ወጣትነትና ፖለቲካ
አስራት አብርሃም
በአሁኑ በሃገረ-ኢትዮጵያ ያለውን ወጣት ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና ሚና ምን እንደሚመስል ለማየት ወደኋላ
መመልከት ያስፈልጋል። ለዚህም መነሻ እና መንደርደሪያ እንዲሆነን፣ ከአሁን በፊት የነበሩት ትውልዶች
በወጣትነት ዘመናቸው ያደርጉት የነበረውን ጉልህ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መፈተሽ ተገቢ ነው። ይህን መነሻ
በማድረግ ከዚህ ቀድም ከነበሩ ሁለት ትውልዶች ማለትም፤ አንደኛ ሀገሪቱ ከኢጣሊያ ወረራ ነፃ ከወጣች በኋላ
የመጣው ዘመናዊ ትምህርት የተማረ ትውልድ እና ቀጥሎ የመጣው የስልሳ ስድስቱን አብዮታዊ ትውልድ
እንደመነሻ ለመዳስስ እሞክራለሁ። ይህን ፅሁፍ ያቀረብኩት በማዘጋጅበት ወቅት የፕ/ር ገብሩ ታረቀ “የትውልዶች
የፖለቲካ ትግል እንደዱላ ቅብብሎሽ ሲታይ” በሚል ርዕስ በቀድሞዋ አዲስ ታይምስ መፅሔት ላይ ባቀረቡት
ፅሁፍ ትውልዶቹን በዘመን ማዕቀፍ የከፈሉበትን መንገድ ከሞላ ጎደል በመቀበል ነው።
በእንግሊዝ መንግስት ድጋፍና በኢትዮጵያ አርበኞች ብርታት የኢትዮጵያ ነፃነት መልሶ ማግኘት ከተቻለ ኋላ
የመጣው፤ የምዕራባውያን ዘመናዊ ትምህርት የቀመሰው አዲስ ትውልድ፤ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ የተሸነፈችበትን ምክንያት ባለመሰልጠኗ፤
በቴክኖሎጂ እና በጦር መሳርያ ወደፊት ባለመራመዷ መሆኑን የተረዳ፤ ይህንም በቁጭት የሚያንገበግበው በመሆኑ ሁኔታውን
ለመለወጥና ሀገሪቷ ጥንታዊ መሰረቷን ሳትለቅ እንድትበለፅግ፤ እንድትሰለጥን ይመኝ የነበረ ትውልድ ነው።
እነዚህ ከውጭ ተምረው የመጡት የአዲሱ ትውልድ አባላትና ወጣት ምሁራን፣ በንጉሰ ነገስቱ መሪነት ሀገሪቷን ለማዘመን የነበራው ጉጉት
እጅግ በጣም የሚደነቅ ነው። በተለይ የኢትዮጵያን ጥንታዊነትና ታሪካዊነት፣ ባህሏና ለዘመናት ይዛው የመጣችውን መንግስታዊው
አሰራርና ስርዓት በመሰረታዊ ሁኔታ ሳይነካ የመዘመንና የመሰልጠንን ሀሳብ ያቀነቅኑ፤ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ በንጉሱ ግንባር ቀድም
መሪነት ያለምንም ጫጫታ፣ ፀጥተኛ በሆነ ሰላማዊና ዘገምተኛ መንገድ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልጉ መሆናቸው ዋንኛ መለያቸው ነው።
በእርግጥ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የመሬት ስሪትና ስር የሰደደው ፊውዳላዊ ስርዓት እንዲህ ባለ የማሻሽያ መንገድ መለወጥ ይቻል
ነበር ወይ? የሚለውን ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፤ ረጋ ባለና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ የተነሱበት
