Saturday, February 22, 2014

ዶ/ር ነጋሶ አንድነትና መድረክ፡ – ታምራት ታረቀኝ

ዶ/ር ነጋሶ አንድነትና መድረክ፡ – ታምራት ታረቀኝ

negasso«ተስማምተን አብረን ያጸደቅነውን ፕሮግራም ከመካዳቸውም በተጨማሪ ወደ መድረክ ሄዶ ውይይት ተደርጎበት ውሳኔ ላይ ካልተደረሰ ወደ ጉባዔው ተመልሶ ለውይይት መቅረብ ሲገባው ወደ መገናኛ ብዙኃን እንዴት ይላካል በሚለውና በሌሎችም ተጨማሪ ምክንያት ልለቅ ችያለሁ፡፡»
ይህን የተናገሩት በቅርቡ ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበርነት የለቀቁትና በተኩዋቸው ኢ/ር ግዛቸው መልሰው የተተኩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ናቸው፡፡ ጥር 18/2006 ዓም ለንባብ ከበቃው ሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፡፡ በቃለ ምልልሱ የተነሱ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበርነት ቆይታቸውን እንዴትነት የሚያመለክቱ ሌሎች ጉዳዮችን ትተን ይህን ንግግራቸውን ብቻ በአትኩሮ ብናየው ብዙ መልእክት ያስተላልፋል፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ወደ አንድነት በገቡበት ወቅት ፓርቲው በከፍተኛ ነውጥ ወስጥ ነበር፡፡ የጋራ ወሳኔ ተፈጻሚ አለመሆን፣ በጋራ ስምምነት የጸደቀ ፕሮግራም አለመከበር፣ግለሰቦች ከህግ በላይ በመሆን እንዳሻቸው የሚሰሩ መሆን፣አንድነት መድረክ የተቀላቀለበት ሂደት በምክክርና በውሳኔ ሳይሆን በጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት ህጋዊ መሰመር ባልተከተለ አሰራር መሆኑና ይህም አባላትን እስከማባረር ለደረስ ልዩነት ምክንያት እንደሆነ ወዘተ በተለያየ መንገድ ለዶ/ር ነጋሶ ተነግሮአቸው ነበር፡፡ ርሳቸው ግን ለሥልጣኑ ያግባቡዋቸው ሰዎች የነገሩዋቸውን ብቻ በማመን አንድነት መግባትን መረጡ፡፡ እነሆ ያኔ ተነግሮአቸው አልሰማ ያሉትን በአምስት ዓመት የም/ሊቀመንበርነትና የሊቀመንበርነት ቆይታቸው በሚገባ የተረዱ ይመስላል፡፡ ከፓርቲው ለመልቀቅ ምክንያት ሆኗቸዋለና፡፡
በጋዜጠኛው ጥያቄዎች መነሻነት ከወጣትነት የፖለቲካ አጀማመራቸው ከአንድነት ሊቀመንበርነት እስከ ለቀቁበት ግዜ ያለውን የፖለቲካ ተሳትፎአቸውን በወፍ በረር ለማየት ችለናል፡፡ ጋዜጠኛው ሌሎች ጥያቄዎችን ማንሳት ቢችል ብዙ ነገር ማንበብ/ማወቅ በቻልን ነበር፡፡ በተለይ ብዙ ተቃውሞ አሰነስቶ የነበረውን አንድነት መድረክ የገባበትን ርሳቸውም አንድነት የገቡበትን በተመለከተ በወቅቱ የተነገራቸውን በቆይታቸው ካረጋገጡት ጋር እያገናዘቡ በነገሩን ነበር፡፡ ይህም ሆኖ የሪፖተር ደምበኞች ከቃለ ምልልሱ የሚገነዘቡት የአንድ ወገን እንዳይሆንባቸውና ለማመዛዘን እንዲረዳቸው ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ በአካል ከነበርኩበት ሂደት ትንሽ ማስረጃ ላካፍል፡፡
ዶ/ር ነጋሶና መድረክ፣
