የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ዝብርቅርቅና ጐደሎዎቻችን
ፍቅር ለይኩን
ባለፈው ሳምንት ከተካሄደው ከአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ጋር ተያይዞ በስብሰባው ላይ በተሳታፊነትና በታዛቢነት ለመገኘት ከተለያዩ አገሮች የመጡ እንግዶች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣
የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮችና ተሳታፊዎች የመግቢያ ካርድ ለማግኘት በግዮን ሆቴል የነበረውን ትርምስ፣ ግርግርና ግራ የሚያጋባ ዝብርቅርቅ አሠራር በተመለከተ የታዘብኩትን ጥቂት ነገሮችን በማንሳት ትዝብቴን አንድ ብዬ ልጀምር፡፡ መንግሥት ከደኅንነትና ከፀጥታ አኳያ እንዲህ ዓይነቱን ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረጉ መልካም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ቁጥጥሩና ማጣራቱ እንዳለ ሆኖ እንግዶች የሠለጠነ፣ ሙያዊ ብቃትን የተላበሰና የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚያገኙበት አሠራር ግን የግድ ሊኖር ይገባል፡፡
ሕጋዊ የጉዞ ሰነድና የግብዣ ወረቀት የያዙ እንግዶችን የግድ ስማችሁ በዚህ በተላከልን ስም ዝርዝር ውስጥ የለም በሚል አሳማኝ ያልሆነ ምክንያት በእንግዶች ላይ እንግልት እንዲደርስባቸው ማድረግ የሚገባ አይመስለኝም፡፡ ያውም የእነዚህን እንግዶች አቤቱታና ደብዳቤ በቅጡ አንብቦና ተረድቶ ምላሽ መስጠት የሚችል ብቁ ባለሙያ እጥረት ባለበት አዳራሽ፡፡
እነዚህ እንግዶች ከድርጅታቸውና ከተወከሉበት መሥሪያ ቤት ሕጋዊ ደብዳቤ ይዘው እያለ ገና ለገና ስማችሁ የለም በሚል ምክንያት መስተንግዶ ሊነፈጋቸው አይገባም ባይ ነኝ፡፡ መቼም ስም ዝርዝሩን የሚጽፈው ሰው ነው፡፡ ከዝርዝሩ ብዛት የተነሳ አንዳንዴ ስም ሊዘለል ይችላል፡፡ እንግዶቹ ሕጋዊ ማኅተም ያለው የጥሪ ደብዳቤ እስካቀረቡ ድረስ የሚመለከተው ክፍል በሚገባ አነጋግሮ ከሚመለከተው አካል ጋር በመወያየት ሊያስተናግዳቸው በተገባው ነበር፡፡
የሚገርመው ለዚህ ሥራ የተመደቡት ሰዎች ከሚመለከተው የመንግሥት መሥሪያ ቤት የተላከውን የተሳታፊዎችን የስም ዝርዝር እንኳን በትክክል አንብበው ለመጥራት ሲቸገሩ ነው ያስተዋልኩት፡፡ ደግነቱ ይህን ችግር የተገነዘቡት የመግቢያውን ካርድ ለመውሰድ የመጡ የውጭ አገር እንግዶች በራሳቸው ተነሳሽነት እገዛ አድርገዋል፡፡ በይበልጥ ደግሞ ከዚያ ወከባ ከበዛበትና አሠራሩ እንዴት እንደሆነ ፈጽሞ ግራ ካጋባቸው የግዮን ሆቴል አዳራሽ ቶሎ ለመውጣት በመፈለግ የስም ዝርዝሩን ከሚጠራው ሰው ተቀብለው እንግዶችን በቅልጥፍናና በትክክል ስማቸውን በመጥራት ቢያንስ ለሥራው መቀላጠፍ የበኩላቸውን አድርገዋል፡፡ ለዚህ ትብብራቸው በአዳራሹ የነበሩ ለዚህ ሥራ የተመደቡ የፀጥታ ሠራተኞች ምሥጋና አላቀረቡላቸውም ነበር፡፡