ሀሳብ ግን ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው።
ምሁራኑ በንጉሱ ላይ የነበረው እምነት ሌላው መታየት የሚኖርበት ጉዳይ ነው። ትውልዱ በተለያየ አጋጣሚዎች ይህን ሀሳቡን ለንጉሰ
ነገስቱ በፅሁፍም፣ በግንባር ቀርቦ በማስረዳትም፤ በተወሰነ ደረጃ በስኬት የተጓዘበትና አንዳንድ ማሻሽያዎች እንዲደረጉ ምክንያት የሆነም
ነው። ለምሳሌ ኤርትራ ከእናት ሀገሯ እንድትቀላቀልና ኢትዮጵያ ጥንታዊው የባሀር በሯን በሰላማዊ መንገድ መልሳ እንድታገኝ በማድረጉ
ሂደት ላይ፣ ያደረገው ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ተጋድሎ ከሚገባው በላይ ፍሬ አፍርቷል። ከዚህ አንፃር ካየነው ከኋላኛው የስልሳዎቹ
ትውልድ ይልቅ የዚህ ትውልድ ባክኖ መቅረት ሀገሪቱን ክፉኛ እንደጎዳት መሳብ ይቻል ይሆናል።
በአንፃሩ በንጉሱ ዘንድ የነበረው ስጋት፣ የእነዚህ ወጣት ምሁራን ብተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እየተገናኙ መምከራቸው፤ አልፎ ተርፎም
በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ተቀራራቢና አንድ ዓይነት ሀሳብ ማራመድ መጀመራቸው እንደ ትልቅ ስጋት መታየት መጀመራውን
የምናስተውልበት ሁለት አጋጣሚዎችን ልጥቀስ መጥቀስ ያስፈልጋል።
እነ አክሊሉ ሀብተወልድ እና ይልማ ድሬሳ ሀገሪቷን ከእንግሊዝ ተፅዕኖ ሙሉ ለሙሉ ነፃ ለማድረግ የዴፕሎማሲና የፖለቲካ ትግል
ለማድረግ በተነሱበት ወቅት፣ በጥልቀት ተወያይተው ያፈቁቱን የመፍትሄ ሀሳብ ወደ ንጉሱ እንዲቀርብ ባደረጉ ጊዜ፣ አፄ ኃይለስላሴ
በአጠቃላይ ሀሳቡ ደስተኛ መሆናቸውን ከገለፁ በኋላ በሌላ በእኩል ደግሞ ያላቸውን ፖለቲካዊ ስጋት፣ ምክርም ማስጠንቀቂያም
በሚመስል መልኩ ሲገስፁዋቸው እንመለከታለን፤
“ሀገር ችግር በሚያጋጥማት ጊዜ እንደዚህ እየተሰበሰቡ ሐሳብን ማስተባበርና ተስማምቶ መስራት ተገቢ ነው። ሆኖም አንዳንድ
ጊዜ ስብሰባ ሲበዛ፤ የአድማ ወይም የፓርቲ አስራር መንፈስ እንዳይፈነጥቅበት መጠንቀቅ ያስፈልጋል።” (ዘውዴ ረታ፥
የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት ገፅ 470)
እንደዚሁም በሌላ ጊዜ ይህን ስጋታቸውን አንስተው ሲናገሩ እንዲህ ነበር ያሉት፤
“ብዙ ጊዜ እየተደጋገመ እንዳየነው፤ እኛ በምናደርገው ስብሰባ ላይ ይልማ ዴሬሳና አክሊሉ ሀብተወልድ እየተደጋገፋችሁ
ታላላቆቻችሁ የሚያቀርቡትን ሐሳብ መቃወምና የራሳችሁን ትልቅ አስመስሎ የመናገር፤ እንደ መልካም ስራ አድርጋችሁ
የምትቆጥሩት ይመስላል። እርግጥ ነው! አንድ ጉዳይ በጉባኤ ቀርቦ ሲጠና፤ እያንዳንዱ ሰው የተለያየ ሐሳብ ሊኖረው ይችላል።
