Sunday, February 16, 2014

የአባይ ግድብና የአገዛዙ ተቃርኖዎች

ቴዎድሮስ ጌታቸው (ከኖርዌይ)                                                                     

 የካቲት 10 2006   
                                                    
በአለም የወንዞች ታሪክ እንደ አባይ የተዘፈነለት፤ የተዘመረለት ወንዝ ያለ መቸም አይመስለኝም በአለም በእረጅምነቱ የሚስተካከለው የሌለው አባይ በትውልድ ሃገሩ  ከዘፈን  ግጥምና ከእንጉርጉሮ አድማቂነት ያለፈ ጥቅም ሳይሰጥ ለዘመናት ያለማቋረጥ መፍሰሱ እርግጥ ነው።   ከወቀሳ እስከ ሙገሳ  ከቁጭት እስከ ብስጭት ብዙ ብዙ ተብሎለታል ለአባይ ያልዘፈነ ዘፋኝ ያልገጠመ ገጣሚ ያልተቀኘ ባለቅኔ ማግኝት  ይከብዳል እናም አባይ ለቁጥር የሚታክቱ የስነጥበብ ጉዳዮችን አስተናግዷል። 
                                             


«አባይአባይ… አባይአባይ
የአገር አድባር  ያገር ኩራትየአገር  ሲሳይ... »                                                                                       ተብሎ ተዘምሮለታ                                                                                                                   

«አባይ ስም ነው' ምን ሰርቷል ላገሩ
ትርፉ ለሌላ ነው ሄዶ መገበሩ... »                                                                                            ተብሎ  ተዚለታ

ባለ ቅኔው ሎሬት ፀጋዬ /መድህን እሳት ወይ  አበባ በተሰኘው የግጥም መድብላቸው ስለ አባይ በፃፉት ስንኝ እንደዚህ ተቀኝለውታል
 «..
አባይ የምድረ ዓለም ሲሳይ
የቅድመ-ጠቢባን አዋይ
አባይ የጥቁር ዘር ብስራት
የኢትዮጵያ ደም የኩሽ እናት
የዓለም ስልጣኔ ምስማክ
ከጣና በር አስከ ካርናክ
በእቀፍሽ ውስጥ እንዲላክ
መመለክ በመመስገን
ጽላትሽ ከዘመን ዘመን
በአዝዕርትሽ አበቅቴሽ ሲታጠን
አቤት አባይ ላንቺ መገን.....

አድርጎሽ ቅድመ ገናና
ዛሬ ወራቱ ራቀና
ምድረ-ዓለም ችን አድናቆት
ፈለጉን መሻት ተስኖት
እንዲህ ባንቺ መንከራተት
ታሪክ ወሮታሽ ጠፍቶበት
ትላንት በባዕድ ጩኸት
ዛሬም ባላዋቂ ሁከት
ቋንቋ ለቋንቋ ቢራራቅ
የቅድሚያሽ ንድፍ ላይፋቅ
እዚህ ደማም እዚያ ተማም
መባልሽ ብቻ ባይበቃም
የቅርስሽ ጭብጥ ይዞታ
ሆሄታሽ እስካልተፈታ….....»  
እንደዚህና እንደዛ እየተባለለት በሃገሩ ከኪነጥበብ ፋይዳነት ብዙም ፈቀቅ ያላለ ጥቅም ሳይሰጥ የኖረው አባይ ለባዕድ ሃገራት ግን የህይወት ምንጫቸው በመሆን በሁሉም እረገድ ሲያገለግላቸው ከመኖሩ የተነሳ መነሻውም መድረሻውም የነሱና የነሱ ብቻ እስኪመስላቸው ድረስ በምድራቸው ያለማንም ከልካይ ለዘመናት ፈሷል።


