Sunday, January 19, 2014

አባይ ጉዳይ ላይ ያጠላበት የፖለቲካ ድባብ አሁን ሊገፈፍ ይገባል!! ግርማ ሠይፉ ማሩ

የአባይ ጉዳይ ላይ ያጠላበት የፖለቲካ ድባብ አሁን ሊገፈፍ ይገባል!! ግርማ ሠይፉ ማሩ

Girma Seifu Maru
የውሃ፣ ኢነርጂና መስኖ ሚኒስትር በአባይ ተፋሰሰ ሀገሮች መካከል በተለይም በግብፅ፣ በሱዳን እና ኢትዮጵያ መካከል ሲደረግ የነበረውን ውይይት እንዲሁም የህዳሴ ግድብ ያለበትን ደረጃ አሰመልክቶ ለምክር ቤት አባላት በባለሞያ የታገዘ ገለፀ ለማድግ ህዳር 22/2006 በምክር ቤቱ ተገኝተው ነበር፡፡ ይህ ገለፃ እና ማብራሪያ ከዚህ ቀደም ለዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ ቀርቦ የነበረ መሆኑ በሚዲያ ተከታትለናል፡፡ በእኔ እምነት ቀድሞ መቅረብ የነበረበት ለምክር ቤቱ ሆኖ ከዚያ ቀጥሎ በየደረጃው ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ቢቀርብጥሩ የፕሮቶኮል አካሄድ ነው ለማለት እችል ነበር፡፡ ለማነኛውም ፕሮቶኮሉን እነተው እና በዚህ ደረጃ ለህዝብ ለማቅረብ ተነሳሸነቱ መፈጠሩ የዘገየም ቢሆን ተገቢ ነው ብዬ መውሰድ አልቸገርም፡፡ “ዘገዬ” የሚለውን ቃል ኢህአዴግና ሹሞቹ በጓዳ ግምገማ ካልሆነ በአደባባይ ውይየት ጊዜ ደስ አይላቸውም፡፡
በነገራችን ላይ ይህ ማብራሪያ አሁን መቅረቡ ጥሩ መሆኑን፤ ነገር ግን ዘግይቷል በሚል ለውሃ፣ መሰኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ለሰጠሁት አስተያየት ሚኒስትሩ “አልዘገየም ድርድሩ እዚህ ጋ የደረሰው በጥቅምት ወር ነው፡፡” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በእኔ እምነት ኢትዮጵያዊያን ማወቅ ያለባቸው የሶስትዮሽ ድርድሩን ሳይሆን አጠቃላይ መንግሰት ግድቡን ለመገንባት የሄደበትን መንገድ ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያዊ ምሁራን እና ጋዜጠኞች ከግብፅ እና የግብፅ ወዳጆች በተለያየ መልክ በሚያስረጩት መረጃ ሳይሆን በቀጥታ ከሀገራቸው ታማኝ መረጃ አግኝተው ጠንካራ አቋም እንዲይዙ ማድረግ የግድ የሚል ነው፡፡ የምሁራኑ እና የጋዜጠኞች መረጃ ማግኘት ያለጥርጥር ህዝቡ ሀገር በቀል መረጃ እንዲያገኝ ዋናኛ መንገዶች ናቸው፡፡ የዘገየ ማብራሪያ የምለውም ስለግድቡ አጠቃላይ ሁኔታ ነው እንጂ ስለ ሶስትዮሽ ውይይት ሂደትና ውጤት አይደለም፡፡ ለምሳሌ በአባይ ተፋሰስ ላይ ቀደም ሲል በአሜሪካ ድጋፍ ቀጥሎም እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2005/6 በተፋሰስ አገሮች ትብብር ሱዳን እና ግብፅ ጨምሮ በተደረገው ጥናት ሶሰት የግድብ ቦታዎች ተመርጠው የአሁኑ “ቦርደር ሳይት” በመባል የሚታወቀው የግንባታ ቦታ በሁሉም ተመራጭ እንደነበር ብዙ የሚያውቅ ሰው የለም፡፡ በአቶ አለማየሁ ተገኑ አገላለፅ “ፕሮጀክቱ ግማሽ