አገራችን በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ስብሰባዎችን እያስተናገደች ነው፡፡ ስለሆነም በእንዲህ ዓይነት ስብሰባዎች ወቅት መንግሥት ጥሩ የእንግሊዝኛና ቢቻልም ተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችን በሚገባ መረዳት የሚችሉ፣ ፈገግታና ጥሩ አቀራረብ ያላቸው ብቁና ቀልጣፋ ባለሙያዎችን መመደብ ያስፈልገዋል፡፡ መንግሥት በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ ሳይሆን በሙያና በችሎታም ጭምር ማመን መቻል አለበት፡፡
አንድ ዓለም አቀፍ የሆነ ስብሰባ በምታስተናግድ የብዙ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መቀመጫ በሆነች አገር እንዲህ ዓይነቱ ዝብርቅርቅ ያለ መስተንግዶና እሰጥ አገባ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በእጅጉ እንዲታዘቡን የሚያደርግ ነው፡፡ ባለ ብዙ ታሪክ፣ ባለ ብዙ ባህል፣ የሰው ልጆች መገኛና እንግዳ ተቀባይ ሕዝቦች ነን እያልን ነጋ ጠባ እየወተወትን፣ በእንዲህ ያለ መስተንግዶ ከሆነ እንግዶችን የምንቀበለው በእውነቱ አሳዛኝ ነው፡፡
የኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ፋውንዴሽንና የናይጄሪያውያኑ ኅብረት
ባለፈው ሳምንት የቀድሞው የናይጄሪያ መሪ በነበሩት ኦሎሴጎን ኦባሳንጆ ስም የተቋቋመው ‹‹የኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ፋውንዴሽን›› ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ጋር በመተባበር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ አፍሪካውያን ወጣቶች በአፍሪካ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያ ጉዳዮች ላይና እንዲሁም በመፃኢቱና ተስፈኛዋ አፍሪካ ዕጣ ፈንታ ላይ የአኅጉሪቱ ወጣቶች ተሳትፎና ኃላፊነት ምን መሆን አለበት በሚል አንድ ስብሰባ አድርጐ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይም ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የመጡ በርካታ ወጣቶችና ምሁራን ተገኝተው ነበር፡፡
በዚህ ራሳቸው ኦሊሴጎን ኦባሳንጆና የቀድሞው የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ጆአኪም ቺሳኖ በክብር በተገኙበት መድረክ ላይ በአፍሪካ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያ ቀውሶች ላይ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የአፍሪካ ልማት ባንክ ኃላፊዎች፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ አፍሪካውያን ፖለቲከኞችና ወጣት ምሁራን በተሳተፉበት የተለያዩ ጥናታዊ ወረቀቶች ቀርበው ሰፋ ያለ ውይይትና ክርክር ተካሂዶባቸው ነበር፡፡ በቀረቡት ጥናታዊ ወረቀቶች ላይም ተሳታፊዎች በቡድን በቡድን ተከፋፍለው ውይይትና ሞቅ ያለ ክርክር ከተደረገ በኋላ፣ እያንዳንዱ ቡድንም በአፍሪካ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ዙሪያ መፍትሔ ይሆናሉ ያሏቸውን ሐሳቦች አቅርበው ነበር፡፡
