Friday, December 27, 2013

የአቶ ኢያሱ አለማየሁ ነገር “ግመል ሰርቆ አጎንብሶ”

(አዲስ አበባ ከሚታተመው ሎሚ ጋዜጣ ላይ የተወሰደ)
ለአቶ ኢያሱ አለማየሁ ‘መልዕክት’ … ከኢሕአፓ መስራች የተሰጠ የአጸፋ ምላሽ
መርዕድ ከበደ
ኅዳር 28 ቀን፣ 2006 ዓ/ም በወጣው ሎሚ መጽሔት ላይ “የኢህአፓ መሪ ኢያሱ ዓለማየሁ ወቅታዊ መልዕክት” የሚል ጽሑፍ ወጥቶ አነበብኩ፤ እኔም ብርሃነ መስቀል ረዳ “አፋኝ የሚለውን የኢህአፓ አመራር” ከኤርትራ ነፃ አውጪዎች ግንባሮችና ከሱማሌ መንግሥት ጋር በማበር ፀረ-ኢትዮጵያ፣ ፀረ-ሉዓላዊነት ተግባር ፈጽሟል ብዬ ከማስረጃ ጋር በተከታታይ ሎሚ መጽሔት ላይ ጽሑፍ አውጥቼ ስለነበረ፣ የእርሳቸው ጽሑፍ አግባብ ባለው ተቃራኒ ማስረጃ ማስረጃዎቼን ወይ ያስተባብሉታል አለያም ‘ስህተት በመፈጸማችን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን፣ አሁን ታርመናልና ለአዲሲቷ ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያ አብረን እንታገል’ ይሉናል ብዬ ነበር የጠበቅኩት፡፡
እርሳቸው ግን “በኢህአፓነቴ በጣም እኮራለሁ፤ የዚህ ድርጅት አባል ባልሆን ኖሮ ህይወቴ የባከነ ይሆን ነበር ብዬም አምናለሁ፤ የአፄውን ስርዓት ለመጣል በተደረገው ትግል መሳተፌም ያኮራኛል፤ ብዙዎቹ ሲያንቀላፉ የግንጠላ አቀንቃኞችን በመታገል የህዝብ እኩልነት ይከበር ብለን በመቆማችንም ተደሳች ነኝ፤ የባዕዳን ወራሪዎችና በዳዮችን ያኔም አሁንም መቃወሜና የድርጅቱን መስመር ማስከበሬም ተገቢ ነው ባይ ነኝ፤ ኢህአፓ አንዴም ቢሆን ለድርጅታዊ ጥቅም ሲል የሀገርን ጥቅም አሳልፎ ባለመስጠቱ እንኳንስ ኢህአፓ ሆንኩ እላለሁ” ብለው አረፉት፡፡ ከኢሕአፓ አመራሮች አንዱ የነበሩት አቶ ክፍሉ ታደሰ ግን እንደ እርስዎ በኢሕአፓነታቸው አልፎከሩም፡፡ ይልቅስ፤ “በትግሉ ንቁና ግንባር ቀደም ሚና ከነበራቸው ግለሰቦች መሀል አንዱ እኔ እንደመሆኔ፣ ይጠበቅብኝ የነበረውን ለማበርከት ባለመቻሌ ልባዊ ሀዘን የተቀላቀለበት ይቅርታ እጠይቃለሁ” ነው ያሉት፡፡
አቶ ኢያሱ፣ ሌላው ቢቀር ከ14 ዓመት ዕድሜ በታች ያሉትን ልጆች በማደራጀት መሣሪያ አስታጥቃችሁ ላስፈጃችኋቸው፣ ሮጠው ላልጠገቡ ጮርቃ ልጆች ወላጆች እንደ አቶ ክፍሉ ታደሰ ተገቢውን ይቅርታ መጠየቅ ነበረብዎ እላለሁ፡፡ እኔ መቼም ለረዥም ዓመታት በመኢሶንም ሆነ በኢሕአፓ በኩል የተከናወኑ ስህተቶችም ሆኑ መልካም ነገሮች ካሉ በግልጽ ቀርበው እንወያይበትና አዲሱ ትውልድ ስህተቱን እንዳይደግም፣ ከጠንካራ ጎናችንም ትምህርት ይውሰድበት ብልም የቀድሞዎቹም ሆኑ የአሁኖቹ ኢሕአፓዎች ለመወያየት ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም ነበር፡፡
አሁን ግን ከ40 ዓመት በኋላም ቢሆን ቅሉ፣ አቶ ኢያሱ ዓለማየሁ በኢሕአፓ በኩል የተፈፀመ ጥፋት የለም፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ ነገርም አልተፈጸመም ብለዋል፡፡ ለውይይት መነሻነት ያሕል የእርሳቸው መልስ የሚበቃን ይመስለኛል፡፡ የውይይት መድረኩ ለኔና ለርሳቸው ብቻ መለቀቅ ያለበት አይመስለኝም፡፡ በዚያን ወቅት በትግሉ ውስጥ የነበራችሁ በውይይቱ ብትካፈሉ በትምህርት ሰጪነቱ ከምትገምቱት በላይ ለወጣቱ ትውልድ ጠቃሚ ነው እላለሁ፡፡ ወጣቱም ትውልድ የሚጠይቀን ነገር ካለ መልካም ነው፡፡ ስህተትን ባለመድገም ጠንካራ ኢትዮጵያን መገንባት የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እንደ አቶ ኢያሱ ዓለማየሁ የኢሕአፓ መሥራች አባል ስሆን፣ የኢሕአፓ አመራር ድርጅቱ ገና በቅጡ ስለ ሀገሪቷ ሁኔታ ተወያይቶ የሚበጀውን አማራጭ አባላት ሳይመክሩበት፣ በተቋቋመ ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ለትጥቅ ትግል በረሀ ገባ፡፡ በጥቂት የአመራር አባላት ውሳኔ በቅጡ ያልተደራጀውን ኢትዮጵያዊ ድርጅት ወስደው ኢትዮጵያዊ ራዕይ ከሌለው ከኤርትራ ተገንጣይ ግንባር ሥር ጥገኛ አደረጉት፡፡ እኔም ይኼንን አዝማሜያ ቀደም ስልም እቃወም ስለነበር ነፃ ውይይትን ከማያደፋፍረው ድርጅት ራሴን በጊዜ አገለልኩ፡፡ የፈራሁትም አልቀረ ጥፋቱ ከኢትዮጵያ ድሀ ገበሬ ጋር ጦርነት በመክፈት ተጀመረ፡፡
የኤርትራ ግንባሮችና የሶማሊያ መንግሥት የሆኑት ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች፣ ከድርጅቱ በሚሠጣቸው መረጃና ወታደራዊ ድጋፍ ተጠቅመው የኢትዮጵያን መከላከያ ኃይል ለማጥቃት ቻሉ፡፡ አቶ ኢያሱ አለማየሁ ይኼ ሁሉ አልሆነም ነው የሚሉት፡፡ የአቶ ኢያሱ ዓለማየሁ ወቅታዊ መልዕክት ለኔ “ግመል ሰርቆ አጎንብሶ” ነው የሆነብኝ፡፡ ሰውዬው ስለ የትኛው አዎንታዊ ትግላቸው እንደሚፎክሩ አይገባኝም፡፡ ያመፀ ሁሉ አብዮተኛ ነው ማን እንዳላቸው አላውቅም፡፡
እኔ የማውቀው በአብዮቱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ስናደርግ የነበርነውን፣ ቅንድብ ቅንድባችንን እያሉ ሲጥሉን ነው የማስታውሰው፡፡ እንደ ተገነዘብኩት ከሆነ አቶ ኢያሱ ባለፈው ሥራቸው አልተፀፀቱም፤ ዕድሉን ካገኙ የበፊቱን ተግባራቸውን እደግመዋለሁ የሚሉም ይመስለኛል፡፡ እርሳቸው ብርሃነ መስቀል ረዳ አፋኝና አምባገነን አመራር ከሚለው አንዱ መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ አቶ ኢያሱ፣ አንድ ነገር ላስገነዝብዎ እወዳለሁ፡፡ ኢሕአፓ ከኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባሮችና ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ሆኖ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ወግቷል ያሉት እርስዎ እንደሚሉት የደርግ አባላት ብቻ አይደሉም፤ የኢሕአፓ አባል ሆነው የታገሉም ጭምር ናቸው፡፡
እንደሚያውቁት በ1964 ዓ/ም ላይ፣ በኋላ ኢሕአፓ ብለን የሰየምነውን ድርጅት ስናቋቁም፣ ከእርስዎ ጋራ አቶ ክፍሉ ታደሰም የአመራር አባል ሆነው እንደተመረጡ አይዘነጉትም፡፡ እርስዎ የድርጅቱን የውጪ ጉዳይ እንዲከታተሉ አውሮፓ ሲቀሩ፣ አቶ ክፍሉ ታደሰ ከሌሎች የአመራር አባላት ጋር ወደ ሀገር ቤት መግባታቸውንም የሚዘነጉት አይመስለኝም፡፡ እኚህ ግለሰብ ድርጅቱ በአገር ውስጥ ስላከናወነው ጉዳይ ከእርስዎ የበለጠ እንደሚያውቁ እርስዎም አይክዱኝም፡፡ እንግዲህ እርስዎ የካዱትን የኢሕአፓን ድርጊት እርሳቸው በሚቀጥለው መልኩ ነው ያቀረቡልን፡፡
ኢሕአፓ ከኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባሮች ጋር ሆኖ ለአገሩ ዳር ድንበር መከበር ሲዋትት የነበረውን የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት መውጋቱ እርግጥ ነው፡፡ ጥቂቶቹን የውጊያ ውሎዎች ከአቶ ክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” መጽሐፍ ላይ አብረን እንያቸው፡፡
