Sunday, February 9, 2014

ወጣቶች ኩርፊያ-በኢትዮጵያ!

ወጣቶች ኩርፊያ-በኢትዮጵያ!

(ጥራኝ ጎዳናው! ጥራኝ መንገዱ!)

(በሰሎሞን ተሰማ ጂ.) http://semnaworeq.blogspot.com   Email: solomontessemag@gmail.com


የኢትዮጵያ ወጣቶች በሦስት መስቀለኛ መንገዶች ላይ ቆመዋል፡፡ የመጀመሪያው መንገድ ከባህልና ከልማድ የተወረሰ ነው፡፡ ዘፈን፣ ቀረርቶና ሽለላም አለው፡፡ አፋሩ፣“ዳሀር ቦር ናሬ!” ይላል፡፡ (“ግመሎቼና ከብቶቼ፣ እውጪ ማደር ልማዳችሁ ነው፤ እኔም እንደናንተ ጠላቴን ሳመነዥገው ደጅ-አድራለሁ!” እያለ ይዘፍናል፡፡) ኦሮሞውም፣“አቢቹ ነጊያ ነጊያ!” የሚል ዜማ አለው፡፡ (የወንድሞችህን ገዳዮች አሰቃይተህ እስከምትገላቸው ድረስ፣ እንቅፋትም አይንካህ! ድል-በድል ያድርግህም!” የሚል መልዕክት አለው፡፡ የአማርኛ ተናጋሪውም ቢሆን፣ “ጥራኝ ደኑ! ጥራኝ ዱሩ!....ላንተም ይሻልሃል ብቻ ከማደሩ!” እያለ ይሸልላል፡፡ ይህ የሚሆነው እንግዲህ ወጣቱ ያኮረፈ ጊዜ ነው፡፡ ምክንያቱ ሊለያይ ይችላል፤ ነገር ግን፣ ወጣቱ ኩርፊያውን ለመግለጽ የሚጠቀምበት ባህላዊ መንገድ “ሽፍትነትን” ነበር፡፡ አብዛኞቹም ሽፍቶች በአካንዱራ (በባህላዊ የጦር ስልት) የተካኑና የተፈጥሮ አደጋዎችን መቋቋም የሚችል ተክለ-ሰውነት ነበራቸው፡፡ የቤተ-ክህነትም ሆነ የዘመናዊ ትምህርት የላቸውም፡፡ (ዛሬ ላይ፣ ይሄን ባህልና ልማድ ጠብቆ ለመሄድ የሚያመች ነባራዊ ኹኔታ የለም፡፡ ደኖች ተጨፍጭፈዋል፤ ተቃጥለዋልም፡፡ በሌላም በኩል፣ የዘመናዊ ትምህርትና የዘመናዊ አኗኗር ዘይቤዎች ወጣቱ ባህልና ልማዱን ተከትሎ እንዳይሄድ ደንቃራ ሆነውበታል፡፡) 
ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች በሚባሰቡባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ኮሌጆች፣ እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጪም ሀገራት ጎዳናዎች ላይ ተቃውሞአቸውን የማሰማት አማራጭን መጠቀም ጀምረዋል፡፡ ነገሩ፣ በ1945/6 ዓ.ም ከኮሪያ ዘመቻ በተመለሱ የክብር ዘበኛ ወጣት መኮንኖችና በቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ-ኮሌጅ ተማሪዎች አማካይነት እንደተጀመረም ይታወቃል፡፡ ዛሬ ላይ ግን፣ ከኢትዮጵያ ዳር ድንበሮችም አልፎ በወጪ አገራት በሚገኙ የአትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላትም ዘንድ ተንሰራፍቷል፡፡ “ጥራኝ ደኑ! ጥራኝ ዱሩ!” በሚለው ሽለላ ምትክ፣ “ጥራኝ ጎዳናው! ጥራኝ መንገዱ!” ወደሚል ተሸጋግሯል፡፡ ለምን? ከላይ እንደጠቀስነው፣ የደኑ መጨፍጨፍና መቃጠል፣ የወጣቱ በዘመናዊ ትምህርት እያደገ መሄድ፣ የዓለም አቀፉ ተጽዕኖ እያደገ መሄድ፣ የግለኝነት ንቃተ-ህሊና መጎልበትና የተከታታይ ሥርዓቶች ያሰረፁት ፍርሃት (ቦቅቧቃነት-Conscious Objector) ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ገጣሚው ኃይሉ ገብረ ዮሐንስን (ከ1958-66ዓ.ም ድረስ፣) “ኧረ! የወንድ ያለህ!” እያለ ያስጮኸው ይኼው የወንድ/የወኔ ዕጦት ጣጣ ወጣቱ አካባቢ “ስላጣ” ነበር፡፡ ያም ሆኖ፣ ዛሬ-ዛሬ፣ “ጥራኝ ጎዳናው! ጥራኝ መንገዱ!” የሚለው የወጣቶች እንቢተኝነት፣ ከአረቦቹ የፀደይ አብዮት በኋላ የሚጠበቅ ነው፡፡ 
 
