Tuesday, October 8, 2013

ቀጣዩ የኢህአዴግ ዒላማ ‘ማህበረ ቅዱሳን’ ይሆን?

በተመስገን ደሳለኝ
የኢህአዴግ ታጋዮች የመንግስት ‹‹ጠንካራ ይዞታ›› የሚባሉ ከተሞችን ሳይቀር መቆጣጠር ችለዋል፤ ወደ
አዲስ አበባ የሚያደርጉት ግስጋሴም ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያምን እንቅልፍ ነስቷል፡፡ በአንዳች ተአምር
ግስጋሴውን መግታት ካልቻሉ፣ በጥቂት ወራት ውስጥ ሁሉም ነገር ታሪክ እንደሚሆን በማወቃቸው፣ መላ
በማፈላለጉ ላይ ተጠምደዋል፡፡ በዚህ ጊዜም ነበር (የሃሳቡ አመንጪ ተለይቶ ባይታወቅም) ‹‹ለዩንቨርስቲ
ተማሪዎች የአጭር ጊዜ ስልጠና ሰጥቶ፣ ከሀገሪቱ ሠራዊት ጎን ማሰለፍና የ‹ወንበዴ›ውን ጦር መድረሻ
ማሳጣት›› የሚለው ሃሳብ እንደ መፍትሄ የተወሰደው፡፡

 እናም መንግስቱ ራሳቸው ተማሪዎቹን በዩንቨርስቲው አዳራሽ ሰብስበው፣ እንዲህ ሲሉ አፋጠጧቸው፡-
‹‹እነርሱ (ኢህአዴግንና ሻዕቢያን ማለታቸው ነው) ለዕኩይ ዓላማቸው ከእረኛ እስከ ምሁር ሲያሰልፉ፣ እናንተ ምንድን ነው የምትሰሩት?
በሰላማዊ ሰልፍና በስብሰባ ብቻ መቃወም ወይስ ወንበዴዎቹ እንዳደረጉት ከአብዮታዊ ሠራዊታችን ጎን ቆማችሁ የሀገሪቱን ህልውና
ታስከብራላችሁ?››
 ይህን ጊዜም አስቀድሞ በተሰጣቸው መመሪያ ከተማሪው ጋር ተመሳስለው በአዳራሹ የተገኙት የደህንነት ሰራተኞችና የኢሠፓ ካድሬዎች
‹‹ዘምተን ከጠላት ጋር መፋለም እንፈልጋለን›› ብለው በስሜትና በወኔ እየተናገሩ በሰሩት ‹ድራማ› ተማሪው ትምህርት አቋርጦ
እንዲዘምት ተወሰነ፤ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲም ተዘጋ፤ ተማሪዎቹም ለወታደራዊ ስልጠና ደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ሚገኘው ‹ብላቴ የጦር
ማሰልጠኛ› ከተቱ፡፡

 …ከመላው ዘማቾቹ አስራ ሁለት የሚሆኑ ተማሪዎች ተሰባስበው ሲያበቁ፣ በየቀኑ ካምፓቸው አቅራቢያ ወደሚገኘው ‹ሚካኤል ቤተ-
ክርስቲያን› በመሄድ፣ ከመዓቱ ይታደጋቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን በፀሎት መማፀን የህይወታቸው አካል አደረጉት፤ ከቀናት በኋላም በአንዱ
ዕለት አንድም ለመታሰቢያና ለበረከት፣ ሁለትም ስብስቡ ሳይበተን ወደፊት እንዲቀጥል በሚል ዕሳቤ ‹ማህበረ ሚካኤል› ብለው
የሰየሙትን የፅዋ ማህበር መሠረቱ፡፡ …ይሁንና ከመካከላቸው አንዳቸውም እንኳ በ1977 ዓ.ም በ‹ፓዊ መተከል› ዞን የተደረገውን
‹የመልሶ ማቋቋም› ፕሮግራም እንዲያመቻቹ በዘመቱ ተማሪዎች ከተመሠረተውና ከተለያዩ የፅዋ ማህበራት ጋር በመዋሀድ የዛሬውን
‹ማህበረ-ቅዱሳን› እንደሚፈጥሩ መገመት የሚችሉበት የነብይነት ፀጋ አልነበራቸውም፤ የሆነው ግን እንዲያ ነበር፡፡

