የአፍሪካ ከተሞች የኑሮ ልዩነትን የሚያሰፉ ‹‹የቅንጦት ዓለም›› ፈጣሪ እየሆኑ መጥተዋል
-ኢትዮጵያን በሚመለከት ባለሙያዎች የተለየ አቋም ይዘዋል
ባለፈው ሳምንት በከተሞች ልማት ላይ ያተኮረ ጥናት ከደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ ይፋ ተደርጓል፡፡ በጥናቱ መግቢያም ላይ እንዲህ የሚል አንቀጽ ሰፍሯል፡፡
‹‹የአፍሪካ ከተሞች የከተማ ፕላን እሱም ካለ ማለት ነው፣ በአብዛኛው የትም ስርቻ ውስጥ ተወታትፎ የሚቀመጥ ነው፡፡ ወይም ደግሞ በመንግሥት ሚኒስቴር ውስጥ የሆነ ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ ሊታይ ይችላል፤ ወይም በሆነ የቴክኒክ ሪፖርት ውስጥ ተወሽቆ የሚገኝ ይሆናል፡፡ ፕላኖቹ የሚያንጸባርቁት የመሬት አጠቃቀምንና በዞን ደረጃ የከተማውን ክፍል የሚያሳይ ዕቅድ ሲሆን፣ አብዛኛው ፕላኑ ላይ የሚታየው ደግሞ በመሬት ላይ ያለውን ዕውነታ ነው …››
አጥኚዋ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬፕታውን የአርክቴክቸር፣ የፕላንና የጂኦማቲክስ ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ቫኔሳ ዋትሰን ናቸው፡፡ መሁሯ ዋትሰን ከላይ ያሰፈሩት መግቢያ፣ በግርድፉ ሲተረጎም የአፍሪካ ከተሞች ቀቢጸ ተስፋ፣ ህልም ወይስ ቅዠት የሚል ርዕስ በሰጡት ጥናት (African urban fantasies: dreams or nightmares?) የድሮው ነገር በፍጥነት እየተቀየረ መምጣቱን አስፍረዋል፡፡
በአፍሪካ ከተሞች ውስጥ ይገነባሉ ተብለው የታሰቡት ማስተርፕላኖች በመላው ዓለም በቀላሉ እየተሰራጩ የሚገኙ፣ በየሥነ ሕንፃውና በግንባታ ኩባንዎች ድረ ገጾች ውስጥ የሚታዩ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ማስተርፕላኖች አንዳንዶቹ ጭርስኑ ከቀድሞው አፍሪካ ከተሞች ማንነት ያፈነገጡ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ መጪዎቹ የአፍሪካ ከተሞች ራዕይ ከዱባይ፣ ከሲንጋፖር ወይም ከቻይናዋ ሻንጋይ ጋር የሚያመሳስላቸውን ስዕል ለመሳል የቋመጡ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ አንዳንድ የዓለምን ቅርጽ የቀየሩ የግንባታ ጥበቦችን ማምጣቱ ክፋት ባይኖረውም የአፍሪካውያኑ አካሄድ ግን የምሁራንን ትችት አስከትሏል፡፡
ጥንተ ነገሩ
በመላው ዓለም በግንባታና በአርክቴክቸር ሙያ የተሰማሩ ድረ ገጾች የሚለቋቸው የመጪዎቹ የአፍሪካ ከተሞች ምስል፣ በመስታወት አሸብርቀው ብቅ ያሉ ዘመናዊ ፋሽን የሚያደምቃቸው፣ ‹‹ስማርት ሲቲ›› የመሆኛቸውን መንገድ የጀመሩ ለሥነ ምህዳር የተስማሙ ከተሞች እየመጡ የሚያስመስላቸውን ገጽታ እንደያዙ ይነገራል፡፡ ፖለቲከኞችና ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ደጋግመው የሚጠቀሙበት ‹‹አፍሪካ እየተነሳች ነው›› የሚለውን አነጋገር የሚጠቅሱት ዋትሰን፣ በእርግጥም አፍሪካ ከ20 ዓመታት በኋላ በዓለም ሁለተኛዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ ምህዋር እንደምትሆን የምትጠበቅ አኅጉር መሆኗን ይጠቅሳሉ፡፡ በርካታ የሰው ኃይል በማፍራት ከቻይናና ከህንድ እንደምትበልጥ ይጠበቃል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ዓለም አቀፍ የሪል ስቴት አልሚዎችንም ሆነ በዘርፉ የሚታወቁትን እንደሚያቋምጣቸው የሚጠበቅ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የአፍሪካ መንግሥታት ለከተማ ፕሮጀክቶችና ለመሠረተ ልማት ግንባታ መስፋፋት የሚኖራቸው ፍላጎት እያሻቀበ ስለሚሄድ እነዚህ ኩባንያዎችን በጥብቅ መፈለጋቸው፣ በእነሱም ላይ ጥገኛ መሆናቸውም እንደማያጠራጥር ዋትሰን ይተነትናሉ፡፡
አፍሪካ በዓለም የኢኮኖሚና የልማት ጉዞ ውስጥ የመጨረሻዋ መዳረሻ አኅጉር መሆኗ እውን እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ፣ የእስያ ከተሞች በንብረትና በመሬት አቅቦት ላይ ከእንግዲህ ሊያቀርቡት የሚችሉት ሀብት ስለሌላቸው፣ በአብዛኛው በድንግልና ወደቆዩት የአፍሪካ ከተሞች ፍልሰት እየተጀመረ መጥቷል፡፡ በአፍሪካ የከተማ መሬትና ንብረት ገበያው እየጦዘና እየከረረ እንደሚሄድ የሚያመላክቱ ፍንጮች መታየት ጀምረዋል፡፡
ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ከተሞችን ለማዘመን የታቀዱት ውጥኖችና በማተርፕላኑ የተከተቡት ውብ መንደሮች ከነባራዊው ዕውነታ ጋር እየተጣረሱ እንደሚገኙ ዋትሰን ይተቻሉ፡፡ አብዛኞቹ ከተሞች ውስጥ ነዋሪው በአብዛኛው ሥር በሰደደ ድህነትና ቅጥ ባጣ አሰፋፈር የሚኖር በመሆኑ ህልመኞቹን ዕቅዶች በመተግበር፣ አብረቅራቂዎቹን የተኮረጁ ሕንፃዎች መገንባት ሊታሰብበት እንደሚገባ ምሁሯ በጥናታቸው ተችተዋል፡፡ አንዳንዶቹ የተዘበራረቁት አሰፋፈሮችና ሰፋሪዎቹ፣ አልሚዎችን በሚያማልሉ የከተሞቹ ክፍሎች ውስጥ የተቸመቸሙ በመሆናቸው ምክንያት ሥጋቱን ይበልጥ ያባብሱታል፡፡ በመሆኑም ቅንጦተኞቹን አዳዲስ የከተማ ልማት ዕቅዶችን በእነዚህ አካባቢዎች እንዲተገበሩ ማድረግ፣ ድሆችን የማግለል ተግባር ያከትላል ሲሉም ዋትሰን አስጠንቅቀዋል፡፡ አብዛኞቹን ከቤት ንብረታቸው በማንሳት ወደሌሎች አካባቢዎች ማዛወርና ማስወጣትን ስለሚያስከትል ጭምር የህልም ዓላሚዎቹን ከተሞች ለመፍጠር የሚደረገውን ሩጫ ይተቹታል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2008 ከተከሰተው የዓለም የፋይናንስ ቀውስ በኋላ በየትኛውም የዓለም የንብረት ዋጋ እየወረደ መጥቷል፡፡ በአፍሪካ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በከተማ ልማት መስኮች ላይ መሰማራቱ አዲስ ተግባር ባይሆንም፣ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ያመጡት እንቅስቃሴ ግን በአዲስነቱ እየታየ የመጣ ነው፡፡
የዋትሰን ጥናት በአፍሪካ የከተሞች ማስፋፋት ወይም አዲስ ሳተላይት ከተሞችን በመገንባት ላይ ያተኮረውን አካሄድ የሚገመግም ሲሆን፣ እነዚህ ህልመኛ ከተሞች መጠነሰፊ መሆናቸውን፣ በእነዱባይ፣ ሻንጋይና ሲንጋፖርን በመሳሰሉ ከተሞች ጫና የሚማልሉ ሆነው መገኘታቸውንም ጥናቱ ይቃኛል፡፡ በየድረ ገጹ የሚታዩት መጪዎቹ የአፍሪካ ከተሞች ዕቅዶች ውይይት ተደርጎባቸው እንደሆነ ወይም ዲሞክራሲያዊ ክርክር ተደርጎባቸው ይሁን አይሁን የሚገልጽ ምልክት የማይታይባቸው መሆናቸውም ለቅጅነታቸው ማሳያ እየተደረገ ሲሆን በተለይ በኡጋንዳ፣ በኬንያ፣ በጋና እንዲሁም በታንዛንያ ይገነባሉ ተብለው ይፋ ከተደረጉት አዳዲስ የዘመኑ ከተሞች ጥያቄ ተነስቶባቸዋል፡፡