በሦስተኝነት የሚመጣው አማራጭ የወጣቶች ብሔራዊ እንቢተኝነት የሚገለጽበት መንገድ ደግሞ ሽብርተኝነት ነው፡፡ ይህንን መንገድ ለመከተል የሚያመች ነባራዊ ሁኔታ የለም የሚሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን አጋጥመውኛል፡፡ በግንባር ቀደምትነት የሚመጡት ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ናቸው፡፡ የእርሳቸውን ንግግሮችም የሚጋሩ በርካታ የግል መገናኛ ብዙኃን ፀሐፍትና አዘጋጆችም አሉ፡፡ የገዢው ፓርቲ ባላጋራ መሪዎችም(ተቀናቃኝ የፖለቲካ ማኅበሮችም) ከፕ/ር መስፍን አባባል ጋር ይስማማሉ፡፡ “የገዢው ፓርቲ መሪዎችና ካድሬዎች፣ ይኼንን ከኢትዮጵያውያን ባህልና ልማድ ጋር የማይሄድ ቋንቋ የሚጠቀሙት የተቃዋሚ አባላትንና የግል ጋዜጠኞችን ለማሰርና ለማሸማቀቅ እንዲያመቻቸው ብለው ነው፤” ሲሉም ይከራከራሉ፡፡ በእርግጠኝነትም፣ የእነአንዱዓለም አራጌንና የርዮት ዓለሙን እስር ከዚህ ጋር ያገናኙታል፡፡ በ1989/90 ላይ ተደርገው የነበሩትንም የነዶ/ር ታዬ ወ/ሰማያትና የሌችንም የፖለቲካና የሙያ ማህበራት መሪዎች የእስር ሂደት ያወሳሉ፡፡ በብያኔውና በትርጓሜው ላይ ብንስማማም-ባንስማማም “ሽብርተኝነት” የኢትዮጵያ ወጣቶች ሊሳቡበት ከሚችሉበት የእንቢተኝነት መንገዳቸው አንደ ነው፡፡ (በእርግጥ! አለ ወይስ የለም? የሚለውን ክርክር ለየቅላን ብንተወው ይሻላል፡፡)
እስካሁን የተነጋገርንባቸውን ሦስት ሃሳቦች በሌላ ቋንቋ መነጋገር አስፈላጊ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች የተቃውሞና “የአልገዛም ባይነት” እንቅስቃሴዎችን በተጠናከረ ኹኔታ እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ እንቅስቃሴዎቻቸውም ሦስት ዓይነት መልኮችን በመያዝ ላይ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የጎዳና ላይ ትዕይንተ-ተቃውሞ ነው፡፡ መነሻውም-መድረሻውም ሰላማዊ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በዋናነት በከፍተኛ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ይታይ ነበር፡፡ ከዓመት ከመንፈቅ ወዲህ ደግሞ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችም ውስጥ የማይናቅ አቅም አጎልብቷል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ የሽምቅ ውጊያ ይዘት አለው፡፡ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት ገደማ የኦሮምኛ፣ የሶማሊኛና የአፋርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በእጅጉ ሲለፉበትና ሲደክሙበት ቆይተዋል፡፡ የትግራይና የኤርትራ ወጣቶችም በዚሁ ዓይነት መንገድ “ናጽነት” አገኘን ብለዋል፡፡ ከሦስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ፣ ይሄው የሽምቅ ውጊያ (የርስ-በርስ ጦርነት) አዝማሚያ ወደ ጋንቤላ፣ ወደ ደቡባዊት ኢትዮጵያና ወደ አማርኛ ተናጋሪ-ወጣቶችም ዘንድ ተዛምቶ ከፍተኛ እንቅስቃሴዎች ባብዛኛው የኢትዮጵያ ገጠራማ ክፍሎች ውስጥ መታየት ጀምሯል፡፡ (የአኙዋክ ወጣቶች ንቅናቄ (አወን)፣ የደቡብ ወጣቶች የጋራ ንቅናቄ (ደወጋን)፣ እና የአማራ ወጣቶች የጋራ ንቅናቄ (አወጋን) የሚባሉት ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የተመሠረቱ “ወጣት-ተኮር” ድርጅቶች ናቸው፡፡)
 
