈትሸዉና
በሃሳብም በተግባርም ጠለቅ ብለን እንድንጨብጠዉ የሚያስችሉ ወይም የሚረዱ አይደሉም። ግን አንድ ዋና
ነገር ብዙዎቻችን የምናምን ይመስለኛል። ይኸዉም ዲሞክራሲ በጥቅሉ ያለዉ ረቂቅ ፍቺ ወይም ከምእራቡ
የፖለቲካ ፍልስፍና ባህልም የታሪክ ሂድትም ያካበተዉ ትርጉም በሙሉ ዉስብስብነቱና ዝርዝሩ እንደኛ ያሉ
“ሶስተኛ አለም” አገሮች ዉስጥ ሊስተጋባ ይችላል ባይባልም በመሠረቱ ወይም በመጠኑ እምቅ አግባብነት
አለዉ። ዛሬ ኢትዮጵያ የገጠመን ተግዳሮት ይህን እምቅ አግባብነት እዉን ማድረግ ነዉ።
እዚህ “እምቅ” የሚለዉ ቃል ላይ አጽንኦት የማስቀምጠዉ ሆን ብዬ ነዉ። ብዙዉን ጊዜ አስመሳይ ሳይሆን
በመርህም በተግባርም በእዉነት የሚሠራ ዲሞክራሲ በቅድሚያ የተሰጠን የፖለቲካ ህይወታችን ማደራጂያ መሣሪያ ወይም የብሔራዊ
ችግሮቻችን መፍቻ ሳይሆን ራሱ እጦታችን፣ ማዳበር ያለብን የፖለቲካ ባህል፣ በመሆኑ ነዉ። ሆኖም የአገሪቱ ምሁራንና የፖለቲካ
ሊህቃን በሚሰነዝሯቸዉ ክርክሮች ባመዛኙ ይህን ቁም ነገር ሃሳብና ትንተና ዉስጥ የማያስገቡ ብቻ ሳይሆኑ ብዙዉን ጊዜ ዲሞክራሲን
በቀጥታ እንደ አገር ችግር መወጫ የማየት አዝማሚያ ያላቸዉ ናቸዉ። ለምሳሌ ይዘቱን በመጠኑ በዢህ መጣጥፍ የማየዉ የዶ/ር
ብርሃኑ ነጋን ዲሞክራሲ አቀራረብ (ዲሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ በተባለዉ መጽሐፉ) ከዚህ አንጻር መመልከት
ይቻላል። ሰሞኑን የዩንቨርስቲዉ መምህር መሳይ ከበደ የጻፈዉም (“Democracy and Its Trade-off: Ethiopia’s Path to National
Reconciliation”) ተመሳሳይ አዝማሚያ ያለዉ ነዉ። ድረገጾች ላይ የወጣዉ የመሳይ ጽሑፍ በገዢዉ ወያኔ ወገንና በተቃዋሚ
ፓርቲዎች መካከል ሰጥቶ መቀበልና ጥቅሞች፣ ፍላጐቶችና ሥልጣን በስምምነት ማሸጋሸግ ወይም መካፈል (እነዚህ ባልተገለጸ ድፍን
እይታ ቀድሞ ያለ ወይም የተሰጠ የዲሞክራሲያዊነት ባህል መገለጫ ባህርያት ሆነዉ ተወስደዉ) እንዴት በኢትዮጵያ ብሔራዊ እርቅ
ሊያመጡ እንደሚችሉ ሊያሳይ የሚሞክር ነዉ።
ይህን ጠቅላላ የአገር ጉዳይ አቀራረብ ሆን ብለንም ባይሆን አትኩረን ባለማስተዋል ስንከተል በሃሳብና በተግባር ፊት ለፊት መግጠም
ያለብንን ጉድለቶች በጐን ማለፍ ብች ሳይሆን ይባስ ብለን ጉድለቶቹን ራሳቸዉን የችግሮቻችን ዝግጁ መፍትሔዎች አስመስለን
እናቀርባለን። እዚህ ላይ ያለንን የሃሳብ ድክመት የሚያሳይ በሌላ መጣጥፍ የጠቀስኩትን ምሳሌ መልሼ ላንሳ። በረሀብ የሚሰቃዩ
የአገራችንን ዜጐች ከርሀባቸዉ የሚያላቅቃቸዉ ምግብ ነዉ ብንል አባባላችን ምንም ያህል ትርጉም ወይም ተጨባጭ የሃሳብ ይዘት
አይኖረዉም። ረሀብተኞቹ ባሉበት ሁኔታ ምግብ ችግራቸዉ እንጂ የችግራቸዉ መፍቻ ሆኖ የቀረበላቸዉ አይደለም፣ማግኘት ያለባቸዉ
ነገር ነዉ። በማመሳሰል፣ ፕሮፌሰር መሳይ እንደሚለዉ በኢትዮጵያ ገዢዉ ወገንና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚወስዷቸዉ ሰጥቶ
የመቀበል፣ ጥቅሞች የማሸጋሸግና ሥልጣን የመካፈል እርምጃዎች ብሔራዊ እርቅ ያካተተ መንግሥት ሊፈጥሩ ይችላሉ ማለት እንደ
አገር የገጠመንን የፖለቲካ ተግዳሮት አትኩሮ ማየትና መቋቋም ሳይሆን በጐን ዙሮ ማለፍ ነዉ። ምክንያቱም እነዚህን የዲሞክራሲ ባህል
መገለጫ እርምጃዎች መዉሰዱ ራሱ ዋናዉ ችግራችን ነዉና።
ጉዳዩ እንግዲህ የዲሞክራሲ ጥቅል አለም አቀፍ ፍቺ ወይም የፖለቲካ መፍትሔነት ሳይሆን በጭብጥ ታሪካዊና አገራዊ ሁኔታዎች ያለዉ
ወይም ሊኖረዉ የሚችል እዉን ትርጉምና ተጨባጭ ሥራዓታዊ ምንነት ነዉ። በኢትዮጵያ ዛሬ የገጠመንና ሳይዉል ሳያድር መመለስ
ያለብን ጥያቄ ለአገሪቱ መላ ዜጐችና ማህበረሰቦች የሚበጅ፣ ከብሔራዊ ህልዉናችን ጋር የሚግባባ፣ አስመሳይ ሳይሆን በእዉነት
የሚሠራ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ምን ይመስላል፣ የሚቋቋመዉስ እንዴት ነዉ የሚለዉ ነዉ። ይህን መሠረታዊ ጉዳይ
በሚመለከት ባለፈዉ ሰሞን ኢትዮጵያ ነገ የሚባለዉ የኢሳት ሳተላይት ቴሌቭዝን ፕሮግራም ባቀረበዉ ዉይይት ተሳትፌ ነበር።
ዉይይቱ ያተኮረዉ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በቅርቡ ያወጣዉ መጽሐፍ ትችት ላይ ቢሆንም አግባብነት ያላቸዉ ሰፋ ያሉ የኢትዮጵያን
