Liberalization of Telecom in #Ethiopia - የኢትዮጵያ መንግስት የቴሌኮም ዘርፍን ለግል ባለሀብቶች እንዲሰሩበት (Liberalization) መፈቀድን በተመለከተ ጥብቅ አቋም ይዞ የቴሌኮም ዘርፍ ከመንግስት እጅ እንደማይወጣ ለረጅም ጊዜያት ሲገልጽ መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡
ይህ ሁኔታም በፋንታው በጉዳዩ ዙሪያ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ሌሎችም ሀሳባቸውን ሲሰነዝሩበት የቆዩበት ጉዳይ ነው፡፡ የብዙዎች ወቀሳ ዋንኛ የማጠንጠኛ ነጥብ፣ ኢትዮቴሌኮም፣ ያለተቀናቃኝ የያዘውን የሀገሪቱን የቴሌኮም ዘርፍ ከሌሎች ሀገራት ወደኋላ አስቀርቶታል ነው፡፡
በተቀሩት የአፍሪካ ሀገራት የሞባይል ስልክ ተጠቃሚው ቁጥር 70% ይህል የደረሰ ሲሆን በኢትዮጵያ ግን 25% ላይ ነው ያለው፡፡ ጎረቤታችን ኬንያ 40% ህዝቧ የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በአንጻሩ 2.5% ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው የኢንተርኔት ተጠቃሚ መሆን የቻሉት፡፡
ምንም እንኳ መንግስት በዓመት 300 ሚሊየን ዶላር ገቢ የማገኝበትን የቴሌኮም ዘርፍ እንዲህ እንደዋዛ የውጭ ተቀናቃኝ ኩባንያዎችን አላስገባበትም፣ ከዘርፉ በኢትዮቴሌኮም በኩል የማገኘውን ገቢም ለሌሎች ዘርፎች መደጎሚያ እጠቀመዋለሁ ሲል ቢሰማም፣ ያለተወዳዳሪ በመስራቱ ሳቢያ ኢትዮቴሌኮም የሚጠበቅበትን እንዳልሰራና ይህም ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ማነቆ እንደሆነ ብዙዎች የሚያነሱት ነጥብ ነው፡፡
ዘ ኢኮኖሚስት በቅርቡ ባወጣው አንድ ጽሁፍ ላይ ግን የኢትዮጵያ መንግስት ሌሎች የቴሌኮም ኩባንያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ቢፈቅድ አሁን ከሚያገኘው ገቢ በላቀ መልኩ 3 ቢሊየን ዶላር ያህል ማግኘት እንደሚችል አላጣውም፣ ነገር ግን በኢትዮቴሌኮም በኩል የሀገሪቱ የጸጥታ ሀይሎች ሊኖራቸው የሚችውን የቁጥጥር ስርዐት የሚያሳጣቸው ስለሆነ ነው ይላል፡፡
ይህን ጉዳይ አስመልክቶ አዲስ አበባ ላይ በሚታተመው ካፒታል በተሰኘው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ላይ የግል አስተያየታቸውን የሰጡት የኧርነስትና ያንግ ኩባንያው ማኔጂንግ ፓርትነር ዘመድነህ ንጋቱ እንደሚሉት፣ የሀገሪቱን የባንክ ዘርፍ ለውጭ ባንኮች አለመከፈቱ ሀገሪቱ ውስጥ ሀብት እንዲፈጠር አስችሏል - ጠቃሚ ነው…የቴሌኮም ዘርፍን በተመለከተ ግን በተወሰነ መልኩ ዘርፉን መክፈት ይገባል ባይ ነኝ ይላሉ፡፡
ያለውድድር በመስራቱ ብቃት በጎደለው ኢትዮቴሌኮም ሳቢያ ኢኮኖሚው ላይ የደረሰው ጉዳት ቀላል አይደለም የሚሉት ዘመድነህ፣ እኔ መንግስትን ብሆን ኢትዮጵያውያን ሌላ አንድ ወይም ሁለት የቴሌኮም ኩባንያ እንዲከፍቱ የሚደረግበትን ሁኔታ አመቻቻለሁ፣ ከዛ ቀስ በቀስ ለውጪዎቹም መፍቀድ ይቻላል ይላሉ፡፡
sourcehttp://diretu.be/632297
No comments:
Post a Comment