1. በ1969 ዓ/ም በመስከረም ወር፣ በትግራይ ክፍለ ሀገር የኢህአሠ ሠራዊት አሃድና የኤርትራ ህዝባዊ ሀርነት ግንባር በመተባበር ባደረጉት ውጊያ፣ ወደ ኤርትራ በመንቀሣቀስ ላይ የነበረውን የደርግ ኃይል በመምታት መሣሪያዎችና ልዩ ልዩ ወታደራዊ ትጥቆች ተገኝተዋል፡፡
(ቅጽ 3 ገጽ 272)
2 . የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊትም (ኢህአሠ) ዘመቻውን በመቃወም ተመሣሣይ ቅስቀሳ ከማድረጉም ሌላ፣ በግንቦት ወር 1968 ዓ/ም ላይ፣ ከኤርትራ ሓርነት ግንባር (ጀብሃ) ጋር በመተባበር ውጊያዎች አካሒዷል፡፡
(ቅጽ 2 ገጽ 51)
3.በመጨረሻም ሁለቱን ወንድማማች ሕዝቦች የሚያፋጀውን ጦርነት ለማስቆምና ከኤርትራ ሕዝብ ጋር የትግል አንድነት ለመመሥረት ሲባል፣ ተራማጆች የኤርትራን ነፃነት እንዲያውቁ የኢሕአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ወሰነ፡፡
(ቅጽ 2 ገጽ 304)
እነዚህ መቼም የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር የተወሰዱ ወታደራዊ እርምጃዎችና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ናቸው አይሉኝም፡፡ ኢሕአፓ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር በተለያየ ጊዜ የተዋዋለው ውል እንደነበረው እርስዎ የውጪ ጉዳይ ኃላፊ እንደመሆንዎ መጠን ያውቃሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ በገባችሁት ውል መሠረት ይመስለኛል የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሶማሊያ ጦር ጋር እንዳይዋጋ ቅስቀሳ ታደርጉ የነበረው፡፡
ስለዚሁ ጉዳይ አቶ ታክሎ ተሾመ “የደም ዘመን” ብለው በግንቦት 2003 ዓ/ም ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ ገልጸውታል፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ የደርግ አባል ሳይሆኑ የኢሕአፓ አባል እንደነበሩ ልብ ይበሉልኝ፡፡
በጦርነቱ ወቅት ከሶማሊያ መንግሥት ጋር የነበራችሁ ግንኙነት በድርጅቱ ውስጥ አለመግባባት ፈጥሮ እንደነበር አቶ አስማማው ኃይሉም “ኢሕአሠ፤ ከ1964-1970 ዓ.ም” ቅጽ 1 ገጽ 207 ላይ፤ “ሁሉም የዞን አመራር አባላት ባሉበት ውይይት ተከፍቶ በእኔ እና በጸሎተ መካከል በአንዳንድ የፓርቲው አቋሞች ላይ አለመግባባት ተከሰተ፡፡ ኢሕአፓ በሶማሊያና በኢትዮጵያ ጦርነት ላይ የወሰደው አቋምና በኢሕአፓ የቅድመ ትውውቅና የዝምድና ሥራዎች ጎልተው ይታያሉ በሚሉ አጀንዳዎች የተካረረ ውይይት ከተካሔደ በኋላ ጸሎተ በእኔ ላይ ጥርጣሬ አሳደረ (ያሬድ)” ብሎ ጽፎታል፡፡
ከዚህም አልፋችሁ ተርፋችሁ በኢትዮጵያ ሠራዊት ብርታት ወደ ሐብሮ አውራጃ እንድታፈገፍጉ እስከተገደዳችሁበት ጊዜ ድረስ፣ ከምዕራብ ሶማሊያ ነፃ አውጪ ግንባርና ከሱማሌ አቦ ነፃ አውጪ ግንባር ጋር በመሆን ግዛት አላስቆርስም ባለው ሠራዊት ላይ በጋራ ውጊያ አካሒዳችኋል፡፡ ይኸንኑም አቶ ክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” ብለው በሰየሙት መጽሐፋቸው ቅጽ III ገጽ 232 ላይ አስፍረውት ይገኛል፡፡ እነዚህ ሁለት ግንባሮች ደግሞ በዚያድ ባሬ መንግሥት የጦር መኮንኖች የሚመሩ እንደነበሩ ኢሕአፓ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፡፡