 ‹ማህበረ ቅዱሳን›
 የ‹ማህበረ ሚካኤል› መሥራቾች፣ ከተማሪ ጓደኞቻቸው ጋር ‹ይለያል ዘንድሮ፣ የወንበዴ ኑሮ›ን እየዘመሩ የገቡበት ወታደራዊ ስልጠና
ተጠናቅቆ፣ ወደ ጦር ሜዳ ከመግባታቸው በፊት፣ አማፅያኑ አሸንፈው፣ የመንግስት ለውጥ በመደረጉ ስልጠናቸውን ሳይጨርሱ
ወደየመጡበት ተመለሱ፡፡ ሆኖም ለውጡ በተካሄደ በዓመቱ እነርሱን ጨምሮ በአምላካቸው፣ በፃድቃን፣ በሰማዕታትና በመላዕክታት ስም
የተመሰረቱ የተለያዩ ማህበራት በአቡነ ጎርጎርዮስ አስተባባሪነት በጠቅላይ ቤተ-ክህነት ግቢ ተሰባስበው ወደ አንድ እንዲመጡ መደረጉ
ሊጠቀስ የሚገባ ልዩነት ባይፈጥርም፣ ስያሜው ግን ብርቱ ክርክር አስነሳ፡፡ በአዳራሹ ከተገኙት ጳጳሳት አንዱ የሆኑት አቡነ ገብርኤልም
‹‹ማህበረ ቅዱሳን ብየዋለሁ›› ብለው ውጥረቱን አረገቡት፡፡ ዕለቱም ግንቦት ሁለት ቀን አስራ ዘጠኝ ሰማኒያ አራት ዓመተ ምህረት
እንደነበር ተጽፏል፡፡
 ዓላማው ምንድር ነው?
 ‹ማህበረ ቅዱሳን› ሲመሰረት ‹ዓላማዬ› ብሎ የተነሳው አራት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር መሆኑን በተለያየ ጊዜ ለህትመት
ባበቃቸው ድርሳናቱ ተገልጿል፡፡ እነርሱም፡- ‹‹ትምህርተ ኃይማኖት፣ ስርዓተ እምነት፣ ክርስቲያናዊ ትውፊት እና የሀገሪቱ ታሪክ
ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ማስቻል›› የሚሉ ናቸው፡፡

 ማህበሩ ከመሰሎቹ የተለየ ጥንካሬ እንዲኖረው ያስቻለው ዓላማውን ከግብ ለማድረስ በዋናነት በሀገሪቱ የተለያዩ ዩንቨርስቲዎችና
ኮሌጆች የሚማሩ ተማሪዎችን አባል ማድረጉ ላይ ተግቶ መስራቱ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ መስፈርቱ እያገለገለ እንደሆነ ይታወቃል፤ ይህ
ሁኔታም ይመስለኛል አንዳንድ ፀሀፍት ማህበሩን ‹የቤተ-ክርስቲያኗ የዩንቨርስቲ እጅ› እንዲሉት ያስገደዳቸው፡፡

 የሆነው ሆኖ ማህበሩ በምስረታው ማግስት በሀይማኖቱ የመጨረሻውን ሥልጣን በያዘው ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ተሰጥቶት፣ በጠቅላይ
ቤተ-ክህነት የማህበራት ማደራጃ ስር እንዲሆን ተደረገ፡፡ በ1985 ዓ.ም ደግሞ መተዳደሪያ ደንቡን አፀደቀ፡፡

 የግጭት-ጅማሬ
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ  ማህበሩ ደንቡን ባፀደቀ ሰሞን ከመንግስት ጋር ብቻ ሳይሆን ‹‹ህገ ቤተ-ክርስቲያንን ባፋለሰ መንገድ በፓትርያርክነት ተሹመዋል››
በማለት ከተቃወማቸው አቡነ ጳውሎስ ጋር አይንና ናጫ ሆነ፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴውም አራንሺ ገ/መድህን ይመራው በነበረው የፀጥታ
ክፍል ስር ወደቀ፡፡

 አንዳንድ የኢህአዴግ አመራሮች በብላቴን ከተመሰረተው ‹‹ማህበረ ሚካኤል›› ጋር በማያያዝ የማህበሩን መሪዎች አልፎ አልፎ ‹‹ተረፈ
ደርግ›› እና ‹‹መዐህድ››… እያሉ ከማሸማቀቅ ባለፈ ብዙም ጫና አያደርጉባቸውም ነበር፡፡ …ዛሬ ማህበሩን በመንግስት ‹ጥቁሩ መዝገብ›
በቁጥር አንድ ጠላትነት እንዲሰፍር ካደረጉ ልዩነቶች (ያለመግባባቶች) መካከል ዋና ዋናዎቹን በአዲስ መስመር እጠቅሳለሁ፡፡

 ኢህአዴግ የሀገሪቱን ምስረታ ከአፄ ምኒሊክ ዘመን የሚጀምር የመቶ ዓመት ማድረጉ፣ ማህበሩ ‹ዓላማዬ› ከሚለው ‹ታሪክን ጠብቆ
ለትውልድ ማስተላለፍ› ጋር መታረቅ አለመቻሉ ያስከተለው ውጥረት የመጀመሪያው ነው፡፡ ማህበሩ የ‹ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ›ን
ታሪክ 2000 ዓመታት ወደ ኋላ ሆዶ ማስላቱ ብቻውን፣ ‹‹አንዲት ኢትዮጵያን በመፍጠር ስም ምኒልክና ተከታዮቹ ያሰፈኑትን ጭቆና
በጠመንጃ ለማስወገድ በረሃ ገባን›› ከሚሉት የህወሕት መስራቾች ጋር ሊያጋጨው መቻሉ የሚጠበቅ ነበር፡፡ ጉዳዩን ከለጠጥነው ደግሞ
‹‹ማህበሩን በ1980ዎቹ አጋማሽ እንደስጋት ይመለከተው የነበረውን ‹የሸዋ ፊውዳል› ወደ ስልጣን ለማምጣት ያደፈጠ ተቃናቃኝ አድርጎ
ፈርጆት ነበር›› ወደሚል ጠርዝ ሊገፋን ይችላል (በነገራችን ላይ በፖለቲካው መንገድ ለሹመት የበቁት አቡነ ጳውሎስም እስከ ህልፈታቸው
ድረስ ማህበሩ በሸዋ ተወላጅ ጳጳስ ሊተካቸው የሚያሴር ይመስላቸው እንደነበር ይነገራል)፡፡ በጥቅሉ በኢህአዴግና በማህበረ ቅዱሳን
መካከል የርዕዮተ-ዓለም (በብሔር እና በኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሠረተ) ልዩነት መኖሩ ላለመግባባቱ መነሾ ነው፡፡