ከጥንታዊያን የኢትዮጵያ ነገስታት ጀምሮ አባይን የመጠቀም ፍላጐትና ሙከራዎች ቢኖሩም የተሳኩ ግን አልነበሩም ላለመሳካቱም በአብዛኛው የእነዚሁ የባዕዳን እጆች ትልቁን ሚና ይይዛል ይሁንና ከውጪው ሃይሎች ተጽህኖ በተጨማሪም ሃገሪቷ ከውስጥም ከውጪም በሚነሱ ያላቋረጡ ጦርነቶች መዘፈቋ ላለመሳካቱ በምክንያትነት ይነሳሉ።

በተለይም የቀዳማዊ ሃይለስላሴ መንግስት አባይን ለመገደብ ሰፊ እቅድ ይዞ እቅስቃሴ ማድረጉን የሚገልጹ መረጃዎች በብዛት አሉ እስከ አሁንም ድረስ የሚያገለግሉት ወንዙ በሚመለከት የተደረጉ ጥናቶች በዛን ዘመን የተደረጉ መሆኑ ይነገራል።  ይሁንና   ወንዝ ዙሪያ .. 1929 ጀምሮ የተለያዩ ስምምነቶችና ድርድሮች ሲካሄዱ ቢቆዩም ሁሉም ስምምነቶችና ድርድሮች አብኛውን የውሃ መጠን የምታበረክተው ኢትዮጵያን ያላሳተ ከግምት ውስጥ ያላስገቡ ነበሩ።  በዚህም ሰበብ ኢትዮጵያ አባይን  ለመጠቀም በምትሞክርበት ወቅት ሁሌ ተቃውሞ ሲገጥማት ቆይቷል  ስለሆነም ቀደም ያሉ ስምምነቶች የግብጽ እና የሱዳንን ጥቅም የሚያረጋግጡ ሆነው በመቆየታቸው ኢትዮጵያ ይን በእንጉርጉሮ ለመሽኝት ለዘመናት ተገዳለች


1929 እና 1959 የተፈጠሩት የቅኝ ግዛት ስምምነቶች በመሆናቸው እንዲሁም የተፋሰሱ የላይኛው ሀገራትን ያገለሉ፤ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የሌላቸውና ሊኖራቸውም የማይችሉ በመሆናቸው በወቅቱ ከቀኝ ግዛት ነፃ የነበረችው ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ  ይህንኑ ይ ለማሳሰብ ሞክራለች  አፄ ኃይለስላሴ 1957 ለሱዳንና ለግብፅ ይህንኑ በሚመላከት የፃፉት ደብዳቤ በተፋሰሱ የላይኛው አገራት ያለው ፖሊሲ ብቻችንን እንልማ የሚል  ሳይሆን በአባይ አጠቃቀም ላይ ያላት አቋም «በጋራ እንጠቀም » የሚል  እንደነበረ ተነግሮዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱም የአፄ ሃይለስላሰሴ መንግስት ይጠቀምበት የነበረው የ 50 ብር ኖት ላይ የነበረው ምስል የአባይ ግድብ ዲዛይን እንደሆነ በብዙዎች ይታመናል ይኅም ወንዙን ለመገደብ በወቅቱ የነበረውን ትልቅ ፍላጎትና ሙከራዎች ያሳያል
(የወቅቱ የአባይ ወንዝ ግድብ ንድፍ 1953. በቀ. . ሥላሴ 50ብር ኖት ላይ)

ይህንን የመሳሰሉ ጥረቶች በየግዜው በነበሩ መንግስታት ቢደረጉም የተሳኩ ግን አልነበሩም  ከዛን ግዜም በኋላ ሃገሪቷ የነበረችበት ያላቌረጠ የእርስ በእርስ ጦርነት እና የገባችበት አስከፊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር አባይን ለመገደብ የማይቻል ብቻ ሳይሆን የማይታሰብ እንዲመስል አድርገውት ቆይተዋል።
ከጥቂት አመታት በፊት የተጀመረው የአባይ ግድብም ከመነሻው  ትልቅ ውዝግብ ያስነሳ እና አሁንም እያስነሳ እንዳለ የታወቀ ነው አባይ በመገደቡ ላይ ልዩነት ባይኖርም ገዥው መንግስት ግድቡን ለተለመደውና የፕሮፓጋንዳው ዘመቻ ፍጆታው ለማዋል መራወጡ  ብዙኋኑን ያላስማማ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞ ያነሳሳ ሆኖል ኢትዮጵያውያንን በጠቅላላ ሊመለከትና ሊያገባ የሚገባው ፕሮጀክት እዳው የሁሉም ጥቅሙ የጥቂቶች መሆኑ ኢትዮጵያውያንን አንድ ከማድረግ ይልቅ ለመከፋፈል በቅቶአል።