ዲሞክራሲያዊ ለዉጥ የሚመለከቱ ጉዳዮች በመጠኑም ቢሆን ተነስተዉ ነበር።
በመጽሐፉ ራሱና በግምገማዉ ተሳትፎዉ ደራሲዉ ለጽሑፉ የተነሳሳበትን አንድ ዋና አላማ በግልጽ አስቀምጧል። አላማዉ
“የዲሞክራሲ ሥርዓት…ምንነት ላይ የጠራ አመለካከት እንዲኖረን አስፈላጊ የሆነዉን ዉይይት ከአሁኑ እንድናደርግ ለመጋበዝ ነዉ።”
በዚህ እቅድ እስማማለሁ። ስለምንፈልገዉ ዲሞክራሲያዊ የመንግስት መርህና መዋቅር የምንጋራዉ ጥራት ያለዉ ግንዛቤ ያስፈልገናል።
ይህ አይነት ግንዛቤ እንዲኖረን ደግሞ የዉይይትና የሃሳብ ልዉዉጥ ባህላችንን ማዳበር ወሳኝ ነዉ። በአገር ጉዳዮች ላይ የምንናገረዉንና
የምንጽፈዉን ሌሎቻችን ከምንለዉ ጋር ከማገናኘት በየፊናችን አመለካከታችንን ወይም ሃሳባችንን እንደመሰለን መሰንዘር ይቀል
ይሆናል። ሌሎች የሚያቀርቧቸዉን ሃሳቦች በሚገባ ማየት ወይም ማዳመጥና ሃሳቦቹ ላይ ተቺ ጥያቄዎች በማንሳት እንዲሻሻሉ ማድረግ
በብቸኝነት ወይም በወገንተኝነት የራስን ሃሳብ ከማቅረብ ይከብዳል። ግን ይክበድ እንጂ የዉይይትና የዲሞክራሲ ባህላችንን
ተስፋዬ ደምመላሽ (ዶ/ር) 2

2

የሚያዳብርልን ይኸዉ አኪያሄድ ነዉ። ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንዲሉ የማሰብ ችሎታችንን አከማችተን፣ አስተባብረንና አትኩረን
አገር ችግሮች ላይ ማነጣጠር፣ መፍትሄዎቻቸዉንም በይበልጥ ዉጤታማነት በጋራ መፈለግና ማግኘት ያስችለናል። እኔ መቸም ሃሳቦችና
ትችቶች ለማቅረብ የምሞክረዉ በዚህ መንፈስና ተስፋ ነዉ።
እንግዲህ ዶ/ር ብርሃኑ የተነሳበትን በኢትዮጵያ የዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ሥርዓትን ምንነትና አቋቋም ግልጽ የማድረግ አላማዉን ምን
ያህል አሳክቷል? ይህን ጥያቄ እዚህ የማነሳዉ የብርሃኑን መጽሐፍ በተለይ ለመገምገም ሳይሆን በጽሑፉ ከቀረቡ አንዳንድ ሃሳቦች
ተነስቼ አግባብነት ያላቸዉን የዲሞክራሲያዊ ለዉጥ ጉዳዮችና ችግሮች ትንሽ ሰፋ አድርጌ ለመመልከት ነዉ። ሥራዓታዊ የፖለቲካ
ለዉጥ ለማምጣት የሚንቀሳቀሱ የአገሪቱ ዜጐች፣ የስቭል ህብረተሰባችን ክፍሎችና የፖለቲካ ወገኖች ስለለዉጡ ያላቸዉ ሃሳባዊና
ተግባራዊ ግንዛቤ ይበልጥ እንዲጠራ መጠነኛ አስተዋጽዎ ለማድረግ ፈልጌ ነዉ።
ብርሃኑ በአጽንኦት የሚያነሳዉ አንድ ጥያቄ አለ። ጥያቄዉ የምንፈልገዉን የመንግሥት አይነት ወይም ጥሩ የፖለቲካ ሥርዓት ምርጫ
“የሚወስነዉ ማነዉ” የሚል ነዉ። ይህን ጥያቄ አንስቶ ሲመልስ ከአብዮታዊ ልምዳችን ጋር ከተያያዘ አምባገነናዊ የፖለቲካ አስተሳሰብና
አሠራር ባህል ለመራቅ በመፈለግ እንደሆነ አረጋግጧል። በተቃዋሚና በገዢ አብዮተኛ ፓርቲዎች (በደርግና በወያኔ) የተስፋፋዉ ይህ
ብልሹ ባህል በብቸኝነት ወገንተኛ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉንም የአገርና የህዝብ ጉዳይ “እኛ እናዉቃለን፣ እኛ ብቻ እንወስናለን”
ባይነት ላይ የተማከለ መሆኑ ከማንኛችንም የተሰወረ አይደለም። ብርሃኑ ከዚህ በጥልቅ እንከናማ የሆነ የፖለቲካ ልምድ ለመራቅ ማሰቡ
ትክክልና ተገቢ ነዉ። ሆኖም ዶ/ር ብርሃኑ የሚያደርገዉ ከልምዱ የመራቅ ሙከራ ራሱ ችግር አለዉ። ችግሩ እንደ ግድግዳ ሰዓት
ተወዛዋዥ ዘንግ ከአንድ ጥግ ወደ ሌላ ጥግ ዥዉ የማለት ነገር ነዉ። ለየት ባለ አነጋገር፣ አንድን ጽንፍ በሌላ ጽንፍ የማስተካከል ወይም
የመሰረዝ ሙከራ ልንለዉ እንችላለን። ጉዳዩን ይበልጥ ዘርዘር አድርጌ ልግለጽ።
ጥሩ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ሥርዓት የመምረጥ እርምጃ የሚወሰደዉ ለህዝብ ተጠያቂ ባልሆነ ሁሉን አዋቂና ፈጻሚ ነኝ ባይ
ብቸኛ ፓርቲ ወይም ገዢ ወገን መሆኑ አንድ ጽንፍ ሲሆን፣ ብርሃኑ እንደሚያመለክተዉ የምርጫዉ ዉሳኔ የአመራርን ወገን መሠረታዊ
አቅጣጫ ሰጭነት የማይጠይቅ፣ በድፍኑ “የማህበረሰቡ” (የህዝብ፣ የአገር) ዉይይትና ስምምነት “ሂደት” ዉጤት ነዉ ማለት ደግሞ ሌላ
ጽንፍ ነዉ። የፊተኛዉን ጥለን የኋለኛዉን ስንይዝ አንድን ዋና ስህተት የምናርመዉ ወይም ለማስተካከል የምንሞክረዉ ሌላ ዋና ስህተት
በመሥራት ይሆናል ማለት ነዉ። እንደሚባለዉ ግን ሁለት ስህተቶች አንድ ትክክል ነገር አይፈጥሩም። የኢትዮጵያ ህዝብ የአገሩን
ጉዳዮችና ችግሮች ለዘለቄታዉ በደንብ ሊሄድባቸዉ በሚያስችለዉ ቋሚ የፖለቲካ መንገድ ወይም ዘዴ ላይ መወያየትና መስማማት