 ሌላው የቅራኔያቸው መንስኤ፣ በወርሃ ሚያዚያ 1993 ዓ.ም ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያምና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ
ተማሪዎች ጋር ሰብዓዊ መብትንና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ባደረጉ ማግስት፣ በዋናው ግቢ
ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጋር የሚያያዘው ሁነት ነው፡፡ በወቅቱ ተማሪዎቹ በሠላማዊ መንገድ ላቀረቡት ጥያቄ የፀጥታ አስከባሪዎች የኃይል
ምላሽ መስጠታቸው ጉዳዩን ከቁጥጥር ውጪ አደረገው፡፡ ድብደባውና ማሰቃየቱ ከአቅም በላይ የሆነባቸው የተወሰኑ ተማሪዎችም
ከፓትርያርኩ ቤተ-መንግስት በአጥር ወደሚለየው ‹ቅድስት ማሪያም ቤተ-ክርስቲያን› ሸሽተው ይገባሉ፤ በአካባቢው የነበሩ የጥበቃ
ሰራተኞችም የግቢውን በር ይቆልፋሉ፡፡ ይሁንና የአቡኑን ድጋፍ ያገኙ ፖሊሶች ተማሪዎቹን በኃይል አስወጥተው ደብድበው አሰሯቸው፤
ድርጊቱንም ማህበረ ቅዱሳን በልሳኖቹ (‹ሐመር› መፅሄትና ‹ስመዓ-ፅድቅ› ጋዜጣ) የቤተ-ክርስቲያኗን ለሸሸ መጠለያነት ታሪክ አጣቅሶ
አጠንክሮ መቃወሙ ከመንግስት ጋር በአደባባይ ቅራኔ ውስጥ ከተተው፡፡

ሌላው ቅራኔያቸውን ያጦዘው ክስተት ደግሞ አቶ ተፈራ ዋልዋ በ1998 ዓ.ም ወርሃ ጥቅምት በደቡብ ዩንቨርስቲ ለሚማሩ ተማሪዎች
‹‹መንግስትና አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› በሚል ርዕስ ስልጠና በሰጠበት ወቅት ኦርቶዶክስን ‹‹የነፍጠኞች ፊት-አውራሪ›› ሲል ካወገዘ
በኋላ፣ ቤተ-ክርስቲያኗን ‹የነፍጠኛ ምሽግ›፣ ጥምቀቱን ‹በውሃ መንቦራጨቅ› ብሎ ማጣጣሉ ሲኖዶሱን ግድ ባይሰጠውም፣ ማህበረ
ቅዱሳንን አስቆጥቶ መልስ እንዲሰጥ ያደረገበት ኩነት መፈጠሩ ነበር፡፡

 የመዋቅሩ ስፋትና የውጥረቶቹ ጡዘት
 የማይቆጣጠረውን የተደራጀ ኃይል አጥብቆ ለሚፈራው ኢህአዴግ፣ የማህበሩ መዋቅር እየሰፋ መሄድ ስጋት ላይ ጥሎታል፡፡ አባላቱ
የዩንቨርስቲ ወይም ኮሌጅ ምሩቃን መሆናቸው ከገጠር እስከ ጠ/ሚንስትሩ ቢሮ ድረስ የራሱ ሰዎች እንዲኖሩት አድርጓል፡፡ የአገዛዙም
ጭንቀት ‹ይህ ኃይል አንድ ቀን በተቃውሞ ፖለቲካ ሊጠለፍ ይችላል› የሚል ነው፡፡ ይህንንም የሚያረጋግጠው አባይ ፀሀዬ መስከረም
2002 ዓ.ም የማህበሩን አመራር በሲኖዶሱ ጽ/ቤት ባነጋገረበት ወቅት ግንባሩን መደገፍ እንዳለባቸው የገለፀበት መንገድ ‹‹ኢህአዴግ
ገለልተኛ የሚባል ነገር አይገባውም›› የሚል መሆኑን ስናስታውስ ነው፡፡

