- ‹‹የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው››
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት መመሥረትን ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋነኛው የሥልጣን ምንጭ ሆኗል፡፡
የኢፌዴሪ መንግሥት ከተመሠረተ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ በተካሄዱ አራት አገር አቀፍ ምርጫዎች አማካይነት አራት ዙር የፓርላማ የሥራ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ አራተኛው የፓርላማ የሥራ ዘመን ሊጠናቀቅ የአንድ ዓመት ዕድሜ ብቻ ቢቀረውም፣ ይህ አራተኛው ዙር ፓርላማ ቀልብን የሚስቡና ጥያቄዎችን የሚጭሩ የተለያዩ አስተያየቶችን አስተናግዷል፡፡
በ2002 ዓ.ም. በተደረገው አራተኛ ዙር አገር አቀፍ ምርጫ ለፓርላማው አባልነት 99.6 በመቶ የሕዝብ ድምፅ ያገኙት የገዥው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞከራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) ተወዳዳሪዎች መሆናቸው ጥያቄውን ከጫሩት ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳል፡፡
ከምክር ቤቱ 547 መቀመጫዎች ውስጥ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይና ሌላ አንድ የግል ተወካይ ብቻ የምክር ቤቱን መቀመጫ ሲያሸንፉ፣ የተቀረው የኢሕአዴግና የኢሕአዴግ አጋር ፓርቲዎች ውክልና መያዙ በበርካቶች ላይ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ፈጥሮ ነበር፡፡
ጥርስ አልባው ፓርላማ
በዚህ አራተኛ ዙር የፓርላማ ዘመን ላይ ምክር ቤቱ ከሞላ ጐደል በኢሕአዴግና አጋሮቹ ብቻ በመሞላቱ ምክንያት በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ለምክር ቤቱ የተሰጠ ስም ነው ‹‹ጥርስ አልባው ፓርላማ›› ማለት፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩት የምርጫ ዘመኖች የተቃዋሚዎች ውክልና በመኖሩ፣ እንዲሁም በሦስተኛው የምርጫ ዘመን ከመቶ በላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የምክር ቤቱን ወንበሮች በማግኘታቸውና በአምስት ዓመታት ቆይታ ጊዜም የደመቀ ክርክር በምክር ቤቱ ውስጥ አባላቱ በመፍጠራቸው ምክንያት ነው ‹‹ጥርስ አልባው ፓርላማ›› የሚለው ስያሜ ለአራተኛው የፓርላማ ዘመን ሊሰጥ የቻለው፡፡ ፓርላማው የክርክርና የሐሳብ ፍጭት የሚታይበት ሳይሆን የኢሕአዴግና የገዥው ፓርቲ ተወካዮች ተመሳሳይ ሐሳባቸውን የሚነጋገሩበት ይሆናል ከሚል ፍራቻ የመነጨ ስያሜ ነው፡፡ ይህ ፍርኃት ሙሉ በሙሉ ባይወገድም፣ የአራተኛው የምርጫ ዘመን የፓርላማ ተወካዮች በተለይ ከ2005 ዓ.ም. ወዲህ የተለየ እንቅስቃሴ በማድረግ የመራጮቻቸውንና የአጠቃላይ ኅብረተሰቡን ቀልብ ለመያዝ ችለው ነበር፡፡
ፓርላማው ጥርስ እያወጣ ነው?
