(የመጽሐፍ ዳሰሳ)
በሻውል በትሩ (ዶ/ር)
ዋሽንግተን ዲሲ መስከረም 2006 ዓ.ም
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደመተንፈሻ እየሆነ የመጣው የአብዮታዊ “ዴሞክራሲ” አስተሳሰብ መሰረቱ አንባገነንነት ብቻ
እንደሆነ በተከራከሩበት መጽሐፋቸው ዶ/ር ብርሃኑ ከተለመደው አካሄድ ወጣ ባለ መንገድ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮችን ከስነ ህዝብ
ለውጥ (demographic dynamics) ጋር በማያያዝ ሰፋ ባለ ሁኔታ ማቅረባቸው በጣም ደስ የሚያሰኝ ጅማሮ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
የደራሲው ስም ባልነበረበትና አብዮታዊ ዴሞክራሲን በድፍረት/በንቀት/ ለከፍተኛ ተቋማት መምህራን በተሰበከበት እ.አ.አ. በ2003 ስብሰባ
ላይ ሰብሳቢ የነበሩት ዶ/ር ካሱ ኢላላ፡ የመምህራኑን ለስብሰባው ፍላጎት ማጣት ቢያዩ ለሚቀጥለው 20 ዓመታት ያላችሁን ራዕይ እስኪ
ንገሩኝ ብለው ጠየቁ። እኔም ወደ ጃፓን ለመሄድ ስዘጋጅ ነበርና እዛው ስብሰባው ውስጥ እያነበብኩ የነበረውን Japan: Profile of a
Nation የሚለውን መጽሃፍ ማንበቤን ገታ አድርጌ ቆምኩና ራዕዮዬን ተናገርኩ፡- “የዛሬ 20 ዓመት ኢትዮጵያ ደን የሚወድ መሪ
ይኖራታል። የአገሪቱ 20% የሚሆነው መሬት በደን የተሸፈነ ይሆናል” ብዮ ሌሎች አጠር ያሉ መምህራን ተኮር ራዕዮቼን ተናግሬ
ተቀመጥኩ። ቅኔው የገባቸው ሳቁ ሌሎችም ይህ ወጣት ባለ ራዕይ መሆኑ ገርሟቸው አጨበጨቡ። ዶ/ር ካሱ ኢላላም ምን እንዳሰቡ
እንጃ ሳቅ አሉ። ዛሬ ራዕዬ ሊፈጸም 10 ዓመት ብቻ ይቀረዋል። በ10ኛው ዓመት ታዲያ የ“ኢትዮጵያ መንግስት” አካልም ባይሆኑ በብዙ
ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው በአንድ ወቅት የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው ተመርጠው የነበሩት ዶ/ር ብርሃኑ በዚህ
ጉዳይ ላይ ከልባቸው ተጨንቀው ስለ አካባቢ ጥበቃ በመጻፋቸውና ለውይይት እድሉ እንዲኖር በማድረጋቸው ራዕዬ ሊፈጸም ይሆንን?
ብያለሁ።
ታዋቂው የጂኦግራፊ ምሁር ጃሬድ ዳይመንድ የአንድ ህብረተሰብ የመውደቅ እና መነሳት ሚስጥር በዳሰሱበት Collapse: How Societies
Choose to Fail or Succeed በሚለው መጽሐፋቸው የአካባቢ ጥበቃ ሁኔታን እንደዋነኛ ግብዓት ዓይተው በስፋትና በጥልቀት
ተከራክረዋል። በዚህ መጽሐፍ አንድ ህብረተሰብ ለአካባቢ እንክብካቤ ትኩረት ባለመስጠት ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ዛሬ ላለው ፍላጎት ብቻ
ማሞያ የሚጠቀም ከሆነ ይዘግይ እንጂ ያ ህብረተሰብ መውደቁ እንደማይቀር ብዙ ታሪካዊና ወቅታዊ ምሳሌዎችን ወስደው አብራርተዋል:: ታዲያ
የሳቸውን መጽሐፍ ሳነብ በየአንቀጹ ውስጥ ኢትዮጵያን ከአካባቢ እንክብካቤ አንጻር ያለችበትን ውጥንቅጥ እያሰብኩ ነበርና የሚታየኝ ነገር
በጣም ያስፈራኝ ነበር።
ድርቅና ረሃብ በአጭር አመታት ውደት የሚፈራረቁባት፣ የህዝብ እድገት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ባለባት ሀገር ኢትዮጵያ የአካባቢ