እነዚህ ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን ይበጃሉ የተባሉ የመፍትሔ ሐሳቦችም በዚሁ ስብሰባ ላይ በተወከሉ ወጣቶች በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ እንዲቀርቡ ተደርጐ ነበር፡፡ እነዚህ ቡድኖች ባቀረቧቸው የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ የቀድሞው የናይጄሪያው መሪ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ አንድ ልብ የሚነካ ማስጠንቀቂያ ጭምር የሚመስል መልእክት አስተላልፈው ነበር፡፡ ‹‹በበርካታ መድረኮች በአፍሪካ ጉዳዮች ዙሪያ ብዙ ተነጋግረናል፣ ብዙም ተብሏል፡፡ ከፕሬዚዳትነቴ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ የአገሬንም ሆነ የአኅጉሬ አፍሪካን ችግሮች ለመፍታት የአቅሜን ያህል እየለፋሁ ነው፣ ውጤቱ ግን የጠበቅነውን ያህል ሊሆን አልቻለም፡፡ ዛሬም በምድራችን አፍሪካ ሙስናው፣ የእርስ በርስ ግጭቱ፣ ጦርነቱ፣ ረሃቡ፣ ስደቱና መፈናቀሉ እንደቀጠለ ነው፡፡ እናም እባካችሁ አፍሪካውያን ወጣቶች፣ ምሁራንና ፖለቲከኞች ለኅብረቱና ለመሪዎቹ የምታቀርቧቸው የመፍትሔ ሐሳቦች ቀላል፣ ተግባራዊ፣ ማንኛውም አፍሪካዊ ሊረዳው የሚችልና የሚያግባባን ይሁን፡፡ ማንም የማያነባቸውንና አቧራ እየጠገቡ መደርደሪያ የሚያሞቁ በርካታ ሺሕ ዶላሮች የተከሰከሰባቸው ዶሴዎችን ወይም የጥናት ወረቀቶችን መላክ ማቆም አለብን፡፡ አፍሪካ የተግባር ሰው ነው የሚያስፈልጋት፤›› ነበር መልዕክታቸው፡፡
የኦባሳንጆ ፋውንዴሽ የአፍሪካውያን ወጣቶች አኅጉራቸው ላሉባት ችግሮች እንዴት ዓይነት መፍትሔ ማምጣት ይችላሉ በሚለው በጠራው ስብሰባ ላይ ለተሳተፉ እንግዶች የምሥጋና ሰርተፊኬት የመስጠት ፕሮግራምና የኮክቴል ግብዣ ያደረጉት ኦባሳንጆ፣ ቀለል ያሉና ብዙም የማይከብዱ፣ ከማንኛውም ዓይነት ሰው ጋር ለመግባባት የሚያስችል ባህርይ ያላቸው፣ ለፕሮቶኮልና ለተዛማጅ ጉዳዮች ብዙም የማይጨነቁ ሰው ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡
ኦባሳንጆ በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ በሊቀመንበርነት በመሩት የውይይት መድረክ ላይም ማንኛውም ተናጋሪ ከሦስት ደቂቃ ያልበለጠ ንግግር እንዳያቀርብ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈው ነበር፡፡ ይህን የሰዓት እገዳቸውን የተላለፈውን መሪ ከኪሳቸው ነጭ መሀረባቸውን በማውጣትና በማወዛወዝ ‹‹እኔ የሰላም ሰው ነኝ፣ ትዕዛዝ ይከበር›› የሚል ምልክት በመስጠት መሪዎቹንና ተሳታፊዎችን ፈገግ አሰኝተው ነበር፡፡
በተጨማሪም ሌላው የታዘብኩት ነገር ቢኖር የአገራቸው የናይጄሪያ ወጣቶችና እንግዶች ለቀድሞ መሪያቸው ያላቸው ቀረቤታና በአፍሪካ ጉዳይ ላይም አገራቸው ናይጄሪያም ሆነች የቀድሞ መሪያቸው ተፅዕኖ እንዲኖራቸውና ድምፃቸው ጎልቶ እንዲሰማ በተቀናጀ ሁኔታ በአንድነት ሲሠሩ ትብብራቸውና ኅብረታቸው ጉድ አሰኝቶኛል፡፡ በእርግጥም ናይጄሪያዎቹ ያስደንቃሉ፣ ያስቀናሉም፡፡