በስልጣን  ላይ ያለው አገዛዝ የፓርቲና የመንግስት  ልዩነት ከሁለት አስርትአመታት በላይ ሥልጣን ላይ ቆይቶ እንኳን መለየት ያልቻለ ሲሆን ሀገሪትዋ ውስጥ የሚካሄደው ጉዳዮች  በጠቅላላ ለእርካሽ የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ማዋሉና ለብሄራዊ መግባባት ምንም አይነት እድል ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ከአገዛዙ ጋር ለመተባበር ያላቸውን ፍላጐት ያጠፋ ክስተት ሆናል።

በሃገሪቷ ሃብትና ንብረት የሚታቀዱና የሚሰሩ ስራዎች የአገዛዙና የደጋፊዎቹ  ግኘት ተደርገው መወሰዳቸው ሃገር ውስጥ የተንሰራፋው የሰብአዊ መብት ጥሰት፤ በየእስር ቤቱ ታጉረው ያሉት ዜጎች ጋዜጠኞችና፤ ፖለቲከኞች እንዲሁም አገዛዙ የሚከተለው የከፋፋለህ ግዛው ውጤቶች የሆኑት የብሄሮችና የሃይማኖት ዙሪያ የተፈጠሩ ውጥረቶችና ልዩነቶች ስር የሰደደውን የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር እጦት ከተቃዋሚው ሃይል ጋር በመግባባትና በመቻቻል ችግሮችን ለመፍታት ምንም አይነት ፍላጐት አለመኖር ዜጐች ተገደው እና ፈርተው ካልሆነ በፍቃደኝነት ከአገዛዙ ጋር ለመተባበር እንደማይፈልጉ የአደባባይ ሚስጥር ነው።

በአንጻሩ የግብፅ መንግስት በአባይ ጉዳይ ላይ ከተቃዋሚዎቹ ጋር ተሰብስቦ በየግዜው በመወያየት በሃገራቸው ጉዳይ ሁሉም ግብፃዊያን እኩል የሚያገባቸውና የሚመለከታቸው መሆናቸውን አሳይቷል በርግጥ ይሄ ኢትዮጵያ ውስ ላለው አገዛዝ ትልቅ ትምህርት ሊሆን ይገባ ነበር የሆነው ሆኖ በአንድ ሃገር ጉዳይ ላይ አንዱ ብቻ አዛዥና ናዛዥ ሆኖ እስከ መጨረሻው መቀጠል እንደማይቻል የሩቁ ብቻ ሳይሆን በጣም የቅርብ ታሪኮች ደግመው ደጋግመው አሳይተዋል።  ለማንኛውም ግብፃውያንን አንድ ያደረገው የአባይ ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው አገዛዝ በሚያሳየው ግብዝነት የልዩነት ምንጭ ሆኖ ቀጥሎዋል ለዚህም ማሳያው በየውጪ ሃገራቱ ለአባይ ግድብ ቦንድ ማሰባሰቢያ  የተካሄዱት ዝግጅቶች አንዳቸውም እንኳን አለመሳካታቸው በቂ ማሳያ ነው ለዚህ ደሞ አገዛዙ ተጠያቂ መሆኑ እርግጥ ነው።

አባይ የሚገነባው በኢትዮጵያውያን ገንዘብ ፤ጉልበት፤ ሃብት ነው በተጨማሪም በኢትዮጵያውያን ስም በሚበደሩት ገንዘብ ነው ስለዚህ ጉዳዩ የህዝብ በመሆኑም የአገዛዙና የደጋፊዎቹ የግል ጉዳይ  መሆኑ አብቅቶ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በሂደቱ መሳተፍ ይኖርባቸዋል።

