Thursday, January 23, 2014

“አገርህን አድን”

1

 ትዝብት ቁ.21 ጥር 11 -2006 ዓ.ም.(19-01-2014)
 “አገርህን አድን”
እናት አባት ቢሞት ባገር ይለቀሳል፣
አገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል።
የናት አገር ጋቢ ያባት አገር ሸማ፣
ነጠላ አይደለም ወይ የሰው አገርማ።፣
አዎ የቤተሰብ አባል በድንገተኛ አደጋ ወይም በበሽታ በሞት ቢለይ ከቀሪ ወዳጅ ዘመድ ጋር ተላቅሶና ተባብሮ ተወልዶ
ባደገበት ወይም በኖረበት አገር መሬት አፈር የማልበሱ ወግና ባህል የተለመደ ነው።ሃዘንና ብሶቱንም ከቀን ብዛት፣
ከቤተሰብና ጓደኛ ድጋፍና ማበረታታት ጋር ይጽናኑታል፤ይህ ሁሉ የቤተሰብ፣ የጓደኛውና የጎረቤቱ የማጽናናቱ ድጋፍ
የሚገኘው ይህን የመሰለው ልማድና ባህል የሚያስተናግድ ሕዝብ የሚኖርበት አገር በመኖሩ ነው። ሃዘኑና መከራው
ቀለል የሚለው በሚያውቁትና በለመዱት፣የኔነው ብለው በሚቀበሉትና በሚያምኑበት አገርና ህብረተሰብ መሃል ሲኖሩ
ነው።ደስታውም እጥፍ ድርብ የሚሆነው በዛው በተወለዱበት አገርና በሚያውቁት ህብረተሰብ መካከል ሲሆን
ነው።ጩኸው በማያለቅሱበት፣ይሉኝታና ፍርሃት በሰፈነበት አካባቢ፣በተለይም በስደት ፣ ሃዘን ሳይወጣ የእግር ውስጥ
እሳት እንደሆነ ይቀራል፡፤ደስታውም ቢሆን እንዲሁ ሙሉ በሙሉ የሚያረካ ሳይሆን ከአንገት በላይ ይሆናል።
አገር የሃዘን ወይም የደስታ መድረክ፣ በልተውና ጠጥተው የሚኖሩበት ቦታ ብቻ አይደለም። የማንነት ምንጭና
መግለጫ፣የታሪክ ፣የመከበሪያ ፣በቋንቋ፣በእምነትና በባህል ተሳስረው የሚኖሩበት፣ትውልድ እየተቀባበለ
የሚረከበው፣የጋራ ንብረት ነው።የአገር መኖር የዜጎች የመኖር ወይም ያለመኖር ጥያቄ ነው። ስለሆነም አገር ከሌለ
ምንም አይነት የሕዝብ ነጻነትና እኩልነት አይታሰብም።ስለሆነም ከሁሉም በፊት የአገር መኖር ቅድሚያ ሊሰጠው
ይገባል። አገር የሌለው ባይተዋር ነው፤ምንም ያህል ሃብትና እውቀት ቢኖረውም በውስጡ የባዶነት፣ የእንግድነትና
ባዳነት ስሜት ተሸካሚ ነው።አገር ያለው ሰው አንገቱን ደፍቶ አያድርም፤ በኩራት ቀና ብሎ ይራመዳል።በተለይም
እንደ ኢትዮጵያ ያለ ባለታሪክ አገር ሕዝብ ለሚገጥመው ጊዜያዊ ችግር እጁን ሊሰጥ አይገባውም።በአገሪቱ ላይ
የሚደርሰው ችግር የሕዝቡ ብልሃትና ችሎታ የሚፈተሽበት ፈተና ነው።ያንን ፈተና ማለፍ ከዘመኑ ትውልድ
ይጠበቃል።አያት ቅድመ አያቶቻችን የገጠማቸውን ፈተና ተባብረው በማለፍ ተወልደን ያደግንባትን አገር አውርሰውን
አልፈዋል።እኛም እንዲሁ አሁን አገራችን የገጠማትን ችግር አሶግደን ለተተኪው ትውልድ ሰላማዊና ጠንካራ አገር
የማውረስ አላፊነትና አደራ አለብን።
አገራችንን ለመውረር በተደጋጋሚ ጊዜ የተነሱባት ጠላቶቿ በሕዝቡ መካከል የነበረውን ጥቃቅን ልዩነትና አለመግባባት
ሊጠቀሙበት ቢያስቡም ህዝቡና መሪዎቹ ልዩነቱን ወደጎን አድርጎ እንደ አንድ ሰው ቆሞ በመታገል ወደመጡበት
መልሶ ያገሩን ነጻነት አስከብሯል፤ለሌሎቹም በቅኝ ግዛት ስር ለሚማቅቁት አገር ሕዝቦች ምሳሌ በመሆን የነጻነት ቀንዲላ
ሆኖ ወደ ድል ጣቢያ መርቷቸዋል።በዚህ አስተዋጽኦ ቅስማቸው የተሰበረው የወራሪ ሃይሎች የጥቃት በትር ለማንሳት
ያልቃጡበት ወቅት የለም።ለዚህ በቀል የሚገለገሉበት ዱላ እንዲሆን የሚመርጡት አገር በቀሉን የሥልጣንና የጥቅም
ምርኮኛ እንደሆነ በታሪካችን ተደጋግሞ ያየነው እውነታ ነው።
በዚህ የታሪክ ውጣ ውረድ ጀግናናና አገር ወዳድ መሪዎች በከፈሉት የደም ዋጋ የእኛ ትውልድ ከወራሪዎች መዳፍ ስር
ሳንወድቅ በአገራችን በነጻነት እንድንኖር አድርገውናል።አገራችን ጀግናና አገር ወዳድ መሪዎችን ብቻ አይደለም
ያፈራችው፣ከአለፉት አርባ ዓመታት ወዲህ በስልጣን ላይ የተቀመጡትን አገርና ሕዝብ ጨፍጭፎና ለአደጋ አጋልጦ
የፈረጠጠውን ፣የምሁር ጠላት የሆነውን ፣የደርግና ኢሰፓ መሪ መንግስቱ ሃ/ማርያምንና የባዕዳን ጥቅም አስጠባቂና
አገር አፍራሽ የሆነውን የህወሃት/ኢህአዴግ መሪ መለስ ዜናዊንም አፍርታለች።እነዚህ ሁለት አምባገነኖች ለኢትዮጵያና
ለሕዝቡ ያበረከቱት ነገር ቢኖር ፍርሃት፣ድህነት ፣ስደት፣አለመተማመን፣የእርስ በርስ ግጭት፣የአገርን ጥቅምና የግዛት
ክልል ለባዕዳን አሳልፎ መስጠት፣እንደ ውጭ ወራሪ ሃይል የአገርን ሃብትና ንብረት መዝረፍና ማዘረፍ፣ባህልና
አንድነትን ማጥፋት ነው።እነዚህ ላለፉት አርባ ዓመታት ለሰፈነው የአምባ ገነን ስርዓት ቁንጮዎች አገሪቱን ወደ ገደል
የመሩ አሸባሪና አሳፋሪ፣የስልጣን እንጂ ያገር ፍቅር የሌላቸው የጥፋት መሪዎች ናቸው። 2

ላለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት በሥልጣን ላይ የተቀመጠው ቡድን ዓላማ የውጭ ጠላቶችን ፍላጎት ለመተግበር የተነሳ
መሆኑን በሚያደርገው ሁሉ ለማረጋገጥ ችለናል።በአገር ውስጥ ሕዝቡ ተከፋፍሎ እንዲበታተን የሚያበቃ ሕግ
አውጥቷል።የአገሪቱ ክፍላተ ሃገራት በብሔር ብሔረሰብ ነጻነት ስም በየተራ እንዲበታተኑ በስሌት እየተንቀሳቀሰ
ነው።የውጭ አገር ባላንጣዎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ሊወሩ የሚችሉበትን መንገድ በማመቻቸት አደጋውን
እውን አድርጎታል።አሁን የደረስንበት ደረጃ አገራችን እንደ አገር ለመኖር የማትችልበት የጥፋት ጠርዝ ላይ
ነው።በልማት ስም አገራችን በውጭ አገር ከበርቴዎችና ሃይሎች ተወራለች፣በአክራሪ የሙስሊም አረብ አገሮችና
አጋጣሚውን በመጠቀም የድንበር ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚሹ የጎረቤት አገራት ድጋፍና አነሳሽነት በነጻነት ስም
የሚንቀሳቀሱ አያሌ አገር በቀል ጠላቶቿ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ የጥቃት ክንዳቸውን ሊያሳርፉባት አኮብኩበው
ይገኛሉ። ኢጅብት ሶማሌና ሱዳን ከአገር ውስጥ ተባባሪዎቻቸው ጋር ሆነው ኢትዮጵያን ለማጥፋት የመጨረሻ ዝግጅት
በማድረግ ላይ ናቸው።ሁኔታው እንዲቀጥል ዕድልና ጊዜ ከተሰጠው የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን የመበታተንና
የውርደት እጣ ፈንታ የቅርብ ጊዜ ትእይንት ይሆናል።
አሁን የኢትዮጵያ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ የሚነሳበት ወቅት ነው።የሥልጣንና የጥቅም ጉዳይ የሚነሳበት
አይደለም።አገር ሳይኖር ሥልጣንና ጥቅም ሊነሳና ሊታሰብ አይችልም።አሁን ማን ለኢትዮጵያ ነጻነትና አንድነት
እንደቆመ የሚታይበት የፈተና ጊዜ ነው።ይህን ፈተና ለማለፍ የሚችለው ይህን የአገር አድን ጥያቄ ለመመለስ ፍላጎትና
ብቃት የሚያሳየው ብቻ ነው።በተለያዩ መጠሪያ ስሞች፣ድርጅቶችና ቡድኖች ተበታትነው የሚፋጩበት ወቅት ሳይሆን
በኢትዮጵያዊነት ለአገር አድን ዘመቻ የሚሰለፉበት ጊዜ ነው። ስለሆነም የተደቀነብንን የጋራ ችግር በህብረት ለማሶገድ
በህብረት መቆምና ለጊዜው መልስ መስጠት በይደር የማናቆየው ብሔራዊ ግዳጃችን መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል።
ያ ግዳጅ ደግሞ ለአገር አድን ጥሪ መሰለፍ ነው።አገር በምን ስርዓት ውስጥ መመራት እንደሚኖርባት የምናነሳው
የአገሪቱ አንድነት ሲረጋገጥ ነው።አገር ሳይኖር ስርዓት አይኖርምና!
መሰባሰቢያ የጋራ ዓላማችን መሆን ያለባቸውም
1. የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ልዑላዊነት መከበር፣
2. የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ስርዓት መመስረት
3. የማንኛውም ኢትዮጵያዊ የዜጋ እኩልነትና የዴሞክራሲ መብቶች መከበር
እነዚህ ሁላችንንም ሊያስማሙ የሚችሉ የጋራ ነጥቦች ሲሆኑ ሌሎቹ እነዚህ በተግባር ከተገለጹ በዃላ የሚስተናገዱ
ይሆናሉ።
የሃይማኖት መሪዎችና ተከታዮች፣የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ተከታዮች፣የሲቪክ ማህበራት መሪዎችና
ተከታዮች፣የሙያ ድርጅቶች መሪዎችና ተከታዮች፣ወጣቶች፣ሴቶች፣የየዕድሜ ክልል አባላት ኢትዮጵያውያን በሙሉ!
አገራችን ያለችበትን አደገኛ ሁኔታ ተገንዝባችሁ በመካከላችሁ ያለውን አላስፈላጊ ልዩነት ሁሉ ወደዃላ አድርጋችሁ
የመጣባችሁን አደጋ በህብረት ተከላከሉ!
አገር ሳይኖር ቤተክርስቲያን፣መስጊድ፣የፖለቲካ ሥልጣን፣የንብረት ባለቤትነት፣ቤተሰብ መስርቶ በሰላም መኖር፣ተምሮ
ሥራ መስራት፣ ተከብሮ መብትን ማስከበር አይቻልምና አገራችሁን ከጥፋት አድኑ፤አገር የማዳኑን ግዳጅ በ”አገር
አድን”መርሆ ተሰብስባችሁ በተግባር ግለጹት።
በኢትዮጵያ አንድነት የምታምኑ፣ለውጥ እንዲመጣ የምትሹ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ደጋፊዎችና የድርጅቱ አባላት፣፣
የሁኔታውን አሳሳቢነት ተገንዝባችሁ፣ከስህተታችሁ ተምራችሁ ፊታችሁን ወደ ብሔራዊ ጥቅምና የአገር ነጻነት አቅጣጫ
አዙራችሁ ነገ ዛሬ ሳትሉ የጸረ ኢትዮጵያን ድንኳን እየጣላችሁ ከኢትዮጵያኑ የአንድነት ድንኳን ትቀላቀሉ ዘንድ ወገናዊ
ምክርና ጥሪ ቀርቦላችዃልና መልስ ስጡ። ሊሰነዘር የታሰበው የጥፋት በትር እናንተንም እንደማይምር ተገንዘቡ።ጊዜው
የብሔራዊ እርቅና መግባባት ነውና ለተዘረጋላችሁ የሰላም እጅ እጃችሁን ዘርጉ።ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን
መንደርደሪያ ለሚሆነው የሽግግር መንግሥት ምስረታ የድርሻችሁን አበርክቱ።አሁን ጊዜው የምርጫ ጊዜ ነው፤ ያም
ምርጫ ኢትዮጵያዊ ሆኖ አብሮ መቆምና መኖር ወይም ሳይሆኑ በእርስ በርስ ጦርነት አጥፍቶ መጥፋት፤በክልል
ተከፋፍሎ በመድከም ለውጭ በዝባዦች መጋለጥ። 3