በእርግጥ ያስፈልገዋል። ግን በተጨማሪ ያለጥርጥር ማለት የምንችለዉ ሌላዉ ነገር ህዝቡ ይህን አስፈላጊ እርምጃ ሲወስድ ከወገንተኛ
ፖለቲካ ባሻገር ብቁ አገራዊ አመራር ይፈልጋል። እንዲያዉም የዛሬዉ የኢትዮጵያ የለዉጥ ትግል የገጠመዉ ዋና ተግዳሮት አስተዉሎና
ራዕይ ያለዉ ለህዝብ መሠረታዊ አቅጣጫ የሚሰጥ ቆራጥ የመሪ ስብስብ ማፍራት ነዉ።
በኔ ግምት ዶ/ር ብርሃኑ “ሂደት” የሚለዉ ነገር ላይ ያሰፈረዉ ያልተመጠነ ትኩረት ይህን ጽንሰሃሳብ ራሱንና በመጽሃፉ ከተካተቱት
ከሌሎቹ ቁልፍ ሃሳቦች፣ ከ“ዲሞክራሲ” እና “ፖለቲካ ሥርዓት”፣ ጋር ያለዉን ትስስር ያደናገረ ነዉ። የሚከተሉትን የብርሃኑን ክርክሮች
እንመልከት። የአገራችን ችግሮች “ማህበረሰቡ” ተወያይቶ በስምምነት የሚፈታቸዉ የዲሞክራሲያዊ “ሂደት” ጥያቄዎች ናቸዉ፣
መፍትሔዎቻቸዉም እንዲሁ የሚወሰኑ ናቸዉ። ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ራሱም የሂደት ግኝት ነዉ። ግን ደግሞ ዲሞክራሲ
የአገር ችግሮችን በዉይይትና ስምምነት መፍታት የሚያስችለን (የሂደት ዉጤት ሳይሆን ከጅምሩ አገልጋያችን የሆነ?) ጥሩ የፖለቲካ
ርብራብ ነዉ። የቱ ነዉ የቱ? ምን ቀድሞ ምን ይከተላል?
በተመሳሳይ መልክ አደናጋሪ ሆኖ ያገኘሁት የኢኮኖሚ ገዳዮችን በሚመለከት ብርሃኑ የሚለዉ ነዉ። የተለያዩ የኢኮኖሚ ጥቅሞችን፣
ፍላጐቶችንና አመለካከቶችን አቻችሎ መያዝ ወይም ችግሮቻቸዉን በነፃ ዉይይት መፍታት “ጥሩ ኢኮኖሚ ለመገንባት [ጥሩ የኢኮኖሚ
ሥርዓት በቦታዉ ስለሌለ?] ለሚደረገዉ ጥረት አስፈላጊ [እና] ወሳኝ…ነዉ” ይላል። ነፃ ዉይይቱና ልዩነቶች ማቻቻሉ “ሂደት” ሲሆኑ
ጥሩ የኢኮኖሚ ሥርዓት “ዉጤት” ይሆናል ማለት ነዉ። ግን ቆይ፣ አከራካሪ የሆኑ የኢኮኖሚ ገዳዮችና ችግሮች በዉይይት “የሚፈቱበት
መንገድ [የፖለቲካ-ኢኮኖሚ] ሥርዓት ምንነት የሚገለጥበት…ነዉ” ደግሞ ይላል። እዚህ ሥርዓት የዉይይትና ስምምነት ዉጤት
አይደለም፣ የተገላቢጦ መፍትሔ ሰጪ ዉይይት የሥርዓት ገጽታ ወይም ባህሪ ሆኖ የሚታይ ነዉ።
እንደሚመስለኝ የክርክሩ መደናገር ዋና ምንጭ ዶ/ር ብርሃኑ ጥሩ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓትን የወደፊት መዳረሻችን አድርጐ
ሲያይ ዛሬ ከየት እንደምንነሳና የትግል አኪያሄዳችን ምን እንደሚመስል እትንተናዉ ዉስጥ ከማስገባት ሆን ብሎ መቆጠቡ ነዉ።
ብርሃኑ “ሂደት” ላይ ያን ያህል አጽንኦት ሲያስቀምጥ ጥሩ የተባለዉን የፖለቲካ ሥርዓት ከትግል አኪያሄድ ጋር ያልተገናኘ መዳረሻ
አድርጐ ማየቱ ምጸታዊ (ironic) ነዉ። እንደ አገር የወደፊት እጣ ፈንታችንን ለመቅረጽና አኪያሄዳችንን የተሳካ ለማድረግ መነሻችን፣
ዛሬ ያለንብት አኳኋን፣ ወሳኝ ነዉ። አኳኋናችን በአሉታዊ ጐኑ መቋቋም ያለብንን ችግሮችና ተግዳሮቶች፣ በትግሉ መለወጥና ማሻሻል
ያለብንን ሁኔታዎች ያካተተ ነዉ። በአወንታዊ ጐኑ ደግሞ ብሔራዊ ህልዉናችንን፣ ተስፋችንንና ምኞታችንን፣ እንዲሁም እንደ አገር
ያሉንን እዉንም እምቅም የለዉጥና መሻሻል አቅሞች፣ ችሎታዎችና ሃይሎች አጠቃሎ የያዘ ነዉ። 3

3

የዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ሥርዓት ምንነት
ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ምን ይመስላል? ከአልባሌ አምባገነናዊ አገዛዝ (ለምሳሌ ከወያኔዉ) በምን ይለያል? በኢትዮጵያ
የዲሞክራሲያዊ ለዉጥ አስፈላጊነት በዜጐች፣ በስቭል ህብረተሰቡ ስብስቦችና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ተደጋግሞ የተረጋገጠ ቢሆንም
እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ የሃሳብ ልዉዉጥና ስምምነት አፍሪ ዉይይቶች በአገሪቱ የፖለቲካ መደብ ዉስጥም ሆነ በምሁራን
አካባቢዎች በቀጣይነት ምንም ያህል አልተኪያሄዱም። በዚህ ምክንያት የዛሬዉ የለዉጥ ትግል ከባድ የሃሳብና የስልት ጥራት ኪሳራ
ገጥሞታል። ኪሳራዉ ወይም ጉድለቱ በአንዳንድ ረድፎች ይበልጥ ተነሻሽ እየሆነና እያደገ የመጣዉ የተቃዉሞዉ ትግል የቆየበትን
ጥቅል ደካማነት የሚያንጸባርቅ ነዉ።

እንቅስቃሴያቸዉ ረባመ አልረባም ቁጥር ስፍር የሌላቸዉ ተቃዋሚ የተባሉ ወገኖች (አንዳንዶቹ በማንነት ፖለቲካቸዉ ከወያኔ ዞር ያሉ