ይህም የዘመኑ ዴሞክራሲ አሰራር የሚጠይቀው ነው ብለን እንቀበለዋለን። ነገር ግን በየስብሰባው ላይ ሁለትና አንዳንድ ጊዜም
ሶስት ሰዎች በአንድ ጉዳይ ሲደግፉም በአንድነት፤ ሲቃወሙም በአንድነት እየሆኑ የምናየው፤ ወደ ፓርቲ ያዘነበለ አሰራር ነው
አስራት አብርሃም
እንጂ፣ የዴሞክራሲ ወግ የተከተለ ነው ማለት አይቻልም። ይህንንም እስከመናገር ያደረሰን አክሊሉና ይልማ በአንድ ድምፅ
እየደጋገማቹ የምትናገሩት እያስገረመን ነው።” (ዝኒ ከማሁ ገፅ 504)
እነዚህ ከላይ የቀረቡት የንጉሱ ንግግሮች ከነፃነት በኋላ በነበሩ ዓመታት በንጉሱና በዚያ ጊዜ በነበሩ ወጣት ምሁራን መካከል የነበረው
ሁኔታ በትክክል የሚያሳዩ ናቸው። በአንድ በእኩል ወጣቶቹ ለሀገር የሚጠቅም ሀሳብ እያመነጩ ያዋጣል፤ ያስኬዳል የሚሉትን ሀሳብ
ለንጉሱ እያቀረቡ ሀገሪቱን የተሻለች ለማድረግ የበኩላቸውን ጥረት ለማድረግ ሲታትሩ፤ በሌላ በእኩል ደግሞ ንጉሱ ምንም እንኳ የእነዚህ
ወጣት ምሁራን አበርክቶ አስፈላጊነት ላይ የተለየ አቋም ባይኖራውም፣ በየጊዜው እየተገናኙ የሚያደርጉትን ውይይትና ምክክር ሌላ
የፖለቲካ መልክ እንዳይዝ፤ በተለይ ደግሞ በዚያ መነሻነት ቀስ በቀስ የፓርቲ ፖለቲካ እንዳይለመድ ወይም የፓርቲ ፖለቲካ እስከማቋቋም
ድረስ እንዳይመኙ የማስጠንቀቅ አካሄድ እንደነበራቸው እንመለከታለን።
ከዚህ አኳያ ንጉሱ አድማና ፓርቲ የሚሉትን ሀሳቦች፣ ከመጀመርያውም ያባኑኗቸው ጀምረው እንደነበር የምንረዳው። በመሆኑም በንጉሱ
በእኩል ለውጥ ሊመጣ ይችላል የሚለው የትውልዱን ተስፋ እየጨለማ በመሄዱ፤ ከዚህ የተለየ ሀሳብ ይዞ የመጣው የእነ ገርማሜ ነዋይ
ቡድን ነው። ይህም ንጉሱ ሳይወገዱ በሀገሪቷ ላይ ለውጥና እድገት ማምጣት እንደማይቻል በመገንዘብ፤ ንጉሱን በመፈንቅለ መንግስት
በመገልበጥ ለውጥ ለማድረግ አስበው ተንቀሳቅሰዋል። ምንም እንኳ የታሰበው መፈንቅለ መንግስት ቢከሽፍ፣ ለቀጣዩ ትልውድ ተገቢ
የሆነ የሀሳብ ትጥቅ ወይም መልዕክት አስተላለፎ ነበር የተዘጋው። ይህ መልዕክትም፣ ንጉሱ ወይም ዘውዳዊው ስርዓት ሳይወገድ ለውጥ
ማምጣት አይቻለም፤ ስለዚህ በተገኘው መንገድ ንጉሱን ማስወገድ ግዴታ ነው የሚል ነው። በአብዛኛው ከመንቅለ መንግስቱ በኋላ
ሲቀነቀን የነበረው ሀሳብ ይሄ ቢሆንም፤ የተወሰኑ ምሁራን ደግሞ በንጉሱ ላይ የነበራቸው ተስፋ አልተሟጠጠም ነበርና በተደጋጋሚ
ጠንከር ባለሁኔታ የስርዓት ማሻሽያ እንዲያደርጉ ንጉሱን ከመጎትጎት ወደ ኋላ ያለበት ጊዜ አልነበረም። ለምሳሌ ያህልም አምባሳደር
ብርሃኑ ድንቄ “እባክዎን ዘውዱን ለራስዎ ስንጣኑን ግን ለህዝብዎ ይስጡ” የሚል ተማፅኖ የሚጠቀስ ነው። ሌሎችም እንደዚሁ
መጭውን አስከፊ ሁኔታ በመተንበይ፤ ንጉሱ እና መሳፍንቱ ከእንቅልፋቸው እንዲነቁ ጥረት ያደርጉ እንደነበር እንረዳለን። “አውቀን
