Saturday, March 29, 2014

አፈና ከሁመራ እስከ አድዋ


ከአስገደ ገ/ስላሴ (መቐለ)

 በሁመራ ከተማ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንዲሰጡን ፣ የፀጥታ ከለላም እንዲያደርጉልን ጠይቀን ከብዙ ውጣ
ውረድ በኃላ አዳራሹ ፈቀዱልን። ቀበሌ 02 ያለው አዳራሽ ግን ከሻዕቢያ ምሽግ በጥይት ተኩስ 400 ሜትር
ርቀት ነው ያለው። ይህን አዳራሽ ለምን እንደሰጡን አላማው አልገባንም። አዳራሹ ለአደጋ የተጋለጠ ስለሆነ
ሌላ አዳራሽ እንዲሰጡን ከስንት መከራ እና ጭቅጭቅ በኋላ ሻዕቢያ ካለበት የራቀ የማዘጋጃ ቤቱ አዳራሽ
እንድንጠቀም ፈቀዱልን። የበተናቸው በራሪ ወረቀቶች ከሁመራ ጀምሮ ወልቃይት ፀገዴን፣ እስከ ሱዳን ድንበር
ያሉትን ቦታዎችን ሸፍነዋል።

በድምፅ ማጉልያም ቀሰቀስን ህዝቡ በከፍተኛ ስሜት ተቀበለን። ቅስቀሳ ስናካሂድ ከቀበሌ እስከ ዞን
አስተዳዳሪዎች፣ የደህንነት የፖሊስ አካላት እየተከታተሉ የህዝቡን ስሜት ያነባሉ። ኣባሎቻችን ዓረና የሚል ፅሁፍ ያረፈበት ቲሸርት
በመልበስ ነበር የሚንቀሳቀሱት። ህዝቡም ያከብራቸዉ ነበር። በቅስቀሳዉ እሰከ ሮብ ማታ ድረስ ያጋጠመን ችግር አልነበረም። ስብሰባዉ
አርብ ከጥዋቱ 2:30 ነበር የሚጀመረዉ።

በዋዜማው፣ ማለትም ሀሙስ ከሰአት በኋላ ከወልቃይት ፀገዴ በአውቶቡስ እና በጭነት መኪና የተጓዘው ህዝብ ሑመራ ከተማ መግባት
ጀመሩ፣ ከተማዋም በብዙ እንግዶች መጨናነቅ ጀመረች። በዛን ጊዜ የምእራብ ዞን አስተዳዳሪዎች የቃፍታ ሑሞራ ፣ የሑመራ ከተማ
ከንቲባ ፣የአካባቢ ቀበሌ ከተማ መሪዎች የፖሊስና የደህነት አባላት በሞተር ሳይክል፣ በኮድ አራት መኪና፣ በባጃጅ ላይና ታች ይላሉ።
በሁሉም ቀበሌ ስብሰባ አደረጉ፣ እኛ ግን አሁንም ቅስቀሳችን አላቋረጥንም።

ሃሙስ 10 ሰአት ሲሆን የሑመራ ከተማ ከንቲባ ፅ/ቤት ጠርቶ ምንም ሌላ መንደርደሪያ ሃሳብ ሳይናገር የምታደርጉት ስብሰባ ሰርዘነዋል
ኣለን። የከተማ ፖሊስ ደህንነት ሃላፊዎች እና የከተማዉ ካቢኔም አብረውት ነበሩ። እኛም ስብሰባውን እናደርጋለን ኣልናቸዉ።
ከንቲባውም አዳራሽ ኣንፈቅድም፣ ወደ ኣዳረሹም ዝር አትሉም ኣሉን። እኛም አዳራሹን ተዉት፣ በየጎደናው ቅስቀሳ እናደርጋለን ኣልን።
ከንቲባውም ኣታደርጉም! የፀጥታ ሃይሎችም እርምጃ እንዲወስዱ ታዘዋል አለን። በቃ ተዘጋ።