እንጂ ያልራቁ፣ ብዙዎቹ የስም ብቻ ህልዉና ያላቸዉ) ላይ ታች ሲሉ ቆይተዋል። የስደተኛ ኢትዮጵያዊያን ተቃዋሚ ሚዲያና ፓልቶክ
እንቅስቃሴዎች እጥረት የለም። ነገር ግን አገር ቤትም ከአገር ዉጪም ያለዉ ተቃዉሞ በጠቅላላ ይህ ነዉ የሚባል ብሔራዊና ስልታዊ
አስኳል የለዉም። ተቃዉሞዉ በፖለቲካ ሃሳብም ሆነ በተግባራዊ ትግል “የስበት መአከል” ያልፈጠረ፣ በአመዛኙ የብዙ ወገኖችና
እንቅስቃሴዎች ጥርቅም ከሆነ ይኸዉ ሩብ ምእተ አመት ሊያስቆጥር ነዉ። ሃቀኝነት ያለዉ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓትን ከተራ፣
ራሱን ዲሞክራሲያዊና ፌደራላዊ አስመሳይ፣ ጐሰኛ አምባገነናዊ አገዛዝ በሃሳብም በተግባርም በጥራት ለይቶ መገንዘብና የኢትዮጵያን
ህዝብ ማስገንዘብ ያልተቻለዉ በከፊል በዚህ ሰፊ የተቃዉሞ ሁኔታ ነዉ።
ቋሚ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት (political system) ከተለዋጭ፣ በተወሰነ ፓርቲ የሚመራ፣ መስተዳደር ወይም አገዛዝ
(government; regime) እንደሚለይ የአሜሪካን ምሳሌ በመጥቀስ ዶ/ር ብርሃኑ በመጽሐፉ በንድፈሃሳብ ደረጃ አመልክቷል። በምርጫ
ዉድድር አሸናፊነት መንግሥት ሆነዉ በፖሊሲ አዉጭነትና ሥራ አስፈጻሚነት ለተወሰነ የሥልጣን ዘመን የሚቆዩና የመንግስት
ሥልጣን የሚቀባበሉ ፓርቲዎች ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ። ጠቅላላ አገራዊ የፖለቲካ ሥርዓቱ ግን በቋሚነት (በየጊዜዉ አሻሻይ ለዉጦች
ቢደረጉለትም) ለዘመናት ይኖራል። ሥርዓቱን ቋሚና ለዘለቄታዉ የተረጋጋ የሚያደርገዉ ያካተታቸዉ መሥራች መርሆች (ለምሳሌ
ሥልጣንን በተለያዩ አንጻራዊ ነፃነት ያላቸዉ ፌደራላዊና አካባቢያዊ የመንግሥት አካላት አከፋፍሎም አስተባብሮም የመደልደል መርህ)
እና ተቋማት ናቸዉ። ቁም ነገሩ መሥራች መርሆቹና ተቋማቱ በአገር ደረጃ የፖለቲካዉን መደብ፣ የምሁራንንና የሌሎች ሊሂቃንን
ስምምነት ከሞላ ጐደል ያገኙ፣ በህብረተሰቡም በኩል እንዲሁ በሰፊዉ ተፈላጊነትና ተቀባይነት ያላቸዉ ናቸዉ። ባጭሩ የፖለቲካ
ሥርዓት የተለያዩ ፓርቲዎችና ስብስቦች ለሚያደርጉት የሥልጣን ዉድድርና አያያዝ በጥቅሉ ሚዛናዊ ሆነዉ የሚታዩ የፖለቲካዉን
ጨዋታ ደንቦች የሚዘረጋና የተለዋዋጭ ወገኖችን የስልጣን ቅብብሎሽ ህጋዊነትና ተገቢነት የሚያረጋግጥ፣ በአንጻሩ ራሱን የቻለ፣
የመርሆችና ተቋማት ርብራብ ወይም መዋቅር ነዉ።
እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ። “ሥርዓት” የሚለዉ ቃል በተለምዶ የፖለቲካ አነጋገር እቅጭና ጥብቅ ፍቺ ያልያዘ
ዝውውር ቢኖረዉም የዲሞክራሲያዊ መንግስትን መዋቅር ከተራ የአምባገነናዊ አገዛዝ ቅርጽ ስንለይ ቃሉን የምንጠቀመዉ በተለመደዉ
ልል ፍችዉ ሳይሆን ይህንኑ ልዩነት በሚግልጽ ጠበቅ ያለ ጽንሰሃሳባዊ ትርጉሙ ነዉ። ይህ አነስተኛ መሳይ ጉዳይ ዲሞክራሲያዊ
መንግሥትን በሚመለከት የምንፈልገዉን የጠራ ሃሳባዊና ተግባራዊ ግንዛቤ ማግኘት አለማግኘታችንን ወሳኝ ነዉ። በኔ ግምት ጉዳዩ
ዶ/ር ብርሃኑ የተነሳበትን ለዛሬዉ የዲሞክራሲያዊ ለዉጥ ትግል የሃሳብና ያመለካከት ጥራት መስጠት ግብ መምታት እንዴት
እንዳጓደለም የሚያሳይ ይመስለኛል።
በንድፈሃሳብ እይታ ብርሃኑ የአሜሪካን ምሳሌ ጠቅሶ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓትን ከአልባሌ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ቢለይም
የኢትዮጵያን ታሪካዊና ጊዜያዊ ሁኔታ ሲተነትን እይታዉን በቅጡ አልተጠቀመም። በንድፈሃሳቡ “ሥርዓት” እንደ ፈርጅ የያዘዉን ለየት
ያለ ትርጉም ችላ ብሎ ወይም እንደነገሩ አይቶ (በመዘንጋትም ሆነ አትኩሮ ባለማሰብ) ለፈርጁ የሰጠዉ የተለመደዉን ጠቅላላ የቃል
ፍቺ ነዉ። በዚህ አቀራረብ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሶስት የተለያዩ “የፖለቲካ ሥርዓቶች” (ፍጹም የዘዉድ ሥርዓትና አምባገነናዊ የደርግና
የወያኔ ሥርዓቶች) ተከታትለዋል ይላል። ይህ አባባል በዘወትር ንግግር ችግር የሌለዉ ቢሆንም የዲሞክራሲያዊ መንግሥትን መዋቅራዊ
ምንነት ወይም ቅርጽ ከለመድነዉ አምባገነናዊ አገዛዝ በጽንሰሃሳባዊ ጥራት መለየት አያስችለንም።