‹‹ናይሮቢ ሜትሮስትራቴጂ 2030›› ተብሎ የሚታቀውና በኬንያ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2008 ይፋ የተደረገው ዕቅድ፣ ናይሮቢን ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን አፍሪካ ሜትሮፖሊስ ከተማ ለመመሥረት ያለመ ነው፡፡ ዕቅዱ ይፋ መውጣቱን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የዲዛይን ጨረታ ይፋ ተደርጓል፡፡ በዕቅሱ መሠረት 15 ያህል ዘመናዊ ሳተላይት ከተሞች ይገነባሉ ተብሎም ነበር፡፡ አንዱም እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ናይሮቢ ሜትሮስትራቴጂ የተባለው ዕቅድ ሲወጣ መነሻ የተደረገው ምክንያት እናቲቱ ናይሮቢ ከተማ ከሚገባት በላይ መጨናነቋን በማስመልከት ነው ተብሏል፡፡ በመሆኑም አዲሱ ሳተላይት ከተማ እያደገ ያለውን የሕዝብ ቁጥር ከእናት ከተማዋ ናይሮቢ ለማስተንፈስ እንደሚረዳም ታምኖበታል፡፡ በመሆኑም ‹‹ታቱ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ ከተማ በቡና አብቃይነቱ በሚታወቀው የኬንያ ክፍል ከተገነባ በኋላ 70 ሺሕ ነዋሪዎችንና 30 ሺሕ ተጨማሪ ሰዎችን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 30 ሺዎቹ ቀን ቀን እየሠሩ ወደናይሮቢ የሚመለሱ የቀን ነዋሪዎች ናቸው ማለት ነው፡፡
ከናይሮቢ 60 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ ይገነባል የተባለው ኮንዛ ቴክኖ ሲቲ ደግሞ የቴክኖሎጂ መንደር ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ አዲስ ከተማ ሲሆን፣ በዕቅዱ መሠረት 30 ሺሕ ነዋሪዎች ይኖሩታል ተብሎ ታስቧል፡፡ ለመጀመሪያ ዙር ግንባታው ሦስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ከሰባት ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ሊከለልለት እንደሚችል ተነግሯል፡፡ የኬንያ መንግሥት ይህንን ከተማ በግሉ ሊያለማለት፣ ለወጪው የሚሆነውን ገንዘብም ይዞ የሚመጣ ኢንቨስተር በማፈላለግ ላይ ይገኛል፡፡ ሆኖም በተለያየ ጊዜ የወጡ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት መንግሥት ከአገሬው ባለይዞታዎች ጋር አለመግባባት ውስጥ ይገኛል፡፡
ጋና ከዋና ከተማዋ አክራ ወጣ ብሎ ሆፕ ሲቲ ብላ የሰየመችውን የቴክኖሎጂ ከተማ ለመግንባት ዕቅዷን ይፋ አድርጋለች፡፡ በጋና ኩባንያ ይገነባል የተባለው ይህ ከተማ አሥር ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል ተብሏል፡፡ 25 ሺሕ ነዋሪዎችንና 50 ሺሕ ሠራተኞችን ያስተናግዳል የተባለው ይህ ከተማ፣ ከነባሩ አካባቢ ጋር የሚገናኘው ምንም ዓይነት ትስስር አለመኖሩ አስተችቶታል፡፡ አንጎላና ታንዛንያም ተመሳሳይ ዕቅድ ይዘዋል፡፡ በተለይ አንጎላ የምትገነባቸው አዳዲስ የሳተላይት ከተሞች ውስጥ የሚገነቡት ሕንፃዎች ይኖራቸዋል ተብሎ የሚጠበቁት አፓርታማዎች ሲሸጡ፣ ከ150 