Tuesday, October 15, 2013

የሪፖርተር ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ከእሥር ተፈታ

-የተጠረጠረበት ወንጀል ሳይገለጽለት ታስሮ ማደሩን ተቃወመ 
የተጠረጠረበት የወንጀል ድርጊት ሳይገለጽለት መስከረም 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ወደ ደቡብ ክልል ሐዋሳ ተወስዶ ለአንድ ቀን ታስሮ ካደረ በኋላ ጥቅምት 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ከእስር
የተፈታው የሪፖርተር ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ መላኩ ደምሴ፣ ወደ ክልል የተወሰደበት ሁኔታ ሕግን የተከተለ አለመሆኑን ተናገረ፡፡ 
መስከረም 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ከሚገኘው የሚዲያ ኤንድ ኮሙዩኒኬሽን ሴንተር (ሪፖርተር ጋዜጣ አሳታሚ ድርጅት) መሥሪያ ቤት፣ በሐዋሳ ፖሊስ ኮሚሽን የፖሊስ አባላት ወደ ክልሉ የተወሰደው ጋዜጠኛ መላኩ፣ ወደ ክልሉ የወሰዱት የፖሊስ አባላትም ሆኑ፣ በክልሉ የሚገኙት የፖሊስ ኮሚሽኑ መምርያ ኃላፊዎች በአግባቡና በሥርዓቱ የያዙት ቢሆንም፣ የተወሰደበት ሁኔታና የሕጉ አግባብነት ግልጽ እንዳልሆነለት አስታውቋል፡፡ 
አንድ በወንጀል የተጠረጠረ ማንኛውም ዜጋ በሚፈልገው አካል በቁጥጥር ሥር በሚውልበት ጊዜ፣ የተጠረጠረበት የወንጀል ድርጊት ግልጽ በሆነ ቋንቋ ከተነገረው በኋላ ለተጨማሪ ጥያቄ ወደ ተፈለገበት ቦታ መውሰዱ ሕጋዊ አግባብነት እንዳለው የተናገረው ጋዜጠኛ መላኩ፣ ከሐዋሳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመያዢያ ትዕዛዝ በማውጣት ወደ አዲስ አበባ የተላከው የሐዋሳ ፖሊስ ኮሚሽን ቡድን የፌደራል ፖሊስንና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ትብብር የሚጠይቅ ደብዳቤ ከመያዝ ውጭ እሱ ስለተጠረጠበት የወንጀል ድርጊት የሚገልጽ ምንም ነገር ይዞ አለመምጣቱን አስረድቷል፡፡ 
መስከረም 30 ቀን 2006 ዓ.ም. በሥራ ላይ እያለ ከጠዋቱ 5፡30 ሰዓት አካባቢ የገጠመውን ጋዜጠኛ መላኩ እንደገለጸው፣ ከጠዋቱ 5፡30 ሰዓት ላይ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ በሚገኘው የሪፖርተር ጋዜጣ አሳታሚ ድርጅት ቢሮ ሁለት ሲቪል የለበሱ ሰዎች መጥተው ‹‹አቶ መላኩ ደምሴንና አቶ ዘካርያስ ስንታየሁን እንፈልጋለን›› አሉ፡፡ ለጊዜው የነበረው እሱ ብቻ ስለነበር ሲያነጋግራቸው ፖሊሶች መሆናቸውን ይነግሩትና ወደ ሐዋሳ ሊወስዱት እንደመጡ በመግለጽ የያዙትን ለፌዴራልና ለአዲስ አበባ ፖሊስ መሥሪያ ቤቶች የጻፉትን የትብብር ደብዳቤ እንዳሳዩት ተናግሯል፡፡ 
ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ለፌዴራል ፖሊስ የተጻፈው የትብብር ደብዳቤ ‹‹አቶ መላኩ ደምሴና አቶ ዘካርያስ ስንታየሁ በተጠረጠሩበት ወንጀል የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለምርመራ ስለሚፈልጋቸው ትብብር እንድታደርጉልን›› ከማለት ውጭ በምን ዓይነት የወንጀል ድርጊት እንደተጠረጠሩ ግልጽ የተደረገ ነገር በደብዳቤው ላይ እንዳልሰፈረ ጋዜጠኛ መላኩ ተናግሯል፡፡ 
የክልሉ ፖሊሶች ያመጡትን ደብዳቤ ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን የተመለከተው ጋዜጠኛ መላኩ፣ ‹‹የተጠረጠርኩበትን የወንጀል ድርጊት ሳትነግሩኝና የተጠረጠርኩበትን ወንጀል የማየት ሥልጣን የክልሉ ይሁን የፌደራል መንግሥት ሳላውቅ እንዴት ልሄድ እችላለሁ?›› የሚል ጥያቄ በማንሳቱ፣ ከክልል የመጡት ፖሊሶችና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለትብብር የተመደበ አንድ ፖሊስ ሆነው ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ እንደወሰዱት ጋዜጠኛ መላኩ ገልጿል፡፡ 
በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ ደርሶ ያለውን ሁኔታ ሲጠይቅ፣ የመምርያው ባልደረባ የሆኑት አንድ ኢንስፔክተር ‹‹የተጠረጠርክበት ወንጀል ግልጽ ስላልተደረገ ምንም የምንለው ነገር የለም፤ በሰው ግድያ ይሁን፣ በስርቆት ይሁን፣ በዛቻ ይሁን… የተገለጸ ነገር የለም፤ ትብብር ስለተጠየቅን መተባበር ብቻ ነው፤ የሆነውን ነገር እዚያው ሄደህ ታውቀዋለህ፤›› ከማለት ያለፈ ክልሉ ሥልጣኑ ይኑረው ወይም አይኑረው መምርያውም ግልጽ ሊያደርግለት ስላልቻለ ጋዜጠኛ መላኩ ወደ ክልሉ ሊወሰድ መቻሉን አብራርቷል፡፡ 
መስከረም 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ወደ ደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ቢሮ የተወሰደው ጋዜጠኛ መላኩ፣ ምሽት ላይ በመድረሳቸው በዕለቱ ቃሉን ሳይሰጥ በኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት ማደሩን ገልጾ፣ በማግስቱ ጥቅምት 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀኑ 5፡.30 ሰዓት ሲሆን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ የሥራ ሒደት ኃላፊ ኮማንደር እያሱ ማቴዎስ ቃሉን እንደተቀበሉት አስታውቋል፡፡ 
በምን ወንጀል እንደተጠረጠረ የማያውቀው ጋዜጠኛ መላኩ ‹‹ጥፋቴ ምንድን ነው?›› በማለት ሲጠይቅ፣ ነሐሴ 29 ቀን 2005 ዓ.ም. በዕለተ ረቡዕ የሪፖርተር ጋዜጣ ዕትም ላይ ‹‹ሦስት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች ከኃላፊነታቸው ተነሱ›› በሚል ስለተዘገበው የዜና ሀተታ መሆኑን መረዳቱን ተናግሯል፡፡ 
የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ነሐሴ 29 ቀን 2005 ዓ.ም. የወጣው ዘገባ ስህተት መሆኑን በመረዳቱ፣ ከአምስት ቀናት ቆይታ በኋላ ጳጉሜን 3 ቀን 2005 ዓ.ም. ሦስቱም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች ከኃላፊነታቸው አለመነሳታቸውን በመጥቀስ፣ የክልሉን መንግሥት፣ ሦስቱን ባለሥልጣናትንና የሪፖርተር አንባቢዎችን በሙሉ ይቅርታ መጠየቁን ለኮማንደሩ እንዳስረዳቸው ጋዜጠኛ መላኩ ገልጿል፡፡ 
ከቀኑ ሰባት ሰዓት ሲሆን ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት ኮማንደሩ የገለጹለት ቢሆንም፣ ወደ ፍርድ ቤት ሳይወስዱት ‹‹ሐዋሳ ሆኖ ዘገባውን ባስተላለፈው ጋዜጠኛ ላይ ምስክር ትሆናለህ›› በማለት በራስ ዋስ ሊለቁት መቻሉን አስረድቷል፡፡ 
ጋዜጠኛ መላኩ ወደ ሐዋሳ በመወሰዱ የተለየና አስቸጋሪ ነገር እንዳልገጠመው ገልጾ፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊዎችና ሐዋሳ መወሰዱን ዘግይተው የሰሙ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የፌዴራል ባለሥልጣናት ድርጊቱ ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ለመለቀቁ ትብብር እንዳደረጉለት አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ተገቢ ያልሆነና ድርጊቱ ክልል ድረስ እንደማያስወስድ እንዲሁም ለክስ እንደማያበቃ እያወቁ፣ አንዳንድ ግለሰቦች ሥልጣናቸውን ለማሳየትና ‹‹እኛ እንዲህ ነን›› ለማለት ሆን ብለው ያደረጉት ሳይሆን እንደማይቀር ጋዜጠኛ መላኩ ከአንዳንድ የክልሉ ነዋሪዎች መስማቱን ጠቁሟል፡፡ ስህተት ከመሥራትና አላስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ከማስተላለፍ በመጠንቀቅ፣ እውነትን የመናገር፣ የመጻፍና ሐሳብን የማስተላለፍ፣ የምርመራ ዘገባዎችን (Investigative Reporting) መሥራት በአዋጅ የተፈቀደ የጋዜጠኝነት ሥራና ሕገ መንግሥታዊ መብት በመሆኑ ጠንክሮ እንደሚሠራም ጋዜጠኛ መላኩ ተናግሯል፡፡ 
Source ; Reporter 

No comments:

Post a Comment