Monday, January 20, 2014

‹‹የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን በራሱ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያስገኛል ብሎ መነሳት አይቻልም››

19 JANUARY 2014 ተጻፈ በ  



አቶ ገረመው አያሌው፣ በንግድ ሚኒስቴር የንግድ ድርድርና ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጄኔራል
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደት ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡ የድርድሩ ሒደት ከጥቅምና ጉዳቱ አንፃር እየታየ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል መሆኗ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይበልጣል ሲሉ አንዳንዶች ይከራከራሉ፡፡ ይህንን አመለካከታቸውም ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ስብሰባ ላይ ሲንፀባረቅ መታዘብ ተችሏል፡፡ ይህንን ሐሳባቸውን ይሰነዝሩ የነበሩት ከተለያዩ ሚኒስቴሮች ተወክለው በኤጀንሲው ሥር ብሔራዊ የመረጃ ማዕከል መቋቋሙን በማስመልከት በተወያዩበት ወቅት ነበር፡፡  
መንግሥት በበኩሉ ምንም እንኳ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ይኼ ነው እየተባለ ሊመነዘር የሚችል ምክንያት ማቅረብ እንደማይቻል ቢያምንም፣ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል መሆን ሊያስገኛቸው ይችላል ያላቸውን ነጥቦች አስቀምጧል፡፡ ይህም ቢባል ግን ኢትዮጵያ ከዓመታት በኋላ አሁን የምትገኝበት የድርድር ሒደት መሀል ላይ መድረሱን በንግድ ሚኒስቴር የንግድ ግንኙነትና ድርድር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ገረመው አያሌው ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ስለአገሪቱ ንግድ ሥርዓት የሚተነትን የውጭ ንግድ መግባቢያ ሰነድ (Memorandum of Trade Regime) ለዓለም ንግድ ድርጅት አስገብታ፣ በዚያ መሠረትም ለዕቃዎች የንግድ መደራደሪያ ሰነድ አቅርባ የአራተኛ ዙር ጥያቄዎችን ከአባል አገሮች በመቀበል ምላሽ ለማቅረብ ዝግጅቷን እንዳጠናቀቀች አቶ ገረመው ይፋ አድርገዋል፡፡ 
አከራካሪው ነጥብ ግን ኢትዮጵያ በመንግሥት ዕቅድ መሠረት በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ የድርድር ሒደቱን አጠናቅቃ ለአባልነት ትበቃለች ወይ የሚለው ሆኗል፡፡ ለዚህ መከራከሪያ እርግጠኛ መሆን የማያስችለው ደግሞ የአገልግሎት ዘርፉ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ቴሌኮም፣ ባንክ፣ ኢነርጂና ሌሎችም መንግሥት ስትራቴጂካዊ የሚላቸው ዘርፎችን ወደ ግል ለማዛወር ያለው ፍላጎት ላይ ያነጣጥራሉ፡፡ ተደራዳሪዎቹ አገሮች እነዚህ ዘርፎች ወደ ግል መዛወር እንዳለባቸው እየጠየቁ ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ ስትራቴጂካዊ በመሆናቸው በቀላሉ እንዳማይከፍታቸው በተዳጋጋሚ አስታውቋል፡፡ ስለዚህም ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ አባል ትሆናለች ብሎ መጠበቅ ከባድ እንደሚሆን ያመለክታሉ፡፡ እነዚህን ነጥቦች በማስመልክት ስለአባልነት ሒደቱ አቶ ገረመው አያሌውን ብርሃኑ ፈቃደ አነጋግሯቸዋል፡፡ 
ሪፖርተር፡- መንግሥት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደቱ በዕቅዱ ዘመን እንዲጠናቀቅ አቅዷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስትራቴጂካዊ የሚባሉት እንደ ባንክ፣ ቴሌኮም፣ ኢነርጂ ያሉትን ዘርፎች ክፍት ለማድረግ ዝግጁ አይደለም፡፡ ሁለቱ አቋሞች አይጣረሱም; 