እንታረም” የሚለው መፅሐፍ የተፃፈውም በዚህ ጊዜ እንደሆነ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። ንጉሱ ግን እያረጁ ሲሄዱ የበለጠ ስልጣን
እየወደዱ፣ የሰው ምክርም መስማት እየተዉ፣ በመሄዳቸን ምክንያት፣ በእርሳው አመራር ስር ሆኖ የሚኖር ሰላማዊ ማሻሽያ ጭራሽ
እንዳይታሰብ አደረገው።
ከዚህ በኋላ ነበር በጣም ጽንፈኛና ነውጠኛ የሆነው የስልሳዎቹ አብዮታዊ ትልውድ እንደማዕበል በአንድ ጊዜ ሀገሪቷን ያጥለቀለቀው። ይሄ
ትውልድ በማርክሲዝምና በሌሊኒዝም ርዕዮተ ዓለም የሰከረ፤ በእነ ማኦ፣ ሆች ሚኒ፣ ቼ ጎቬራ የትጥቅ ትግል ዜና አቅሉን ያጣ፤ እያንዳንዱ
ፖለቲካዊ አቋሙን በዚሁ ርዕዮተ ዓለም ብቻ መተንተን እንደ ብቸኛ አማራጭ እና እንደ እምነት የተቀበለ፤ የሀገሪቱን ታሪክ፣ ባህል፣ የቆዩ
እሴቶች፣ ጂኦፖለቲካ ሁኔታ ሳያገናዝብ፤ የሀገሪቷን መሰረታዊ ጠላቶች በመደብ ትንተና ወዳጅ ናቸው ያለ፤ ነገሩን በወጉ ሳይገባው
ከመፅሐፍ ያነበበውን እንደወረደ በጭፍን ተቀብሎ ያስተጋባ ነውጠኛ የሆነ ትልውድ ነበር።
ያ ትውልድ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት እስከመገንጠል በማቀንቀን፤ የኤርትራ ኃይሎች በአረብ ሀገራት እየተደገፉ የሚያደርጉትን
የመገንጠል ትግል “የነጻነት ትግል ነው!” ብሎ ያወደሰ፤ ከሀገሩ ይልቅ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ለዐም የሚያስቀድም ነበር። በእኔ አተያይ፣ ይህ
ትውልድ ከእርሱ በፊት ከነበረው ትውልድ ምንም የወረሰው ቁም ነገር ያለ አይመስልም። ስለዚህ በእርሱና ከእርሱ በፊት በነበረው
ትውልድ መሀል ምንም ዓይነት የትግል ዱላ ቅብብል አልነበረም። የመጀመርያዎቹ ትውልዶች ያሱትን የትግል ዱላ በመጣል፤ ሌላ የራሱን
የትግል ዱላ ያነሳው ማለት ይቻላል።
ያ ትውልድ ያሳካው ዋናው መሰረታዊ ነገር የ“መሬት ላራሹ”ን መፈክር ብቻ ይመስላል። ያ ትውልድ እርስ በራሱ በነበረው መሰረታዊ
ያልሆነ ልዩነት ምክንያት እርስ በራሱ ተጨፋጭፎ የተላለቀ፤ ራሱንና ትልውዱን ለወታደራዊው ደርግ ጭፍጨፋ ያጋለጠ፤ በዚህ ሁኔታ
ከተደመሰሰ በኋላ የተረፈው በአራቱም የሀገሩቱ አቅጣጫዎች ተበታትኖ እንዲሰደድ ሆኗል። እዚያም ከሄደ በኋላ አውሮፓና አሜሪካ
መሽጎ፤ ሲመቸው በጡሩንባ ሳይመቸው ደግሞ በስማ በለው ትግሉን ከሩቅ ሆነ ለመምራት የሚፈልግ፤ የዚህን ትውልድ ጭሆት የቀማ፤
ራዕዩን ያመከነ ትውልድ ሆኖ ይሰማኛል። በሌላ በእኩል የዚህ ትውልድ ትርፍራፊ የሆነው ነው፤ በአሁኑ ሰዓት ስልጣን ላይ ሆኖ ሀገሪቷን
እያመሰ ያለው። በተቃማዊው አከባቢም ቢሆን፣ በአመራር ደረጃ ያለው በአብዛኛው የዚያ ትውልድ አካል ነው። ከአርባ ዓመታት በኋላም