አሁንስ መንግሥቱ ኃለማሪያምን መሰልከኝ እስከሚል በዘለቀ ልዩነት ከቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር ተጣልተው፣ በዚህም ከኦህዴድም ከኢህአዴግም ተለያይተው፣ በፕሬዝዳንትነት ከገቡበት ኢዩበልዩ ቤተ መንግሥት የወጡት ዶ/ር ነጋሶ በምርጫ 97 ወደ ትውልድ ቀያቸው አምርተው በግል በመወዳደር ተመርጠው ብቸኛው የግል ተመራጭ የፓርላማ አባል ለመሆን በቁ፡፡ አቶ ስዬ አብርሀ ደግሞ በሙስና ተከሰው ኑሮአቸው በቃሊቲ ከሆነ በኋላ ለርሳቸውም ግልጽ ባልሆነ መንገድ(ራሳቸው የተናገሩት ነው) ከቅንጅት አመራሮች አስቀድሞ ከእስር ተለቀቁ፡፡ ሁለቱም ተዋቂ ግለሰብ የሚል ቅጽል ተሰጥቷቸው እያንዳንዳቸውም ከአንድ ፓርቲ እኩል ታይተው የምክክር መድረክ በስድስት ፓርቲዎችና በሁለት ተዋቂ ግለሰቦች መመስረቱ ተገለጸ፡፡
አንድነት በዚህ ወቅት ገና በምስረታ ላይ የነበረና የህጋዊነት ማረጋገጫ የምሥክር ወረቀት ያላገኘ ስለነበረ ምክክር መድረኩ ራሱን ይፋ ለማድረግ ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ እንዲገኝ የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ በፓርቲ ደረጃ መገኘት የማያስችለው በመሆኑ የውጪ ጉዳይ ኃላፊው በግል እንዲገኙ ተደረገ፡፡
ከዚህ በኋላ አንድነት የመድረክ አባል እንዲሆን ለቀረበው ጥያቄ ለምን ዓላማ ፣በምን አግባብ፣በምን ደረጃ ፣እስከምን ድረስ ወዘተ የሚለው መጠናት አለበት እንዲሁም የመድረኩ ዓላማ፣ የአባላቱ ማንነት፣ የጎሳና ሀገራዊ ፓርቲዎች በአንድ ላይ አባል የሆኑበት ሁኔታ ወዘተ መታወቅ አለበት ስለሆነም ሰነዶቻቸውን አግኝተን እንያቸው ከአመራሮቹ ማብራሪያ ይጠየቅ በማለት የአንድነት ሥራ አስፈጻሚ የተስማማው ያለ ልዩነት ነበር፡፡
በዚህ ወቅት የአንድነት ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለእስር ተዳረገች፡፡ ጥቂት የአመራር አባላት ባልታወቀ ምክንያትና ፍጥነት አቋማቸውን ከመቅጽበት ለውጠውና በግል ያነሱዋቸውን ጥያቄዎች ሳይቀር እንዳልተነሱ ቆጥረው ምንም ምንም ነገር ሳያስፈልግ አንድነት መድረክ መግባት አለበት ብለው ተነሱ፡፡ ምክር ቤቱ ተነጋግራችሁ የውሳኔ ሀሳብ አምጡልኝ ብሎ ቢወስንም ምክር ቤቱን ከምንም ባለመቁጠር የካቲት 12/2001 ዓም ከመድረክ አመራሮች ጋር ሆነው አንድነት የመድረክን መስፈርቶች አሟልቶ በመገኘቱ ተቀላቀለ የሚል መግለጫ ሰጡ፡፡
ሂደቱን የተቃወሙ ሁለት የሥራ አስፈጻሚ አባላት (አንዱ እኔ ነኝ) ታገዱ፣ የሊቀመንበሯ መታሰርን ጨምሮ በብዙ ችግሮች በተወጠረው አንድነት የመድረክ ጉዳይ በእሳት ላይ ቤኒዚን ሆነ፡፡ ችግሮች ተባባሱ፣ አመራሩ ውይይት አሻፈረኝ አለ፣ ልዩነቱ እየሰፋ ነገሩ እየተካረረ ሄዶ ደም ከማፍሰስ እስከ ፍርድ ቤት ክስ ተደረሰ፡፡
የአንድነት መድረክ አለመጣጣም ከመሰረቱ በጥናት ሳይሆን በስሜት በእምነት ሳይሆን በግፊት በጥቂት ሰዎች ፍላጎት የተፈጸመና ስድስት ዓመት ሙሉ ውኃና ዘይት እንደሆነ ያለ እንጂ ከግዜ በኋላ የመጣ ወይንም የተቀየረ አይደለም፡፡