ድረስ በትብብር የተሰራ ነው”፡፡ ይህን የትብብር ስሜት ያፈረስው ምን አልባትም የግብፅ ከልክ ያለፈ አልጠግብ ባይነት እና በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚገኝ ቢሆንም አባይን የሚመለከት ፕሮጀክት በባለቤትነትን የመያዝ እና የማስተዳደር ፍላጎት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመጣው ከንቀት ጭምር ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከግብፅ ጋር በሽግግር መንግስት ወቅት የገቡት ቃል ወይም ስምምነት ለመናቃችን አንዱ የቅርብ ምሳሌ ነው፡፡ ኦቶ መለስ ይህን ቃላቸውን አጥፈው፣ ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያዊያን ቁጥጥር እና ባለቤትነት እንዲካሄድ የወሰዱት አቋም ተገቢም ትክክል ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ አቋሞች በብዙ ሁኔታዎች የታዘብን ቢሆንም
በዋነኛነት “ባንዲራ ጨርቅ ነው” በባንዲራ ቀን አከባበር፤ “የአክሱም ሀውልት ለወላይታ ምኑ ነው” በብሔር ብሔረሰቦች በዓል አከባበር ቀጥሎም በብሔር መለያየትን “ልዩነታችን ውበታችን” በሚል መፈክር መታጀቡ እና በሌሎች ሁኔታዎችን የተገነዘብን ሰዎች የሶስት መቶ ስልሳ ዲግሪ መታጠፍ አድርገን ልንወስደው እንችላለን፡፡ ለማንኛውም ኢትዮጵያን እና ህዘቦቿን ወደሚጠቅም አቋም በፈለጉት ዲግሪ መታጠፍ ቢዘገይም በአዎንታ መቀበል ይኖርብናል፡፡
በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ጥሩ አካሄድ ሊባል የሚችለው የውጭ ዜጎችን በመጠቀም ዙሪያ በመንግሰት የተያዘው አቋም ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከወንድሞቻችን ኤርትራዊያኖች ጋር በመሪዎች ፍላጎት በገቡት “የድንበር” ተብዬ ግጭት፣ ችግሩን ለመፍታት በተለይም የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ የሀገር ውስጥ ባለሞያዎችን እና ታሪክ አዋቂዎቸን ባለመጠቀም የደረሰባትን ኪሳራ በደንብ የተረዱት ይመስላሉ፡፡ በአባይ ጉዳይ ዋናዎቹ ተዋናዮች ኢትዮጵያዊያኖች እንደ ነበሩ ለመረዳት ችለናል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም በቀጣይ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ በሚደረግ ውይይት ከውጭ የሚባል አይኖርም፤ የሚያስፈልግ ባለሞያ ቢኖር ቀጥረን አገልግሎት ከመስጠት በዘለለ ገብቶ መፍተፈት አይፈቀድም፡፡ የሚል አቋም ኢትዮጵያ ይዛለች የሚለው መስመር እሰይ የሚያስብል ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አቋም የሚመራው በኢህአዴግም ቢሆን መደግፍ የግድ ይለናል፡፡