 በምርጫ 97 ዋዜማም አቶ መለስ የኃይማኖት ተወካዮችን ሰብስቦ ወደ ፖለቲካው እንዳይገቡ ባስጠነቀቀበት መድረክ ተመሳሳይ አቋም
ታይቷል፡፡ በወቅቱ የብስራተ ገብርኤል አስተዳዳሪ የነበሩት አባ ኪሮስ መለስን ‹‹ከምስራቅ ይነሳል የተባለው ቴዎድሮስ እርስዎ ኖት›› ሲሉ
አወድሰውት ነበር፤ አባ ተ/ሚካኤል የተባሉ መንፈሳዊ መሪ ደግሞ (በ2003 ዓ.ም ህይወታቸው ሲያልፍ ‹አቡን› ተብለው ነበር) ከአባ
ኪሮስ ፍፁም በተቃረነ መልኩ ‹‹የሩሲያው ቪላድሚር ፑቲን በሃይማኖታዊ በዓላት ላይ ይሳተፋሉ፣ ያስቀድሳሉ፣ ለኃይማኖታቸውም
ይቆረቆራሉ፤ እርስዎ ግን ይህንን ሲያደርጉ አይስተዋሉም›› በማለት ወቀሳ አዘል አስተያየት አቅርበውለት ነበር፤ መለስ በበኩሉ
ለውዳሴውም ሆነ ለወቀሳው ትኩረት የሰጠ በማይመስል አኳኋን እንዲህ በማለት ነበር በጅምላ የሸረደዳቸው፡- ‹‹እውነተኞቹን በገዳም
ያሉትን መነኮሳት በርሃ እያለሁ አውቃቸዋለሁ፡፡›› ይህ የመለስ ሽርደዳ ዓላማ ወደ ተቃውሞ ጎራ ሊሳቡ ይችላሉ ብሎ የጠረጠራቸውን
የቤተ-ክርስቲያኒቱ መሪዎችንና ማህበረ ቅዱሳንን ‹‹ለእኛ ካልወገናችሁ ‹የቄሳርን ለቄሳር› አስተምህሮአችሁን መከተል ግዴታችሁ ነው፤
አሊያም ‹ሃሳዊ› ብለን እንፈርጃችዋለን›› የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ይመስለኛል፡፡
የሆነው ሆኖ በኢህአዴግና በቅንጅት መካከል በድህረ-ምርጫ የተፈጠረው አለመግባባትን ቤተ-ክርስቲያኗ ‹የቄሳርን ለቄሳር› ብላ
ለማንም ሳትወግን እርቅ እንዲፈጠር መሸምገል እንዳለባት ማህበሩ በልሳኖቹ መወትወቱ፣ የተገላቢጦሽ አገዛዙን ይበልጥ አስኮረፈው፡፡
በአናቱም ከአማራ ክልል የተላከው ሪፖርት ‹በገጠር ያሉ የማህበሩ አባላት ለተቃዋሚዎች ቀስቅሰዋል› ማለቱ ውጥረቱን አንሮታል፡፡ 
 በሌላም በኩል መንግስት ለሶስተኛ ጊዜ ባካሄደው የህዝብ ቆጠራ ‹‹የክርስቲያኑ ብዛት 33 ሚሊዮን ነው›› ማለቱ፣ ‹‹45 ሚሊዮን ነው›› 
ከሚለው ማህበረ ቅዱሳን ጋር አለመግባባት ውስጥ ከትቶት እንደነበረ ይታወሳል፡፡ 
 
 የኢህአዴግ ክሶች 
 ኢህአዴግ፣ በ1999 ዓ.ም በጅማ ከአጋሮ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ‹በሻሻ ገብርኤል› ግቢ ውስጥ ካህናትና ምእመናን ‹የእስልምና 
እምነት ተከታዮች ናቸው› በተባሉ ሰዎች አንገታቸው በስለት ተቆርጦ መገደላቸውን የሚያሳየውን ፊልም በሲዲ አባዝቶ ያሰራጨውም ሆነ 
ከጭፍጨፋው ጀርባ የመንግስት እጅ አለበት የሚል የስም ማጥፋት ዘመቻን የመራው ማህበሩ ነው ብሎ ያምናል፡፡ 
 
 ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት›፣ በጎንደር ደግሞ ‹ጎዶልያስ› (የእግዚአብሔር ጦር) የሚል ፅሁፍ 
የታተሙባቸው ቲሸርቶች አዘጋጅቶ ያሰራጨው ማህበረ ቅዱሳን ነው ሲል ይከስሳል፡፡ ነሐሴ/2005 ዓ.ም በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር 
በዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም ስም ‹‹የአክራሪነት/ጽንፈኝነት ዝንባሌዎችና መፍትሔዎቻቸው›› በሚል ርዕስ የተሰራጨው ሰነድም ክሱን፡- 
‹‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ነች›፤ ‹አንድ አገር አንድ ኃይማኖት› ወዘተ… ጉዳዮችን በማቅረብ በአንድ በኩል የአገራችንን የኃይማኖት 
ብዝሃነት የሚጻረር፣ በሌላ በኩል ደግሞ አገራችን የኃይማኖቶች ብዝሃነት መሆኗን የሚቃወም አካሄድ ነው፡፡›› ሲል ያጠናክረዋል፡፡ 
 (በነገራችን ላይ ከጥቂት ዓመት ወዲህ በጥምቀት በዓል ታቦታቱ የሚያልፉበትን መንገዶች አፅድተው ቀይ ምንጣፍ የሚያነጥፉና 
አደባባዮችን በባንዲራ የሚያስጌጡ በርካታ ወጣቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ኢህአዴግ ይህ መነሳሳት አልሸባብ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ 
የሚያደርገውን የመስፋፋት ሙከራ ይገድባል የሚል እምነት ቢኖረውም፣ ከወታደራዊ መረጃና ከደህንነቱ እንቅስቃሴው ከቁጥጥር 
እንዳይወጣም ሆነ እንዳይደበዝዝ የሚከታተል ቡድን በስውር ማዋቀሩን ሰምቻለሁ) 
 