የፓርላማው መቀመጫዎች 99 በመቶ ኢሕአዴግና የኢሕአዴግ አጋር ፓርቲዎች ተወካዮች መያዛቸው ብቻ ሳይሆን፣ አብዛኞቹ ተወካዮች በሥራ አስፈጻሚው መንግሥት መዋቅር ውስጥ፣ በፌዴራልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያትም በሕግ አውጪው የመንግሥት አካል ውስጥና በአስፈጻሚው አደረጃጀት ላይ መደበላለቅን ፈጥሯል የሚሉ ትችቶች ተሰንዝረው ነበር፡፡ በመሆኑም ይህ አራተኛው ዙር የፓርላማ ዘመን ሙሉ በሙሉ ፈዛዛ ሆኖ ይቀጥላል፣ ይህም በቋፍ ላይ በሚገኘው የአገሪቱ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያደርሳል የሚሉ ፍራቻዎች በተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች ላይ አሳድሯል፡፡ ፓርላማው በዚህ በተጠቀሰው የሥራ ዘመን የመጀመርያዎቹ ዓመታት ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ፍርኃቱን የማጠናከር አዝማሚያ በበርካቶች ላይ ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ በተለይ በ2005 ዓ.ም. ግን የተለየ ባህሪይ ይዞ ወይም ተላብሶ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡
ይህንን ልዩ ባህርይ ለማሳየት ከሚያስችሉ ሁነቶች መካከል በርካቶች በአብነት የሚጠቅሱት የፌዴራል ዋና ኦዲተር የመንግሥት ተቋማት የ2004 ዓ.ም. የበጀትና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ይገኝበታል፡፡ ይህ ሪፖርት ኦዲት በተደረጉ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በአግባቡ ሥራ ላይ ለመዋሉ ማረጋገጫ ስላልተገኘለት 6.5 ቢሊዮን ብር የሚተነትን ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሪፖርት ለበርካታ ዓመታት ሲቀርብ የነበረና በ2005 ዓ.ም. የቀረበውም ከዚህ ቀደም ከነበሩት የኦዲት ግኝቶች የተለየ ወይም የበለጠ የተጋነነ ብክነት ባይኖርበትም፣ የፓርላማ አባላቱ ግን ልዩ ትኩረት ሰጥተው ተከራክረውበታል፡፡
‹‹እስከ መቼ ነው ይህንን መሰሉን ሪፖርት እየሰማን እምንኖረው? ላለፉት ሦስት ዓመታት የሚቀርቡ ሪፖርቶች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ የመዘበሩ ተቋማት ኃላፊዎች በሕግ ሊጠየቁ ይገባል…›› በማለት ጠንከር ያለ አቋማቸውን ጠንከር ባለ ድምፅ ገልጸዋል፡፡
‹‹ይህ ዓይነቱን የሕዝብ ገንዘብ ብክነት ዓይቶ ማለፍ አይገባም እኛም ተጠያቂ ነን፡፡ ፓርላማው በኦዲት ሪፖርቱ የተጠቆሙ ተቋማት ኃላፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ አለበት…›› በማለት አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪና የኢንፎርሜሽንና መገናኛ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የ2005 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት፣ በተለይ በስልክ መቆራረጥ ላይ የሰጧቸው ምላሾች ለምክር ቤቱ አንዳንድ አካለት የሚዋጡ አልነበሩም፡፡
‹‹ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ለምንድነው ውጫዊ ምክንያቶችን የሚዘረዝሩት? ኢትዮ ቴሌኮም ችግር የለበትም እያሉ ነው፡፡ ለምንድነው ከምክር ቤቱ ለሚቀርቡት ጥያቄዎች በቁጣ የሚመልሱት…›› በማለት በምክር ቤቱ አባላት ባልተለመደ ሁኔታ ተገልጸው ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት የፍትሕ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ብርሃን ኃይሉ የሚኒስትር መሥሪያ ቤቱን የሥራ አፈጻጸም ለፓርላማው ለማቅረብ ተገኝተው በነበረበት ወቅት ተመሳሳይ ተግሳፅ ደርሶባቸዋል፡፡
‹‹ክቡር ሚኒስትር ለአንድ አገር ሕልውና የፍትሕ ሥርዓት ያለውን አስተዋጸኦ እንደሚረዱት አውቃለሁ፡፡ በፍትሕ ሚኒስቴር ያሉ ችግሮች በዚህ መልኩ የሚቀጥሉ ከሆነ ግን ለዚች አገር አስጊ ነው፡፡ የተቋሙ ዓቃቢያን ሕጐች ያለ በቂ ምክንያት የጀመሩትን የወንጀል ምርመራ እንደሚያቋርጡ፣ ይህም የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ እንደሆነ እናውቃለን…›› በማለት ተወቅሰው ነበር፡፡