ጉዳዩን እትዮጵያ ነገ የሚባለዉ የኢሳት ፕሮግራም በአቀረበዉ ዉይይት አንስቼዉ ዶ/ር ብርሃኑ የተረዳዉ ቢሆንም አቃሎ የቋንቋ
አጠቃቀም ችግር አድረጐ ከማየቱ ባሻገር ፍጹም ዘውዳዊ መንግሥት የራሱ ተቋማት ያላጣ ቋሚ “ሥርዓት” ነበር የሚል መልስ ነዉ
የሰጠዉ። ይህ መልስ የዲሞክራሲያዊ መንግስትን ሥርዓታዊ ምንነት ወይም ህልዉና በሚመለከት “የፈርጅ ስህተት” (category error)
ስለሚሠራ “ፖለቲካ ሥርዓት” የሚለዉን ሃረግ አጠቃቀም በሚመለከት ከመደናገር የሚያወጣን አይደለም።
ነገሩ እንዲህ ነዉ። የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት “የራሱ” ተቋማት (ለምሳሌ ምክር ቤትና የሚንስትሮች ካቢኔ) ይዞ የነበረዉ በደርግና
በወያኔ አይን ያወጣ “አበዮታዊ” ፈላጭ ቆራጭነት መልክና መጠን ባይሆንም የፍጹም ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዙ ተቀጥላና ቀጥታ ታዛዥ
በማድረግ እንጂ ተቋማቱ አንጻራዊ ነፃነት ያለዉ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት አካላት እንዲሆኑ ፈቅዶ፣ የራሱ ሃይል ላይ እዉን 4

4

ህገመንግሥታዊ ገደብ አስቀምጦ አልነበረም። ቋሚነት ወይም ቀጣይነት ደግሞ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አሰፈላጊ እንጂ በቂ ገጽታ
አይደለም። አምባገነናዊ አገዛዝ ለረጅም ዘመን ቀጣይ ሊሆን ይችላል። የዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ሥርዓት ዋና መለያዉ ጠቅላላ
የመንግሥት ተቋማትና ሥልጣን በአንድ አምባገነናዊ ወገን ወይም ግለሰብ ቁጥጥር ሥር የሚወድቁ ሳይሆኑ በራሳቸዉ እግር የቆሙና
የራሳቸዉ መዋቅራዊ ተጽእኖ ያላቸዉ መሆኑ ነዉ። እዚህ የምንፈልገዉ የአመለካከት ጥራት እንግዲህ ሁለት ረድፍ አለዉ። በአንድ
በኩል በንድፈሃሳብ ደረጃ የፖለቲካ ሥርዓት ስንል “ምን ማለታችን ነዉ” የሚለዉ የትርጉም ግልጽነት ጉዳይ ነዉ። በሌላ በኩል ደግሞ
ንድፈሃሳባዊ አባባላችን ለይቶ የሚጠቁመዉ፣ የሚመለከተዉና የሚገልጸዉ፣ ተጨባጭ የፖለቲካ እዉነታ ወይም የመንግሥት አይነትና
ባህሪ ነዉ።
የዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ሥርዓት አቋቋም
አብዛኛዉን ጊዜ ቋሚ የሆነ ዲሞክራሲያዊ የመንግሥት መዋቅር በሃሳብ፣ በመርህና በተቋማት ቅርጽ የሚይዘዉ ሰብአዊነት የሌለዉ፣
በጥቅሉ “የማህበረሰቡ” ውይይትና ስምምነት ቀጥታ ዉጤት ሆኖ ሳይሆን በአመዛኙ በተወሰነ አመራር ስብስብ አድራጊ ፈጣሪነትና
መሥራችነት ነዉ። የመሪ ስብስቡ ድርጊት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ቢቀርጽም ቀራጭ ድርጊቱ ራሱ በሰፊዉ ዲሞክራሲያዊ ነዉ
የሚባል አይደለም። የአመራሩ አቅጣጫ ሰጪ ተነሳሽነትና እንቅስቃሴዎች የብዙሃን ህብረተሰብ ክፍሎች ውይይትና ስምምነት ቅርብ
ዉጤቶች ናቸዉ ልንላቸዉ አንችልም።
ለምሳሌ ብዙ የሚባልለትን የአሜሪካ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት አመሠራረት እንዉሰድ። “የመሥራች አባቶቹ” ስብስብ እርስ
በርስ የተመራረጡ ከበርቴ ነጭ ወንዶችንና ምሁራንን ብቻ ያካተተ ነበር። የሥርዓቱ ነዳፊዎች በሰዉ ልጅ “እኩልነት” እምነታቸዉን
በንድፈሃሳባቸዉ ቢያረጋግጡም በጊዜያቸዉ የነበረዉን የጥቁሮች በባርነት መገዛት የተቀበሉ፣ በቀጥታ የባርነት አገዛዙ ተጠቃሚ ሰዎች
ነበሩ። ለነጮች ሴቶችም የሙሉ ዜግነት (የስቭልና የፖለቲካ) መብቶች ነፍገዋል። ይሁን እንጂ ሥርዓቱን የመሠረቱበት የፖለቲካ ሃሳብ
ራሱ እነሱ ከሰጡት የተወሰነ አተረጓጐምም አፈጻጸምም ያለፈና የላቀ እምቅ ተራማጅ ይዘት ነበረዉ። ስለዚህ ሥርዓቱ በታሪክ ሂደት
ጭቁን የአሜሪካ ህብረተሰብ ክፍሎች፣ በተለይ ጥቁሮችና ነጭ ሴቶች፣ በስቭል መብቶች ትግል ያሳረፉበትን ተጽእኖ በተለማጭነት
ከሞላ ጐደል በማስተናገድ ራሱን ማሻሻል፣ ይበልጥ ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ችሏል።
በዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ምሥረታ አቅጣጫ ሰጪ ወገኖች ላይ ሳተኩር ኢዲሞክራሲያዊ ስብስባቸዉን አቃልዬ በማየት፣
