Friday, February 28, 2014

ኢህአዴግ ተሸንፏል! (የጉዞ ማስታወሻ)

ኢህአዴግ ተሸንፏል! (የጉዞ ማስታወሻ)

ጌታቸው ሺፈራው
ዛሬ የማወራው በምርጫ ስለመሸነፍ አይደለም፡፡ በምርጫ መሸነፍማ ወግ ነው፡፡ በተለይ ምርጫን ፍትሃዊና ዋነኛው የስልጣን ምንጭ አድርጎ ሽንፈቱን በጸጋ ለተቀበለ ‹‹ሽንፈቱ›› አሸናፊነት በሆነ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ይህኛውን ወግ አላገኘውም፡፡ እንዲያውም አስከፊው ሽንፈት ሳያውቁት፣ በግድ መሸነፍ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አዎ ኢህአዴግ ይህን ሽንፈት ተከናንቦታል፡፡ ኢህአዴግ ይህንን ሽንፈቱን ለመሸፈን ለ23 አመታት በግድ መግዛትን መርጧል፡፡
ከ1997 በኋላ ተቃዋሚዎች ቢዳከሙም፣ ህዝብ በፖለቲካው ተስፋ ቆርጦ ‹‹ዝም ብሎ ለመገዛት›› የቆረጠ ቢመስልም ኢህአዴግ ግን ሽንፈቱን ይደብቅልኛል ያለውን ወከባና ጥርነፋ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት ደግሞ በፖለቲካው መስክ መነቃቃቶች እየታዩ ነው፡፡ ይህኛው ‹‹ዝም›› ያለው ህዝብ ኢህአዴግን እንደማይፈልግ፣ ኢህአዴግ ምንም ያህል የመጨቆንና የማታለል አቅም ቢኖረውም የህዝብን ልብ መግዛት አለመቻሉንና መሸነፉን የሚያሳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ለመሸነፉ እጅግ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ አሁን ግን ለሱዳን አሳልፎ ከሰጠው መሬት ጋር በተያያዘ ያለው ጉዳይ ላይ ብቻ ማተኮር ወደድኩ!
የሰማያዊ ፓርቲ የጎንደር ጉዞ
ሰማያዊ ፓርቲ ወደ ጎንደር ከማቅናቱ በፊት በጽ/ቤቱ በድንበሩ ጉዳይ ጥናት ካደረጉት መካከል ብቸኛው የሆኑትን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምን በመጋበዝ ህዝብን አወያይቶ ነበር፡፡ በዚህ ውይይት ወቅት ፕሮፌሰሩን ጨምሮ ተሰብሳቢዎቹ ‹‹ኢህአዴግ አገር ሻጭ›› መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሁሉም እንደ መንግስት ሳይሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አሳልፎ ለመስጠት የተነሳ አንዳች ባዕድ ሀይል እንደሆነ ተግባብቶበታል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ደግሞ ይህን የፕሮፌሰር መስፍንና የሌሎችን ጥናት እንዲሁም መረጃዎች በግብዓትነት ወስደው ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር ወደ ጎንደር ለማቅናት በዝግጅት ላይ ነበሩ፡፡
ሰማያዊ ወደ ጎንደር ሲያቀናም ኢህአዴግ መሸነፉን በጉልህ ተመልክቻለሁ፡፡ አድርባይ ደህንነትና ፖሊስ የማይፈሩት ወጣቶች ወደሚታሰሩበት፣ ወደሚደበደቡበትና መስዕዋትነት ወደሚያስከፍል ተልዕኮ ሳይሆን ለሰርግ አሊያም ለሌላ ቅንጦች የሚጓዙ ያህል ደስተኞች ነበሩ፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ በሚወገዝበት ስርዓት አብዛኛዎቹ ወጣቶች ‹‹እኔ አልቀርም!›› በማለት የፓርቲውን አመራሮች ሲለምኑ፣ በመቅረታቸው ቅር መሰኘታቸው ስርዓቱ ሊያስገባቸው ከሚፈልገው የፍርሃት አዙሪት ሰብረው መውጣታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