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ ዶላር ገንዘብ የሚጠይቁ በመሆናቸው፣ አብዛኛው ሕዝቧ ከሁለት ዶላር በታች በቀን እያገኘ ለሚኖርባት አገር ቅንጦት አሰኝቶባታል፡፡ በዋና ከተማዋ ሉዋንዳ ውስጥ የሚገነባው ሉዋንዳ ሳተላይት ከተማ 890 ሺሕ ነዋሪዎችን እንዲያስጠልል የሚታሰብ ነው፡፡ ዲዛይኑን የሠራው ኩባንያ ሳይቀር በቅንጦተኝነቱ (ቢሮዎቹ በቤሩት፣ በለንደንና በካይሮ ይገኛሉ) የተተቸባት አንጎላ፣ አብዛኛው የከተማ ነዋሪ ሕዝቧ አሰፋፈር መደበኛ ካለመሆኑም በላይ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ በሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ተፈናቅሎ እዚህም እዚያም ሰፍሮ የሚገኝ በመሆኑ እንዲህ ያለውን የቅንጦት ከተማ ለመገንባት ማሰቧ እያስተቻት ይገኛል፡፡
ያልተመጣጠነ የኑሮ ደረጃ እንዲፈጠር፣ በሀብታምና በድሃው መካከል የሚታየው ከፍተኛ የኑሮና የኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲከሰት የሚያደርጉ የቅንጦት ከተሞች እየመጡ መሆናቸው አግባብ አይደለም ሲሉ ዋትሰን ይተቻሉ፡፡ አርጅተዋል የተባሉ ከተሞችን በማፍረስ አዳዲስ ቅንጡ ከተሞችን መገንባቱ ነባሮቹን የከተማ ነዋሪዎች ከማፈናቀልና የንብረት ባለቤትነታቸውን ከማሳጣት በላይ፣ የኢኮኖሚ አቅማቸውንና መተዳደሪያቸውንም መንጠቅ እንደሆነ የዋትሰን ጥናት ዋቢ አለው፡፡
በኢትዮጵያስ;
በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ግንባታዎችና የከተማ ልማት ሥራዎች እንደሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች ያህል ድሃውን ለችግር እንደማያገጋልጡ፣ በድሃውና በሀብታሙ መካከል ያለውን የኑሮ ልዩነትም ይበልጥ ያስፋፋሉ ተብሎ እንደማይታሰብ የሚገልጹ ባለሙያዎች አሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ማኅበረሰብ (ሶሺዎሎጂ) መምህር የሆኑት ዶክተር የራስወርቅ አድማሴ፣ በዚህ ክልል ውስጥ ከሚጠቀሱ ምሁራን መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በእሳቸው እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ለግሉ ዘርፍ ደረጃቸው ከፍ ያሉ የሀብታም መኖሪያዎች እንዲገነቡ ከመፍቀዱም ባሻገር መካከለኛና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላላቸው ሰዎች የሚሆኑ አንድ ሚሊዮን ቤቶችን በአሥር ዓመት ውስጥ፣ 100 ሺሕ ቤቶችን በዓመት ውስጥ እገነባለሁ ማለቱ፣ በሀብታምና በድሃው መካከል ያለውን ልዩነት እንዳይሰፋ የሚረዳ መሆኑን ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰዎች (10/90 የቤት ልማት ዕቅድ) 24 ሺሕ ቤቶችን ገንብቶ ዘንድሮ እንደሚያስርክብ ይፋ ማድረጉና፣ 23 ሺሕ ሰዎችም መመዝገባቸውን ዶክተር የራስወርቅ አስታውሰዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ቅድሚያ ክፍያ መቆጠብ የሚጠበቅባቸው አራት ሺሕ ብር መሆኑም ድሃ ተኮር ግንባታዎች እየተካሄዱና መንግሥት ለእነሱም ትኩረት መስጠቱን እንደሚያመለክት ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር 20/80 እንዲሁም 40/60 የተባሉት የቤት ግንባታዎች ለአነስተኛውና መካከለኛው ነዋሪ የተዘጋጁ በመሆናቸው በኢትዮጵያ የሚካሄዱት ግንባታዎች፣ በድሃውና በሀብታሙ መካከል ያለውን የኑሮ ልዩነት ለማጥበብ እንደሚረዱ በመግለጽ ይከራከራሉ፡፡ ይህም ሲባል ግን ችግሮች የሉም ማለት እንዳልሆነ ይታወቅልኝ ያሉት ዶክተር የራስወርቅ፣ በኢትዮጵያ ያለው የቤት ችግር፣ ከኪራይና ከዋጋ ጋር በተያያዘ የሚጠቀስ ትልቅ ችግር እንደሚታይበት ይናገራሉ፡፡ በዚህ መቀጠል የለበትም ሲሉም ያሳስባሉ፡፡ ሆኖም መንግሥት የሚያካሂዳቸው የቤት ግንባታዎች አሁን የሚታየውን ችግር እንደሚቃልሉ ያምናሉ፡፡
የአፍሪካ መዲና ለሆነች ከተማ የሚካሄዱት ግንባታዎች አያንሷትም የሚሉት ዶክተር የራስወርቅ፣ በአዲስ አበባ የሚታየው የሀብታሞች ግንባታም በቅንጦት የተጨማለቀ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ነፃ ከወጣች ከ20 ዓመት በኋላም የጥቁሮች የቤት ችግር እንዳልተፈታ ሆኖም አገሪቱ በዓለም ላይ የነጭ ወርቅን ጨምሮ ልዩ ልዩ የከበሩ ማዕድናት መገኛ ብትሆንም ከቤት አቅርቦት መሠረታዊ ችግር አለመላቀቋን ማጣቀሻ ያደርጋሉ፡፡
ከዚህ ይልቅ የሚተኮርበት ነገር አለ የሚሉት ምሁሩ፣ በተገነቡትና እተገነቡ ባሉት የኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ ለዕድር፣ ለሠርግና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች የሚውሉ አዳራሾችን መገንባት እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ የመኪና ማቆሚያ፣ የሕፃናት መጫወቻዎች ይታሰብባቸው ይላሉ፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የውኃ አቅርቦት በአግባቡ ሊታይ ይገባል ሲሉም ያስጠነቅቃሉ፡፡ በየጊዜው እየጨመረ ለመጣው የኮንዶሚኒየም ቤት፣ ለንጽህና ፍጆታ የሚውል ውኃ አቅርቦት ላይ መንግሥት ሊያስብ እንደሚገባው ባለሙያዎች እያተኮሩበት መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ በየዓመቱ መቶ ሺሕ ቤት የሚገነባ ከሆነ መቶ ሺሕ ቤት ውስጥ ለመታጠቢያ፣ ለሽንት ቤት አገልግሎት የሚውል የውኃ አቅርቦት ስለሚያስፈልገው ይህንን ጥያቄ እንዴት ሊያስተናግደው እንደሚችል ለመንግሥት መጠቆሙና መወትወቱ እንደሚሻል ይመክራሉ፡፡
በሌላ በኩል የተገነቡትና እየተገነቡ ያሉት ኮንዶሚኒሞች የአንዳንድ ነዋሪዎችን ኑሮ እያናጉ እንደሚገኙም ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ጠላ በመሸጥ፣ እንጀራ በመጋገርና በመሳሰሉት መተዳደሪያዎች ኑሯቸውን ይገፉ የነበሩ ሰዎችን ከአካባቢያቸው በሚነሱበት ወቅት፣ ለሚሰጣቸው የኮንዶሚኒየም ቤት ቅድሚያ ክፍያ እንዲከፍሉ ከመጠየቅ ጀምሮ ቀድሞ በሚተዳደሩበት ሁኔታ ኑሯቸውን ለመግፋት አለመመቸቱን በመጥቀስ የሚተቹ የማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁራን የቤት ሥራው፣ አኗኗርን አሻሽሏል ለመባል መሠረታዊ መተዳደሪያቸውንም ታሳቢ ማድረግ ነበረበት በማለት መንግሥትን ይተቻሉ፡፡
No comments:
Post a Comment