በነገራችን ላይ በዚህ በኦባሳንጆ ፋውንዴሽን የስብሰባ መድረክ ላይ የተገኙትን አቅም የሌላቸውን በርካታ ወጣት አፍሪካውያንን ፋውንዴሽኑ የአውሮፕላን ትኬት፣ የሆቴልና ሌሎች ወጪዎችን በመሸፈን፣ በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይም ድምፃቸው እንዲሰማ ያደርጋል፡፡ ፕሬዚዳንቱና ይህን ስብሰባ እንድሳተፍ የጋበዘኝ በአገራቸው ልጅ የተቋቋመውና መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው አፍሪካ 2.0 በቅንጅት የፈጠሩት መድረክ የእርሳቸውንም ሆነ የናይጄሪያውያኑን አቅማቸውን፣ ትብብራቸውንና ኅብረታቸውን በእጅጉ እንዳደንቅ አድርጎኛል፡፡
ራሳችንን የታዘብኩበት የኦባሳንጆ ፋውንዴሽንና የአፍሪካ ኅብረት መድረክ
ይኼው እኛ የዛሬ አንድ መቶ ዓመት የተለዩንን መሪዎቻችንን ሳይቀር መልካሙ ሥራዎቻቸውን አጨልመንና ጥላሸት ቀብተን፣ ታሪክን እንዳሻንና እንደሚመቸን እየመነዘርንና እየሸቃቀጥን ይህ ጎሳና ነገድ የዚህ ንጉሥና ገዢ ዘርና ሐሳብ ደጋፊ ነው፣ ስለዚህ አባቶቹ ወይም አያቶቹ ላደረሱት በደልና ግፍ ዕዳውን ሊከፍል ይገባል በሚል የጦር አውርድ ዘመቻ በከፈትንበት ወቅት፣ እንዲህ መሪያቸውን የሚያከብሩ ብቻ ሳይሆን ዓላማቸውን ለማሳካት ናይጄሪያውያኑ የሆዳቸውን በሆዳቸው አድርገው እንዲህ ሲተባበሩና ሲረባረቡ ማየቴ እፍረት እንዲሰማኝ አድርጎኛል፡፡
ኅብረት መፍጠርና መስማማት ተስኖን ነው እንጂ በአፍሪካም ሆነ በዓለም መድረክ የአገራችንም ሆነ የመሪዎቿን መልካም ሥራዎቻቸውን በማጉላትና ከፍ በማድረግ፣ እኛም ከናይጄሪያዎቹም ሆነ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች በበለጠ ከአፍሪካውያን የነፃነት ተጋድሎ ጋር አያይዘን የአገራችንን ክብርና ጥቅም ከፍ የምናደርግባቸው በርካታ ታሪክና ቅርሶች አሉን፡፡ ግን የሚገባውን ያህል እየተጠቀምንባቸው አይደለም፡፡
ለምሳሌ በዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ኅብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ በቅርቡ በሞት በተለዩን አፍሪካዊው የፀረ አፓርታድ ታጋይ፣ የነፃነት አርበኛና የይቅርታ ጀግና በሆኑት በሮሂላላ ኔልሰን ማንዴላ ስም እንዲሰየም ተደርጓል፡፡ በእርግጥ ይህ ለማዲባ ቢያንሳቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይደለም፡፡
እዚህ ላይ ግን አንድ ጥያቄ ማንሳት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ለምን ኅብረቱም ሆነ የአፍሪካ አገሮች ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነፃነት ቀንዲል የለኮሰውን የዓድዋን አንፀባራቂ ድል የሚዘክር አንድ መታሰቢያ በኅብረቱ አዳራሽ እንዲኖር አላደረጉም? እኛ ኢትዮጵያውያንም ሆን መንግሥት ይህ እንዲሆን ለኅብረቱ ሐሳብ አላቀረብንም፡፡ ከእዚህ የበለጠ ምን ጉድለት አለ?