 የአቦይ ስብሃት-ኩዴታ 
 በ2001 ዓ.ም ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ ከሹመታቸው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሲኖዶሱ አባላት ጠንካራ ተቃውሞ አጋጥሟቸው 
እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ከዚህ ንቅናቄ ጀርባ አቡነ ሳሙኤልን እና ሁለት የማህበረ ቅዱሳን የስራ አስፈፃሚ አባላትን የያዙት አቦይ 
ስብሃት ነጋ እንደነበሩበት ለጉዳዩ ቅርብ ከነበሩ ሰዎች አረጋግጫለሁ፡፡ 
 
 አቦይ ‹አቡነ ጳውሎስ ለኢህአዴግ ዕዳ ነው› ብለው መደምደማቸው ለኩዴታ እንዳነሳሳቸው ይነገራል፡፡ በወቅቱ የተፈጠረ አንድ 
አጋጣሚም ለሴራው የ‹መና› ያህል ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- ፓትርያርኩ ወደ ውጪ ሀገር የሚያደርጉት ጎዞ፣ የሲኖዱሱን ይሁንታ 
ማግኘት እንዳለበት ህገ ቤተ-ክርስቲያን ይደነግጋል፤ ይሁንና በዛን ሰሞን አቡነ ጳውሎስ እንደለመዱት ለማንም ሳያሳውቁ ጣሊያን 
በሚደረገው የ‹ጂ 20› ሀገራት ስብሰባ ላይ ለመገኘት ይሄዳሉ፤ ሲኖዶስም ባልተጠበቀ ሁኔታ ድርጊቱን ይቃወማል፡፡ ከቀናት በኋላም 
(የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተወካይ ባለበት) በሲኖዶሱ ስለድርጊታቸው ማብራሪያ የተጠየቁት አቡነ ጳውሎስ ‹‹እኔ በህገ ቤተ-
ክርስቲያን አላምንም›› የሚል ምላሽ በመስጠት ጉዳዩን ጭራሽ ሰማይ ጥግ ያደርሱታል፤ በዚህ ከመጠን በላይ የተበሳጩት አቡነ 
መልከፀዴቅ‹‹እርስዎ የጦር ጄነራል ኖት›› የሚል ኃይለ ቃል እስከመናገር ደርሰው ነበር፡፡ 
 
 የሆነው ሆኖ የአቦይ ስብሃትን ፖለቲካዊ ድጋፍ ይዘው፣ አጋጣሚውን በረቀቀ መንገድ የተጠቀሙበት አቡነ ሳሙኤል ዕለቱኑ 
ፓትርያርኩን ከአስተዳደር ስራ አውጥቶ በ‹ባራኪነት› ብቻ ወስኖ የሚያስቀምጣቸውን ‹ፍኖተ-ካርታ› ያዘጋጃሉ፡፡ ይሁንና ሃሳቡ ውሳኔ 
ሳያገኝ ቀኑ በመምሸቱ፣ ለማግስቱ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት ይለያያሉ፡፡ ግና ሁሉም አባቶች ‹በማታ እንግዳ› ተጎብኝተው ነበር፡፡ 
 
 አቡነ ሳሙኤል ከተመረኮዙት የጠነከረ የፖለቲካ ኃይል ያለውን ወገን ያያዙት ፓትርያርክ፣ ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ ወደ ጳጳሳቶቹ 
ማደሪያ በርካታ የደህንነት ሰራተኞችን አሰማርተው ከፍተኛ እንግልትና ማስፈራሪያ አደረሱባቸው፤ በተለይ ደግሞ በስብሰባው ላይ 
ጠንካራ ተቃውሞ ያቀረቡትን አቡነ መልከፀዲቅ ከዛው ከፓትርያርኩ ቤተ-መንግስት ከሚገኘው ማደሪያቸው በኃይል ኢሚግሬሽን ግቢ 
ወስደው አሰቃይተዋቸዋል (ዘግይቶ ሕይወታቸው ያለፈውም ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደሆነ የቅርብ ሰዎቻቸው ይናገራሉ)፡፡ የኩዴታው 
መሪ አቡነ ሳሙኤል ወደስብሰባው አዳራሽ ለመሄድ ማልደው ከመኝታቸው ቢነሱም በበርካታ የፖሊስና የደህንነት ሰዎች ተከበው 
ከቤታቸው ወደየትም መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ይነገራቸዋል፡፡ በወቅቱ በአካባቢው ከነበረ ሰው ባገኘሁት መረጃ መሰረት አቡኑ ወደ 
አቦይ ስብሃት ስልክ ደውለው ስለክስተቱ አማክረዋቸዋል፤ ያደረጉት ንግግርም ይህንን ይመስላል፡- 
 