ጥበቃ ሊታሰብበት የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ጃፓን ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ያገኘሁት አንድ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣን
ስለ አካባቢ ጥበቃ አሳሳቢነት ባነሳበት “እኛ የምዕራባዊያን ቅንጦት የለንም“ ነበር ያለኝ። የጃሬድ ዳይመንድን ኮላፕስ፤ የማልተስን
ጭንቀት እያሰበኩ እቺ ለ30 ሚሊዮን በቅጡ ያልበቃ የአካባቢ ጥበቃ አያያዝ የላት አገር ሶስት እጥፍ ህዝብ ኖሯት እንዴት ልትሆን
እንደምትችል ማሰብ በጣም ከባድ ነው። ለኔ ግን የሚታየኝ ግን ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ላይ የምታውለው መዋዕለ ነዋይ የህልውና ጥያቄ
እንጂ የቅንጦት ፈጽሞ ሊሆን አይችልም።
ይህንን የዶ/ር ብርሃኑን መጽሃፍ ሳነበውና የአካባቢ ጥበቃን በሚመለከት ያቀረበውን የተግዳሮት ትንተና ላይ የራሴን አስተያየት ልሰጥና
በመጽሐፉ ውስጥ እንደተጠበቀው የዚህ ማህበራዊ ውይይት አካል ለመሆን ሳስብ ዋናው ዓላማዬ የኢትዮጵያን የተፈጥሮና አካባቢ
ጥበቃ ጉዳይ ምን ያህል ከፍተኛ አደጋ ላይ እንዳለ ከግል ልምዴና ሞያዊ ቀረቤታዬ ማሳሰቢያዬንም ለመስጠት ነው። እንደ ዶ/ር
ብርሃኑ ያለ የሚናገረውንና የሚጽፈውን እንዲሁም የሚያደርገውን በቅጡ አብሰልስሎና አብላልቶ የሚያደርግ ሰው ስራ ላይ ትችት
ወይም አስተያየት መስጠት በጣም ከባድ ነው። ነገር ግን ዶ/ር ብርሃኑ ሊጽፍ ባቀደው መጽሐፍ ላይ የአካባቢ ጥበቃን እንደ አንድ አብይ
ጉዳይ ሊያነሳው እንዳሰበና አንዳንድ ሙያዬን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ያለኝን ምልከታ እንድሰነዝር ሲጠይቀኝ በጣም ነበር ደስ ያለኝ።
ሙያዊ ጥቆማዬም ይህ ነው የሚባል ባይሆንም በጥቂቱ በመሰንዘሬ በመጽሀፉ ምስጋና ከተቸራቸው ጥቂት ሰዎች መካከል እንድጠቀስ
አድርጎኛል። መጽሐፉ አላማ ብሎ የተነሳውና በርዕሱም በግልጽ እንደተቀመጠው ሁለንተናዊ ልማት ለማምጣት የዲሞክራሲን
አስፈላጊነት ፓለቲካውን፣ ኢኮኖሚውን እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃውን በመውሰድ በስፋት የመከራከሪያ ሃሳብን ያስቀምጣል። እኔን
ወደሚመለከተኝና እጅግ ወደሚያሳስበኝ የአካባቢ ጥበቃ ተግዳሮቶች በቀጥታ እገባለሁ። ምንም እንኳን ዶ/ር ብርሃኑ የዲሞክራሲን አስፈላጊነት ለመከራከር የአካባቢ እንክብካቤን እንደምሳሌ የተጠቀመበት ቢሆንም ያልታለመለት ሌላ
ግብ የሚመታ ወይም የመታ ይመስለኛ:: ይህንን ትልቅ ሀገራዊ ጉዳይ ማዕከላዊ የውይይት ስፍራ እንዲይዝና በቸልተኝነት እንዳይታለፍ
ያደርገዋል:: ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያችን ችግር የፓለቲካና የኢኮኖሚ ብቻ እንደሆነ፤ እነዚህም ችግሮች ቢቀረፉ ሁሉም ችግሮቻችን
እንደጉም በነው እንደሚጠፉ በሚታሰብበት ሁኔታ፤ መጽሐፉ አዎን እነዚህ ችግሮች አሳሳቢ ናቸው፤ ነገር ግን በተጨማሪ የአካባቢ
ጥበቃ ተግዳሮት ፓለቲካውን አልፎ ተከትሎን የሚዘልቅ ነውና ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሊታሰብበትና ሊታቀድበት ይገባል ብሎ
በማሳሰቡ እንደ ጠንካራ ጎን ሊጠቀስ ይገባል እላለሁ። ስለ አካባቢ ጥበቃ ማሰብና መጨነቅ አገሮች ኢኮኖሚያዊ እድገታቸው ከፍተኛ
ደረጃ ሲደርስ የሚሆን እንደሆነ የብዙ እያደጉ ያሉ አገሮች ተሞክሮ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች አንዱን ከሌላው