የተሸናፊው ወከባ
የተሸነፈ የሚወስደው እርምጃ ግብታዊ ነው፡፡ ተረጋግቶ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ማዋከብ፣ መደናበር ልዩ ባህሪው ነው፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ልዑካን ወደ ጎንደር አቅንተው እንደገና አዲስ አበባ እስኪመለሱ ያጋጠማቸውም ይህ የተሸናፊዎች እርምጃ ነው፡፡ ወከባው የጀመረው የጎጃሟ ሉማሜ ከተማ ላይ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ጀምሮ በርካታ የትራፊክ ፖሊሶች እየገላመጡ ቢያሳልፉንም ከላይ አንዳች ትዕዛዝ የተሰጣት የምትመስለዋ የሉማሜዋ የትራፊክ ፖሊስ ግን በቀላሉ የምታሳልፈን አልነበረችም፡፡ መውጫው የምትቆዩበትን ቀን በግልጽ አላስቀመጠም በሚል ሰንካላ ምክንያት መኪናችን አስቆመች፡፡ ካልተቀጣችሁ አትሄዱም በማለቷ ላለመዘግየት ‹‹ቅጣታችን›› ቶሎ መክፈልን ወሰንን፡፡ ምን አልባትም ከ‹‹በላይ አካል›› ትዕዛዙ የመጣላት የምትመስለው የትራፊክ ፖሊስ ውሳኔ ግን ቢሮ ውስጥ የነበረውን አለቃዋንም ያስገረመ ነበር፡፡ ለመክፈል ወደ አለቃዋ ቢሮ ያቀኑት የልዑካኑ አባላት እንዳረጋገጡልን የትራፊክ ፖሊሷ ያቀረበችው ሰንካላ ምክንያት ለማስቀጣት ይቅርና ለተግሳጽ የሚያበቃ አልነበረም፡፡
መስዋትነት ወደሚያስከፍል ተልዕኮ ሳይሆን ወደ አንዳች ደስታ ቦታ የሚያቀኑ የሚመስሉት የልዑካኑ አባላት መንገዱን በሙሉ የአገራቸውንና የፓርቲያቸውን መዝሙር በመዘመር፣ እንዲሁም በመቀላለድና በመሳሳቅ ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ ይህን ደስታቸውን ከጥቂት አመታት በፊት በርካታ ወጭ ፈሶበት በጥቂት አመት ውስጥ የፈረሰው ቻይና ሰራሽ መንገድ እንኳ አላቀዘቀዘውም፡፡ ሆኖም የመኪናችንን ፍጥነት በእጅጉ ቀንሶታል፡፡ በዚህም ምክንያት በጊዜ መግባት ሲገባን ግማሹን ሌሊት ሁሉ ለመጓዝ ተገደናል፡፡
አይደለም ሰማያዊን የግንባሩን አባላት የማያምነው ኢህአዴግ የልዑካኑንና ከልዑካኑ ጋር የሚገናኙትን አካላት በቅርብ እርቀት መከታተሉ የሚጠበቅ ነው፡፡ ስለሆነም የት እንደደረስን፣ መቼ ጎንደር እንደምንገባና ሌሎች መረጃዎችን ለአገሪቱ ሳይሆን ለስልጣን ማራዘሚያ በሚጠቀምባቸው የደህንነት ተቋማቱ ሊያዳምጥ እንደሚችል ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ይህን እያወቅንም ቢሆን እኛ እንደልባችን እናወራለን፡፡ የት እንደደረስን፣ መቼ እንደምንገባና ሌሎች መረጃዎችንንም በነጻነት እንለዋወጣለን፡፡ በተለይ ጎንደር ከሚገኘው የፓርቲው ቅርንጫፍና ቀድመው ወደ ጎንደር ካቀኑት የፓርቲው አመራሮች ጋር እነዚህን መረጃዎች በተከታታይ ተለዋውጠናል፡፡