‹የታጠቁ ሰዎች ከበውኛል፤ ወዴትም መሄድ አልቻልኩም!› 
‹ዝም ብለህ ሂድ!› 
‹እንገልሀለን እያሉኝ እኮ ነው?› ‹ይግደሉህ!› 
‹ሹፌሬን አግተው የመኪናውን ቁልፍ ነጥቀውታል?›
‹በእግርህ ሂድ!› 
 
ይሁንና አቡነ ሳሙኤል መሄድ ሳይችሉ ቀሩ፤ ስብሰባውም እርሳቸው በሌሉበት ተካሄደ፤ በውጤቱም ፓትርያርኩ አሸነፉ፡፡ በወቅቱ 
መንግስት ማህበረ ቅዱሳንን የሴራው ጠንሳሽ አድርጎ ፈርጆታል፡፡ በግልባጩ ማህበሩ የእንቅስቃሴው ተቃዋሚ መሆኑን የተረዱት አቦይ 
ስብሃት ነጋ ጥርስ እንደነከሱበት ይነገራል (በነገራችን ላይ የአቦይ እቅድ ቢሳካ ኖሮ፣ ተያይዘው የሚነሱ አለመግባባቶችን በመጠቀም 
ማህበሩን መምታትንም የሚያካትት ነበር) 
 
 የዋልድባ ጉዳይ
  
 የዋልድባ ጉዳይ 
 በመንግስትና በማህበረ ቅዱሳን መካከል የነበረውን አለመግባባት ወደላቀ ጠርዝ ያደረሰው በዋልድባ ገዳም አካባቢ ይቋቋማል የተባለው 
የስኳር ፋብሪካ ጉዳይ ነው፡፡ በገዳሙ የሚኖሩ መነኮሳትን ጨምሮ፣ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ያሰሙትን ተቃውሞ ችላ በማለት ወደ ስራ 
ለመግባት በሞከረው መንግስት ላይ የተነሳው ተቃውሞ በመጠንከሩ፣ ስርዓቱ ‹ገዳሙ ላይ አይደርስም› በማለት ሲያስተባብል፣ ቤተ-
ክህነትም የማጣራት ስራ መሰራቱን ገልፆ ‹‹ምንም አይነት ችግር የለም›› ብሎ ከመንግስት ጎን ቆመ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ማህበረ ቅዱሳን 
ግንባታውን አጥብቆ ተቃወመ፡፡ በአናቱም ጉዳዩን ቦታው ድረስ ሄዶ የሚያጣራ (ወጪው በስኳር ኮርፕሬሽን የሚሸፈን)፣ አምስት አባላት 
ያለው ቡድን (ሶስቱ ከአዲስ አበባ፣ ሁለቱ ከጎንደር) ወደ ዋልድባ ላከ፤ ቡድኑም አጥንቶ ባቀረበው ሪፖርት፡- ‹‹16.6 ሄክታር መሬት 
ከገዳሙ ተወስዷል፣ ወደፊት ገዳሙን የውሃ መጥለቅለቅ ያሰጋዋል፣ የቅዱሳን አፅም ወጥቶ መሬቱ ታርሷል፣ ፋብሪካውን ተከትሎ ከተማ 
መመስረቱ ስለማይቀርም ቡና ቤትና ሴተኛ አዳሪዎች በብዛት የሚገኙበትን ሁኔታ ይፈጥራል፤ ይህ ደግሞ ገዳማውያኑን ይፈትናል… 
በጥቅሉ ከተማና ገዳም አብረው ሊሄዱ አይችሉም፤ ምክንያቱም የስነ-ሕዝብ አወቃቀርን (Demography) ይቀይራል›› ካለ በኋላ 
ከዋልድባ ውጪ ያሉ አማራጮችን ጭምር ለመንግስት አቅርቧል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የዶ/ር ሽፈራው ሰነድ የማህበሩን ጥናት እንዲህ 
ሲል ኮንኖታል፡- 
‹‹መንግስት በሃይማኖታችን ጣልቃ ገብቷል በሚል ገሐድ ፍላጎትና ድብቅ አሰራር ካላቸው የውጭ ቡድኖች ጋር በማበር ሰላምን አደጋ 
ውስጥ የማስገባትን ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይማኖት ሽፋን ለመናድ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በቅርብ በነበረው የፓትርያርክ ምርጫና 
በዋልድባ ገዳም ዙሪያ የተፈጠረው ዝንባሌ የነዚህ ፍላጎቶች ማሳያ ነው፡፡›› 
 