ከዚህ በተረፈ አባይን ለመገደብ ዙኝ ልቀቁኝ የሚለው መንግስት እግረመንገዱንም የሰብአዊ መብት ጥሰትንም፤ ሞልቶ የፈሰሰውን የህዝብ ብሶት አብሮ መገደብ ይኖርበታል።  አገዛዙ በግለሰብ ነፃነት፤ በሃይማኖት ጉዳዮች ውስጥ፤ ሀሳብን በመግለፅና፤ በመምረጥና መመረጥ መብት ውስጥ ጣልቃ ገብቶ የሚያደናቅፈውን ህገወጥ ተግባራት  አብሮ ለመገደብ መነሳት ይገባዋል።  ኢትዮጵያ ሊገደቡ የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች የታጨቁባት ሃገር ነች ስደትና የስደት መንስኤዎቹ ሊገደቡ ግድ ይላል የኑሮ ውድነቱ፤ ዘረኝነትና፤  ሙስናው ሊገደብ ይገባዋል  ቦንድ የማያስፈልጋቸው የቻይና ብድር የግብፅ እሰጥ አገባ የማይኖራቸው ብዙ ግድቦች ያስፈልጋሉ  ያለበለዚያ አባይ ቢገደብ ለብቻው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ እንዲሁም መፍቻና መፍትሄ ባለመሆኑ አገዛዙ የፕሮፓጋንዳ እረፍት አድርጐ ወደራሱ ቢመለከት ለሁሉም ይበጃል።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ፀሐፊውን ለማግኘት: thhe2011@gmail.com





1 comment:

  1. ፋክት፡- የህዳሴውን ግድብ በሚመለከት
    የዲያስፖራው አቋም ምን እንደሚመስል ልትነግረን
    ትችላለህ?
    ታማኝ፡- ይኸውልህ፤ እዚህ ግራና ቀኙን
    የምትመረምርበት እድል አለ። የምንኖረው
    የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን እያየንና የመንግስት
    ፕሮፓጋንዳን ብቻ እየሰማን አይደለም።
    እንደምራለንም፤ እንቀንሳለንም። በዙሪያ ባሉ
    ጠላቶች በአይነ-ቁራኛ የሚታይ ይሄን መሰል
    ፕሮጀክት መገንባት የነበረበት፣ የጠበቀ አንድነት
    በፈጠረ ማህበረሰብ መካከል ነው። ከኢትዮጵያ
    ህዝብ በተሻለ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ የሚገኘው
    ዳያስፖራ፣ ይህን ግድብ ለመስራት ፈቃደኛ
    ነው። ውጪ ያለውን ሰው በቀላሉ ልታታልለው
    አትችልም። ሊታሰርበት የማይችልበት ቦታ
    ስለሚኖር ሀሳቡን በነፃነት ይገልፃል። ከዚያ በፊት ግን
    የሚስተካከሉ ጉዳዮች ሊኖሩ ይገባል። መጀመሪያ
    አንድ ለአምስት የተቆለፈውን ህዝብ መፍታት፣
    ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር ያስፈልጋል። ይህ
    ከሆነ መንግስት ካሰበው በላይ ሊያደርግ የሚችል
    አቅም ዲያስፖራው ዘንድ አለ። ይሄ መልስ ካላገኘ
    ዲያስፖራው እድሜ ማራዘሚያ ሊሆን አይችልም።
    በአባይም ጉዳይ ያለው ክርክር ይሄው ነው። የዜጎች
    መብት በቅድሚያ መከበር አለበት። ስለኢትዮጵያ
    ሲሉ የፃፉ፣ ስለኢትዮጵያ ሲሉ የታሰሩ መፍትሄ
    ከተገኘላቸው፣ በአባይ ጉዳይ የማንስማማበት ምንም
    ምክንያት የለም። ይሄ የዲያስፖራውም፣ የእኔም
    አቋም ነው።

    ReplyDelete