ጎንደር ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ ደረስን፡፡ እነዚህን መረጃዎች ሲያዳምጥ የነበረው ገዥው ፓርቲ የተሸናፊ እርምጃ ሊወስድ እንደነበር የሰማነው ግን በነጋታው ጠዋት ላይ ነው፡፡ እንፍራንዝ የተባለችውን ከተማ እኛ ያለፍናት ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት አካባቢ ነው፡፡ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት አካባቢ ‹‹ሰማያዊ ነው!›› ተብሎ መኪና መዘረፉን የነገረን በአካባቢው የሚገኝ አንድ የሰማያዊ ፓርቲ ደጋፊ ነው፡፡ አዎ የተሸነፈ የሚወስደውን እርምጃ አያውቅም፡፡ ለማመዛዘን ጊዜም ሆነ ብቃት አይኖረውም፡፡
ወከባው ጎንደር ከደረስን በኋላም ቢሆን አላቆመም፡፡ ካድሬዎች ያረፍንበትን ሆቴል ማጨናነቅ ዋነኛ ስራቸው ሆነ፡፡ ከዚህም አልፈው ‹‹እነዚህን ሰዎች አስወጡልን!›› እስከማለት መድረሳቸውን በግልጽ ሰምተናል፡፡ በሌላ በኩል የሰላማዊ ሰልፉ እንዲካሄድ ባለመፈለጋቸው አንቀበልም ከማለትም አልፈው ሲደበቁ የሰነበቱት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባለስልጣናት የሰማያዊ ወጣቶች ገፍተው ከገቡበት እውነት ጋር መፋጠጥ የግድ ሆኖባቸዋል፡፡
ሀሙስ ጥር 22 ስድስት ሰዓት ላይ ሰው የሚበዛባት አራዳ ለቅስቀሳ ተመርጣለች፡፡ ከየት እንደመጡ ያልታወቁት የሰማያዊ ወጣቶች በፍጥነት ወረቀቶችን ለህዝብ ማድረስ ጀመሩ፡፡ መኪና ላይ ሆነው መሬቱን አሳልፈው እንደማይሰጡ ህዝብን ቀሰቀሱ፡፡ ቅስቀሳውን ከአራዳ እስከ መስቀል አደባባይ በፍጥነት አከናወኑ፡፡ ምን አልባት እስራት ካለ ህዝብ በስፋት ከሚያይበት የመስቀል አደባባይ ላይ መታሰሩ አዋጭ እንደሚሆን ታምኖበታል፡፡ እንደተገመተው የተደናገጡት የከተማው ባለስልጣናት መስቀል አደባባይ ላይ እየቀሰቀሱ የነበሩትን ወጣቶች ለማስቆም ጥረት አደረጉ፡፡ ማስቆም የፈለጉበት መንገድ ግን የሚያስገርም ነበር፡፡
ልክ ሉማሜ ላይ እንዳደረጉት የላኩት የትራፊክ ፖሊስ ነው፡፡ ምን አልባትም መኪናቸውን ከተቀሙ እንቅስቃሴው ይገታል ከሚል እሳቤ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ጎንደር ላይ ግን በቀላሉ የሚሳካ አልነበረም፡፡ ሲቪል የለበሱ የትራፊክ ፖሊሶች ሳይቀሩ ለወጣቶቹና ተሸናፊዎች ላስደፈሩት ሉዓላዊነት ዘብ ቆመው ታይተዋል፡፡ ቅስቀሳውን እንዲያስቆሙ የተላኩት ፖሊሶች መኪናው ምን እንዳጠፋ ንገሩን ሲባሉ ምክንያት አልነበራቸውም፡፡ ግን ‹‹ከበላይ አካል›› ይዛችኋቸው ኑ መባላቸውን ብቻ ነው በተደጋጋሚ የሚገልጹት፡፡ የሰማያዊ ወጣቶች ደግሞ ጥፋታችንን ካልነገራችሁን ቅስቀሳውን አናቆምም ካለንበትም አንንቀሳቀስም አሉ፡፡ ቅስቀሳውን የደገፈው ህዝብም ቢሆን ተመሳሳይ አቋም ያዘ፡፡ ቅስቀሳውን ሲከታተል ከነበረው ህዝብ ‹‹ከህዝብ ጋር እንዳትቀያየሙ›› የሚል ምክር የተሰጣቸውና ወትሮውንም ያላመኑበት የትራፊክ ፖሊሶች መለሳለስ ጀመሩ፡፡ ትንሽ ቆይተው የወጣቶቹን ቅስቀሳና ከፖሊስ ጋር የሚያደርጉትን ትዕይንት እንደ ህዝብ ታድመዋል፡፡