በሦስተኛው ዓይነት የኢትዮጵያ ወጣቶች ተቃውሞአቸውንና “ያልገዛም ባይነታቸውን” የሚገልጹበት መንገድ በኅቡዕ የመደራጀት አማራጭ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አደረጃጀት መነሻውም-ሆነ-መድረሻው ምስጢራዊ ነው፡፡ ሄዶ-ሄዶም፣ የራሱን የመገናኛ ኮድና የራሱን ጠንካራ የሰው ኃይል አደራጅቶ (Networked Structure) ወደ ሽብርተኝነት ያድጋል፡፡ በርግጥ! ብዙዎች “የኢትዮጵያ ህዝብ የባህል፣ የሃይማኖትና የማኅበራዊ ኹኔታ ለዚህ አደረጃጀት (ለሽብርተኝነት ኔትዎርክ) የሚመች አይደለም” ይላሉ፡፡ ከዚህ ሃሳብ አቀንቃኞች መካከልም ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ይገኙበታል (“አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ” የሚለውን መጽሐፋቸውን መመልከቱ ጥሩ ነው፡፡) በሌላ በኩል ደግሞ፣ ኢትዮጵያን የሽብርተኝነት አደጋ እየተጋረጠባት ነው በማለት፣ ገዢው ፓርቲ ወያኔ-ኢህአዴግም ሁለት አዋጆችን አውጥቷል፡፡ አንደኛው “የፀረ-ሽብር ሕግ” (አዋጅ ቀጥር 652/2001) እየተባለ የሚታወቀው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ “ሽብርተኝነትን በገንዘብና ቁሳቁስ መደገፍን የሚከለክል ሕግ” (አዋጅ ቁጥር 780/2005) ነው፡፡
እዚህ ላይ ሊጤን የሚገባው ትልቅ ቁምነገር አለ፡፡ እርሱም፣ ሽብርተኝነት ከባህልና ከሃይማኖት፣ ብሎም ከፖለቲካ-ኤኮኖሚ ጋር አያይዞ አለመመልከቱ ጥሩ ነው፡፡ ከ1957 ዓ.ም ወዲህ እንዳየነው ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች አይሮፕላን የመጥለፍም ሆነ የአቬሽን እንቅስቃሴዎችን የማስተጓጎል ባህልና ዝንባሌ አልነበራቸውም፡፡ ግና፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ኮሞሮስ ደሴቶች አካባቢ በግዳጅ እስካረፈው አይሮፕላናችን ድረስ ኢትዮጵያውያኑ ጉዳት የማድረስ አቅምም ክህሎትም እንዳላቸው ታይቷል፡፡ ነገሩ የዓለም ዓቀፉ ትኩሳትም ማሳያ (ነጸብራቅ) አካል ነው፡፡ በቀላል አማርኛም የየዘመኑን ፋሽን የመከተልም ዝንባሌ (ስበት) ተደርጎም ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን፣ ወደ ሽብርተኝነትና ወደ ኅቡዕ መዋቅሮች ውስጥ ሊገቡ የሚችሉት ወጣቶች ከአንድ ከተወሰነ ሃይማኖት፣ የኤኮኖሚ መደብ፣ ከሆነ ዘር/ብሔር፣ አለያም ደግሞ ከአንድ የማኅበራዊ መድሎ ከደረሰበት ክፍል ብቻ አድርጎ ማሰላሰሉ አያዋጣም፡፡ 
ወደ ሽብርተኝነቱ ጎራ ለመቀላቀል የሚፈልጉ ወጣቶች ካሉ የሚከተሉት ሦስት አማራጮች ምቹ መደላድሎች ይሆኗቸዋል፡፡ 1ኛ) የፖለቲካ-ኤኮኖሚው የሚፈጥርባቸው ኩርፊያ ነው፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ፣ ገዢዎቻችን እንደሚነግሩን ሳይሆን ስር-የሰደደ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ዱካክ ወጣቱን አስኮርፎታል፡፡ መሥራት ከሚችሉት መካከል 45% (በመቶ) የሚሆኑት