የምናማርጥበትና ለኢኮኖሚው እድገት ሲባል የአካባቢ ጥበቃን ጉዳይ ለይደር የምንተወው እንዳልሆነ ዶ/ር ብርሃኑ የራሳቸውን የመስክ
ላይ ምልከታ ምሳሌ በመውሰድ አንባቢያቸውን ሞግተዋል። የአለማያ ሐይቅ በሃምሳ አመታት ውስጥ ያሳየውን የ"ማንነት” ለውጥለተመለከተ በአገራችን ያለውን የቸልተኝነት መጠንና የችግሩን ግዙፍነት ያሳያል። ለዚህ የምሁራን ቸልተኝነት (indifference) እኔ
እስከማውቀው ድረስ ብቸኛና ታሪካዊ የደን ሳይንስ ማዕከል የሆነው የወንዶ ገነት የተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ በተቋቋመበት የአባሮ ተራራ
ላይ ያለው የተፈጥሮ ደን፤ አይናችን እያየ ተቃጥሎ ተቋሙ ምሳሌ መሆን በማይችልበት ደረጃ መድረሱ በግሌ የምመሰክረው አሳዛኝ
እውነት ነው። ተማሪዎች እያለን እንዴት ባለ ሞራል በቂ ስልጠናና መሳሪያ ሳይኖረን እንኳን በየጊዜው የሚነሱ እሳቶችን ለማጥፋት
የተረባረብንባቸው ጊዚያቶች ነበሩ፡፡ ኋላ ላይ ግን ትላልቅ ታሪካዊ ደኖች እንኳን ሲቃጠሉ ዝናብ ዘንቦ እንዲያጠፋቸው ወይም በራሳቸው
ጊዜ ቶሎ እንዲጠፉ ከመጸለይ ያለፈ መንግስት ላይ እንኳን ጫና መፍጠር ተስኖን እንታያለን።
ሌላው መጽሃፉ የሚያነሳውና በቅጡ የሚከራከርበት ነጥብ ሀገሪቱ ያላት የመሬትና የሰው ሃብት የዛሬውንና የወደፊቱን በማንሳት ሊኖር
የሚችለውን ውጥረት ያትታል። ብዙ ጊዜ በምናደርጋቸው ውይይቶች ያየሁት መደናገር ለቁጥሮች ትኩረት ባለመስጠት የሚመጣ ነው።
አንዳንድ ጊዜ መንግስት በተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚያቀርባቸው አኃዞች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በጣም የተጋነነ አሊያም የተንኳሰሰ
ሲሆን ይታያል። ለምሳሌ አገራችን ያላት አጠቃላይ የመሬት ስፋት 112 ሚሊዮን ሄክታር ሆኖ ሳለ ለግብርና የሚሆነው መሬት 78
ሚሊዮን ሄክታር ነው የሚል መረጃ ይወጣል። ነገር ግን ዶ/ር ብርሃኑ የአለም አቀፉን የምግብና የግብርና ድርጅት (FAO) መረጃ
ጠቅሰው ይህ የሚባለው መሬት በአሁኑ ሰአት በአንድ ወይም በሌላ የደን ወይም የቋሚ ተክሎች የተያዘ እንደሆነና ይህንን መሬት
ለማልማት ካስፈለገ አሁን ያለውን የደንም ሆነ ሌሎች የምርት ስርዓቶችን ማፋለስ እንደሚያስፈልግ አሳይተው ያለውንም የዘለቄታነት
ችግር አመልከተዋል።
በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የተፈጥሮ ደን ሽፋን ከአጠቃላይ መሬት ውስጥ ከሁለት ፐርሰንት ያነሰ መሆኑንና አፋጣኝ እርምጃ ተወስዶ የቀሩት ደኖች
እንክብካቤ ካልተደረገ በስተቀር በደቡብ ምዕራብ የቀሩን ደኖቻችንን ሊጠፉ እንደሚችሉ ማወቅ ይገባል። ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ እያየን
ያለነው የመሬት ቅርምት ትኩረት በእነዚሁ ቀሪ የተፈጥሮ ደኖች ውስጥ መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል:: በእነዚህ ከፍተኛ ዝናብና
ሙቀት ያላቸው አካባቢዎች ደኖቻቸው እንደተመነጠሩ ግብርና ሲካሄድባቸው የሚያሳዩት ጊዜያዊ ለምነት የሚያማልል ቢሆንም ለዘላቂነት
የሚቆይ ግን አይሆንም:: ይህ የሚሆንበት ምክንያት በእነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ የህይወት ውደት ስላለ የአፈሩን ለምነት በዘለቄታ