ለነገሩ በትናንትና ታሪካችን ላይ አንዳች ስምምነት ከሌለንና ስለዓድዋም ሆነ አባቶቻችን በቅኝ ገዢ ተስፋፊዎች ላይ ስላስመዘገቧቸው ድሎች ሲነሱ ይህ ጎሳና ከማሰብ ይልቅ፣ እነዚህ ባንዳዎች ነበሩ፣ ዓድዋ ለነፍጠኞች የግዛት ማስፋፊያ ወረራቸው አንዱ ምዕራፍ ነው፣ የዓድዋ ድል የምትሉት ለእኛ ምናችን ነው? በሚል በጥቂት ሰዎች ምክንያት ሁሉንም በአንድነት ጨፍልቀን ለምንፈርጅ ለአብዛኞቻችን፣ ይህ የአንድነት መንፈስና ቀናነት በቀላሉ ይታሰባል፣ ዕውን ይሆናል ማለት አዳጋች ነው፡፡
እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ አፄ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱም ሆኑ በዓድዋ ጦር ግንባር ዘር፣ ሃይማኖት፣ ፆታ፣ ዕድሜ፣ ካህን፣ ሼክ ሳይባል ቀፎው እንደተነካ ንብ ሆ ብሎ የወጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ጀግንነት የአውሮፓን ወራሪና ቅኝ ገዢ መክተው በአፍሪካና በመላው ዓለም አንፀባራቂ ድል ያስመዘገቡ የቀድሞው አባቶቻችንና እናቶቻችን፣ ለዛሬው ለጥቁር ሕዝብ ነፃነት፣ ለዛሬው የአፍሪካ ኅብረት ዕውን መሆን መሠረት የጣሉ መሆናቸውን በማስታወስና በማጉላት፣ ዛሬም በአፍሪካም ሆነ በዓለም መድረክ ለክብራችንና ለጥቅማችን ለማዋል በተቻለን ነበር፡፡
ግና ያ አልሆነም ዛሬም ከአጥንት ቆጠራና ከመንደርተኝነት (ከጠባብ አስተሳሰብ) ለመውጣት የተቻለን አይመስልም፡፡ የትናንትናውን የአባቶቻችን በደል በይቅርታ ዘግተን በብሩህ ተስፋና በፍቅር እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደ ፊት ከመራመድ ይልቅ ትናንትና በልግዛህ አልገዛም፣ በገብር አልገብርም በገዢዎችና በሠራዊቶቻቸው አማካይነት በሕዝቦች ላይ የደረሰውን በደል ሽምጥጥ አድርገው በካዱና ይህን ታሪክ የማይዘነጋውን በደልና ክደት እንበቀላለን በሚሉ ሰዎቻችን መካከል ከሰሞኑ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ያስተዋልነው የጦር አውርድ እሰጥ አገባ፣ የትናንትና ታሪካችንን በተመለከተ ያለን ግንዛቤና ትርጓሜ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ያሳየ ነው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ የትናንቱን ጥፋት ለዛሬ እንደ ትምህርት በመውሰድ አገር ከመገንባት ይልቅ የበቀል ነጋሪት መጐሰም ጠንቅ የት ይደርስ ይሆን?
የታንዛኒያውያኑ ፓርላማ አባላት ቅሌት በአገራቸው ልጅ ሲተረክ
በዚሁ በኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ፋውንዴሽንና በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ከታንዛኒያ ከመጣ ወጣት ጋር በነበረን ቆይታ ያጫወተኝንና ያስገረመኝን ትዝብቴን ላካፍላችሁ፡፡ ከዚህ ወጣት ጋር በአገሩ ስለሚገኙ ፓርቲዎችና የፓርላማ አባላትን በተመለከተ አንዳንድ ነገሮችን ተጨዋውተን ነበር፡፡
ይህ እንግዳ እንደነገረኝ በታንዛኒያ የፓርላማ አባል ሆኖ መመረጥ ብዙዎች መንግሥተ ሰማያት የመግባት ያህል የሚመኙት ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የደመወዛቸውና የሚያገኙት ጥቅማ ጥቅም ጉዳይ የትየለሌ የመሆኑ ሚስጥር ነው፡፡ የታንዛኒያ ፓርላማ አባላት በሙሉ ከመንግሥት ‹‹ቪ8›› መኪና በስጦታ ይሰጣቸዋል፡፡ ልብ በሉ ይህ መኪና እስከ መጨረሻው የእነርሱ ንብረት ሆኖ የሚዘልቅ ነው፡፡ የሾፌርና የነዳጅ ወጪያቸውም በመንግሥት የሚሸፈን ነው፡፡ የስልክ ቢልም የመንግሥታቸው ዕዳ ነው፡፡