በዚህ አጋጣሚ እሰከ ዛሬ በነበረው ውይይት ከውጭ ሀገር ማለትም ከጀርመን፣ ከእንግሊዝ፣ ከፈረንሳይ እና ከደቡብ አፍሪካ ተወክለው ምክረ ሃሳብ ያቀረቡት ባለሞያዎች ጥንቅር “ለምን ከወዳጆቻችን ከነቻይና አልመጣም?” የሚል ፈገግ የሚያሰኝ በዚያውም የህውሃት አባላት አሁንም መንግሰት ሶሻሊሲት እንደሆነ የሚያሳብቅ ጥያቄ አንድ የምክር ቤት አባል ሰንዝረዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ነጭ ካፒታሊዝም ነው የምንከተለው ይበሉ እንጂ አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ በዚህ የሚስማሙ እንዳልሆነ በተለያየ መግለጫ ታዝበናል፡፡ እኛም ብንሆንን የምንስማማው አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ በሚገልፁት መስመር ነው፡፡ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከካፒታሊዝም ሳይሆን ወደ ሶሻሊዝም የሚጠጋ ርዕዮት እንደሆነ ነው የሚገባን፡፡ መድበለ ፓርቲ ስርዓት፣ ነፃ ገበያ፣ የግል ሀብት፣ ወዘተ ለእርዳታ ሰጪዎች ሲባል የሚቀርቡ ሹፈቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሹፈቶች ግን ይዋል ይደር አንጂ ዋጋ የሚያስከፍሉ ናቸው፡፡
በግሌ የኢህአዴግ በደል ከፍቶ ፅዋው ሞልቶ ቢፈስ እንኳን የሀገሬን ጥቅም አሳልፌ የምሰጥበት ምንዳም ሆነ የግፍ መጠን እንደሌለ በተደጋጋሚ ይፋ አድርጊያለሁ፣ ከዚህ የግል እምነቴ ጋር የሚፃረር ፓርቲም ሆነ ሌላ ስብስብ ጋር እንደማልሰራ አውቃለሁ፡፡ እንደዚያም ሆኖ የመንግሰት ሹማምንት የአባይ ግድብን ያህል ትልቅ ፕሮጀክት ይዘው ተቃዋሚና ገዢ ፓርቲ የሚል ክፍተት መፍጠር እንደሌለባቸው ሲነገራቸው፣ በተግባር የሚሰሩትን ሀቅ ወደ ጎን ትተው ጉዳዩን በሙሉ ፕሮፓጋንዳ ያደርጉታል፡፡ ኢህአዴግ ለፕሮፓጋንዳ የሚከፍለው መሰዋዕትነት የፈለገ ውድ ቢሆን ለመክፈል ዝግጁ ነው፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስለግድቡ በቂ መረጃ በሌላቸው እና ይልቁንም ግርማ ሠይፉ ማሩ በመንግሰት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ፍፁም ደስተኛ ባልሆኑበት ሁኔታ፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መንግሰትን ደግፈው ገንዘባቸውንያለምንም ጥያቄ እንዲቸሩ ይጠይቃል፡፡ በሀገር ውስጥም ቢሆን ሁሉን ተዉት ገንዘብ አምጡ ዘመቻ የሚያስገርም ነው፡፡ በውጭ የሚኖሩኢትዮጵያዊያን ይህን ግድብ በሚያስደንቅ ሁኔታ ሊገነቡት የሚችሉበት አቅም እንዳለ ተገንዝቦ ግብፅን አንገት የሚያስደፋ መንገድ ከመቀየስ ይልቅ አሁንም በውጭ የሚገኙትን ዜጎች መከፋፈል ተገቢ አይደለም የሚል እምነት አለኝ፡፡ መንግሰት ከዚህ አንፃር
የሚጠበቅበት ለውጥ፤ ግብፅን አና ወዳጆቿን እሞኑኝ ብሎ ለልምምጥ ከሚያጠፋው ጉልበትና ሀብት የሚበልጥ አይደለም፡፡ መንግሰት ከዚህ አንፃር የሚከተለውን የኮሚኒኬሽን ስትራቴጂ እንደገና መገምገም እና ሁሉንም በሚያሳትፍ መልኩ መቀረፅ እንዳለበት ማስገንዘብ ቢዘገየም የረፈደ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ግን የሚሰማ አይመስልም፡፡ ማን ነው ኢህአዴግ ሀፍ እንጂ ጆሮ የለውም ያለው?