 እኛም የሁመራ ከንቲባ ፍትህ ስለነፈገን ወደ ምእራባዊ ዞን (ወልቃይት ፀገዴ) አስተዳደር ሄድን። ዋናዉ አስተዳዳሪ በመቐለ የክልሉ
ፓርላማ ጉባኤ ተሳታፊ ስለነበር ወደዛ ሄደዋል፤ ያለዉ ምክትሉ ነዉ። እሱጋ ሄድን። ተገቢውን አክብሮት ስጥቶ ተቀበለን። የደረሰብን
ጉዳይ ነገረነው። ምክትል ዞኑ ሁኔታዉን ምንም እንደማያውቅ በድርጊቱ ያዘነ መስሎ በመናገር ውጭ ቆዩና ከዞኑ ካቢኔ ጋር ተወያይተን
መልስ እንሰጣቹሃለን አለን።

ካቢኔዉ ከ10 ደቂቃ ያልበዛ ጊዜ ተሰበሰቡ። የሰጡን መልስ እኛ በወረዳ (ከንቲባ) ስራ ጣልቃ አንገባም። እነሱ የወሰኑትን ለማፍረስ
ስልጣን የለንም አለን። በሌላ በኩል ስብሰባ እንዳይደረግ የክልል መሪዎች ትእዛዝ መሆኑ የውስጥ ምንጮች ነገሩን።
አሁንም ምክትል አስተዳደሪዉን በመማፀን አጥብቀን ለማስረዳት ሞከርን። ከንቲባውም ጠርቶ እንዲያወያየን ጠየቅነዉ። ከንቲባዉ
ተጠርቶ መጣና የባሰውን ሊያስፈራራን ሞከረ። ምክትል አስተዳዳሪዉ ከመቐለ በሚደወል ስልክ ተጠምደዋል። ስብሰባችን ላለማድረግ
አልወሰንም።

 ሁኔታዉ እንደዚህ ሆኖ ጊዜዉ መሽቷል። ርቦናልም። አንድ ምግብ ቤት አግኝተን ገባን። ምግብ አዘን ተሰርቶ እስኪቀርብልን እየጠበቅን
ነው። ድንገት 4 የህዋሃት ሰላዮች መጥተዉ የአባይ ፏፏቴ ምግብ ቤት ባለቤት ጠርተው “ምግብ እንዳትሸጪላቸው” ብለው
አስፈሯሯቸዉ። ሴትየዋም የ24 ሰዎች ምግብ ከሰሩ በኃላ እየተንቀጠቀጡ ምግብ የለንም አሉን። እኛም ወጥተን ወደ አንድ ስጋ ቤት
ሄደን። ስጋ አስቆርጠን እየተጠበሰ እያለ እንደተለመደዉ እነዛ 4 ባንዳዎች መጥተዉ የስጋ ቤቱን ባለቤት አስፈራሩት። እኛ ዓረና የሚል
ካናቲራ እንደለበስን ነን። ሰዉየዉ እናንተ ምን አገባችሁ ህጋዊ ሆነዉ ሲንቀሳቀሱ ሰንብተዋል፤ አሁን ምን ተገኘ? እናንተ አጭበርባሪዎች
ናችሁ ብሎ ፖሊስ ጠርቶ አስወሰዳቸዉ። ፖሊሱ ዘወር ብሎ ለቀቃቸዉ። እኛ ግን በግርግር ራታችንን በላን።

