‹‹የውስጡ ሽኩቻ እንዲህ ባለ ድፍረት ሊቀለበስ ይችላል፡፡ ጊዜያዊው የግብፅ መንግሥት ዜጐቹን ለማሳመን የፈጠረው መላ ሊሆን አይችልም? ከሙርሲ ጥፋት ለመማር ፈልጐ መሆኑ ደግሞ ይገርማል፤››
ይህንን ያለው ብሩክ በርሀ የሚባል ወጣት ሲሆን፣ የዓባይን ወንዝ በተመለከተ በቅርቡ ሕዝበ ውሳኔ በተሰጠበት አዲሱ ሕገ መንግሥት የተካተተውን አንቀጽ አስመልክቶ በማኅበራዊ ድረ ገጽ በሰጠው አስተያየት ነው፡፡
ጉዳዩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ውስጣዊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የሚያደርጉትን ክርክር የቀለበሰ ይመስላል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ በሰሜን አፍሪካዊቷ ቱኒዝያ የተለኮሰው ‹‹የዓረብ አብዮት›› እየተባለ በሚታወቀው ለተወሰኑ የዓረብ አገሮች መሪዎች ከሥልጣን መነሳት ምክንያት የሆነው ክስተት በግብፅም ጦሱ ዛሬም እንዳለ ነው፡፡
ይህ በግብፅ የቆየ አለመረጋጋት እየቀጠለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ይፋ ማድረጓ የሁለቱንም አገሮች ግንኙነት አወሳስቦታል፡፡
አዲሱ መላ
የግብፅ መሪዎች ቀደም ሲል እ.ኤ.አ. በ1929 እና በ1959 በቅኝ ግዛት ዘመን ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችባቸውን ስምምነቶች ሁሌም ‹‹ታሪካዊ መብት›› ይሉታል፡፡ ግብፅ በብቸኝነት በወንዙ የመጠቀም የቆየ ልማድን ሕጋዊ ከለላ የሚሰጡ ነበሩ እነዚህ ስምምነቶች፡፡ ግብፆች በመጨረሻ እንቢተኛ ቢሆኑም፣ በአግባቡ መሠረት ከአሥር ዓመታት ድርድር በኋላ በስድስት አገሮች የተፈረመው የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የትብብር ማዕቀፍ (CFA) ሕግ ሆኖ ፀድቋል፡፡ የሚቀረው ነገር ቢኖር ለተግባራዊ ተፈፃሚነቱ እያንዳንዱ ፈራሚ አገር በፓርላማው ማስፀደቅ ብቻ ነው፡፡ ይኼው የአሥር የተፋሰሱ አባል አገሮች የአሥር ዓመት ድርድር ውጤት የሆነው ሕግ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አገሮች ውኃውን በኃላፊነትና በፍትሐዊነት የመጠቀም መብት የሚያጐናጽፋቸው ብቻ አይደለም፡፡ ግብፃዊያን ቀን ከሌሊት የሚጠቅሷቸው፣ በአባል አገሮቹን ግን ዕውቅና የሌላቸው የቀድሞዎቹ የቅኝ ግዛት ‹‹ስምምነቶች››ን የሚሽር ነው፡፡ ስለዚህ የውኃ ደኅንነት፣ ታሪካዊ የመጠቀም መብትና የቀደሙ ስምምነቶች የሚሉ አስተሳሰቦች ምንም ተቀባይነት እንዳይኖራቸው እንዳደረገ ለብዙዎች ግልጽ ነው፡፡
አሁን ያለው የግብፅ የሽግግር መንግሥት በወታደራዊ ኃይል አማካይነት የተቋቋመ በመሆኑ ቀደም ሲል የሕገ መንግሥቱ አንኳር የነበሩት እስላማዊ መርሆዎችን በማስወገድ፣ ዓለማዊ የሚመስል ሕገ መንግሥት መረቀቁን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ለወታደራዊ መንግሥት ያልተወሰነ መብት የሚሰጥ መሆኑም ይነገራል፡፡
ይኼው ባለፈው ሳምንት ሕዝበ ውሳኔ የተሰጠበትና ውጤቱ ይፋ ያልሆነው ሕገ መንግሥት በብዙዎች እንደተጠበቀው አገሪቱ ከገባችበት ቀውስ ሊታደግ ይችላል ተብሎ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም በአገሪቱ ያሉት የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች የሚያስደምጧቸውን ዕይታዎችና ልዩነቶች የሚያስተናግድ አይደለም በሚል አስተያየት ይሰማል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተካተተው ሌላ ጉዳይ ግን የዓባይን ወንዝ በተመለከተ ለተፋሰሱ አባል አገሮች አሳሳቢ የሆነው በአንቀጽ 44 ላይ የሠፈረው ነው፡፡ የአንቀጹ ይዘት እንዲህ ይነበባል፡፡