የሚያስጠብቅ የአፈር ጥልቀት አይኖርም:: ስለዚህ ለዕጽዋት የሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮች ስስ በሆነው አፈርና በዕጽዋቶች መካከል እየተዘዋወረ
መቀጠል ይገባቸዋል:: በእነዚህ አካባቢዎች ግብርናን ለማካሄድ የግድ መሬቱን ከአፈር መሸርሸር የሚጠብቁ የተለያዩ የተዳፋት እንክብካቤ
ስራዎችን ማከናወን ግድ ይላል:: ይህ ስራ ደግሞ በስፋትና በጥልቀት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተሰራ እንደሆነ የሚያሳይ መረጃ አናገኝም።
ከመሬት ሃብት ስርአት ጋር አያይዘውም የህዝብ ብዛት በተለይ የገጠሩን ህዝብ መጨመርና የእርሻ መሬት እየጠበበ የመሄድን ችግር
ከምርታማነት እንብዛም አለመለወጥ ጋር አያይዞ በተለይ በደጋማው ከፍተኛ አካባቢዎች ሊፈጠር የሚችለውን የምርት እጥረትና ያንን
ችግር ለመፍታት የሚኖረውን ተግዳሮት አስረድተዋል። ወደ ሰባ ፐርሰንት የሚጠጋው ምግብ ከአገዳ ሰብሎች በሚገኝባት ከእጅ ወደ አፍ
በሆነ ግብርና በሚተዳደር ህዝብ የመሬት ይዞታው እያነሰ ሲሄድ ገበሬው ቤተሰቡን ለአመት በሕይወት ማቆየት የሚችልበት አቅም አጥቶ
በድህነት አረንቆ ውስጥ እንደሚቀር እናያለን::
ሰፋ ያለ ውይይት ሊደረግባቸው ሊደረግባቸው ሊደረግባቸው ይገባል ከምላቸው በመጽሐፉ የተነሱና ሌሎችም የአካባቢ ጥበቃን የተመለከቱ ጉዳዬችo የአካባቢ ጥበቃው ሁለንተናዊ እድገትን ለማምጣት እንደሚያስፈልግ መገልገያ እንጂ በራሱ መጠበቁ የስነ ምህዳር ጤንነት ላይ
ያለው ተጽእኖ
o የደኑ መኖር የአፈር ለምነትን እንዲሁም የወንዞችን ዘለቄታዊ ፍሰት ከማስተማመን ባሻገር እራሱ በቀጥታ የሁለንተናዊው
እድገት አካል እንደሆነ ማሳየት ተገቢ ይሆን ነበር። ለምሳሌ፤ ለወረቀት ምርት የሚያስፈልገውን የፐልፕ ግብዓት ከውጭ
የምናስገባ ስለሆነ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ አገር ውስጥ በዘለቄታነት በሚመረት ምርት መተካት
ይቻላል። ትላልቅ ከተሞች አካባቢ ያሉትን የዛፍ ተከላዎች (planta ons) በማጠናከር ከሌሎች አገሮች የምናስገባውን
በአገር ውስጥ የእንጨት ምርት በመጠቀም ከተማ ውስጥ ለሚኖሩ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የስራ እድል
መክፈት ይቻላል።
o የማዳበሪያ ግብዓት በጣም በዝቅተኛ ደረጃ መኖሩ አፈሩን የንጥረ ነገር ደሃ እንደሚያደርገው እና በዚህ ረገድ ህዝብ እየጨመረ ሲሄድ
የግድ ምርታማነት መጨመር ስለሚገባው የማዳበሪያ ኢንደስትሪን መጀመርና ማሳደግ ግድ ይላል:: በመጽሐፋ ውስጥ የህንድን
ማዳበሪያ አጠቃቀም ልምድ ተወስዶ የታየውን አሉታዊ በመጥቀስ ኢትዮጵያ ውስጥም ማዳበሪያን መጠቀም መበረታታት
እንደሌለበት ጠቁሟል:: ምንም እንኳን ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮች ቢኖሩም ሳይንሳዊ በሆነ
መንገድ የተመጣጠነ ሰው ሰራሽ ማዳባሪያን መጠቀም አሁን ካለው የህዝብ እድገት አንጻር የግድ ይላል:: በተጨማሪ በአማካይ ሲታይ
የኢትዬጵያ ገበሬዎች በሄክታር የሚጠቀሙት ከሌሎች አገሮች አንጻር ሲታይ ገና ዝቅተኛ ነው::
o ኢትዮጵያ በመስኖ ውሃ አጠቃቀም ረገድ ከ2% በታች የሚሆነውን የውሃ ሃብት ብቻ እየተጠቀመች ስላለች ይህን ሃብት በሚገባ
