Sunday, September 1, 2013

የዛሬው አዲስ አበባ ውሎ... አፈና! አፈና! አፈና!

(ኢ.ኤም.ኤፍ) አክራሪነትን ለመቃወም በተጠራው ሰልፍ ላይ በርካታ ህዝብ ተገኝቶ
ነበር። በዚሁ ሰልፍ ላይ ሙስሊሞች ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ ቀርቦ እንደነበር
ይታወሳል። በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ ቀን ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እቅድ
ይዞ፤ በፖሊስ እንደከሸፈበት ተመልክተናል። እነዚህን ሶስት ጉዳዮች ይዘን ከዚህ በታች
ያሉትን ወቅታዊ መረጃዎች እና ፎቶዎችን ለአንባቢዎች ለማቅረብ እንወዳለን።
ሰማያዊ ፓርቲ ከትላንት ምሽት ጀምሮ ቢሮው ሲበረበር እና አባላቱ ሲታሰሩ ነው።
ፓርቲው በትላንትናው እለት... “በአዋጁ በግልፅ እንደተደነገገው ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ህገ
መንግሥታዊ መብት እንደሆነና ማንም ሊከለክለን እንደማይችል በማያሻማ መንገድ
ተገልጿል፡፡ ሰልፉን የማሳወቁ ዓላማ የጥበቃ አገልግሎትና አንዳንድ አስተዳደራዊ ድጋፎችን
ለማግኘት ነው፡፡ በዚህ አሰራር ውስጥ መንግሥት የጥበቃና የቦታ ችግር ካለ ሰልፉን ለሌላ
ጊዜና ቦታ እንዲያደርግ ለሚመለከተው አካል ደብዳቤ በደረሰው በ24 ሰዓት ውስጥ በፅሑፍ
መልስ ይሰጣል የሚል ድንጋጌ አለ፡፡ ነገር ግን በመንግሥት በኩል ላቀረብነው የመብት ጥያቄ
ምላሽ መሰጠት ሲገባው እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ የመንግሥት መዋቅር ሙሉ በሙሉ
በመጠቀምና ዜጐችን አስገድዶ ሰልፍ እንዲወጡ በማስፈረም ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ በጠራበት
ቀንና ቦታ ሌላ ሰልፍ በተደራቢ በሃይማኖት መቻቻል ስም ህገ መንግሥቱን በመጣስ
የሃይማኖት ተቋማትን ለራሱ የድርጅት ፖለቲካ መጠቀሚያና የሰማያዊ ፓርቲን ህጋዊ
እንቅስቃሴ ለመግታት እየተጠቀመበት ነው፡፡ ይህ አሰራር እንዲስተካከል መንግሥትን
በመግለጫ ብንጠይቅም የተሰጠን ምላሽ ግን በሚያሳዝን ሁኔታ የሀገሪቱን ህገ መንግሥትና
የሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን ሙሉ በሙሉ በመጣስ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን
በኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዲኤታ እንዲሁም ሰልፍ ጠሩ በተባሉ አካላት ግልፅ የሆነና
የተቀነባበረ ህገ ወጥ ሴራ ሆኗል፡...” በማለት መግለጫ ሰጥቶ ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መግለጫውን በሰጠ
በሰአታት ውስጥ ከአንድ መቶ ያላነሱ የፓርቲው አባላት ባሉበት የሰማያዊ ፓርቲ ዋና ቢሮ
ግቢውን እና በሩን ጥሰው የገቡ ከባድ መሳርያ የታጠቁ የፈዴራል ፖሊስ አባላት የእገታ-ሽብር
ፈጽመዋል። ድርጊቱን ሽብር የሚያሰኙት ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም በግቢው ውስጥ የነበሩት
የፓርቲው አባላት ከትጥቅ ትግል ይልቅ ፍፁም ሰላማዊ ትግል ለሀገራችን ይበጃል ያሉ
ከመፈክር እና ብዕር ሌላ ምንም መሳርያ የሌላቸው ንፁሃን ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ከዚህም
በላይ የፌዴራል ፖሊስ ግቢውን ለመውረር የፍርድቤት ትእዛዝ አለመያዙ ሌላው ህገ ወጥ
ተግባር ነበር። የዚህ አይነቱ የማሸበር ተግባር በመንግሥትነት ደረጃ ባሉ ፖሊሶች መፈፀሙ
እጅግ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን ''ተከታታይ ትውልድ ለሰላማዊ ትግል አልታደለምን?'' የሚለውን