እንኳ የእነ አቶ ስዬ አብርሃ፣ አቶ ገብሩ አስራት እና ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ወደ ተቃውሞ ጎራ መቀላቀል ጩቤ ያስረገጠው፤ አሁን ደግሞ እነ
አቶ ለንጮ ለታ ወደ ሀገር ቤት መመለስ ነጋሪት እያስጎሰመ ያለው፤ እነዚህን የስልሳዎቹ ፖለቲከኞች የሚተኩ፤ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ወጣት
የፖለቲካ ልሂቃን ማፍራትና ማብቃት ስላልተቻለ ነው።
አሁን ወዳለው ወጣት ስንመጣ ደግሞ፣ ፕ/ር ገብሩ ታረቀ እንዳሉት አንድ ዓይነት የሆነ ወጥ መልክ ይዞ አናገኘውም። በዛሬ ጊዜ ያለው
አብዛኛው ወጣት በወላጆቹ፣ ወይም በአጠቃላይ ከእርሱ በፊት በነበረው ትውልድ ላይ የደረሰውን እልቂት እየሰማ ያደገ፤ አሁን ያለውን
የአለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጠቅላይነት ከፍተኛ ተፅዕኖ ያጠላበት፤ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ የመዝናኛ ሚዲያዎች፣ በእግር ኳስ፣
በኃይማኖት፣ በብሄር ተፅዕኖ ስር የወደቀ፤ ብሎም የተከፋፈለና ቀልቡ የተወሰደበት ወጥ የሆነ መልክ የሌለው ነው። ፕ/ር ገብሩ ታረቀ
ይህን ትውልድ በሶስት ይከፍሉታል። በመጀመርያ ደረጃ የሚመደበው የራሱን ህይወት ብቻ መኖር የሚፈልግ፤ የግሉን ጥቅም ብቻ
እየተከተለ የሚጓዝ፤ በዚህም ምክንያት ከማንኛውም ወገን ጋር ጥቅም እስካገኘበት ድረስ ከገዚው ፓርቲ ጋርም ቢሆን ተሰልፎ መስራት
የሚችል ነው።
ሁለተኛው፣ ስደት ያስገኘዋል ተብሎ በሚታሰበው ቁሳዊና ህሊናዊ ጥቅም ምክንያት ልቡ የሸፈተ፤ አሜሪካ እና አውሮፓ መሄድ
እንደዋነኛ ግቡ ያደረገ ወጣት ነው። ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሳ በተገኘው መንገድ ሁሉ
በእግርም፣ በመኪናም፣ በአውሮፕላንም በጀልባም ስራ ሊገኝበት ይችላል ወደ ተባለ ሀገር ሁሉ እየተመመ ያለው ወጣት በዚህ ሊጠቃለል
የሚችል ነው። በዚህ ምክንያትም ነው ለመገመት የሚከብድ መከራና ግፍ እየወረደበትና ውድ የሆነው ህይወቱን ጭምር እየከፈለ
እየተሰደደ ያለው።
የመጨረሻው ደግሞ፣ በተለያየ መልኩ አሁንም ለፖለተካዊ ለውጥ በሰላማዊ መንገድ እንደቀድምቶቹ እየታገለ የሚገኘው ወጣት ነው።
አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ በፖለቲካው መስክ ላይ ተሰልፎ የምናገኘው ወጣት በጣም ጥቂት የሚባል ቢሆንም በደንብ
የሚያደራጀውና የሚያነቃው ከተገኘ ሊደራጅና ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ለመገመት የሚከብድ አይደለም። እዚህ ላይ ያለው ዋናው
መሰረታዊ ችግር፣ ወጣቱ ሊሰለፍለት የሚችል ራዕይና ዓላማ በአግባቡ ማስያዝና ማስረፅ የመቻሉ ጉዳይ ነው። የዚህ ትውልድ ግቦች
