Wednesday, December 18, 2013

የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊው የመጽሐፋቸው ሻጭና ገንዘብ ሰብሳቢ ሜጋ ማተሚያ ቤት ነው አሉ

18 DECEMBER 2013 ተጻፈ በ  

የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊው የመጽሐፋቸው ሻጭና ገንዘብ ሰብሳቢ ሜጋ ማተሚያ ቤት ነው አሉ

-ከእህትና ከወንድማቸው ጋር የተመሠረተባቸው ክስ ውድቅ እንዲሆን ጠየቁ
በሥልጣን አላግባብ የመገልገል ወንጀል ከቀድሞው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጋር ከተመሠረተባቸው ክስ በተጨማሪ ከእህታቸው፣ከወንድማቸውና ከቅርብ ጓደኛቸው ጋር
በሌላ የክስ መዝገብ አዲስ ክስ የቀረበባቸው የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅነነት አገልግሎት የአገር ውስጥ ኃላፊ አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤል፣ “Terrorism in Ethiopia and the Horn of Africa” የሚለው መጽሐፋቸው ሻጭና ገንዘብ ሰብሳቢ እሳቸው ሳይሆኑ፣ ሜጋ ማተሚያ ቤት መሆኑን ተናገሩ፡፡ 
አቶ ወልደ ሥላሴ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸውን ክስ ለሚመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ታኅሳስ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ እንዳስታወቁት፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ እሳቸው መጽሐፉን ለተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከሸጡና ገንዘቡን ከተቀበሉ በኋላ ለድርጅቶቹና ለግለሰቦቹ መጽሐፉን እንዳልሰጧቸው ገልጿል፡፡ ነገር ግን የመጽሐፉን ሽያጭ ያከናወነው ሜጋ ማተሚያ ቤት ነው፡፡ ገንዘቡን የተቀበለውም ማተሚያ ቤቱ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ወይም ድርጅት የገዛውን ዕቃ ከገዛበት ቦታ መውሰድ ይችላል፡፡ ካልወሰደም ድርጅቱን መጠየቅ ይችላል፡፡ ይኼም ትክክለኛው የሕግ አካሄድ ነው፡፡ ሜጋ ማተሚያ ቤት መጽሐፉን ለገዛው ወገን አላስረክብም አለማለቱንና ያልወሰደ ካለ ከሜጋ ማተሚያ ቤት መውሰድ እንደሚችል በመቃወሚያ መልሳቸው ገልጸዋል፡፡ 
የመጽሐፉን ሽያጭ በሚመለከት የቀረበባቸው ክስ ‹‹ፍፁም ወንጀል አይደለም›› ያሉት አቶ ወልደ ሥላሴ፣ ወንጀል እንደሆነ ቢታመን እንኳን ሊጠቀስ የሚገባው የወንጀል ሕግ 417 ሳይሆን፣ በፍትሐ ብሔር የሽያጭ ሕግ የሚሸፈን መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ወንጀል ሳይሆን በይመስላል አጠጋግቶ ወንጀል ለመመሥረት መሞከር በወንጀል ሕግ አንቀጽ 2(3) የተከለከለ በመሆኑ፣ ክሱ ሊሰረዝ እንደሚገባ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ማመልከቻ አስረድተዋል፡፡ 
“Terrorism in Ethiopia and the Horn of Africa” የተሰኘውን መጽሐፍ በሚመለከት አስተያየት እንዲሰጡዋቸው፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ በየነ ገብረ መስቀልን የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዙ ማድረጋቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፉን በግላቸው ቢያሳትሙት ተመራጭ መሆኑን አስተያየት እንደሰጧቸው ካስረዳ በኋላ፣ መጽሐፉ በመሥሪያ ቤቱ እንደተዘጋጀ በማስመሰል የተሳሳተ ግንዛቤ አስጨብጠዋቸዋል ማለት እርስ በርሱ የሚጋጭ ከመሆኑም በላይ፣ ተከሳሹ ለየትኛው ተግባር መከላከል እንዳለባቸው የማያስረዳና የመከላከል መብታቸውን የሚያጣብብ በመሆኑ ክሱ ሊሰረዝ ወይም ሲሻሻል እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ 