የከተማው አስተዳደር ግን ቅስቀሳው መቆም እንዳለበት ቆርጧል፡፡ በመሆኑም የትራፊክ ፖሊሶችን ተክቶ ፖሊስ ተላከ፡፡ ኢህአዴግ ከምንም በላይ የሚፈራው መረጃን ነው፡፡ በመሆኑም የፖሊሶች የመጀመሪያ ኢላማ የሆነው ፎቶ ግራፍ የሚያነሳው ወጣት ነበር፡፡ ካሜራውን ለመንጠቅ ሲሞክሩ ግን ከሰማያዊ ልጆች ከፍተኛ ትግል ገጠማቸው፡፡ ፖሊስና ወጣቶቹ ተናነቁ፡፡ ህዝብ ተሰበሰበ፡፡ ወጣቶቹ ህግ አያከብርም የሚሉት ኢህአዴግ የላካቸውን ፖሊሶች እየተፋለሙ ‹‹በህግ አምላክ! በህግ አምላክ!›› ይላሉ፡፡ በህግ ሳይሆን በጉልበት ቅስቀሳውን እንዲያስቆሙ የተላኩት ፖሊሶች ግን ከዚህ በላይ መታገል አልፈለጉም፡፡ አዎ! ከበላይ አካል ከተሰጣቸው ይልቅ ‹‹በህግ አምላክ›› ሲባሉ ተደናግጠው ቆሙ፡፡ ጎንደር ላይ በህግ አምላክ ተከበረ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች በቀላሉ እጅ የሚሰጡ አልነበሩም፡፡ እናም አምነውበት ሳይሆን ከበላይ አካል የተላኩት ፖሊሶች ያለ ግድ በውድ ለሰማያዊ ወጣቶች ካሜራውን ለቀቁ፡፡ አሁን ኢህአዴግ ተሸንፏል፡፡ ወጣቶቹ ደግሞ በአሸናፊነት ይዘምራሉ፡፡
ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም፣
በአባቶቻችን ደም፣
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም ያስደፈረሽ ይውደም፣
‹‹የትግል ጉዞ ታሪካዊ፣
ዓላማው ፍጹም ህዝባዊ፣
ራዕያችንም ኢትዮጵያዊ…››
ያም ሆኖ ፖሊሶቹ ‹‹ይዛችኋቸው ኑ!›› የተባሉትን ትዕዛዝ አልረሱም፡፡ ወጣቶቹ በመኪና ተጫኑ፡፡ ከፖሊሶቹ ጋር ሆነው ግን ወረቀት ከመበተን፣ በሞንታርቮ ከመቀስቀስ ያገዳቸው አካል አልነበረም፡፡ እንዲያውም ወደ ፖሊስ ጣቢያው የሚያደርሰውን ረዥም መንገድ ይዘው ሲጓዙ ፖሊሶቹ ሰላማዊ ሰልፉ እንዲካሄድ ፍላጎት እንደነበራቸው ያሳያል፡፡
ቅስቀሳ ላይ የነበሩት ወጣቶች ከታሰሩ በኋላ የኢትዮጵያ ፖሊስ የሚታወቅበትን ድብደባና ዘለፋ አልፈጸመም፡፡ ይህ ግን የፖሊሶቹ ደግነት ብቻ አልነበረም፡፡ የከተማ አስተዳደሩ አንዳች ቅርቃር ውስጥ መግባቱን ራሱ አስመስክሯል፡፡ ወጣቶቹ እስር ቤት እያሉ ከቀናት በፊት የማሳወቂያ ደብዳቤውን አልቀበልም ያሉት አካላት አመናጭቀው የመለሷቸውን ሰዎች አስጠርተው ተለማምጠዋል፡፡
በአንድ በኩል ተርበትብተው መደራደር የሚፈልጉት የጎንደር አስተዳደር ሰዎች በሌላ በኩል ማዋከባቸውን ግን አላቆሙም፡፡ የታሰሩት ቢፈቱም ቅስቀሳውን ለማሰናከል መሳሪያዎቹ በፖሊስ እንደተያዙ ቆይተዋል፡፡የመቀስቀሻ መሳሪያዎቹ በፖሊስ እጅ በመውደቃቸውና ለአንዳንድ ጥንቃቄዎች ሲባል አርብ ጥር 23 ወረቀት መበተንና ሌሎች ግልጽ ቅስቀሳዎች አልነበሩም፡፡ ይህም በስጋት የተዋጡት የከተማው አስተዳደር አካላትን አስጨንቋል፡፡ እናም በተቀላቀለ ስሜት ደውለው ‹‹ምነው ጠፋችሁ!›› እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ቅዳሜ ጥር 24 ኮሌጅና አዘዞ ለቅስቀሳ ተመርጠዋል፡፡ ለቅስቀሳ የወጡት ወጣቶች ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲው አካባቢን በፍጥነት ከቀሰቀሱ በኋላ ወደ አዘዞ ሲደርሱ ፖሊስ አስቁሟቸዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ልዑካን ወደ ጎንደር ካቀኑበት ጊዜ ጀምሮ ከወትሮው በተለየ መልኩ ኢንተርኔትና ስልክ ተቋርጦ ለረዥም ሰዓት መቆየት ጀምሯል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከሆቴሉ ጎን የሚገኝ ቤት በእሳት ተያያዘ ተብሎ ጥይት በመተኮስ ጫጫታ ለመፍጠርና መብራት በማጥፋት ለማደናገጥም ተሞክሯል፡፡ ተቃጠለ የተባለው ቤት ከሆቴሉ ጎን ቢሆንም ምንም አይነት ጭስ፣ የእሳት ምልክትና ሽታ አልነበረውም፡፡ ወዲያውኑ ደግሞ ጠፋ ተባለ! በቅስቀሳ ላይ የነበሩት ወጣቶች አዘዞ ላይ በተያዙበት ወቅት እንደተለመደው ወዲያውኑ ኢንተርኔትና ስልክ እንዲጠፋ ተደረገ፡፡