‹‹መንግሥት የዓባይን ወንዝ ደኅንነት የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ የግብፅ ታሪካዊ የመጠቀም መብትን ያስጠብቃል፡፡ ዜጐች ከወንዙ የሚያገኙት ጥቅምም የላቀ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ወንዙን ከብክለትም ሆነ ከብክነት ይጠብቃል፡፡ በወንዙ ውስጥ የሚገኘውን ተፈጥሯዊ የማዕድን ሀብት ይጠብቃል፤ የውኃውን ደህንነትን የሚያስጠብቁ ማዕቀፎች ይነድፋል፡፡ በወንዙ ላይ የሚካሄዱ ሳይንሳዊ ምርምሮችንም ይደግፋል›› የሚል ግርድፍ ትርጉም አለው፡፡
እንዲህ ዓይነቱ አንቀጽ በቅርቡ በፕሬዚዳንት ሙርሲ ዘመን የተረቀቀውን ጨምሮ በቀደሙት የአገሪቱ ሕገ መንግሥታት ያልተለመደ ሲሆን፣ የተለያዩ አንድምታዎች እየቀረቡ ነው፡፡ የተስፋ መቁረጥ ምልክት መሆኑንም ተንታኞች ይናገራሉ፡፡
ግብፅ ይህንን አንቀጽ በሕገ መንግሥቷ ያካተተችበት ወቅት ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ሲያደርጉት የነበረው የሦስትዮሽ የድርድር ስብሰባ ያለ ውጤት በተጠናቀቀ ማግሥት ነው፡፡
‹‹የውሸት ጡጦ››
በዚሁ አንቀጽ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡት ምሁራን መካከል የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቁና በዓባይ ወንዝ ላይ የመመረቂያ ጽሑፍ የሠሩት አቶ ወንድወሰን እማየ ሚጫጐ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢጋድ ውስጥ የሙያና የተዛማጅ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት አቶ ወንድወሰን፣ እንዲህ ዓይነት አንቀጽ በግብፅ በሕገ መንግሥት በመስፈሩ በተፋሰሱ አባል አገሮች ላይ ይኼ ነው የሚባል ተፅዕኖ የሚኖረው አይሆንም ይላሉ፡፡
‹‹ሆኖም ግን ግብፃዊያን አሁንም ባረጀና ባፈጀ ፋሽን ላይ ለመሆናቸው ትልቅ ማሳያ ነው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡ አንቀጹ የተካተተበት ዋነኛ ምክንያት ግን መንግሥት በዓባይ ወንዝ ላይ የግብፅን መብት እያስከበረ አይደለም በሚል በተለያዩ ፖለቲከኞች ለሚቀርብበት ትችት ማሳመኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፖለቲከኞቹ ሕዝቡን በቀላሉ ለማሳመን ያህል ነው፡፡ ልክ ለሕፃን የውሸት ጡጦ እንደመስጠት ነው፤›› ብለዋል፡፡
የታላቁ የዓባይ ግድብ ፕሮጀክት ይፋ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ ሲያሳዩዋቸው የነበሩ የተለያዩ ተለዋዋጭ አቋሞች የሚያዝ የሚጨበጥ ማጣታቸውን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