ከ20 በላይ አባሎቻችን ገነት ሆቴል አልጋ ይዘዋል። ከንቲባዉ መጥቶ የሆቴሉን ባለቤት አስፈራርቶ ‘መታወቂያ ቸዉን ሰብስብ’ አለዉ፣
ህገ-ወጥ ናቸዉ ብሎ ለማሰር እንዲያመቸዉ። በሌላ በኩል በሆቴሉ አካባቢ እነዛ 4 ሰላዮች የሚያስተባብሯቸዉ ማጅራት መቺዎች
ጨለማን ተገን በማድረግ ቁመዋል። በመሃሉ ሁለት አባሎቻችን - ስልጣን ሕሸ የዓረና ስራ አስፈፃሚ እና ገብረኪሮስ የወቕሮ ፅፈት ቤት
ሃላፊ - ያላአንዳች ምክንያት አሰሩዋቸዉ። ጥዋት በብዙ ችግር ያለ ይቅርታ ተፈቱ። በዛን ወቅት ታዋቂ የሆነ ሞባይል ስልካችን ተዘጋ፤ ወደ
መቐለ፣ አዲስ አበባ ወይም ወደ ውጭ ለመደወል አስቸጋሪ ነበር። ኢንተር ኔት ቤት ብንገባም እየተከታተሉ ለማሰራት ከለከሉን። ሃሙስ
 አቶ አስገደ ገ/ስላሴ ኣልፎ አርብ ተተካ፣ ስብሰባውን የሚሳተፍ ህዝብ በብዛት መጥቷል። ከተማዉ በፖሊስ፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ በታጠቁ
ሚሊሺያዎች፣ በርቀትም መከላከያ ሃይል ይታያል። ፖሊሶች፣ የቀበሌ የወረዳ መሪዎች በሞተር ሳይክልና በባጃጅ እየዞሩ ህዝቡን ወደ
ስብሰባ እንዳይገባ በየቤቱ ቁጭ እንዲል አዘዙት። ህዝቡ ግን በሁሉም አቅጣጫ እየመጣ አዳራሹን በጥዋቱ ሞላዉ። ፖሊሶች ሲበትኑት
ህዝቡ ሲሰበሰብ ኣረፈደ ። ህዝቡ በጣም ተበሳጭተዋል። እኛም አባሎቻችን በብዛት በማሰማራት በአካልና በስልክ እየተገኙ ስለአፈናዉ
እንዲነግሩትና ወደየመጣበት እንዲሄድ አደረግን ። አርብ ከሰአት በኃላ ከሕሞራ ተነስተን ሽሬ ገባን። ባጠቃላይ የሕሞራ አፈና ባጭሩ ይህን
ይመስል ነበር። ታዲያ የህዋሃት መሪዎች ምን ስም እንስጣቸዉ?

የህወሓት መሪዎች የአድዋ የአፈና ስልትስ?

ዓረና መድረክ የአድዋና የአካባቢዉን ህዝብ በአድዋ ከተማ ሰብስቦ አማራጭ ሃሳቡን ለማስተዋወቅ አዳራሽ እንዲሰጠዉ በጠየቀዉ
በሁለተኛ ቀን አዳራሽ ሰጡን። ፖሊስ ፅጥታ እንዲያስከብር እንደታዘዘም ደብዳቤ ተፃፈልን። እኛም የተዘጋጀ በራሪ ወረቀት በአድዋ ከተማ
በገጠር ወረዳዎች በማይቀነጣል፣ በነበለት፣ እምባስነይቲ፣ በዕዳጋ ዓርቢ (እንዳባ ፃሕማ) በፈረስማይ፣ በእንትጮ በድምፅ ማጉሊያ
ቀሰቀስን፣ ወረቀት በተን።

በቅስቀሳዉ ወቅት በገጠር ወረዳዎች ምንም ችግር አላጋጠመንም። በአድዋ ከተማ ጠ/ር መለስ በተወለዱበት ጎጥ 20 የሚሆኑ ቀስቃሽ
የዓረና ሰዎችን ለመምታት ሞክረዉ የአካባቢ ህዝብ ፖሊስ ጠርቶ አስበተናቸዉ። በሌላ በኩል ከአድዋ ዋና ከተማ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት
የምትገኝ ስብሃት ነጋ ጎጥ በርከት ያሉ ወጣቶችና ልጆች ተደራጅተዉ ቆይተዉ አባሎቻችንን በድንጋይ መምታት ሲጀምሩ በአንድ አካባቢ
የነበሩ ትላልቅ ሰዎችና ወጣቶች ተከላከሉላቸዉ። እኛም ፖሊስ ጠርተን በፍጥነት ደርሶ ዋና ዋና ረብሸኞችን ብናሳስርም ፖሊስ ግን አስሮ
ወዲያውኑ ለቀቃቸዉ። ከዛ በኃላ በአደዋ ከተማ በምንንቀሳቀስበት ጊዜ ፖሊስ ጥበቃ አድርጎልናል። ባረፍንበት ሆቴልም አስተናጋጆች
አክብሮት በመስጠት በፈገግታ አስተናግደውናል። እኛም በግልፅ ዓረና የሚል ካኔትራ ለብሰን ቀንና ሌሊት ስንዞር ወጣቶች ሆኑ
ሽማግሌዎች በበፈገግታ ነበር የሚመለከቱን። ቁጭ ባልንበት ቦታ ጠጋ ብለዉም ያበረታቱናል። በከተማዉ ያለዉ ችግር ስብሰባ ላይ
እንድናነሳዉ ይጠቁሙናል። ስለሆነም በቅስቀሳ ወቅት የአድዋ ህዝብና የአድዋ ፖሊስ ላደረገልን ትብብር አመስግነናል። የከተማ
አስተዳደርም አዳራሽ በመስጠትና የፀጥታ ሃይል በመፍቀድ በቅስቀሳ ወቅት ከዓዲግራት፣ከተምቤንና ከሽሬ በመማር ረብሻ ባለመፍጠሩ
እናመሰግናለን።