የኢትዮጵያ ወጣቶች ሥራ-አጥ ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ችሎታውና አቅሙ እያላቸው በክልል መንግሥታትና ሹመኞች (ፖለቲካዊ በሆነ አድሎና መድሎ) ለሥራ-የደረሱ እጆቻቸውን አጣጥፈው የተቀመጡ ናቸው፡፡ ጉዳይ ፖለቲካዊ በመሆኑና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖውም ፋታ የማይሰጥ በመሆኑ ከፍተኛ ኩርፊያን አስከትሏል፡፡ ኩርፊያውም እያደገ ወደ ከባድ የተስፋ መቁረጥን ደረጃ በመድረስ ላይ ይገኛል፡፡ 2ኛው) ችግር ደግሞ ከወጣቱ ንቃተ-ኅሊና ጋር የማይሄድ የገዢዎቹ ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ገዠዎቹ “ወጣቱ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ተረካቢ ነው፤” እያሉ ሲሸነግሉት ኖረዋል፡፡ ነገር ግን፣ ወጣቱ “የአሁኒቷም ኢትዮጵያ ባለድርሻ ነኝና የሚገባኝን ድርሻዬን አምጡ፤” በማለት ላይ ይገኛል፡፡ (የገዢዎቹ “ወደፊት ጠብቁና” የወጣቶቹ “አሁኑኑ አምጡ” ንትርክ ማቆሚያም ያለው አይመስልም፡፡ ስለሆነም አስገድዶ ድርሻን ለመንጠቅ የሽብር አማራጭ ሊከተል ይችላል፡፡) ዛሬ፣ ተደራጅተው የልጃገረዶችን ተንቀሳቃሽ ስልኮችና ጌጣጌጦች ከመንጠቅ አልፈው፣ ትልልቅ የኮንተራባንድና የዕጽ-ማዘዋወር ተግባራት ላይ ኔትወርክድ ሆነው ሊደራጁ ይችላሉ፡፡ 
ሦስተኛ(3ኛ)ው ነጥብ ደግሞ፣ የወጣቶቹ በዘመን አመጣሽ አስተሳሰቦች መማረክና በባዕዳን ኃሎች የመጠለፍ እድላቸው እያደገ የመሄዱ ጉዳይ ነው፡፡ በ1960ዎቹ የነበሩት የኢትዮጵያ ወጣቶች በኮሚኒዝም አስተምህሮዎችና መሪዎች እንደተሳቡት ሁሉ፣ ያሁኖቹ ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅና በሩቅ ምስራቅ አካባቢ ባሉ የኅቡዕ ድርጅቶችና መሪዎች ሊማረኩ የማይችሉበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ይህ የስሜት የ(Impression) ጉዳይ ነው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ፣ በአሁኑ ሰዓት ድንበር-ዘለል የኅቡዕ ድርጅቶ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጉርሻና ጠቀም ያለ ክፍያን ለወጣቱም ሆነ ለቤተሰቡ ይከፍላሉ፡፡ ይህ ማበረታቻም ከስሜት ድጋፍ ሰጭነታቸው ባሻገር፣ ሳቢና ማራኪ ነው፡፡ 
ይህንን የሽብር አማራጭ ሳይጠቀሙ የተሻለና እጅግ አመርቂ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለው መንገድ የትኛው ነው በሚለው ላይ የበለጠ መነጋገር፤ መወያየትም የተገባ ነው፡፡ ከ“ጥራኝ ደኑም ሆነ ከሽብሩ መንገድ” ይልቅ “የጥራኝ ጎዳናው! የጥራኝ መንገዱ!” አማራጭ እጅግ አዋጪ ነው፡፡ የህንን የምለው የግብጽን፣ የቱኒዚያንና የሌሎችን አረብ አገር “የፀደይ ወራት!” ብሔራዊ እንቢተኝነት እንድገም ለማለት አይደለም፡፡ በዚህ አመለካከቴም፣ከልጅ ተመስጌን ደሳለኝና ከተወሰኑት ባልደረቦቹ የተለየ አቋም ነው ያለኝ፡፡ እነርሱ፤ “መስቀል አደባባይን የጣህሪር አደባባይ እናደርጋታለን” የሚል ሃሳብ ያንፀባርቃሉ (አዲስ ታይምስ መጽሔት፣ 2005ዓ.