በልዩ ልዩ ስም ታጥቀው በየፊናቸው የሚንቀሳቀሱት በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጣ የሚታሰበው አደጋ በራሳቸው ላይ የታሰበ
መሆኑን ተገንዝበው ጥቃቱን በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከልና መሬት ላይ ሆነው ሊከላከሉ እንደሚችሉ ማመንና
መዘጋጀት፤በማንኛውም የውጭ አገር መንግሥትና ሃይል እምነት አለመጣል ይጠበቅባቸዋል።በያዙት መንገድ
ከቀጠሉበት እነሱም ለጥቃት የተጋለጡ ይሆናሉ።የጥፋቱም ተባባሪ በመሆን ሊጠየቁበት ይችላሉ።
የአገር አድኑ ዘመቻ ለውጤት እንዲበቃ በውጭ አገርና በአገር ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያውያንና ድርጅቶች ጠንካራ
ግንኙነት ሊመሰርቱ ይገባል።ለዚህ የተለያዩት የመገናኛ አውታሮች፣የዘመኑ የሶሻል ሜዲያ መስመሮች ጠቃሚና ወሳኝ
ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።በተለይ ኢሳት የራዲዮና የቴሌቪዥን አገልግሎት፣የተለያዩት ድረገጽና የውይይት ጣቢያዎች
(Pal Talk Rooms )ከድርጅታዊ ንብረትነትና አገልግሎት ተላቀው ሙሉ ለሙሉ ነጻ ሁነው ወደ ብሔራዊ አገልግሎት
ላይ መዋልና ማተኮር ይኖርባቸዋል። ጊዜው በጋራ የሚታገሉበት እንጂ የድርጅት ጭፍራ ሆኖ ተለያይቶ እርስ በርስ
እየተጠላለፉ የሚባክኑበት አይደለም።በድርጅት ላይ ድርጅት መመስረቱም መፍትሔ አይሆንም፤ይበልጥ ችግሩንና
መከፋፈሉን ይበዛዋል።
ለአገር አድኑ ዘመቻ በቅድሚያ የሚከተሉትን በአስቸኳይ በተግባር መግለጽ ያስፈልጋል
1. ከሁሉም የህብረተሰቡ ክፍሎች፣ተቋማትና ድርጅቶች(ከፖለቲካ ፣ከሃይማኖት፣ከጾታ፣ከሙያ፣ከመረዳጃና
ግብረሰናይ፣ከወጣትና አዛውንት የተውጣጣ አስተባባሪ ብሄራዊ ግብረ ሃይል በውጭና በአገር ውስጥ ማቋቋም፣
2. አደጋው ምንና እንዴትስ ሊወገድ እንደሚችል ማጥናትና በፍጥነት በተግባር መግለጽ
3. ለአገር አድኑ ዘመቻ የሚገባውን አስተዋጽኦ ማበርከት፣በተለይም የገንዘብና የቁሳቁስ አቅምን ማጎልበት
የጋራ ስራን ጥቅም በሚመለከት ሰሞኑን በአንድ የቴሌቪዥን ፐሮግራም ላይ የተላለፈውንና ያየሁትን እንደምሳሌ
ለማካፈል እወዳለሁ፡
ፕሮግራሙ ከአንድ ሰዓት በላይ የፈጀ ዶኩመንታሪ ሲሆን ያተኮረው በአትላንቲክና በፓስፊክ ደቡብ ውቅያኖስ
ስለሚኖሩት የፔንጉዊን ማህበረ አእዋፍ ነበር።ፔነጉዊን ተብለው የሚጠሩት የወፍ ዘሮች በውሃ ውስጥና በመሬት ላይ
የመኖር ልምድ አላቸው።ፒንጉዊን ከሰላሳ ሴንቲሜትር እስከ ዘጠና ከዛም በላይ የሆነ ቁመት አለው።በሁለት እግሩ ቆሞ