 የፓትርያኩ ህልፈት 
 በ2004 ዓ.ም መጨረሻ አቡነ ጳውሎስ ማለፋቸው ሌላ ፍጥጫን አስከትሏል፡፡ ማህበሩ ስደተኛውን ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስን 
ከአሜሪካ አምጥቶ ወይም እንዳሻው የሚያሽከረክረውን ጳጳስ መንበሩ ላይ ለማስቀመጥ ምርጫው በሚፈልገው መንገድ እንዲጠናቀቅ 
በርትቶ እየሰራ ነው የሚለው ወቀሳ የመንግስት ቁጣን የበዛ አድርጎታል፡፡ የጠቀስኩት ሰነድም ውንጀላውን በገደምዳሜ ገልጾታል፡- 
‹‹በእስልምናም ይሁን በክርስትና ሃይማኖቶች ሽፋን የሚደረገው የአክራሪነት/ጽንፈኝነት እንቅስቃሴ በዋናነት እያነጣጠረ የሚገኘው 
የተቋማቱን የበላይ አመራር እርከኖች መቆጣጠር ነው፡፡›› 
 
 ናዳው እየመጣ ነውን? 
 ባለፉት ሁለት ዓመት የእስልምና እምነት ተከታዮች ‹መንግስት በኃይማኖታችን ጣልቃ አይግባ› በሚል የጀመሩትን ትግል ተከትሎ 
አገዛዙ ማህበረ ቅዱሳንንም ደርቦ የመምታት ዕቅድ እንዳለው የሚጠቁሙ ምልክቶች ታይተዋል፡፡ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤትን 
በሚንስትር ማዕረግ የሚመራው ሬድዋን ሁሴን ‹‹መንግስት ጉዳዩን በሰላም ቢጨርሰው የተሻለ ነው›› ሲሉ ምክር ለመለገስ ለሞከሩ 
የምዕራብ ሀገራት ዲፕሎማቶች ‹‹የአወሊያን ቡድን በዚህ መልኩ ሳናንበረክከው ቀርተን፣ መጅሊሱን እንዲወስድ ብናደርግ፤ ነገ ደግሞ 
ማህበረ ቅዱሳን ‹ሲኖዶሱን አምጡ› ቢለን ምን መልስ ይኖረናል?›› ሲል የሰጠው ምላሽም ይህንኑ የሚያመላክት ነው፡፡ 
 
 የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መ/ቤት ባለፈው ዓመት ወርሃ የካቲት ‹‹ለሃይማኖት ተቋማት የተዘጋጀ›› ብሎ ያሰራጨው ሰነድ ማህበረ 
ቅዱሳን እና መብታቸውን እየጠየቁ ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮችን የጥቃቱ ዒላማ እንደሆኑ ያሳያል፡፡ ሂደቱን በመምራትም ሆነ 
በማስፈጸም ከፌደራል ጉዳዮች ጀርባ ሆኖ በዋናነት የሚሰራው ‹የፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል› እንደሆነ ይታወቃል፡፡ 
 
 በአንድ ወቅት ዶ/ር ሽፈራው ‹‹የከፍተኛ የትምህርት ተቋም የፖለቲካ ርብርብ ሜዳ አይሆንም፤ …የመንግስት መስሪያ ቤቶችም 
ከማንኛውም ኃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ነፃ መሆን አለባቸው›› ያለበትን አውድ ሰነዱም ‹‹በዩንቨርስቲዎች የአካዳሚ ትምህርትን ተገን 
በማድረግ እምነትን ማስፋፋት አይቻልም›› በማለት ማህበሩ እንደቀድሞ አባላትን ለመልመል የሚጠቀምበትን መስፈርት አግዷል፡፡ 
 
 በ2006 ዓ.ም በዩንቨርስቲዎች ይተገበራል የሚባለው ‹አለባበስንና አመጋገብን› የሚመለከትው መመሪያም ራሱን የቻለ አደጋ አለው፡፡ 
እንዲሁም የኃይማኖት ማህበራት አላማቸውን አሳውቀው እንዲመዘገቡ የሚያስገድደውን ህግ በምክር ቤት ለማፅደቅ ዝግጅቱ ተጠናቅቋል፡፡ መዝጋቢው ክፍል ማህበራቱን በፍርድ ቤት ከማስቀጣት እስከ ማፍረስ የሚያደርስ ስልጣን እንደሚሰጠው ምንጮቼ መረጃ
አድርሰውኛል፡፡ ይበልጥ የምንደነግጠው ደግሞ በዚህ መልኩ ማህበራቱን ከጠለፉ በኋላ ማንም ሰው ‹‹ቅዱስ ቃሉን›› ለመስበክ ፍቃድ
ማግኘትን ግዴታ ለማድረግ መታቀዱን ከዶ/ሩ ሰነድ ስናነብ ነው፡- 
 
‹‹የሰባኪያን/ዳኢዎች ሚናን የበለጠ ለማጎልበትና የተጠያቂነት ስርዓት ለመትከል እያንዳንዱ የሃይማኖት ተቋም የራሱን መምህራን 
የሚለይበትን የመታወቂያ ስርዓት ሊያበጅና በዚህም የክትትል ስራ እንዲሰሩ መደገፍ ይቻላል፡፡›› 
 