አቶ ገረመው፡- የድርድር ሒደቱ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ውስጥ እንዲጠናቀቅ በመንግሥት በኩል ይጠበቃል፡፡ ሆኖም ሒደቱ ድርድር ነው፡፡ መንግሥት ድርድሩ በዚህ ጊዜ ውስጥ እንዲያልቅልኝ እፈልጋለሁ ብሏል፡፡ ስትራቴጂካዊና ትልቅ ትኩረት የሰጣቸው የአገልግሎት ዘርፎች ላይ የሚያደርገው ድርድር ገና አልተጀመረም፡፡ የአገልግሎት ንግድ መደራደሪያ ‹‹ሰርቪስ ትሬድ ኦፈር›› የሚባለው ሰነድም ገና አልቀረበም፡፡ ተጠናቅቆ በቅርቡ ለተደራዳሪ አገሮች ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኢትዮጵያ እየተጠየቀች ያለው በቴሌኮም፣ የፋይናንስና የሌሎች አገልግሎቶችን በር እንድትከፍት ነው፡፡ እነሱ የሚጠይቁት (ተደራዳሪ አገሮች) የአገልግሎት ዘርፉን ለግሉ ዘርፍ እንዲከፉት ነው፡፡ የአገሬን ፖሊሲዎች ለማስከበር መከላከል አለብኝ፡፡ አባል አገሮችን በሚቻለው መጠን በማሳመን እንዲቀበሉት ማድረግ አለብኝ፡፡ ስለዚህ በዚህ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን እነዚህ በመንግሥት ስትራቴጂካዊ ተብለው የተለዩት ዘርፎች ክፍት ይደረጋሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ መንግሥት ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ ድርድሩን እጨርሳለሁ ብሎ ሊነሳ ይችላል፡፡ ድርድር በመሆኑ የደርድሩ ሒደት ሲጠናቀቅ ነው ይኼ ሊወሰን የሚችለው፡፡ 
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በድርድር ላይ ነች፡፡ ሆኖም ሒደቱ የተወሰነ ጊዜ ወስዷል፡፡ እስካሁን የተቆዩባቸው ጊዜያት ደግሞ በመጀመርያው የድርድር ሒደት ላይ እንድትገኝ አድርገዋል፡፡ አሁንስ መንገዱ በቅርብ ጊዜ አባል እንደምትሆን የሚያሳይ ነው;
አቶ ገረመው፡- የለም፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የመጀመርያው ሒደት ላይ አይደለንም፡፡ ከድርድር ሒደቱ አጋማሽ ላይ ነን፡፡ ይኼ ማለት ምንድን ነው ተከታታይ ጥያቄዎችን በአራት ዙር ተቀብለናል፡፡ ለሦስቱ ምላሽ ሰጥተናል፡፡ የአራተኛው ዙር ጥያቄዮች ምላሽም ተዘጋጅቷል፤ በቅርቡ ይላካል፡፡ ስለዚህ በድርድሩ ሒደት አንዱ አካል የሆነውን የጥያቄና መልስ ሒደት ጨረስን ማለት፣ የብዙ ወገን (የመልቲ ላተራል) ድርድር ሒደቱን እንጨርሳለን ማለት ነው፡፡ በድርድሩ ሒደት ሁለት ዙር አለ፡፡ አንደኛው የሁለትዮሽ ድርድር ሲሆን ሌላኛውና እኛ የምንገኝበት የድርድር ሒደት የብዙ ወገን ድርድር ሒደት ዙር ነው፡፡ የብዙ ወገን ድርድሩን ጨረስን ማለት ደግሞ የመግለጫው ማጠቃለያ አለቀ ማለት ነው፡፡ በየጥያቄው ላይ በሰጠነው ምላሽ አገሪቱ በእንዲህ ጉዳይ ላይ እንዲህ ብላለች እየተባለ የሚጠቀስ ሲሆን፣ መጨረሻ ላይ ለሰጠናቸው ምላሾች ግዴታ እንገባለን ማለት ነው፡፡ 
ስለዚህ የመጀመርያውን የድርድር ሒደት እያጠናቀቅን ነው፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ የሁለትዮሽ ድርድር ሒደት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ከእያንዳንዱ ፍላጎት ካለው አገር ጋር ቁጭ ተብሎ በሚስጥር መደራደር ነው፡፡ ከእያንዳንዱ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል አገር ጋር የምንገባው ቃልና የምንገባው ግዴታ በመጨረሻ የሁለትዮሽ ድርድሩ አካል ይደረጋል፡፡ ይኼንን በቅርቡ እንጀምራለን፡፡ አንዱ የሚጠበቀው የአገልግሎት ንግድ ላይ የምንሰጠው የመደራደሪያ ሰነድ ነው፡፡ እሱን ለማዘጋጀት ረጅም ጊዜ ወስዷል፡፡ የአገልግሎት ንግድ ውስብስብ በመሆኑም ነው ረጅም ጊዜ የወሰደው፡፡ እሱን እንዳቀረብን ለሚነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ እንሰጣለን፡፡ ምላሹ ካለቀ ሒደቱ አለቀ ማለት ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- አንዳንድ አገሮች 20 ዓመት ድረስ የድርድር ሒደቱ እንደሚወስድባቸው ከቻይናና ከሩሲያ መመልከት ይቻላል፡፡ የአባልነቱ ጉዳይም  አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች ይነሱበታል፡፡ ከአካባቢና ከዓለም አቀፍ አገሮች ጋር መነገድ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት ድርድር ውስጥ ተገብቷል፡፡  አባል የመሆን ትክክለኛው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ተተንትኖ ሲቀርብ አይታይም፤ በግልጽ አይቀርብም፡፡