ሲሄድ ሲያዩት ከጥቁርና ነጭ ላባው ጋር ሻሽ(ቶባ) አልጠመጠመም እንጂ የኢራኖችን የሃይማኖት መሪዎች አያቶላዎችን
ይመስላል።ሲሞቀው ወደ ባህር፣ሲበርደው ወደመሬት ቦታ እየቀያየረ ይኖራል።በሁለት ሳምንት ውስጥ በውሃ ግፊትና
በእግሩ ከእረፍት ጋር ከሁለት ሽ ኪሎሜትር በላይ ይጓዛል፣ደርባባና ቀርፋፋ የመሰለው የማይበረው ወፍ ካሰበበት
ለመድረስ የቆረጠ ነው።በበረዶም ላይ በደረቱ እየተንሸራተተ የመሄድን ችሎታ አዳብሯል።መእበልና ብርድ ካስቸገረው
ከለላ ይሰራል፣ምሽግ ይቆፍራል ወይም ከፍ ካለ ቦታ ላይ ይወጣል፡፤ኮረብታውን ለመውጣት ክንፉን፣እግሩንና
መቆርቆሪት አፉን አስተባብሮ እንደ እጅ ይጠቀማል።ቢንከባለል ተስፋ ቆርጦ በቃኝ አይልም፣እጅ አይሰጥም
እስከሚሳካለት ድረስ እየወደቀ እየተነሳ ይታገላል፤ካሰበበት ይደርሳል።የፒንግዊን አእዋፍ ጉዞአቸውና ኑሮአቸው በጋራና
በህብረት ነው።አንዱን መሪ አድርገው ተከታትለው ይጓዛሉ፣ለብቻዬ ልጓዝ የሚል የለም፣ከዃላ ቢቀር ሌሎቹ
ይጠብቁታል።ለጥቃት አይመቹም፤የተጣለ እንቁላል ሊዘርፍ የሚመጣውን ጆቢራ በህብረት ይከላከላሉ፣አንድ ላይ
በመጮህ ብቻ ወደ መጣበት ባዶ እጁን ይመልሱታል።ክፍተት ሲያገኝና ተከላካይ ደካማ መስሎ በሚያይበት ቦታ
ከሰማይ አነጣጥሮ ያያትን እንቁላል መንጭፎ ይበራል።ከዚህ ጥቃት ተመክሮ የተነሳ የጆቢራውን ሙከራ በጋራ
ይከላከላሉ፤እንቆላሉም ተፈልፍሎ/ተፈልፍላ ለማህበረተኛነት ይበቃል/ትበቃለች።ፒነጉዊን ደፋርም ነው።ከውሃ ውስጥ
ወጥቶ ሲጓዝ ከባህር ዳር አድፍጦ የሚጠብቀውን የባህር ውሻ/seal/ መንጋ በድፍረት ሰንጥቆ ያልፋል።የጠላቱን
ቀርፋፋነት ስለሚያውቅ ይባስ ብሎም ከአንዱ ጀርባ ወደሌላው በመዝለል እንደደረጃ ተጠቅሞበት ለማለፍ ድፍረትን
ብልሃት አለው።
ፒንግዊን ከሚያደርገው የመኖር ትግል ጎን ፍቅርም ያውቃል።ወንዱ ወይም ሴቷ የኑሮ ጓደኛ ይሻሉ፤ለመማረክ ስልት
ይጠቀማሉ።የከጀላት ወይም የከጀለችው ባለበት/ ባለችበት ረጋ ብሎ መራመድ፣ መሽኮርመምና ማሽኮርመም፣ጠጋ ብሎ
መተሻሸት የተለመደ ነው።አንዷ ወይም አንዱ የፈለጋትን/የፈለገችውን ሌላ ላሽኮርምም ካለ ግብ ግቡ ይነሳል፣በተለይ
በሴቶቹ መካከል የሚነሳው አምባጓሮ ቀላል አይደለም።የክንፍ ጥፊውና በአፍ የመጠቃጠቁ ግብግብ በአንዱ አሸናፊነት
ይጠናቀቅና የተሸነፈው/የተሸነፈችው ዕድሏን ለመሞከር ወደ ሌላ ፊቷን/ፊቱን ያዞራል።ከቶ ምን ሲደረግ ብሎ/ብላ ድርቅ
አትልም፤አቅማቸውን ያውቃሉ።ከዚያ በኻላ ሰላም ሰፍኖ በጠላትነት ሳይተያዩ ሁሉም የጋራ ኑሮውን ይቀጥልበታል። 4