‹‹የፍትሕ ሚኒስቴር ዓቃቢያን ሕጐች የጀመሩትን የወንጀል ምርመራ መዝገብ ያለምክንያት በመዝጋታቸው፣ ፍትሕ የተነፈጉ ዜጎች ፓርላማ ድረስ አቤተታ አቅርበው ወደ እርስዎ እንደተመራ ያውቁታል…›› የሚሉና ሌሎች የሰሉ ወቀሳዎች ተሰንዝሮባቸዋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስትሩ ይህንን ወቀሳ በጥሞና ካዳመጡ በኋላ በሥልጣን ላይ መቆየት የቻሉት ለአንድ ቀን ብቻ ነው፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ባልተለመደ ሁኔታ የተንሳቀሱት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ብቻ አይደለም፡፡ በኦዲት ግኝቱ በርካታ የገንዘብ ጉድለት የተገኘባቸው የመንግሥት ተቋማት የ2006 ዓ.ም. በጀት እንዲቀነስ ሁሉ ጠይቀዋል፡፡ ይህ ክስተትና ሌሎችም በተደጋጋሚ በመገናኛ አውታሮች ቴሌቪዥንን ጨምሮ መዘገባቸው፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ አግራሞትን ፈጥሯል፡፡ ‹‹ፓርላማው ጥርስ እያወጣ ነው›› የሚል ጥያቄ አዘል መደነቅ አሳይቷል፡፡
ይህ ፊት ለፊት ያለ እውነት ቢሆንም የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ አባ ዱላ ገመዳ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ምክር ቤቱ ቀድሞውንም ‹‹ጥርስ እንዳለው›› ተናግረዋል፡፡
የሆኖ ሆኖ ይህንን ልዩ የፓርላማ ባህርይ የተመለከቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን በ2006 ዓ.ም. ፓርላማው በዚሁ ጥንካሬው ይቀጥል ይሆን የሚል ጉጉታቸውን በጥያቄ መልክ ሰንዝረዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ፓርላማው በተጠቀሰው ዓመት ያሳየውን የሥራ አፈጻጸሙንና የመቆጣጠር ኃላፊነቱን ጥራት ያላቸው ሕጐችን በማፅደቅ ላይ እንዲጠነክር በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ጠይቀዋል፡፡
የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው
ከላይ እንደተገለጸው በርካቶች የተቀበሉት እንዲሁም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተመኙት የፓርላማው እንቅስቀሴ የ2006 ዓ.ም. የሥራ ዘመን የተጀመረው በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ነበር፡፡ ፓርላማው ከመስከረም ወር ጀምሮ የተለያዩ የብድር ስምምነቶችን፣ እንዲሁም የተለያዩ አዳዲስና የማሻሻያ አዋጆችን አፅድቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአስፈጻሚው አካል የተለያዩ ኃላፊዎችን በመጥራት በሥራ ክንውናቸው ላይ ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ አዋጅ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት አዋጅ፣ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ፣ የማዕድን አዋጅ፣ የቁም እንስሳት ግብይት አዋጅ፣ የከተማ መሬትና ነክ ንብረቶች ምዝገባ አዋጅ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት የተጠቀሱት ሕጐችና ሌሎችንም ባፀደቁባቸው ወቅቶች ሰፊ ምርምራ በአዋጆቹ ላይ በማድረግ የአዋጆቹን የጥራት ደረጃ በመጠበቅ እንዲፀድቁ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት በተለያዩ አዋጆች ላይ የሚያነሷቸውን አስተያየቶች በመተው፣ ያቀረቡትን ሐሳብ የሚያፈርስ ድምፅ ሲሰጡ መታየታቸው ጥያቄዎች እንዲነሱ አድርጓል፡፡
ለአብነት ከሚጠቀሱት መካከል የከተማ መሬትና መሬት ነክ ንብረቶች ምዝገባ አዋጅ ይገኝበታል፡፡ ይህ አዋጅ በሁሉም ክልሎች ከተሞች ውስጥ የሚገኙ መሬቶችንና የማይንቀሳሱ ንብረቶችን በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ በሆነ መንገድ መመዝገብ የሚያስችል ነው፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ ስለሌሎች መሬትን ከማስተዳደር አኳያ ከሚሰጠው ሥልጣን ጋር ተያይዞ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ይሁንታ መጠየቅ ይገባል የሚል ሐሳብ በሚመለከተው ቋሚ ከሚቴ ቀርቦ ነበር፡፡
