‹የዜግነት ክብር›
ዳንኤል ክብረት
ኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ሲዘመር ከሚያነሣቸው ነጥቦች መካከል ‹የዜግነት ክብር› የሚለው የተለየ ስሜት ይሰጠኛል፡፡ ለአንዲት ሀገር ሰው ትልቁ ዋጋው ‹የዜግነት ክብር› ነው፡፡ ሀገር አለኝ ብሎ ማሰብ፤ የሚያስብልኝ፣ የሚጮህልኝ መንግሥት አለኝ ብሎ ማመን፤ የእኔ ጉዳይ ጉዳዩ የሆነ አካል አለ ብሎ መመካት፡፡
እንዲህ እንደ ሰሞኑ ያለ፣ በሳዑዲ እየተፈጸመ እንዳለው ነገር ያለ ስናይና ስንሰማ ደግሞ ‹የዜግነት ክብር› መዝሙር ብቻ ይሆንብናል፡፡ ‹ኢትዮጵያዊ ማለት› ብለን ልንተረጉም ይቸግረናል፡፡ ማንም የአራዊት ጠባይ ያለው ሁሉ ተነሥቶ መንገድ ላይ ደሙን የሚያፈሰው፣ እግሩን የሚቆርጠው፣ የሚደበድበውና በፈለገበት ቦታ የሚያሥረው ከሆነ፣ ይህማ እንኳን የዜግነት ክብር የስደተኛነት ክብርም አላገኘም ማለት ነው፡፡ ሀገር አልባ ጂፕሲዎች ከሚደርስባቸው ግፍ በላይ ባለሀገሩ ኢትዮጵያዊ ከደረሰበትማ ‹የዜግነት ክብር› የቱ ላይ ነው፡፡ ደግሞስ በአንድ ኢትዮጵያዊ ላይ ሰው መሆኑን የሚያጠራጥር ከዚህ በላይ ምን ሊደርስበት ይችላል፡፡
ይህ ነገር ሁለት ነገሮችን እንድናስብ ማድረግ አለበት፡፡
1. የመንግሥት አካላት በየሀገሩ ያሉትን ዜጎቻችንን ለማወቅ፣ ለመከታተልና መብታቸውን ለማስከበር ያላቸውን ብቃት
2. እንዲህ ዓይነት ነገር በሌላ ጊዜና በሌላ ሀገር እንዳይደገም ልናደርገው የሚገባንን ዘላቂ መፍትሔ
የዜግነት ክብር የሚኖረው አንድ ዜጋ የትም ቦታ ቢኖር የዜግነት መብቱ እንዲከበርለት፣ በዜግነቱ እንዲኮራና የዜግነቱንም ግዴታ እንዲወጣ ሲደረግ ነው፡፡
ይህ የዜግነት ክብር እንዲጠበቅ መንግሥት፣ የዲፕሎማቲክ ሚሽኖች፣ የዲያስጶራ ማኅበረሰቦችና ጠቅላላው ሕዝብ ከዚህ ጊዜ የተሻለ የመንቂያ ጊዜ አያገኙም፡፡ ይህንን ለማሰብ እስከዛሬ የፈሰሰው ደም በቂ ካልሆን፤ የሚያስፈልገን የስንት ሰው ደም ይሆን?
No comments:
Post a Comment