ከባለሥልጣናት ጋር ለሳምንት ቤት እንቀያየር
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚያዊ ግስጋሴዋ ተስፋ ከሚታይባቸው አገሮች መካከል ናት፡፡ የአገሪቷ ጅምር ዕድገትን እንደ ዓለም ባንክ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ የሚመሰክሩት ነው፡፡
በአገሪቷ የሚካሄዱት በርካታ እንቅስቃሴዎችም በዕድገት ጐዳና ላይ መሆኗን ያመላክታሉ፡፡ ይህ የዕድገት ጐዳና ሁሉንም ዜጋ የሚያስደስት መሆኑም አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን ይህ ጐዳና ለእያንዳንዱ ዜጋ ሊያስገኘው የሚገባው ጥቅም ደግሞ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የአገሪቱ ዕድገት ይቀጥል ተብሎ የሚበረታታው እያንዳንዱ ዜጋ ከዚህ ዕድገት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ዕድል ሲያገኝ ነው፡፡
ሆኖም የኢኮኖሚው ዕድገት ያመጣውን ቱርፋት ሕዝቡ እያጣጣመው ስለመሆኑ አጠያያቂ ነው፡፡ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት መሸከም አቅቶት የሚንገዳገደው ሕዝብ፣ በተለያዩ የአገልግሎቶች መዘበራረቅ ታክሎበት እየተማረረ ይገኛል፡፡ በእነዚህ ችግሮች ላይ ደግሞ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ብሎም የሰብዓዊ መብት መጓደሎች በችግሩ ላይ ተጨማሪ ሸክም እየሆኑበት ይገኛሉ፡፡ በሕዝቡ ላይ የሚታዩት ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመቃለል ይልቅ እየተጠናከሩ በመሄዳቸው፣ ምናልባት ለችግሩ መፍትሔ የሚሰጡት ባለሥልጣናት ለችግሮቹ አፅንኦት ይሰጧቸው ዘንድ፣ ለአንድ ሳምንትም ቢሆን ቤት ብንቀያየር ሳይሻል አልቀረም፡፡
ከሕዝቡ በተደጋጋሚ የሚሰሙት የብሶት መልዕክቶች በአፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጣቸው ባለመቻሉ ምናልባትም ለሳምንት ቤት መቀያየሩ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ በየጊዜው የፀረ ልማት አሉባልታ ናቸው እየተባለ ምላሽ የተነፈጋቸው የኅብረተሰቡ ችግሮች በኋላ መዘዛቸው የከፋ መሆኑ አይቀርም፡፡
መንግሥት የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ሽፋን ከ99 በመቶ በላይ መሆኑን ባገኘበት አጋጣሚ ቢለፍፍም፣ በተግባር የሚታየው ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በሆነችው በመዲናችን አዲስ አበባ በርካቶች በውኃ እጥረት ሲሰቃዩ ማየቱ ያስተዛዝባል፡፡ ለ15 ቀናትና ከዚያም በላይ ለሆነ ጊዜ ያለውኃ መኖር ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ሊረዱ ያልቻሉት ባለሥልጣናት፣ ምናልባትም ለአንድ ሳምንት ቤት ተቀያይረን ችግሩን ቢቀምሱት መፍትሔ ሊያመጡልን ይችላሉ፡፡
ከዚህም ባለፈ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የኤሌክትሪክ ኃይልም እንዲሁ እንደ ውኃ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በርካቶች በየዕለቱ በሚያጋጥም ተደጋጋሚ የሆነ የኃይል መቆራረጥና መጥፋት ሳቢያም ለከፍተኛ ኪሳራ እየተዳረጉ ናቸው፡፡
በተለይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አፍሰው የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ደፋ ቀና የሚሉ ባለኢንዱስትሪዎች በዚህ በኃይል መቋረጥ እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ ኅብረተሰቡም ቢሆን በዚህ የኃይል መቆራረጥ ሳቢያ ለበርካታ እንግልት እየተዳረገ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ በሚቃጠሉ ዕቃዎች ምክንያት ላላስፈላጊ ወጪ እየተዳረገ ነው፡፡ ይህ ችግር ከአሁን አሁን ይሻላል ቢባልም፣ ከድጡ ወደማጡ እየሆነ በመምጣቱ ምናልባት ቤት መቀያየሩ መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ባለሥልጣናቱ ይህ ችግር እየገጠማቸው ካልሆነ የችግሩን አንገብጋቢነት ሊረዱ ስለማይችሉ ቤት መቀያየሩ አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡
የሕዝቡ ችግር በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እጅግ አንገብጋቢ እየሆነ የመጣው የትራንስፖርት ችግር ማብቂያው የት እንደሆነ ከፈጣሪ ውጪ የሚያውቀው ያለ አይመስልም፡፡ ሕዝቡ በትራንስፖርት ችግር ምክንያት የእንጀራው ማብሰያ የሆነውን ጊዜውን ከማቃጠሉም ባሻገር፣ በፀሐይና በዝናብ ሲደበደብ ማየት ያሳዝናል፡፡ በዚህ በትራንስፖርት ችግር ሳቢያ አገሪቱ እያጣችው ያለው ነገር በጥናት ባይታወቅም፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እየጎዳው ስለመሆኑ አይጠረጠርም፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት ከባድ ምሬት እያስከተለ ነው፡፡ የእውነት ችግሩ መፍትሔ ታጥቶለት ነው ወይ ያስብላል፡፡ ምናልባት ባለሥልጣኖቻችን ባማሩ መኪኖች ከቦታ ቦታ እንደፈለጉ ስለሚንቀሳቀሱ የጉዳዩ አንገብጋቢነት አይገባቸው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለአንድ ሳምንት የሕዝቡን ገፈት መቅመስ ቢችሉ ምናልባት አፋጣኝ መፍትሔ ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ለአንድ ሳምንት እንኳን ቤት እንቀያየር፡፡
መንግሥት የሕዝቡን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ አሁንም ቢሆን ሕዝቡ በየጊዜው በሚንረው የቤት ኪራይ ምክንያት እየተሰቃየ ነው፡፡ ወሩን ሙሉ ለፍቶ የሚያገኘውንም ደመወዝ ከቤት ኪራይ ውጪ ለሌላ ነገር ማዋል እስኪያቅተው ድረስ በቤት ኪራይ ችግር እየተንገላታ ነው፡፡ መንግሥት ለባለሥልጣናቱ ያማሩ ቤቶችን ስለሚሰጣቸው ምናልባት ስለቤት ኪራይ ችግር ዘንግተውት ይሆናል፡፡ ለዚያም ነው እስቲ እነዚያ ያማሩ ቤቶቻችሁን ልቀቁና የሕዝቡን የቤት ኪራይ ችግር ተገንዘቡት የምንለው፡፡ እንደዚያ ቢሆን ምናልባትም መፍትሔ ለታጣለት ለዚህ ችግር አፋጣኝ ምላሽ ይገኝ ይሆናል፡፡
በየአካባቢው የፀጥታ ችግርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ዜጎች ሊያገኙት የሚገባቸውን ከተለያዩ ጥቃቶች የመጠበቅ መብት በተለያዩ ሕገወጥ አካላት እየተጣሰ በየቦታው በሕይወትና በንብረት ላይ አደጋ ሲከሰት ይታያል፡፡ ባለሥልጣኖቻችን የግል ጠባቂዎች ስላሏቸው ምናልባት ሕዝቡ በአጠቃላይ በሰላም ውሎ በሰላም የሚገባ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ እውነታው ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ስለዚህ እስቲ ለአንድ ሳምንት ቤት እንቀያየርና ችግሩን እናንተም ቅመሱት ነው የምንለው፡፡
አሁን እነዚህን ጉዳዮች ለአብነት አነሳን እንጂ በበርካታ ችግሮች ምክንያት ሕዝቡ እየተማረረ ነው፡፡ በእነዚህ ችግሮች ላይ ደግሞ የኑሮ ጫናው ሲጨመርበት ኅብረተሰቡ ምን እንደተሸከመ ባለሥልጣናቱ መረዳት አያዳግታቸውም፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ለእነሱ መንግሥት እያደረገ ያለው ነገር አይገባቸውም እያልን ሳይሆን፣ ሕዝቡ ቢያንስ ከምሬት ውስጥ የሚያወጡት መሠረታዊ ነገሮች ይኑሩት ነው የምንለው፡፡ ባለሥልጣናቱ ሕዝብን እስካገለገሉ ድረስ የሚያገኙት ጥቅም ይገባቸዋል፡፡ መረሳት የሌለበት ግን ሕዝቡም እነዚህን ጥቅሞች አቅም በፈቀደ መጠን ማግኘት አለበት፡፡ ለዚህ ነው ከባለሥልጣናቱ ጋር ለአንድ ሳምንት ቤት እንቀያየር የምንለው፡፡
No comments:
Post a Comment