በአባይ ዙሪያ በኢየትዮጵያ ለሚታሰብ ማንኛውም እንቅስቃሴ በቂ ተቃውሞ በግብፅ ስለ አለ በሀገር ውስጥ ሌላ ጠላት ለምን ትፈልጋላችሁ? ለሚል ጥያቄ ኢህአዴግ ሆደ ሰፊ መሆን አይችልም፡፡ ኢህአዴግ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ገንዘብ ማግኘት የሚፈልገው፣ ለአብታዊ ዲሞክራሲ እግረ መንገዳቸውን ገብረው እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ እኔ እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ አባል ለስልጣን ነው ትግል የማደርገው፡፡ ስልጣን ብንይዝ ይህች ሀገር ኢነርጂ እንደሚያስፈለጋት ለማወቅ ስልጣን መያዝ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ የአባይን ግድብ ለመገንባት መንግሰት የሚያወጣውን ዕቅድ በተመለከተ የተሟላ መረጃ እንዲኖረኝ የግድ ይላል፡፡
የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ከዚህ አንፃር በጭፍን የአባይን ግድብ እንዲደግፉ እንጂ መረጃን መሰረት አድርገው ትንተና እንዲሰሩ እና የራሳቸውን ምክረ ሃሳብ እንዲሰጡ እድል የላቸውም፡፡ ለዚህ ጉዳይ የሚፈለጉት ልማታዊ የሚባሉት ጋዜጠኞች ብቻ ናቸው እነርሱም መንግሰት የሚለውን እንደ በቀቀን መድገም ነው የሚጠበቅባቸው፡፡ በግብፅ ግን የግልም ሆነ የመንግሰት ሚዲያዎች ለሀገራቸው ይጠቅማል ያሉትን እንዲዘግቡ መረጃ ይስጣቸዋል፡፡ ማግለል ይቅር ስንል የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን
ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን ሚዲያውንም ጭምር ነው፡፡ አሁንም የአባይ ጉዳይ እና መረጃ ሁሉም ሚዲያዎች በሚያሳትፍ መልኩ ለሚዲያዎች መሰጠት ይኖርበታል፣ ሚዲያዎችም ይህን ኃላፊነት እንደሚወጡ ጥርጥር የለኝም፡፡ ለዚህም ማሳያ የ “ፋክት” አምደኞች ቤተሰብ የነበረችው መፅሄት አዲስ ታይምስ ከዓመት በፊት የአባይን ጉዳይ በልዩ ዕትም ቅፅ 1 ቁጥር 9 ህዳር 2005 ማውጣቷ እና በዚህ ዕትም ያስተላለፈችው መልዕክት ድጋሜ መነበብ የሚገባው ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ በኤክሰፐርቶች ፓናል ውስጥ ተሳታፊ ለሆናችሁ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ሁሉ ከመቀመጫዬ ብድግ ብዬ አድናቆቴን መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡
ግብፆች የአባይ ጉዳይ ሲነሳ የፖለቲካ ልዩነታቸውን ትተው እንደ ግብፅ ሲያስቡ እኛን መለያየት ለምን ያስፈልጋል? የአባይ ግድብ ፕሮጀክት በተግባር የኢትዮጵያ ህዝብ ፕሮጅክት አንዲሆን የፖለቲካ ድባቡ ላይ ያጠላው የፕሮፓጋንዳ አዚም ሊገፈፍ ይገባል፡፡ አንድነት ፓርቲ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን መጠቀም ተፍጥሯዊ መብቷ ነው ይላል፡፡ ይህ የማይገሰስ መብት ላይ ምን ፕሮፓጋንዳ ያስፈልጋል፡፡ የዛሬው መልዕክቴ ዋና ማጠንጠኛ በሀገር ጉዳይ እንዳንግባባ አዚም ያደረገብን ማን ነው? የዚህ አዚም መፍቻ ቁልፍ መተማመን እና ሀገራዊ ዕርቅ ይመስለኛል፡፡
መልካም በዓል ቸር ይግጠመን !!!!!!
girmaseifu32@yahoo.com

No comments:

Post a Comment