አሁን ሰላማዊ ሰልፉ እየተቃረበ እንደመሆኑ የከተማውን አስተዳደር ይበልጡን ፈርቷል፡፡ ሰልፉ እንደማይቀር ከሰማያዊ ወጣቶች ድፍረትና ቆራጥነት ተረድተዋል፡፡ በመሆኑም የከተማውን ነዋሪ በመሰብሰብ ማስፈራራት ነበረባቸው፡፡ ለዚህም ሰማያዊ ፓርቲን ስም እየለጠፉ ህዝቡን ለማራቅ ከመሞከር ባለፈ ‹‹ልጆቻችን ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ቢሳተፉ በጥይት ይመታሉ!›› ብለው እስከማስፈራራት ደርሰዋል፡፡ የተሸናፊዎቹ አቅም ይህ ነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፉ ሊደረግ 10 ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ በየ መግቢያው የተደረደሩት ፖሊሶች ህዝብን ወደ መስቀል አደባባይ እንዳይሄድ ሲያግዱ ተስተውለዋል፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ ወቅትም የቀበሌ ካድሬዎች ከሰልፉ በኋላ በመሆን ህዝቡን በመቅረጽ ለማስፈራራት ሞክረዋል፡፡ በእርግጥ ከዚህ አልፈው ሰላማዊ ሰልፉ ከተጠናቀቀ በኋላ እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውም ተሰምቷል፡፡ ሰላማዊ ሰልፉ ካበቃ በኋላ በቅርብ እርቀት ሲከታተሉ የነበሩት ካድሬዎች በሰልፉ ላይ የተሳተፉትን ወጣቶች የቀበሌ መታወቂያ ቀምተዋል፡፡ ወደ ቀበሌ ሄደው መታወቂያቸውን በተቀበሉበት ወቅትም ዳግመኛ ሰማያዊም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎች በሚጠሩት ሰልፍ እንዳይሳተፉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሰልፉን ያስተባበሩት የጎንደር የፓርቲው አባላትና ቤተሰቦቻቸው ላይ ደህንነቶች እየደወሉ ሲያስፈራሩዋቸው ሰንብተዋል፡፡
ሆኖም በሰልፉ የተገኙት ወጣቶችም ይህን የአካባቢው ቅርንጫፍ በደረሰባቸው ወከባ አለመደናገጣቸውን ደውለው ነግረውኛል፡፡ ለሰላማዊ ሰልፉ በሄድንበት ወቅት ጎንደር ውስጥ ካገኘኋቸው የኢህአዴግ አባላት መካከል አብዛኛዎቹ መሬቱ ለባዕድ ተላልፎ መሰጠቱን ከመቃወም አልፈው በጉዳዩ ከተቃዋሚዎች ጋር አብረው ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ተረድቻለሁ፡፡ ደብድቡ ተብለው የተላኩት ፖሊሶችና የከተማው አስተዳደርም እንደ ፌደራል መንግስቱ ግትር አቋም አለመውሰዱ የሽንፈቱ አንድ አካል ነው ማለት ይቻላል፡፡
ጉዞ ወደ አዲስ አበባ