ሰነዱ ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሚገቡ ተማሪዎችንም መልምሎ የሲኖዶሱን፣ የማህበረ ቅዱሳንን የመጅሊሱን… አመራርነት የመያዝ ዕቅድ 
እንዳለው በዘወርዋራ ይጠቁማል፡፡ የፌደራል ጉዳዮች በ2004 ዓ.ም ለስልጠና ባዘጋጀው ማንዋል ላይም ‹‹በኦርቶዶክስ ክርስትና መድረክ 
አክራሪው ኃይል ማህበረ ቅዱሳን ነው›› ሲል መፈረጁ ይታወሳል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ማህበረ ቅዱሳንን የግቢ ጉባኤን በማዳከም፣ ከሰንበት 
ትምህርት ቤቶች፣ ከሰበካ ጉባኤ እና ከሀገረ ስብከት አስተዳዳሪዎች ጋር በማጋጨት፣ በካህናት በማስወገዝና በመሳሰሉት ተጠቅሞ 
ሊያፈርሰው እንደተዘጋጀ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ 
 
 በጥቅሉ ሰነዱ ማህበረ ቅዱሳንን ‹‹በሃይማኖት ሽፋን ‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት መንግስታዊ ሃይማኖት መሆን ይገባዋል› በሚል 
አቋራጭ የፖለቲካ መሣሪያ ለማድረግ የሚንቀሳቀስ›› ሲል ይኮንነዋል፡፡ መብታቸውን የጠየቁትን ሙስሊሞችን ደግሞ፡- ‹‹የተመለሱ 
የሃይማኖት ጥያቄዎችን ያልተመለሱ በማስመሰልና በሕዝበ-ሙስሊም ውስጥ ጥርጣሬ በመርጨት የቆየ›› ብሎ ካወገዛቸው በኋላ 
ስለሚወስደው እርምጃ፡- 
 
‹‹የአክራሪነትና የጽንፈኝነት ምንጩን የማድረቅ ስራ እየተሰራ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ስራም ጎን ለጎን መፈጸም ያለበት ነው›› ሲል 
ጥቁምታ ይሰጣል፡፡ 
 
 መፍትሄው ምንድር ነው? 
 ከላይ በጥቅሉ እንደጠቀስኩት የሃያ ሁለት ዓመታቱ ሂደት የሚያስረግጠው፣ የኢህአዴግን ማንኛውም ዓለማዊም ሆነ ኃይማኖታዊ ተቋም 
‹ነፃነት› ያለማክበሩ ብቻም ሳይሆን፣ ቀስ በቀስ ህልውናቸውን ለዘላለሙ ለማጥፋት በሙሉ ኃይሉ እየሰራ እንደሆነ ነው (በነገራችን ላይ 
ማህበረ ቅዱሳን የሀገሪቱን ታሪክ ‹ክርስቲያናዊ› ለማድረግ መሞከሩን፤ አንዳንድ የእስልምና ልሂቃኖችም ‹ታሪክን የማስለም› ዕቅዳቸው 
ስህተት መሆኑን ተረድተው ከድርጊታቸው ካልታቀቡ፣ ሂደቱ አገዛዙን ከመጥቀም ያለፈ ፋይዳ የለውም) 
 
የሆነው ሆኖ የማህበረ ቅዱሳን ሰዎች ተቋማቸውን ለመከላከል ከሕዝበ-ሙስሊሙ እንቅስቃሴ የተሻለ የሚመርጡት መንገድ ያለ 
አይመስለኝም፡፡ በዚህ መንገድ ተጉዘው ህዝበ-ክርስቲያኑ ህዝባዊ ንቅናቄ ፈጥሮ በመከራው ጊዜ የደረሰለትን ‹‹የእምነቱን ዘብ 
እንዲታደግ›› ጥሪ ማስተላለፍና ማነሳሳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ 
 
 ማህበሩ በእስልምና ኃይማኖትና በተከታዮቹ ላይ ያለውን ከተጨባጭ እውነታ ጋር የሚጣረሱ ምልከታዎቹን እና ለፍትሐዊው ሕዝበ-
ሙስሊም ጥያቄ ያሳየውን ዝምታ በመግራት የራሱን ህልውና እጅግ በፍጥነት ለመታደግ መሞከር ይኖርበታል፡፡ ከስርዓቱ የፖለቲካ ዘዬ 
እንደተረዳነው ቀስ በቀስ እየጠበቀ በመጣው አፈና ላይ ማህበሩ በዚህ መልኩ አንገቱን ቀብሮ፣ ጣልቃ ገብነቱን ቸል ብሎ የማንገራገሩ 
አካሄድ፣ በአንድ ክፉ ቀን በመጅሊሱ የተፈፀመው ታሪክ በራሱም ላይ መደገሙ አይቀሬ እንደሆነ ለመናገር ‹ነብይ› መሆንን አይጠይቅም፡፡ 
በርካታ ምዕመናን መኖራቸው፣ አለማዊ የትምህርት ተቋማትን የረገጡ ከተሜ ወጣቶች በማህበሩ ውስጥ መብዛታቸው የመውጫ 
መንገዱን በአመራሩ ላይ ይጥለዋል፤ ‹‹ለትናንት አናረፍድም፣ ለነገ አንዘገይም›› እንዲሉ የቤተ-ክርስቲያኗ ሊቃውንት፡፡ 
 
 
 
 
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com 
October 6, 2013 
 

No comments:

Post a Comment