ሊሆኑ የሚችሉት ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነትና ዴሞክራሲ ናቸው። እነዚህ ደግሞ ከዴሞክራሲያዊ ሰርዓት የሚመነጩ እንጂ ዝም ብለው
የሚገኙ ነገሮች አይደሉም።
ስለዚህ አሁን ላለው ወጣት የቤት ስራ ሆኖ የቀረበው፤ ዘላቂ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲመጣ፤ ከማንኛውም ፖለቲካዊ እና
ወታደራዊ ትፅዕኖ ነፃ የሆኑ ተቋማትና ህገ-መንግስት የመትከል አጀንዳ ነው። ከዚህም ባሻገር የጋራ እሴቶቻችን እስኪጠፉ ድረስ እጅግ
በጣም ጫፍ ድረስ የተለጠጠው የዘርና የጎጥ ፖለቲካ፤ ሀገሪቷን ለብተና፣ ህዝቧን ደግሞ ለእልቂትና ለመበታተን እንዳይዳርጋት እነዚህን
የመታደግ፤ የሀገሪቷን አንድነት የማስጠበቅ፤ ዴሞክራሲያዊት የሆነች፤ ሁሉም በእኩልነትና በፍትህ የሚኖርባት ኢትዮጵያን ማዋለድ የዚህ
ትውልድ ግብ መሆን ይኖርበታል።
በትግል ላይ መረባረብ ካብንም ትግላችን ለዚሁ ዋና ዓላማ መሆን አለብት። ደራሲው “ጥሩ ነው ወጣት መሆን” ያለው ለእንደዚህ
ዓይነቱ ወሳኝ ጊዜ የሚሆን ጠንካራ ትክሻ፣ ፅኑ ልብ እና የማያወላውል አቋም በመያዝ ግንባር ቀደም ሆኖ ተገቢ ሚናውን ሊጫወት
የሚችለው ወጣቱ በመሆኑ ነው።
በእርግጥ ፈረንጆቹ፣ “ፖለቲካ የጎልማሶች ስራ ነው።” (Politics is an adult business) የሚሉት ነገር አላቸው። በእርግጥም
ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረት በጣለባቸው ሀገሮች ፖለቲካ በእድሜ፣ በእውቀት እና በልምድ የበሰሉ ሰዎች ለመሪነት የሚወዳደሩበት
የህይወት መስክ ሊሆን ይችላል። ወደ እኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ስንመጣ ግን የተደላደለ ፖለቲካዊ ስርዓት፣ ነፃ የሆኑ ተቋማት በሌሉበት፤
እነዚህን መደላድሎች ለመፍጠርና እንዲኖሩ ለማድረግ በራሱ እህል አስጨራሽ ትግል የሚያስፈልገው በመሆኑ፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ
በእድሜና በእውቀት የበለፀጉ ብቻ ሳይሆኑ፣ እንያዳንዱ ወጣትም በብርታት እንዲታገል ያስገድዳሉ።
በተለይ ደግሞ ከዚህ በፊት ያለው ትውልድ፤ በተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች በተገቢው ሁኔታ ግንባር ቀደም መሪ ሆኖ ተገቢ
ሚናውን መጫወት ባልቻለበት አውድ፤ እርሱን ወደ ጎን በመተው በራስ መንገድ በአዲስ ሁኔታ ትግሉን ማስኬድና ግንባር ቀደም መሪ
ሆኖ መገኘት የግድ የሚል ነው።
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
February 26, 2014
No comments:
Post a Comment