እኛ ከነዚህ እንስት ምን እንማራለን?
1 . ተስፋ አለመቁረጥ ችግርን ለማለፍ ቁርጠኛ መሆን
2. ሊበላቸው አሰፍስፎ ይጠብቅ የነበረውን የባህር ውሻ በዘዴና ስልት እንዳለፉት እኛም አገራችንን ሊያጠፋ የተነሳውን
ሃይል ለማንበርከክ የጋራ ስልት መንደፍ
3. እንቁላላቸውን ሊዘርፍ የመጣውን ጠላት ለብቻ እንደማይቋቋሙት ተገንዝበው በህብረት በመመለስ እንቁላላቸውን
አድነው ዘራቸውን እንዳበዙት እኛም አገራችንን ለማጥፋት የተነሳውን የጋራ ጠላታችንን እንደወፎቹ በጋራ በመታገል
እኛም ሆን ተተኪው ትውልድ ባለአገር እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባን ልንማር እንችላለን።
ከነዚህ እንስሳት አለመማር ከነሱ ማነሳችንን ያረጋግጧል።
 በእኛ አለመተባበር ምክንያት በአንቀጽ 39 ቅምር ሊከሰት የሚችለውን የወደፊቱን ያገራችንን እጣ ፈንታ ከዚህ በታች
ያለውን የቪዲዮ መልእክት በመመልከት ለመረዳት ይቻላል።
http://www.youtube.com/watch?v=Uxp90A8kdhU
አገር እንደዳቦ እየተቆረሰ፣
ጅቡቲ ተበልቶ ኤርትራ ደረሰ፣
ኤርትራ ተበልቶ ወልቃይት ደረሰ፣
ወልቃይት ተበልቶ ጋምቤላ ደረሰ
አገር እንደዳቦ እየተገመሰ፣
ዳር ዳሩ ተበልቶ መሃል ተደረሰ።
ለውስጥ ተነፍጋ ለውጭ የታደለች፣
 ኢትዮጵያ አገራችን ክብ ዳቦ ሆነች፣
በዚህ ከቀጠለ ሙልሙል ትሆናለች፣
በዛም አያበቃ ኩርማን ትሆናለች።
አገር አፍ አውጥታ ጮሃ ትጣራለች
አድኑኝ!አድኑኝ!አድኑኝ! ትላለች።
 እናድናት!!!!