 በሌላ በኩል ግን የህዋሃት መሪዎች ተፈጥሯዊ ባህሪያቸው የሆነውን ሴራ በረቀቀ ዜዴ ህዝቡን ስብሰባ እንዳይሳተፍ ለ4 ቀን ያህል ቤት
ለቤት በመዞር በ1 ለ5 በ1 ለ10 ቡድን መሪዎች በቀበሌ አስተባባሪዎች እንዲሁም የህዋሃት አባላት ሰብስበዉ ስልጠና በመስጠት 1ኛ
ሁሉም የቡድን መሪ ቡድኑን እንዲቆጣጠር 2ኛ ሁሉም አባል ቤት ለቤት እየዞረ ወላጆች ልጆቻቸዉ ስብሰባ ላይ እንዳይገኙ፣ ከተገኙ
የአድዋን ታሪክ ማበላሸት መሆኑን ያስጠነቅቃሉ። የገጠሩ ነዋሪ በመኪና ወደ አድዋ ሲገባ የቀበሌ መሪዎች ደግሞ መኪና በመመደብ ወደ
መጣበት ይመልሱታል።

 የሁሉም ቀበሌ ሃላፊዎች በየመስሪያቤቱ የሚገኙ ሃላፊዎችና ኣባላት ወደ አዳራሽ የሚወስዱ ጎደናዎች በየ ሻሂ ቤቱ ቡና ቤት መናፈሻ
ሆነዉ አዳራሽ የሚገባውን ሰዉ በሞባይል ካሜራ በማንሳት እንዲያስፈራሩ ተመድበዋል።

 ፖሊሶች ለስብሰባዉ ፀጥታ ሊያስከብሩ የጠየቅነዉ በቁጥር ከ አምስት የማይበልጡ ቢሆንም፣ የአድዋ ፖሊስ አዛዦች ግን ብዙ ፖሊሶች
በመሰብሰብ በኣዳራሹ ዙርያ በ20 በ50 በ200 እና በ 500 ሜትር ርቀት ፖሊሶችን አቆሙ። ሲቪል ለባሽ ፖሊሶችም በብዛት በር በሩን
መንገድ ዘግተዋል። በዞን ወቅት አድዋ ከተማ ከጥዋቱ 1:00 ሰአት እስከ 8:00 ሰአት በመንገድ ይሁን ከቤት ውጭ ሰዉ አይታይበትም።
ጭር ብሎ ነበር፤ ተአምረኛ በዲሲፕሊን የተሰራ አፈና።

- የስብሰባዉ ሰአት ደረሰ። ስብሰባውን ለመሳተፍ የደፈሩ ወጣቶች መምጣት ጀመሩ። ቀስ በቀስ ለህዝቡ መልእክት
ሊያስተላልፉ የሚችሉ ወገኖች ገቡ። በተጨማሪም የህዋሃት አባላትም ተመልምለዉ የገቡ ነበሩ። ስብሰባዉም ተጀመረ። እነዛ የግራዚያኒ
ተላላኪዎች ለመረበሽ ሞክረዉ ነበር። ነገር ግን ነፃ የሆኑ ወገኖች ትእግስት አደርጉ። ከህዋሃት ሃሳብ ሌላ ሃሳብ መስማት እንፈልጋለን
ብለዉ ወቀሱዋቸዉ። ኣንዳንድ የህዋሃት አባላትም በትእግስት እየተከታተሉ ይጠይቁ ነበር። ኣንዳንድ ባንዳዎችም ወደ ስብሰባዉ ገብተዉ
ከተሰብሳቢዉ ህዝብ ይዘዉ ለመውጣት ይሞክሩ ነበር። ነገር ግን የሚሰማቸዉ ሰዉ አልነበረም። እንደዚያም ሆኖ ስብሰባዉ በጥሩ ሁኔታ
ተጠናቀቀ። በፀጥታ በኩል ግን ውስጣዊ ሴራውን ትተን የዓዲግራት ፖሊሶች ቆመዉ በህፃናት እንዳስጨፈጨፉን ይቅርና ሶስት ቀን ሙሉ
ጠብቀዉናል አመሰግናቸዋለሁ። ለወደፊት ግን ከተደበቀ ሴራ ተቆጥበው የፖሊስ ነፃነታቸዉን ጠብቀዉ እንዲያገለግሉ
ሃሳቤን እለግሳቸዋለሁ።