የአንድነት አመራሮች ሁለቱን ተዋቂ ግለሰቦች (ዶ/ር ነጋሶንና አቶ ስየን) ለም/ሊቀመናብርትነት የፈለጓቸው ውስጣዊ ትኩሳቱን ለማብረድና የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየስ ሲሆን የተዋቂ ግለሰቦቹ ወደ አንድነት መግባትን የመረጡበት ምክንያት ግን ግልጽ አይደለም፡፡ ዶ/ር ነጋሶ መድረክ ወደ ጥምረት ሲሄድ እኔ የአንድ ፓርቲ አባል መሆን ስለነበረብኝ አንድነትን መረጥሁ ያሉት ብቸኛ ምክንያት ተብሎ ሊያሳምን አይችልም፡፡ አስገራሚው ነገር ግን የአንድነት መድረክን መቀላቀል ከሚገባው በላይ ሲደግፉና ሲያሞግሱ በዛው አንጻር በርጋታ ተጠንቶ ይፈጸም በማለት የጥድፊያውን መቀላቀል ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል እንዳይሆን በማለት የተቃወሙ አባልትን ሲያወግዙ ሲፈርጁና ሲዘለፉ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ዋናኛ ተቀዋሚ ሆነው መታየታቸው፣ እንዲሁም ለበርካታ አባላት መባረርና ጥሎ መውጣት ምክንያት የነበረው የአንድነት መድረክ ጉዳይ ዛሬ ከአምስት ዓመት በኋላ ለዶ/ር ነጋሶም ከፓርቲ መልቀቅ ምክንያት መሆኑ ነው፡፡
ከተዋቂ ግለሰብነት ወደ አንድነት ም/ል ሊቀመንበርነት፡
ዶ/ር ነጋሶ ወደ አንድነት ሊገቡ ነው የሚል ወሬ እንደተሰማ አንድነት የነበረበትን የተበለሻሸ ሁኔታ በመግለጽ የአንድነት አመራር ከሚሆኑ ተዋቂ ግለሰብነታቸውንና የቀድሞ ፕሬዝዳንትነታቸውን ተጠቅመው አስታራቂና አቀራራቢ ሽማግሌ ቢሆኑ እንደሚሻል በተለያየ መንገድና ዘዴ ተነገሮአቸው ነበር፡፡
አንድነት መግባታቸው የግድና የማይተውት ከሆነ ደግሞ ለውይይት አሻፈረኝ ያለውን አመራር በማግባባት አንድነት ችግሮቹን በውይይት እንዲፈታ እንዲያግዙ በአካል ተጠይቀዋል፣ ደብዳቤ ተጽፎላቸዋል፡ በጋዜጣ አስተያየት ቀርቦላቸዋል፡፡
ነጋሶ ግን አንዱንም ሊቀበሉ ባለመፍቀድ አንድነት ሁለቱን ተዋቂ ግለሰቦች ወደ አመራርነት ለማምጣት ሀሙስ ሕዳር 17/2002 ዓም በግዮን ሆቴል ባዘጋጀው የምልጃ ግብዣ ላይ «ብሔረተኞች የዕንቁላል ሽፋኗን ገና ሰብራ እንዳልወጣች ጫጩት ናቸው፡፡ጫጩቷ በዕንቁላሉ ሽፋን ተሸፍና እስካለች ውጪ ያለውን ለማየት አትችልም፡፡ እኔ ግን ያንን ዕንቁላል ሰብሬ ሌላ አቅጣጫ ማየት የጀመርኩት ገና በ1983 ወደ ሀገር ለመመለስ በወሰንኩበት ግዜ ነው» በማለት መለወጣቸውን ተናግረው የአንድነትን ግብዣ መቀበላቸውን አረጋገጡ፡፡ አቶ ስዬ ግን እኔ አባል የምሆነው በፕሮግራሙ ውስጥ እንዲለወጡ ያልኩዋቸው አንቀጾች ከተለወጡ ብቻ ነው አሉ፡፡
ይህን ብለውም ምክትል ሊቀመንበርና የውጪ ጉዳይ ኃላፊ ተብለው በምርጫ የሚሆነውን በሹመት በጉባኤ የሚፈጸመውን በጓዳ ስምምነት ሲጨብጡ አሰራሩ ደንብን ያልተከተለ ሕገ ወጥ እንደሆነ በመግለጽ ይህም ሆኖ ስልጣናቸውን ተጠቅመው የአንድነት ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ አስተዋጽኦ አንዲያደርጉ በተለያየየ መንገድ ተጠየቁ፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ግን የሚያዳምጡትም የሚያምኑትም ለሊቀመንበርነት ያበቁዋቸውን ሰዎች ሆነና አብረው ተደርበው የውይይት ጥያቄ የሚያነሱትን ሕገ ወጥ ማለት ጀመሩ፡፡