መሃበረሰቦችን ከመወከል አኳያ ሰብስባቸዉ የሚያሳየዉን ጉድለትና ዉስንነት ከምንም ባለመቁጠር አይደለም። በኢትዮጵያዉ
ዲሞክራሲያዊ ለዉጥ እንቅስቃሴ “መሥራች አባቶች” (“እናቶችም” ጭምር) በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ህዝቡን በሰፊዉ ቢወክሉ
ይመረጣል። ማድረግ የፈለኩት በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታ ተብላልተዉ የሚቀርቡ ጉዳዮች፣ ሃሳቦችና አላማዎች
ከአቅራቢዎቻቸዉ ማንነት ወይም ምንነት ይበልጥ ክብደትና ዋጋ ያላቸዉ መሆኑን ለማስገንዘብ ነዉ። ቁም ነገሩ ዲሞክራሲያዊ
መሥራች ሃሳቦችንና መርሆችን ማን (የቱ ጐሰኛ ስብስብ ወይም ወገንተኛ ቡድን) ያቀርባል ሳይሆን የሚቀርቡት ሃሳቦች ጥራት፣ ስፋትና
ጥልቀት፣ በዚህ ሁኔታቸዉም ከአገሪቱ ዜጐችና ማህበረሰቦች የጋራ ጥቅሞችና ምኞቶች ጋር ያላቸዉ ግንኙነት ነዉ።
ከዚህ አንጻር ሲታዩ በኢትዮጵያ የዘር ብሔርተኝነት ከሚከተሉ ግንባሮችና ወገኖች ጋር የተያያዙ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ አነጋገርና
አኪያሄድ መንገዶች ለአገሪቱ የዲሞክራሲ ለዉጥና ግንባታ እቅድ ሁለት የተያያዙ መሠረታዊ ችግሮች አሏቸዉ። አንደኛ፣ ከዘር ፖለቲካ
ባሻገር ያለን ወይም ሊኖረን የሚችል ለዲሞክራሲ መርሆች፣ እሴቶችና ደንቦች ሰፊ ቃል ኪዳን በተጣበቡ፣ ከአገር ህልውና አኳያ እዚህ
ግቡ በማይባሉ፣ የጐሳ ማንነትና “ራስን በራስ ወሳኝነት” በተባሉ በሃሳብ ያልተብላሉ ቀኖናዊ አቋሞች መመንዘር ነዉ። በዚህ ውስን
ሁኔታ የተለያዩ ወገኖች የሚሏቸዉ ነገሮች ልዩነትንና ማንነትን በብቸኛና አምባገነናዊ መንፈስ የሚያውጁ ወይም የሚያረጋግጡ እንጂ
በሰፊዉ የዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ሥርዓትን ሃሳቦችና እሴቶች በአገር ደረጃ ምንም ያህል የሚቀርጹ ወይም ሊቀርጹ የሚሞክሩ
አይደሉም።
ሁለተኛ፣ ጐሰኛ ግንባሮች በአንድ በኩል “ብሔራዊ ራስ ዉሰናን” ከተራ ዘረኝነት ጋር በተደባለቀ ርእዩተአለማዊና ድርጅታዊ አገባብ
በብቸኝነት ለማከናወን ሲጥሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የግንባሮቹ ፖለቲካ ትረካ ሆን ተብለዉ የአገር ህልዉናን ተቃርነዉ ወይም ርቀዉ
በወገንተኝነት የተቀረጹ ማንነቶችን በተፈጥሮ የተሰጡ ወይም በቀጥታ የታሪክ ሂደት የተገኙ ህዝባዊ እዉነታ ያስመስላል። በሁለቱም
በኩል የማንነት ፖለቲካ የዘውግ፣ የቋንቋና የባህል ብዙሃንነት ያላቸዉ፣ ግን የተሳሰሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች በነፃነት ሊሳተፉባቸዉ
ከሚችሉ አገራዊም አካባቢያዊም የዲሞክራሲ መርሆችና ሂደቶች ያርቃል። እነዚህ ሁለት የተያያዙ የአገሪቱ ችግሮች ዲሞክራሲያዊ
የፖለቲካ ሥርዓት በአቋቋምና በእድገት የሚወጣቸዉ ጣጣዎች ናቸዉ።
ሥርዓቱ ራሱን ችሎ የሚቋቋመዉና የሚጠናከረዉ ለዜጐችና ለልዩ ልዩ ማህበረሰቦች ማንነቶች፣ ጥቅሞች፣ ፍላጐቶችና ጥያቄዎች
በቀጥታ በሚሰጠዉ ውክልና አይደለም። ይልቅስ እነዚህን ሰፋ ባሉ የሰብአዊነት፣ የዜግነትና የፖለቲካ መብቶችና ግዴታዎች ሸምግሎ፣
አሸጋሽጐና አጠቃሎ ህብረተሰባዊ ህግና ደንብ ሲፈጥር፣ በዚህ አኪያሄዱም የራሱን ሥርዓታዊ ህልውና ብቻ ሳይሆን በህዝብ ዘንድ
ተገቢነቱና ተቀባይነቱን ሲያረጋግጥ ነዉ። የዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ሥርዓት ፍቱንነትና ተሰሚነት የሚታየዉ በሁለት እርከን ነዉ። 5

5

በአንደኛ ደረጃ ዜጐች፣ የስቭል ህብረተሰብ ስብስቦችና የፖለቲካ ወገኖች በድርጊቶቻቸዉና በእንቅስቃሴዎቻቸዉ ተግባራዊ ወይም
ተፈጻሚ ሲያደርጉት፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሥርዓቱ በሰፊዉ የጋራ ፖለቲካዊና ብሔራዊ ህይወታችን ርብራብ ሆኖ ራሱን እያደሰና
እያሻሻለ በቀጣይነት ሲጠብቅ ነዉ።
የዲሞክራሲያዊ ለዉጡ የአገር ባለቤትነት
ለአርባ አመት ያህል በአብዮታዊነት የተፈረጁ ዲሞክራሲያዊ የተባሉ የፖለቲካ አስተሳሰባና አገዛዝ ለዉጦች በኢትዮጵያ ተኪያሂደዋል።
የነዚህ ለዉጦች መሠረታዊ ችግር ሃቅኛ፣ እዉን ዲሞክራሲያዊ ይዘት ወይም ትርጉም ያልነበራቸዉና የሌላቸዉ መሆናቸዉ ብቻ