- የአድዋ አፈና የረቀቀ ያልኩበት ምክንያት ዓረና መድረክ ከተመሰረተ ቀን ጀምሮ ህዝብን ሰብስቦ በሚያስተምርበት ጊዜ
ህዝብ እንዳይሰበሰብ በማድረግ በዓረና ስብሰባ ቀን ወደ ሌላ ስብሰባ መጥመድ፣ አባላትን መምታት፣ በራሪ ፅሁፎችን መቅደድ፣ መቀማት፣ በህዝብ እጅ የገቡ ፅሁፎች ፖስተሮች ሰብስቦ ማቃጠል፣ በስብሰባ ኣዳራሽ ውስጥ ገብተዉ መበተን፣ መሳደብ፣ ህዝቡ ወደ
ስብሰባ ሲገባ መመዝገብ፣ ፎቶ ማንሳት፣ ከስብሰባ በኃላ የተሳተፉ ዜጎችን በመጥራት ማስፈራራት፣ የመንግስት ሰራተኛ ከሆነ ከስራ እስከ
ማባረር ወይም ዋስትና እንዲያጣ ማድረግ። እንኚህ እኩይ ምግባሮች ባገር ውስጥም በውጭ አገርም ኪሳራ ስላስከተለባቸዉ የአድዋ
የተራቀቀ አፈና ግን ህዝብ የሚመለከተዉ ሁሉ በግልፅ እየተባበሩ እንዳሉ ህዝብን የሚያታልል ስራ ሆኖ በቅስቀሳ ጊዜ ምንም እንቅፋት
ከመፍጠር ከመቆጠብ በላይ እንደጠቀስኩት በቤት ቁጥር ጥበቃ በማድረግ ህዝቡ በቤቱ ታስሮ እንዲውል አደረጉ። ይህ ደግሞ በአይኑ
እንዳይመለከት እንዳይሰማ እንዳይናገር አድርገዉ በማፈን በአድዋ ህዝብ የማይረሳ ጠባሳ አስቀምጠዋል። በጣም የሚገርመዉ ግን የአድዋ
ህዝብ ከትግራይ ክልል ከተሞች እጅግ የደኸየና የተራበ የታፈነ መሆኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖች የተገነዘቡት ጉዳይ አይደለም። የህ.ዋ.ሃ.ት
መሪዎች ጥቂት ሰዎችን እየጠቀሙ ህዝቡን ለድህነትና ለስደት ዳርገውታል። የአድዋ ህዝብ በዓረና ስብሰባ ላይ ከተገኘ በኋላ የአድዋ ታሪክ
አበላሽተሃል ተብሎ ወቅሰዉታል። የአድዋ ታሪክ እንዳታበላሹ የሚሉት ባንዳዎች ደግሞ ሀገራቸዉን የባህር በር እንዳይኖራት ያደረጉ፣
ኤርትራን ለመገንጠል ህግ ያፀደቁ ከሕሞራ እስከ ጋምቤላ ያለዉ እነአፄ ዮሃንስ የሞቱበት መሬታችን ለባእድ የሚሰጡ፣ ሃገራችን በዘርና
በሃይማኖት እየለያዩ ለአደጋ ያጋለጡ ናቸው የአድዋን ህዝብ “ታሪክ እንዳታበላሽ” እያሉ የሚመጻደቁ።