ሰላማዊ ሰልፉ ተደርጎም ቢሆን ማዋከቡ እንደማይቆም ቀድመው የተገነዘቡት የፓርቲው አመራሮች ጎንደርን ቶሎ መልቀቅን እንዳለባቸው አምነዋል፡፡ እናም ሰላማዊ ሰልፉ ከተጠናቀቀ ከሁለት ሰዓት በኋላ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ተጀመረ፡፡ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች መሬቱን ለማስመለስ የተደረገውን ግፊት ቢያደንቁም ሰማያዊ በመመለሱ ከመጠን በላይ የሚቆራረጠው የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ጋብ እንደሚል በግልጽ ይናገሩ ነበር፡፡ ሰላማዊ ሰልፉ በሰላም መካሄዱ ያናደደው የሚመስለው ገዥው ፓርቲ ግን ከጎንደርም ውጭም እየተከተለ መተንኮሱን አላቆመም፡፡ አዲስ አበባ ለመድረስ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩንም ቢሆን ‹‹ከበላይ አካል›› ትዕዛዝ የተላለፈላቸው የሚመስሉት የትራፊክ ፖሊሶች ደብረ ጽጌ ላይ በመሳሪያ አስቆሙን፣ አስጸያፊ ስድብምና ማስፈራራትም ተጨመረበት፡፡
ይህ ሁሉ ወከባ ግን ልዑካኑን አላስደነገጠም፡፡ ወደ ጎንደር ጉዞ ከጀመሩበት ወቅት አንስቶ ወጣቶቹ በድፍረት ከተሸናፊው መንግስት ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጠዋል፡፡ ደብረ ጽጌ ላይም ያደረጉት ተመሳሳይ ነው፡፡ ትራፊክ ፖሊሶች መኪናውን ወደ ጣቢያ እንዲወስድ ሲወተውቱት የሰነበተውና ከልዑካኑ ጋር ሁለቱንም ቀን የታሰረው ሾፌር ደብረ ጽጌ ላይም ልክ እንደ ሰማያዊ ወጣቶች መብቱን አሳልፎ ላለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት አሳየ፡፡ የልዑካኑ አባላት መሳሪያ አውጥቶ ‹‹እበትንሃለሁ!›› ላለው ፖሊስ ደረታቸውን ሰጡ፤ አጸያፊ ስድብ የተሳደበውን አፋጠጡት! አሁን ልዑካኑን ለማስቆም የጣሩት ፖሊሶች እንደገና መደናገጥ ጀምረዋል፡፡ የከተማው ህዝብ ወጣቶቹና የትራፊክ ፖሊስ የሚያደርጉትን ክርክር እየተመለከተ ተስብስቧል፡፡
የሰማያዊ ወጣቶች ዋናው ሰላማዊ ሰልፍ ከመደረጉ በፊት መስቀል አደባባይና አዘዞ ላይ ፖሊስ ሲያስቆማቸው ሲይዛቸው በመዘመር፣ ህጉን በማስረዳት ህዝብን ሰብስበዋል፡፡ በጽናታቸውና በድፍረታቸው ፖሊሶቹን ሳይቀር አስገርመዋል፡፡ ደብረ ጽጌ ላይ በመሳሪያ ለማስቆም ሲጥርም ሌላ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል፣ ህዝብን ሰብስበው ስለመብቱ አስተምረዋል፡፡ ከፖሊስ ጋር እየተከራከሩ፣ ህዝብን ሰብስበው እያስተማሩም ለቀሪው ህዝብ በስልክና በማህበራዊ ድህረ ገጾች ትዕይንቱን ማካፈላቸውን ቀጥለዋል፡፡ በተለይ በፌስ ቡክ ዜናው በስፋት መዳረስ ጀምሯል፡፡ ይህን ሁሉ ያልጠበቁት ትራፊክ ፖሊሶችን የላኩት የበላይ አካላትም ይሁኑ የከተማው ካድሬዎች ወጣቶቹን ለመልቀቅ ተገድደዋል፡፡ ለኢህአዴግ ሌላ ሽንፈት! ለሰማያዊ ወጣቶች ሌላ ድል! ከድል በኋላም የድል መዝሙር!
ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም፣
በአባቶቻችን ደም፣
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም ያስደፈረሽ ይውደም፣
……….
‹‹የትግል ጉዞ ታሪካዊ፣
ዓላማው ፍጹም ህዝባዊ፣
ራዕያችንም ኢትዮጵያዊ…››
(ይህ ጽሁፍ በማተሚያ ቤት ምክንያት ከዘገየችው ነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ የተወሰደ ነው፡፡)

No comments:

Post a Comment