ም፣ ቁጥር-3ን ይመልከቱ፡፡) የምለው፤ በ1966እና በ1983ዓ.ም እንዳደረግነው፣ ሕዝባዊ እንቢተኝነታችንን ለታጣቂ ኃይሎች ላለማስከብ፣ በቅድሚያ ጠንክረን መሥራት ይገባናል ነው፡፡ የመጀመሪያው ሥራ፣ ወጣቱንና ሕዝቡን በተሳካ ኹኔታ በማደራጀት ነው፡፡ ከገጠር እስከ ከተማ ድረስ ጠንካራና ሰላማዊ የሆነ ድርጅት መሥራት የግድ ይላል፡፡ ከገዢው ፓርቲ ጋር የሚደረገውም ትንቅንቅ ቀላል አይሆንም፡፡ ያንን ተቋቁሞ የተሳካ አደረጃጀትና ታዓማኒነት ያለው የፖለቲካ አመራር ማዘጋጀትም ያስፈልጋል፡፡ 
“ሥልጣን” የምትባለውን ጉደኛና አደገኛ “ሰይጣንም” ለመያዝ፣ በወታደሩና በፀጥታ ኃይሎች አካባቢ የሰላማዊ ታጋዮቹ አላማና ርዕይ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያለመታከት መሥራትን ይጠይቃል፡፡ የወጣቶቹ ሰላማዊ አደረጃጀትና ተዓማኒነት ያለው አመራር ዕውን ከሆነ፣ በወታደራዊውም ሆነ በፀጥታና በደኅንነቱ አካላት ዘንድ ያሉትን በመቶ ሺ የገመቱ ወጣቶችን ልብ ለማሸፈት አቅም ይኖረዋል፡፡ ከዚህም ሌላ፣ በሰላማዊ መንገድ የሚዳጁት ወጣቶች ያሏቸውን የተለያዩ የመገናኛና የመልዕክት ማስተላለፊያ ዘዴዎች ይበልጥ ጠንካራና የማይታወኩ አድርገው መሥራት አለባቸው፡፡ ለዚህም ተግባር የሚያግዙ በርካታ በጎ ፈቃደኞችንና የተለያዩ ጥቅማ-ጥቅሞችን የሚያገኙ የቴሌ፣ የፖስታ፣ የመንገድ ትራንስፖርት፣ የአቬሽንና የመገናኛ ብዙኃን ሰራተኞችን ከወዲሁ ማዘጋትም የግድ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ያሉትንና በተለያዩ ኤጀንሲዎች ተጽፎ የሚሰጣቸውን መግለጫና ዜና ለእጀራቸው ብለው የሚያቡትን (የሚያነበንቡትን) ጋዜጠኞች መጥላቱም ሆነ ማጥላላቱ ጊዜ ማጥፋት ነው፡፡ ከእነርሱ ይልቅ፣ ከኋላ ሆነው የሚያቅዱትና ስልቶችን የሚነድፉት “ጎበዞችና ጎበዛዝት” ላይ ማተኮሩ ተገቢ ነው፡፡
ይህ ሃሳብ ወደ አንድ አቅጣጫ ይመራናል፡፡ ወጣቱ ያለውን ውሱን ጥሪትና የሰው ሃይል በሚገባው ቦታና ሰዓት አውሎ፣ ትግሉን አስተማማኝና እጅግ ሰላማዊ መሆኑን ለማረጋገጥ ከፈለገ፣ የሚያተኩርባቸውን “ጎበዞችና ጎበዛዝት” ማንነት፣ አድራሻ ቦታ፣ የዘወትር እንቅስቃሴያቸውንና የእነማን ወዳጅና ጠላት እንደሆኑ ኹሉ አብጠርጥሮ ማወቅ አለበት፡፡ እነማን የንግድ ሸሪኮቻቸው እንደሆኑ፣ እነማንስ ቂመኞቻቸው እነደሆኑ ከወዲሁ ለይቶ ማወቅ ይገባዋል፡፡ ይህንን ማድረጉ ለሁለት ነገሮች ይጠቅመዋል፡፡ አንደኛ፣ እባብ ተይዞ በትር ስለማይፈለግ ነው፡፡ በእርግጥም፣ ለፍርድ መቅረብ ያለባቸውን ከሌለባቸው ለመለየት ስለሚበጅ ነው፡፡ ሁለተኛ፣ “መረጃ አይናቅም፣ አይደነቅም!” ከሚለው መርሆም በመነሳት ነው፡፡ ለብሔራዊ እንቢተኝነት የሚዘጋጁትን ወጣቶችና ደጋፊዎቻቸውን እነማን እያሳደዷቸው እንደሆኑና እነማንስ ያላግባብ በህዝብና በሀገር ክብር ላይ እየቆመሩ እንዳሉ ማወቁ በራሱ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ (ክፍል-2ን ሳምንት ይጠብቁ፡፡)

No comments:

Post a Comment