የአድዋ ህዝብ እነሱን ጠንቅቆ ቢያውቃቸውም፣ በአፈናው ግን ወዶ ሳይሆን ተገዶ ቤቱ ውስጥ ታስሮ ውለዋል። የህ.ዋ.ሃ.ት መሪዎች
ለመጭዉ 2007 ምርጫ እንዴት ህዝቡን እንደሚያፍኑ ካሁኑ ዝግጅታቸውን ጀመረዋል።

የውስጥ ምንጮች እነደ ነገሩኝ በመጭዉ ሚያዚያና ጉንበት ትልቅ ህዝባዊ ኮንፈረንስ በማድረግ 1

 የ2007 ዓ/ም አገራዊ ምርጫ
ለተቃዋሚ ፓርቲ የረቀቀና በተቀናበረ በማይጋለጥበት መንገድ ለማፈን 2

 ህ.ዋ.ሃ.ት እየተፍረከረከ ስላለ በሌሎች አባል ድርጅቶችና
አጋሮቹ የበላይነትን ለማረጋገጥ ባገር ውስጥና በውጭ ያሉ የህዋሃት ታጋዮች በመሰባሰብ ህ.ዋ.ሃ.ት.ን ለማጠናከር ያለመ 3

 ከትግራይ
ህዝብ ስለተለያየን ያለውን ችግራችን በመለየት ከህዝብ ጋር መታረቅ እስከ ቀበሌ ኮንፈረንስ ማድረግ 4

 በትግራይ የተደረገ እንቅስቃሴ
በሁሉም አባል ፓርቲዎች እንዲደረግ ማድረግ የሚሉ ናቸዉ። በተጨማሪም ለምርጫ 2007 ዓ/ም ምርጫዉ የሚያፍኑና
የሚያጭበረብሩ ከወዲሁ ስልጠና እየተሰጣቸዉ ይገኛሉ። በዚህ ስራ ሴራውን ለመጠንጠን …ስብሰባ ለማሰናከል የተጠቀሙበትን የአፈና
ዘዴ እንደተሞክሮ ቆጥረውት የሚቀጥሉበት መሆናቸዉ መናፈስ ጀመሯል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎችስ ምን ማድረግ አለባቸዉ?

የህወሓት መሪዎች በነፃ ምርጫ ተሸንፈዉ ስልጣን ላለመልቀቅ ሲሉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ፣ የማይሸርቡት ተንኮል የለም። የህወሓት
መሪዎችና አጋሮቻቸዉ ስለ ህዝብ ስራ አጥነት፣ ስደት፣ ድህነት፣ ችግር መፍታት አያሳስባቸውም። የሚያሳስባቸው ነገር ካለ የአገሪቱን ሀብት
እንዴት በስልጣን ላይ እያሉ አሟጠው የግል ሀብታቸውን እንደሚያደልቡ ነው።

በገዢው ቡድን ተስፋ የቆረጠው ህዝብ ዛሬ ከባድ ችግር ውስጥ ገብቶ ከችግሮቹ ያላቁቁኛል ብሎ ተስፋ ለጣለባቸው ተቃዋሚ ኃይሎች
የድረሱልኝ ጥሪውን እያሰማ ይገኛል። ይህ እጅግ የተበደለ እና የተዳከመ ህዝብ ለመታደግ ተቃዋሚዎችስ እምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
ተቃዋሚዎች መሰረታዊ ባልሆኑ ልዩነቶች እየተነታረኩ ጊዜአቸውን እያባከኑ ናቸዉ። እነዚህ ወገኖች ከወዲሁ ሁኔታቸውን አስተካክለዉ
ወደ ህዝብ ወርደዉ የህወሓት መሪዎችን ሴራ እያጋለጡ ህዝብን ከጎናቸዉ በማሰለፍ ለምርጫ 2007 ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ ከወዲሁ
ይጠበቅባቸዋል። “ስታንቀላፉ ከርማችሁ ምርጫ ሲደርስ በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብትሉ ምንም ፋይዳ አለው!” የሚለውን የህዝብ
ማስጠንቀቅያ ዘንድሮም ፈጽሞ መሰማት የለበትም።



ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
March 25, 2014 

No comments:

Post a Comment