ቼንጂ ይባል ከነበረው መጽሄት ጋር መጋቢት 2002 ዓ.ም ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከቀረቡላቸው ብዙ ሞጋች ጥያቄዎች መካከል እርስዎና አቶ ስዬ ወደ አንድነት ስትመጡ በፓርቲው ውስጥ ያለውን ችግር በሰላም ትፈቱታላችሁ የሚል ተስፋ ነበር፣ምን እያደረጋችሁ ነው ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ «እኔ በድርጅት አሰራር የማምን ሰው ነኝ፡፡ ህገ ደንብ አለ፡፡በዚያ መሰረት መስራት ነው፡፡ ችግር ፈጥረሀል ተብሎ እምቢ ከተባልኩ ወደ ፍ/ቤት ነው መሄድ ያለብኝ፡፡ አለበለዚያ ሌላ ፓርቲ ማቋም ወይም ወደ ሌላ ድርጅት መግባትም አለ፡፡ ስለዚህ ድርጅቱ የድርጅቱ ህጋዊ ውሳኔ ስላለ እነዚህ ከድርጅቱ የተወገዱ ሰዎች ራሳቸውን አይተው የድርጅቱን አሰራር ተቀብለውና ታርመው ይቅርታ ጠይቀው ቢመለሱ ይሻላል….»አሉ፡፡
ጥቅምት 11/2003 ዓም ከፍትህ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ደግሞ «ርስዎ ወደ አንድነት ከገቡ በኋላ ችግሩን በሽምግልና ለመፍታት ለምን ሙከራ አላዳረጉም »ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ «በፓርቲው የተፈጠረ ችግር የህገ ደንብን አለማክበር ነው፡፡ የወጡት ሰዎች ደንብ ለማክበር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ የእነርሱ ችግር ህገ ደንብን መጣሳቸው ነው፡፡ይህ ደግሞ የሚፈታው ህግ በማክበር እንጂ በሽምግልና አይደለም» አሉ፡፡ዶ/ር ነጋሶ ያው ጥያቄ ዛሬ ቢነሳላቸው ምን ይመልሱ ይሆን? ሁለቱንም ህትመቶች ዛሬ ከፓርቲ ነጻ በሆኑበት መንፈስ እንዲያነቡዋቸው እጋብዛለሁ፡፡
« የሚገርመው ነገር ብሔራዊ ምር ቤቱ አሻሻልኩ ያለው ሰነድ ለሥራ ስፈጻሚው (ለእኔ) ቀድሞ መድረስ ሲገባው በመገናኛ ብዙኃን ከተገለጸ በኋላ በሳምንቱ ነው የደረሰኝ፡፡
በዚህ ግዜ አካሄዱ ትክክል አለመሆኑን በመግለጽ ደብዳቤ ጻፍኩኝ፣ምልሽ ሊሰጡኝ ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም» የሚለው የዶ/ር ነጋሶ አነጋገር ትንሽ የሚመስል የትልቅ ነገር ምልክት ነው፡፡ የዶ/ር ነጋሶ የሊቀመንበርነት ሥልጣን እንዴትነት ላይም ጥያቄ የሚያሰነሳ ነው፡፡ ዶ/ር አልገለጹትም እንጂ ብዙ ነገሮችን ርሳቸው ይሰሙ የነበረው ካለፉ ወይንም ከተፈጸሙ በኋላ እንደነበር ራሳቸውን ከህግ በላይ በማድረግና ሊቀመንበሩን ከምንም ባለመቁጠር ያሻቸውን በሚሰሩ ሰዎች አድራጎት ይበሳጩ የነበሩ ሰዎች በወቅቱ ይናገሩት የነበረ ነው፡፡ ይህን እንደሰማሁ በኢሚይል አድራሻቸው ደብዳቤ ጽፌላቸው ነበር፡፡ ዶ/ር ነጋሶ በዚህ ሁኔታ ሶስቱን ዓመት እንዴት ችለው ጨረሱት? መርህ ይከበር ዝም አንልም ብለን የታገልነው እንዲህ አይነቱን እርሳቸው ያኔ ሕጋዊ ብለው የተከራከሩለትና ዛሬ ያወገዙትን ከህግ በላይ የመሆን አድራጎት በመቃወም ነበር፡፡
«አንድ የገረመኝና ያስደነገጠኝን ነገር ልንገርህ፣ኢ/ር አግዛቸው ሽፈራው ለተወሰነ ግዜ ጠፍቶ ነበር፡፡ አንድነት ግምገማውን ባደረገበት ቀን ግን ተገኝቶ ነበር፣አንድነትን ወደ መድረክ ያስገባሁት እኔ ነኝ አሁን ደግሞ የመጣሁት ከመድረኩ ላስወጣው ነው ….»ብሎ ተናገረ፡ ይላሉ ዶ/ር ነጋሶ፡፡
1. ጠፍቶ የከረመ ሰው ባሻው ሰዐት ዘው ብሎ መጥቶ ግምገማ የሚቀመጥበት ምን አይነት ድርጅታዊ አሰራር ነው? ሊቀመንበሩስ ይህን የመከላከል ኃላፊነት የለበትም? ይህስ በፓርቲው ውስጥ ሥርዓት ያለመኖሩን አያሳይም?