አይደለም። ሆን ተብለዉም ሆነ አልሆነ በአመዛኙ ብሔራዊ ህልዉናችንን፣ የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነት፣ የራቁና የተቀናቀኑ ነበሩ፣
ናቸዉም። ለዉጦቹ ኢትዮጵያ ዉስጥ ተኪያሄዱ እንጂ የኢትዮጵያ የራሷ ለዉጦች ነበሩ ማለት ያዳግታል። እንዲያዉም፣ የወያኔ አገዛዝ
እንዳሳየን፣ የኢትዮጵያ አንድነት ደመኛ ሆነዋል። ስለዚህ የዛሬዉ ዲሞክራሲያዊ ለዉጥ የአገርና ህዝብ ባለቤትነት ገዳይ በሚገባ
ልናነሳዉና ልንገነዘበዉ የሚያስፈልገን ነገር ነዉ። ጉዳዩን ችላ ብለን በረቂቁ ዲሞክራሲ፣ ዲሞክራሲ ብንል (በአለፈዉ ዘመን ሶሻልዝም፣
ሶሻልዝም እንዳልነዉ) ራሳችንን ለታሪክ ስህተት ደጋሚነት ማጋለጥ ነዉ የሚሆነዉ።
ከዚህ አንጻር ዲሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ ያቀረበዉ አመለካከት ላይ የአገራዊ ባለቤትነቱን ጥያቄ ማንሳቱ ትምህርት
ሰጪ ይመስለኛል። አመለካከቱ አሉታዊም አወንታዊም ምሳሌ ሊሆነን ይችላል። ማለትም፣ ምን ማድረግ እንደሌለብንና እንዳለብን
የሚያሳየን ይሆናል። የባለቤትነቱን ጉዳይ በጠቅላላ ከመቃኘቴ በፊት ጽሑፉ የጥሩ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሥርዓት መመዘኛ መስፍርቶች
በረቂቁ ማስቀመጡ ራሱ ከዛሬዉ የለዉጥ ትግል አኳያ በእምቁ ያለዉን ጠቃሚና ጐጂ ጐን ልጠቁም።
በረጂ ጐኑ የመስፍርቶቹ አቀራረብ ተመኔታዊ ወይም በንጹሁ ሃሳባዊ መሆኑ በሁለት ረድፍ ትግሉን ይጠቅም ይሆናል። በአንድ በኩል
መስፍርቶቹ የወያኔን ዘረኛ ገዢ “ዲሞክራሲ” (አብዮታዊም ተባለ ልማታዊ) ከሥር እስከ ቅርንጫፉ በአርአያነት መመዘኛ፣
መገምገሚያና ማስወገጃ መሣሪያ ሆኖዉ ሊያገለግሉ ይችላሉ፣ ምንም እንኳን ደራሲዉ “ርእዩተአለማዊ ክርክር ዉስጥ አልገባም” ብሎ
ለዚህ አይነት ጥቅም ሊያዉላቸዉ ባይፈልግም። በሌላ በኩል የመስፍርቶቹ ጥቅልነት በተለያዩ የትግሉ ተሳታፊ ወገኖች መካከል
አለመስማማትን ቀንሶ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መግባባትን ይጨምር ይሆናል። ለምሳሌ አንድ ወገን በድፍኑ “ፍትሃዊነት” የጥሩ
መንግሥት ገጽታና ባህሪ ነዉ ቢል ከሌሎች ወገኖች ምንም ያህል እሰጥ አገባ አይገጥመዉም። ስለ ፍትህ ይዘት ወይም አስተዳደር
የኢትዮጵያ ዜጐችና ወገኖች ሊከራከሩ ይችላሉ፣ ፍትሃዊነት ራሱ ወይም በጥቅሉ ግን የሚያስማማቸዉ እንጂ የሚያጣላቸዉ አይደለም።
ይህ ነጥብ በብዙ የአገሪቱ ወገኖች ዘንድ በጥቅሉ ተፈላጊ ለሆኑ ሌሎች እሴቶች፣ እንበል “ነፃነት”፣ “ዲሞክራሲ” እና “እኩልነት”፣ እንዲሁ
አግባብነት አለዉ።
ይሁን እንጂ የጥሩ ፖለቲካ ሥርዓት መመዘኛ መስፍርቶቹ አቀራረብ የዛሬዉን የለዉጥ ትግል ሊጐዳ ወይም ሊያደናቅፍ የሚችል ጐንም
አለዉ። የመስፍርቶቹ ረቂቅነት፣ አየር ላይ መንጠልጠል፣ ከተጨባጭ ትርጉም የለሽነት ጋር የሚያያዝ ነዉ። የተወዳዳሪና ተቀናቃኝ
ወገኖችን ራስን አገልጋይ “እዉን” ፍቺ ሰጭነት የሚጋብዝ አጉል ክፍትነት ወይም ተለማጭነት አለዉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ ዲሞክራሲያዊ
የፖለቲካ ሥርዓት ገንቢና አራማጅና ሳይሆን ከጅምሩ አፍራሽና አሰናካይ ነዉ። የሚያረጋግጥልን ነገር ቢኖር በሥርዓት ማቋቋሙና
ግንባታዉ እንቅስቃሴ ዋናዉ የአመራር ሥራ ሃሳቦችን በረቂቁ ማስፈር አይደለም። በጥቅሉ ዲሞክራሲን፣ ነፃነትንና ፍትሃዊነትን የጥሩ
ፖለቲካ ሥርዓት መስፍርት ማድረግ ምንም ያህል ምሁራዊና ፖለቲካዊ “ክብደት ማንሳት” የሚጠይቅ አይመስለኝም። ዋናዉና ከባዱ
የአቅጣጫ ሰጪነት ሥራ እነዚህን ሃሳቦች በአፈጻጸማቸዉ ብቻ ሳይሆን ከጽንሳቸዉ ወይም በንድፋቸዉ ከህዝብና ከአገር ትግል ጋር
በማገናኘት ተንቀሳቃሽም አንቀሳቃሽም ሃይል ማድረግ ነዉ። በሌላ አባባል፣ ሃሳቦቹ ህያዉ ቅርጽና ትርጉም የሚይዙበትን መንገድ
ማሳየት ወይም መቀየስ ነዉ።
ከነዚህ ጉዳዮችና ችግሮች ባሻገር የዲሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ የጥሩ ፖለቲካ ሥርዓት ተመኔታዊ መስፍርቶች
አቀራረብ በኢትዮጵያ አገባቡ ጠቅላላ እንከን አለዉ። በኔ ግምት ችግሩ አብዮታዊ ልምዳችን ያስያዘን የዉስጥ ፖለቲካ አባዜ ዉጨኛ
ምልክት ወይም መገለጫ ነዉ። አባዜዉ አገርንና ህዝብን በአንድነት የመሠረታዊ ፖለቲካ ለዉጥ ትግል ባለቤት ያለማድረግ በሽታ ነዉ።