አቶ ገረመው፡- በመጀመርያ ደረጃ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን በራሱ ይኼንን የኢኮኖሚ ጥቅም ያስገኛል ብሎ መነሳት አይቻልም፡፡ ለምንድን ነው ከተባለ የዓለም ንግድ ድርጅት የዓለም አገሮች በአንድ ሕግ የሚተዳደሩበት የንግድ ሥርዓት ነው፡፡ የንግድ ሥርዓቱን ለበጎ ዓላማ መጠቀም ይቻላል፡፡ እነቻይና የቤት ሥራቸውን ሠርተው ለመግባት ሲሉ ከአሥራ አምስት ዓመት በላይ ፈጅቶባቸዋል፡፡ የቤት ሥራቸውን ሲጨርሱ ገቡ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዓለም ሁለተኛው ኢከኖሚ ባለቤት ሆኑ፡፡ ሌሎች አገሮች ደግሞ ድርድሩ የወሰደባቸውን ጊዜ ፈጅተው አባል ሆኑ፡፡ ነገር ግን ከነበሩበት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ምንም ለውጥ ሳይታይ ቀረ፡፡ የአንዳንዶቹ እንዲያውም እየቀነሰ ሄደ፡፡ 
ስለዚህ አባል ለመሆን ሒደቱን መጨረስ በራሱ የመጨረሻ አይደለም፡፡ የአባልነቱን ዕድል ለልማት መጠቀም ነው ዋናው፡፡ ለኢንቨስተሮች መተማመንን ይፈጥርላቸዋል፡፡ ይኼ ከተፈጠረ ኢንቨስተሮች ወደ አገራችን ይመጣሉ፡፡ ሕጉ አስተማማኝ ነው፣ ይህቺ አገር በሕግ የምትገዛ ናት፣ ሕጎቿን እንደፈለገች አትለዋውጥም፣ ስለዚህ ወደዚያች አገር ሄደን ብናመርት ወይም ብንሠራ ይሻላል እንዲሉ ዕድሉን ይፈጥራል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የመልክዓ ምድር አቀማመጥ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለን፡፡ በአፍሪካ ቀንድ እንደመገኘታችን የደቡቡን፣ የሰሜኑን፣ የምሥራቅና የምዕራቡን ሳይቀር ማግኝት የምንችልበት አቀማመጥ ላይ እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ጠቀሜታዎች አሉ፡፡ ሰላማላዊ መሆናችንና የተማረ ሰው ኃይላችን እየጨመረ በመምጣቱ እነዚህን ሁሉ አሟልተን ሳለ ከዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ውጪ ብንሆን የምናጣው በእኛ ተማምነው ሊመጡ ይችሉ የነበሩትን ኢንቨስተሮች ነው፡፡ ስዘሊህ አባል ሆኖ መግባቱ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡:
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ አባል አለመሆኗን እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠው የቀሩ አሉ ማለት ነው;
አቶ ገረመው፡- አባል አለመሆናችንን እንደ ቅድመ ሁኔታ አይተው የቀሩ ኢንቨስተሮች የሉም፡፡ ይኼንን ብናደርግ ግን ሊመጡ ይችላሉ ብለን እናስባለን፡፡ ስላልገባችሁ አልመጣም ያለ የለም፤ ሊልም አይችልም፡፡ ግን መጀመርያ ይህቺን አገር ሲያስብ መጀመርያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ናት ወይ ብሎ ማሰቡ ግን አይቀርም፡፡ ስለዚህ ያንን መተማመን ነው የምንፈጥረው፡፡ አባል የመሆናችን ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ይኼ ነው ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከምትደራደራቸው መካከል እነ ካናዳ፣ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ተጠቅሰዋል፡፡ አሁን ደግሞ ኮሪያ መጥታለች፡፡ ከዚህ ቀደም ይቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎች በርካታ ነበሩ፡፡ በመሀል እየቀነሱ የነበሩት መልሰው እየተበራከቱ መጥተዋል ተብሏል፡፡ የጥያቄዎቹ መብዛትና ማነስ ምንን ያመለክታል;