እርስዎ እንግዲህ ዐይኔን ግንባር ያድርገው ካሉ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ መቼም ከፍ ብለን የጠቀስናቸው ኃይሎች ለኢትዮጵያ መልካም አሳቢ እንዳልሆኑ ይታወቃል፡፡ ኢሕአፓ መኢሶንን ከደርግ ጋር ተባበረ ብሎ እያወገዘ፣ (ያውም ደርግ አብዮቱን በሚመራበት ወቅት በመተባበሩ) ምን ይበጀኝ ብሎ ነው ብሔራዊ ጥቅማችንን ከሚፃረሩ ኃይሎች ጋር ተባብሮ በብሔራዊ ጥቅማችንና በአብዮታችን ላይ አብሮ የዘመተብን? አቶ ኢያሱ ይኼ ሁሉ ሀሰት ነው የሚሉኝ ከሆነ፣ የሚኮሩበትን ኢሕአፓ ነፃ ሊያወጡት የሚችሉት በአንድ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ይኼውም እስካሁን ድረስ ከኢትዮጵያ ሕዝብና አምነው ከተከተሏችሁ አባሎቻችሁ ጭምር ምስጢር አድርጋችሁ የያዛችሁትን የውል ሠነድ፣ ማለትም ከኤርትራም ሆነ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር የተዋዋላችሁትን ሙሉ ይዘቱን ይፋ ያድርጉት፡፡ የውል ሰነዱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ሆኖ ካገኘነው፣ ያሉትን ሁሉ እናምንዎታለን፤ ይህንን ማድረግ ካልፈቀዱ ግን፣ በአቶ ክፍሉ ታደሰና በሌሎቹ የኢሕአፓ አባሎች የቀረቡልንን ማስረጃዎች ማመን አንገደዳለን፡፡
በአብዮቱ ወቅት የኢትዮጵያ ተራማጆች ከደርግ ጋር የፖለቲካ ሕብረት ፈጥረው የታገሉት፣ የብሔራዊ አብዮታዊ ዲሞክራቲክ ፕሮግራም በአዋጅ አውጀው ይፋ በሆነ መንገድ ስለሆነ፣ ፕሮግራሙ የኢትዮጵያን ሠፊ ሕዝብ ጥቅም ይፃረር አይፃረር እንደነበረ መነጋገር ይቻላል፡፡ በእናንተ ጎራ መካከል የነበረው ውል ግን ድብቅ ስለሆነ እስካሁን ድረስ በስምምነት ሠነዳችሁ ላይ መወያየት አልቻልንም፡፡ እኛ የታገልንለትን የብሔራዊ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፕሮግራምን ረስቼዋለሁ በይፋ አውጣው ካሉኝ፣ ለማውጣት ዝግጁ ነኝ፡፡
የታሪኩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ አመራሩን በማመን ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ አባሎቻችሁ፣ በደርግ ምርመራ የተሰቃዩትና በረጅም ዓመት እስር ሕይወታቸው የተመሰቃቀለባቸው የኢሕአፓ አባላት ጭምር የሰነዶቹን ሙሉ ይዘት ማወቅ አለባቸው፡፡ ይኼንን ሰነድ ደብቃችኋቸው እንደገና ተከተሉን ብላችሁ ዳግም ከተከተሏችሁ፣ ሁለት ጊዜ በእባብ የተነደፈውን ሞኝ ሰው ነው የሚያስታውሱኝ፡፡
በነገራችን ላይ አቶ ኢያሱ እግረ መንገድዎን “ያንኪ ጎ ሆም” ብለን የሸኘናቸው አሜሪካኖች ካርቱም ድረስ አውሮፕላን ይዘው መጥተው ወደ አሜሪካን እንዴት ሊወስዷችሁ ቻሉ? ይኽንን ዐይነት ድርጊት ከዚህ ቀደም ለሌሎች “ኮሙኒስቶች” ያደረጉት አይመስለኝም፡፡ ከናንተ መሀል ለአሜሪካኖች የሚሠሩ ነበሩ ልበል? …በትግሉ ወቅት የፖለቲካ ትምህርት ቤቱን በፈንጂ አጋይታችሁታል፤ በአዲስ አበባና በኢሉአባቦራ የከፈትናቸውን መጽሐፍት ቤቶች አቃጥላችኋል፤ በድንጋይም ደብድባችኋል፡፡ መቼም ማርክሲዝምን መዋጋት የእናንተ ዓላማ ሳይሆን የሲአይኤ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ነው የምጠይቅዎ፡፡ መልስዎን እጠብቃለሁ፤ አበቃሁ፡፡

No comments:

Post a Comment