ጥያቄ ይጭራል።
በአዲስ አበባ አራት ኪሎ (ግንፍሌ አካባቢ) የሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት
የእገታ-ሽብር ተግባር እንደተፈፀመበት ተገልጿል። ፓርቲው ቀደም ብሎ ለነሐሴ 26/2005
ዓም ፍፁም ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ ለመንግስት ከሶስት ወር በፊት ማስታወቁ
ይታወቃል። ከቀናት በኋላ መንግስት ቀደም ብሎ በሰማያዊ ፓርቲ እንዲያውቀው የተደረገውን
ፍፁም ሰላማዊ ሰልፍ ማስታወሻ ወደጎን በማለት ''የሃይማኖት ተቁዋማት የጋራ ጉባኤ''
የጠራው ሰልፍ ቅድሚያ በመስጠት በመስቀል አደባባይ፤ መንግስት የጠራው ሰልፍ
ተከናውኗል።
በከፍተኛ የመንግስት አካላት ጭንቀት እና ውጥረት የተካሄደው ይህ ሰልፍ ተጠናቋል።
ጅምሩም መጨረሻውም በውል ያልተለየው የዛሬው ሰልፍ ከፍተኛ ውጥረት የነገሰበት ነበር፡፡
ህብረተሰቡ አክራሪነትን ለመቃወም ሙሉ እምነት እና ሞራሉ ያለው ቢሆንም በደረሰበት
ግዳጅ እና ማስፈራሪያ በዝናብ ከቤቱ ተገዶ በመውጣቱ በተሳታፊው ላይ ድብርትን እና
መሰላቸን አስከትሏል፡፡ ተፈጥሯዊው የሆነውም ዝናብ ሰልፉ አንዲቀዛቀዝ እና ህዝቡ በሰልፉ
ላይ ተገዶ መሰለፉን በውስጡ አንዲያማርር ከፍተኛውን ድርሻ ወስዷል። ሰልፉ የተጠራበት
አጀንዳ ታላቅ እና አገራዊ አጀንዳ ቢሆንም ህብረተሰቡ ላይ በተፈፀመበት የማስገደድ ተግባር
ሰልፉ ላይ ውሃ ሊከልስበት ችሏል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙም ጉዳዩ ከማንም በፊት ይመለከተኛል
በማለት በሰልፉ ላይ ተገኝቶ አክራሪነትን ለመቃወም ቢያስብም አብዛኛውን ሙስሊም
ማህበረሰብ መንገድ በመዝጋት እንዳይካፈል አድርገውታል፡፡
የተካፈሉትንም ሙስሊሞች ህገ ወጡ የመጅሊስ ሹመኛ ንግግር ሲያቀርቡ ጆሯቸውን
በመያዛቸው ካሉበት በደህንነቶች እየታፈኑ ተወስደዋል፡፡ እስካሁን ቁጥራቸው ከ 50
የሚበልጡ ሙስሊሞች ከህዝብ መሃል ታፍነው ተወስደዋል፡፡ ሰልፉ በመንግስት
እንደሚካሄድ ከታወጀበት ቀን አንስቶ ከባድ ቅሰቀሳ በሚዲያዎች እና ቤት ለቤት ቅስቀሳ
ቢካሄድም በዛሬው ዕለት ግን ሚዲያዎች የቀጥታ ስርጭት እንኳን ሳይሰጡት ቀርተዋል፡፡
ፕሮግራሙ በሰላም ስለመጠናቀቁ ከማብሰር ውጪ ሌላ ያሉት ነገር የለም፡፡ ይህ የሚያሳው
ሙስሊሙ ማህበረሰብ አክራሪነትን ለመቃወም በነቂስ እንደሚወጣ ጥሪ በመደረጉ
በመንግስት በኩል ከፍተኛ ድንጋጤ በመፈጠሩ ነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ተብሎ በአካባቢው ግን
የጦር አውድማ እስኪመስል በወታደር እና በጦር መሳሪያ አካባቢውን መጨናነቁ በመንግስት
በኩል የተፈጠረውን መሸማቀቅ እና ፍርሃት ቁልጭ እርጎ ያሳየ ነበር፡፤ ህዝበ ሙስሊሙ
በሰልፉ ላይ የሚሳተፍበትን ምክንያት ጥርት ባለ መልኩ ማስቀመጡ የሚታወስ ቢሆን ሰላም
ወዳዱን ሙስሊም ማህበረሰብ በሰልፉ ላይ እሳተፋለው በማለቱ ብቻ ለማሸማቀቅ ተሞክሯል፡፡ የሰልፉ ስነ ስርአት መጀመሩ ከተነገረ በኋላ
ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተገዶ ተሰላፊዎች ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ሰልፉን በመተው ወደመጡበት ሲመለሱም ታይቷል።
በአጠቃላይ ሰልፉ ከመጀመሩ በፊትም ሆነ በኋላ መንግስት በሙስሊሙ እና በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የሚያደርገው አፈና እንደቀጠለ
ነው። የዛሬው የአዲስ አበባ ውሎ እና አፈናውም ይህን ይመስል ነበር። (ፎቶዎቹም እኛ ካልነው በላይ ይናገራሉና ፎቶዎቹን ልብ ይበሉ።)

No comments:

Post a Comment