አቶ ገረመው፡- ጥያቄዎቹ እየቀነሱ መምጣታቸው ለአባል አገሮች የምንሰጣቸው ምላሾች እየተስማማቸውና እያረካቸው መምጣታቸውን ያመለክታሉ፡፡ እየጨመሩ መምጣታቸው ደግሞ አዳዲስ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ማለት ነው፤ ያልገለጽናቸው ነገሮች አሉ ማለት ነው፡፡ እነሱን መግለጽ ይጠበቅብናል፡፡ ጥያቄው መጨመሩ ምናልባትም አዳዲስ ሰነዶችን ስናቀርብ እዚያ ውስጥ ያልገባቸውን ነገር የሚጠይቁበት ነው፡፡ በቅርቡ ለድርድር የምናቀርባቸው አምስት ያህል ሰነዶች አሉ፡፡ ከዚያ ውስጥ በትክከል ያልገለጽነው ወይም በደንብ ያላብራራነው ነገር ካለ ጥያቄ ይመጣል፡፡  የጥያቄዎቹ መብዛትና ማነስ፣ አባል አገሮቹ ስለእኛ የንግድ ሥርዓት ያላቸው ዕውቀት እስከምን ደረጃ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ የምንሰጠው ምላሽ ለዓለም ንግድ ድርጅት ተስማሚ ከሆነ ጥያቄው እየቀነሰ ይመጣል፡፡ የደበቅነው ሚስጥር ካለ ደግሞ ጥያቄው እየጨመረ ይመጣል፡፡ እዚህ ያሉት አብዛኞቹ ኤምባሲዎች የሚሠሩት እኮ የንግድ ‹‹ኢንተሊጀንስ›› ነው፡፡ እኛ ብንደብቅ መረጃውን ኤምባሲዎቹ ያገኙታል፡፡ ስለዚህ መደበቅ የለብንም፡፡ 
ሪፖርተር፡- ኮሪያዎች ምን የተለየ ነገር እየጠየቁ ነው; 
አቶ ገረመው፡- የተለየ ነገር የለም፡፡ ግልጽ እንዲደረግላቸው የጠየቋቸው ነገሮች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ኤዲቶሪያል ናቸው፡፡ እዚያ ጋ በመንግሥት እጅ የሚገኙ ድርጅቶች 12 ናቸው ብላችሁ ነበር፣ እዚህ ጋ ግን 11 ብላችኋል፡፡ ይኼ እንዴት ነው የሚሉ ጥያቄዎችን እያቀረቡ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የአገሮቹ አብዛኞቹ ጥያቄዎች ምንድናቸው; ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ከመሆኗ በፊት ምን እንድታሟላላቸው ይፈልጋሉ;
አቶ ገረመው፡- አሁን በብዙ ወገኖች ድርድሩ ላይ ማሟላት የሚገባንን ሳይሆን፣ ላቀረብናቸው መግለጫዎች ማብራሪያ ነው የምንጠየቀው፡፡ ይኼንን ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው? ይኼንን እንዴት ነው የምታዩት? እንዲህ ዓይነቱ ነገር በምን ሕግ ነው የሚተዳደረው? ወዘተ ያሉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እውነተኛው ድርድር የሚመጣው በሁለትዮሽ ስንገናኝ ነው፡፡ ያኔ ነው እያንዳንዱ አገር ፍላጎቱን የሚያንፀባርቀው፡፡ አሁን እውነቱን በመፈለግ ሒደት ላይ ነው የምንገኘው፡፡ 
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ አባል እንድትሆን ድጋፍ እየሰጡ ነው;
አቶ ገረመው፡- ከጠየቅን ይሰጡናል፡፡ ድርድሩን በሚመለከት ከአሜሪካ የሚሰጠን ድጋፍ ነበር፡፡ አሁን ተቋርጧል እንጂ ‹‹WTO Accession Plus Ethiopia›› የሚባል ፕሮጀክት ነበር… 
ሪፖርተር፡- ኮሪያስ;
አቶ ገረመው፡- እነሱ ምንም የሰጡን ነገር የለም፡፡ 
ሪፖርተር፡- በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማትና የንግድ ጉባዔ (UNCTAD) አንድ ሥልጠና ሰጥቶ ነበር፡፡ ምን ላይ ነበር ያተኮረው;
አቶ ገረመው፡- የንግድ ፖሊሲያችን ላይ አንድ ወጥ የሆነ ሰነድ የለንም፡፡ የንግድ ፖሊሲው በተለያዩ የፖሊሲ ሰነዶች ውስጥ የተንፀባረቀ ነው፡፡ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ ላይ፣ በኢንዱስትሪ፣ በግብርናውና በተለያዩ ፖሊሲዎች ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ በአንድ ወጥ ሰነድ ውስጥ የሚዘጋጅበትን ጥናት አስጠንቶልናል፡፡

No comments:

Post a Comment