‹‹በቅርቡ በተደረጉ ድርድሮች በግብፅ በኩል ከቀረቡ አቋሞች የግድቡን የውኃ መጠን በተመለከተ ጥያቄ ማቅረባቸው፣ ግድቡን በጋራ ለመገንባት መነጋገር መፈለጋቸው የግድቡ ግንባታ ወደ ኋላ እንደማይመለስ ማሳያ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ግብፆች ከዚህ በፊት የሚተማመኑበት በተለይ እ.ኤ.አ. በ1959 በሱዳንና በግብፅ መካከል የተደረገው የውኃ ክፍፍል ስምምነት አደጋ ላይ መውደቁንም ማሳያ ነው ይላሉ፡፡ ሱዳን በግብፅ ላይ ፊቷን ማዞሯና የኢትዮጵያን አቋም መደገፏ ለግብፆች የመጨረሻ ሞት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
‹‹አሁን ወደ ሕገ መንግሥት መግባታቸው እ.ኤ.አ. ከ1959 ስምምነት መሸሽ ነው፡፡ ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ በቃ ስደት በለው፡፡ ሁለት ባላ ትከል አንዱ ሲሰበር በአንዱ ተንጠልጠል እንደሚሉት ነው፤›› ብለው፣ በራሱ ዕርምጃው አደጋ ነው ብለዋል፡፡ የተፋሰስ አባል አገሮች በወንዙ ላይ ያላቸውን ፖሊሲ ለማስታረቅ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ወጪ ሲያደርጉበት ለቆየው ለናይል ተፋሰስ ኢንሼቲቭ ትልቅ ኪሳራ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
‹‹ውኃውን ለብቻችን እንጠቀማለን፣ ሌሎችን እንዳይነኩም እንጠብቃለን የሚል ትርጉም አለው፤›› የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የዓባይ ግድብ የሦስትዮሽ ተደራዳሪ ቡድን አባል የሆኑት ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ናቸው፡፡
‹‹በተዘዋዋሪ ይህ ፀብ አጫሪ አንቀጽ ነው፤›› የሚሉት ዶ/ር ያዕቆብ፣ ‹‹እያንዳንዱ ዜጋ የመጠቀም መብት አለው፤›› ስለሚለው ክፍል ይናገራሉ፡፡ ‹‹እያንዳንዱ ግብፃዊ የዓባይን ውኃ መጠቀም አለበት፡፡ መጠቀም አለበት፡፡ ጥሪ ሲደረግለት መምጣት አለበት፡፡ ሌሎች ይህንን የሚጠቀሙ ኃይሎች መከልከል አለባቸው፤›› የሚል ትርጉም እንዳለው ያብራራሉ፡፡
በመቀጠልም የአሁኑ መንግሥት ከቀደሙት ሁሉ ለግብፅ ሕዝብ ጥቅም ቆሜያለሁ የሚል ትርጉም እንዳለው አዲስ ብሔርተኝነት የሚቀሰቅስና ሕዝብን የሚያነሳሳ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ የውስጥ ችግራቸውን ለመግፋት የሚያደርጉት ጥረት ቅጥያ መሆኑንም አክለዋል፡፡
‹‹በሰው አገር ሕገ መንግሥት ምንም ማለት አይቻልም››
ሪፖርተር ያነጋገራቸው አራት የውኃ ባለሙያዎች በአንድ ነገር ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አንቀጹ በተጋሪ አገሮች መካከል የፈለገውን ያህል አለመተማመን ቢፈጥርም፣ ‹‹ሕገ መንግሥታችሁ አሻሽሉ፣ እንዲህ ብላችሁ ለምን ጻፋችሁ ብሎ መናገር አይቻልም፤›› የሚል፡፡
‹‹በግብፅ ሕገ መንግሥት እንዲህ ዓይነት አንቀጽ ሠፈረም አልሠፈረም አባል አገሮቹ ውኃቸውን ከመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ድርድሩ የሚቀጥል ከሆነ በጊዜው ጉዳዩን ማንሳት ተገቢ ቢሆንም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መቃወምና መግለጫ መስጠት ግን ብዙም አስፈላጊ አይለደም፤›› ብለዋል ዶ/ር ያዕቆብ፡፡
ተባባሪ ፕሮፌሰርና የሕግ ባለሙያው ዶ/ር ያሬድ ለገሰ መንግሥቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት አንቀጹ በሕገ መንግሥት ውስጥ መካተቱ ያልተለመደ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡
በስፔንና በፈረንሳይ ሕገ መንግሥቶች የአገር ግዛት አንድነት የሚነጣጥል ነው የሚሉ ተመሳሳይ ሕጐች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹እንዲያውም ባያካትቱ ነበር የሚገርመው፤›› በማለት፡፡ በተለይ የኢትዮጵያን የመጠቀም መብት ከግምት ያላስገባ መሆኑን፣ እንዲሁም በቀጣዩ እንዴት እንደሚተረጉሙት አስቸጋሪ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹በኢትዮጵያም ላይ ችግር መፍጠሩ አይቀርም፤›› በማለት፡፡ በተለይ አንዳንድ አገሮች እንዳደረጉት የማይሻሻል አንቀጽ ከሆነ ደግሞ የበለጠ አስቸጋሪ ይሆናል ብለውታል፡፡ ‹‹ሆኖም በሰው አገር ሕገ መንግሥት ላይ መንም ማለት አይቻልም፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
‹‹ግትርነታቸው ያባብሳል››
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር አቶ ዘሪሁን አበበ በበኩላቸው፤ በግብፅ ሕገ መንግሥት ውስጥ መሥፈሩ ምንም የሚያመጣው ነገር የለም ይላሉ፡፡ ከዚህም በፊት ግትር አቋም የነበራቸው ግብፃዊያን በሚያደርጉዋቸው የውኃ አጠቃቀም ድርድሮች ግን የባሰ ግትር እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡ ከፖሊሲ ወደ ሕገ መንግሥት መሸጋገሩን በመግለጽ፡፡
ሆኖም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉት የውኃ ስምምነቶችና የትብብር መርሆዎችን የሚገዛ ሕገ መንግሥት አይሆንም ይላሉ፡፡ ‹‹ከሕጐች ሁሉ ያፈነገጠ አንቀጽ ነው፤›› በማለት፡፡
ምሁራኑ በጉዳዩ ላይ የተስማሙበት ሌላው ጉዳይ፤ አንቀጹ የገባበት ምክንያት ሲሆን፣ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ እየተገነባ ባለበት ሁኔታ መሆኑ ተስፋ የመቁረጥ ምልክት ነው ይላሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱን በማርቀቅ ረገድ የተሳተፉ በቁጥር 50 የሆኑ ሰዎች ሊቀመንበር ዑመር ሙርሲ ሲባ፣ በ1990ዎቹ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩ ናቸው፡፡
የዓባይ ጉዳይ በውጭ ፖሊሲ እንዲካተት ያደረጉ ከመሆናቸውም በላይ፣ ቀደም ሲል የዓረብ ሊግ ሊቀመንበር የነበሩና በኢትዮጵያ ላይ ሁሌም መልካም ያልሆነ አመለካከት ያላቸው ናቸው በማለት አቶ ዘሪሁን ያስረዳሉ፡፡
ሌሎቹ የአልአሐራም የፖለቲካና የስትራቴጂ ጥናት ማዕከል ተመራማሪዎች ሲሆኑ፣ የግድቡን ጉዳይ በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩና ግንባታው እንዲቋረጥ ሲጠይቁ የቆዩ ናቸው፡፡
መቋጫ የሌለው ጦስ
ገጽታውን እየቀያየረ የሚከሰተው የግብፅ አብዮት የዕድሜ ልክ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሆስኑ ሙባረክ ከተባረሩ ጊዜ ጀምሮ አገሪቱ በየቀኑ አዲስ የአመፅና የትርምስ መናኸሪያ እየሆነች ነው፡፡
እ.ኤ.አ. ግንቦት 2012 በተካሄደው ምርጫ በጠባብ ልዩነት ተቀናቃኛቸውን አሸንፈው ግብፅን በፕሬዚዳንትነት መምራት የጀመሩት መሐመድ ሙርሲ፣ ካደረጓቸው ማሻሻያዎች መካከል አዲስ ሕገ መንግሥት ማፅደቅና አዲስ ፓርላማ ማቋቋም ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱን በምርጫ ከማሸነፋቸው ቀደም ብሎ፣ የአገሪቱ ፓርላማ እሳቸው በሊቀመንበርነት የሚመሩት የሙስሊም ወንድማማቾች የበላይነት ቁጥጥር ሥር ነበር የወደቀው፡፡ አብዮተኞቹ የፈለጉት ለውጥ አልመጣላቸውምና አመፁ ቀጠለ፡፡ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ እንደገና የመንግሥት ለውጥ ተካሂዶ በምርጫ የመጡት ሙርሲ በጦር ኃይሉ ተሳትፎ ከሥልጣናቸው ተወግደዋል፡፡