ይህ ሐሳብ በተወኑ የምክር ቤቱ አባላት በከፍተኛ ደረጃ ተተችቷል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱ መሬትን በተመለከተ ለፓርላማው የሰጠው ሥልጣን ግልጽ ነው፡፡ ሐሳቡን ያቀረበው ቋሚ ኮሚቴ ሥራውን በአግባቡ ስላልሠራ እንጂ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚመራ ጉዳይ የለም፡፡ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የማይጣጣም ከሆነ ውድቅ ማድረግ፣ ከፓርላማው ሥልጣን ጋር የሚጣጣም ከሆነ ደግሞ አስፈላጊውን ምልከታ አድርጐ ማፅደቅ ነው ከኛ የሚገባው፤›› የሚሉ የቋሚ ኮሚቴውን የውሳኔ ሐሳብ የሚቃረኑ አባላት አስተያየቶቻቸውን በወቅቱ ሰጥተው ነበር፡፡
በወቅቱ ለተሰነዘሩት የተቃውሞ ክርክሮች ምላሽ ቢሰጥም ሐሳቦችን ማስታረቅ ባለመቻሉ ግን አፈ ጉባዔው በድምፅ ለመለየት ተገደዋል፡፡ የተቃውሞ ክርክር ሲያደርጉ የነበሩ የፓርላማው አባላት ተቃውሟቸውን በሚሰጡት ድምፅ ይገልጻሉ ተብሎ ቢገመትም ይህ አልሆነም፡፡ የውሳኔ ሐሳቡን ተቃውመው የተከራከሩት የምክር ቤቱ አባላት የድጋፍ ድምፅ በመስጠት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መርተውታል፡፡
ይህ አዋጅ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ለውይይት በቀረበበት ወቅት ተመሳሳይ ክርክር ተነስቶ ነበር፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልና የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬና ሌሎች ሁለት አባላት ፓርላማው የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ይሁንታ ሳይጠይቅ በራሱ ማፅደቅ ይችል ነበር በማለት ተከራክረዋል፡፡ ወደ ድምፅ በተገባበት ወቅትም በተመሳሳይ ተቃውሟቸውን ድምፅ በመንፈግ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ቦርድ አባላትን ሹመት ለማፅደቅ በቀረበ ጥያቄ ላይ አንድ የምክር ቤቱ አባል የቀድሞው የቦርድ አባላት ጊዜያቸውን እንዳልጨረሱና ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ በሌላ የሚተኩበት ምክንያት ምንድን እንደሆነ እንዲብራራላቸው ጠይቀዋል፡፡ ጥያቄውን ያቀረቡት አባል ምክር ቤቱን በመወከል የቦርድ አባል እንደሆኑ ጠቅሰው በቀረበው አዋጅ እየተተኩ ከሚገኙት መካከል እርሳቸው አንዱ መሆናቸውን በመግለጽ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡ የቦርድ አባላቱን ሹመት በደብዳቤ የላኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በመሆናቸውና እሳቸው በወቅቱ በምክር ቤቱ ያልተገኙ በመሆናቸው ማብራሪያ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የማቅረብ ግዴታ እንደሌለባቸው በአፈ ጉባዔው ተገልጾ ወደ ድምፅ መስጠት ተገብቷል፡፡ በዚህ ወቅትም ከላይ እንደተገለጸው ማብራሪያውን የጠየቁት አባል የአዲሶቹን ሹመት በድምፃቸው ይቃወማሉ ተብሎ ቢገመትም የሆነው ተቃራኒ ነው፡፡ ይህንንና ሌሎች ተመሳሳይ አስተያየቶችን የተመለከቱ በምክር ቤቱ ታይቶ የነበረውን ተስፋ ሰጪ እንቅስቀሴ በጥያቄ ይመለከቱታል፡፡
የፓርላማውን እንቅስቃሴ ‹‹የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው›› በማለት ይተቹታል፡፡ ፓርላማው የክርክር መድረክ ነው ለማስባል እንጂ፣ የመጨረሻ ውጤቱ የቀረበለትን ማፅደቅ ነው በማለት ይወቅሱታል፡፡
የምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተሾመ እሸቱ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ ፓርላማው የማንም ተፅዕኖ እንደሌለበት፣ ምክንያቱ ደግሞ ሁሉም የመንግሥት አካላት የሚያስፈጽሙት የኢሕአዴግን ፖሊሲ እንደሆነ በቅርቡ ለፓርላማው መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል፡፡
‹‹እያንዳንዱ አባል በምክር ቤቱ የመወከል ፋይዳዬ ምንድንነው የሚለውን መመለስ ከቻለ፣ የምክር ቤቱ ሥራ አሁን ካለበት በተሻለ መንገድ ይፈጸማል፤›› ብለዋል፡፡
No comments:
Post a Comment