ከልምዱ የመነጨዉና ዛሬም በገዢዉ “የትግሬ ህዝብ ነጻ አዉጪ” ፓርቲ ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚዉ ሰፈር በሚገኙ አንዳንድ ወገኖችና
አካባቢዎች መካከል የሚታየዉ የፖለቲካ አስተሳሰብ ኢትዮጵያን የሚያየዉና ሊለዉጥ የሚሞክረዉ እጋራ ብሔራዊ ህይወታችን ላይ
ተመሥርቶ፣ አገራዊ ተንቀሳቃሽነታችንንና አድራጊ ፈጣሪነታችንን ተቀብሎና አረጋግጦ አይደለም። በአመዛኙ በቀጥታ ከዉጭ ሰርጐ
ከገባ፣ የማንነት ፖለቲካን ያማከለ፣ ረቂቅ ርእዩተ አለም ተነስቶ፣ በይበልጥ ጽንፈኛ አቀራረቡም ብሔራዊ ህልዉናችንንና ባህላችንን
በጅምላ እንደ ችግር አይቶ ነዉ። አስተሳሰቡ በብዙዎቻችን የአብዮቱ ትውልድ አባላት ከሞላ ጐደል ተንጸባርቋል።
በተወሰነ መጠንና ደረጃም ቢሆን ዲሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ የዚህን ፖለቲካ አስተሳሰብ ፈለግ ይከተላል፣ እንከናማ
አብዮታዊ ልምዳችንን ያስተጋባል። ከምእራቡ ከተገኙ ጥቅልና ረቂቅ “የጥሩ ፖለቲካ-ኢኮኖሚ ሥርዓት” መመዘኛ መስፍርቶች በቀጥታ
ሲነሳና አገሪቱ እነዚህን ከዉጭ ተቀርጸዉ የቀረቡ መስፍርቶች “ያለማሟላቷ” ገዳይ ላይ ሲያተኩር አስልቶም ባይሆን በድርጊት 6

6

ልምዱን እየተከተለ ይመስለኛል። ኢትዮጵያን ከአለችበት አሰከፊና አስጊ ሁኔታ መዉጣት የሚያስችሏት የራሷ አቅሞች፣ ችሎታዎችና
ፀጋዎች ምንም ያህል የሌሏት፣ የችግሮቿ ድምር ብቻ የሆነች አገር አድርጐና በዉጭ የፖለቲካ ሃሳቦችና መፍትሔዎች ተቀባይነት ወስኖ
ሲመስል፣ ሆን ብሎም ባይሆን በዉጤት ይህንኑ ጠቅላላ ልምድ እያስተጋባ ነዉ። ኢትዮጵያ እንደ አገር የራሷ ዲሞክራሲያዊ ለዉጥ
ባለቤት ወይም አድራጊ ፈጣሪ የምትሆንበትን አኪያሄድ በሚገባ ባለመመልከት ወይም ባለመፈተሽ ነዉ።
ለማጠቃለል፣ በኢትዮጵያ ለመላ ዜጐች የሚበጅ እዉን ዲሞክራሲያዊ ለዉጥ ለማምጣት ስናስብ የተወሰኑ የአገር ታሪካዊ፣
ህብረተሰባዊና ባህላዊ ሁኔታዎች ዉስጥ ሆነን ነዉ። ሃሳባችን በቅድሚያ ዝግጁ ሆኖ የሚፈልቅበት የዉጭ ርእዩተ አለማዊ ምንጭ
ወይም የሚቀረጽበት ንጹህ ዉስጣዊ ፅላት የለዉም። በወደፊት አኪያሄዳችን መግጠም ያለብን ዋና ተግዳሮት እንግዲህ ዛሬ በአገራችን
ሥርዓታዊና ተፈጻሚ ማድረግ የምንፈልገዉን የዲሞክራሲ ፖለቲካ ሃሳብ በታሪክ ዝግመት ከዳበረ ብሔራዊ ህልዉናችን ጋር ማጣላት
ሳይሆን ማስታረቅ፣ ማራራቅ ሳይሆን ማቀራረብ ነዉ። አንዱን ጥሎ ሌላዉን መያዝ የሚባል ነገር የለም።
ይህን የግጥሚያ ጥሪ በብቃት ለመመለስ ይረዳሉ የምላቸዉን ሁለት ነጥቦች ባጭሩ በማስገንዘብ ውይይቱን ልዝጋ። አንደኛ፣ ተጋርተን
የምንኖረዉ ተጨባጭ ብሔራዊ ህይወታችን የፖለቲካ ንቃተ ህሊናችን፣ የዲሞክራሲያዊ ለዉጥ እንቅስቃሴያችን፣ መሠረትና መነሻ
ነዉ። ከረቂቅ ርእዩተ አለም ወይም ከጐሰኛ ብሔርተኝነት ተነስቶ ወደ እዉን አገራዊ ህልውና መግባት አይቻልም። የነፃነት፣ የፍትህና
የዲሞክራሲ ሃሳቦች ስናስብ የነገድ፣ የባህልና የቋንቋ ብዙሃንነትን ካካተተ የጋራ ብሔራዊነታችን ተነስተን ነዉ። ይህ አነሳሳችን ራሱ
ንድፈሃሳባዊ አይደለም፣ ሊሆንም አይችልም። በመሠረቱ የምናስበዉ ሳይሆን የሆንነዉ ነዉ። እንደ አገር የኑሯዊ ሁኔታችን ገጽታ፣
የብሔራዊ ህልዉናችን መገለጫ ነዉ።
ሁለተኛ፣ የዲሞክራሲ ጥቅልና ረቂቅ “ጥሩነት” ወይም ንድፈሃሳባዊ ትክክለኛነት በኢትዮጵያ ዜጐችና ማህበረሰቦች ዘንድ የሞራል ግዴታ
ይሆናል ወይም በቀጥታ የእምነትና የባህል ተገቢነት ያገኛል ማለት አይደለም። ዲሞክራሲ ጥሩ የፖለቲካ ሃሳብ ወይም ስነአመክንዮ
ቢያካትትም ይህ ሁኔታዉ ራሱ በብዙሃን ህዝብ ዘንድ እንደ እሴት ተፈላጊነቱንም ሆነ አገራዊ አገባቡን ወሳኝ አያደርገዉም። ስለዚህ
በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ለዉጥና ግንባታ በፖለቲካ አስተሳሰብና ድርጊቶች አለም ዉስጥ ብቻ የሚኪያሄዱ አይደሉም። በተለያዩ
መስኮች፣ ሁኔታዎች፣ ደረጃዎችና መንገዶች በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በቀጥታም በተዘዋዋሪም የሚከናወኑ ናቸዉ።
Email: tdemmellash@comcast.net




ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
March 7, 2014






No comments:

Post a Comment