ከቅኝ ግዛት ጀምሮ ግብፃዊያን ዓባይን ከሥሩ ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ አንዳንድ መዛግብት እንደሚጠቁሙት ደግሞ አገሪቱን ‹‹የዓባይ ስጦታ›› አድርገው የሚቆጥሩ ግብፃዊያን፣ መነሻው ኢትዮጵያ የሆነውን የዓባይ ወንዝ ለመቆጣጠር ያለው ፍላጐት እስከ ዝነኛው የፈርዖን ዘመነ መንግሥት የሚዘረጋ ነው፡፡
በቅርቡ የታሪክ ትዝታ ግን በተለይ በዶጋሊ በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት በራስ አሉላ አዝማችነት ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ ግብፆች የከፈቱት ጦርነት ያለ ታሪክ ነጋሪ ድል የሆኑበት ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሕይወት ዘመናቸው ግብፅን በተመለከተ ከተናገሩዋቸው አስደናቂ ንግግሮችም ይኼው ይገኝበታል፡፡
የአሶሼትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ ‹‹ግብፅ አገርዎን ብትወርስ?›› በማለት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹እንግዲህ ኢትዮጵያን የወረሩ ቀደምት አባቶቻቸው በጦርነቱ የሆነውን ታሪክ መልሰው መናገር የሚችሉ አልነበሩም፡፡ የአሁን ፖለቲከኞች ይህንን ታሪክ ይዘነጉታል ብዬ አላስብም፤›› የሚል ነበር ምላሻቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌላ ጊዜ ታላቁ የዓባይ ግድብ ፕሮጀክት ይፋ በሆነ ሳምንት ከፓርላማ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፣ ‹‹ያረጁ ያፈጁ›› ያሏቸውን ሦስት ዋና ዋና ስትራቴጂዎች ተናግረው ነበር፡፡
ኢትዮጵያን መከፋፈል፣ ኢትዮጵያን ማደህየትና ኢትዮጵያን ማተራመስ፡፡ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አማፂዎችን መርዳትና ማስታጠቅ፣ ኢትዮጵያን ለማደህየት አገሪቱ የዓባይን ወንዝ ምንም ዓይነት የልማት ተግባር እንዳታከናውን የውጭ ዕርዳታ ማስከልከልና በዓለም አቀፍ የዕርዳታ ተቋማት ውስጥ የተሰገሰጉ የግብፅ ከፍተኛ ባለሙያዎችና ዲፕሎማቶች ሥራ ነበር ብለው ነበር፡፡
እነዚህን ስትራቴጂዎች ግምት ውስጥ ያስገቡ ይመስል ታላቁ ግድብ ያለምንም ዕርዳታ በራሱ በመንግሥትና በሕዝቡ ጥረት ለመገንባት የ80 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት በድፍረት ይፋ አድርገዋል፡፡
ግብፆች ኢትዮጵያውያን ግድቡን በገንዘብ እጥረት ምክንያት ያቋርጡታል የሚል እምነት የነበራቸው ቢሆንም፣ ይህ እምነታቸው እየተሸረሸረ የመጣ ይመስላል፡፡ ሰሞኑን ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለማናቸውም ጉዳዮች ኢትዮጵያን መርዳት እንዲያቆሙ እየወተወቱ ናቸው፡፡ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ለመውሰድም መነሳታቸውን እየተናገሩ ናቸው፡፡
No comments:
Post a Comment