2. ያስገባሁት እኔ ነኝ ላወጣው ነው የመጣሁት ማለትስ አንድነት የግል ንብረት ነው ማለት ነው? ይህንንስ ሊቀመንበሩም ሆኑ ሌሎች የአመራር አባላት እንዴት ተቀበሉት? ኢ/ር ግዛቸው መልሰው ሊቀመንበር እንደሚሆኑ አስቀድመው አረጋግጠው ነበር ማለት ነው?
3. እንዲህ አይነት አስተሳሰብ ያላቸውና ከሊቀመንበርነት ከወረዱ በኋላ የጠፉ ሰው ተመልሰው መጥተው ሊቀመንበርነቱን መያዛቸውን ዶ/ር እንዴት ይመለከቱታል፡፡ለአንድነት እድገት ወይንስ ውድቀት?
ለነገሩ ኢ/ር ግዛቸው አንድነትን መድረክ ያስገባሁት እኔ ነኝ አሉ እንጂ ለመደገፍም ለመቃወምም መቸገራቸውን ነው በቅርብ የነበርን ሰዎች የምናውቀው፡፡ ለዚህ ደግሞ አንድነት ከመድረክ ተቀላቀለ የሚለው የየካቲት 12/2001 መግለጫ ላይ አለመገኘታቸው በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የነበሩትን ዶ/ር ሽመልስን ከመግለጫው እለት አንድ ቀን አስቀድሞ የተቃውሞ ደብዳቤ ጻፍና አምጣልኝ እኔ ለሥራ አስፈጻሚው አቅርቤ አስወስናለሁ ብለው ደብዳቤው ሲደርሳቸው የፈጸሙት ክህደትም ሌላው በማስረጃነት የሚቀርብ ነው፡፡ ሌላም ሌላም መጥቀስ ይቻላል የማስረጃ ብዛቱ ሳይሆን እውነትነቱ ነው እንጂ ወሳኙ፡፡
ዶ/ር ነጋሶ በሪፖርትር ጋዜጣ አማካኝነት በጨረፍታ ከነገሩን የምንረዳው የሊቀመንበርነቱን ስሙን እንጂ ሙሉ ሥልጣኑን እንዳልያዙ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ደብዳቤ ጽፈው እንዴት ምልሽ ያጣሉ፡፡ደብዳቤ የጻፉትስ ጠርተው ለማነጋገር የሚያበቃ ሥልጣን አጥተው ይሆን!
ውሻን በምን ይፈሩታል በአጥንት ይላሉ አበው ነገርን በምሳሌ ሲያስረዱ፡፡ዶ/ር ነጋሶ ወደ አንድነት ከመግባታቸው በፊት የአንድነት አመራር በአባላቱ ላይ ከፈጸመው ቢማሩ የተነገራቸውን ቢሰሙ ኖሮ ዛሬ ፓርቲውም ፖለቲካውም በቃኝ እንዲሉ ያስገደዳቸው ሁኔታ ውስጥ ባልገቡ ነበር፡፡ ግን ያለፈው ዳግም ላይመለስ ነጉዷል፡፡ለወደፊቱ አባሉ በጽናት ደጋፊው በእምነት ከፓርተው ጋር እንዲጓዝ አመራሩንም ወገቡን ጠበቅ አድርጎ እንዲሞግትና እንዲያስተካክል ዶ/ር ነጋሶ በሊቀመንበርነት ቆይታቸው ያዩ የታዘቡትን በዝርዝርና በግልጽ ይናገሩ፡፡ንስሀም ይሆናቸዋል፡፡ (የካቲት 5/2006 ዓም ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የወጣ)

No comments:

Post a Comment