በመጠቀምና በመጠበቅ ያለውን ስነ ምህዳራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን እንዲሁም ተግዳሮቶቹን ማንሳት ቢቻል፡፡
o የኢኮ-ቱሪዝም ዞን በማቋቋም ከፍተኛ የሆነ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ማስፋፋት ይቻላል።
o ከሁሉም በላይ ደን ውስጥ ያሉ፡ ነገር ግን የእንጨት ምርት ያልሆኑ non-forest products የሚባሉትን ለአካባቢው local
ነዋሪዎች በባህላዊ መድሃኒትነት፡ በቅመማ ቅመም፡ እንዲሁም በምግብ ምንጭነት ያላቸውን አስተዋጽኦ ማንሳቱ የመጽሃፉ ዋና
አላማም ባይሆን ለአካባቢ ጥበቃ አስፈላጊነት መከራከሪያን ያጠናክራል ብዬ አስባለሁ።
o ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር የመሬት ባለቤትነት የተግባር እርምጃን ያመላከተ አንድምታ ካልሆነ በስተቀር የማህበረሰብ ባለቤትነት
ከሚበረታታባቸው የመሬት ይዞታዎች አንዱ ይመስለኛል። ለምሳሌ ፓርኮች፣ የከተማም ይሁኑ የተፈጥሮ፣ በመንግስት መዋዕለ
ነዋይ ሊያዙ የሚችሉ ናቸው። ይህም በመሬት ይዞታ ውይይት ውስጥ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ ይመስለኛ።
o ለአለም ሙቀት መጨመር ምክንያት የሆነውና ከፔትሮሊየም አጠቃቀም የሚመነጨው ዝቃጭ ሃይድሮ ካርቦን ሳይሆን ካርቦን ዳይ
ኦክሳይድ ነው። ተክሎች በአብዛኛው ከከባቢ አየር ወይም አትሞስፌር የሚወስዱትና ለአለም ሙቀት መጨመር ዋነኛ ምክንያት
የሆነውን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ እንጂ የናይትሮጂን ኮምፓውንድ እንዳልሆነ ቢታይ (ናይትሮጅንን ከከባቢ አየር ለመውሰድ ከፈንገስ ዝርያዎች ጋር ሽርክና (symbaiosis) መፍጠር የሚችሉ ሊግሙኒየስ የሚባሉ እንደ የአኩሪ አተር ያሉ ናቸው እንጂ ሁሉም ተክሎች
አይደሉም:: ተክሎች ናይትሮጂን የሚያገኙት ከአፈር ውስጥ ሲሆን አፈሩ ከምርቱ ጋር ተመጣጣኝ ማዕድን ካላገኘ የግድ ሰው ሰራሽ
ማዳበሪያ መጠቀም ግድ ይላል:: )
o ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችንና፡ የአኗኗር ዘይቤዎች ማበረታታት። በመገናኛ አውታሮች አማካኝነት ትርጉም ያለው
ውይይት በተከታታይ ማድረግ።
ባጠቃላይ ለአብዛኛው አንባቢ በሚገባ መልኩ የቀረበ እንዲሁም ለሞያተኞች ጥሩ የውይይት መድረክ እንዲከፈት የሚያደርግ መጽሃፍ
ነውና ሁሉም የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ዜጋ ሊያነበውና ከኔ ምን ይጠበቃል ብሎ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ አበረታታለሁ።
ሁለተኛው መጽሃፍ ወደ ፖለቲካው የሚያደላ እንደሚሆን ቢጠቀስም በዚህ መጽሐፍ የተነሳው ጉዳይ በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ለብዙ
ጊዜ የሚቆይና ለውጥ አምጪ የሆነ ውይይት እንደሚጭር እምነቴ ነው።
____________________________________________________________________________________
በዚህ ጽሁፍ ለማቅረብ የፈለኩት ሙሉውን መጽሐፍ ለመዳሰስ ሳይሆን፡ ደራሲው ሃሳቡን ለማቅረብ ያነሳውን የአካባቢ ጥበቃ ተግዳሮት
ትኩረት እንዲያገኝ ውይይቱን ለመቀጠል ነው::
ፀሃፊውን በ shawelbetru@gmail.com ማግኘት ይችላሉ::
No comments:
Post a Comment