በተጨማሪም ይችን “ላሜ ቦራ” የምትል የፈጠራ ድራማ ለግንዛቤ በመወርወር እደመድማለሁ
የላሜ ቦራን ታሪክ የማያውቅ አለ ብዬ አልገምትም።ላሜ ቦራ ለመጣው ለሄደው የምትታለብ ደግ ላም ነች።ታዲያ በአንድ ውቅት
ላይ እንደላሜ ቦራ የሚጠየቁትን የሚያደርጉ ሰዎች በአንድ አዳራሽ ላይ ተሰብስበው በመሪያቸው አስተባባሪነት የሚወርደውን
መፈክር እንደሚከተለው አስተጋቡ
 አውራጅ፣ በዓባይ ግንባታ ስም እንታለባለን!
 አዎ እንታለባለን!
ለጎሳ ድርጅቶች እንታለባለን! 5

 አዎ እንታለባለን!
ለመጣ ለሄደው ደካማ ድርጅት እንታለባለን!
 አዎ እንታለባለን!
ብቻየን እታገላለሁ ለሚል ድርጅት እንታለባለን!
 አዎ እንታለባለን !
ለውሸታም የዜና ተቋም እንታለባለን !
 አዎ እንታለባለን !
ለኢትዮጵያ አንድነት እንታለባለን!
 ዝም……………..
በአንድነት ለመታገል እንታለባለን!
 ዝም……………….
ኢትዮጵያ ለቅርጫ ወደ ቄራ ስትሄድ እንታለባለን !
 እልልልልልልልል………………….

ከእንዲህ አይነቱ ጥፋት ያድነን!!!
 “አገርህን አድን!!!”
አገሬ አዲስ


No comments:

Post a Comment