ክሱ አቶ ወልደ ሥላሴ አቶ በየነን የተሳሳተ ግንዛቤ አስጨብጠዋቸዋል የሚል ከሆነ፣ ተከሳሹ የማታለል ተግባር ፈጽመዋል የሚል ይዘት ያለው ክስ በመሆኑ፣ አሳሳች ነገር በማስጨበጥ ሕገወጥ ጥቅም ማግኘት ስለሚሆን፣ በወንጀል ሕግ 407 ሥር የሚወድቅ አለመሆኑን፣ በማታለል ወንጀል ሕግ 692 ሥር የሚሸፈን በመሆኑ፣ ዓቃብ ሕግ ክሱን እንዲያነሳ ወይም አሻሽሎ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡ 
አቶ ወልደ ሥላሴ የደኅንነት ተቋም ሠራተኛ በመሆናቸው ተሰሚነታቸውን በመጠቀም አላግባብ በሥልጣን መገልገላቸውን የሚጠቅስ ክስ የቀረበባቸው ቢሆንም፣ በተሰሚነት ብቻ የተፈጸመ ከሆነ በሥልጣን አላግባብ ተገልግለዋል ማለት እንደማይቻል፣ የተጠቀሰው የሕግ አንቀጽና የወንጀሉ ዝርዝር ፍፁም የማይጣጣም በመሆኑ ክሱ እንዲሰረዝ አመልክተዋል፡፡ የአትክልትና ፍራፍሬ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ አባል መሆናቸውንና ተሰሚነታቸውን በመጠቀም መጽሐፍ አስገዝተው ለሦስተኛ ወገን እንዲተላለፍ አድርገዋል በሚለው ክስ ውስጥ፣ ሦስተኛ ወገን ማን እንደሆነ ማንነቱ ባለመገለጹ የመከላከል መብታቸውን እንደሚያጣብብ በማስረዳት ተሻሽሎ እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡ 
አቶ ወልደ ሥላሴ የደኅንነት ተቋም ኃላፊ በነበሩበት ወቅት የተቋሙን ሠራተኛ በተደጋጋሚ በማዘዝ፣ በመንግሥት ተሽከርካሪና ነዳጅ አንዲት ሴት አገልግለዋልና ጉዳይ አስፈጽመዋል የሚለውን ክስ በሚመለከት ባቀረቡት ማመልከቻ እንደገለጹት፣ ታዟል የተባለው የተቋሙ ሠራተኛ ማንነት አልተገለጸም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ሚስጥራዊ ክስም ለፍትሕ መድረክ መቅረብ እንዳልነበረበት፣ ሕገወጥ ትዕዛዝ ለሠራተኛ ሰጥቷል ከተባለ የሠራተኛው ስም መጠቀስ እንደነበረበት ጠቁመው፣ በደፈና ለቀረበ ክስ ጭብጥ ይዞ ለመከላከል እንደማይቻልና የመከላከል መብትን እንደሚያጣብብ በመግለጽ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በኮ/ር/መ/ቁጥር 57644 ትርጉም የሰጠበት በመሆኑ ክሱ ሊሰረዝ እንደሚባው ገልጸዋል፡፡ 
ተመሳሳይ የሆኑ ክሶችን በአንድ ላይ ማቅረብ እንደሚገባ በወንጀል ሕግ 31(2) ተደንግጎ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ወልደ ሥላሴ፣ በወንጀል ሕግ 117(1) መሠረት ተጠቃሎ መቅረብ ሲገባው፣ ክሶቹን ሸንሽኖ ማቅረብ አግባብነት የሌለው በመሆኑ በወንጀል ሕግ 119 መሠረት ክሱ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ 
አቶ ወልደ ሥላሴ ታክስ አለመክፈላቸውን በሚመለከት ለቀረበባቸው ክስ በሰጡት መቃወሚያ እንዳስረዱት፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ከሥልጣኑ ውጭ ነው፡፡ ክሱን የማቅረብ ሥልጣን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ነው፡፡ በመሆኑም ክሱ ውድቅ ሆኖ ከነወንድማቸው (ዘርዓይ ወልደ ሚካኤል) በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ መጠቀምን በሚመለከት ለቀረበባቸው ክስ በሰጡት የመቃሚያ መልስ፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ሥልጣን አለመሆኑንና ሥልጣኑ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ስለሆነ ክሱ ውድቅ ሊሆን እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ 
ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብና ንብረት ከግብረ አበሮቻቸው ጋር ይዞ መገኘትን በሚመለከት ለቀረበባቸው ክስ አቶ ወልደ ሥላሴ በሰጡት ምላሽ፣ ተመሳሳይ ክስ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ ቁጥር 141352 ሥር በ92ኛ ክስ ላይ ተጠቅሶ የቀረበባቸው መሆኑን በማስታወስ፣ በወንጀል ሕግ 130(2)ሀ/ረ መሠረት ክሱ ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ በራሳቸው ደራሲነት የተዘጋጁ በርካታ መጻሕፍት ተሽጠው 1.5 ሚሊዮን ብር ማግኘታቸው በክሱ መገለጹን ጠቁመው፣ በሌላ በኩል ገቢን አሳውቆ ግብር አለመክፈል ወንጀል ክስ መመሥረት፣ እንዲሁም ገቢው ያልታወቀ ገንዘብና ንብረት ይዞ ስለመገኘት የቀረበባቸው ክስ እርስ በርሱ የሚጋጭ መሆኑን በመግለጽ፣ የዓቃቤ ሕግ ክስ ውድቅ ሆኖ በነፃ እንዲሰናበቱ በመቃወሚያቸው በዝርዝር በማስረዳት ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡ 
ሌላው የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበባቸው ክስ መቃወሚያ ያቀረቡት የአቶ ወልደ ሥላሴ የቅርብ ጓደኛ መሆናቸው የተገለጸው አቶ ዱሪ ከበደ ናቸው፡፡ አቶ ዱሪ በመቃወሚያቸው እንደገለጹት፣ በክሱ የተጠቀሰውን ሀብት ለመያዝ የሚያስችለው አቅም እንደሌለው እያወቀ የሚል ፍሬ ነገር ተጠቅሶ ለክሱ መሠረት መደረጉን አስታወሰዋል፡፡ በወንጀል ሕግ 419 መሠረት ግን ከሕጋዊ ገቢው በላይ ንብረት አፍርቷል በሚል ተጠያቂ የሚሆነው፣ ሕጋዊ ገቢ ያለው የመንግሥት ሠራተኛ ከሆነ ወይም ከነበረ ብቻ ነው፡፡ ሌላው ግን ይህ ክስ ሊቀርብበት አይችልም፡፡ አቶ ዱሪ ግን ነጋዴ መሆናቸው በክሱ ተገልጾ እያለ፣ የቀረበባቸው ክስ ከሕጉ ድንጋጌ ጋር የሚዛመድ አለመሆኑን በመጠቆም ተቃውመዋል፡፡ 
አቶ ዱሪ ራሳቸው ባፈሩት ንብረት ሳይሆን የአቶ ወልደ ሥላሴ ንብረትን አስመልክቶ በወንጀል ሕግ 33 መሠረት ልዩ የወንጀል ተካፋይ ሆነዋል የሚባል ቢሆን እንኳን፣ የክሱ ይዘት ይህንን የማያመላክት መሆኑን በመቃወሚያቸው አስረድተዋል፡፡ አቶ ዱሪ ተሳትፏቸው ባልተገለጸበት ሁኔታ በወንጀል ሕግ 33 መሠረት ሊሳተፉበት የሚችሉበት ዕድል እንደሌለ፣ ንብረቱ ከተፈራ በኋላ በሚስጥር ለመያዝ ‹‹ተፈጸመ›› የተባለ ድርጊት በመሆኑ፣ በወንጀል ሕግ 33 እና 419 መጠቀሱ ከቀረበው ክስ ጋር ምንም ተዛምዶ እንደሌለው በማስረዳት፣ በወንጀል ሕግ 130 እና 112 መሠረት እንደሚቃወሙ አሳውቀዋል፡፡ 
በሙስና የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ ከመቅረቡ ውጪ፣ አቶ ዱሪ የትኛውን ወንጀል እንደፈጸሙና መቼ እንደፈጸሙ፣ እንዲሁም ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ድርጊት ምን እንደሆነ ተብራርቶ አለመገለጹን በመጠቆም ክሱን እንደሚቃወሙ ለፍርድ ቤት ባቀረቡት ማመልከቻ አሳውቀዋል፡፡ ሌላው የቀረበባቸው ክስ ‹‹አክሲዮን ገዝተሃል›› የሚል መሆኑን ከመጠቆማቸው ውጭ ያሉት የለም፡፡ 
አቶ ዱሪ ከእነ አቶ ወልደ ሥላሴ ጋር አንድ ላይ የቀረበባቸው ክስ ተነጥሎ እንዲቀርብላቸውም ጠይቀዋል፡፡ ምክንያታቸውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(1) የተጠበቀላቸውን የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት የሚነካ መሆኑ ነው፡፡ 
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕትማችን አራተኛ ተከሳሽ አቶ ዱሪ ከበደ ውክልና በመውሰድ ብለን የዘገብነው፣ አቶ ዱሪ ከበደ አቶ ወልደ ሥላሴ በወንድምና በእህታቸው በሚስጥር የያዙትን ሀብት፣ በሚስጥር ለመያዝና ንብረቱን በበላይነት በመምራት ተብሎ እንዲነበብ አንባብያንን ከይቅርታ ጋር እንጠይቃለን፡፡ 
Source reporter

No comments:

Post a Comment