ሌላው ደግሞ በጣሙን ያስገረመኝ የታንዛኒያ የፓርላማ አባላት ከደመወዛቸው ውጪ በእያንዳንዱ የፓርላማው ስብሰባ ላይ ሲሳተፉ በቀን አበላቸው የሚያገኙት ገንዘብ በርካታ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ አስተዛዛቢው ነገር ታዲያ በዚህ ስብሰባ ላይ ጠዋት ወንበራቸው ግጥም ብሎ የሚሞላው አዳራሽ ከሰዓት በኋላ በአብዛኛው ባዶ ነው የሚሆነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የፓርላማው አባላት የዕለቱ አበላቸው ወደ ባንክ አካውንታቸው መግባቱን ካረጋገጡ ከሰዓት በኋላ ወደ ስብሰባው አዳራሽ ተመልሰው የሚመጡት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡
የሚበዙት የታንዛኒያ ፓርላማ አባላት ቀጣዩን ዳጎስ ያለ አበል የሚያፍሱበትን ስብሰባ ነው በጉጉትና በንቃት የሚጠባበቁት፡፡ ይህ በኅብረቱ ስብሰባ ላይ የተዋወቅኩት እንግዳ የታንዛንያን ፓርላማ አባላት ጉድ ሲነግረኝ ወቸው ጉድ ለካ ‹‹የባሰ አለ አገርህን አትልቀቅ!›› የተባለው ተረት እውነት ነው አሰኝቶኛል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ የይቅርታ መታሰቢያ ቀን አዋጅ
በስተመጨረሻም የዘንድሮው አፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የኅብረቱን የመሰብሰቢያ አዳራሽ በደቡብ አፍሪካዊው የነፃነት ታጋይ፣ የሰላም አርበኛና የይቅርታ ጀግና በኔልሰን ሮሂላላ ኔልሰን ማንዴላ (ማዲባ) ስም ከመሰየሙም ባሻገር ወርኃ ሰኔ የይቅርታ ወይም የዕርቅ ወር ሆኖ በምድረ አፍሪካ እንዲታሰብ ተስማምቷል፡፡
ይህ የይቅርታ አዋጅ በጥላቻ ፖለቲካ፣ በቂም በቀል፣ በወንድማማቾች የእርስ በርስ እልቂትና ፍጅት አበሳ ፍዳዋን ለሚያሳያት ለአፍሪካ፣ ለአፍሪካውያን፣ ለመሪዎችና ለፖለቲከኞች የሚገባ መልዕክት ይመስለኛል፡፡ ግና ዋናውና ትልቁ ቁም ነገር ‹‹የእርቅ ወይም የይቅርታ ቀን›› ብሎ ማወጅ ብቻ አይደለም፡፡ በተግባርም እንደ ታላቁ አፍሪካዊው ጀግና ማዲባ የይቅርታና የፍቅር ሰው ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል፡፡
‹‹ሥልጣን ወይም ሞት!›› በሚል የአምባገነኖች መፈክር ወንበራቸውን ርስት አድርገውና የሙጥኝ ብለው አገራቸውን የዕልቂትና የደም ምድር እያደረጉ ያሉ የአፍሪካ መሪዎችና ፖለቲከኞች ከራስ ወዳድነት፣ ከጥላቻ ፖለቲካ፣ ከእልህና ከቂም በቀል ወጥተው ልክ እንደ ማንዴላ ሁሉ የልባቸውን በር ለሰላማዊ ውይይትና ለዕርቅ ወለል አድርገው በመክፈት ጀግንነታቸውን በተግባር ሊያሳዩን ካልቻሉ፣ ‹‹የዕርቅ ወይም የይቅርታ ቀን›› ብሎ በማወጅ ብቻ ምንም ማምጣት አይቻልም፡፡ የቀድሞው የናይጄሪያ መሪ ኦባሳንጆ እንደተናገሩት፣ ‹‹አፍሪካ የተግባር ሰው ትፈልጋለች!›› ዕርቅንና ሰላምን በተግባር የሚያሳያት!!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው fikirbefikir@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡
No comments:
Post a Comment